የአብይ አህመድ የብልፅግና አገዛዝ አስከፊነት ለሕወሓት የጥፋት ወጥመድ እጅ የመስጫ ምክንያት ይሆናልን?

(የአማራ ሕልውና ትግል እና የ«ጽምዶ» እውነተኛ ገጽታ)
የፖለቲካና ስትራቴጂያዊ ጥናት – በዶ/ር ሶስና ታደሰ
የትንተናው ዋና መንደርደሪያ (Executive Summary)
ከአማራ ሕዝብ ጥቅምና ሕልውና አኳያ፣ በፋኖ፣ በTDF (ሕወሓት) እና በOLA (ኦነግ ሸኔ) መካከል ሊደረግ የሚታሰብ ማንኛውም ዓይነት ጥምረት ጥልቅ መዋቅራዊና ሞራላዊ ውድቅነት ይገጥመዋል። የዚህ ዓይነት አጋርነት የአማራን ሕዝብ ደህንነትና ታሪካዊ ጥያቄዎች በጊዜያዊ ወታደራዊ ስሌት ለውጦ አሳልፎ የሚሰጥ «የሕልውና ቅራኔ» (Existential Contradiction) ነው የሚሉ በርካታ ምክንያቶች አሉ፦
- የሰማዕታት ደም ክህደትና ታሪካዊ ጠባሳ፦ጥምረቱ በሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ ኃይሎች በአማራ ንጹሐን ላይ ለተፈጸሙ የጅምላ ጨፍጨፋዎች (እንደ ወለጋ፣ ኮምቦልቻ፣ ማይካድራና ጭና ያሉ) ተጠያቂ ለሆኑ አካላት ያለምንም ፍትህ ያለ ዋጋ ይቅርታ መስጠት በመሆኑ፣ የትግሉን ሞራላዊ መሠረት ያፈርሰዋል።
- የርስትና ማንነት ጉዳይ (የወልቃይትና ራያ አጥር)፦ሕወሓት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ የትግራይ ግዛቶች ናቸው ብሎ በሚያምንበት፣ ፋኖ ደግሞ የአማራ ታሪካዊ ርስቶች ናቸው በሚልበት ሁኔታ ጥምረት መፍጠር፤ ወልቃይትና ራያን ለሕወሓት አሳልፎ መስጠትን ይጠይቃል—ይህ ደግሞ የሕልውና ትግሉን ዓላማ ሙሉ በሙሉ መካድ ነው።
- የተቃረነ የፖለቲካ ራእይ፦የኦነግ ሸኔ አጀንዳ “የኦሮሚያ ሪፐብሊክን” መመሥረት፤ የሕወሓት የፖለቲካ ግብም “ታላቋ ትግራይ” ን እውን ማድረግ ሲሆን፣ የሁለቱም ኃይሎች ግብ በአማራ መቃብር፣ በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ እንዲሳካ የሚፈልጉት ነው፡፡ የፋኖ ዓላማ ደግሞ የአማራን ሕልውና በማስከበር የተረጋጋችና ፍትሐዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነው። እነዚህ ሁለቱ ራእዮች ሙሉ በሙሉ የሚጋጩ ናቸው።
- የሕዝባዊ ቅቡልነት ማጣት፦የአማራን ሕዝብ በብሔሩ ለይተው በቀጥታ ሲያጠቁ ከነበሩ ኃይሎች ጋር መሰለፍ ፋኖ የነበረውን ሕዝባዊና ሞራላዊ የበላይነት የሚያሳጣው ከመሆኑም በላይ፣ በየአካባቢው ባሉ የፋኖ ክንፎች መካከል ጥልቅ ክፍፍልን ይፈጥራል። አሁንም ፈጥሯል፡፡
- የስልታዊ መጠቀሚያነት አደጋ፦ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ፋኖን ማዕከላዊ መንግሥቱን ማዳከሚያ መሳሪያ አድርገው ከተጠቀሙበት በኋላ፣ ዓላማቸው ሲሳካ መልሰው የተበተነውን የአማራ ክልል እንደሚያጠቁት ግልጽ ነው።
የ«እባብ» እና የ«ጅብ» ምስላዊ ፍተሻ (Visual Truth Test)
«አንድ ሰው ከጀርባህ ስላለው ተናዳፊ እባብ ቢያስጠነቅቅህ፣ ከፊትህ ወዳለው ጅብ እየሳበህ ነው ማለት ነው? ሁለቱም ከፍተኛ ጉዳት ባደረሱ ሁለት ተላላፊና አዳኝ ኃይሎች መካከል ለምን የተሳሳተና (False dichotomy) የግዴታ ምርጫ እንድናደርግ ይፈለጋል? የዚህ አጀንዳ ባለቤት ማን ነው? ሕወሓት? ኤርትራ? ወይንስ ግብፅ?»
