ጥለሽ – ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

በአለማችን መንግሥታትን በሀይል ለመጣል የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ድርጅቶችን የማወዳደር ፍላጎት ቢኖረን ለመሆኑ ህ.ወ.ሀ.ት ማንን ሊመስል ይችላል?

ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሀ.ት) ራሱን ካልሆነ በስተቀር ማንንም አይመስልም፡፡ በአለማችን ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ጨካኝና መሰሪ ቡድን ነው፡፡

ይህ ለማለት ያህል ብቻ የተባለ ነገር አይደለም የጭካኔውን ጥግ ለማሳየት ብዙ፣ እጅግ በጣም ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ አይገድም፡፡

ለምሳሌ ወልቃሂት-ጠገዴ  ውስጥ ህያዋንን በቁማቸው መቅበሩ ሳያንሰው አፈር እንዳይለብስ ሆነ ተብሎ ከመሬት በላይ እንዲቀር በተተወው የራስ ቅላቸው ላይ ጨው አምጥቶ በመነስነስ በአካባቢው ለግጦሽ የተሰማሩ የቀንድ ከብቶች የአሞሌ ጨው መስሏቸው እንዲልሱትና እንዲቆረጥሙት ፈቅዷል፡፡

በአገር ከሀዲነት ተነሳስቶ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ድንገት የከፈተውን ጥቃት ተከትሎ በጁ የገቡትን ምርኮኞች አፍኖ እየነዳ ወደመንገድ በማስገባት አይናቸው እያየ በላያቸው ላይ የሲኖ-ትራክ መኪና እንዲነዳባቸው አድርጓል፡፡

መቀሌ ላይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ባልደረባ የነበረውንና የራሴ ወገን ነው የሚለውን ወጣት መሀንዲስ አፍኖ ከወሰደውና ደብድቦ በግፍ ከገደለው በኋላ አስከሬኑን ከተቀበረበት አውጥቶ በዱር አውሬ እንዲበላ አድርጓል፡፡

በሕግ ማስከበር ዘመቻው በተደቆሰ ማግስት በየዋሻው ሲንከራተት ከሰነባበተ በኋላ መንግሥት ለሰብኣዊነት ሲል በተናጠል የወሰደውን የተኩስ ማቆም እርምጃ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም እንደገና ለማንሰራራት የሞከረው ወራሪ ጉጅሌ እስከመሃል የአማራ ክልል ዘልቆ በገባበት ወቅት በነፋስ መውጫ ከተማ ባልና ሚስቱን አቶ ደሴንና ወ/ሮ ገነትን በጭካኔ አርዶ በአጠገባቸው ያገኘውን የሁለት ዓመት ህጻን ልጃቸውን በደም እንደተነከረ በወላጆቹ አስከሬኖች መካከል ጥሎት ሄዷል፡፡

ይህ ቡድን ነሀሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም በደመ-ነፍስ ከርቀት የወረወረው ከባድ መሳሪያ ደብረ-ታቦር ከተማ ውስጥ የእድሜ ባለጸጋ በሆኑት በአቶ ድረስ ነጋ መኖሪያ ቤት ላይ በማረፉ የአምስት ቤተ-ሰብ አባሎቻቸውን ህይወት ነጥቆ አዛውንቱን ብቻቸውን አስቀርቷቸዋል፡፡

ተመሳሳይ ዱላ ባረፈባት በሰሜናዊቷ የአዲ-አርቃይ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አገሬ መኮንን በአንድ ጊዜ እስከስድስት የሚደርሱ ቤተ-ሰቦቻቸውን በከባድ መሳሪያ ድብደባ ማጣታቸው ሳያንስ የሰለባዎቹን አስከሬን አንስተው እንዲቀብሩ እንኳ ስላልተፈቀደላቸው ፍጹም በተሰበረ ልብ ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ ተመልክተን ክፉኛ ተሸማቀናል፡፡

ወራሪውና አረመኔው ቡድን እንደመርሳ ባሉና ለአጭር ጊዜም ቢሆን ዱካው አርፎባቸው በቆዩት የሰሜን ወሎ ከተሞች ከመሰረታዊ የጤና ሕግጋት ውጭ ምንነቱ ያልተረጋገጠ መርፌ እየወጋ ዜጎቻችን እንዲኮላሹ ወይም በተፈጥሮ እንዳይራቡ ያለውን ብርቱ ፍላጎት ለአለም ይፋ አድርጓል፡፡

በርግጥ የወንጀሉ ዝርዝር ማለቂያ የለውም፡፡

ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህ.ወ.ሀ.ት በተሰኘው የትግርኛ ቋንቋ የአህጽሮት መጠሪያው ይበልጥ የሚታወቅ ቢሆንም ይኸው ወደአማርኛ ልሳን ሲመለስ ት.ህ.ነ.ግ ይሰኛል፡፡ እኔም በዚህ መጣጥፍ ውስጥ ቡድኑን ት.ህ.ነ.ግ እያልኩት እስከመጨረሻው ብዘልቅ እመርጣለሁ፡፡

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ት.ህ.ነ.ግ) ገና ከጠዋቱ ደደቢት በረሃ ላይ የተጸነሰ፣ በሕገወጥ መንገድ የተቋቋመ፣ ይህ ቀረሽ ሳይባል ከመሃል አገር እየዘረፈ ባግበሰበሰው ሀብትና ንብረት ራሱን ያደለበና እስከአፍንጫው ድረስ የታጠቀ ብቻ ሳይሆን አመሻሹ ላይ ደግሞ ቢዘገይም እንኳን ሆነ በሚያስብል እርምጃ በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት በሽብርተኛ ድርጅትነት የተፈረጀ አደገኛና ተሳዳጅ የወሮበሎች ቡድን ነው፡፡

