ለ ትግራይ ልሂቃን፣ ምሁራንና የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች
ጉዳዩ፡- የአማራ እና የትግራይ ሕዝብ ብሎም የኢትዮጵያ ሐገረ-መንግሥት አንድነት አደጋ የሆነውን የጥፋት ቡድን በጋራ መታገል ይመለከታል፡፡
ከጅምሩ የኢትዮጵያን የጋራ ማንነት ክዶ ለ‹‹ታላቋ ትግራይ›› የአገር ምስረታ የተነሳው ህወሓት፣ በዓለም የፖለቲካ ታሪክ የሚጠላውን ሀገርና ሕዝብ የመራ ብቸኛው ድርጅት ስለመሆኑ ከመላው የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች የተሰወረ ሐቅ አይደለም፡፡ ይህንን እውነታ የትግራይ ልሂቃን፣ ምሁራንና የፖለቲካ መሪዎች በጊዜ ሂደት ተረድታችሁታል ብለን እናምናለን፡፡
በህወሓት የጥፋት ሴራ ደም ያልፈሰሰበት የኢትዮጵያ ግዛት የለም፡፡ ‹‹ለብሔሮች እና ብሄረሰቦች መብት ታገልኩ›› ቢልም በገቢር የኢትዮጵያን ልጆች ለሥልጣኑ የበላይነት ሲል እርስ በርስ ሲያጋጭና በመካከላችን በሚፈጠረው ቅራኔ የፖለቲካ ትርፍ ሲሰራ የኖረ የጥፋት ቡድን ነው፡፡ ይህንኑ የጥፋት ዓላማውን ዛሬም ቢሆን የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነቱ እንዲፋታ እና እርስበርስ እንዲከፋፈል የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡
የህወሓት የፖለቲካ ግብ በአማራ ቁልቁለት እንዲሁም ሕብረትና አንድነቷን ባጣች የተዳከመች ኢትዮጵያ ስር የበላይነቱን ማረጋገጥ ስለመሆኑ ከፈጠራቸው የውሸት ትርክቶች፣ የጥላቻ ፖለቲካው እና ከግዛት ተስፋፊነቱ መረዳት ይቻላል፡፡
መላው የትግራይ ልሂቃን፣ ምሁራን እና የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች እንደሚያውቁት ህወሓት ለሠላሳ ዓመታት በወረራ ይዟቸው በነበሩ በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን ነው፡፡ ለዚህ የወንጀል ድርጊት የሰውና የጅምላ መቃብር ምስክሮችን አስረጅ ምሳሌ አድርገን እናቀርባለን፡፡ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ‹‹አማራ ነኝ›› ማለት የጥቃት ምንጭ ነበር፡፡ 2008 ዓ/ም የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የህዝቡን ጥያቄ አንግቦ በመነሳት ሕጋዊ እና ሕገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ጥያቄውን ለሚመለከታቸው አካላት ቢያቀርብም፤ ህወሓት ጉዳዩን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድረ ገፅ አጠፋለሁ ብሎ በመነሳት ኮሚቴውን ለግድያ፣ እስር እና መሳደድ መዳረጉ እና በመጨረሻም ዜጎች አማራ በመሆናቸው ብቻ ማይካድራን በመሰሉ ቦታዎች በጅምላ ተጨፍጭፈዋል፡፡
አሁን ላይ ያ ሁሉ መከራ አልፎ፣ እነዚህ አካባቢዎች ነጻ ከወጡ ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ይገኛል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ እየጠየቀ ያለው፣ ‹ማንነቴ አማራ ነው፤ ማንነቴና አስተዳደራዊ ፍላጎቴ ተከብሮልኝ በአማራ ክልል ስር ልተዳደር› የሚል ነው፡፡
ህወሓት በአማራ ሕዝብ ላይ በተከለው የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ የተነሳ የአማራ ጥያቄ የሌሎችን መብት የሚጋፋና የሚጨፈልቅ እንዲመስል ለማድረግ ሞክሯል፡፡ እውነታው ግን አማራ የሚፈልጋት ኢትዮጵያ ከማንም በላይ አልያም ከማንም በታች መሆን ሳይሆን፡- ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሕ እና በህግ-ተገዥነት የተመሠረተ ዴሞክራሲ የሰፈነባት ጠንካራ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ያላት አገር ተገንብታ ማየት ነው፡፡