ክፍል 1፦ ታሪካዊ ሥርወ-መንስኤና የብልፅግና ውላጅነት
በፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አንድ ሕዝብና ሀገር ለደረሰበት አጠቃላይ ቀውስና የሕልውና አደጋ መፍትሔ ለማግኘት፣ የመከራውን ሥርወ-መንስኤ (Root Cause) በጥልቀት ማወቅና መተንተን ግዴታው ነው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ፣ በተለይም በአማራ ሕዝብና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት፣ የርስት መነጠቅና ሀገር አልባ የማድረግ ዓላማ ያለው ጦርነት የተከፈተው፤ በድንገት ከአየር ላይ የወደቀ ወይም በቅርብ ጊዜ የተፈጠረ አይደለም። ይልቁንም ሕወሓት በደደቢት በረሃ ከፃፈው ማንፌስቶ ጀምሮ ድኀረ-1983 ሲተገብረው የነበረው የጥላቻ ፖለቲካ እና የፈጠረው ህገ-መንግስታዊ ስርአት ቀጥተኛ ፍሬ ነው።
የአማራ ሕዝብ በዘመናዊ ታሪኩ ከፋሽስት ጣሊያን በኋላ እንደ ሕወሓት አቅዶ የሰራበት ስርዓተ-ጠላት አላጋጠመውም። የአሁኑ ዘመን የኦሕዴድ ብልጽግና የጥፋት ምዕራፍ መሠረቱ የተጣለው በዘመነ ሕወሓት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አማራን የገጠሙት ጠላቶች ለመገንጠል ካርታ አስምረው፣ የሰው ልጅ ሕይወት በጅተው፤ ሕዝብ ጨርሰው “ሀገር እንሆናለን” ብለው የሚያልሙ ፋሽስቶች ናቸው፡፡ ይህ እውነታ የገባቸው ጥቂት የአማራ ልሂቃን፣ ይህ የሕልውና ትግል ውስብስብና ግንባረ-ብዙ መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡
ባለፉት 6 ዓመታት ብቻ እንኳን እንደታዘብነው፣ አማራን ለማጥፋት ጦር የሰበቁ ጠላቶች በዓለም ፊት ራሳቸውን ሲገልጹ፦
- ሕወሓት፦“የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን እንደሚታገል”፤
- ኦሕዴድ ብልጽግና፦“የሕግ የበላይነትን ለማስከበር“ የሚያደርገው ትግል እንደሆነ አድርገው ይሰብካሉ።
በአንጻሩ አማራው ራሱን ከጥፋት ለመከላከል የሚያደርገውን በይዘቱ ልዩ የሆነውን ፍትሃዊ የሕልውና ትግል፣ ለዓለማቀፉ ማኀበረሰብ በአግባቡ ማስረዳት አልቻለም፡፡
የቀጠናው ጂኦ-ፖለቲካዊ ቁማር እና የ«ጽምዶ» እውነተኛ ገጽታ
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ በተቃርኖ የተሞሉ ኃይሎች “ጽምዶ” (Tsimdo) በሚል አወዛጋቢ ቀጣናዊ የኃይል አሰላለፍ ፈጥረዋል፡፡ ይህ የሕወሓት፣ ኤርትራ እና ሱዳን ኃይሎች ጥምረት ከአማራ ሕዝብ መሠረታዊ የትግል ዓላማ እና መዳረሻ ግብ አኳያ አንድም የጋራ ፍላጎት የሌለው፣ ይልቁንም በዘላቂ የአማራ ጥቅሞች ላይ በተቃርኖ የሚቆሙ ኃይሎች የሞሉበት ስብስብ ነው፡፡
«ጽምዶ» የአማራ ሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄም ሆነ የፋኖ የትግል ግብ አይደለም፤ ከቃሉ መጠሪያ ጀምሮ በስያሜም ሆነ በገቢር የአማራ የሆነ አንዳችም ነገር የለውም። ይህ አጀንዳ የራሱ የሆነ ጂኦ-ፖለቲካዊ መነሻና መድረሻ ያለው የፖለቲካ ገበያ ሸፍጥ የፈጠረው የቀጠናዊ ቁማር አካል ነው። ለዚህም ነው ሦስቱ አካላት ጥምረቱን ለራሳቸው ጥቅም ብቻ የሚፈልጉት፦
የቀጠናው አካላት ስትራቴጂያዊ ድብቅ ፍላጎት (Strategic Interest)፦
- ጽምዶ – ለኤርትራ መንግሥት፦በኦሕዴድ መራሹ ብልፅግና ላይ የተፈጸመበትን ክህደት ለመበቀል ሲል ጦርነቱን ቢፈልገውም፣ ጦርነቱ ወደ ግዛቱ እንዳይመጣበት የጦርነት ሜዳውን ወደ ኢትዮጵያ የሚገፋበት (Strategic Depth) ስልታዊ መሳሪያው ነው።
- ጽምዶ – ለሱዳን ወታደራዊ መንግሥት፦ኦሕዴድ/ብልፅግና በሱዳን የውክልና ጦርነት እጁን ማስገባቱን ተከትሎ፣ ተፋላሚ ኃይሉን (RSF) ለማጥፋት የኢትዮጵያን ክፍል ለማጥቃት፣ ብሎም በአማራ በኩል ያለውን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መሬት (አልፋሽጋ) ጠቅልሎ ለመውሰድ ያቀደው ነው።