ይህ የአረመኔዎች ስብስብ ወታደራዊውን የደርግ አገዛዝ ከሌሎች የጊዜው ተነቃናቂ ሀይሎች ጋር በማስወገድ ስም ለ17 ዓመታት ሲታገልና ሲያታግል እንደቆየ በአታካች ቱሪናፋው አበክሮ ቢያደክመንም በመጨረሻዋ የምጥና የጭንቀት ሳኣት በሻቢኣ ትከሻ ታዝሎ ሳያስበው አዲስ አበባ ደርሶ አፍሪካዊቷን መዲና በመዳፉ ስር ካስገባ በኋላ ማእከላዊ መንግሥቱን በመቆጣጠር ሀገሪቱን ለ27 ዓመታት ያህል ያለአንዳች ተቀናቃኝ እስከመግዛት ደርሶ ነበር፡፡

እንዲያም ሆኖ ታዲያ ለግማሽ ክፍለ-ዘመን ያህል አገልድሞት የኖረውን የአንድ ጠባብ አካባቢ ነጻ አውጪነት ጭንብል መንግሥት ነኝ ካለ በኋላ እንኳ በቀላሉ ለማውለቅና ማንነቱን በአደባባይ ለማሳየት የሚያፍር ግብዝና ይሉኝታቢስ ሀይል እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

መፍቀሬ-ሥልጣን ወይስ አፍቃሬ-ህዝብ?

በመሰረቱ ት.ህ.ነ.ግ የቱንም ያህል ሲምልና ሲገዘት ቢኖር በተፈጥሮው የለየለት መፍቀሬ ሥልጣን እንጂ አፍቃሬ-ህዝብ ሆኖ አያውቅም፡፡

ይልቁንም ትግራይ መሬት ላይ በቅሎ የዚያን ኩሩ ህዝብ ትኩስ ደም እድሜ-ልኩን እየጠጣ ለእርጅና ዘመን የበቃው ይህ የክፉዎች ቡድን እንደሰም አቅልጦና እንደብረት ቀጥቅጦ እየገዛት ለነበረችው መላዋ ኢትዮጵያ ይቅርና ለራሱ ለትግራይ ህዝብም ቢሆን ቅንጣት ታህል ፍቅርና አክብሮት ኖሮት አያውቅም፡፡

አማራንና የአማርኛ ቋንቋን የማግለል አባዜ

በብሔራዊ ማንነቱና በሚናገረው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ አንድን ህዝብ መርጦ በመጥላትና አምርሮ በማጠልሸት የቆረበ የሚመስለው ይህ ጠባብ ቡድን ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ ለአማራ ህዝብና ለአማርኛ ቋንቋ ያለው የመረረ ጥላቻ እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡

ይህንኑ በሚገባ ለማረጋገጥ አንድ ነጠላ ምሳሌ ብቻ ለአብነት ላንሳ መሰለኝ፡፡

የደርግ አገዛዝ እንደወደቀ በአማጽያኑ ፈሊጣዊ አነጋገር የአዲስ አበባው የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ጉባኤ ተጠርቶ ነበር፡፡ ይኸው ጉባኤ ተካሂዶ እንደተጠናቀቀ ታዲያ ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም አንስቶ ከሁለት ወራት ለማይበልጥ ጊዜ በሥልጣን ላይ የቆየው የጉልበተኞቹ ጊዜያዊ አስተዳደር ለይስሙላም ቢሆን በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አጋፋሪነት በተመሰረተው የሽግግር መንግሥት መተካት ነበረበት፡፡

ያኔ ነበር በ1980 ዓ.ም የታወጀውና ለአጭር ጊዜም ቢሆን በሀገሪቱ ጸንቶ ሲሰራበት የቆየው የኢትዮጵያ ህዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ (ኢ.ህ.ዴ.ሪ) ሕገ-መንግሥት ታግዶ በአዲስ እስኪተካ ድረስ መለስ ዜናዊ ጫት እየቃመ በምርቃና ያረቀቀውና ራሱ መለስ ዜናዊ ቡራኬ የሰጠበት የሽግግር ወቅት ቻርተር ቁጥር 1/1983 ዓ.ም የጸደቀው፡፡

በመሰረቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ በፓርላማም ሆነ በሕግ አስፈጻሚ አካሎቿ አማካኝነት የምታወጣቸው ሕጎችና የማስፈጸሚያ ደንቦች ሁሉ አስገዳጅ ሆነው በስራ ላይ እንዲውሉ ከመደረጋቸው በፊት በነጋሪት ጋዜጣ፣ (ከ1987 ዐዓ.ም ወዲህ ፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ እያልን ነው የምንጠራው)፣ በሁለቱም ቋንቋዎች፣ ማለትም በአማርኛና በእንግሊዘኛ  ቋንቋዎች በትይዩ እየታተሙ ለተጠቃሚው ህዝብ ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ሕግ ያዛል፡፡ ይህ አሰራር ራሱ ነጋሪት ጋዜጣችን እንደአንድ ተቋም እውቅና ተሰጥቶት በአዋጅ ከተመሰረተበት ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ ሳይቋረጥ የቀጠለ መሆኑን እዚህ ላይ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡

ወታደራዊው አገዛዝ በተሸኘ ማግስት በነጋሪት ጋዜጣ 50ኛ ዓመት ቁጥር 1 ላይ፣ ሀምሌ 15 ቀን 1983 ዓ.ም) የታተመው የሽግግር ወቅት ቻርተር ግን በአንቀጽ 19 ላይ የሚከተሉትን ያልተለመዱ ባለሁለት ዘለላ ድንጋጌዎች በንቃት አስፍሯል፡-

“ይህ ቻርተር የተጻፈባቸው የአማርኛና የእንግሊዘኛ ቋንቋ ቅጅዎች እኩል ሕጋዊ ተቀባይነት አላቸው”፡፡

“በሁለቱ ቋንቋዎች መካከል አለመጣጣም የተፈጠረ እንደሆነ ግን የተወካዮች ምክር ቤት ይወስናል”፡፡

እንግዲህ በሆነ አጋጣሚ አማርኛ በሐገሪቱ የመንግሥት ስራ ማከናወኛ፣ ይልቁንም ሕገ-መንግሥቱን ጨምሮ የብሔራዊ ሕጎቿ ኦፊሴላዊ ማተሚያና ማሳወቂያ ቋንቋ ሆኖ ለረዥም ጊዜ ሲሰራበት መቆየቱ ክፉኛ ያበገነው የወያኔ ፊት-አውራሪ በዚህ ኩነት እንኳ ምን ያህል እንደተበሳጨና የበታችነት ስሜት ይሰማው እንደነበር አይነተኛ ማረጋገጫ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

ለዚህ ነው፣ መሰርዩ መሪያችን ብጽኣይ መለስ ከዚያ በፊት ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ የጋራ መኩሪያችን የሆነውን የሀገሪቱን የስራ ቋንቋ ለአለም-አቀፍ ግንኙነቶች መሳለጥ ስንል እናት አገራችንን ኢትዮጵያን ባያጠቃልልም ከባእዳኑ የአፍሪካ ቅኝ ገዢዎች ተውሰን በሁለተኛ ደረጃ የመግባቢያ ቋንቋነት ከምንገለገልበት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጋር እኩል መሆን አለበት ሲል ከፍተኛ ንቀት በተመላበት ደባና ተንኮል ተሟግቶ ያስደነገገልን፡፡

ሰውየው ከዚያም እላፊ ሄዶ በሁለቱ ቋንቋዎች በተጻፉት የቻርተሩ ድንጋጌዎች መካከል የትርጉም መዛባት ወይም አንዳች አይነት አለመጣጣም ከተፈጠረ በአገርኛው ቋንቋ ተጽፎ የተገኘው የአማርኛ ቅጅ የበላይ መሆኑ ቀርቶ ሁለቱም ቋንቋዎች እኩል ተቀባይነት ያላቸው ከመሆኑ የተነሳ በዚሁ ሳቢያ የተፈጠረው ቴክኒካዊ አለመግባባት መለስ ወዳቋቋመው አሻም-ጉልት የተወካዮች ምክር ቤት ተመርቶ እርሱ ብቻ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ነበር የተደነገገልን፡፡

ደግነቱ የሽግግር ወቅቱ ተጠናቀቀና ሀገሪቱ በጊዜያዊነት ስትተዳደርበት የነበረው ቻርተር ተሽሮ በ1987ቱ የኢ.ፌ.ደ.ሪ ሕገ-መንግሥት ሲተካ አቶ መለስን በውል ገብቶት ይሁን በሁኔታዎች ተገፍቶ ያድርገው ባይታወቅም ወደነበርንበት ተመልሰናል፡፡ እንዲያ በመሆኑም በስራ ላይ ባለው ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 106 ስር እንደተጻፈው የሀገሪቱ ሕጎችና ደንቦች ዛሬም እንደወትሮው በፌደራሉ መንግሥት ነጋሪት ጋዜጣ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች በትይዩ እየተሰናዱ መታተማቸው የቀጠለ ሲሆን በሁለቱ ቅጂዎች መካከል አለመጣጣም የተፈጠረ እንደሆነ ግን የአማርኛው ቅጅ የበላይነት እንዲኖረውና የመጨረሻ ተቀባይነት እንዲያገኝ ተብሎ መደንገጉን እንገነዘባለን፡፡

ጦርነቱ ‘ህዝባዊ’ ነውን?

እነሆ በወራሪው ት.ህ.ነ.ግና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል በአሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ ያለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ራስን ከጥፋት የመታደግና ህልውናን የማረጋገጥ መሆኑ አይካድም፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶች ደጋግመው እንደሚናገሩት ከወራሪዎቻችን አንጻር በአንድና በተመሳሳይ ጊዜ በበርካታ ግንባሮች የተከፈተብን ጥቃት ‘ህዝባዊ ጦርነት’ ሊባል ከቶ አይገባውም፡፡

ቀድሞ ነገር እነደብረ-ጽዮን ባልተገራው አንደበታቸው ጠዋት ማታ ሲያላዝኑ እንደምንሰማው ሰብኣዊ ማእበል እየተጠቀሙ ኋላቀርና አስከፊ ውጊያዎችን ማካሄድ አንድን ጦርነት ‘ህዝባዊ’ ሊያሰኘው ከቶ አይችልም፡፡ ይህ እንዲያውም ጨዋነት የተመላበት አባባል ካለመሆኑም በላይ አረዳዱ የተሳሳተ ነውና በአፋጣኝ ሊታረም ይገባል፡፡

