በላይነህ እባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሲርያክ ፕሬስ* የተባለ ጋዜጣ በየካቲት 19, 2026 እትሙ አሲሪያንስ ለሶስት ሺ ዘመናት በተፈጠመባቸው የዘር ማጥፋት ዘመቻና ስደት እየጠፉ እንደሆነ ያትታል፡፡ ይህ ጥሪ ለቅጥራን ለቀሩት አሲሪያንስ ጅብ ተሄደ ውሻ ጮኸ ይመስላል፡፡ ክርስቶስ አራማይክ የሚባለውን ቋንቋቸውን ይናገርላቸው የነበሩት አሲርያውን በጥንት ዘመን እጅግ ገናና መንግስት የገነቡና ስልጣኔን ያስፋፉ እንደነበሩ ታሪክ ያስተምራል፡፡ ዳሩ ግን ለሶስት ሺህ ዘመናት በተፈጠመባቸው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ቀስበቀስ ጠፍተው ጥንት ይኖሩ እንደነበር እንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ተረስተዋል፡፡ ከግማሽ ክፍለ-ዘመን በፊት ጀምሮ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እየተኪያሄደበት ያለው አማራ ውቡን ቋንቋውን አማርኛን እህት ቋንቋ ከሚሉት ከአሲሪያንስ ምን ሊማር ይገባዋል?
አማራ ከአሲሪያውያን ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም የዘር ማጥፋት እኩይ ተግባር ከሚፈጠምባቸው ፍጡራንም ትምህርት ቀስሞ ሳይጨልም ህልውናን ማስቀጠል ይኖርበታል፡፡ ማንኛውም ፍጡር ዘሩን ከመጥፋት ለማዳን የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ አጋም ፍሬውን ሲነጥቁት በእሾሁ ይዋጋል፡፡ እሬት በልተው እንዳይጨርሱት ይመራል፡፡ አውራ ዶሮ ጫጩቶቹን ለማዳን ተጭልፊት ይገጥማል፡፡ ንብ “ከራሴ በፊት ቀፎዬን” በሚል ክርክር ሳይጠላለፍ ለህልውናው ያጠራቀመውን ማር ሊዝቅ የመጣውን ሁሉ ሞረሽ ተጠራርቶ እየነደፈ እባጭ በእባጭ ያደርጋል፡፡ የዛሬው አማራ ግን እርስቱንም ህይወቱንም ሲወስዱት “ከራሴ በፊት ቀፎዬን” በሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ሲነታረክ ዘሩ መጥፋቱን ቀጥሏል፡፡
የስንቱን ወራሪ ወገብ እየሰበሩ ወደ መጣበት ሲመለሱ ሺህ ዘመናት ያስቆጠሩ አርበኞች ተከታይ ትውልድ የዛሬው አማራ “ቋንጃህን ሰበርንህ” ሲሉት ቀፎዬን አትስበሩት እንጅ ወርቼንስ ይሁን እያለ ግማሽ ክፍለ- ዘመን አስቆጠረ፡፡ አማራ ግዛቱን ተግዛታቸው ሲያስገቡት፣ ንብረቱን እየቀሙ ከቅድመ አያቶቹ እርስት ሲያፈልሱትና ዳግም ዘጽአትን ሲፈጽሙበት፣ ዘሩን እየለዩ በከተማ በገጥሩ ሲረሽኑት፣ ከርቸሌ አያስገቡ በኮረንቲ ሲጠብሱትና የጠርሙስ ውሀ እያንጠለጠሉ ሲሰልቡት፣ በመድሀኒት ሴቶቹን ሲያመክኑ፣ ከሥራ ሲያባርሩት፣ በርሃብና በበሽታ ሲቀጡት ሁሉ ቀፎዬን አይንኩት እንጅ እኔስ እችለዋለሁ ሲል ኖረ፡፡ ሃይማኖቱን ሲያረክሱ፣ ባህሉን ሲያቆሽሹ፣ የአምልኮት ሥፍራውንና ቅርሱን ሲያጋዩም “ቀፎዬን እስካልነኩ ድረስ እችለዋለሁ” ሲል ዘመን አስቆጠረ፡፡
ቀፎውን በክልል ሲከፋፍሉና በጪስ እያጠኑ ማሩን ሲዝቁ የኖሩት ምላሳቸውን ቅቤ ተቀብተው “ስንኖር የቀፎ ንቦች ስንሞትም የቀፎ ንቦች” ብለው ሲሸነግሉት ደሞ ሲሰሩ የኖሩቱን ረስቶ አሸብራቂ አሻንጉሊት እንዳሳዩት ህጻን “እንግእእእእ…” ብሎ በደስታ እየፈነደቀ ቀፎዬን የሚያድኑ “ሙሴዎችና እያሱዎች” መጡ እያለ በመላው ዓለም ጨፈረ፡፡ የምራቅ ጠብታ ሳይደርቅ ግን ከበፊቱም የከፋ የዘር ምንጠራው ቀጠለ፡፡ በመላ አገሪቱ ባለቤት እንደሌለው ጫካ ተጨፈጨፈ፣ ዓይኑን በጦር እየተቆፈረ ወጣ፣ እሬሳው በኮረኮንች መንገድ ተጎተተ፤ ተቃጠለ፡፡