- ጽምዶ – ለሕወሓት፦የእነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ሁለት ሀገራት አቅሞች በመጠቀም፣ የአማራ ታሪካዊ ርስቶችን እነ ወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን በመጠቅለል የሁመራ ኮሪደርን ለመያዝ እና የዘመናት ቅዥቱ የሆነውን “ታላቋ ትግራይ”ን እውን ለማድረግ የተጠቀመበት ነው።
“ጥቅምን በሚስጥር መያዝ” በሚል የማደንዘዣ ቃል፣ የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል፣ ከመሠረታዊ እና ዘላቂ ጥቅሞቹ በተቃርኖ ከተሰለፉ ኃይሎች ጋር በትብብር ስም በመሰለፍ የአማራን ሕዝብ ደምና መስዋዕትነት በግልጽ ለሽያጭ ያቀረበ አደገኛ ስሌት በአደባባይ እየተነገረ ነው።
ፋኖን በሱዳን ጦርነት ልክ እንደ “አርሚ 70” (አርሚ 70 ማለት የቀድሞው ሳምሪ ወይም በማይካድራ ላይ ጭፍጨፋ የፈጸመው ገዳይ ቡድን ማለት ነው) በቅጥረኛነት የማሰለፍ ድብቅ ዕቅድ በትብብር ስም ቀርቧል፡፡ በቀጣይም እነዚህ ሦስት ቡድኖች የፋኖን የወል ስም በመጠቅለል፣ ያለምንም ሕጋዊ ውክልና ‘የወታደራዊ ስምምነት’ በሚል አደገኛ የቁማር ጥምረት የመጫወቻ ካርድ ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ሞጋች ጥያቄ 1፦ ታሪካዊ ወንጀልንና የሕዝብ ደምን የመሸጥ አጣብቂኝ
«የ«ጽምዶ» አራጋቢዎች፤ ሕወሓት ላለፉት 40 ዓመታት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶና በአማራ ሕዝብ ላይ ለፈጸመው የዘር ማጥፋት፣ ላለፉት 27 ዓመታት የዘረጋው ስርአታዊ ማግለል፣ የማዕከላዊ እስር ቤት ሰቆቃ፣ የወልቃይት/ ጠለምትና የራያ አፓርታይድ ጭቆናና የርስት ወረራ፣ የሰሜን እዝን በመምታት በአማራ ሕዝብ ላይ በከፈተው ጦርነት ያደረሰው አሰቃቂ ውድመት፣ አንድም ይፋዊ ይቅርታ ሳይጠይቅና ላደረሰው ወንጀል ፍትሕ ሳይቀበል፣ ዛሬ አብይ አህመድን ስለተቃወመ ብቻ ከሕወሓት ጋር በጥምረት ስም መሻረክ—በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ሰማዕታትን ደም አሳልፎ ለፖለቲካ ቁማር መሸጥ ነው ወይስ አይደለም?
መልሳችሁ ‘አዎ’ ከሆነ ትግሉንም የአማራን ሕዝብም ከድታችኋል፤ ‘አይደለም’ ካላችሁ ደግሞ ሕወሓት የፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል አጥባችሁ ለፍትሕ እንዳይቀርብ ነጻ እያወጣችሁት እንደሆነ ለሕዝቡ አደባባይ ላይ አረጋግጡ!?»
1. የደደቢት ማንፌስቶ፦ የአማራና የኦርቶዶክስ አከርካሪን የመስበር ስትራቴጂ
ሕወሓት ገና በደደቢት በረሃ ትግል ሲጀምር ባወጣው ማንፌስቶ ላይ አማራን የትግራይ ሕዝብ ዋና ታሪካዊ ጠላት አድርጎ ፈርጇል። ኢትዮጵያዊነትን እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ደግሞ የትምክህትና የጨቆና ተቋማት አድርጎ በመፈረጅ፣ “አከርካሪውን እንሰብራለን” በሚል የጥላቻ ርዕዮተ-ዓለም ተነሥቷል። ይህ ማንፌስቶ ላለፉት 40 ዓመታት በስርዓት ሲተገበር የነበረ ከሕወሓት ወደ ኦሕዴድ/ብልፅግና የተላለፈ የፖለቲካ ፕሮግራም ነው። ሕወሓት ራሱ በ1968 ዓ.ም. በማንፌስቶ ያስቀመጠውን ፀረ አማራነት በሀገር ሕገ-መንግሥት ደረጃ በማስቀጠል፣ ፀረ አማራነት ሀገራዊ ቅርፅ አስይዟል፡፡
2. በወልቃይትና ራያ የተፈጸመው የአፓርታይድ ስርዓት
ሕወሓት በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በወልቃይትን፣ ጠገዴ፣ ጠለምት በኃይል ወረራ ሲፈጽም፣ የተገበረው የለየለት የአፓርታይድና የዘር ማጥፋት ስርዓት ነው። የአማራ ግዛቶችን ወደ ትግራይ ከጠቀለለ በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችን በጅምላ በመጨፍጨፍና በማፈናቀል፣ በቦታቸው ከትግራይ በመጡ ሰፋሪዎች የመተካት የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ወንጀል ፈጽሟል። የአማራ ሕዝብ አማርኛ የመናገር፣ የባህልና የማንነት መብቱን በመንጠቅ ከአካላዊ ዘር ማጥፋት እስከ ባህል ማጥፋት (Cultural genocide) ድረስ ፈጽሟል፡፡
