መረራ ጉዲና፣ ግንቦት 2018
መግቢያ
አማረ ተግባሩ ”ከአዲስ አቤበነት እስከሉላዊነት” በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ በአምቦ አካበቢ በመኢሶን መሪዎች ላይ በተፈጸመው ታሪክ ይቅር ማይለው ግድያ ውስጥ እጄ እንደለበት እንደነሳ መጽሐፉን ያነበቡ ሰዎች ነገሩኝ። ስሜን ያነሳበትን ገፆች ኮፒ ልከውልኝም አነበበኩ። ጥረቱ ታላቅ ወንድሜን ጨምሮ በአምቦ አካበቢ በተገደሉት የመኢሶን መሪዎች ታሪክ ውስጥ አማረ ተግባሩ ራሱና ታናሽ ወንድሙ ሲራክ ተግባሩ የፈጸሙትን ክህደት ለመሸፋፈን እንደሆነ ይገባኛል። ይሁንና፣ አንድም ክህደቱ አያቃዠው ካልሆነ በስተቀርና፣ ያለዚያም ከዘረጋልኝ ወጥመድ መትረፌ ስለቆጨው ካልሆነ በስተቀር፤ በጤናው ያለ ሰው ያንን የሚያክል ውሸት ደርሶና በመጽሐፍ ጠርዞ ይበትናል ብዬ አላምንም።
ስለጉዳዩ አጣቃለይ ሁኔታ በ2005 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ በሚለው መጽሐፌ ውስጥ ከገጽ 82–98 በሰፊው ተርኬአለሁ። ዝርዝሩን ከዚያ ለማንበብ ይቻላል። አሁን ባጭሩ የተመለስኩበት ጉዳዩ በርዕሱ እንዳልኩት የሌባ ዓይነ ደረቅ፣ መልሶ ልብ ያደርቅ እንደሚባለው መሆኑን አጥቼው አይደለም። አማረ በመጽሐፍ ጠርዞ በይፋ የረጨው ውሽት አንባቢዎቹንና የፖለቲካ ታሪክ ተመራማሪዎችን ሊያሳሰት ስለሚችል ባጭሩ ልመለስበት ስለወሰንኩ ነው።
ሲራክ ተግባሩ ለእናታቸውና ለታላቅ ወንድሙ ለአማረ ተግባሩ የነገረው
አማረ በተጠቀስው መጽሐፉ ከገጽ 480–481 ውስጥ ታናሽ ወንድሙ ሲራክ ተግባሩ በወቅቱ ለእናታችው የነገረውንና ለእኔ ነገረኝ የሚለውን እንደሚከተለው አስፍሯል። የብዙዎችን ቁስል ባያክ እንደሚሻለው እየመከረኩት፤ እውነታውን በድጋሚ አጋራለሁ።
ሲራክ ለእናታቸው፡ “ወንድሜን አውቀዋለሁ። እጅህን ስጥ ብለው እሺ ብሎ እጁን አይሰጥም። በያዘው መሣሪያ እራሱን ይገድላል። ወይም የደርግ ወታደሮች ይገድሉል። ወንድምህ ያለበትን እናውቃለን። እዝያው ድረስ ሄደን በአሰሳ ከምንገድለው እዚህ አምጥተህ አስረክበን ሲሉኝ፤ ከሚገድሉት ብዬ ሳልነግረው አምጥቼ አስረከብኩት።”
