- የኢትዮጵያ እና ቱርክ ግንኙነት የተጀመረው እአአ ከ1896 ጀምሮ በንጉሥ ዳግማዊ ሚኒሊክ እና በቱርኩ ሱልጣን አብዱልሃሚድ ሁለተኛ ዘመን ነበር፤
ቱርክ ከሰሀራ በታች ለመጀመሪያ ጊዜ ኤምባሲ የከፈተችው በአዲስ አበባ እአአ በ1926 ሲሆን፤
ከዚህ ኤምባሲዋ በፊትም እአአ በ1912 በሀረር የመጀመሪያውን ቆንስላ ከፍታለች፤
ኢትዮጵያም እአአ በ1933 በቱርክ አንካራ ኤምባሲዋን ከፍታለች፤ ሆኖም በደርግ ዘመነ መንግስት እአአ በ1984 ዘግታ ዳግም እአአ በ2006 ከፍታ ግንኝነቱን አስቀጥላለች፤
የሁለቱ አገራት መሪዎች ጉብኝት፣ የቱርክ አየር መንገድ የቀጥታ በረራ መጀመር፣ የቱርኩ “ቲካ” በአዲስ አበባ ቢሮ መክፈት፣ ልዩ ልዩ የልማት ድጋፎችና መሰል ትብብሮች የአገራቱን ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ አድርሰውታል፤
እአአ በ2003 በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረገ የቱርክ ኩባንያ አንድ ብቻ የነበረ ሲሆን፤ ሰራተኞቹም ከአምስት አይዘሉም ነበር፤
በአሁኑ ወቅት ግን የቱርክ ባለሀብቶች በከፍተኛ መጠን ወደ ኢትዮጵያ በመግባታቸው 200 ኩባንያዎች ከ20 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንን ቀጥረው በማሰራት ላይ ናቸው፤
እነዚህ ኩባንያዎች ያስመዘገቡት የኢንቨስትመንት መጠንም ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደሚልቅ መረጃዎች ያሳያሉ፤
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠንም እአአ በ2020 ላይ 272 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፤
በቅርቡ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጠይብ ኤርዶጋን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ ውይይት ማድረጋቸውንና አገራቸው ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ያላትን ድጋፍ ገልጸዋል፤
ቱርክ ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ማቅረብ እንደምትቀጥል ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አረጋግጠውላቸዋል፤
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ግብዣ ዛሬ ለሥራ ጉብኝት ቱርክ መግባታቸውም ይታወቃል፤
ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማግኘታቸወም ይታወሳል፤
(ኢ ፕ ድ)