በሕወሓት ፋሽስታዊ ጭካኔ ለአርባ ዓመታት በጅምላ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንን አፅም ዛሬም ድረስ ለቅመን በክብር አላሳረፍንም፡፡ ያረፈብን የታሪክ ጠባሳ ገና አልሻረም፤ አሁንም የወገኖቻችን ትኩስ ደም እየፈሰሰ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሕወሓት ጋር ”ጽምዶ” በሚል መጠመድ ታሪካዊ ክህደት ነው፡፡
3. የማዕከላዊ እስር ቤት ዘግናኝ ወንጀሎች
ሕወሓት በ27 ዓመታት የግፍ አገዛዙ፣ ሀገሪቱን በጥቁር ሽብርና በሰቆቃ ምድርነት ቀይሯት ነበር። በስሙ «ማዕከላዊ» ተብሎ በሚጠራውና በሌሎች ምስጢራዊ እስር ቤቶች ውስጥ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን፣ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ እና ሞጋች ጋዜጠኞችን፣ የአማራና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምሁራንንና አባቶችን በማሰር ወንድ ሴት ሳይመርጥ የእጅና የእግር ጥፍር በመንቀል፣ በጨለማ ክፍል ውስጥ ለአመታት ዘግቶ ማስቀመጥ እና ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ ማሰቃያዎችን መተግበር የሕወሓት መለያዎች ነበሩ።
4. ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ፦ አማራን ሀገር አልባ የማድረግ የጥፋት መረብ
ሕወሓት በ1987 ዓ.ም የዘረጋው ህገ-መንግስት፣ ኢትዮጵያዊነትን በማፍረስ በዘርና በብሔር ላይ የተመሰረተ የታሪክ ጥፋት ነው። ከሁሉ በላይ ይህ ህገ-መንግስት አማራውን በገዛ ሀገሩ “መጤ”፣ “ነፍጠኛ” እና “ጨቋኝ” አድርጎ በመፈረጅ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተፈጸሙትና ዛሬም ለሚፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋዎችና መፈናቀሎች ህጋዊና ፖለቲካዊ ሽፋን የሰጠ ሰነድ ነው። ዛሬ የአማራ ሕዝብ ህልውናውን እንዳይጠፋ፣ ማንነቱን አስከብሮ የሀገር ባለቤትነቱን ለማስመለስ በመታገል ላይ ያለው፣ በሕወሓት ተተክሎ በኦሕዴድ የጥፋት ዕድገቱ የጨመረውን ጸረ-አማራ መርዛማ የሥርዓቱን ፍሬ ለማምከን ነው፡፡
5. ሞጋቹ እውነታ፦ የአብይ አህመድ አገዛዝ የሕወሓት/የስብሃት ነጋ የዘር ውላጅ ነው!
አሁን ላይ ያለው የኦሕዴድ ብልፅግና/የአብይ አህመድ አገዛዝ ከባዶ አየር የመጣ ወይም አዲስ አገዛዝ አይደለም፤ ይልቁንም ሕወሓት ያረገዘው፣ ያሳደገውና የወለደው ቀጥተኛ የዘር ውላጅ ነው። አብይ አህመድና የኦሕዴድ ብልፅግና አመራሮች ሙሉ በሙሉ በሕወሓት የደህንነት፣ የጦርነትና የፖለቲካ ትምህርት ቤት (ኢህአዴግ) ውስጥ ሰልጥነው ያደጉ ናቸው። ሕወሓት በህገ-መንግስቱ ያስቀመጠውን “የአማራና የኦርቶዶክስ አከርካሪ የመስበር” አጀንዳ፣ አብይ አህመድ በድሮን ጥቃት፣ በታጠቁ ኃይሎች የጅምላ ጭፍጨፋ እና ስልታዊ ጥቃቱን ከገዳማት እስከ ሲኖዶሱ ድረስ hard እና soft power በመጠቀም በፍጥነት እያስፈጸመው ይገኛል።
ክፍል 2፦ የ«ጽምዶ» ወጥመድ እና ስትራቴጂያዊ መውጫ መንገድ
በማንኛውም ሀገርና የማኀበረሰብ ቡድኖች ውስጥ በሚካሄዱ የሕልውናና የፖለቲካ ትግሎች፣ የጋራ ጠላትን ለመመከት በሚል ስም የሚደረጉ ጥምረቶች የሚመሩት በጋራ መከባበር፣ በግልጽ ስትራቴጂያዊ ጥቅም እና በእኩልነት ላይ ተመሥርቶ ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በሕወሓት እና በአፋብን (AFNM) ጥቂት አመራሮች መካከል እየተራገበ ያለው «ጽምዶ» በአማራ ሕዝብ ላይ የተቃጣ ስውር ሴራ እና ለአጠቃላዩ የአማራ ፋኖ ሰራዊት የተዘጋጀ ‘የባርነት ካምፕ’ ነው!
