
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፀረ ሽብር እና ሕገ ምንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት ዐቃቤ ሕግ በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች ላይ ሁለት ምስክሮችን ለነገ ጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም አቅርቦ እንዲያስመሰክር ትዕዛዝ ሰጠ ።
ዐቃቤ ሕግ የምስክሮች ስም ዝርዝር በደህንነት ስጋት በመገናኛ ብዙኃን እንዳይጠቀስ በሚል ያቀረበውን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።
በዛሬው ችሎት ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የዘጠኝ ምስክሮችን ስም ዝርዝር በወረቀት አስፍሮ ለዳኞች፣ ለጠበቆች እና ለተከሳሾች አቅርቧል።
የምስክሮች ስም ዝርዝር በመገናኛ ብዙኃን ይፋ መደረግ አለበት ይፋ መደረግ የለበትም በሚለው ጭብጥ ላይ ሰፊ ክርክር ተደርጓል።
ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ እንዲመሰክሩ ከያዛቸው 21 ምስክሮች መካከል ከዘጠኙ ውጪ ያሉት በግልፅ ችሎት ቀርበው ለመመስከር ፈቃደኛነታቸውን ለማወቅ ገና በማግባባት ሂደት ላይ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክሯል።
ጠበቆች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 124 እና 136 መሠረት ምስክሮቹ ተጠቃለው መቅረብ እና ቃለ መሀላ ፈፅመው ምስክርነታቸውን መስጠት ሲገባቸው ” እንዲቀርቡ እያግባባሁ ነው” በሚል በዐቃቤ ሕግ የቀረበውን ክርክር በመቃወም ተከራክረዋል።
ተከሳሾች ለምስክርነት እንቀርባለን ያሉት ሰዎች ሀሰተኛ ናቸው፣ ክርክሩ 15 ወራትን የፈጀው በዚህ ምክንያት ነውና ዐቃቤ ሕግ ፍትሕን የማስፈን ኃላፊነቱን ለመወጣት ቀናነት ካለው የተራዘመ ክርክር ሊኖር እንደማይገባ ጠቅሰው ተከራክረዋል።
ዐቃቤ ሕግ የምስክሮች ስም ዝርዝር በመገናኛ ብዙኃንና በማሕበራዊ መገናኛዎች ይፋ መውጣት የለበትም ብሎ ሲከራከር ምክንያት ብሎ ያስቀመጠው “ምስክሮችን በምክንያት ከማያስብ ደጋፊ ለመጠበቅ ነው፣ ምስክሮች ላይ ጉዳት ይደርሳል ከሚል መነሻ ነው” ብሏል።
ተከሳሾች በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ “ጉዳዩን ከግልፀኝነት እና ተጠያቂነት አንፃር ” እንዲመለከተው ጠይቀዋል።
“እኛ ፍርድ ሳይሰጥ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት ሞክረዋል ተብሎ በመገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ ተነግሮብን እያለ ፣ የምስክሮች ስም ዝርዝር ለሕዝብ ይፋ የማይደረግበት ምክንያት ምንድን ነው“? በማለት ችሎቱን ጠይቀዋል።
” የተከሰስንበት ጉዳይ እስከ ሞት እና እድሜ ልክ የሚያስፈርድ ሆኖ እያለ ዐቃቤ ሕግ የምስክሮች ስም ዝርዝር በመገናኛ ብዙኃን ይፋ መውጣት የለበትም ማለቱም ኢ – ፍትሓዊ የሆነ ሀሳብ ነው” በማለት ተከራክረዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ከዚህ በፊት አንድ ምስክር ድብደባ እንደተፈፀመበት በመግለፅ በዚህም ላይ በፎቶ የተደገፈ ማስረጃ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ይህም ምስክሮች ወደ ችሎት እንዳይቀርቡ እና እንዳይመሰክሩ ከማድረጉ ባለፈ አሉታዊ ተፅእኖ ስለሚያሳድር ስም ዝርዝራቸው በይፋ የመገለፁ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ በማንሳት ክርክር አድርጓል።
ተከሳሾችም ተደበደበ እና በፎቶ የተደገፈ የተባለው ምስክር ማስረጃ ለፍርድ ቤቱም ለችሎቱም እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ በዚህ ጉዳይ ውሳኔ ለመሥጠት በዚሁ ዕለት ለ 8:30 ቀጥሮ ሰጥቶ ለምሳ ወጥቷል።
ከምሳ በኋላ በቀጠለው ችሎት የምስክሮች ስም ዝርዝር በመገናኛ ብዙኃን ይገለፅ በሚለው ጭብጥ ላይ ምስክሮች ስም ዝርዝራቸው በመገናኛ ብዙኃንም ይሁን በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች እንዲገለፅ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል።
በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ ነገ ጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጥዋት በሚያስችለው ችሎት ሁለት ምስክሮችን ችሎት አቅርቦ በግልፅ እንዲያስመሰክር ብይን ሰጥቷል።
የሌሎችን ቀሪ ምስክሮች ስም ዝርዝርንም ለፍርድ ቤቱ፣ ለጠበቆች እና ለተከሳሾች እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
DW