በላይነህ አባተ ([email protected])
ሳይንስ የተማሪ ወይም የአንባቢ ትኩረት ከ10-15 ደቂቃ አይበልጥም [1] የሚለውን በመመርኮዝ አብዛኞቹን ጦማሮቼን ከ፪ ገፆች የማይበልጡ ለማድረግ ብሞክርም አንዳንድ አንባቢዎች አሁንም አሳጥር ይሉኛል፡፡ ከዚህ በላይ እንዴት ላሳጥር ብዬ ስጠይቃቸው “ በዚህ ዘመን ሰው ከአራትና ከአምስት መስመር በላይ ለማንበብ ትዕግስት የለውም” የሚል መልስ ይሰጡኛል፡፡ ይህ ለማንበብ ወይም ለማወቅ ትእግስት የማጣት አሳሳቢ ቀውስም ስለ ማህበረሰባዊ የማንበብ ትኩረት ማሽቆልቆል የተሰሩትን የምርምር ስራዎች እንድፈትሽ ገፋፍቶኛል፡፡
በትኩረት ዘርፍ (Attention span) ከተደረጉት ድንቅ ምርምሮችን አንዱ ኒዩ ዮርክ በሚገኘው የኮሎምቢያና ሌሎችም ዩንቨርስቲዎች ለብዙ ዘመናት የተኪያሄደው የፕሮፌሰር ግሎሪያ ማርቆስ ምርመር ነው፡፡ [2] ፕሮፌሰር ማርቆስ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ አንጡራ ትኩረት(focus) በአማካኝ ከ2 ደቂቃዎች ወደ 47 ሰከንዶች አሽቆልቁሏል ብለው እያስተማሩ ነው፡፡ በእርሳቸው አገላለጥ እነዚህ የአንጡራ ትኩረት ሰኮንዶች አንባቢ ገጥ ወይም የኮምፑተር ስክሪን ሳይቀይር የመቆየት ችሎታን ወይም አንጡራ ትኩረትን የሚለኩ ናቸው፡፡ በጥናታቸው መሰረት የአንጡራ ትኩረት አማካኙ 47 ሰከንዶች ይሁን እንጅ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝብ አንጡራ ትኩረት ከ40 ሰከንዶች በታች ነው፡፡ ይህም ማለት አብዛኛው ሕዝብ በግማሽ ደቂቃ ውስጥ ከአንዱ ወደ ሌላው ገጥ እንደ ፌንጣ እየተፈናጠረ ከገለጣቸው ገጦች ውስጥ አንድም ቁም ነገር ሳይማር ጊዜውን ያጠፋል ማለት ነው፡፡
በፕሮፌሰር ግሎሪያ ማርቆስ ግንዛቤ የትኩረት መጠን ማሽቆልቆል የጀመረው ጮሌ ስልክ (smart phone)ና የማህበራዊ ግንኙነት ሜዳዎች (A.K.A social media) በስፋት እስራ ላይ ከዋሉ በኋላ ነው፡፡ ይህ የጮሌ ስልክና የማህበራዊ ግንኙነት ሜዳዎች በማህበረሰብ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት በምርምር መረጋገጡ የበለጠ ታማኝ ያደርገዋል እንጅ ጉዳቱን በሳይንሳዊ መንገድ ያልፈተሸ አስተዋይ አንባቢም የሚገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ዘመን አብዛኛው ተምሬአለሁ የሚለው ሕዝብ እንኳን ትእግስት ኖሮት መጻሕፍትን በአንክሮ አንብቦ ሊጨርስ ተጋዜጣ አንድ ጦማር የማንበቢያ ትእግስቱንም እያጣ ነው፡፡ እንደሚታየው አብዛኛው ተማርኩ ባይ ቅጠል ቦጭቃ እንደምትበር ድንቢጥ የሚናፈስ ወሬ ከፌስ ቡክ፣ ከትዊተር፣ ከሁዋትስ አፕ፣ ከቴክስት፣ ከዩ ቲዩብ፣ ከቲክ ቶክ ወይም ስልክ ተቀብሎ ከወዲያ ወዲህ ሲያነፍስ ቀኑ ውሎና መሽቶ የሚነጋለት ነው፡፡