ሕወሓት ከ27 ዓመታት አምባገነናዊ አገዛዝ በኋላ እንኳ ለራሱ ለትግራይ ሕዝብ ያተረፈለት ስደት፣ ያልተቋረጠ ጦርነት እና በሌሎች ወንድም ሕዝቦች ዘንድ መጠላትን ብቻ ነው። ታዲያ የሕዝባዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ መሠረቱን ሙሉ በሙሉ ካጣ የከሰረ መርዛማ ብራንድ ቡድን ጋር እንዴት ጥምረት ይታሰባል?
ሞጋች ጥያቄ 2፦ የተሳሳተው ምርጫ (False Dilemma) እና የባርነት ካምፕ
««የሕወሓትን ወጥመድ ከተቃወማችሁ የአብይ አህመድ ደጋፊዎች ናችሁ» የሚለው የከሰረ ትረካችሁ የሚያሳየው የፖለቲካ ድርቀታችሁን ነው። ለመሆኑ የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል በራሱ እግርና መርህ ቆሞ ሁለቱንም የዘር ማጥፋት አበጋዞች (ሕወሓትንና ብልፅግናን) እኩል መታገል አይችልም ብላችሁ ታምናላችሁ?
ወይስ የአማራ ሕዝብ ነፃነት የሚረጋገጠው ሁልጊዜ በአንዱ በዳይ ጫማ ስር ወድቆ ዳግማዊ ኢሕዴን በመሆን ብቻ ነው ብላችሁ ነው የምታስቡት?»
1. የሕወሓት ያልተለወጠው የበላይነት አቋም እና የአመራሮቹ የትርክት ውድቀት
ሕወሓት በየመድረኩ የአማራን የሕልውና ጥያቄ በግልጽ እያጣጣለ ነው፡፡ ዛሬም ለአማራ ሕዝብ የትግል መነሻ የሆኑ የወሰንና ማንነት ጉዳዮችን በሚጨፈልቅ ፍላጎት ላይ ተቸክሏል፦
- የሕወሓት ቃል አቀባይ የአቶ ሚካኤል ይፋዊ ንግግር፦በአደባባይ ወጥቶ፦ “እኛ እንደ ብልፅግና በሌላ ኃይል አንተማመንም፤ ‘በዚህ ግባ፣ በዚህ ውጣ’ ብለን የምንጋብዘውና የምንጠራው ኃይል የለም! በራሳቸው ፍላጎት ከመጡ የራሳቸው ጉዳይ ነው” በማለት ፋኖን እንደ አቻ ኃይል ሳይሆን “ተገዢና ተላላኪ” አድርጎ እንደሚመለከተው አረጋግጧል።
- የፈትለወርቅ (ሞንጆሪኖ) የጦርነት መፈክር፦የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ፈትለወርቅ (ሞንጆሪኖ) በመድረክ ላይ ወጥታ፦ “ሕልውናችን በጠላቶቻችን መቃብር ላይ ይረጋገጣል!” እና “የሰማዕታት አደራ የሆነው መሬት — ወልቃይትና ራያ — አንዲት ስንዝር እንኳ አትቆረስም!” እያለች በየመድረኩ መፈክር ስታሰማ ታይቷል።
ሞጋች ጥያቄ 3፦ የተንበርካኪነትና የክህደት ፍተሻ
«የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል ‘ማንንም አልጠራንም፣ በራሳቸው ፍላጎት ከመጡ የራሳቸው ጉዳይ ነው’ ብሎ አናቁቷችሁ እያለ፤ የሕወሓት አመራሯ ሞንጆሪኖ ደግሞ ‘ወልቃይትና ራያ አትቆረስም፣ ሕልውናችን በጠላቶቻችን መቃብር ላይ ይረጋገጣል’ እያለች በየመድረኩ እየፎከረች፦
ጥቂት የአፋብን (AFNM) አመራሮች የሕወሓት ጥገኞችና ተንበርካኪዎች ከመሆናችሁ ውጭ፣ ይሄን ያፈጠጠ ውርደት ለሕዝቡ ‘ስትራቴጂያዊ አጋርነት ነው’ ብላችሁ ለማስረዳት የምትጠቀሙበት የሞራል ልዕልና ከየት ልታመጡ ነው?»
2. ፋኖ የሕዝብ ልጅ እንጂ የጥቂቶች የግል ንብረት አይደለም!
በአፋብን ውስጥ ባሉ ሰብሳቢውን ጨምሮ እጅግ ጥቂት ግለሰቦች የሚመራው የ«ጽምዶ» ቅዠት መገንዘብ ያቀተው ዋናው እውነታ፦ ፋኖ የጥቂት አመራሮች የግል ንብረት ሳይሆን፣ ሕዝባዊ መሠረት ያለው የአማራ ሕዝብ ልጅና የነፃነት ታጋይ መሆኑን ነው!
