– የእስክንድ ነጋ የፖለቲካ አካሄድ ችግር ሊኖርበት ይችላል። ይሁንና የእሱን ክፍተቶች ለመሙላትና ስህተቶቹን አርሞ ለመሄድ ተነሳሽነትና ችሎታው ያለው ማነው? እስካሁን ማንንም አላየንም። መሬት ላይ ወርዶ መሥራት፣ ከዳር ቁሞ/ተቀምጦ እንደመተቸት ቀላል አይደለም። እስቲ የተሻለ ብቃት አለን የምትሉ ግቡና ሞክሩት!?
– እስክንድር “እስር ቤቱን ቋሚ መኖሪያው አደረገው” እያሉ የሚሳለቁትማ ሞራላቸውን አንጠፍጥፈው የሸኑ ናቸው። እውነት ነው፤ እስክንድር የዕድሜው እኩሌታ በእስርና በእንግልት የተሞላ ነው። በተደጋጋሚና ለብዙ ዓመታት መታሰር ይቅርና፣ የመታሰር አደጋ ባለበት ቦታ ዝር የሚለው ማነው? ይህን አደጋ የሚደፍረውና በተደጋጋሚ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ያለው እስክንድር ነው። ስለእስር ቤት ህይወት አስከፊነት ከእስክንድር በላይ የሚያውቅና ሊናገር የሚችል ሰው የለም። እስክንድር በእስር የሚማቅቀውኮ የሚወዳትን ባለቤቱንና የአብራኩ ክፋይ የሆነውን ልጁን ባህር ማዶ ትቶ ነው። እስቲ ይህንንም በደንብ አስቡት!
– እስክንድር ነጋ ድጋሜ ለመታሰር መንግሥትን ደጅ እየጠና እንደሆነ የሚተቹ ሰዎች፣ ያለንበትን ሁኔታ የዘነጉ፣ ወይም ሆን ብለው ያንቀላፉ መሆን አለባቸው። ያለንበት ሁኔታ፣ ፖለቲካዊ ሴራ፣ አስተዳደራዊ በደሎች፣ ቢሮክራሲያዊ አሻጥሮች፣ አድሎና መገፋት የበዛበት፣ በአጠቃላይም በፈርጀ-ብዙ ችግሮች የተተበተብንበት ሁኔታ ነው ያለው። በዚህ ሁኔታ፣ ደፍሮ መውጣትና የፖለቲካ ሥርዓቱን ፊት-ለፊት መጋፈጥ የሚችል ሰው የተገኘው እስክንድር ነጋ ነው። ተችዎቹ እንደሚሉት “እሰሩኝ” ብሎ ደጅ ለመጥናትምኮ ጀግንነት ይጠይቃል። መታሰርን በመፍራት፣ ስንቱ ከሰውነት ደረጃ ወርዶና ተዋርዶ እንደሚኖርኮ ይታወቃል።
– መቼም፣ የእስክንድር ነጋ ትግል ገፊ ምክንያት የለውም ብሎ ሊሞግት የሚችል ሰው አይኖርም። በገፊ ምክንያቱ ላይ መግባባት ካለ፣ እነእስክንድርን ቀረብ ብሎ ማገዝ፣ ወይም የአካሄድ ክፍተቱን ለመሙላት የሚያስችል አማራጭ መንገድ ፈጥሮ ማሳዬት ነው። እስክንድር ነጋና ባልደረቦቹ እየከፈሉት ባለው ከፍተኛ ዋጋ ለመሳለቅ የሞራል ብቃት ያለው የለም።
Mohamed Ali Mohamed