በመምህርነት ሙያ የተሰማራ ተገንዝቦታል ብዬ እንደምገምተው ተማሪው አስተማሪውን በማዳመጥ ፋንታ ከጮሌ ስልኩ ጋር ተጣብቆ ተፌስ ቡክ፣ ኢንስቲግራም፣ ትዊተር፣ ቴሌግራፍ፣ ቴክስት፣ ሁዋትስ አፕ ወይም ሌሎች ሜዳዎች ወሬውን ይለቅማል፤ አለዚያም አማዞን ገብቶ ሸቀጡን ሲቃርም የትምርህት ክፍለ-ጊዜው ይነጉዳል፡፡ በትምህርታዊ ውይይቶችና ሌሎችም ስብሰባዎች እንደሚታየውም አብዛኛው ተሳታፊ ትምህርት ሰጪውን ወይም ተናጋሪውን ማዳመጥ ትቶ ከጮሌ ስልኩ ጋር እንደ መዥገር ተጣብቆ ወሬ ሲለቃቅም ጊዜው እንደ አቦ ሸማኔ ይፈተለካል፡፡
ሕዝብ ከመጻሕፍት ዓለም ስለራቀና የመማር ትኩረቱ ስለዘቀጠ ማይምነትና ድንቁርና እየተስፋፉ ነው፡፡ በእኔ አስተያየት ማይም ሰው ማለት ማንበብና መጻፍ የማይችል ሳይሆን ቀደምት አባቶቻችን እንደ ሶቅራጥስ“ራስህን እወቅ” ይሉት የነበረውን የመንፈስ ልእልና ገፎ አለማወቁን እንኳ የማያውቅ የድንቁርና በሽተኛ ነው፡፡ እውቀት የሚገኘው ከማንበብ ብቻ ሳይሆን በአንክሮ ከማዳመጥ፣ ከኑሮ፣ ከባህል፣ ከሃይማኖትና ከሥራ ልምድም ነው፡፡ የጠነጠነች አገር ገንብተው ያለፉት አብዛኞቹ የጥንት አባቶቻችን ማንበብና መጻፍ የማይችሉ እንደነበሩ የሚታወቅ ነው፡፡ እነዚህን አባቶች እውቀት ይመግባቸው የነበረው በአንክሮ የማዳመጥ ችሎታቸው፣ በጥናት የያዙት ባህላቸው፣ ሃይማኖታቸውና የኑሮ ልምዳቸው እንደነበር የምናውቀው ነው፡፡ አይምሯቸው በመንፈስ ልእልና የተሞላም ስለነበር ራሳቸውን ፈትሽው የማያውቁትን አናውቅም ለማለት የማያፍሩ እንደነበሩም የሚታወቅ ነው፡፡
አሁን የምናስተውለው ግን አለማወቁን አውቆ አላውቅም የሚል ሳይሆን መሐንዲሱን ዝም አስኝቶ ስለመንገድና ህንፃ አሰራር፣ ሐኪምን ሰጥ አሰኝቶ ስለ ህክምና፣ የህግ ባለሙያውን አፉ አዘግቶ ስለሕግ ወዘተርፈ ሲያወራ ትንሽ ቅፍፍ የማይለው የመንፈስ ልእልና እንደ ውቃቢ የራቀው ከንቱ ነው፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ባለሙያ ነኝ እያለ በሚንቦጣረረው የመንፈስ ልእልና ድሀ በኩል የምናየውም ወገኑ እንደ ጫካ ሲጨፈጨፍና ሲሰደድ ደንታ የማይሰጠውና አፉን ከምግብ ተክሎ ወደ ሞት ገበያ ለመሄድ የቆረጠ መሀንዲስ፣ ሐኪም፣ ጠበቃ፣ ፋርማሲስት፣ የምጣኔ ሐብት በለሙያ፣ መምህር ወዘተርፈ ነው፡፡
