በበላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የግዕዝና አማርኛ መዝገበ-ቃላት ምሁር የሚለውን ጽንሰ-ሐሳብ ትምህርት የጠገበ፣ አዋቂ፣ ልባምና አስተዋይ እያለ ይተረጉመዋል፡፡ [፩]ትምህርትን ደግሞ እውቀት፣ ድርሳን፣ ምዕዳን እያለ ይገልጽና መምህርን በበኩሉ የትምህርት አባት የሚል ፍች ይሰጠዋል፡፡ [፪] በተመሳሳይ መንገድ ይህ መዝገበ-ቃላት ምግባር ማለት ሥራ ነው [፫] ይልና የሥነን ሥር ሥንን መልካምነት በጎነትና ውበትን ገላጭ ቃል መሆኑን አብራርቶ ሥነ-ምግባር የሥራን ውበት፣ በጎነትና መልካምነት የሚገልጽ ፅንሰ-ሐሳብ መሆኑን ያብራራል፡፡ [፬-፭]

በቅድመ እያቶቻችን ዘመን የምሁር፣ መምህር፣ ግብርና ሥነ-ምግባር ትርጉሞች በመዝገበ-ቃላት የሰፈሩ ብቻ ሳይሆኑ ሕብረተሰቡ በሰፊው በእለት ኑሮው የሚተገብራቸው ብሩክ የኑሮ ዘይቤዎች ነበሩ፡፡ ያ ዘመን መምህር ወይም የትምህርት አባት ከሥጋ አባት ያላነሰ የሚደመጥበትና የሚከበርበት ዘመን ነበር፡፡ ምሁርም “የተማረ ይግደለኝ” እስተሚባል ድረስ የሚከበርብት ዘመን ነበር፡፡ መምህርና ምሁር እጅግ ይከበሩ የነበረበት ምክንያትም መምህር ወይም የትምህርት አባት በመልካም ሥነ-ምግባር ተጠምቆ ተማሪውን አርሞና ኮትኩቶ ለማሳደግ ከወላጅ የበለጠ ይጥር ስለነበረ ነው፡፡ መምህር ይኸንን ጥኑ ኃላፊነት ይወጣ የነበረውም ተማሪው ለራሱና ለወላጆቹ ብቻ ሳይሆን ለአገርምና ለዓለምም የሚጠቅም ዜጋ እንዲሆን ነው፡፡ ምሁርም “የተማረ ይግደለኝ” እየተባለ ይከበር የነበረው በትምህርት ጠጋብነቱ፣ በአዋቂነቱ፣ በልባምነቱና በአስተዋይነቱ ለተራው ዜጋ ወይም ለሕብረተሰብ የማይታየውን ጎጅ ክስተት ከሩቅ አይቶና አበክሮ ተገንዝቦ እንደነቢያት ይተነብይና ሕብረተሰብን አስጠንቅቆ ከክፉ ነገር ይጠብቅ ስለነበረ ነው፡፡
ብዙዎቹ የድሮ መምህራንና ምሁራን ኃላፊነትንና ሥነ-ምግባርን እንደ ብልኮና ጃኖ የሚጎናጸፉ ናቸው፡፡ እነዚህ መምህራንና ምሁራን ራሳቸውን ከፍ ከፍ ሳያደርጉ፣ የትምህርት መረጃ ዲግሪን ቅድመ ወይም ድህረ ሥም “ፒ ኤች ዲ” ወይም “ኤም ዲ” እያሉ እንደ መኪና ታርጋ ሳይለጥፉ የመምህርንና የምሁርን ምግባር እስከ መቃበር ብቻ ሳይሆን ከመቃብር ውስጥ ሆነውም በዘመን ተሻጋሪ መጻሕፍቶቻቸውና ቅርሶቻቸው የሚፈጥሙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከመቃበር በታችም ሆነው የምሁርነትን ምግባርን መፈጸምን ከቀጠሉት መምህራንና ምሁራን መካከልም መምህር ኤርምያስ፣ የኔታ አስረስ የኔሰው፣ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ፣ አቡነ ጎርጎሪዎስና ክቡር አቶ ሀዲስ አለማየሁ በአርአያነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ታላቁ ምሁር መምህር ኤርምያስ ከሶስት መቶ አምሳ ዓመታት በፊት በጎንደር የአጤ ዳዊት ፍትሀ ነገስት አውጪ የነበሩ ሊቅ ናቸው፡፡ በዚያን ዘመን በሁለት የካህናት