
ገንዳውኃ፡ ጥቅምት 15/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በጠገዴ አርማጭሆና አካባቢው በጎ አድራጎት ማኅበር አዘጋጅነት በምዕራብ ጎንደር ዞን የአማራና ቅማንት ሕዝቦች የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት በጋራ ለመጠበቅና መልካም ግንኙነታቸውን በዘላቂነት ለማስቀጠል የሕዝብ ለሕዝብ ምክክር አካሂደዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በግል ጥቅመኞች የሰው እገታ፣ የሀብት ዘረፋ፣ የሰው ግድያ፣ የመንገድ መዘጋት፣ የጥይት ተኩስ እና መሰል የኅብረተሰቡን ሰላምና እረፍት የሚነሱ ወንጀሎች እየተበራከቱ መጥተዋል። በዚህም የኅብረተሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲላላ ከማድረግ ባሻገር ሥነ ልቦናዊ ጫና እያደረሰም ነው፡፡
የአማራና የቅማንት ወንድም ሕዝቦች ባካሄዱት ምክክር በአካባቢው እየተፈጸሙ ያሉ ኢሰባዊና አስነዋሪ ድርጊቶች ምንጫቸውን በዘላቂነት ለማድረቅ ሁለቱ ወንድም ሕዝቦች በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡ የአማራና የቅማንት ወንድም ሕዝቦች ወራሪውን የትህነግ ቡድን በመደምሰስ፣ ጽንፈኛውን ኮሚቴና ግብረ አበሮቹን በመዋጋት፣ ሌባና አጋቾችን በማውገዝ የአካባቢያቸውን ሰላም እንደሚያስጠብቁ እና ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ነው ያስረዱት።
በመድረኩ በአካባቢው በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ቁመዋል ያሉት የአካባቢው ባለሀብት አቶ ተመስገን ሰጣርገው ችግሩን ለመፍታት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ከጠገዴ እና ከአርማጭሆ ኅብረተሰብ ተሞክሮ መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
የሕዝብ ለሕዝብ ምክክሩ ዋና ዓላማ ችግር ፈጣሪውን በመለየት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ በማስቀመጥ የአካባቢውን ሰላም እና ደኅንነት በዘለቄታ ማስጠበቅ ነው ያሉት ደግሞ የጠገዴ አርማጭሆና አካባቢው የበጎ አድራጎት ማኅበር አስተባባሪ አቶ አሰማረው መኮንን ናቸው።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የጠገዴ አርማጭሆና አካባቢው የበጎ አድራጎት ማኅበር አባል ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጽሐዬ “አብሮነት ለሰላምና ለዘላቂ እድገት” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ስለተፈጠረው አሁናዊ ችግር መነሻው ምዕራባዊያን እንደሆኑ አስገንዝበዋል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰሩ የምዕራባዊያንን አጀንዳ ተሸክመው ለሚመጡ ባንዳዎች ፈጣንና ተገቢውን ግብረ መልስ መስጠት ጊዜው የሚጠይቅ ሆኗል ብለዋል። በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት ዓላማው የትኛውንም ብሔር ነጻ ለማውጣት ሳይሆን ኢትዮጵያዊያንን እርስ በእርስ በማባላትና በማናከስ ለምዕራባዊያን ዕድል መፍጠር እንደሆነ አብራርተዋል።
በምክክሩ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች፣ ከሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ከላይ አርማጭሆ ወረዳ የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የጦር ጀነራሎች፣ መኮነኖች እና ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡–ቴዎድሮስ ደሴ–ከገንዳውኃ
አሚኮ