በዚህ ዘመን እንኳን ሌላው “የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ነን” እያሉ የሚያላግጡትም ቅድመ አያቶቻችን ቆዳ ፍቀው ብራና ሰርተው፣ ቅጠል ቀጥቅጠውና ቀለም በጥብጠው ጥፈው ከተውልንን የሃይማኖት፣ የቅኔና የፍልስፍና መድብሎች እውቀት የሚቀስሙ ሳይሆኑ ተፌስ ቡክ፣ ትዊተርና ኢንስትግራም እንደ ብረት ምጣድ ተጥደው ውለው የሚያድሩ ናቸው፡፡ በእነዚህ ከንቱ ወሬ ከፌስ ቡክ ሲለቅሙና ከኢንሲግራም የእንስት ተክለ ቁመና ሲያደንቁ በሚሉ “የሃማኖት አባቶች” ተበዮች እንዝላልነት ሃይማኖታችንና ባህላችንም አለቦታው በበቀለ አረም ስለተወረሩ ከሃይማኖትና ከባህል የሚገኘው እውቀት እንደ በጋ ጅረት እየደረቀ ነው፡፡ ጮሌ ስልክና የማህበራዊ ሜዳዎች በክልል መዶሻ እንደ ሸክላ ተተፈረካከሰው የሃይማኖትና የአስኳላ ሥርዓተ-ትምህርት ጋር ተዳምረው እንኳን መጽሐፍ አንድ ገጥ ጦማርም የማንበብ ትእግስትና ትኩረትን ግሽልጥ አድርገው እያጠፉት ነው፡፡
የጮሌ ስልክንና ማህበራዊ ግንኙነት ሜዳዎችን ቴክኖሎጅ ፈጥረው በሐብት የናጠጡት አገሮች የእነዚህን “አገልግሎቶች” የሕብረተሰብ ጠንቆች ተመራምረው ስለደረሱባቸው ጉዳቱን ለመቀነስ እርምጃ እየወሰዱ ነው፡፡ ከዚህ በፊት “ሲጃራ ለጤና ጥሩ ነው” የሚል የማታለያ ምርምር ሰርተው በስልጣኔ ስም በፊልም ተዋንያን አማካኝነት ያስፋፉት ሱስ በአሁኑ ወቅት ይበልጥ እየጎዳ ያለው ሳይፈትሹና ሳይመረምሩ መጤ ባህልን የሚቀበሉትን አገሮች ነው፡፡ የማታ ማታ የጮሌ ስልክና የማህበራዊ ሜዳዎች ሱስም ሲያቀጭጭና ሲያኮሰምን የሚኖረው የራሱን ባህል፣ ሃይማኖትና የኑሮ ዘይቤ ትቶ ካልተፈተሸ መጤ ድፍርስ የባህል ባህር ዘሎ ገብቶ የሚማቅቅን መሰረቱን የሳተ ማህበረሰብ ነው፡፡
“በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንደሚባለው በታሪካዊ ወራሪዎች አዛዥነትና በአገር በቀል ከሀዲዎች ሎሌነት እንደ ቀንበር ተጣለብን እርኩስ ዘረኛ አገዛዝ በተጨማሪ ጮሌ-ስልክና የማህበራዊ ግንኙነት ሜዳዎች ተቅደመ- አያቶቻችንን የወረስነውን የመንፈስ ልእልና፣ እውቅት፣ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቁምነገረኝትና ትኩረት አሳጥተው ማይምነትና ድንቁርናን እያስፋፉ ነው፡። ይኸንን በአሁኑም ሆነ በቀጣዩ ትውልድ የወደቀውን ከባድ አደጋ ለመቅረፍ በእኔ አስተያየት ቢያንስ የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡
፩. ኢትዮጵያ ከመላው አፍሪካ፣ ኤሺያና ላቲን አሜሪካ በተለዬ መልኩ ነፃነቷንና የመንፈስ ልእዋላዊነቷን ጠብቃ የኖረቸው ከሌሎች የበለጠና የረቀቀ የጦር መሳሪያ ኖሯት ሳይሆን እጅግ የጠንከረ መንፈሳዊ ሐብት (ሃይማኖት፣ ባህል፣ የመንፈስ ልእልናና ረጅም ታሪክ) ስለነበራት መሆኑን በሚገባ መርምሮ መረዳት፡-
፪. አቡነ ቴዎፍሎስና መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ይሉት እንደነበረው በባዶ ራስ-ቅል የውጭን ትምህርት፣ የሃይማኖትና የባህል አተላ እንደ በግ ቅልጥም ምጎ እንደ ሰካራም ከመደናበር በፊት የራሳችንን የእውቀት፣ የሃይማኖትና የባህል መድብል በሚገባ መርምሮና አውቆ በራስ የመተማመንን መንፈስ መገንባት፡-
፫. ከቁስ አካላዊ ይልቅ መንፈሳዊ ሐብት እጅግ የበለጠ ጠቃሚና የተቀደስ ሐብት መሆኑን በመረዳት ለብዙ ሺ ዘመናት የዳበረውን የራስን መንፈሳዊ ሐብት እንደ ጃኖ መልበስና ይኸንን ጃኖ አስወልቆ ራቁት ለማስቀረት የሚመጣውን ሰይጣናዊ ኃይል ሁሉ እንደ ቅድመ አያቶች በጥኑ መታገል፡-
፬. እንደ ቅድመ አያቶቻችን ሁሉ ዘርፎ ወይም አታሎ በወረቅ ያሸበረቀን ደንደሳም ተጠይፈን በእውቀት ለከበረ ኮስማና ክብር መስጠት፡-
፭. እውቀትን ለመገብየትና ለትውልድ ለማስተላለፍ ቆዳ ገሽልጠው፣ ብራና ፍቀው፣ ቅጠል ቀጥቅጠው፣ ቀለም በጥብጠው በቁም ጽሑፍ የሃማኖት፣ የፍልስፍና የእውቀት መድብል ትተውን ያለፉትን ቅደመ አያቶች ፈለግ ተከትሎ ለትምህርትና ለእውቀት ትኩረት በመስጠት ማዳመጥን፣ ማንበብን፣ መጻፍንና ማስተማርን መውደድ፡-
፮. ጊዜ ህይወት ነውና ጊዜን ከጮሌ-ስልክ ጋር ተጣብቆ በማህበረሰባዊ ግንኙነት ሜዳዎች ወሬ በማናፈስ ወይም የእውቀት መሰረት የሌለው ባዶ አስተያየት በመወሽከት ከማሳለፍ መቆጠብ፡-
፯. ተመሬት የወጣ ወርቅን ትቢያውን አጥበን እንደምንጠቀምበት ሁሉ ተውጪ የመጡትን ጮሌ ስልክና የማህበረሰባዊ ግንኙነት ሜዳዎችም ተሸክመውት የሚመጡትን እድፍ በእንዶድ፣ በአመድና በሳሙና ፍንትው አድርገን አጥበን ራሳችንን፣ ቤተሰባችንንና አገራችንን ተማይምነትና ተድንቁርና መከላክል፡፡
አመሰግናለሁ፡፡
ዋቢ
- Neil Bradbury, Attention span during lectures: 8 seconds, 10 minutes, or more?Attention span during lectures: 8 seconds, 10 minutes, or more? | Advances in Physiology Education
- Gloria Marks, Attention Span: A Groundbreaking Way to Restore Balance, Happiness and Productivity Hardcover – January 10, 2023
ህዳር ሁለት ሺ አስራ ሰባት ዓ.ም.
ድሮ ልጅ እያለን መናኙ መነኩሴ ከተማ ገብተው ጆሮ ያለው ይስማ የዓለም ፍጻሜ በደጅ ነው እያሉ በአደባባይ ሲጮሁ ልጅ ሆነን ጠጋ ብለን ስናዳምጥ ሰማህ አለኝ ስለሺ ደበሌ ከጎኔ በጣቶቹ ጎኔን እየጎሸመ እውቀት ይበዛል አሉ እኮ መማር አይስፈልግም አለኝ። አይ ይሄ የእኛን ት/ቤት አይጨምርም እንዳልኩት ትዝ ይለኛል። ዛሬ ስለሺ ደበሌ የት እንዳለ አላውቅም። ይሁን እንጂ ሰው ከእንስሳ መጣ የሚሉን ጅሎች ዛሬ ያለንበትን ባይመለከቱ ነው፡፡ ቢያዪ ኑሮ ስሌታቸውን ደግመው ያጤኑት ነበር። ያለንበት ዘመን ሰው ከሰውነት ወደ እንስሳነት የተቀየረበት ጊዜ ነውና። ቆሞና ተቀምጣ የሸናው/ችው ጾታ የለንም የሚሉበት፤ ልክ እንደ ጆርጅ ኦርዌሉ እይታ ባርነት ነጻነት፤ ነጻነት ባርነት የሆነበት እንዳለንበት ዘመን ያለ ያለፈ ጊዜ ተመዝግቦ አላየንም።