የወራሪው ቡድን መሪዎችና ያልሠለጠኑ አፈ-ቀላጤዎቻቸው ለአካለ-መጠን ያልደረሱ ልጆችን እየማገዱ እነርሱ ከርቀት ሆነው የሚሞቁትን እሳት አይናቸውን በጨው አጥበው ህዝባዊ ጦርነት ነው በማለት ሊያሽሞነሙኑት ቢሞክሩ አንዳች ሀፍረት ስለማይሰማቸው እምብዛም ላይገርመን ይችል ይሆናል፡፡ እኛ ግን የነዚያኑ ደናቁርት አባባል እንደወረደ እየተቀበልን ከማስተጋባታችን በፊት ሁለት ጊዜ ማሰብ ይኖርብናል፡፡

ማንም በቀላሉ እንደሚረዳው እነርሱ ሊያስደነግጡንና ሊያስበረግጉን የሞከሩትና የሚሞክሩት ራሳቸውን በ’ሰብአዊ ጋሻ’ ስር ሸጉጠውና በአለም-አቀፍ ሕግ የተከለከለ አድራጎት መሆኑን እያወቁ እድሜያቸው ለውጊያ ያልደረሰ ለጋና ታዳጊ ብላቴናዎችን በማሰለፍ አንደኛው ዙር ሰብኣዊ ማእበል በነበልባሉ ብቻ እየወደቀ ተበልቶ ሲያልቅ ሌላውን ዙር ያለእረፍት ወዲያውኑ እየጨመሩ ርህራሄ በጎደለው አኳኋን የእሳት ራት በማድረግና አከታትሎ በማስጨረስ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

እኛ ግን የምናደርገው ይህንን አይደለም፡፡ በህልውናችን ላይ የተቃጣውን አስከፊ የጠላት ወረራ ለመቀልበስና አመቺ ሆኖ ባገኘነው በየትኛውም ዘዴ ሁሉ ተጠቅመን ራሳችንን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብት እንዳለን ጠንቅቀን ብናውቅም ጦርነትን ከጦርነት ሕግ ውጭ ያካሄድንበት ጊዜና አጋጣሚ የለም፣ አናካሂድምም፡፡

መላው ህዝባችን ቀፎው እንደተነካበት ንብ በቁጣ ወጥቶ ራሱን እንዲከላከል የክተት ጥሪ ብናውጅም እናቶችንና ህጻናትን በሰብኣዊ ጋሻነት ተጠቅመንና እነርሱን ወደፊት አስቀድመን አልተዋጋንም፣ አንዋጋምም፡፡

ለወታደራዊ ግዳጅ እንዲመለመሉና በጦርነት እንዲሳተፉ ያልተፈቀደላቸውን እንቦቃቅላ ህጻናትና ነፍሰ-ጡር ሴቶች ኀላፊነት በጎደለው መንገድ በስፋት እያሰለፍን የጥይት ማብረጃዎች እንዲሆኑ በማስገደድ አናስጨርስም፤ ትውልዱንም አናመክንም፡፡

ምንም ቢሆን ጦርነት ነውና እጃችን ላይ የወደቁ የጠላት ምርኮኞችን ተቀብለን ሕግ በሚያዘው መሰረት አቅማችን የፈቀደውን ያህል ተገቢ አያያዝና እንክብካቤ እናደርግላቸው እንደሆነ ነው እንጂ ሰብእናቸውን በሚጎዳ ሁኔታ በአደባባይ አሰልፈን አናዋርዳቸውም፣ አንዘባበትባቸውም፡፡

የት.ህ.ነ..ግ አማጽያን ግን ከዚህ በተቃራኒው ማይካድራን በጋሊኮማ፣ ጋሊኮማን ደግሞ በአጋምሳ እየደገሙና እየደጋገሙ በጦርነቱ ውስጥ አንዳች ተሳትፎ ያልነበራቸውን ንጹሃን ወገኖች ሳይቀር በጭካኔ እያረዱ በአደባባይ ሲጨፍሩ መላው አለም በአንክሮ ተመልክቷቸዋል፡፡ ሆኖም አለም-አቀፉ ሕብረተ-ሰብ  ለዚህ አይነቱ አረመኔያዊና ኢ-ሰብአዊ ድርጊታቸው አይቶ እንዳላዩ ከማለፍ በስተቀር እስካሁን የሰጠው ምላሽ በጣም ቀዝቃዛና የተቆጠበ ሆኖ ታዝበነዋል፡፡

በመሰረቱ ሉአላዊ መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ እንደት.ህ.ነ.ግ ያሉ ታጣቂ ቡድኖች ጭምር በየትኛውም የግጭት ደረጃ ቢሆን እድሜያቸው ገና ለጋ ከመሆኑ የተነሳ አካላቸው ያልጠነከረና አእምሯቸው ያልጎለመሰ ታዳጊ ልጆችን ለውትድርና እንዳይመለምሉና በጦርነት እንዳያሳትፉ የተከለከለ ስለመሆኑ አለም-አቀፉን የህጻናት መብቶች ጥበቃ ስምምነት ለማሟላት የተ.መ.ድ ጠቅላላ ጉባኤ በ54ኛ መደበኛ ስብሰባው እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በሜይ 25 ቀን 2000 ዓ.ም መክሮ በውሳኔ ቁጥር 54/263 አማካኝነት ያጸደቀው አማራጭ ፕሮቶኮል በአንቀጽ 4 ንኡስ አንቀጽ (1) ስር ይደነግጋል፡፡

