June 10, 2014
17 mins read

Health: ሁካ (ሺሻ) ምን ይጠቅማል? ምን ይጎዳል?

hukka

ሺሻ፣ ሁካ፣ ናርጊሌ፣ ጌሊዮን እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ስሞችን በመያዝ የሚታወቀው ዕቃ የተለያዩ ቅጠላ ቅጠል፣ ፍራፍሬ፣ የቶባኮ ቅጠል፣ ወይንም ሐሺሽ ለማጨስ የተሰራ ከመስታወት በተሰራና ጠርሙስ መሰል ዕቃ በትቦ አማካኝነት የተፈለገውን የዕፅ አይነት በውሃ ፊልተር አድርጎና ሙቀትን ተጠቅሞ የተፈገለውን ውጤት ለማድረስ የተዘጋጀ ዕቃ ነው፡፡

ሁካን ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጠረው ሐኪም አብዱል ፉት የተባለው ህንዳዊ ሐኪም ሲሆን ይሄም ቶባኮ በጤና ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለመቀነስ በመጀመሪያ ጭሱ በውሃ ውስጥ ማለፍ አለበት ብሎ በማሰቡ የተነሳ ነው፡፡ ሺሻ በህንድ ሀገር ውስጥ በሚጠቀሙበት በተለይ በድሮ ጊዜ እንደ ባህል ከመታየቱም በላይ በተወሰነ መልኩ ከሀብት ከክብር ጋርም ይያያዝ ነበር፡፡ ከጊዜም በኋላ ከህንድ ሀገር አልፎ በአብዛኛው የአረብ ሀገሮች ውስጥ ለረዥም ጊዜ መታየት የጀመረው ሺሻ ወደ ሌሎች የዓለም ክፍሎች ብሎም ወደ ሀገራችን መግባቱ አልቀረም፡፡
በአብዛኛው በሀገራችን ላይ የሚታየው የሺሻ አጠቃቀም ከጫት ጋር ተያይዞ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወዲህ ሺሻን ለብቻው የሚጠቀመው የሰው ቁጥር እጅግ እየጨመረ ከመሄዱም በላይ በተለይ በወጣቱ ላይ ገኖ መታየቱ ለሁኔታው የበለጠ ትኩረት እንድንሰጠው አድርጎናል፡፡
ሺሻን በተመለከተ የተለያዩ ሀገሮች የተለያየ የመከልከል አጋጣሚ ሲኖረው ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት በጤና ላይ የሚያስከትለው ችግር ከጊዜ በኋላ በጥናት እየታወቀ በመሄዱ ሺሻ በሚጨስበት ወቅት የአጫሹን ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡንም ጤና ሊጎዳ በመቻሉ የተፈጠረ ሁኔታ ነው፡፡

ሺሻ ማጨስ በጤና ላይ ምን አይነት ችግር ሊያስከትል ይችላል

በመሰረቱ ሺሻ ከሲጋራ ያነሰ የጤና ችግር ያመጣል የሚል የተሳሳተ እምነት አለ፡፡ ይሄም የሆነበት ምክንያት በውሃ ውስጥ የሚያልፍ እንደመሆኑና ወደ የአየር ትቦ ሲገባም የመክበዱ መጠን የሲጋራ ያህል ባለመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ሺሻ በጤና ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለማወቅ በርካታ ጥናቶች በሂደት ላይ ቢሆኑም ዳሩ ግን እስከ አሁን የተደረጉ ጥናቶች የሚያመላክቱት ሺሻ ማጨስ ሲጋራ ከማጨስ የበለጠ ጉዳት እንደሚያስከትል ነው፡፡
– በሺሻ ዕቃ ውስጥ ያለው ውሃ በቶባኮው ውስጥ ያለውን የጤና ጠንቅ ነገሮች አጥልሎ አያስቀረውም፡፡

