ከጀዋር መሐመድ ወቅታዊ የትግል ስልቱና ዓላማውን በመገምገም ልጀምር!
ደህንነቱ በሚጠበቅበት፣ በውጭ አገር በድሎት ተቀምጦ፣ ምንም አይነት መስዋዕት ሳይከፍል የራሱን ትግል በሩቁ በመምራትና፤ ጊዜው ሲደርስ ኦሮሞውን በመወከል የሁሉም ብሔሮች አማራጭ ፖለቲከኛ ሆኖ የስልጣን ወምበር ላይ መቀመጥ የሚያልም ይመስለኛል።
ይህን ህልሙን እስከሚያሳካ ድረስ አንዳንዴ ብቅ እያለ የሁሉም ወዳጅ በመምሰል፤ የድሮ የሚታወቅበትን የዘረኛ ኦሮሙማ ፕሮፋይሉን ዳብዛ ለማጥፋት ጠንክሮ መስራት ይሆናል።
በተጨማሪም በቄሮ እንቅስቃሴ ጊዜ የገነባውን ታዋቂነት ተጠቅሞ የተለያዩ የውጭ ሀይሎችን፣ የስላ ድርጅቶችን፣ በአገር ውስጥ ጠንካራ የትጥቅና የሰላማዊ ትግል የሚያካሒዱ ድርጅቶችን፣ ታዋቂ ባለሀብቶችን፣ በአብይ አህመድ መንግስት ውስጥ የሚገኙ ባለስልጣናትንና፣ የቀድሞ ሹማምንቶችን ወዘተ … በማቀናጀት የፋይናንስና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ማካበት ያቀደም ይመስላል።
አሁን “አልፀፀትም” ያለውን መፅሐፍና ወደፊትም የሚፅፋቸውን መፅሐፍትና አጫጭር ፅሁፎችን በመጠቀም ለዚህ የፖለቲካ እቅዱ ለማዋልም አስቧል።
ጀዋር አሁን የተሳፈረበትና የሚለፍፈው “ኢትዮጵያዊነት” አቋም ድሮ ከሀያ ዓመት በፊት፣ መጀመሪያ ከአገር ሲወጣ፣ የአማራ ሊሒቃንን ድጋፍ ለማግኘት በቪኦኤ ኢንተርቪው አድርጎ የተጠቀመበት ተመሳሳይ አቋም ነው። በበዚያን ጊዜ በኢትዮጵያዊነት በሚታገሉት ኢትዮጵያውያን ካምፕ ውስጥ የሚመኘው የፖለቲካ የበላይነት በአጭ ጊዜ እንደማይሳካ ስለተገነዘበ፤ ሰበብ ፈልጎ የኦሮሙማ አቀንቃኝ ሆኗል።
በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያዊነት ላለመታገል ያቀረበው ተቃውሞ እንዲህ በማለት ነበር። “ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅነው የኢህአዴግ ተቃዋሚ ካምፕ ውስጥ የኦሮሞ ድምፅና የኦሮሞ አጀንዳ የተዋጠ ነው።” ከዚያ በኋላ ከመቅፅበት ከኢትዮጵያዊነት ወደ “Oromo First” ተቀይሮ የኦሮሞ ካምፕ ጠቅሎ ገብቷል።
አሁን ደግሞ ተመልሶ ወደ “ኢትዮጵያዊነት” ካምፕ ለመግባት የአገራዊ ፖለቲካ አቀንቃኝ ለመሆን እቅድና ዝንባሌ እያሳየ ነው።
ከእስር ከተፈታ በኋል ያሉት ክስተቶች፤
ጀዋር ከእስር ከወጣ በኋላ የአብይ አህመድን ጨካኝ፤ ካስፈለገም ገዳይ መሆኑን በመገንዘብ በፍርሀት ተሸማቆ፣ አንገቱን አቀርቅሮ ከቆየ በኋላ በስደት ኬንያ ሔዷል። በኬንያ ምንም አይነት የተቃውሞ ቃል ሳይተነፍስ ሁለት ዓመት የሚሆን ቆይቷሎ።
አሁን የአብይ አህመድ መንግስት በሁሉም አቅጣጫ ተወጥሮ ሲንገዳገድ በማየቱ የልብ ልብ ተሰምቶት፤ ተመልሶ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልክ ወደ ፖለቲካው መድረክ ተመልሷል።
