June 24, 2013
64 mins read

ስለኢሳት ለኢትዮጵያውያን የተላከ መልእክት!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ኢትዮጵያ ሀገራችን የለየላት የዜጎቿ እሥር ቤት ከሆነች በጥቂቱ 22 ዓመታት አለፉ፡፡ ከ22 ዓመታት በፊት የነበረው ሥርዓተ መንግሥቷ አሳሪና ገዳይ ቢሆንም እንደሥርዓትና የገዢዎቹም ማንነት እንደሀገራዊ ስብዕና ሥርዓተ መንግሥቱ በኢትዮጵያዊ ወገናዊነቱ የማይታማ፣ የመንግሥት አገልጋዮችም በሀገር ወዳድነታቸው ጥያቄ ውስጥ የማይገቡ ከደነዝነታቸውና ድንቁርናን መሠረት ካደረገው ዕብሪታቸው በስተቀር ሌላ ጠላት የሌላቸው ገልቱ ሥርዓትና ጨካኝ ኢትዮጵያውያን ባለሥልጣናት እንደነበሩን የምናስታውሰው ነው፡፡ የአሁኖቹ ግን ስንዴ መሃል እንደበቀሉ እንክርዳዶች የሚመሰሉ የታሪክ አሽክቶች እንደመሆናቸው አዘናግተውና አንድን የታሪካችንን ስብራት አጋጣሚ ተጠቅመው ሥልጣነ መንግሥቱን ከያዙ በኋላ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊውያን ነን የሚሉ ወገኖችን ጠራርገው ለማጥፋት የተነሱ በጭካኔ ወደር የማይገኝላቸው የራሳችን ወገኖች ናቸው፡፡ በበቀልና በጥላቻ መንፈስ የሚነዱት እነዚህ ወገኖቻችን የሰበቀቡን ጦር ወደሰገባው የሚመለስበት ዘመን እየራቀ በመምጣቱ በተለይ በአሁኑ ወቅት የሕዝቡ ሁለንተናዊ ሕይወት ከድጡ ወደማጡ ሆኖ ኢኮኖሚያዊ ሕይወቱ ይቅርና መንፈሳዊ ሕይወቱ ራሱ ከዓለም ሕዝቦች በተለዬ አሰቃቂ ሁኔታ ወደ መቀመቅ እየወረደ ነው፡፡
መብላት መጠጣት፣ መልበስና ማማር ሊቀር የሚችል ተራ ነገር ነው፡፡ ማጣትና ማግኘት ተፈራራቂ በመሆናቸው ዛሬን ያጣ ነገ ያገኛል ተብሎ ይገመታልና ይህም ምንም ማለት አይደለም፡፡ አሁን እያስፈራን የሚገኘው ትልቁ መርዶ ግን አንድ ሕዝብ በዜግነት ማንነቱ፣ በባህሉ፣ በሃይማኖቱ፣ በትምህርት አቋሙ፣ በማኅበራዊ ሥነ ልቦናው፣ በአጠቃላይ የግንዛቤና ዓለምን የመረዳት የአስተሳሰብና የአመለካከት አድማሱ… በነዚህና በመሳሰለው አእምሮኣዊና መንፈሣዊ ኅልውናው ላይ አሁን የተጋረጠበት አደጋ ሊያስከትለው የሚችለው የትውልድ ምክነትና የኅልውና ቀጣይነት ችግር ነው፡፡ ይህ ዓይቱ ችግር ነው ብዙዎቻችንን እንቅልፍ እየነሳን የሚገኘው፡፡ ይህ ዓይነቱ በሰው አምሳል የሚንቀሳቀስ ሞራለቢስና በሀገሩ ላይ ሀገር አልባ የሆነ ትውልድ በብዛት የሚያመርት ሀገራዊ ችግር ነው ጥቂት የማንባል የቀደመው ትውልድ አባላትን የኅሊና ዕረፍት እያሳጣን የሚገኘው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሀገር ያለች እየመሰለች ነገር ግን ሁለመናዋ የጠፋና እንደፀጉራም ውሻ አለች ሲሏት የሞተች ሀገር ውስጥ የመኖር አደጋ ነው እየተንሰራፋ ያለው፡፡
ከቁሣዊው ሕይወት አንጻር ዛሬ ቢርበንና ቢጠማን ምንም አይደለም፡፡ ዛሬን ብንታረዝ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ዛሬን ብንከሳና ብንጠቁር፣ ብንኮስስና ብንገረጣ ብንታመምም ምንም አይደለም፡፡ ጦርነትና ርሀብ ተከስቶ የተመሰቃቀለ ችግር ቢፈጠርም አላፊ ነውና ምንም ማለት አይደለም፡፡ በጥቅሉ ዛሬን ተፈጥሯዊ ችግርን ብንቸገር በኛ ብቻ ስላልሆነ ምንም አይደለም፡፡ ይህ እንግዲህ በሥጋዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ብዙ የዓለም ሀገሮችም በዚህ ሂደት አልፈዋል፤ ዛሬ የሥልጣኔና የቅንጦተኛ ኑሮ ቁንጮ የሆኑት እነአሜሪካና (ቻይና?)፣ እነጃፓንና ከሞላ ጎደል ሁሉም የአውሮፓ ሀገሮች በጠኔና የርስ በርስ ጦርነትን ጨምሮ በአሰቃቂ ችግሮች ውስጥ አልፈው ነው (በአንጻራዊ ሁኔታ የአሁኑ) ምድራዊ ገነት ውስጥ ሊገቡ የቻሉት፡፡ በታሪክ አንቀልባ ታዝሎ መኖር ለማንም አልጠቀመም እንጂ ኢትዮጵያም አንድ ወቅት ለተቸገሩ ሀገሮችና ሕዝቦች የምትረዳ ርህሩሂት ሀገር እንደነበረች የቅርብ ጊዜው ታሪካችን የሚዘክረውና ፈረንጆችና ሌሎች የውጪዎች ሊያምኑት የሚቸግራቸው ተኣምር ነው፡፡ ለጃፓን፣ ለኮርያ፣ ለካናዳና ለብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ፍጡነ ረድኤት የነበረች ሀገራችን ዛሬ ሌሎችን መርዳት ይቅርና ቅን አሳቢ ሰው የማይወጣባት፣ መጭና ወበሎ የሚበቅልባት፣ ጅቦችና ዓሣማዎች የሚራቡባት (የሚፈለፈሉባት ለማለት እንጂ ርሀቡስ ሲያልፍም አይነካቸው!) እጅግ አሳዛኝ ሀገር ሆናለች፡፡ ጤናማ ዜጎቿ እግር ባወጣ እየተሰደዱ፣ በሀገር ቤት ያሉትም በፍርሀት ተሸብበው አንገታቸውን እየደፉ፣ ብዙዎች “ምሁራኗ” ወያኔ የቀደዳለቸውን ቦይ በመከተል በዘርና በጎሣ ተከፋፍለውና በአጥፊና ጠፊ አማሳኝ ጎራዎች ተቧድነው ኃይላቸውን በልማትና በችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ሳይሆን በጉንጭአልፋ ንትርክ የሚያባክኑ፣ በውጤቱ ደግሞ ታሪካዊ ጠላቶቿ ያሰማሯቸው የውስጥ የጠላት ቅጥረኞችና ሸማቂዎች ያገኙትን ወርቃማ ዕድል ተጠቅመው ሀገሪቱ ዳግም እንዳታንሰራራ የሚቀጠቅጡበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸው ሳንወድ በግዳችን በታሪክ ጠማማ ፍርድ እየተንገፈገፍን እንገኛለን፡፡ ቅጥቀጣው ቁሣዊ ብቻ ቢሆን እንደገለጽኩላችሁ ብዙም ባልከፋ፡፡ የቅጥቀጣው መሠሪነትና አሰቃቂነት ግዘፍ ነስቶ የሚታየው ነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖር ሆን ተብሎ ታቅዶ በሚደረገው ሁልአቀፍ ጥረት አማካይነት እየታዘብነው በምንገኘው ወደርየለሽ ጭካኔ የተሞላት ዕኩይ ድርጊት አማካይነት ነው፡፡ ለአብነት በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም የትምህርት ተቋም የሚመረቅ ወጣት – አብዛኛው ማለት በሚቻል ሁኔታ – ስሙን በእንግሊዝኛ አስተካክሎ የሚጽፍ ስለመሆኑ በርግጠኛነት መናገር አይቻልም፤ ይህ የተደረገውና እየተደረገ ያለውም ሆን ተብሎ በተጫነ ትውልድ ገዳይ የመማር ማስተማር ሂደት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም የትምህርት ተቋም የሚመረቅ ወጣት ሀገርህ የት ነው ተብሎ ቢጠየቅ ‹ኦሮምያ፣ ትግራይ፣ደቡብ፣ ሶማሌ፣አፋር…› ከማለት ውጪ ‹ኢትዮጵያ ናት› የሚል ለማግኘት በጣም የምንቸገርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ ዓይነቱ ወያኔያዊ ከፋፍሎ የመግዛት ዘዴ ሀገራችንን እያጠፋት ነው – የፈጣሪ ሥራ ካልተጨመረበት በስተቀር በቀላሉ ልታገግም በማትችልበት ሁኔታ እየወደመች ናት፡፡
በየቀኑ እንደ አሸን የሚፈላውን የሕዝብ ቁጥር ስትመለከቱ ደግሞ ደንብራችሁ ገደል ልትገቡ ትችላላችሁ – እንዲህም የምትሆኑት ስለነገዋ ኢትዮጵያና ሥራ አጥቶ በየባቡር መንገዱ ካለሥራ የሚርመሰመሰውን ሕዝብ ተመልክታችሁ የምትጨነቁ ከሆናችሁ እንጂ ወያኔን ይመስል እንደመጋዣ ያገኛችሁትን እያሞነዠካችሁ የምትኖሩ እንስሳት ከሆናችሁ ምንም ላይሰማችሁ ይችላል – ወያኔዎች እኮ ከሕዝብ መፈጠራቸውን ረስተው በሕዝብ ስቃይ የሚፈነጥዙ በሩቅ ሀገር ሰውነት የሚፈረጁ ጥፉዎች ናቸው፡፡ ሰውን ወደ እንስሳነት መለወጥ ደግሞ የወያኔ አንዱና ትልቁ የአገዛዝ ስትራቴጂው ነው፡፡ የሕዝቡ ብዛት እንግዲህ በእጅጉ የሚያስደነግጥ የወቅቱ ወረርሽኝ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እውነት ነው – የሕዝብ ብዛት በራሱ ችግር ሊሆን እንደማይችል ቻይናውያን አመላክተዋል፡፡ ግን ግን ከዘመኑ ጋር የተገናዘበ ሀገራዊ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ፣ የሕዝቡ ብዛት ከሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብትና የታህታይና ላዕላይ መዋቅሮች አኳያ መመጣጠን እንደሚገባው፣ የሕዝብ ብዛት መጨመር ወይም መቀነስ ለሕዝብ ከሚቆረቆርና ለሕዝብ ከሚሠራ መንግሥት ጋር የቀጥታ ግንኙነት እንዳለው፣ የሕዝብን ብዛት ወደ ተጨባጭ የሀብት ምንጭነት ሊለውጥ የሚችል መንግሥት በአንድ ሀገር ሊኖር እንደሚገባ … መጠቆሙ ጊዜ ያለፈበት አስተያየት ሊባል የሚችል አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ እኛ በሕዝብ ብዛት የምንጨነቀውን ያህል ወይም ከኛውም በበለጠ ‹የሀገራችን የሞትና የወሊድ ምጣኔ በዚህ መልክ ከቀጠለ በዚህን ያህል ዓመተ ምሕረት የዚህች ሀገር ዜጎች ከምድረ ገጽ ይጠፋሉ› ብለው የሚጨነቁና ጋብቻንና ወሊድን በስፖንሰርነት የሚደግፉ የአውሮፓ ሀገሮች እንዳሉ እንሰማለን፡፡ …
በዚህ የጭንቅ ዘመን የሕዝቡን አንድነት ሊያስተባብርና የጋራ የትግል መድረክ ሊፈጥር የሚችል የተስፋ ጭላንጭል ከወደ አሜሪካ ተከስቷል፡፡ ይህ የሕዝቡን ተስፋ በማለምለም ላይ የሚገኘው ዕፁብ ድንቅ ክስተት የኢትዮጵያ ሣተላይት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ (ኢሳት) አየር ላይ መዋል ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ባብዛኛው መንቀፍን እንጂ ማበረታታትን የማንወድ፣ ማቀጨጭን እንጂ ማወፈርን የምንጠላ፣ መውለድን እንጂ ተንከባክቦ በማሳደግ ለወግ ለማዕረግ ማብቃትን የምንጠየፍ፣ በምቀኝነት ታውረን የሌሎችን ስኬት ማንቋሸሽ እንጂ በመንፈሣዊ ቅናት ተመርተን የማንተባበር፣ እንደድመትና ጥንቸል ወልዶ የመብላት ሾተላይ የተጣባው ጠባያችን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ጅል ዐመል ያከናነበን በመሆናችን እንጂ በተስፋ መቁረጥ የጽልመት ማዕበል ተውጦ እየተንገላታ የመከራ ኑሮ ለሚኖረው ምሥኪን ሕዝባችን የምናስብ ብንሆን ኖሮ ይህን አዲስ ተስፋ – ይህን የጋራ የመረጃ ማዕከል ካላንዳች የመቋረጥ ሥጋት ቀጥ አድርገን መያዝ በቻልን ነበር፡፡ ግን እባብ የልቡን አይቶ እንዲሉ የየልባችን ሃሳብና ናፍቆት ለየቅል በመሆኑ ይመስላል ከመተባበር ይልቅ ተለያይተን ለጥገናም በሚያስቸግር መልክ ተሰባብረን መኖርን መረጥንና ስደትና እንግልት የተመቸን ያህል በየሀገሩ የሰው ጫማ ሥር ወድቀን የምናገኛትን ሣንቲም ከቁም ነገር ጥፈን ውርደትንም እንደክብር ቆጥረን ለመኖር ያህል ብቻ እንኖራለን – ምን የመሰለች ቆንጆና የ13 ወር ፀጋ የፈሰሰባት ገነት ምድር እያለችን የሌሎች ባርያ መሆን አማረን፡፡ አያናድድም? መቼ ይሆን ሰው እምንሆን? መቼስ ይሆን የሚቆጨን? መቼ ይሆን ከእልህና ከቂም በቀል ልክፍት ተፈውሰን ለጋራ ቤት በጋራ የምንነሳው?
በመሠረቱና እንደኔ ኢሳት የገንዘብ ልመና ውስጥ መግባት አያስፈልገውም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይና ለሀገር በሚጠቅም ኢሳትን በመሰለ የዜና መድረክ ላይ የገንዘብ ልመና ሲደረግ በበኩሌ አዝናለሁ፤ አፍራለሁም፡፡ ብዙዎቻችን የዜግነት ግዴታን ምንነት ለማወቅ ባለመቻላችንም እንዲሁ አፍራለሁ፡፡ ማን ለማን ገንዘብ ይለምናል? ጤናማ የእምነት ተከታይና ጤናማ ሀገር ወዳድ ሰው የሃይማኖትና የዜግነት ግዴታውን ሳይለመንና ነጋ ጠባ ሳይጎተጎት መወጣት ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ብዙ ሊያናግረኝ የሚችለውን የዐውደ ምሕረቱን ነገር ለጊዜው ልተወውና ኢሳት ላይ ላተኩር፡፡ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ኢሳትን ከጠላት ጎልያዳዊ ጦር መጠበቅ ነውና፤ በኃይል ሚዛን ብቻ ሳይሆን በጠባይም እንደጎልያድ የሚመሰሉት ወያኔዎች ኢሳትን ከአየር ለማውረድ ያደረጉትን ቀጣይነት ያለው ሙከራና ስኬት እናውቃለን – ሊያውም በራሳችን ገንዘብና በራሳችን የፖለቲካና የዲፕሎማሲ መስመር፡፡ እኔን መሰሉ ድሃ የኢሳት ተመልካች እንኳን ያቺው ኢትዮጵያዊነትን የምታስታውሰን የጋራ ተስፋ እንዳትቀርብን ብለን ከመቶ ብር የማስተካከያ ክፍያ እስከ ዲሽ መለወጥና አልኤንቢ መጨመር ድረስ ሄደን ስንትና ስንት ወጪ ማውጣታችንም ይታወቃል፡፡ ይህ ሁሉ እልህ ውሸት ነግሦብን ለምን የወያኔን ቅርሻትና ትውከት ብቻ እንድንጋት እንገደዳለን፤ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ከሌላ አቅጣጫስ ለምን አናገኝም ከሚል ቁጭት ነው፡፡ ይህን ወርቃማ ዕድል ማጣት ለኔ ዓይነቱ ዜጋ ትልቅ የልብ ስብራት ነው፡፡ ታዲያን የዳዊትን ወንጭፍ ለማስታጠቅ ሁላችንም በያቅማችን ጠጠር ካላዋጣን ጎልያድ ማጥቃቱን ይቀጥላል፤ ነጻነታችንም በቶሎ አይመጣም – በቦሌም በባሌም መምጣቱ ባይቀርም፡፡ ግን ግን ልብ በሉ! በባሌ የሚመጣ ነጻነት ባፍንጫችን ቢወጣ ይሻለናል! በቦሌ እንዲመጣ ነው መትጋና ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ያላንዳች ማመንታት በፍቅርና በውዴታ ማድረግ የሚኖርብን፡፡ ይህን ስል ቅኔየ የማይገባው ካለ በቦሌ ስል በሁላችን ፈቃድና የደምም ይሁን የገንዘብና የዕውቀት አስተዋፅዖ የሚመጣ ሕጋዊ ነጻነት ማለቴ ነው፡፡ በባሌ ስል ከወያኔ የተሻለም ይሁን የከፋ ግን ልክ እንደወያኔዎቹ የደም ዋጋ የሚያስከፍለን አደገኛ የማፍያ ቡድን ማለቴ ነው፡፡ በጦር የሚገባን የንቅናቄ ጎራ አጥብቆ መፍራት ይገባል፤ ‹የአበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም›፡፡ ከሚገባን በላይ ተቀጣን፡፡
ኢሳትን በገንዘብ ስናጠናክር ግን መጠንቀቅ የሚኖርብን ነገር አለ፡፡ መጽሐፉ ግራህ ስትሰጥ ቀኝህ አትይ እንደሚለው ሳይሆን የኛ መስጠት አደጋ ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔታ በመኖሩ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ዋናው ፈቃዳችን ነው እንጂ ኢሳትን መርዳት ከፈለግን ከየትም ሆነን መርዳት እንችላለን፤ ቃል ስላጣሁ ነው ‹መርዳት› የምለው- (በግላቸው የኢኮኖሚ ችግር በሌላቸው ደህና ኗሪ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የተቋቋመው ኢሳት እኔን ሊረዳ ቆሞ ሳለ ኢሳትን እኔ ስረዳው አልታይህ ስለሚለኝ ነው ቃሉ የሚከብደኝ – ጭንቀቴን ተረዱልኝ – ምናልባት መደገፍ፣ ማገዝ፣ መተባበር… ሊሆኑ ከቻሉ አላውቅም፡፡ ግን ለጋራ የሀገር ጉዳይ አንዱ ረጂ ሌላው ተረጂ አይሆኑም ብዬ አምናለሁ – በትክክል ተረድታችሁኝ ከሆነ፡፡)
ኢሳት ከተቋቋመ ሦስት ዓመታት ያህል ሆኑት፡፡ በግል ገንዘባቸውና ጥረታቸው ይህን ውድ ገጸ በረከት ለሀገራቸው ሕዝብ ያበረከቱትን ወገኖች እግዚአብሔር ይባርካቸው፤ ዘራቸውንም ያለምልምልን፡፡ ለጓደኛው የአንድ ብር ዳቦ ገዝቶ ወስፋቱን በመሸንገል ሰኞን ማክሰኞ ማድረግ የሚያቅተው ገብጋባ ነገር ግን በምሽት ክበባት እየደነሰና ከታዳጊ ሕጻናት ጋር በወሲብ ዳንኪራ ልቡ እስኪወልቅ እየጨፈረና እየደነሰ በሺዎች የሚገመት ገንዘብ አላግባብ የሚያባክነው ዜጋ ቁጥር ቀላል ባልሆነባት ሀገራችን ውስጥ እንደዚህ ያለ ታላቅ ቁም ነገር መሥራት በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ታላቅ ገድል ነውና እነዚህን ሰዎች በሞትም ሆነ በሕይወት ዘመናቸው ፈጣሪ በፀጋው ይገብኝልን፤ እንደሃይማኖተኝነቴ ኅያው እግዚአብሔር የመንግሥቱ ወራሽ አድርጎ እንዲመዘግብልኝ ዘወትር እጸልያለሁ፡፡ የሆኖ ሆኖ ‹ጓደኛህ ማር ቢሆን ጨርሰህ አትላሰው› ይባላልና እንደገናም ‹ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም› እንላለንና ጅምራቸውን ከዳር ማድረስ ያለብን ሁላችንም ተጋግዘንና ተባብረንም ሊሆን ይገባል እንጂ ‹በገቡበት ይወጡት፤ እኛን ምን አገባን፤ ሺም ታለበ መቶ ያው በገሌ፤ ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቅ…› ብለን