በዚህ መሻቱ ውስጥ በመሰረታዊነት የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ከታሪክ፣ ከሕግ፣ ከሞራል የሚቃረኑ አይደሉም፡፡ የወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ ጉዳይም በዚሁ አግባብ የሚታይ ነው፡፡
ስለሆነም የትግራይ ልሂቃን፣ ምሁራን እና የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች :-
1.ከምስረታው ጀምሮ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ፣ በትርክት፣ በተቋምና በሥርዓት አማራን ሲያጠቃ እና በሌሎች እንዲጠቃ ሲያደርግ፤
2.በግዛት ተስፋፊነቱ ተከዜን ተሻግሮ የስሜን በጌምድር አካል የሆኑትን ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት እንዲሁም የወሎ ክፍለ-ሀገር አካል የሆነውን ራያን በወረራ ወደ ትግራይ ሲያጠቃልል፤
3.በእነዚህ አካባቢዎች ባለርስት ሆነው ይኖሩ በነበሩ የአማራ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸም፣ በጅምላ ወደ እስራት ሲያግዛቸው፣ ከቀያቸው በገፍ ሲያፈናቀላቸው…ወዘተ እውነታውን እናንተ ታውቁ ነበር፡፡
ይህ አልበቃ ብሎ፣ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝን ከጀርባ በመውጋት፣ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ክህደት በመፈጸም ደም አፈሳሽ ጦርነት መቀስቀሱ፣ ይህንን ተከትሎ በማይካድራ፣ ጭና፣ ቆቦ፣ አጋምሳ ወልድያ፣ ንፋስ መውጫ፣ ጋሸና፣ ኮምበልቻ፣ በተለያዩ የአማራና አፋር አካባቢዎች የፈሰሰው የንጹሃን ደም ጠባሳው ዛሬም አልሻረም፡፡
ህወሓት እነዚህን ወንጀሎች የፈጸመው በ ‘ትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭነት’ ስም እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ አሁንም የጦርነት ዝግጅት እያደረገ ያለው በትግራይ ሕዝብ ስም ነው፡፡ ስለሆነም የትግራይ ልሂቃን፣ ምሁራን እና የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች ከአማራ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ጋር በጋራ በመቆም ‹‹በስሜ ይህ አይደረግም» («Not in My Name») በማለት፣ ከጋራ ጥፋተኝነት ራሳችሁን እንድታድኑ፤ የጋራ ትግል ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የትግራይ ልሂቃን ህወሓት በአማራ ሕዝብ ላይ በተለይም ደግሞ በወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ ያደረሰውን ግፍና በደል እያዩ እየሰሙ ‹‹በስሜ ይህ አይደረግም» በማለት ፈንታ፤ አንዳንዶች የዘር ማጥፋቱን በሀሳብና በድርጊት ሲደግፉ ታይቷል፡፡ ይህ ታሪክ ከእንግዲህ እንዳይደገም፣ የጋራ ትግል እንድናደርግ ታሪካዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ዛሬም ቢሆን፣ በሕወሓት ፋሽስታዊ ጭካኔ ለአርባ ዓመታት በጅምላ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንን አፅም ለቅመን በክብር አሳርፈን አልጨረስንም፡፡ ያረፈብን የታሪክ ጠባሳ ገና አልሻረም፤ አሁንም የወገኖቻችን በደል ፍትህ አልተሰጠም፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ወልቃይት ጠገዴ ጠለምት የሚመጣ ወንጀለኛ ካለ የሚመጣው ለፍርድ ብቻ ይሆናል!!