ቡድኖች መካከል የነገረ-መለኮት ልዩነት ክርክር ተነሳና አጤው በማያውቁትና በማይገባቸው የነገረ-መለኮት ክርክር ጣልቃ በመግባት ለስልጣናቸው የሚበጃቸውን አንደኛውን ክፍል ደግፈው ሌላውን አስፈራርተው ጭጭ ለማሰኘት ሞክሩ፡፡ ብዙዎቹ ካህናት አጤን ፈርተው እየተልፈሰፈሱ ከሚያምኑበት የነገር መለኮት አቋም ሲያፈገፍጉ መምህር ኤርምያስ ግን በእምነታቸውና በማተባቸው ጸንተው አጤውን ተቃወሙ፡፡ በዚህም ምክንያት በአጤው ቀጭን ትዕዛዝ ወህኒ ቤት ተዶሉ፡፡ በወህኒ ቤት ቆይታቸው እንኳን ድሮ እጃቸውን ለመሳም ይሽቀዳደም የነበረው ሕዝብ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸውም በፍርሀት ተውጠው አንዲትም ቀን ወህኒ ቤት ሄደው “እግዚአብሔር ያስፈታዎ” ሳይሏቸው ቀሩ፡፡ እንዲያውም የድሮ ጓዶቻቸውና ሌሎችም በአጤው ይበልጥ ለመወደድ መምህር ኤርምያስ ያላሉትን ሁሉ “አሉ” ብለው እያሳበቁና ያልሰሩትን ወንጀል እየፈጠሩ እስራቱ እንዲጠብቅባቸው አደረጉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን አጤ ዳዊት ሞተው በአጤ በክፋ ሲተኩ መምህር ኤርምያስ ተፈቱ፡፡ ከተፈቱ በኋላ በአንድ ሰንበት ቀን የመወድስ ቅኔ እንዲቀኙ ተጋብዘው “አልቦ ዘመድ” የሚለውን ታሪካዊ ቅኔ እንዲህ ሲሉ ተቀኙ፡፡ [፮]
አልቦ ዘመድ ጊዜ ተዋርዶ፥ ወይከውን ባዕደ ጊዜ ተዋርዶ ዘመድ፡፡
እመሰ ይትሌዓል በንብረተ ሥጋ ማዕድ፥
ጥቀ ዘመዱ፥ ወጥቀ ነገድ፥
ባእድ ይዛመድ፥
እም ኀበ አልቦ ነገድ፡ ወእም ኀበ አልቦ ትውልድ፥
ሶበሂ ተስአልዎ ለሐዋርያ አይሁድ፥
ኀደገ ፈጣሪሁ ወቆመ ምስለ ባዕድ፥
ዘመድሰ ዮሐንስ ወልደ-ነጎድጓድ፥
ኢተፈልጠ ምስለ እሙ እስከ መቃብር ይወርድ፡፡
አንድ የግዕዝና የቅኔ ሊቅ እንደተረጎሙትም
ቀን የጎደለበት ወዳጅ ዘመድ ያጣል
ወዳጁ ዘመዱ አላውቀውም ይላል፡፡
አይሁድ ሲጠይቁት ታውቀዋለህ ብለው
የቅርብ ወዳጁ ጴጥሮስ ሐዋርያው
አላውቀውም ብሎ ክርስቶስን ካደው፡፡
ሀብት ሲትረፈረፍ ሲሰፋ ማዕድ፥
ዝምድና የሌለው ይሆናል ዘመድ፡፡
ይህ ከሆነ ዘመድ ይቅር ይጠንቀር፥
የማይዘልቅ ከሆነ እስከመቃብር፡፡
ዝምድና ይሉሐል እንደ ዮሐንስ
ከመቃብሩ ላይ ቆማ ስታለቅስ
ከማርያም ጋር ጸና፡ እስከ ሞት ድረስ፡፡
ይህ በጥቂት መስመሮች የሰፈረው ቅኔ የቅዱሳን መጻሕፍትን አንኳር መልዕክት ከሰው ባህሪ አዛምዶ የያዘና በዝርዝር ቢጻፍ ትልቅ መጽሐፍ የሚወጣው ነው፡፡ ይህ ቅኔ ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ እስካሁን ያለውንና የወደፊቱንም በጎ ወይም ከንቱ የሰው ልጅ ባህሪ የሚገልጽና እንደ ዓባይ ወንዝ ሲፈስ የሚኖር ጥልቅ ትምህርትና የአገር ሐብት ነው፡፡