ምን ይሄ ብቻ፡፡

በሠላማዊ ህዝብ ላይ ስለሚፈጸም ወንጀል በብሔራዊ ደረጃ የሚደነግገው የኢ.ፌ.ደ.ሪ የወንጀል ሕግ ነው፡፡ ይኸው ሕግ በአንቀጽ 270 ፊደል ተራ ቁጥር ኀ) ስር ደንግጎት እንደምናገኘው “ማንም ሰው በጦርነት፣ በጦርነት ግጭት ወይም በጠላት ወረራ ጊዜ የአለም-አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎችንና የአለም-አቀፍ የሰብኣዊነት ሕግጋትን በመጣስ በሠላማዊ ህዝብ ላይ ቡዳት ለማድረስ በማደራጀት፣ በማዘዝ ወይም ድርጊቱን በመፈጸም ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ” “እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ወደጦርነት ገብተው እንዲሳተፉ ለማድረግ ለወታደራዊ አገልግሎት አባልነት የመለመለ እንደሆነ” “ከአምስት ዓመት እስከሀያ አምስት ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑእ እስራት፣ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ በእድሜ-ልክ ጽኑእ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል”፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ መላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ከብዙዎች በቀደመ መጠሪያ ስሟ ኢትዮጵያ በምትሰኝ ነጻና ሉኣላዊ አገር ውስጥ የምንኖር ኩሩና የራሳችን ፖለቲካዊ ህልውና ያለን ህዝብ ነን፡፡ የፈለገው አይነት የራሱ የሆኑ ህጸጾች  ይኑሩበት መንግሥታችንም ቢሆን ከነጉድለቶቹ ሕጋዊ ሰውነትና አለም-አቀፋዊ እውቅና የተቸረው መንግሥት እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

“አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” ሆኖበት ነው እንጂ በአንጻሩ ወራሪው ት.ህ.ነ.ግ ግን እንደአንድ ክልላዊ መንግሥት ይቅርና እንደፖለቲካ ቡድንም ቢሆን እንዲፈርስ አስቀድሞ የተወሰነበት ብቻ ሳይሆን በአሸባሪነት የተሰየመ ተሳዳጅ ጉጅሌ መሆኑን አለም በሚገባ ይረዳል፡፡

እንግዲህ እነሳማንታ ፓዎርና እነአንቶኒዮ ጉተሬሽ “በመካሄድ ላይ ባለው የሰሜኑ ጦርነት የተጠመዳችሁ ተፋላሚ ወገኖች ሁሉ ግጭቱን በአስቸኳይ አቁማችሁ ያለአንዳች ቅድመ-ሁኔታ በጠረጴዛ ዙሪያ ለሠላማዊ ድርድር ተቀመጡ” የሚሉን ይህንኑ መሪርና ያፈጠጠ ሀቅ ልቦናቸው እያወቀው መሆኑን ይታዘቧል፡፡

“ዎይ ነዶ” አሉ ነጋድራስ ለጥ ይበሉ፡፡

ለመረዳት አዳግቶን የሰነበተው የጦር ሜዳ ውሎ ጉራማይሌ

ታሪክን የኋሊት ስንመረምር በመንግሥታትና በተገዳዳሪ ቡድኖች መካከል በርካታ ግጭቶች ተካሂደው ያውቃሉ፡፡ በተለይ በድህረ-ቅኝ አገዛዝ አፍሪካ ውስጥ ይህ አይነቱ የመንግሥት ሥልጣንን በሀይል ለመጨበጥ የሚካሄድ ደም አፋሳሽ ግብግብ ያን ያህል ያልተለመደ ነገር አይደለም፡፡

ይሁን እንጂ በሥልጣን ላይ ባለ አንድ ማእከላዊ ወይም ክልላዊ መንግሥት ስም የተሰለፈ ሰራዊት እንደክላሽኒኮቭ ባሉ ቀላልና የነፍስ-ወከፍ ጦር መሳሪያዎች ራሱን ለመከላከል ሲሟሟት እየታየ በደፈጣ ተዋጊዎች ቅርጽ ተደራጅተው ለወረራ የሚንቀሳቀሱ የዱር አማጽያን በተቃራኒው ዘመናዊ ታንክ፣ ሞርታርና ዙ 23ን የመሳሰሉትን ከባድ የጦር መሳሪያዎች እየተጠቀሙ ጥቃት ሲፈጽሙ የተስተዋለበትን ጊዜና አጋጣሚ አይተንም ሆነ ሰምተን አናውቅም፡፡

እንግዲህ የፌደራሉ መንግሥት የጥቅምቱን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ፍጻሜ በይፋ ካወጀ በኋላ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ትግራይን በፖለቲካዊ ውሳኔ ለቆ የመውጣቱን የተናጠል እርምጃ እንደወሰደ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ሲካሄዱ የሰነበቱት የጦር ሜዳ ፍልሚያዎቻችን በመጠኑም ቢሆን ሚዛናቸው የተዛባ መስሎ የታየው በዚህ አይነቱ የሀይል አለመመጣጠን እንደነበር አንድና ሁለት የለውም፡፡

ጻድቃንና ተዋጊ ጀሌዎቹ

በአንድ አገር እጅግ በጣም ከተከበረ ጠቅላይ የታማጆር ሹምነት ማማ ወደዱር ሽፍቶች ንቅናቄ መሪነት ቁልቁል ተምዘግዝጎ እንጦርጦስ የወረደው ጻድቃን ገብረ-ትንሳኤ በትግራይ መከላከያ ሀይል ስም ያደራጀውና ለዝርፊያ ያሰማራው ሰራዊት በወራሪ የአንበጣ መንጋ ሊመሰል ይችላል፡፡ ግር ብሎ ይመጣና በሰፈረበት ቦታ ያረፈበትን ወይም ያጋጠመውን ሁሉ እምሽክ አድርጎ ያጭዳል፣ የበላውን በልቶ የቀረውን ያለምህረት ያወድማል፡፡