– በሺሻ አማካኝነት የሚጨሰው ኒኮቲን የተወሰነው ያህል በውሃው ውስጥ ይቅር እንጂ አሁንም ቢሆን ሱስ ለማስያዝና በጤና ላይም ጉዳት ለማስከተል በቂ የሆነ የኒኮቲን መጠን በበቂ ሁኔታ ወደ ሰውነታችን እንደመግባቱ እንደ ማንኛውም አደንዛዥ ዕፅ ሱስ ሊያስይዝ ይችላል ማለት ነው፡፡
– ከሺሻ የሚወጣው ጭስ ከሲጋራ ጋር ሲነፃፀር እኩል ወይንም የበለጠ የካርቦን ሞኖኦክሳይድ እና የታር መጠን እንዲሁም ደግሞ የተለያዩ ከባድ ንጥረ ነገሮችን በብዛት እንደመያዙ የአፍን የአየር ቧንቧ ካንሰር የመከተል እድሉ አሁንም ቢሆን ከፍ ያለ ነው፡፡

– የዓለም የጤና ድርጅት በቅርቡ እንዳሳወቀው የሺሻ አጫሾች አንድ ሲጋራ ወይንም ሲጋራዎች ከማጨስ ይልቅ ረዥም ጊዜ እንደመወሰዳቸው መጠን የሚከሰተው የጤና ችግር እጅግ የጨመረ ነው፡፡ ይሄንንም ስንል የተለመደ የአንድ ሰዓት የሺሻ ማጨስ ከሲጋራ ይልቅ ከ100-200 እጥፍ ለሚሆን የጭስ መጠን ያጋልጣል፡፡ እንዲሁም በአንድ ጊዜ የሚደገውና የሚጨሰው የሺሻ መጠን የሚያስከትለው የጤና ችግር 70 ሲጋራ በማጨስ ከሚከተለው ችግር ጋር ይመጣጠናል፡፡

– በዚህም አማካኝነት ሺሻ ማጨስ ለአፍና ለድድ፣ ኢንፌክሽን፣ ለቲቢ፣ ለአፍ ካንሰር፣ ለአየር ቧንቧ በተለይም ለሳንባ ካንሰር፣ እንዲሁም ለተለያዩ ሁኔታዎች ያጋልጠናል ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይም ሲጋራ ማጨስ ለሰውነትና ለጤና የሚጎዳ ነው፤ ሺሻ ማጨስ ደግሞ እንደየሁኔታው ከሲጋራ ማጨስ ባይብስ እንኳን ያነሰ እንደማይሆን ግን እርግጥ ነው፡፡

የተለያዩ ሱስ የሚያስይዙ ኬሚካሎችን የያዙ ነገሮችን ለዚሁ ተግባር ብለን የምንጠቀምባቸው ከማንጠቀምባቸው ሰዎች አሁን አሁን እየጨመርን የመጣን ይመስላል፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱና ብዙ ሰው የሚጠቀምበት ሲጋራ ይገኛል፡፡ በሲጋራ ውስጥ የሚገኘው ቶባኮ የሚባለው የቅጠል አይነት በውስጡ ኒኮቲን የተባለ ሱስ የሚያስይዝ ኬሚካል እንደመኖሩ መጠን ይሄንን የቶባኮ ቅጠል በተለያየ መልኩ ለሱስ ማርኪያነት መጠቀም ከተጀመረ በርከት ያሉ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡

ነገር ግን ይህ የቶባኮ ቅጠል ከሲጋራ መልኩ ማጨስ የተጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሲሆን የሲጋራ አጫሽ ቁጥር መጨመሩም ሆነ በሲጋራ ምክንያት የሚመጡት ችግሮች መብዛታቸው በቅርቡ የመጣና እየታየ ያለ ችግር ነው፡፡ ያልተቃጠለ የቶባኮ ቅጠል በውስጡ ኒኮቲን፣ ለካንሰር የሚዳርጉ ንጥረ ነገሮችና እንዲሁም ሌሎች ለድድና ለአፍ ካንሰር የሚያጋልጡ፣ መርዛማ ኬሚካሎች ሲኖረው፣ በሚቀጣጠልባቸው ወቅት በጭስ መልክ ወደ ሳንባችን የሚላከው የኬሚካሎች ጥርቅም ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ካርቦን ሞኖኦክሳይድ እንዲሁም ሌሎች ከ4000 በላይ የሆኑ የተለያዩ ኬሚካሎች በተለያየ መልኩ ይኖረዋል፡፡ በመሰረቱ ባደጉ ሀገሮች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር እየቀነሰ ባለበት ዘመን በሀገራችን ደግሞ የሲጋራ አጫሽ ቁጥር መጨመሩ ሳይስተዋል አይታለፍም፡፡ የሲጋራ ሱስን በተመለከተ የተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች ሲኖሩ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ለሲጋራ ሱስ እንድንጋለጥ ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ የሰውነት ጂኖች ሲኖሩ እነዚህም አንዳንዶቹ በሰውነት ውስጥ የገባውን የኒኮቲን መጠን ተጣርቶ የመውጣቱን ሂደት የሚያስተጓጉሉ ሲሆኑ ሌሎች አይነቶች ደግሞ አንድ ሰው ሱሰኛ የመሆን ዕድል እንዲኖረው የሚያጋልጡ የጂን አይነቶች ናቸው፡፡ ከዚህም እንደምንረዳው አንድ ቤተሰብ ውስጥ የሲጋራ ሱሰኛ ያለ እንደሆነ በተመሳሳይ ቤተሰብ ውስጥ የሲጋራ አጫሽ የመኖር እድሉ ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ስንል ግን በመሰረቱ በዘር የመተላለፍ ሁኔታው ለዚህ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ ጂኖች መኖራቸውን እንደሚያመላክተው ሁሉ፣ በአንፃሩም ደግሞ የማህበረሰባዊ ግንኙነት እና ሌሎች የሚያደርጉትን አዲስ ነገር ከመሞከርና ከመልመድ ጋርም ተያይዞ ሊታይ ይችላል፡፡ በዚህም ሳቢያ የተሻለ ስለሱስ ግንዛቤ ሊሰጡን የሚችሉ ጥናቶች አሁንም እየተካሄዱ ነው፡፡

ሲጋራ ማጨስ ሊያስከትላቸው የሚችላቸው ችግሮች

በሀገራችን ያለው የሲጋራ አጫሽ ቁጥርና በሲጋራ ሳቢያ የሚሞተው የሰው ቁጥር በውል ባይታወቅም በአሜሪካ ውስጥ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ400,000 በላይ ሰዎች በሲጋራ ምክንያት ካለ ዕድሜያቸው ለተለያየ ችግርና ብሎም ለሞት ይጋለጣሉ፡፡ ሲጋራ ከሚያጨሱ ሰዎች ውስጥም 40 በመቶ የሚሆኑት ሲጋራ ማጨስ ያላቆሙ እንደሆነ በአፍላ ዕድሜ ለሞት ይጋለጣሉ፡፡

በሲጋራ ሳቢያ የሚመጡ ችግሮች እንደሚጨሰው የሲጋራ ብዛትና ጊዜ ይወስን እንጂ በጥቅሉ ግን ማንኛውም የሲጋራ አጫሽ ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ችግሮች ሲጋራ ከማያጨሱ ሰዎች ይልቅ የተጋለጡ ናቸው፡፡

– የአተነፋፈስ መስመር ችግሮች /Respiratory system/፡- የሲጋራ ጭስ በዋነኝነት የሚገባውና ተጣርቶ የሚወጣው በሳንባ እንደመሆኑ መጠን በአተነፋፈስ መስመሮች ላይ የሚደርሰው ጊዜያዊም ሆነ ቀጣይነት ያለው ችግር በርካታ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ሲጋራ ማጨስ ባቆመ ከ1-2 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ሁሉም ነገር ከነጭራሹ ወደ ነበረው ይመለሳል ማለት ባይቻልም ከዛ ብዙ የማይተናነስ ለውጥ ይታያል፡፡

– የልብና የደም ስሮች ችግሮች /Cardiovascular sysetem/፡- የሲጋራ አጫሾች ለልብ ድካምና ለተለያዩ የልባና የደም ስር ችግሮች የበለጠ የተጋለጡ ሲሆኑ በተለይ ደግሞ የደም ግፊት፣ የስኳር ህመምና ከፍተኛ የሰውነት ቅባት መጠን ያለባቸው ሰዎች ላይ ይህ ችግር ገኖ ይታያል፡፡ አንድ ሰው ሲጋራ ማጨስ ካቆመ በኋላ ግን እነዚህ የተለያዩ ችግሮች በተወሰነ መልኩ የመከሰት ዕድላቸው ይቀንስና ከ15 ዓመታት በኋላ ሲጋራ አጭሶ ከማያውቅ እኩል የመሆን ዕድል ሊኖረው ይችላል፡፡