እንደ መምህር ኤርምያስ ሁሉ የኔታ አስረስ የኔሰውም በኢትዮጵያ ሃማኖታዊ ትምህርት፣ ቅኔና ፍልስፍና ታሽተው የወጡ ሊቅ ናቸው፡፡ የኔታ አስረስ የኔሰው ትምህርት ጠጋብ፣ አዋቂ፣ ልባምና አስተዋይ እንደነበሩ ሕዝባቸውንና አገራቸውን ከአደጋ ለመከላክል የተገበሯቸው ግብሮች የሚመሰክሩት ነው፡፡ ለምሳሌ ትቤ አክሡም (አክሱም ትናገር)ና የካም መታሰቢያ በሚሉ መጻሕፍቶቻቸው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ምንጭ ራሷ ኢትዮጵያ እንደሆነችና ከግሪክም ሆነ ከአረብ የተበደረችው እንደሌለ በሚገባ ያስተማሩ ናቸው፡፡[፯-፰] ሰሚ ባያገኙም ትቤ አኩሱም በሚለው መጽሐፋቸው የምዕራባውያንን ተንኮል በተለይም የፖርቹጋሎችን ሸር በዝርዝር ያስገነዘቡ ናቸው፡፡ ምዕራባውያን ከእነርሱ እጅግ እሩቅ ዘመን በፊት የጠነከረች አገር በነበረችው ኢትዮጵያ ፈጠራና ስልጣኔ እንዳይስፋፋ በሽመና፣ ቀጥቃጭነትና ቆዳ ፋቂነት የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ጥበበኞችን በዝቅተኝት መንፈስ እንዲታዩ ለማድረግ የሰሩትን ደባ ለሕዝብ ለማስረዳት የዋተቱ ምሁር ናቸው፡፡
እንደ የኔታ አስረስ የኔሰው ትምህርት ጠጋብ፣ አዋቂ፣ ልባምና አስተዋይ የነበሩት መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ለአገር ነፃነት መሰረት በሆነችው የኢትዮጵያ ቤተክርርያን ጥርሳቸውን የነከሱ የምዕራባውያን መንግስታት ሰላዮችን በሃይማኖት ሰባኪ መልክ እየላኩ የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና በጥቅማጥቅም እየደለሉ ከእምነታቸውና ከወላጆቻቸው ቤተክርስትያን እየነጠቁ መውሰድ ሲጀምሩ ኮኮሐ ሃይማኖትና መድሎተ አሚን በሚባሉት ጥልቅ ፍልስፍና አዘል የሃይማቶ መጻሕፍቶቻቸው የታግሉ ናቸው፡፡[፱-፲] ሊቁ መልአክ ብርሃን አድማሱ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና አይምሮን ተጠቅሞ የሃይማኖቱን ምስጢር በመመርመር ከነጣቂ ተኩላዎች ራሱን እንዲከላክለል “ሰው ሆይ!” እያሉ የተማጸኑና በመማጸን ላይ ያሉ ዝንተ ዓለም አስተማሪ ናቸው፡፡ ፋሽሽት ኢትዮጵያን ሲወርና እነ አቡነ ጴጥሮስን በባሩድ ሲጨፈጭፍም ጥራኝ ጫካው ብለው በርሃ የገቡ አርበኛም ናቸው፡፡ ፋሽሽት ኢትዮጵያውያንን በባርነት ሊገዛና ሃይማኖትንም ሊቀይር እንደመጣ ሕዝብን በመቀስቀስ፣ አርበኞችን ስለኢትዮጵያ ታሪክና ሃይማኖት በማስተማር፣ በአርበኞችና በፋኖዎች መሪዎች መካከል ግጭት ሲኖርም በማስታረቅ ከማንኛውም ስም ጥር አርበኛ ያላነሰ ለነፃነትና ለሃማኖታቸው የታገሉ ናቸው፡፡ ዛሬም በይዘታቸው አቻ በሌላቸው መጻሕፍቶቻቸው ለተዋህዶ ቤተክርስትያንና ለአገራቸው ከመቃብር ሆነው ትግላቸውን የቀጠሉ ባለማተብ አባት ናቸው፡፡
እንደ ሊቀ መልአክ አድማሱ ጀምበሬ ሁሉ አቡነ ጎርጎሪዎስ የኢትዮጵያን ልጆች በሰላይ የሃይማኖት ሰባኪዎች ከቤተክርስትያናቸው እንደ በግ ግልግል እየተነጠቁ ከመወሰድ ለማዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ታሪክና የቤተክርስትያን ታሪክ በዓለም መድረክ የሚሉ መጻሕፍት በመጻፍ፣ [፲፩-፲፪] ወጣቶች በሃይማኖታቸው ትምህርትና ታሪክ ታንጸው የሚወጡበትን ሥርዓት-ትምህርትና ገዳም ለመገንባት ከአቡነ ቴዎፍሎስ ጋር ሌት ተቀን የዋተቱ አባት ናቸው፡፡ አቡነ ጎርጎሪዎስ የአገራቸውን የትምህርት ቀለም እሲቲበቃቸው እንደ ወተት ተግተው እውቀት የጠገቡ፣ ግሪክ አገር ሄደውም ሃይማኖትና ፍልስፍና የተማሩ ሊቅ ናቸው፡፡