ለነሱ ብቻ የምንተወው ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደዚያ ካልን ፈሪዎች ብቻ ሳንሆን ሀገር የለሾች ነን፡፡ እንደዚያ ካልን ለልጆቻችን ማፈሪያና መጠቋቆሚያ የሚሆን መጥፎ ታሪክ መተዋችንን አንርሳ፡፡ እንደዚያ ካልን ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› ካለችው እንስሳ የማንሻል አሞስኪ ወይም ሰልቃጭ እንስሳ እንደሆንን አንዘንጋ – ይህን እያልኩ ያለሁት አባታችሁ ወይም ወንድማችሁ የምሆን እኔ ምሥኪኑ ዜጋ ዳግማዊ እንጂ የኢሳት የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ እንዳልሆነ እዚህችው ላይ ማስታወስ እፈልጋለሁ፤ ለሀገሬና ስለሀገሬ የሚሰማኝን ሳልፈራና ሳላፍር የመናገር መብት አለኝ፡፡ መከራውን ለጥቂቶች ደስታውን ለሁሉም የማድረግ የቆዬ ፈሊጥ ማስቀረት አለብን፡፡ ነገ ይታዘበናል፤ ነገ ማለት ደግሞ ታሪክ ማለት ነው፡፡ እንዲህ የምለው ለስብከት ሳይሆን ለጋራ የአሁንና የወደፊት ጥቅም ነው፡፡ እየቻልን አለማድረግ መረገም ነው፡፡ መረገምን ማስወገድ ደግሞ ይቻላል፤ ቶሎ መንቃትና መፍትሔ ሥራዩን ማፈላለግ ነው፡፡ የተኛንበት ምክንያት ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድም አለማወቅ ወይም የግንዛቤ እጥረት ሊሆን ይችላል፡፡ አንድም ግዴለሽነት ሊሆን ይችላል፡፡ አንድም በዓላማ ደረጃ ሲታይ የአጥፊዎች ወገን ሆኖ መገኘትም ሊሆን ይችላል፡፡ አንድም ገብጋባነት ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ነው ጣጣው፡፡ የዞረ ድምሩ ግን አንድ ነው፡፡ ማገዝ የሚገባህን ክቡር ዓላማ ማገዝ በሚገባህ ጊዜ ሳታግዝ ቀርተህ ቆይቶና ሌላ ጊዜ ወደኅሊናህ ትመለስና ልታግዘው የምትፈልግበት ሌላ ፍላጎት ቢያድርብህና ያኔ ከእልህ ሳይሆን ከእውነት እገዛህ ሳያስፈልገው የሚቀርበት አጋጣሚ ቢፈጠር ያኔና ከዚያም በፊት ተጎጂዎቹ አንተና በአስፈላጊ የችግሩ ወቅት ልታግዘው የሚገባህ አካል ናችሁ – ሁልጊዜም መዘንጋት የሌለብን ሃቅ ድርጊትና ቁጭት/ፀፀት ጓደኛሞች መሆናቸውን ናው፡፡ የተምታታ ነገር ተናጌሬ ሊሆን ይችላል፤ ግን እውነት ነው፡፡ ዳሩ ዛሬ ማን ያልተምታታበት አለና፡፡
መራር አነጋገሬ የሚገባው ይግባው፡፡ የማይገባው ቢኖር ልብ ይስጠው ከማለት ውጪ ረቂቅ ነገርን በጥብጦ መጋ ስለማይቻል ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ማወቅ ያለብን ነገር ግን አለ – ያም ማንኛውም የሕይወት እንቅስቃሴ በደግም ሆነ በክፉ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑን ነው፡፡ ክርስቶስ እንዲህ አለ፡- ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ ያለ ሁሉ መንግሥተ ሰማይ አይገባም፤ አጭር ቃል፡፡ ዛሬ ብዙዎቻችን ብቻችንንም ሆነ ከጠላቶች ጋር ወግነን እንደፈለግን በሕዘብ ላይ ብንፈነጥዝና ብናሸካንን ነገ ደግሞ ሌላ ቀን ነውና ላያችን ላይ የሚያሻካንን ነገር ከላይ ወይም ከታች ይላክብናል – የላዩ ግዴለም፤ መፍራት የታቹን ነው – የሰውን(መርምረህ ድረስበት!)፤ ዓለም ዘወርዋራ ናት – ለማንም አትሞላም አትጎድልምም፡፡ ዛሬ ያለህና ሞልቶ የፈሰሰ የሚመስልህ ነገር ምናልባት ትናንት ያጣኻውን ባንተ በጭብጧ ሕይወት ግን ሲደርስ ያላስተዋልከውን ወይ ከናካቴው ያልደረሰብህን ሊሆን ይችላል፤ ምድር የዕዳ ክፍያ መድረክ መሆንዋን አንርሳ – የአባባ ተስፋየን እረኞች ያሳድዱት የነበረውን ነብርና ከአደጋ ያዳነውን ሚዳቆ ይሁን ድኩላ ታሪክ አስታውስ – ቀን ሰጠኝ ብለህም በሰውና በሀገር ላይ አትፏልል፤ ሁሉም ነገር እንደጤዛ ረጋፊና እንደጉም በናኝ ነው – ነገ ጥርኝ አፈርና ብናኝ አቧራ የሚሆን ሰው ደግሞ ቆሻሻ ታሪክ ትቶ ላለማለፍ መትጋት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ዋናው ሰው የመሆን መፍትሔ ወደኅሊና መመለስ ነውና ከጥፋት ጎዳና በአፋጣኝ ወጥተን ዒላማችንን ወደ ሀገራችን እናቀጣጭ፡፡ ከየገባንበት የግል ዓለም ስንወጣ ደግሞ ኢሳትንም ባይሆን ሌላ ለሀገር የሚሠራ ጤናማ ተቋም ፈልገንና አፈላልገን በከንቱ ከምንምነሸነሽበት ገንዘብም ሆነ አለመላው ከምናባክነው ጊዜ፣ ጉልበትና ዕውቀት ቀነስ አድርገን ለታሪካችን ማማር እንዲሁ በነጻ እናውል፤ ለገንዘብ በገንዘብ ስለገንዘብ ብለንም ገደል አንግባ፤፤ ሁሉንም ነገር ከገንዘብ አንጻር፣ ከወጪና ቀሪ ሥሌት አኳያ ካየነው በዓለም ላይ ስንዝር አንራመድም፡፡ እንዲህ አድርጌ ምን አተርፋለሁ የሚባለው በሀገር ጉዳይ ሳይሆን በተለይ በዘመናችን ብዙም ሰብኣዊነትና ርህራሄ በማይታይበት በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው ፡፡ እንጦርጦስ እየወረድክ ባለህበት ቅጽበት ከዚያ አዘቅት እንዲያወጣህ ከመጣ ኃይል ጋር የሒሣብም ይን የሥልጣን ድርድር ማድረግ ሞኝነት ነው – ቀድመህ ከሞት መውጣትህን አስብ እንጂ ሰው ሠራሹ ወረቀትና እልቅና ሊያብከነክንህ አይገባም፡፡ ለወገንህና ለሀገርህ ፈጥነህ መድረስህ ከገንዘብ በላይ ዋጋ አለው፡፡ ለማረፊያ ሀገርህ ገንዘብህንና ዕውቀትህን ብቻ ሳይሆን እንደነኢንጂኔር ቅጣው እጅጉና አሰፋ ማሩ… ሕይወትህንም ብትሰዋ ለአንተና ለትውልድህ ታላቅ ክብር ነው – እስኪ አስበው – ጋዜጠኛና እክቲቪስት እስክንድር ነጋ እኮ በአሥሮችና ከዚያም በላይ የሚሆኑ እኔን መሰል የቀን ሠራተኞችን ሊቀጥርና ሊያሠራበት የሚችል ወረት ነበረው፡፡ ግን ‹ለማን ብሎ ከርቸሌ ወረደ?› ብለህ አስብ – ሌሎችም የታሠሩት ለሌላ ሥውር ጉዳይ ሳይሆን ለሕዝባዊ ዓላማ ነው፡፡ ይህን ስልህ ሕይወትን ለሀገር መስጠት ቀላል ነው፤ ማንም በቀላሉ ያደርገዋል ለማለት ፈልጌ ሳይሆን ይህን ያደረጉና እያደረጉም ያሉ ወገኖች ስላሉ ለእነዚያ ድንቅ ዜጎች ያለኝን አክብሮትና ፍቅር ለመግለጽና የቻለ ሁሉ አርአያነታቸውን እንዲከተል ለመጠቆም ነው፡፡ አለበለዚያ ‹የሚጠሩ ብዙዎች፤ የሚመረጡ ጥቂቶች› መሆናቸውን ዘንግቸቼ እንዳልሆነ ተረዳልኝ፡፡ ገንዘብም ሆነ ስምና ዝና አላፊ ጠፊ ናቸው፡፡ የማይጠፋና የማይጠወልግ ለሀገር የሚያደርጉት መልካም አስዋፅዖና ሱታፌ በረከት ነው፡፡ እንደሃይማኖታዊ ስብከት አትውሰዱብኝ፡፡ ሃቁን እየተናገርኩ ነው – ሊመርር ይችል ይሆናል፡፡ እውነታው ግን ይውና ይሄው ብቻ ነው፡፡ አጥፊና ጠፊ፣ እንዲሁም መሀል ሠፋሪና በሀገር ጉዳይ የማይሞቀን የማይበርደን ግዴለሾች ሆነን እስከመቼም አንዘልቅም፡፡ ደግሞም ይህን ልብ እንበል፡- የጓሸው የሚጠራበት፣ የጠራው የሚደፈርስበት ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡
ስለራሴ አንድ ምሳሌ እንድናገር ይፈቀድልኝ፡፡ እኔ ኢሳትን መደገፍ የሚያስችለኝ አንዳች አቅም ባገኝ አሁኑኑ አደርገው ነበር፡፡ ግን አልችልም፡፡ የአለመቻሌ ምክንያት ደግሞ የወር ገቢየ የወቅቱን ገበያ ከመሸከም አቅም በእጅጉ ያነሰና ለራሴም የማይበቃ በመሆኑ ነው – ለገንዘብ ስል ለልጆቼና ለቀሪው ትውልዴ መጠቋቆሚያ የሚሆን መጥፎ ነገር ውስጥ አለመዘፈቄና በንጹሕ ድህነት መኖሬ ራሱም ትልቅ ነገር ነው – ድህነታቸውን ለማስወገድ ብዙ ወንጀልና ኃጢኣት የሚሠሩ ወገኖች እንዳሉ እረዳለሁና፡፡ ይህን ስል ደግሞ ለሀገሬ ምንም አልሠራሁም አልሠራምም ማለቴ እንዳልሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ የሚጨበጥና የሚዳሰስ ነገር ባልሠራም ቢያንስ በሃሳብና በጭንቀት ከሚዋትቱ ወገኖች ውስጥ እመደባለሁ ብዬ ስለማስብ ያ ብቻውን ያስደስተኛል፡፡ ከአጥፊዎቿ የስም ዝርዝር ውስጥ አለመገኘቴ ራሱ ለኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሁለንተናዊ ትግሉን የሚያግዝ ዕድል ቢኖረኝ ክብርና ሞገሱ ለኔ እንጂ ለማንም አይደለምና አቅምና ችሎታየ በፈቀደ የምሳተፍበት ዕድል ቢፈጠር አላፈገፍግም፡፡ እማምላክን – አሁን አሁን በማየውና በምሰማው በሚደርስብኝ የሕይወት እንግልትም ክፉኛ እየመረረኝ ነው፤ በሌላ አንጻር ግን በርካታ ዜጎችን ስናይ ብዙ የሚያሳዝንና የሚያስተዛዝብ ነገሮችን እየታዘብን ነው – “ ‹ሀ› ራስን ማዳን” በሚሉት ፈሊጥ፡፡
ቀደም ብዬ ለመጠቆም እንደሞከርኩት ለአልባሌ ነገር ስንትና ስንት ገንዘብ የሚያወድሙ ሰዎች ቆም ብለው ቢያስቡና ለዚህ ለተቀደሰ ተግባር – ለግብር ይውጣና ለታይታ ሳይሆን – ለዓላማ ብለው በቋ ሚነት አንዳች ነገር ቢመድቡ ኢሳት በቀላሉ እያደገና እየተመነደገ ይሄዳል፡፡ በቁጥ ቁጥ የልመና ገንዘብ አንድን የመረጃ ተቋም ማሳደግ ግን አይቻልም፡፡ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ እርግጥ ነው እስካሁንም ቆሞ ያለው መስዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁ በሆኑ ጥቂት ዜጎች አማካይነት መሆኑን እናውቃለን፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ግን ለጋራ ዓላማ አንዱ ለማኝ ሌላው ተለማኝ እንድንሆን መጠበቅ እንደማይገባንና ሁሉም ተባብሮ ይህን በወያኔ መንደር ሽብርና ብርክ የለቀቀ የመረጃ ማዕከል መደገፍ እንደሚገባ ነው፡፡ ‹ወንድሜ ታሟል እባካችሁን የቻላችሁትን ዕርዱኝና ላሳክም› ማለት አንድ ነገር ነው – ከዚያ ይሠውር እንጂ ይቻላልም፡፡ ‹በሀገራችን ላይ የሚፈጸምን ግፍና በደል ለሕዝባችንና ለዓለም እናጋልጥ፤ ይህን ግፍና በደል በጋራ ተቋቁመን ነጻ ሀገር እንፍጠር…› ለማለት ግን ልመና በጭራሽ አያስፈልግም፡፡ እንደዘመነ ኢሕአፓ ለሞት ተልእኮም እንኳን ቢሆን በእኔ እቀድም እኔ እቀድም ዕድሉን ለማግኘት መሽቀዳደም ሲገባን የሁላችን ጉዳይ ለተወሰኑ ዜጎች የተጣለ ያህል ቸልተኛና ግዴለሾች መሆን አይጠበቅብንም፡፡ የሀገራችን ጉዳይ ለአንዱ ሸክም ለሌላው ከመጤፍ የማይቆጠር ገለባ ሆኖ ማየትም ያሳፍራል፡፡
አንድ እውነት ልንገራችሁ ደግሞ፡፡ ይህን ሁሉ ማስፈራሪያም በሉት ዛቻ ለእንቅልፋሞች የምወረውረው ኢሳት ቢቋረጥ የሚከተለውን አደጋ ከግምት በላይ ስለምረዳ ነው፡፡ ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት ኢሳትን የሚመለከተው እንደመሲሕ ነው፤ የብዙ ሰው መጽናኛ ሆኗል፡፡ መሲሕ ማለት በዚህ በኔ ዐውድ የአንድን ነገር መምጣት የሚያበስር እንደመንገድ ጠራጊ የሚቆጠር በጎ መፃኢ ነገርን አመላካች ማለት ነው፡፡ ወያኔ እንደጦር የሚፈራውም አለምክንያት አይደለም፡፡ ወያኔዎች የሚፈሩትን ነገር ለምን እንደሚፈሩ ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ በፈሩት እንደሚጠፉም ያውቃሉ፡፡ ስለዚህም ነው ኢሳትንና እነእንቶኔን የሚፈፈሩት – ስማቸውም ሲጠራ ገደል እስከመግባት በሚያደርስ ድንጋጤ የሚዋጡት፡፡ ለዚህም ነው እኔም ኢሳትን የወደድኩትና ከጎኑ ለመቆም የቆረጥኩት፡፡ ለዚህ ነው ለኢሳት የማልሆነው የሌለኝ – ምን ማለታችሁ ነው፡- 450 ብር ሆጭ አድርጌ እኮ ነው በዚያን ሰሞን ለስንተኛ ጊዜ ኢሳትን ያስገባሁት፡፡ …
ኢሳት ጉደለት አለው የለውም የሚለው የዘበናዮች አነጋገር ለጊዜው የሚያነጋገር አይደለም – እየየም ሲዳላ ነው ጌቶቼ፡፡ ጉድለት እንኳንስ በችሮታና በቡገታ ገንዘብ የሚተዳደር አንድ አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ ታዳጊ የዜናና መረጃ ማዕከል ይቅርና ቢቢስና አልጀዚራን በመሳሰሉ በቢሊዮኖች ዶላርና በሺዎች ዕውቅ ባለሙያዎች የሚተዳደሩ ዕድሜ ጠገብ ጣቢያዎችም ስንትና ስንት ጉድለትና እንከን አለባቸው፡፡ ይህን እውነት የኢሳት ኃላፊዎችም የሚያጡት አይመስለኝም፡፡ ዐይን ውስጥ ያረፈች ትንኝን በለስላሳ ነገር በብልሃት እንደማውጣት በወስፌና በጉጠት የሚደነቁል ሰው ካለ ስህተቱ የትንኟ ወይም የዐይኑ ሳይሆን ትንኚትን አወጣለሁ ብሎ የሚነሳው ጀብደኛና አቅለቢስ ሰው ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢሳታውያን፣ ኢሳትን ሕዝብ ስለወደደውና ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ሥርጭትን በሚመለከት ብቸኛ የሕዝብ አለኝታና ዋስ ጠበቃ የመሆናቸው አጋጣሚ አንዳች ግርዶሽ አጥልቶባቸው ‹እኛ ፍጹማን ነን፤ ለትችት የሚያጋልጠን አንዳችም ነገር አንሠራም፤ የሚተቸን ሰው ካለም ወያኔ ነው…› የሚሉ አይመስሉኝም – እንደዚህ ዓይነት ነገር በግልጽ አይደለም በምልክትም እንኳን ቢያሳዩ ሌላውን ተውት እኔና ምሥኪን ብዕሬም በቻልነው ሁሉ እንታገላቸዋለን፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ ተስፋ መጨለም የለበትም፡፡ ተራርመን፣ ተወቃቅሰን፣ ተማምረን ይህችውን ያለችንን ብቸኛ መድረክ በመጠቀም ለሀገራችን ነጻነት መብቃት ይኖርብናል፡፡ የሦስት ብር ገመድ የሁለት መቶ ብር ዶሮ ይዞ መጥፋት የለበትም ባይ ነኝ፡፡ (የስሙኒ ዶሮ የብር ገመድ … ይባል ነበር ዱሮ!)
እርግጥ ነው – ይህ ሲባል እዚህም ሆነ እዚያ ኮሽ አይበል ማለት አይደለም፤ ይሄኛውም አንዱና ሌላው መጥፎ ጫፍ ነው፡፡ መወቃቀስና መተቻቸት አንዱ የዴሞክራሲ ባህል በመሆኑ መለማመድ ያስፈልጋል፡፡ በነባሩ ኢትዮጵያዊ የመኮራረፍና የመጠላለፍ ባህል በትንሹም በትልቁም እጅጌያችንን አንሰብስብ እንጂ ስህተት በመሰለ ነገር ላይ በጨዋነት መነጋገሩ ተገቢ ነው – መጥፎው እንዲያውም እየተፈራሩ አለመነጋገሩና ቅሬታን እንደቁስል እየሸፋፈኑ ለበለጠ የማይድን ምርቀዛ መዳረጉ ነው፤ እናም በሰለጠነ መንገድ እንወቃቀስ፣ ስንወቃቀስም በግል ስብዕና ውስጥ እየገባን “እንዲህ ነህ፤ እንዲህ ነበርክ፤…” ከማለት ተቆጥበን በወቅቱ ጉዳይ ላይ ብቻ እናተኩር እንጂ ወደሽመልና ግላዊ የሽሙጥና አግቦ ዘመቻ አንግባ፡፡ ከዚህ በተያያዘ እንደፌንጣ እየዘለሉ በዶንኪሾታዊ ምናብ አከል የጠብ ያለሽ በዳቦ ልክፍት መጠመድ ጤናማነት አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሰው መለየትና ማስተማር፣ መገሰጽና ካልተቻለም በጊዜ ማራቅ በሥራውም ተቀይሞ አጉል እልህ ውስጥ አለመግባት እንደሚያስፈልግ መረዳት ጠቃሚ ነው – በዚህ ዓይነቱ ሸውራራ አካሄድ በውነቱ ብዙ ተጎድተናል፤ ብዙ ሰውና ብዙ ጥረትም ባክኖብናል፡፡ በዚህ ዓይነቱ የማይጠቅም የሃሳብና የተግባር ግጭት ውስጥ መግባት የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የጉልበትና የትኩረት ‹ሪሶርስ›ን አላግባብ እያባከኑ ትግልን ማቀጨጭ ያስከትላል – ልክ እንደ እስካሁኑ፡፡
ከጀመርኩት ሃሳብ እንዳልወጣ እንጂ ቅሬታዎችን በተመለከተ አንድ ሃሳብ አለኝ፡፡ እንዲህ ቢሆንስ – ከታወቁና ከታላላቅ የሁሉም ክልሎቻችን ሰዎች አንድ ትልቅ ኮሚቴ እናቋቁም – ከተቻለ ከሀገር ውስጥም ካልተቻለ ግን በውጪ ከሚኖሩ፡፡ ይህ ኮሚቴ በታወቁ የሃይማኖት ሰዎች እንዲመራ እናድርግ፡፡ የዚህ ኮሚቴ ዋና ተግባርም የሀገራችንን ፖለቲካ በሚመለከት የሚፈጠሩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በሰከነ ሁኔታ እየመረመረ ግለሰቦችን ወይም ድርጅቶችን የሚያስታርቅና ወደመግባባት የሚያመጣ ይሁን፡፡ የዚህ ኮሚቴ ቢሮም በግድ የታወቀና የተወሰነ ቦታ ላይ ሊሆን አይጠበቅበትም፡፡ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ስለሆነ በያሉበት በኢሜይልና በመሰል የቴክሎጂ ውጤቶች ሊካሄድ ይችላል፡፡ ይህ ኮሚቴ እያጣራ አጥፊን የሚገስጽበትና ከማኅበር እንዲገለል የሚያወግዝበት ብልሃት እንዲኖረው ይደረግ፡፡ ኮሚቴው ተዓማኒነትና ተፈቃሪነት ካገኘ በዚህ ኮሚቴ ሥር በባህልና በሃይማኖታዊ ትዕዛዛት እየተዳኘ አፈንጋጭ የሚስተካከልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ሃሳቡን ‹የሚገዛኝ› ባገኝ በ‹ነጻ› እሸጣለሁ፡፡ ተጨነቅን እኮ ጎበዝ! አዳሜ እየተነሣ ‹እንዲህ ካልሆነ እንዲህ እሆናለሁ/አደርጋለሁ!