– ካንሰር፡- በሲጋራ ሳቢያ ሊከተሉ የሚችሉ የካንሰር አይነቶች እጅግ በርካታ ሲሆኑ እነዚህም የአፍ፣ የላይኛው የትንፋሽ ቧንቧ፣ የሳንባ የምግብ ቧንቧ፣ የጣፍያ፣ የኩላሊት፣ እንዲሁም የሽንት ፊኛ ካንሰር በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማህፀን በር ካንሰርና የጨጓራ ካንሰር የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን የሚያመላክቱ በርካታ ጥናቶች አሉ፡፡ ሲጋራ ማጨስ ማቆምን ከመቀጠል ይልቅ ለካንሰር የመጋለጥ እድልን እጅግ ይቀንስ እንጂ ከ20 ዓመት በላይ ሲጋራ ማጨስ ባቆሙ ሰዎች ላይ ራሱ ሲጋራ አጭሰው ከማያውቁ ሰዎች ይልቅ ለካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸው የጨመረ ነው፡፡
– እርግዝና ላይ የሚያመጣው ችግር፡- ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ምንም ሲጋራ ባያጨሱ በእርግዝናው ወቅት በፅንሱ ላይ የሚታይ ችግር የለም ማለት ይቻላል፣ ነገር ግን በእርግዝና ወቅት ሲጋራ ማጨስ ለተለያዩ ከማስወረድ እስከ ቀድሞ ካለጊዜው ምጥ መምጣት የሚደርስ የእርግዝና ችግር ከማስከተሉም በላይ በተጨማሪ በጽንሱ ላይ የሚያስከትለው ችግር ከአዕምሮ ዘገምተኝነት እስከ ሞት ድረስ ሊሆን ይችላል፡፡ ከተወለደም በኋላ አካላዊ የሆነ የተዛባ አፈጣጠር ይዞ የማደግ ዕድል ሊኖረው ይችላል፡፡

– ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ዋና ዋና ይሁኑ እንጂ በተጨማሪም ደግሞ የጨጓራ ቁስለት፣ የአጥንት መሽከርከርና መሳሳት፣ የአይን ሞራ፣ ከጊዜው ቀድሞ ማረጥ፣ የቆዳ መሸብሸብና መጨማደድ፣ በሴቶች ላይ የሐሞት ጠጠር እንዲሁም በወንዶች ላይ ደግሞ ስንፈተ ወሲብ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢ ብክለት እንደማስከተሉ መጠን በአካባቢው ያለውን ሰው በመበከል እነዚህ የሁለተኛ ደረጃ አጫሾች የተባሉት ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች በከፊልም ቢሆን እንደየሁኔታው የተጋለጡ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ስናየው ግን ሲጋራ ማጨስን ከነአካቴው አለመጀመርና አጠቃላይ አለማጨስ የተሻለው አማራጭ ሆኖ ሳለ ሲጋራ የሚያጨሰውም በራሱ ላይና በህብረተሰቡ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር በማሰብ የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሞ ማቆም ተገቢ ነው፡፡ ጭስ በጨሰበት የሚታይ እሳት ብቻ ሳይሆን ልክ እንደ ሲጋራው ብዙም ሳይታይ የሚያቃጥል ብሎም የሚያጠፋ እሳት አለውና ህይወት ማጥፋቱን እያወቅን ከሲጋራ የጥፋት እሳትና የድብብቆሽ ሱስ የማርካት ፍላጎት ልንርቅ ይገባል፡፡

Previous Story

የዘ-ሐበሻ 6ኛ ዓመት የፊታችን እሁድ ጁን 15 በሚኒሶታ ይከበራል

Next Story

በጋምቤላ ክልል ጎደሬ ልዩ ስሙ ዱንቻ አማርኛ ተናጋሪ ዜጎች ተፈናቀሉ ‪

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop