‹‹የዶሮ ሥጋ፣ እንደ ብዙዎቹ የፕሮቲን ምግቦች ሲሶቴይን የተባለ ተፈጥሯዊ አሚኖ አሲድ አለው፡፡ ሥጋው በሚቀቀልበት ጊዜ ይህ አሚኖ አሲድ ይወጣል፡፡ ሲሶቴይን ዶክተሮች በብሮንካይትስና በሌሎች የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ለተያዙት ሰዎች ከሚያዙት አሴትልሲስቴይን ከተባለው መድኃኒት ጋር በጣም ይመሳሰላል፡፡ በመሆኑም የዶሮ ሾርባ እንደ ጉንፋን ላሉት የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ይጠቅማል›› ሲል ፉድ፣ ዩር ሚሩክል ሜዲሲን የተባለው መጽሐፍ አስታወቀ፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ከዶሮ ላባና ቆዳ ይዘጋጅ የነበረው ይህ መድኃኒት በአፍንጫ፣ በጉሮሮና በሣንባ ውስጥ የተጠራቀመውን ንፍጥ የማቅጠንና ወደ ውጭ እንዲፈርስ የማድረግ ችሎታ አለው፡፡ ሾርባው የተዘጉ የመተንፈሻ አካላትን የመክፈት ኃይሉ እንዲጨምር ነጭ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርትና እንደ ሚጥሚጣ የመሳሰሉትን ተኮስ የሚያደርጉ ቅመሞች መጨመሩ ጥሩ እንደሚሆን ዶ/ር ዚመንት ይመክራሉ፡፡