ሲራክ ለአማረ “(ታናሽ ወንድሜን)ሲራክ ተግባሩን በጅባትና ሜጫ ስለደረሰው እልቂት ስጠይቀው፣ እሱን ከ2ተኛ ፖሊስ ጣቢያ መረራ ጉዲናን ደግሞ ከ6ኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዷቸውና […] አምቦ ሲደርሱም አምሳ አለቃ መኅተበ ተደባልቋቸው ወደ ጥቁር እንጭኒ ጉዞ እንደቀጠሉና […] እዝያም ሲደርሱ እነዶ/ር ተረፈንና ቡድኑን ያስቀመጡበትን የዘመዶቻቸውን ቤት መርተው ያሳዩት እነርሱ እንደነበሩና […] እሱም (ወንድሜም)፣ መረራም፣ አምሳ አለቃውም ግድያውን ከፈጸመው ቡድን ጋር እንደተመልሱና እሱና መረራ እንደታሰሩ ነግሮኛል።”
ሲራክ ለእናታቸው የነገረውን የሚመለከተውን፣ ለአንባቢዎቹ አስተያየትና አመለካከት ትቼ አልፈዋለሁ። አማረ ሲራክ ነገረኝ እያለ የተረከውን በሚመለከተው ግን፣ እኔ ከ6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተውስጄና እስከ ጥቁር እንጭኒ ድረስ ተጉዤ በእነዶ/ር ተረፈና ቡድኑ ላይ አልመራሁም። ከዝያም ግድያውን ከፈጸመው ቡድን ጋር ወደአዲስ አበባ ተመልሼ አልታሰርኩም። እኔ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ የደረስኩት ግድያው ከተፈጸመ ከ25 ቀናት ቦኋላ፣ ያውም ምርመራ የሚባለውን ሁሉ በግዜው ወደ ደርግ ጽ/ቤትነት በተለወጠው የምንልክ ቤተመንግስት ውስጥ በሚገኘው የደርግ ዋና ምርመራ ክፍል ከጨረስኩ በኋላ እንደነበር የሚመሰክሩ በሕይወት ያሉና በግዜው የነበሩ የመንግስት በለሥልጣናት ጭምር በሺዎች ባይሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ አሉ። ዶር ሙሉጌታ ደበበ የሚበል በግዜው የካድሬች ሀላፊ የነበረ አሁንም በከተማው አለ።
እውነታው
ከነሐሴ 1969 እስክ ጥር 1970 ዓ.ም ድረስ ፀረ-ደርግ ትግላችንን ለማስተባበር በአምቦ አካባቢ ስርቻለሁ። በነዶ/ር ከበደ መንገሻ መገደልና በኃይሌ ፊዳ መያዝ በመደናገጣችን፣ አምቦ ኣካባቢ የምንችለውን ያክል ጥንቃቄ ማድረግ ጀመርን። ወደ አምቦ ቅርብ ከነበረው ጉደር ከተማ አካባቢ የነበሩትን የመኢሶን ጓዶች ራቅ ወዳለው ጥቁር እንጭኒ ወረዳ መውሰድ ስለነበረብን፣ ቦታ ተዘገጅቶላቸው ለማንቀስቀስ ስንሞክር፣ አማረ ተግባሩ “እግሬን ያመኛል፣ ህክምና ማግኘት ከምችልበት አካባቢ ርቄ መሄድ የለብኝም” እያለ እንግዳ ጠባይ ማሳየት ጀመረ። እንግዳ ጠባዩን የተጠራጠረው ኢዮብ ታደሰ ‘ይህ ሰው ተንኮል ማሰብ የጀመረ ይመስለኛል። እንልቀቀው ይላል’። የቡድኑ መሪ ዶ/ር ተረፈ ወ/ፃዲቅ ሃሳቡን ሲቀበል፤ የሽዋ ክፍለ ሀገር የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ የነበረው ከበደ ድሪባ “አብረን ወጥተን እንዴት እንበላለን” ብሎ አጥብቆ ተቃወመ። ቡድኑ በመጨረሻ በደረሰበት ስምምነት መሰረት፣ እነዶ/ርተረፈን ራቅ ወዳለው የጥቁር እንጭኒ ወረዳ (ለክፉም ለደጉም ለጅባት ተራራ ቅርብ የሆነ ቦታ) እንዲሄዱና፣ አማረን ደግሞ ወለንኮሚ ከተማ በምትኖርና አባላችን በነበረች የመንግስት ሰራተኛ ጋ እንዲቀመጥ አደረግን፡፡