ስልጣኔው መሰይጠን ሆኖ ሰውን ጭካኔ እያላበሰው ሶፋ ላይ ተቀምጦ በማያውቀው ሃገርና ህዝብ ላይ እሳት የሚያዘንብበት ይህ አረመኔ ጊዜ ትውልድን የቁስ አካል ተገዥ በማድረግ ስልካቸውን አቅፈው የሚተኙ፤ በቪዲዪ ጫወታ ጭንቅላታቸው ተወስዶ ቀንና ሳምንቱን ለይተው የማያውቁ እየሆኑ እንደሆነ አይናችን እያየ ነው። መብትና ስልጣኔ ያለ ገደብ ገዳዪች መሆናቸውን የዓለም መንግስታት የገባቸው አይመስልም። ወጣቱ ቲክቶክና በፌስቡክ ላይ ተጥዶ እየዋለ ማንበብና መጻፉ ሁሉ ተረስቶት የድህረ ገጽ አማካሪዎችን እርዳታ እንደሚሻ አፍጠን እያየን ነው። በቴክኒክና በቀለም በተነከረ ውበት ልባቸው ዝሎ ትንፋሽ አተው እውን ነው በማለት እንቅልፍ የሚያጡ ወይም ተዋንያኖችን ለመመሰል እየቃጣቸው የሚይዙትና የሚጨብጡት እያጡ ድንገት ዛሩ እንደተነሳበት ቃልቻ ሲፈራገጡ ማየት ወቸው ጉድ አስብሎ አፍን አስከፍቶ የሚባል ያሳጣል።
የሰዎችን ባህሪና እይታ ቀምሮ ስምና አድራሻቸውን ገቢያ የሚያወጣው የኢንተርኔት አገልግሎት ዛሬ ላይ ያም አልበቃ ብሏቸው የሰውን ዲንኤ፤ አረማመድ፤ድምጽና የፊት ገጽታውን በመጨመር ማን ማን መሆኑን ለይተውና አበጥረው ያውቃሉ። በክፉም በደጉም ሰው የሚመዘነው በጉልጉል የፍለጋ ውጤት በመሆኑ ነገሩ ውሸትም ሆነ እውነት ወሬው እየተናፈሰ የስንቱ ቤት እንደፈረሰ ቤቱ ይቁጠረው። አሁን ደግሞ ይባስ ተብሎ ኤ አይ በነበረው ክምር ዳታና አዲስ እየጨመረ የሰውን እሳቤ ቀድሞ ፈጣሪን ተፈጣሪ ለማድረግ እየተውዘገዘገ ይገኛል። የሰው ልጅ ግን ተማረም አልተማረም ጅል ነው። ቢበዛ 70 ዓመት ለማይሞላው ምድራዊ ኑሮ ስንቱን አተራምሶ ራሱም ታምሶ ያልፋል። ይህም ለገባው ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው። ከላይ መናኙ የዓለም ፍጻሜ ቀርቧል ብለው ከሰበኩ ቆየ። ዓለማችን ግን እየተንገዳገደችና ወድቃ እየተነሳች እልፎችን እየገደለችና እያስለቀሰች አሁንም አለች። ግን ፍጻሜዋ ቅርብ ነው። የዓለም ፍጻሜ ከሰማይ በሚመጣ ሃይል ሳይሆን እኛው ራሳችን በሰራነው ሥራ ስንፈርስ ስንጠፋ ጭላንጭሉ ዛሬ ላይ ይታየኛል። የሶሻል ሚዲያውና የሌላውም ማህበራዊና ግብረገባዊ ውድቀት የውድቀታችን ዋዜማው ነው። መከራን የማያውቅ ትውልድ፤ ለሞት ቅርብ ነው። የኢንተርኔትና የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀምም ለቤተሰብ መጠበቂያ እንደሚገዙት መሳሪያ ነው። አጠቃቀሙን ለይተውና ጠንቅቀው ካላወቁ የራስ መሳሪያም ለራስ ማጥፊያ ይሆናል። ግን ወደ እማንመለስበት ጎዳና ስለገባን ዓለማችን ከጥፋት አትድንም።