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከትግራይ ልሂቃን፣ ምሁራን እና የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዎች በትንሹ የሚከተሉት ኃላፊነቶች ይጠበቃሉ፡፡
አንደኛ፡- ህወሓት በወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የአማራ ተወላጆች ላይ ለፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል እውቅና መስጠት፤
ሁለተኛ፡- ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በእነዚህ አካባቢዎች የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ ልዩ ልዩ ግፍና በደሎች ለተፈጸመበት የአማራ ሕዝብ የፍትሕና የካሳ ጥያቄው እንዲመለስለት አጋርነትን ማሳየት፤
ሦስተኛ፡- በትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ የተሸሽጉም ሆኑ በስደት ዓለም ያሉ የዘር ማጥፋት ወንጀሉን በሃሳብ የደገፉ፣ በተግባር ያስፈጸሙ፣ አሁንም ለዳግም ደም አፋሳሽ ጦርነት እየተዘጋጁ ያሉ የጥፋት ቡድኑ የህወሓት አመራሮች፣ አባላትና አጋሮቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ አሳልፎ መስጠት፤
አራተኛ፡- ወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ በታሪክ የአማራ ግዛት መሆናቸውን፣ ድኀረ-1983 በጉልበት ተነጥቀው ተወስደው እንደነበሩ አምኖ መቀበል፤ ናቸው፡፡
የወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ አማራ አስተዳደራዊ ፍላጎቱን በተመለከተ ትላንትም ሆነ ዛሬ ቃሉ አንድ ነው፡፡ ‹ማንነታችን አማራ ነው፤ አስተዳደራዊ ፍላጎታችን በአማራ ክልል ስር መተዳደር ነው› የሚለው ሕዝባዊ መሰረት ያለው ጥያቄ ሊከበርለት ይገባል፡፡ ‹ከትግራይ የሚመጣ ጥሩ ጎረቤት እንጅ፤ አስተዳደር ፈጽሞ አንቀበልም!› እያለ ያለው ሕዝቡ ‹ዛሬ ወደኋላ ላንመለስ ነጻ ወጥተናል› የሚል አቋሙን በአደባባይ ደጋግሞ አሰምቷል፡፡ ስለ ሕዝቡ ማንነት ከራሱ በላይ ምስክር ሊሰጥ የሚችል አንዳች አካል የለም፡፡ ከእንግዲህ ከሕወሓት ሊቃጣ የሚችል የትኛውም ዓይነት
የጦር ወረራ ከአሸባሪነት እና ከአገር አፍራሽነት ተግባር ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ፣ የራሳችንን አሳልፈን አንሰጥም አልን እንጂ የማይገባንን ለሁለታችንም ተፈጥሯዊ ወሰን የሆነውን ተከዜ ወንዝን አልፈን አልጠየቅንም፡፡ እኛ የናንተን ትግራዋይ ማንነት እና ወሰን እንደምናከብረው ሁሉ እናንተም የኛን አማራዊ ማንነት እና ወሰን ልታከብሩ ይገባል፡፡
የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት አማራ ሕዝብ እንኳንስ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ከሚጋራቸው ሕዝቦች ቀርቶ ከጎረቤት ሀገራት ወንድም ሕዝቦች ጋርም በሰላም፣ በፍቅርና በመከባበር መኖር የሁልጊዜም ምርጫው፤ የጥንት ታሪኩም አካል ነው፡፡
በሌላ በኩል በአንዳንድ የትግራይ ልሂቃን ዘንድ ችግርን ወደ ውስጥ ከማየት ይልቅ ችግሩን ውጫዊ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ ይታያል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ወደ ውስጡ በማየት ግማሽ ክፍለ ዘመን በላዩ ላይ ተጣብቆ የቆየውን ሕወሓትን ኦዲት ሊያደርገው ይገባል! ተጠያቂነትን የማያውቀው የዚህ ድርጅት አሰራር የትግራይን ሕዝብ ዘመድ እያሳጣው፣ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል፡፡ እንደ ሰላም ወዳድ ጎረቤት ምክራችን የትግራይ ልሂቃን፣ ምሁራን እና የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች የትግራይን ውስጣዊ ቀውስ ወደ ውስጥ በመመልከት እንጅ ውጫዊ በማድረግ የሚገኝ መፍትሔ፤ የሚቀየር ሁኔታ የለም፡፡
በመሆኑም በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግዱ የጥፋት ቡድኑ አመራሮች፣ እያደረጉት ያለው አውዳሚ የጦርነት ዝግጅት፣ በተግባር በመቃወም፤ አውዳሚ ጦርነቱን ለማስቀረት ከወገናችሁ የአማራ ሕዝብ እና ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመሰለፍ ታሪካዊና ሞራላዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኀበር
ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም.
ሁመራ-ጎንደር ኢትዮጵያ