አንድ ቀን “እኔን ብቻየን ሰው በማላውቅበት ሀገር ጥለውኝ ሄዱ። እደጋ ውስጥ ነኝ” የሚል ጭንቀት ውስጥ ያለ ሰው የሚመስል መልእክት በግንኙነት መስመራችን በኩል ደረሰኝ፡፡ ደንግጬ ወዲያውኑ ጥንቃቄ በተሞላበት አዲስ ቦታ እንዲዘጋጅለት አድርጌ መኪና ልኬለት እንዲንቀሳቀስ ቢነገረው፣ ሃሳቡን ለውጦና ተመችቶት እንደሚኖር ሊወስዱት ለሄዱት ሰዎች ገልጾ ለመሄድ ፈቃደኛ ያለመሆኑን ይነግራቸዋል። ትንሽ ግራ ቢገባኝም እንደክፋት ስላላየሁት፣ እሱ ከተመቸው ጥሩ ነው ብዬ ዝም አልኩ፡፡
ጥቂት ቀኖች ቆይቶ “መረራን ለማነጋገር እፈልጋለሁ” የሚል መልእክት ላከብኝ። እኔም ሀገር ሰላም ነው ብዬ እርሱ ወዳለበት ወለንኮሚ ከተማ ለመሄድ አቅራቢያው ወዳለው ግኒጭ ከተማ ገባሁ፡፡ የግንኙነት መስመራችንን ይዤ ወደ እሱ ለመሄድ የሚወሱዱኝን ሰዎች ስጠብቅ፣ የአምቦው ዋናው ቡድንን እኔ ሳልጠራቸው በሙሉ ተሰብስበው ጊንጭ ከተማ ላይ አገኘኋቸው። “ለምን መጣችሁ? ማን ጠራችሁ?’ ብዬ ስጠይቅ፣ የሁሉም መልስ አማረ ሆነ፡፡ በእውነቱ ከእኔ የተሻለ አማረን የሚያውቀው ኢዮብ ታደሰ የመጠርጠሩ መረጃ ቢኖረኝም፤ በድርጅታዊ ዲሲፒሊን ምክንያት በተለይም እኔ አስተባባሪው ሳላውቅ በአካባቢው ያሉ የግንኙነት መስመሮቻችንን የሚያንቀሳቅሱ በሙሉ በአንድ ላይ መሰብሰባቸውን ስላልወደድኩት፣ ሁሉም እንዲበተኑ አድርጌ ለምን እንደፈለገኝ በማስታወሻ እንዲልክልኝ በግንኙነት መስመራችን በኩል ልኬበት ወደመጣሁበት ቦታ ተመለስኩ፤፤ የላኩትን ልጅ ከሶስት ቀናት በኋላ ተመለስ ስላለው፣ ከሶስት ቀናት በኋላ መልሼ ላኩት፡፡ የሚያገናኘንን ልጅ ሌላ ሴራ ጠንስሶ ጠበቀው፡፡ አቅጣጫ ለማሳሳትም ጭምር ይሁን፣ በእጅ ጽሁፍ 20 ገጾች የሆነ በታይፕ ተመቶ እንዲበተን መልእክት የያዘ ጽሁፍ ላከልኝ፡፡
ጽሑፉን ሳይ፣ የዛን ቀን እርሱን ሳላገኝ በመመለሴ በጣም ተናደድኩ። አዘንኩም፡፡ የአማረ ጽሁፍ በአጭሩ የሚለው፡ አሥር ሺ ኪሎ ሜትሮችን ስለአካለለው የቻይናው ረጅም ጉዞ (Long March): ቬትናሞች እንዴት ኃያሉን የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም በቁርጠኝነት ተቋቁመው በመጨረሻ ላይ ማንበርከካቸውን የሚገልጽና እኛም እንዲህ አይነቱ ፈታኝ ችግሮች ሊገጥሙን እንደሚችሉ ካተተ በኋላ፣ ሐቀኛና ጠንካራ ጓዶች ለሆዳቸው ሊያድሩ ከሚችሉ ልፍስፍስ ጓዶች የሚለዩበት ጊዜ መድረሱን ይጠቁማል፡፡ ለጥቅም ብለው ጓዶቻቸውን ለጥይት አሳልፈው የሚሰጡ ከሀዲዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ያብራራል፡፡ ከዛም አልፎ በሶቪየት ሶሻል ኢምፔሪያሊስቶች የሚመራው ቀልባሽ ሃይል የሆነው ወታደራዊ ጁንታ እውነተኛ የሶሻሊስት ጽሑፎችን ሊያጠፋ ስለሚችልና ለወደፊቱም ቤተ መጽሐፍቶቻችን የኢትዮጵያ ጫካዎች ስለሚሆኑ፤ ወደ ገጠር እንድናሽሽ የሚመክርም ጽሁፍ ነበር፡፡
ይህን ለረጅም ዓመታት ትግል የተዘጋጀ የሚመስል ጽሑፍ በመዘጋጀቱ ደስ ብሎኝ በታይፕ ተጽፎ በፍጥነት እንዲሰራጭ ወደ ከተማ ላኩ። እዚህ ላይ የአማረን የድርሰት ችሎታን ማድነቄን ሳልገልጽ ባልፍ ሐጢእት ይሆንብኛል፡፡ አምቦ ከተማ ጽሑፉን አድርሶ የተመለሰው ልጅ (ሶሪ ደንደና የሚበል አሁንም በሕዪወት አለ) ግን አስደንጋጭ ዜና ይዞልኝ መጣ፡፡ ይኸውም አንድ አሳሽ ቡድን ከአዲስ አበባ መጥቶ በአካባቢው ያሉ የመኢሶን ካድሬዎች የመኢሶን መሪዎችን ከደበቁዋቸው ሕዝብ ጋር ሊመታ እንደሚችል ትልቅ ስጋት ውስጥ እንደወደቁ እንደነገሩትም አወራልኝ፡፡
ወታደራዊ አሰሳ ይደረጋል የሚባለው የሁልጊዜም ስጋታችን ነበር፡፡ የአማረን ወረቀት ከተማ አድርሶ የተመለሰው ሶሪ ደንደና ያመጣው የአሰሳ ወሬ ስጋት ውስጥ ስለጣለኝ በዛው ሌሊት አምቦ ከተማ ውስጥ ገብቼ ማጣራት ውስጥ ገባሁ፡፡ ክሁሉም መስመሮች የመጡትን መረጃዎች ለማየት ስጀምር፣ እጅግ በጣም ግራ ያጋባኝ መረጃ ከሦስት ቀን በፊት ስለታሪካዊ የቻይና ረዥም ጉዞ (Long March) ሁሉ ሲተርክ የነበረው ሰው “ሁላችንም ወደ እዲስ አበባ ከተማ እንድንመለስ ተተኪው የመኢሶን አመራር አዞናል የሚልን ደብዳቤ” ክህደቱን እንዲያስፈጽም ግዳጅ በተሰጠው ታናሽ ወንድሙ በኩል ለእኔ ምንም ትንፍሽ ሳይል ለነዶ/ር ተረፈ ልኮ መሰወሩ ነበር።
እነዶ/ር ተረፈ መስመሩን ሳይጠብቅ በወንድሙ በኩል በአማረ ተፈርሞ የመጣላቸው ደብዳቤ እንግዳ እንደሆነባቸውና ይህንኑን በፍጥነት አጣርቼ አስፈላጊውን እርምጃ እንድወስድ የሚያሳስብ መልዕክት ላኩብኝ፡፡ እኔም በአንድ በኩል፣ አማረ የት እንደደረሰና በመኢሶን እመራር አምቦ ላለው ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ የተወሰነ ነገር ካለ እንዲያጣራ ሶሪ ደንደናን ወደ አዲስ አበባ ሰደድኩኝ። በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሜን እነዶ/ር ተረፈ ካሉበት ወደ መኪና መንገድ ወደሚቀርበው ዘመዶቻችን ቤት እንዲያሳርፋቸው ላኩት፡፡