› ይላል፤ ገና በሳይጋገር ተቦካ እምቡር እያለ በረት እንደሚበጠብጥ ፊጋ በሬ ስብስቦችን ስለሚያውክ የጋራ ትግል ጥረቶች ከመጀመራቸው እየመከኑ የጠላት መጫወቻና መሣለቂያ ሆነን ቀረን፤ እኛም ለሀፍረትና ለውርደት እንዲሁም ለትዝበት እንደተዳረግን መኖር ዕጣ ፋንታችን ሆነ፡፡ ይሄ ‹ታዋቂ ግለሰቦች› የሚሉት ፈሊጥ ደግሞ አንዱ የጠመሰን ነገር ነው፡፡ ታዋቂነትን እኛው እንፈጥረውና መልሶ እኛኑ ይጨቁነናል፡፡ ምን ዓይነት ፍርጃ ነው? እኛው ቁጭ ብለን ሰቅለን ቆመን ማውረድ ያቅተናል፡፡ እኔ ታዋቂነትን የምረዳው ከትህትናና ከጥበብ ጋር ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲገባ ትርጉሙ የማይለወጥ ወይ ቢያንስ የማይጣመም ነገር ጠፋና የኛ ሀገር ታዋቂዎች ሥልጣኑም ምኑም ምናምኑም ‹ከኛው ግዛት አይውጣ› ከሚል ይመስላል አሽርጋጅና አከንፋሽ ቲፎዞም ከጎናቸው በማሰለፍ ጭምር ብዙ የፖለቲካና ሲቪክ ማኅበራትን ሲያውኩ ይስተዋላል ይባላል፡፡ ይሄ ታዋቂነትና ዝና የሚሉት አስካሪ መጠጥ ናላን ከሚያዞር እንክርዳድ የሚጠመቅ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ማን ነው ያ አንድ የቀድሞ ‹ወዳጄ› በታዋቂነት መርዝ ጭንቅላቱ ዞሮ በየስብሰባው ሲኮፈስ ባጅቶ አሁን እንደፈሳች ጅንጀሮ ብቻውን ይንከላወሳል ሲሉ ሰማሁ፡፡ አሁን የሚያስፈልገን ሐኪም ለዚህ ዓይነቱ በገንዘብም ይሁን ወይ በትምህርት ልሂቅነት ወይም በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ዕውቅና የሚያገኝ ሰው ያገኘው ስመጥርነትና የሕዝብ ፍቅር ራሱን እንዳያዞረውና ወደመታበይ እንዳያመራ የሚረዳው መድሓኒት መፍጠር የሚችል ብልህ ሰው ነው፡፡ በዚህም ክፉኛ ተጠቅተናል ጎበዝ፡፡ የፈረንጅ ታዋቂ አይታበይም ይባላል – የኛ ግን ገና ከመታወቁ አናቱ ላይ ቂብ የሚልበት ዛር ቢጤ አለ አሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎችን በዐይኑ እንትን ማየት ይጀምራል፤ ከእርሱ በላይ ሰውም ላሳር ነው፡፡ ትልቅ መረገም!
ለመሆኑ መቼ ነው ሰው መሆናችንን ለዓለምና ለኛው ለራሳችን የምናሳየው? መቼ ነው ታላቆች እንደነበርን፣ አስታራቂዎች እንደነበርን፣ ምራጮች ሳንሆን መራጮችና ተመራጮች እንደነበርን የምናስመሰክረው? መቼ ነው ከታጥቦ ጭቃነት የምንወጣው? መቼ ነው ቀፍድዶ ከያዘን የምቀኝነትና የተንኮል አባዜ የምንፈወሰው? መቼ ነው በስኬታማ ወገኖች ዐይን ላይ ሚጥሚጣና በርበሬ መነስነሳችንን የምናቆመውና ‹ኦ! ጥሩ ሠራህ! እባክህን ወንድሜ እኔም እንዳንተ እንዲሳካልኝ ምከረኝ!› እያልን እርስ በርስ የምንደናነቀውና በልበ ቀናነት የምንመካከረው ? መቼ ነው ከባንጠጣው እናደፍርሰው የጠነዛና የገለማ ባህል ራሳችንን ነጻ የምናወጣው? መቼ ነው ራሳችንን ከቀፍዳጅ አመለካከትና አስተሳሰብ ነጻ ወጥተን ሀገራችንን ነጻ የምናወጣው? በሀገር ውስጥና በውጪ በስደት የሚንገላታው ወገናችን ችግር የሚገባን መቼ ነው? ከግል የሥልጣንና የሀብት ማጋበስ ፍላጎት ወጥተን መቼም ለማይሞት የሀገር ክብርና የወገን ፍቅር የምንማረከው መቼ ነው? የወገናችን ቁስል እንደራሳችን የሚሰማንና ሌት ከቀን የሚጠዘጥዘን መቼ ነው? ወያኔ ካጠመደብን የክፍፍል የፈንጂ ወረዳ ራሳችንን ነጻ የምናወጣው መቼ ነው? ከሥልጣን ሱስና አራራ የምንላቀቀው መቼ ነው? ከአፍ እስካፍንጫችን ማሰቡን አቁመን ሰፊ የአስተሳሰብ አድማስ ባለቤቶች የምንሆነውና ከመሳቂያነት የምንወጣው መቼ ነው? መቆሚያና ሁነኛ ምላሽ የሌላቸውን እነዚህን መሰል ብዙ ጥያቄዎች መጠየቅ ይቻላል፡፡ እባካችሁን ጊዜ እየቀደመን ነውና አሁኑኑ እናስብበት፡፡
ኢሳትን በሚመለከት ግን በኢትዮጵያ ሕዝብ በዐይኑ በብረቱ እንደመምጣት ነውና በዚህ ተቋም ላይ እጃችሁንና ሁለንተናችሁን ያነሳችሁ ወገኖች ሶብሩ – አደብ ግዙ፡፡ በጥፋት መንገዳችሁ የምትጓዙ ከሆነ ወያኔ ባትሆኑም እንኳን የሕዝብ ችግርና ብሶት የማይገባችሁ ደናቁርት ወይም ግዑዛን ድንጋዮች ናችሁና የታሪክ ፍርድ በእናንተና በትውልዳችሁ ላይ ይውረድ፡፡ ኢትዮጵያን እያጠፉ ያሉ ወገኖቻችን የእርግማን ውጤቶች መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ የእናንተ የተረገመ ትውልድ ግና ሌላ የመከራ አዙሪት በሀገራችን ሕዝብ ላይ ሳያስከትል በእንጭጩ እንደጤዛ ይርገፍ፡፡ በሀገርና በሕዝብ የሚቀልድ ከአሁን በኋላ የዶግ አመድ ይሁን፡፡ ሳትፈሩ አሜን በሉ፤ ምናባቱ ሊጠቅመን፡፡