ገዳይ መርዝ ሲረጭበት ግን ለወሬ ነጋሪ እንኳ እንዳይተርፍ ሆኖ የጠፋ ይመስልና በአንድ ጊዜ ተበታትኖ ለአይን እይታ እንኳ ይሰወራል፡፡ ያም ሆኖ ታዲያ ያልተቋረጠ ክትትል ካልተደረገበት በስተቀር ተደመሰሰ ሲባል ከየተደበቀበት ጥሻ ይወጣና እንደአዲስ ወረራ ሊያካሂድ ይችላል፡፡

ጡረተኛው ጀኔራል ከታላቋ ኢትዮጵያ ማህጸን ታላቋን ትግራይ ሊያዋልድ እያሟሟቀ በስተርጅና ዘመኑ ወደጫካ ተመልሶ ይንከላወሳል፡፡ ይህንን ክፉ ምኞቱን ገቢራዊ ለማድረግ ግን በተዳከመ የጡረተኝነት አቅሙ የቀየሰው በሰብአዊ ወጀብ የመዋጋቱ ኋላ-ቀር ስትራቴጂ ያን ያህል የሚያዋጣው መስሎ አይታይም፡፡

“ችኩል ጅብ ቀንድ ይነክሳል” እንዲሉ በነጻድቃን ሊጥ አእምሮ አብዝታ የምትመላለሰው ታላቋ የትግራይ ሪፓብሊክ በመሬት ላይ የለችም፡፡ ሆኖም በቀን ቅዠታቸው መሰረት ተወልዳ ገና ነጻና ሉኣላዊት አገር መሆኗ በቅጡ ሳይረጋገጥ ጻድቃን ያልጠና የመከላከያ ሀይል አበጅቶላታል፡፡

ምእራባውያን ጋሻጃግሬዎቹ ሳይቀሩ በየፕሬሶቻቸው የሚያንቆለጳጵሱት ይህ ጀሌ ነው እንግዲህ በጡረተኞቹ አዋጊዎች ትእዛዝና ምሪት ከአቅሙ በላይ የሆነ ስምሪት እየተሰጠው ከራሱ ክልል አልፎ ወደአማራና አፋር ክልሎች ዘው ብሎ እየገባ ሰላማዊ አካባቢዎችን የሚያተራምሰው፣ ማሕበረ-ሰቦችን የሚያምሰውና በመጨረሻም ህልውናቸውን የመጠበቅ መብት ባላቸው ወገኖች የተባበረ ክንድ አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ በተከታታይ የሚደቆሰው፡፡

መጠነ-ሰፊ በሆነ የህዝብና የመንግሥት ሀብትና ንብረት ዝርፊያና ውድመት ጭምር እየታጀበ በመካሄድ ላይ ያለው የግፍ ወረራ በጠባዩ ሁለንተናዊና ገጽታውም አስከፊ መሆኑ አያከራክርም፡፡

ሴቶችና ህጻናት በብዛት ያልቃሉ፡፡

ሰላማዊ ዜጎች ከርቀት በሚወረወሩ ከባድ መሳሪያዎች ከቤት ንብረቶቻቸው ጋር ይነዳሉ፡፡

ወታደራዊ ኢላማ መሆን የማይገባቸው የሲቪል አገልግሎት መስጫ ተቋማት በሚዘገንን ሁኔታና ቅጽበት ይወድማሉ፡፡

እንደእውነቱ ከሆነ እነጻድቃን በግፍና በምቀኝነት ተነሳስተው የከፈቱብን ጦርነት በታወቁ የጦርነት ሕግጋት የሚመራ እንኳን አይደለም፡፡ በርግጥ ለሆዳቸው ያደሩ የኛው የራሳችን ግብረ-በላዎች ባያወሳስቡት ኖሮ በመቶዎችና በሺዎች እየሆነ ወደማያውቀው ቀጣና የሚተመውንና በዘፈቀደ የሚተኩሰውን እንግዳ የት.ህ.ነ.ግ ኮልኮሌ በየገባበት አንቆና ደፍቆ ለማስቀረት ይህንን ያህል ባልከበደና ጊዜ ባልወሰደ ነበር፡፡

አልሚ የእርጥባን ብስኩት እየተመገቡ ውጊያ ማካሄድ አለ እንዴ?

ይህንን እውነት ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በቅርቡ ያረጋገጠው እርሱ ይመራው የነበረው የጠላት ጦር ጋሳኝ ላይ ከተደመሰሰ በኋላ የወራሪው ቡድን ሰራዊት እግሬ አውጪኝ ብሎ በተበታተነበት ወቅት በዚያ የተማረከው አዋጊ ኮሎኔል፡፡ ገብረ-ህይወት ገብረ-አእላፍ ነው፡፡ ምርኮኛው ኮሎኔል ሳያፍር እንደተናገረው ከሆነ አለም-አቀፉ የዩናይትድ ስቴትስ እርዳታ ድርጅት አልሰማ ይሆናል እንጂ አዋጊው መኮንን ጋሳኝ ላይ በተማረከበት ወቅት በኪሱ የተገኘው ያ ሀይልና ጉልበት ሰጪ ብስኩት የተጠቀሰው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ስምና አርማ ይታይበታል፡፡