የአማራ ሕዝብ ልጆቹን ያስለፈውና ደሙን ያፈሰሰው በየጊዜው ለሚለዋወጡ የፖለቲካ ቁማርተኞች መጫወቻ እንዲሆን ወይም ዳግማዊ ኢሕዴን ተፈጥሮ ወደ ሕወሓት የባርነት ካምፕ እንዲነዳ አይደለም።
ጥቂት የፋኖ አመራሮች የወጡለትን ሕዝባዊ አደራ ረስተው ለመንበርከክ ቢጣደፉም፣ መሬት ያለው እውነተኛው ፋኖ እና መላው ሕዝብ ይህንን የቅዠት ጥምረት ውድቅ ማድረጋቸው የትግሉን ሕዝባዊነት ያረጋግጣል። ምክንያቱም የአማራ ፋኖ ትግል የጀመረውን በሕዝባዊ ጥያቄ መሠረት እንጂ በጥቂት የጥቅም ቡድን ፍላጎቶች አይደለም፤ የአማራ ፋኖ የጥቂት አመራሮች የግል ንብረት አይደለም፤ ምክንያታዊና ሕዝባዊ መሠረት ያለው የአማራ ሕዝብ ልጅና የነፃነት ታጋይ ነው!
ሞጋች ጥያቄ 4፦ የመሬት ላይ እውነታ እና የ«ሚስጥር ኪስ» ቁማር
«መሬት ላይ ያለው እውነተኛው ፋኖ (እንደ ጎንደር ፋኖ ያሉት መዋቅሮች) የ«ጽምዶ»ን ሴራ በፅናት ውድቅ አድርገውት እያለ፤ የሕዝቡ የደም ዋጋ የሆነው የወልቃይት፣ የራያ የርስት ጉዳይ፣ የደብረብርሃን ተፈናቃዮችና የወለጋ አማራዎች ጭፍጨፋ የፍትሕ ጥያቄ ‘በሚስጥር ኪስ’ የሚያዝ ሸቀጥ ሊሆን አይችልም እያሉ ባለበት ሁኔታ፦
ጥቂት የ«ጽምዶ» የደም ነጋዴዎች የሕዝቡን አደራ ሽጣችሁ የሕወሓት መጠቀሚያ ከመሆን ውጭ፣ መሬት ላይ ያለው ፋኖና ሕዝቡ ከጎናችሁ አለ ለማለት የምታቀርቡት አንድም መሬት ጠብ የሚል እውነት የላችሁም?! ካላችሁ እስኪ አሳዩን?»
ክፍል 3፦ የትግሉ ስትራቴጂያዊ መውጫ መንገድ (The Strategic Way Forward)
የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ከነባሩና ከአሁኑ ስርዓት የጥፋት አዙሪት ወጥቶ አሸናፊ ይሆን ዘንድ የሚከተሉትን 4 መሠረታዊ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች መውሰድ ይኖራበታል፦
- የ«ድርብ መከላከል» (Double Defense) ስትራቴጂን መተግበር፦
የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል በአንድ ጊዜ በሁለት ተቃራኒ ግን እኩል አደገኛ በሆኑ ኃይሎች መሃል የተካሄደ «ባለ ሁለት ግንባር ፍልሚያ» (Two-Front Battle) ነው። በአንድ በኩል የአሁኑ የብልፅግና አገዛዝ በመንግሥታዊ መዋቅርና በኃይል ሰፊ የዘር ማጥፋትና ጥቃት እያደረሰ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሕወሓትና የቀጠናው ስትራቴጂያዊ አጋሮቹ («ጽምዶ») ትግሉን የመጠለፍ፣ ታሪካዊ ርስቶችን የመንጠቅና የአማራን የትግል አቅም ለራሳቸው ቀጣናዊ ቁማር የመጠቀሚያ መሳሪያ የማድረግ ድብቅ አጀንዳ አላቸው። ስለሆነም ስትራቴጂያዊው የመውጫ መንገድ—በአንዱ ጠላት ቀጥተኛ ጥቃት ምክንያት ለሌላኛው አድፍጦ ለሚጠብቅ ኃይል ጀርባን አሳልፎ አለመስጠት፣ በታክቲክ ደረጃ ከሁለቱም ወገን የሚመጡ ስጋቶችን በንቃት እየተቆጣጠሩ በስትራቴጂ ደረጃ ደግሞ ዘላቂ ጥቅምን፣ ማንነትና ርስት የማስከበር ዓላማን ሳይቀይሩ በራስ መርህ ላይ ጸንቶ ሁለቱንም አደጋዎች እኩል የመመከት «የድርብ መከላከል» መስመር መያዝ ነው።
- የፖለቲካና የወታደራዊ ነፃነትን በራስ አቅም ማረጋገጥ፦
ትግሉ የማንኛውም ሌላ ኃይል መጠቀሚያ ወይም የቀጠናው ቁማር የኪሳራ ከላላ (Buffer) ከመሆን ሙሉ በሙሉ ነፃ መውጣት አለበት። የትግሉ የጀርባ አጥንት በፅኑ ማማ ላይ መገንባት ያለበት በአማራ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ባጠነጠነ በራሱ በሕዝቡ መሪነትና መስዋዕትነት፣ በራሱ ድርጅታዊ ጥንካሬ፣ በራሱ የትግል ግብና ራእይ ላይ ብቻ ነው።