ኢሳት ውስጥ በግሌ የማልወደው ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ያ ግን ከኢሳት አጠቃላይ ተልእኮ ጋር በአጋም በቀጋ አይገናኝም፡፡ በዚያ ላይ ተነስቼ ኢሳት ላይ የምዘምት ከሆነ ሳልወለድ ብጨነግፍ ይሻለኛል – እንዲህ ዓይነቱ ነገር የሚያመለክተኝ ከጤፉ ይሁን ከበርበሬው እንደምናገኘው የሚጠረጠረው የምቀኝነት ጄኔቲክ ንጥረ ነገር የሚያሳድርብን አፍራሽ ኃይል እንደተጠናወተን ነውና በዚህ ራቁቱን በወጣ ሰይጣናዊ መንገድ መሄዱ ይቅርብን፡፡ መወቃቀስ ካለብን በየግል የኢሜል አድራሻዎቻችን እየተነጋገርን አለመግባባታችንንም ቢሆን በዚያው እልባት እንስጠው እንጂ ሁሉንም ተራ የመንደር ጠብና የጓደኝነት ዘመን ንትርክ ወደ ሀገር አናምጣው፤ አሉቧልታና የግል ቅያሜ ወደሥራው ዓለም ሲዛነቅ እጅግ ጎጂ ነው፤ ያለማደግና በዚያው በአነስተኛ የአስተሳሰብ ደረጃ ተወስኖ የመቅረትም ምልክት ነው፡፡ እንኳንስ የአሠርት ዓመታት ጠብና ቅራኔ ይቅርና አደጉ የተባሉ ሰዎች በደቂቃዎች ውስጥ ተነታርከው በደቂቃዎች ውስጥ ቅራኔያቸውን አስወግደው በደቂቃዎች ውስጥ ሰላማዊ ግንኙነታቸው አድሰው እንደቀድሟቸው ይሆናሉ – ማደግ ሲባል ደግሞ በአካል መንጀርገግ ወይም በሀብት የባንክ አካውንትን ማስጨነቅ አይደለም፤ እንደዚያ ዓይነቱ እንዲያውም የዕድገት ፀር እንጂ ከዕድገት ዐበይት መገለጫዎች የሚመደብ አይደለም (ከፈለጋችሁ የረጂሙ አሥራትን ሞኝነትና የቱጃሩ እንትናዬን አጠቃላይ ብልግና ታዘቡና የአባባሌን ደርዘኝነት አመሳክሩ፤ ቁመትና ሀብት ሲበዛ በሞኝነትና በትዕቢት ያናፍላል እንጂ አስተዋይነትን አይጨምርም – አንዳንድ በስተቀሮችን ግን ከዚህ በተቃራኒ በሚገኝ ታሳቢነት ያዙልኝ)፡፡ እኛ ታዲያ ጅሎች ፍጡራን የሆንን ይመስል የአርባ ዓመት ጠብ እየቀሰቀስን እንደአዲስ ስንነቋቆርና ሌሎችን ሰላም ስንነሳ እንገኛለን – ሥራ እንደሌለው ሰው፡፡ የምንገርም ፍጡራን ነን! ደግሞም ‹ኢትዮጵያውያን አስተዋይና በመቻቻል የሚኖሩ ትግስተኞች ናቸው› ይባልልናል – ‹ዶሮን ሲያታልሏት ዳይኖሰር ነሽ አሏት አሉ – እነሱ ባይሉም እኔው ብልስ፡፡ ወገን፤ ግዴላችሁም ጓዳችንንና ጉዳችንን አንደ በአንድ እንፈትሽ፡፡ ትክክለኛውን ራሳችንን ዕንወቅ፡፡ የአሁኑን ዘመን ዜጎች ከጥንቶቹ ጋር እንናወዳድርና ጉድለት ካለብን እናስተካክል፤ መልካም ጎንም ካለን አጠናክረንና አሻሽለን እንቀጥል፡፡ የሆነው ቢሆን ታዲያ ኢሳትን ለቀቅ እናድርግና ይልቁናስ በተቻለን መጠን በመላው አቅማችን ተረባርበን ቀጥ አድርገን እናቁመው፡፡ የግል ጠብና ቅራኔን ከጋራ የሀገር ጉዳይ እንለይ፡፡ ደግሞም በብዙኃን የአብላጫ ድምፅ የመገዛትን ባህል እናዳብር እንጂ የኛ ሃሳብ ብቻ ተቀባይነት ካላገኘ ‹ወዮልሽ!› እያልን በአምባገነንነት እምቡር አንበል‹ ጥረታችን ነሁሉ አምባገነንነትን ለማፈራረስ እንጂ በእስካሁኑ ማኅበረሰብኣዊ ሕይወታችን ቋቅ ያለንን ፈላጭ ቆራጭነት በአንድ ወይ በሌላ መልክ ለመመለስ መሆን የለበትም፡፡ የማያዋጣ ጸሎት ለብራቅ እንደሚዳርግ ከኛ በላይ የሚያውቅ የለምና ጅልነታችንን በአስተዋይነት እንለውጥ፡፡ … ጋን በጠጠር ይደገፋል፤ ሃምሳ ሎሚም ለአንድ ሰው ሸክም ለሃምሳ ሰው ጌጥ ነው፡፡ እናም ኢሳትን በእግሩ ለማቆም በምንችለው ሁሉ ከልብ እንረባረብ፡፡ ልብ ይስጠን፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሁኑኑ በልዩ ጥበቡ ይባርክ፡፡ ሰውም ይላክልን፡፡ አሜን፡፡
ma74085@gmail.com

 ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ጋዜጠኛ ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳንን እንኳን ደስ ያለህ ማለት እፈልጋለሁ፤ ይህን ወረቀት ጽፌ ጨርሼ አርትዖት ላይ እያለሁ ኢቲቪ ሦስት ላይ አንድ የቀይ መስቀል ሎተሪ ማስታወቂያ ስመለከት በሞባይል በሚላክ የሁለት ብር ሎተሪ አማካይነት ባለ 65000 (ስድስት መቶ ሃምሣ ሺ ብር) ዳብል ጋና ፒክኣፕ መኪና እንደደረሰው አየሁ – ዕድልን እግዜር ይስጣት፤ ልጅም ይውጣላት፡፡ ደስታየ ወሰን አልነበረውም፤ እሰይ!! ለዕድገቱ ያድርግለት! በተለይ በኢትዮ. የጋዜጠኛ ኑሮ ያሳዝናል፡፡
 ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም ጋዜጠኛ አሰግድ ተፈራን ሲያነጋግር የተጠቀመውን የአንቱታና የአንተታ ድብልቅ አነጋገር አልወደድኩለትም፡፡ ጋዜጠኛና አርቲስ ባብዛኛው አንተ እንጂ አንቱ በመባል አይታወቅምና በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ሌላ አጋጣሚ ካላገኘሁ የተሰማኝን ቅሬታ በዚሁ ልተንፍሳት ብዬ ነው፡፡
 ኢሳት ፕሮግራሞቹን በጣም መደጋገሙ ላይ በጣቢያው በሚተላፍ የሕዝብ አስተያየት ሳይቀር በስፋት ትችት እየቀረበበት ነው፡፡ በግሌ ችገሩ ይገባኛል፡፡ ይህ ችግር ሊቀረፍ የሚችለው ደግሞ ኢኮኖሚያዊ አቅሙ ሲዳብርና አጋዥ ኃይል ሲበራከት በመሆኑ መታገስ እንደሚኖርብን ይሰማኛል፡፡ የጣቢያው የሥራ ኃላፊዎችም የሚያስቡበት ይመስለኛል፡፡ በዚህ ግን ብዙም ባንከፋ ደስ ይለኛል፤ በመሠረቱ የፕሮግራምና የዜና መደጋገም በሌሎችም ላይ ያለ ነው – እየመረጡና ሰዓትን እየለዩ መከታተል ደግሞ የአድማጭና ተመልካች ድርሻ ነው፡፡ ለነገሩ ጣቢያውም ለዚህ ተገቢ ቅሬታ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ይመስለኛል – ለዚህ ግን የሁሉም ዜጎችና በተለይም የባለሀብቶች ትብብር ወሳኝ ነው፡፡

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop