አንዱ ዓለም ተፈራ
ነሐሴ ፲ ፯ ቀን ፳ ፻ ፲ ፰ ዓ. ም.
በአንድ አገር፤ ከመሬት ተነስቶ አገራዊ ምክክር ኮሚሺን አይቋቋምም። ምንም እንኳን እያንዳንዱ አገር የየራሱ የሆነ የአሠራርም ሆነ የተለያዬ የግንዛቤ እምነት ቢኖረውም፤ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚቋቋመው፤ አንድ የታሪክ ምዕራፍ ላይ፤ የተለያዩ ክፍፍሎችና አመለካከቶች በአገሪቱ ሰፍነው፤ አገሪቱ ውጥረት ውስጥ መግባቷን በማመን፤ አገሪቱ ወደፊት እንድትሄድ፣ የውጥረቱ ባለድርሻ የሆኑ አካላት በጋራ አምነውበት፣ በአንድነት የሚመሠርቱት ተቋም ነው። ይህ ውጥረት ሊከሰት የሚችለው፤ የመንግሥት አስተዳደር፤ ባንድም ሆነ በሌላ ምክንያት፣ ክፍት ሆኖና ቦታውን ለመሙላት ስምምነት ባለመኖሩ፣ ሁሉን የሚያስማማ ውስኔ ላይ ለመድረስ፤ ሁሉን ያቀፈ አካል ጉዳዩን እንዲያጠናና መፍትሔ እንዲሠጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ነው። በሌላ በኩል፤ ገዢው ቡድን በሙስናና በአድልዖ ተጨማልቆ ሲገኝና፣ በገዢው ቡድንና በተፎካካሪነት ሕዝቡን እንወክላለን ባይ ድርጅቶች፤ በሕዝቡ መካከል የነገሠውን አለመጣጣም ሲጠቀሙበት፤ ይሄው ተቋም ግድ ይሆናል። ሌላም፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ገዢው ፓርቲ ተፋጠውና የሕዝቡን ድምጽ ተካፍለው ሲገኙ፤ አገሪቱን አብረው በሚስማሙበት መንገድ መምራት የማይችሉበትና ገዢው ፓርቲም የበላይ የሚያደርገው ድምጽ ሲያጣ፤ ኮሚሽኑ ይቋቋማል። አገሪቱን ወደፊት ለመውሰድ ወሳኝ የሆነ እንቅፋት ሲገጥማትና የመላ ሕዝቡን ድጋፍ መሰብሰብ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም፤ ይሄው ኮሚሽን ሊቋቋም ይችላል። ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ለማጽደቅም፤ ይሄው ሊደረግ ይቻላል።
በምንም ምክንያት ሆነ በምንም፤ ይሄን የመሰለ አገር አቀፍ የምክክር ኮሚሺን ሲቋቋም፤ ሁለት ወሳኝ የሆኑ መለያዎች አሉት። የመጀመሪያው፤ ባለጉዳይ የተባሉት ተለይተው የታወቁና፣ ግራና ቀኝ ሆነው አብረው ለመሥራት የተሳናቸው አካላት መኖራቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ አገር አቀፍ ምክክር ኮሚሽኑ፤ ከመንግሥት ቁጥጥር ነፃ መሆኑ ነው። የመጀመሪያው ወሳኝ የሚሆንበት ምክንያት፤ ያ እውነታ ከሌለ፤ የምክክር ኮሚሽኑ አስፈላጊ ስለማይሆን ነው። ሁለተኛው አስፈላጊ የሚሆነው፤ መንግሥት እንደልቡ የሚዘውረው ከሆነና ሌላ ድምጽ መስማት የማይፈልግ ከሆነ፤ ኮሚሽኑ ያንገት ጌጥ ብቻ ስለሚሆን ነው። ይህ እጅና እግሩን ጠርንፎ አላሠራ የሚል እንቅፋት ባለበት እውነታ፤ እውነተኛ አገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን የለም። አሁንም በአገራችን እያየን ያለነው፤ ይሄን ሀቅ ነው።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በድረገጹ ላይ ራዕይ ብሎ ያሰፈረው፤ “እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ፤ አገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየት’’ ይላል።
ዕሴቶች ብሎ የሚዘረዝራቸው፤ “አካታችነትና አሳታፊነት፣ ገለልተኛነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ብቃትና ሙያተኛነት፣ አጋርነትና ትብብር፣ የህግ የበላይነት፣ ተዓማኒነትና ቅቡልነት፤” ናቸው።
ተልዕኮ ብሎ ያሰፈረው፤ “በኢትዮጵያ፤ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች፤ ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሀገራዊ ምክሮችን በማካሄድ፣ ምክረ ሀሳቦችን በማቅረብ፣ እና ለተግባራዊነቱም የመከታተያ ስርዓት በመዘርጋት፤ ለሀገራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር።” ነው።
በዚህ በተልዕኮው፤ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም ምክንያቱን እናገኛለን። ልዩነቶች እና አለመግባባቶች አሉ! ይለናል። እነማን ናቸው የተለያዩት ወይንም ያልተግባቡት? ይሄ ለኛ የተተወ ጉዳይ ነው።