- የመሬት ላይ እውነተኛና መርህ-ተኮር አንድነትን መፍጠር፦
የአማራ ሕዝብ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን የደረሰበትን መከራ የተረዱ፣ ይህን መዋቅራዊ የጥቃት መሠረት ከጥፋት ጥንስሱ (ሕወሓት) እስከ ውርስ አስቀጣዩ (ኦሕዴድ) ድረስ ያሉ ጠላቶችን ጠንቅቀው የተረዱ እውነተኛ የአማራ ፋኖዎች መሬት ላይ ያሉ የሕዝብ መዋቅሮች የ«ጽምዶ»ን ወጥመድ ውድቅ ማድረጋቸው እንደ ትልቅ ጥንካሬ የሚወሰድ ሲሆን፤ የውስጥ አንድነትን በመርህ ላይ ተመሥርቶ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ባለፈው ሐምሌ 5 ቀን 2018 ዓ.ም. የጎንደር ፋኖዎች ያወጡት የአቋም መግለጫ እውነተኛ የአማራ የሕልውና ትግል መንፈስ የተንጸባረቀበት ነው፤ ይህ መንፈስ በሁሉም ቀጠና መታየት አለበት፡፡
- የማይደራደሩበት መርህ-ተኮር ዲፕሎማሲን መከተል፦
ከማንኛውም ቀጣናዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ ኃይል ጋር የሚደረግ ንግግርና ግንኙነት የሚቻለው፣ የሕዝቡ የሕልውና፣ የርስትና የፍትሕ ጥያቄዎች በይፋ፣ በቅድመ-ሁኔታና ያለምንም መሽኮርመም ሙሉ በሙሉ ሲቀበሉ ብቻ መሆን አለበት።
የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ከነባሩና ከአሁኑ ስርዓት የጥፋት አዙሪት ወጥቶ አሸናፊ ይሆን ዘንድ የሚከተሉትን ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች መውሰድ ይኖርበታል፦
- የፖለቲካና የወታደራዊ ነፃነትን ማስጠበቅ፦ትግሉ የማንኛውም ሌላ ኃይል መጠቀሚያ ወይም የቀጠናው ቁማር የኪሳራ ከላላ (Buffer) ከመሆን ሙሉ በሙሉ ነፃ መውጣት አለበት።
- በራስ የትግል ግብና አቅም ላይ መተማመን፦የትግሉ የጀርባ አጥንት በፅኑ ማማ ላይ መገንባት ያለበት በአማራ መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ያጠነጠነ በራሱ በሕዝቡ መሪነትና መስዋዕትነት፣ በራሱ ድርጅታዊ ጥንካሬ፣ በራሱ የትግል ግብና ራእይ ላይ ብቻ ሲሆን ነው።
- የመሬት ላይ እውነተኛ አንድነትን መፍጠር፦የአማራ ሕዝብ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን የደረሰበትን መከራ የተረዱ፣ ይህን መዋቅራዊ የጥቃት መሠረት ከጥፋት ጥንስሱ (ሕወሓት) እስከ ውርስ አስቀጣዩ (ኦሕዴድ) ድረስ ያሉ ጠላቶችን ጠንቅቀው የተረዱ እውነተኛ የአማራ ፋኖዎች መሬት ላይ ያሉ የሕዝብ መዋቅሮች የ«ጽምዶ»ን ወጥመድ ውድቅ ማድረጋቸው እንደ ትልቅ ጥንካሬ የሚወሰድ ሲሆን፤ የውስጥ አንድነትን በመርህ ላይ ተመሥርቶ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ባለፈው ሐምሌ 5, 2018ዓ.ም የጎንደር ፋኖዎች ያወጡት የአቋም መግለጫ እውነተኛ የአማራ የሕልውና ትግል መንፈስ የተንጸባረቀበት ነው፤ ይህ መንፈስ በሁሉም ቀጠና መታየት አለበት፡፡
- መርህ ተኮር ዲፕሎማሲ፦ከማንኛውም ኃይል ጋር የሚደረግ ንግግር የሚቻለው፣ የሕዝቡ የሕልውና፣ የርስትና የፍትሕ ጥያቄዎች በይፋና በቅድመ-ሁኔታ በግልጽ ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ያለምንም መሽኮርመም ሲቀበሉ ብቻ መሆን አለበት።
እንደመውጫ፦ ሞጋች ጥያቄ 5፦ (የጎንደር ፋኖን ተጋድሎና እውነታ የሚያሳይ)
«የ«ጽምዶ» አራጋቢዎች፤ የጎንደር ፋኖና መሬት ላይ ያለው እውነተኛው ሰራዊት ዛሬም በየግንባሩ ከአገዛዙ ሰራዊት ጋር ደሙን እያፈሰሰ፣ ሕይወቱን እየገበረና ውድ መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል!