የጀዋር የአሁኑና የወደፊት አቋም አጠራጣሪ መሆኑ ግልፅ ነው። “ከእባብ እንቁላል እርግብ መጠበቅ” አይገባምና፤ የአማራ ፖለቲከኞችና ልሒቃን ከጀዋር ጋር በሚያደርጉት ግንኙነትና የአሁኑን የጀዋርን “ተሀድሶ” እንደወረደ መቀበል የለባቸውም የሚል እምነት አለኝ።
“ልጅ ከሆነ ይገፋል ሽል ከሆነ ይጠፋል” እንደሚባለው፤ የሚያደርገውንና የሚፅፈውን የወደፊት አቋሙን ሁሉ፣ በጥንቃቄ መመርመርና መገምገም ተገቢ ይመስለኛል።
የጀዋር ጥቂት ወዳጆች ብዙ ጠላቶች፤
ጀዋር በተለያየ ገፅታው ሲገመገም፤ የሚታይበት የአቋም ተቃርኖና ግለሰባዊ ፀባዩ ብዙ ጠላቶችና ጥቂት ብቻ ወዳጆች ያለው ፖለቲከኛ አድርጎታል። አይዲዎሎጅን መሰረት ያደረገ መጠጊያና የተረጋገጠ የስትራተጅክ አጋር የለውም። ስለሆነም የኔ ብሉ በዘላቂነት የሚያስጠጋው ግለሰብም ሆነ ቡድንና በሙሉ ልብ የኔ ብሎ የሚሞትለት የፖለቲካ አቋም ያለው ግለሰብ አይመስለኝም።
ጀዋር መሐመድ፤ አብይ አህመድ እንደ ለማ መገርሳ፣ ገዱ አንዳርጋቸውና አንዳርጋቸው ፅጌ ወዘተ… ተጠቅሞበት የጣለው ግለሰብ ነው። አሁንም እንኳን፣ አብይ አህመድ የድሮ ሰዎችን በሚፈልግበት ጊዜ፤ በአዲስ መልክ ሊጠቀምበት ስላልፈለገ፤ በካልቾ ብሎ ከአገር ውጭ በፍርሀት እንዲሰደድ አድርጎታል። አልፎ ተርፎም በስደት ሆኖ መፅሐፉን እንዳያስመርቅ ደንቃራ በመሆንና በማስፈራራት፣ በብልፅግና አክቲቪስቶች በኩል የስም ማጥፋት ካምፔን አስከፍቶ፣ ስሙ በኦሮሞው ህብረተሰብ እንዲጠላ እያደረገ ነው።
ጀዋር የእነ ጃል መሮ ኦነጋዊ ቡድንም ከባድ ቂም የያዘበት ግለሰብ ነው። ከዛሬ አምስት አመት በፊት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የኦነግ ታጣቂዎችን በእርቅ ስም ለአብይ አህመድ እጅ እንዲሰጡና ካምፕ ገብተው፣ ቀልጠው እንዲቀሩ ስላደረገ ፍፁም ደስተኛ አልነበሩም።
ከውጭ ያሉ የኦሮሞ ሊሒቃን ስብስብ፣ የእዝቅኤልና የፀጋየ አራርሳ ቡድን፣ በግል ቁርሾና በኢጎይስት ፀባዩ በሚል የጀዋርን ዓይን ማየት አይፈልጉም። ከበቀለ ገርባ ጋርም የተኮራረፉ መሆኑ ይነገራል። ለማ መገርሳ ደግሞ ከጀዋር ጋር ሳይሆን ከሌሎች ጋር ቢሰራ ይመርጣል።
ጀዋር እንደገና የቄሮ አይነት እንቅስቃሴ ለመጀመር ሁኔታውና ጊዜው ስለተቀየረ የማይወጣው እንደሆነም ተገንዝቧል።
ከዚህ በፊት ከአማራ ህብረተሰብ ጋር ያለው ግንኙነት የታወቀ ቢሆንም አሁን ከአማራው ጋር መወዳጀት የፈለገው መጠጊያ ስላጣ ይመስላል የሚል ግምትም አለ።
በአጠቃላይ የጀዋር የአሁኑ ቁመና ሲገመገም፤ ብዙ ጠላት እንጅ ወዳጅ የሌለው፤ ግን የድሮ ዝናውና እንደ ስለት ቢለዋ የሚቆርጥ ምላሱ ብቻ የቀረው ግለሰብ ነው ማለት ይቻላል
የሳምንት ዝና ያሰከረው ጀዋር፤