ይኸንን ስቃይን ማየት የመረራቸው የንብ ፋኖዎች እንደ አያቶቻቸው አሻፈረኝ ሲሉም ብዙ ድንጉል የአማራ ምሁር ቀፏችንን ሊሰብሩ የመጡ አክራሪዎች እያለ የእምዬን ወደ አብዬ ዓይነት ወቀሳ በፋኖ ላይ መሰንዘር ጀመረ፡፡ ይኸንን የድንጉሎች መንዘላዘል የተረዳ የንብ ዘር አጥፊም ከቱርክና ከአረብ እየተረጠበ ለሰርግ፣ ለሐዘንና ለጸሎት አማራ በሚሰበስብበት ቦታ ሳይቀር የድሮን ባሩድ ማርከፍከፍና ዘር የማጣፋት ዘመቻውን አጧጧፈ።፡ ይህ እየሆነም አብዛኛው አማራ “ቀፏችንን ትኑር እንጅ ይህም ይቻላል” እያለ መተኛቱን ቀጠለ፡፡
ምሁርን ነኝ ባዩ አማራ ቅድመ አያቶቹ አገር ገንብተውም ሆነ አገር ተከላክለው መኖር የቻሉት እንደ ንብ በአንድነት ተመው ተሩቅም ተቅርብም ዘር አጥፊ ራሳቸውን ተከላክለው መሆኑን ረሳ፡፡ ቅድመ አያቶቹ እንደ ንቦቹ እነሱ ከሌሉ ቀፎው እንደማይኖር የተገነዘቡ እንደነበሩ ለመመርመር ሰነፈ፡፡ በዚህም ምክንያት ገዥ ነኝ እያለ ለመጣው አረመኔ፣ ሌባ፣ ዘራፊ፣ ከሃዲ፣ ቀጣፊ ሁሉ መጨዋቻ አሻንጉሊት ሆነ፡፡ በገነባት አገሩ እንኳን የመወሰን መብቱ ሊከበር ዘሩ በዚያች ምድርም እንዳይኖር ፍንቀላው፣ ጭፍጨፋው፣ በርሃብና በበሽታ መቅጣቱ ተጧጧፈ፡፡ የአማራ ምሁር ግን አሁንም “ለቀፎዬ ስል” የሚለውን የአድርባይ ድስኩር ጣጡቱን እያፍተለተለ መደስኮሩን ቀጠለ፡፡ ዘር የሚጠፋው በመከራ ጊዜ መርዘም እንጅ በአንድ ጀንበር አለመሆኑን በዓለም ከጠፉትና ከመነመኑት የሕዝብ ዘሮች ለመማር ሰነፈ፡፡
ማተብ የለሽ፣ ቃል አባይ፣ ዋሾ፣ ቀጣፊ፣ ሌባ ዘራፊና አረመኔ ሽምግልናና ድርድር ያውቅ ይመስል ዛሬ እንኳ ከግማሽ ክፍለ ዘመን ክህደቶች በኋላ ችግሩ በሽምግልናና በድርድር ይፈታ እያለ መደስኮርን ቀጠለ፡፡ የሮማን፣ የኦቶማን፣ የእንግሊዝንና ሌሎችንም ተስፋፊዎች የረቀቀ ሥለላና ሸር ያላታለለው የአማራ ቅድመ አያት በጂላጅል ካድሬዎች የመደመር ስብከት ከንፈሩን የሚጥል ምሁርን ነኝ ባይ የልጅ ልጅ ተካና አረፈ፡፡ ራስን ከመጥፋት ለማዳንም ሆን ቀፎውን ህልውና ለማስጠበቅ እንደ ንብ ሞረሽ ተጠራርቶ ራስን የመከላከል ጥበብን አስፈላጊነት መረዳት ለተሳነው ዲግሪ ጫኝ አገሩን ጥሎ አለፈ፡፡
በምሁራን ተብዮች ጉንጭ አልፋ ክርክር እየተደናበረ አማራ የቅደመ አያቶቹን ጥበብ፣ ጽናት፣ ጀግንነትና ፍትሐዊት ተጎናፅፎ በአንድነት በመትመም ራሱንና እገሩን ከመጥፋት ለማዳን ዘገዬ፡፡ “ከራሴ በፌት ቆፎዬን” የሚል የሞኝ ተረት እየተረተ እርስቱ እየተኮማተረ፣ ዘሩንም እየመነመነ መሄዱ ቀጠለ፡፡ “ከራሴ በፊት ቀፎዬን” የሚለው ጅል መንገድ ለቀፎውም ለንቡም መጥፊያ ሆነ፡፡
የአድማጭ ያለህ! የዓለም ታሪክ እንደሚያስረዳው ዘር እሚጠፋው መከራና ቸነፈር ለዘመናት ሲዘልቅ ነው፡፡ ገናና ታሪክ የነበራቸው አሲሪያውያን በሶስት ሺህ ዘመን የዘር ማጥፋት ዘመቻ የጠፉት ዘመቻው ሲጀመር እንጠፋለን ብለው ስላላሰቡና እንደ ንብ ግር ብለው ወጥተው ለህልውናቸው ስላልታገሉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የአሲርያን ንቦች ዛሬ እንኳን ቀፎ ሊኖራቸው ዘራቸውም በአብዛኛው ዓለም በላንባ ዲና ተፈልጎ የማይገኝ ነው፡፡ ከራሴ በፊት ቀፎዬን እየሚለው ከንቱ ተረት የአማራን ንብ መከራና ቸነፈር እንደ አሲርያውያን እያራዘመው ነው፡፡ የሰሚ ያለህ! ቀፎ እሚኖረው ንብ ካልጠፋ ነው፡፡ “ቀፎዬ ከሚጠፋ እኔ ልጥፋ” ለሥጋም ለነፍስም የማይበጅ የሞኝ ዘፈን ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
*The Assyrians Are Disappearing: – https://syriacpress.com/blog/2026/02/19/the-assyrians-are-disappearing-and-the-silence-is-dangerous/
ነሐሴ ሁለት ሺ አስራ ስምንት ዓ. ም.