መሬት ላይ ያለው እውነታ ይህ ሆኖ እያለ፦
- በየቀኑ ከብልፅግና ጦር ጋር ሀይለኛ ተኩስ ውስጥ ያለን የሕዝብ አርበኛ፣ ‘ከሌላኛው ጸረ-አማራና ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይል (ከሕወሓት) ጋር አልሰለፍም’ ስላለ ብቻ ‘የብልፅግና ደጋፊ’ ብሎ መፈረጅ—የራሳችሁን የፖለቲካ ውድቀትና ተንበርካኪነት ለመሸፈን የምታደርጉት የከሰረ የፕሮፖጋንዳ ሸፍጥ አይደለምን?
- ለመሆኑ በግንባር ከአገዛዙ ሰራዊት ጋር የሚዋጋው የጎንደር ፋኖ ‘የአብይ ደጋፊ’ ከተባለ፤ በአዲስ አበባ ምቾት ውስጥ ሆኖ የሕወሓትን ወንጀል የሚያጥበውና የሕዝቡን የደም ዋጋ ‘በሚስጥር ኪሱ’ ይዞ የሚነግደው ጥቂቱ ቡድን ደግሞ የማን ቅጥረኛና ተልእኮ አስፈጻሚ ሊባል ነው?”
ማጠቃለያ
የአብይ አህመድ የብልፅግና አገዛዝ አስከፊነት ለሕወሓት የጥፋት ወጥመድ እጅ የመስጫ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ከአማራ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም አኳያ ሕወሓት በአደባባይ አጋርነቱን ሳይሆን ጠላትነቱን ነው ዛሬም እያሳየ ያለው፡፡ በአማራ ጉዳይ ነባር አቋሙን ሳይቀይር፣ የፍረጃ ስም እየለዋወጠ የጠላቶቹን መቃብር እየተመኘ በሚፎክርበት አደባባይ፤ በትብብር ስም የትግሉን አደራ ለሕወሓት አሳልፈው ለመስጠት የሚሮጡ ጥቂት አመራሮች የሕዝቡን መስዋዕትነት በግልጽ የካዱ ናቸው!
የሕወሓትን ወንጀል ማጠብ እና የፍርሃት ጦርነት በፕሮፖጋንዳ መልቀቅ የአማራ ሕዝብን ልዕልና መናቅ ነው፡፡ የአፋብን ሰብሳቢ ዘመነ ካሴ፣ በአንድ ንግግሩ አማራውን ብቻውን ለማቆም ሩጫ አለ፣ ካልተባበርን “ግብግቡ በሚያስነሳው ማዕበል ውስጥ ይሰጥማል” የሚል የሕልውና ስነ-ልቦናዊ ፍርሃት ለመፍጠር ያለመ የፕሮፖጋንዳ ንግግር መናገሩ ይታወሳል፡፡
ይህ ንግግር ፈጽሞ የተለጣፊነት ባህሪ መለያ ከመሆኑ ባሻገር የሕወሓትን የጥፋት ታሪክና የአሁኑን ወታደራዊ ዝግጅት በይፋ “የማጠብ” ስልታዊ ማለማመጃ ወንጀል ነው።
ሕወሓት ወልቃይትና ራያ ላይ የደቀነውን ወታደራዊ ወረራና የቀጠና ፍላጎት ሆን ብሎ በቃላት በመሸፈን፣ ጠላትን አብይ አህመድ ላይ ብቻ ለመገደብ የሚደረገው የፕሮፖጋንዳ ሸፍጥ፣ የአማራ ሕዝብን የአስተሳሰብ ልህቀት እንደ ሕዝብ የመናቅ ሥርየት የለሽ ወንጀል ነው፡፡
“ብቻችንን ከቆምን እንሰጥማለን” የሚል ስነ-ልቦናዊ የፍርሃት ጦርነት በፋኖው ውስጥ በመልቀቅ፣ ከዘር አጥፊዎቹ ከሕወሓትና ከኦነግ ጋር መሻረክን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ ማቅረብ ዳግማዊ ኢሕዴንን የማዋለድ የታሪክ ክህደትና የተንበርካኪነት መንገድ ነው፡፡
የአማራ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት እየታገለው ያለው ለፍትሕ፣ ለሕልውናው መረጋገጥ፣ ለታሪካዊ ርስቶቹ መከበር፣ ለሰብአዊ መብቱ መከበር እና የሀገር ባለቤትነቱን በዘላቂነት በማጽናት እኩልነትን ለማረጋገጥ እንጂ የሌሎች ገንጣይ እና አስገንጣይ ቀጣናዊና ውስጣዊ ኃይሎችን የትርክት ፍጆታ ለማስፈጸም አይደለም።
በጥቅሉ የአማራ ሕዝብ አሸናፊ የሚሆነው አንዱን በዳይ በሌላው በዳይ ለመተካት ሲሮጥ ሳይሆን፤ በራሱ የእውነትና የፍትሕ ጥያቄ፣ በራሱ የአማራዊ መርህ እና በራሱ የተስተካከለ ድርጅታዊ ጥንካሬ ላይ ጸንቶ ሲቆም ብቻ ነው!!