የአንድ ሳምንት ዝና ያሰከረው ጀዋር መሀመድ ‘ከኔ በላይ ዝነኛ ፖለቲከኛ የለም’ በሚል የኢጎ ፈረስ እየጋለበ ይመስላል። የጀዋር መሀመድ ጀምበር የጠለቀ እንደሆነ የታወቀው፣ በመፅሐፉ ራሱ እንደገለፀው፣ አብይ አህመድ መዳፉን እየመታ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ቀን ነው። “ከወደቁ በኋላ መፈራገጥ ለመላላጥ” እንደሚባለው ካልሆነ በቀር፤ የጀዋር የፖለቲካ ህይወቱ እንደ ታዬ ደንደአ፣ ለማ መገርሳ፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ልደቱ አያሌው ወዘተ ያለቀለት ነው።
ጀዋር ሰሞኑን የሚያልመው ዓይነት የትግል ስልት፤ የአብይ አህመድን አገዛዝ መንበር ለማነቃነቅ፣ ጥርስ የሌለው ስለሆነ፤ የቁንጥጫ ያህል እንኳ አቅም የለውም።
የጀዋር ህልም አመታቶም ቢሆን በኦሮሞ ትግል የበላይነት ለማግኘት ነው። ግን መጠቀሚያ ከመሆን የዘለለ ሚና አይኖረውም። የOLF ታጣቂ ቡድኖች ለዓመታት ታግለው በደም ያገኙትን የመሪነት ሚና ለጃዋር አሳልፈው ይሰጣሉ የሚል ቅዠት የሚታለመው በጃዋር ጭንቅላት ብቻ ነው። ከትግሬውና ከአማራው ጋር ደም የተቃባው ጀዋር እንዲሁ መጠቀሚያ እንጅ፤ “አንተ ምራን ተብሎ” ተደማጭነት ማግኘት ሳይሆን “እባክህ አታደንቁረን” የሚባል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። የውጭ ሀይሎችም ጠመንጃ አንግተህ ተከታይ ከሌለህ ዞር ብለው አያዩህም።
ብዙዎች እንደሚገምቱት፤
የጀዋር ካልኩሌሽን አብይ አይመድ ስለተዳከመ ባስፈራራው የሆነ ቦታ ይሰጠኛል የሚል ነው። የአብይ ሰላይ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ያላቸውም አይጠፉም።
የኦሮሞ ሊሒቃን፤ ተከታያቸውን በስሜት መንዳትና ጥላቻን መጋት እንጅ፤ ገዥዎችን ከተራው ህዝብ ነጥለው በማየትና አብሮ መኖርና መበልፀግን አያስተምሩም። ጀዋርም በመፅሃፉ ያደረገው ይህንን ነው። የሰውን ክብር የሚያወርድ ፣የጅምላ የቃላት አጠቃቀም ችግር አይፈታም፤ አያቀራርብም። የጀዋር መንገድ የሚረዳ ቢሆን ኖሮ፤ እስከዛሬ በሁለቱም ወገን የሚወረወሩት ቃላት ወደ መጠፋፋት አይወስዱንም ነበር።
በምቾት ከከተማ ከተማ እየተዘዋወሩ መለፍለፍና ለህዝብ የመጨረሻውን መስዋዕትነት ከፍሎ መታገል የተለያየ ነው።
የሰላሙ መንገድ በተደጋጋሚ ተሞክሮ ነበር። አብይ አህመድ የውሸት የሰላም ድርድር ለማድረግ ጥሪ እያደረገ ተቃዋሚዎችን ለመከፋፈልና ለማጥፋት ጊዜ መግዣ እያደረገው መሆኑ እየታወቀ፤ ጀዋር መሐመድ የሚያደርገውም ጥሪ ለአብይ አህመድ ተቀባይነት እንደሌለው እየታወቀ ባዶ ጥሪ ይመስላል። ጀዋር በየከተማው እየዞርህ የሚያሰለች ተመሳሳይ ንግግር ማድረግ በትጥቅ ለሚታገሉት ቡድኖች ቅንጣት ለውጥ አያመጣም። ይህን የመዝናኛ ጉብኝትህን ስትጨርስ ምን ልታደርግ ነው? አብይ አህመድ ካልተቀየረ ተመሳሳይ አሰልች ስብከትህን አቁመህ ራስህን ለትጥቅ ትግ ታዘጋጅ ይሆን።