የመጀመሪያ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዓላማ ተደርጎ የተቀመጠው፤
- “በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች፤ወሳኝ ምክንያቶችን በመለየት፣ እና ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት፣ ምክክር እንዲደረግባቸው ማመቻቸት።”
የሚል ነው።
እንግዲህ፤ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተፈጠሩ ልዩነቶች አሉ! ካለ፤ እኒህም ወሳኝ ምክንያቶች ናቸው! ካለ፤ በገዢው ቡድን እምነት፤ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋም አስፈላጊነት ግድ ሆኗል። ችግር እንዳለ ተረድቷል። እናም የምክክር ኮሚሽን መቋቋም እንዳለበት ተረድቷል። ስለዚህ፤ ግድ ስለሆነበት የፈጠረው ነው።
ከዚህ ተነስተን፤ ምን ተካሄደ? የሚለውን እንመርምር።
መጀመሪያ፤ በገዢው ቡድን አማካኝነት የተሰበሰቡት በሙሉ፤ የተለያዩ አይደሉም። ሁሉም የብልፅግና አባላት ናቸው። ገለልተኛነትና እምነት፤ ቦታ አጡ! ልዩነት ያሏቸው ክፍሎች አሉ! በአገራችን ችግር ተፈጥሯል! የሚለው ሁሉ ገደል ተጣለ! አሁን በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች፤ ሕዝባዊ አመጾች እየተካሄዱ ናቸው። እኒህ ክፍሎች ያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ። ከነዚህ አንጻር፤ የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽኑ፤ ምን እያደረገ ነው? እኒህን ክፍሎች የማካተት ኃላፊነት ነበረው? ያገባዋል? ወይንስ አያገባውም? እስኪ ይሄንን ለአንባቢ ልተውና፤ ይሄ የገዢው ቡድን፤ ምን አያደረገ እንደሆነ እንመለከት።
“እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ፤ . . . ” ሲል፤ ምንድን ለማመልከት ነው? አገራዊ መሠረታዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
አገር ሲባል፤ የተወሰነ ዙሪያ ገጠም የሆነ ድንበር ያለው፣ የመለያ ሰንደቅ ዓላማ ያለው፣ የመንግሥት ሥራ ማስኬጃ ቋንቋ ያለው፣ የመንግሥት መቀመጫ የሆነ ዋና ከተማ ያለው፣ . . . እያለ ይቀጥላል።
ይህ ኮሚሺን፤ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ሊስማማ አልቻለም። በተፎካካራነት የተለዬ ሃሳብ ያቀረቡትን አደንቃቸዋለሁ። አገር አፍራሽ የሆኑትን እና ገዢው ቡድን ሊያራምድ የፈለገውን አጀንዳ ባለመቀበል ጸንተው የቆሙትን አመሰግናቸዋለሁ። ለነገሩ ግን፤ ኢትዮጵያ የምትባል፣ የሁላችን የሆነች አገር አለች ወይ? ኮሚሽኑን እንተወው፤ እውነት ኢትዮጵያ የምትባል አገር አለች ወይ? የሚለውን እንጠይቅ። ይሄ ኮሚሽን፤ አገር እንዳለን እንኳ ሊያረጋግጥልን አልቻለም። እየነገረን ያለው፤ “የተቋቋምኩት አንድም ገዢው ቡድን ግድ ስለሆነበት ለይስሙላ፤ አለያም የገዢውን ቡድን ፍላጎትና ዓላማ እንዳሳካ ነው!” የሚለውን ነው። ቁጥር ወዲያና ወዲህ! አካላት ከዚህና ከዚያ! ወሳኝ ይሄና ያ! የሚለው ሁሉ፤ አጃቢ ጥላ ነው።
የማጠቃልለው፤ ኮሚሽኑ ከመጀመሪያዉኑ በገዢው ቡድን፤ አብይ መራሹ የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ የተቋቋመና የዚህን ገዢ ቡድን ፍላጎትና ዓላማ ለማሳካት የተነሳ በመሆኑ፤ ይሄንን እንደ ተቋም መመልከትና ከዚህ አካል ውጤት መጠበቅ፤ ላም አለኝ በሰማይ! ነው። ይህ ስርዓት፤ ማንኛውንም ሁላችንን በአንድ አሰባስቦ የያዘንን የኅብረተሰብ ሰንሰለት በጣጥሶ፤ ሕዝቡን እርስ በርስ ማፋጀትና አገር ማፍረስ ይዟል። መወገድ እንዳለበት ያልተረዳ የለም። ጥያቄው፤ እንዴት ነው በአንድ ተሰባስበን፣ በአንድ መክረን፣ ነገ አገር እንዲኖረን የምናደርገው? የሚለው ነው። ይሄ በምኞት ወይንም በየመቀመጫችን ላይ ሆነን የኮምፒውተር የፊደላት ቁልፍችን በመጠብጠብ የሚደረግ ክንውን አይደለም። ለወገን ህይወታቸውን እየከፈሉም በትግል የተሰማሩ አርበኞች አሉን። እኒህ ፋኖዎች፤ ይህ ሰርዓት መለወጥ እንጂ፤ መሽሞንሞን እንደሌለበት እየነገሩን ነው። በያለንበት ይሄን ተቀብለን አብረን የምንጓዝበትን መንገድ መፈለግ፤ ግዴታችን ነው። ነገ በአገሬ የኅብረተሰብ ክንውን እሳተፋለሁ ባይ፤ ዛሬውኑ የትግሉ አካል መሆኑን ማሳየት አለበት። አልመሸም፤ እንቆጠር።