እንደሚታወቀው ፓርቲያችን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ኢትዮጵያ ችግሮቿን በምክክርና በውይይት መፍታት ብቸኛው አማራጯ ነው ብሎ በፅኑ ያምናል።
ይህንን እምነቱንም ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የታገለበትና እየታገለበት ያለው ፕሮግራሙ ላይ በግልፅ አሥፍሮ ለተግባራዊነቱ በመታገል ላይም ይገኛል።
ስለሆነም አሁን ያለንበትን ሀገራዊ ውጥንቅጥ ለመፍታት እንምከር ብለን የወተወትነው ጥያቄአችን ምላሽ አግኝቶ የምክክር ኮምሽን የማቋቋም ፅንሰ-ሀሳቡ ሲነሳ ትግላችን ፍሬ አፈራ ብለን በደስታ ነበር የተቀበልነው። ጅማሮው እንዲቃናም በኮምሽነሮች ምልመላው ላይ የበኩላችንን አስተውፅኦ አድርገን ነበር፤ ምንም እንኳን የኮምሽነሮች ምልመላው ገና ከጅምሩ መጣመም ሲጀምር ተቃውሟችንን ብናሰማም።
በመቀጠልም ምክክሩ ከነ ችግሩም ቢሆን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሲጀምር የአካሄድ ጥመቶችን እየሞገትን የተወሰነ ርቀት አብረን ብንቀጥልም ኮምሽኑ የተቋቋመለትን ዓላማ ሐዲድ ስቶ ባልተሰጠው የስህተት መንገድ ላይ መንደርደሩን ሲቀጥል ወደ ተቋቋመበት ዓላማ እንዲመለስ የሚጠቁም ባለ 6 ነጥብ አንኳር ቅድመ ሁኔታዎችን የያዘ እና አፋጣኝ ምላሽ የሚሻ ደብዳቤ አስገብተን ፓርቲያችን በቅድመ-ሁኔታ እራሱን ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም አገለለ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኮሚሽኑ በተለያየ መንገድ እንድንመለስ ይጠይቀናል እንጂ ጥያቄዎቻችንን ቢያምንባቸውም ምላሽ ሊሰጥባቸው ግን ፈቃደኛ አልሆነም።
ፓርቲያችን መኢአድ ያስቀመጣቸው የቅድመ-ሁኔታ ጥያቄዎች (ለአብነት ያህል)፦
1. ሁሉን አቀፍ እና አካታች ምክክር ለማድረግ ጦርነት በአፋጣኝ ይቁም።
- በማንነታቸውና በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሠሩ የግፍ እሥረኞች ይፈቱና የምክክሩ አካል ይሁኑ።
- የአጋችና ታጋች ድራማ በአስቸኳይ ቆሞ የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ይረጋገጥ፤ እና የመሳሰሉት እነዚህ ነጥቦች አንድም ምላሽ ሳያገኙ የአቋም ለውጥ የለንም በማለት ከምክክር ተሳትፎ ራሱን አግልሎ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እያለ ግን ምክክሩ የሀገርን በጀት ከማውደምና ከማዛባት የዘለለ ምንም ሀገራዊ ችግር ካለመፍታትም አልፎ ሀገራችንን ወደ የማትወጣው ውጥንቅጥ ውስጥ የሚከቷት፣ ሊነሱ እና ሊጠየቁም ጭምር ፅዩፍ መሆን የሚገባቸውን የባዕዳን ጥያቄዎች በቡድን እየተደራጁ በየውይይት ቡድኑ ውስጥ እነዚሁ ሀገር አፍራሽና አውዳሚ እንዲሁም ዘላቂ የቁርሾ ቅርስ ተክሎ ለማለፍ ተግተው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ በየውይይት ቡድኑ ውስጥ ከሚገኙ ተሳታፊ ግለሰቦች መረጃዎች እየደረሱን ይገኛሉ።
እነዚህ እየደረሱንና ሀገርም በአግራሞት እያያቸው ያሉ የአደባባይ ምስጢር የሆኑ መረጃዎች እንዲህ በዋዛ የአንድ ሰሞን የአግራሞት መነጋገሪያ ብቻ ሆነው የሚያልፉ ከሆነና ገዢው ፓርቲም “በምንም አታመጡም” ባይ ቋሚ ባህሪው አፅንቶ የሚያልፈው ከሆነ ለትውልድ የማይነቀል የሀገርን ሕልውና እስከ ወዲያኛው ቅርቃር ውስጥ ከትቶ የሚያልፍ መርዝ መሆኑን ተረድቶ እነዚህን የባዕድ አጀንዳዎች ጠንስሶ የመጣ አካል ከወዲሁ እጁን እንዲሰበስብ እያሳሰብን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም እሱን በማይወክለው ስብስብ በአንድ አዳራሽ ውስጥ ሀገር አፍራሽ ሴራ እየተሴረ መሆኑን ተረድተን ይኼንን ሴራ ሊያስቆም የሚችል የፀና ሁሉን አቀፍ ሰላማዊ ትግል ለማድረግ በንቃት እንድንዘጋጅ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)
ድምፃችን ለሀገር ኑሮና ሉዓላዊነት ቀጣይነት!
ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ።
“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!”