የእኔ ሀሳብ አማረ የጻፈው እውነት ከሆነ፣ በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ነበር። ውሸት ከሆነና ደርግ አሰሳውን ባስቸኳይ ካደረገ ጥቁር እንጭኒ ስለሚሆን፣ እኛ ቀድመን ወደ ግንደበረት እንዲሻገሩ ለማድረግ ነበር፡ ወንድሜ የታዘዘውን ፈጽሞ ሪፖርት አደረገልኝ። አማረ የት እንደገባ የማጣራቱ ተግባር በፈለግነው ፍጥነት አልሄደልንም፡፡ ስለ ክህደቱ ፍንጭ ያገኙ ካድሬዎች በፍርሃት ምንም ፍንጭ አልሰጥም አሉኝ፡፡ በተለይ ኩማለ ተሬሣ የሚባል የአካባቢው ልጅ የአማረንና የወንድሙን የክህደት እንቅስቃሴ የተሻለ እያወቀ የፍርሃት ይሁን ሊተባበራቸው ስለፈለገ ትንፍሽ አልል አለኝ፡፡ ከሱ ፍንጭ ባገኝ ኖሮ ቢያንስ ለጊዜው ሕይወታቸው ይድን ነበር።
ወደ አዲስ አበባ የተላከው ልጅ አማረ እንደከዳና ለማስመሰል ደርግ ጽ ቤት እንደ እስረኛ እንደወሰዱት፣ የመኢሶን አመራር ምንም አይነት ውሳኔ እንዳልወሰነ አረጋግጦ ሲመለስና የእነዶ/ር ተረፈና የወንድሜ መገደል መርዶ አንድ ላይ ደረሰኝ፡፡ የተሻለ የመጓጓዝ ፍጥነት ስለነበራቸውና እኛ ጨርሶ ያልጠበቅነውን ስልት ስለቀየሱ በሰዓታት ቢሆንም ቀደሙን፡፡
የአማረ ወንድም የሁሉም ካድሬዎች እስቸኳይ ስብሰባ እዲስ አበባ ላይ ተጠርተዋል እንሂድ ብሎ ያገኘውን ካድሬ ይዞ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ይጀምራል፡፡ ከካድሬዎቹ ውስጥ ዲማ ጉዲና የሚባለው ወንድሜና ኩማላ ከሮርሣ የሚባል ረዳቱ ነበሩበት፡፡ መናገሻ ሲደርሱ ወንድሜንና ረዳቱን አስይዞ እነዶ/ር ተረፈ ያሉበትን እንዲጠቁሙ ያስደበድባል፡ እንደሰማሁት፣ ትንሽ ድብደባውን ለመቋቋም የሞከረውን ወንድሜን በሽጉጥ ይመቱትና ለረዳቱ “እርሱን ገድለነዋል። አንተም እንደርሱ ትገደላለህ” ብለው በማስፈራራት እንዲመራቸው ያደርጋሉ፡፡
የዛኑ ሌሊት ራሱን ስቶ የነበረውን ወንድሜንና ረዳቱን ይዘው ጉዴላ የምትባለውን የቶኬ ኣካባቢ ከተማ የዘመቻ ማዕከል አድርገው ተንቀሳቀሱ፡፡ ካሳየ አራጋው በተባለው የደርግ አባል የተመራው ዘመቻ፣ አንድ የኮማንዶ ቡድንን ይዞ እነዶ/ር ተረፈ ወዳረፉበት የእጎታችን ቤት ይለካል፡፡ እነዶ/ር ተረፈ ባልጠበቁት ሰዓት መከበባቸውንና መንገራገር ቢመክሩም ከኮማንዶ ጋር ለመዋጋት የሚያስችል አቅም ስላልነበራቸው እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡ ከተያዙበት ቦታ አንድ ኪሎ ሜትር እንደሄዱ የቱኩስ አሩምታ ተከፍቶባቸው ተጨፈጨፉ፡፡ መንገድ የመራቸው የወንድሜ ረዳት መገደላቸውን አይቶ በመጮሁ እሱንም እዛው ጨመሩት፡፡ በዚህ ፋሽሽታዊ ጭካኔ በዕለቱ የተጨፈጨፉት ዶ/ር ተረፈ፣ የዶ/ር ተረፈ ባለቤት፣ ከበደ ዲሪባ፣ ኢዮብ ታደሰ፣ ለማ ፊዳ፣ ሽመልስ ኦላና፣ መርዕድ ከበደ፣ አሰፋ ነመራ፣ ዲማ ጉዲና፣ ኩማላ ከሮርሣ ነበሩ። አጥናፍ ጥይት ብቻ ነው የሚለኝ ብላ ወደ ከተማ ልንመልሳት ያደረግነውን ጥረት እምቢ ያለችንና በመጨረሻም ጥይት ሊልያት ያልቻለ ታጋይ ሴት ነበረች፤፤
ወንድሜን ሊያመልጥ ሞክሯል ብለው የገደሉት አምቦ ከተማ ውስጥ ነበር። በጊዜው እኔ አምቦ ከተማ ውስጥ ብሆንም በቀላሉ ሊያገኙኝ ባለመቻላቸው ጭምር ከእልቂቱ ተረፍኩ። እነ እማረ ለዓላማ ሳይሆን ለትርፍ ብሎ አንድ ጉድጓድ ውስጥ አብረን እንቀብራለን ሲሉዋቸው የነበሩትን ጓደኞቻቸውን ለጥይት አሳልፈው የሰጡበትን ክህደት ሳስታውስ እስከ ዛሬ ይዘገንነኛል። ለሆዳቸው ሲሉ ከሚያስገድሉት ይልቅ፣ ባልወዳቸውም ለዓላማቸው ሲሉ የሚገደሉትን አክብራለሁ።
የአምቦ ቡድን ሙሉ በሙሉ ከተመታ በኋላ የቀረኝ፣ ሕይወቴን ማትረፍና ከቻልኩም አቅጣጭ ለውጬ ትግሉን ለመቀጠል ብቻ ነበር። ሃሳቤ ቤተሰቦቹ ጊንጭ አካባቢ ስለሆኑ ወደ አዲስ አበባ ቀረብ ብዬ አዲስ አበባ ውስጥ ከቀሩን የመኢሶንም ሆነ የኦብዲን ጓዶች ጋር የግንኙነት መስመር ለመፍጠር እንድችል እንዲረደኝ የማውቀውን የግኒጭ ልጅ ሲመሽ መጥቶ እንወድሰደኝ ነገርኩት፡ ለዚህም፣ በተለይ የተረፉ የኦብዲን ጓዶችን በቅርበት ስለማውቅ፣ የግንኙነት መሥመሮችን ያለችግር መቀጠል እችላለሁ ብዬ ገምቼ ነበር፡፡ ያም ሆነ፣ ይህ ቀኑን እስክመሽልኝ ድረስ የቆዬሁበት ቦታ በአካባቢው ከብቶች የሚሠማሩበት ቦታ ስለሆነ፣ ከብቶቻቸውን ለመቆጣጠር የሚመጡ ሰዎች ሌባ መስያቸው ፖሊስ እንዳይጠሩብኝ መሥጋቴም አልቀረም፡፡
ወደ ግኒጭ እንዲወሰደኝ የነገርኩት ልጅ በቀጠሯችን ሰዓት ስላልመጠልኝ በዛ እጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥጋ ዘመዶቼ ከመሄድ ውጭ የተሻለ ምርጫ አላገኘሁም:: የምርጫዬ ዋናው ምክንያት፡ ደርግ በእኛ እካባቢ ያለውን በሙሉ ስለእጠናቀቀ ወደዛ የሚያተኩርበት ምንም ምክንያት