በስም የተጠቀሰው ለጋሽ ድርጅት አስተዳዳሪ እመቤት ሳማንታ ፓዎር ግን ስለጉዳዩ ተጠይቀው በወቅቱ ለዜና ሰዎች ሰጡት ተብሎ አለም-አቀፍ የመገናኛ ብዙኀን የተቀባበሉት ምላሽ በጣም አስቂኝና ከዓመቱ መሪ ቀልዶች አንደኛውን የሚወክል ይመስላል፡፡

የሀምሳ ዓመቷ አይሪሽ-አሜሪካዊት እመቤት “በአሁኑ ወቅት ሰባት ከመቶ የሚሆኑትን ተረጂዎቻችሁን የምንመግበው እኮ እኛ ነን” በማለት ከተመጻደቁ በኋላ እንዳሉት ብስኩቱ ሆነ ተብሎ ለት.ህ.ነ.ግ ተዋጊዎች የተለገሰ ሳይሆን ለተራቡ ወገኖች ከተሰራጨ በኋላ እዚያ የተሰረቀ ሊሆን ይችላል፡፡

ሰቆቃወ-ራሄል

ይህንን መጣጥፍ በመጦመር ላይ እያለሁ የወገን ጦር በአፋር ግንባር ከማረካቸው መካከል አንደኛው ታዳጊ ወጣት ያለው ታወሰኝ፡፡ ከባድ ሲቃ እየተናነቀውና ትኩስ እንባውን እያዘራ ለኢትዮጵያ ቴሌ ቪዥን ጋዜጠኛ የተናገረው ነገር ልብ ሰባሪ ነው፡፡

“በውጊያው ያለቁት ጓደኞቼ እንደኔ ቢማረኩ ምእኛ መልካም በሆነ ነበር” ሲል እያለቀሰ በተናገረ ጊዜ እኔም አብሬው አልቅሻለሁ፡፡

ያ ትንሽ ብላቴና የደብረ-ጽዮንና የጌታቸው ልጆች አብረዉት እንዳልተሰለፉና አላማ በሌለው ጦርነት እየተማገዱ ጭዳ የሆኑት ሁሉ የድሃው የትግራይ ህዝብ ልጆች እንደሆኑ በጣፋጭ፣ ግና ደግሞ አሳዛኝ አንደበቱ መስክሮልናል፡፡

በተመሳሳይ አጋጣሚ “እኛ እኮ ቀድሞውኑ ልንወጋው ከማይገባን ህዝብ ጋር ነው እንድንዋጋ እየተደረገ ያለው” በማለት ወደኋላ የቀሩት የትግራይ ወጣቶች የገዛ ልጆቻቸውን ወደአውሮፓና አሜሪካ ልከው በቅንጡ ትምህርት ቤቶች በሚያስተምሩት በነጻድቃን ገብረ-ተንሳይ የክተት ጥሪ እየተታለሉ በጭራሽ እንዳይከተሏት ያስጠነቀቀችውን ሌላዋን እንስት የት.ህ.ነ.ግ ምርኮኛም ፈጽሞ አልረሳትም፡፡

ታዲያ ይሄ ሁሉ ብሶት የወለደው የልጆች ድምጽ ምን ይፈይዳል ትላላችሁ ወገኖቼ?

እነዚህን ለጋ ህጻናት ሆነ ብለው ለጥይት ማብረጃ ያሰለፏቸው ደም መጣጭ አሸባሪዎች ይቅርና የቡድኑ ቀንደኛ ደጋፊዎች እነአንቶኒ ብሊንከን፣ እነሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድና እነሳማንታ ፓዎር እኮ ለዚህ አይነቱ ሰቆቃወ-ራሄል  ጥሪ መስሚያ ጀሮ የላቸውም፡፡

በቀቀኑ ሴኮና ክልፍልፉ ጌቾ

ቅድመም ሆነ ድህረ-ለውጥ መቅኔያቸው ፈስሶ እስኪሟጠጥ ድረስ ሊታመን በማይችል ፍጹም አጎብዳጅነት ት.ህ.ነ.ግን እስከመጨረሻው ያገለገሉት ጌታቸው ረዳና ሴኩቱሬ ጌታቸው ከልብ ያሳዝኑኛል፣ ያበሳጩኛልም፡፡

ሁለቱም አማሮች ናቸው፡፡ መባልን እሰማለሁ፡፡ በርግጥ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አማርኛ ሊሆን እንደሚችል ካልተሞረደው አነጋገራቸው ቅላጼና ዘዬ ብቻ በግርድፉም ቢሆን ለመገመት አያዳግትም፡፡

እንዲያም ሆኖ “የአገሩን በሬ በአገሩ ሰርዶ” እንዲሉ ክፋተኛው ት.ህ.ነ.ት አማራን ለመምታትና እስከወዲያኛው ለመቅበር እንዴትና ምን ያህል እያሾረ በአለንጋነት ሲጠቀምባቸው እንደኖረ አብዝቶ ይገርመኛል፡፡

እነዚህ ሁለት ወንድሞቻችን በማንነት ቀውስ ውስጥ ወድቀው ክፉኛ የሚሰቃዩና የትግሬነትን ብራንድ በቅልውጥ ብቻ ለማግኘት የምራቸውን ደፋ ቀና ሲሉ የኖሩ መሆናቸውን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ እምብዛም ያልተሳካላቸውና በአመዛኙ ለሆዳቸው ብቻ ያደሩ ከሀድያን ናቸው፡፡

‘ናቸው’ አልኩ እንዴ ጎበዝ?