ረጅም ቅዱስ ሥራቸውን በትምህርት አባትነት (መምህርነት) የጀመሩት ክቡር አቶ ሀዲስ አለማየሁ አገር ተረካቢ ትውልድ በእውቀትና በሥነ-መግባር በማነጽ ላይ ሳሉ ፋሽሽት ኢትዮጵያን በመውረሩ የፋሽሽትን አረመኔነትና ፈሪነት፣ የኢትዮጵያን ጀግኖች አይበገሬነትና አሸናፊነት በድርሰትና በትያትር እያስተማሩ ሕዝብን ለነፃነቱ ለመታገል እንዲዘጋጅ የቀሰቀሱ አለኝታ ናቸው፡፡ አርበኞች ተዘጋጅተው ሲዘምቱም በአንድ እጃቸው ጠመንጃ በሌላው ደግሞ የሰላ ብዕር ይዘው በጌምድርና ስሜን እንደዚሁም ትግሬ ጠቅላይ ግዛት የዘመቱ አርበኛ ናቸው፡፡ የፋሽሽት ጦር ጠንጥኖ የኢትዮጵያ አርበኞች ወደ ደቡብ ምዕራብ ሲያፈገፍጉ እርሳቸው የጦር መሳርያና የሌላም ቁሳቁስ ለአርበኛው ለማግኘት በእግራቸው እየኳተኑ ሱዳን ሄደው እርዳታውን ይዘው በጋምቤላ በኩል ወደ አገራቸው ገብተው እንደገና የጥቁር አንበሳን አርበኛ ተቀላቅለው ከፋና ወለጋ የዘመቱ ድካምን የማያውቁ ብርቱ ሰው ናቸው፡፡ የፋሽሽት ጦር አሁንም እያየለ በመምጣቱ ከራስ እምሩ ጋር ተይዘው ጣሊያን የሄዱና በግዞት እያሉም የኢትዮጵያን ኃያልነት ለጣሊያኖች ያስተማሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ [፲፫] በአርበኞችና ፋኖዎች ኢትዮጵያ ነፃ ስትወጣም ወደ አገራቸው ገብተው በተለያየ ዘርፍ የመምህርነትና የምሁር ምግባራቸውን የቀጠሉ የማይታክቱ ሰራተኛ ናቸው፡፡ በወንጀለኛው ዳኛ የፍትህ መጓደል በአገር ሊያደርስ የሚችለውን ከፍተኛ አደጋ ያስተማሩ፣ በፍቅር እስከ መቃበርም ሕዝብና መንግስት መጠበቅ ወይም መተው ያለበትን ባህልና ሥርዓት ያስገነዘቡ፣ በየልምዣት የራሳቸውን ባህል፣ ሃይማኖትና ታሪክ በደንብ ሳይረዱ የምእራቡንም የምስራቁንም የባህል ግሳንግስ ያግበሰበሱ ምሁራን በአገራቸው እንደሚያፍሩና አላውቃትም እያሉ እንደሚተዋትና እንደሚያሰቃዩአት የተነበዩና ትቢቱንም በዓይናችው ያዩ ነቢይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳር ያስፈልጋታል በሚለው መጽሕፋቸው ደግሞ ኢትዮጵያ ከኋላቀርነት የሚያወጣትንና አንድነቷን ጠብቆ የሚያኖራትን የሐሳብ ሰነድ ለሕብም ለመንግስትም ፍንትው አርገው ያቀረቡ አርቆ አሳቢ አባት ናቸው፡፡ [፲፬-፲፯] ሰሚ ቢያጡም ክቡር አቶ ሀዲስ አለማየሁ የመምህርንና የምሁር ምግባራቸውን በሚገባ የተወጡና አሁንም በመወጣት ላይ ያሉ፣ ትምህርት የጠገቡ፣ አዋቂ፣ ልባም፣ አስተዋይ፣ መምህር፣ ምሁር፣ ደራሲና አርበኛ ናቸው፡፡
እነዚህን እውነተኛ መምህራንና ምሁራንን ከእኛ የእነሱን የምግባር ዋንጫ በክብር በመቀበል ፋንታ ከሰበርነው ከንቱዎች የሚለዩአቸው ዘርፎች ብዙ ናቸው፡፡ እነርሱ የሌላውን ዓለም ሃይማኖት፣ ፍልስፍና፣ ትምህርት፣ ባህልና ታሪክ እንደ ሐሽሽ ከመጋት በፊት የራሳቸውን ከጫፍ እስከ ጫፍ ለማወቅ የሚተጉና በራሳቸው የሚተማመኑ ሙሉ በኩሉሄ መምህራንና ምሁራን ናቸው፡፡ እነሱ የሚማሩትና የሚመራመሩትም የቢኤ፣ ማስተርስ፣ ኤም ዲ፣ ወይም ፔ ኤች ዲግሪ ድሪቶ ለመቀበል ሳይሆን የትምህርትና የእውቀት ጥማትን ለማርካት ነው፡፡ እነርሱ ትምህርታቸውና እውቀታቸውን የሚጠቀሙበትም ገንዘብ ለማግበስበስ፣ ስልጣን ለመቆናጠጥ፣ ጉራን ለመቸርቸርና ለሌላም ጥቅማጥቅም ሳይሆን እግዚአብሔርን፣ አገርና ሕዝብን ለማገልገል ነው፡፡ እነሱ ለመጻፍ ብዕር የሚያነሱት ብዙ መጻሕፍትን አንብበው በእውቀት ሲጠግቡና የአጻጻፍ ዘይቤንም ከተማሩ በኋላ፤ የሚናገሩትም ብዙ ካዳመጡና ካሰላሰሉ በኋላ ብቻ ነው፡፡ እነሱ እሚጽፉት ዛሬ ተነስቶ ነገ እሚጣል ፍሬ አልባ ኮተት ሳይሆን ዘመን ሲጨምር ይበልጥ እሚወደድና እሚጣፍጥ የማይጠፋ ቅርስ ነው፡፡ እነሱ እሚደመሩትም እንዳለቀ የጥርስ ሳሙና ቱቦ ሲጨምቁት ቢያመሹ እውነት ከምላሱ ጠብ ከማይለው ሰባኪ ካድሬ ጋር ሳይሆን የሰባኪውን ታሪክ ከኋላው፣ ኪሱን ከከጎኑ፣ አንጎሉን ደሞ ከፊቱ በዓይኑ ቀዳዳ አልፈው ፈትሸው ነው፡፡ ተቀበሉ ብለው ያስረከቡን ዳሩ ግን ክስክስ አድርገን የሰበርነው የእነ ክቡር አቶ ሀዲስ አለማየሁ የምሁራን ምግባር ዋንጫ ይህ ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ዋቢ
፩. ምሁር፡-አለቃ ኪዳነ ወልክ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገፅ 579
፪. ትምህርት/መምህር፡-አለቃ ኪዳነ ወልክ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገፅ 579
፫. ምግባር፡-አለቃ ኪዳነ ወልክ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገፅ 298
፬. ሥነ፡- አለቃ ኪዳነ ወልክ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገፅ 672
፭. ሥነ-ምግባር፡- አለቃ ኪዳነ ወልክ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገፅ 672
፮. አልቦ ዘመድ በብርሃኑ ድንቄ
፯. ትቤ አክሡም በአስረስ የኔሰው
፰. የካም መታሰቢያ በአስረስ የኔሰው
፱. ኮኮሐ ሃይማኖት በአድማሱ ጀምበሬ
፲. መድሎተ አሚን በአድማሱ ጀምበሬ
፲፩. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ታሪክ በአቡነ ጎርጎርዮስ
፲፪. የቤተክርስትያን ታሪክ በዓለም መድረክ በአቡነ ጎርጎርዮስ
፲፫. ትዝታ በሀዲስ አለማየሁ
፲፬. ወንጀለኛው ዳኛ በሀዲስ አለማየሁ
፲፭. ፍቅር እስከ መቃብር በሀዲስ አለማየሁ
፲፮. የልምዣት በሀዲስ አለማየሁ
፲፯. ኢትዮጵያ ምን አይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል? በሀዲስ አለማየሁ
ግንቦት ሁለት ሺህ አስራ ስምንት ዓ.ም.