አይኖረውም የሚል ግምት ስለነበረኝ ነበር፡፡ መንገዱን በዕድገት በሕብረት ዘመቻ ጊዜ ከሁለቴና ሦስቴ በላይ ስለሄድኩበት፣ እጠፋለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። በጣም ርቄ ከሄድኩ በኃላ ከመንገድ መጥፋቴ ታወቀኝ፡፡ ወደ መንገዴ ተመልሼ ትንሽ እንደሄድኩ አንድ ዘመቻ ላይ ሆኜ የማውቀው የገበሬ ማኀበር ሊቀመንበር ፈረሱ ላይ ሆኖ መጣብኝ፡፡ እንዲረዳኝ ልጠይቀው አልኩና ፈራሁት፡፡ እሱም እኔን ማናገር ፈርቶ ይመስለኛል፣ ተገላምጦ እያየኝ ሄደ፡፡ ኋላ ሳየው ይህ የገበሬ ማኀበር ሊቀመንበር ዘመዶቼን ጭምር ስለሚያውቅ እርዳታ መጠየቁ ይሻለኝ ነበር፡፡ ጥሩ ዕድል አመለጠኝ፡፡
ከገበሬ ማኀበሩ ሊቀመንበር አልፌ ትንሽ እንደሄድኩ፣ በብዛት ሆነው እህል የሚወቁ ገበሬዎች ቁም አሉኝ። እንዳይጠጉኝ ከነገርኳቸው በኋላ፣ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከሦስት ሞቶች መካከል የትኛውን መምረጥ እንዳለብኝ አሰብኩኝ፡፡ አንደኛው ሞት እጄን ሰጥቼ ከጥቂት ቀኖች በፊት እንደሞቱት እነዶ/ር ተረፈ መሆን፣ ሁለተኛው ሞት በነፍሰ ገዳዬች እጅ ተደብድቤ ከመሞት እራሴን መግደል፣ ሦስተኛው ሞት ምንም ሳያውቁ ሊይዙኝ ከሚፈልጉ ገበሬዎች ጋር ተታኩሶ መሞት ነበሩ፡፡ ትንሽ የመሮጥ አቅም ቢኖረኝ ኖሮ ወደ መታኮሱ እሄድ ነበር፡፡ ላላመልጥ ዳቦ በልተው ያልጠገቡትን ገበሬዎች መጨረስ ትርጉም የለሽ እርምጃ ሆኖ አገኘሁት፡፡
የተያዝኩበት የአካባቢው ገበሬዎች እንዳንዶቹ እኔንም ሆነ መኢሶንንም በስም ስለሚያውቁ ለመንግሥት እንስጥና አንስጥ በሚል ጥያቄ ለሁለት ቀናት ተጨቃጨቁ፡፡ ከሁለት ቀናት ጭቅጭቅ በኋላ፣ አሳልፈን እንስጥ የሚለው ክፍል አይሎ አሳልፈው ሊሰጡኝ ተሰማሙ። ጉደር ከተማ ለሚገኘው የአምቦ ወረዳ አስተዳደር ያለደረሰኝ አስረከቡኝ፡፡ የአምቦ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ፣ ከጉደር ከተማ የተሻለ ጥበቃ ወዳለበት የአምቦ ከተማ ወዲያውኑ ወሰደኝ።ክዛም በሶስተኛው ቀን ወደ አዲስ አበባ ተውስድኩ፡፡ በአጭሩ እነዶ/ር ተረፈ ከተገደሉ ከ9 ቀናት በኃላና በምንልክ ቤተመንግስት ለ15 ቀናት ያህል ከተመረመርኩ በኃላ ወደ 6ተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስጄ የ7 ዓመት የእስር ዘመኔን ጀመርኩ፡፡
እውነተኛው ታሪክ ባጭሩ ይኼው ነው። ማመሳከሩ የታሪክ ባለሙያዎች ድርሻ ነው።