አይ የኔ ነገር፡፡

አፈሩ ይቅለለውና አንደኛው ክልስቱ፣ ማለትም ሴኩ ቱሬ ጌታቸው አለቆቹን በፕሮፓጋንዳ እወጃ የቀደመ መስሎት የሰሜን ወታደራዊ እዝ መብረቃዊ ሊባል በሚችል ፍጥነት በከሀዲው ቡድን አፈና በ45 ደቂቃ ውስጥ ተመትቶ መፈራረሱን አደባባይ ወጥቶ ባወጀና በጠላትም ሆነ በራሱ ላይ የማያወላውል ምስክርነት በሰጠ ማግስት ራሱ በጠራው መብረቅ ድባቅ ተመትቶ እስከወዲያኛው ማሸለቡን ዘንግቼው እኮ ነው፡፡

3 Comments

 1. አቶ መርሀጽድቅ መኮንን፦
  እንንደ እነዶ/ር ጌታቸ ሀይሌ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምና ወዘተ የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች በጠፉበት በዚህ ክፉና በጭካኔ የተሞላ የሞላጮች ዘመን እርሰዎን የመሰለ ችግር አሻጋሪና መካሪ ሰው በማግኘታችን እድለኞች ነን፡፤ ወያኔ መጥፋት ብቻ ሳይሆን ሞቶ መቀበሩ በተግባር መረጋገጥ ያለበት ለማንም የማይጠቅም ብልሹ ድርጅት ነው፡፡
  ትህነግ በመርዝ ቀምሞ ያፈራቸውና አሁን በማቆጥቆጥ ላይ ያሉት የኦሮሙማ ሽብር ፈጣሪዎች ለተላሎች የከሰረ የሚመስለን ነገር ግን ሰንሰለቱ እስከላይኛው የቤተመንግስት ጫፍ ድረስ የሚዘልቅ ስውር ሀይል ነው፡፡ ይህ በስውርም በግልጽም ከላይኛው ኦሮሙማ ጀምሮ እስከታች ድረስ በድብቅ በመንግስት የሚዘወረው አማራ ጠሉና ኢትዮጵያን አፍራሹ የሴራ ፖለቲካ በተራው ወይንም አንድ ላይ እንደትህነግ እከሚወገድ ድረስ እባክዎን አይጥፉብን፡፤ አገሪቱም እኛም እንፈልግወታለንና፡፡

 2. አቶ መርሀጽድቅ፦
  እነ ዶ/ር ጊታቸው ሀይሌና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ወዘተ የመሳሰሉ ታላላቆች በሌሉበት በዚህ መጥፎና ጨካኝ ዘመን እርሰወን አይነት ሰው በማግኘታችን እድለኞች ነን፡፡ ትህነግ ወደር የማይገኝለት አረመኔ ስብስብ ነው፡፤ መጨረሻ ላይም ቆሜለታለሁ ለሚለው ለትግራይ ህዝብም እንደስብስብ ለራሱም ሳይሆን ቀረ፡፡
  በተመሳሳይ መልኩ ከላይ እስከታች በመንግስት ውስጥ በግልጽም በስውርም በአማራ ጠልነትና በተረኝነት ታውሮ ለመስፋፋት የሚጥረው አረመኔውና አራጁ የኦሮሙማ “ምርጥ” ቡድንም እንደዚሁ በተራው ይጠፋል፡፡ ከአናቱ ጀምሮ ባለው መንግስት ውስጥ ተሰግስገው እንደዚሁም በከፍተኛ የመሪነት ቦታ ላይ ተቀምጠው በዘረኝነት ገምደው በሶረቡት ሴራ ይወድቃሉ፡፡ በዘረኝነትና በተረኝነት የበላይነትን መቀዳጀት አይቻልም፡፡ አገራችንን ለማፍረስ የሚጥሩ ሁሉ ለጊዜው ቢመስላቸውም መጨረሳሻ ላይ አይሳካላቸውም፡፤ ዉጤቱ እልቂት፣ ውርደትና የታሪክ አተላነት ብቻና ብቻ ነው የሚሆነው፡፤ የማንኛውም የእልቂትና የተንኮል ፖለቲካ ሄዶ ሄዶ ሲቸርስ ውጤቱ ጸጸት፣ ውድቀትና የህዝብ እልቂት እንጅ የሚቀየር እውነታ ፈጽሞ አይኖርም፡፡ ስለዚህ ይህንን መጥፎ ዘመን ጠንክረን እየታገልን እንድንወጣው እባክዎትን ከጠቃሚ ምክርዎ ጋር አይጥፉብን!!!

 3. አቶ መርሀጽድቅ፦ እነ ዶ/ር ጊታቸው ሀይሌና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ወዘተ የመሳሰሉ ታላላቆች በሌሉበት በዚህ መጥፎና ጨካኝ ዘመን እርሰወን አይነት ሰው በማግኘታችን እድለኞች ነን፡፡ ትህነግ ወደር የማይገኝለት አረመኔ ስብስብ ነው፡፤ መጨረሻ ላይም ቆሜለታለሁ ለሚለው ለትግራይ ህዝብም እንደስብስብ ለራሱም ሳይሆን ቀረ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ከላይ እስከታች በመንግስት ውስጥ በግልጽም በስውርም በአማራ ጠልነትና በተረኝነት ታውሮ ለመስፋፋት የሚጥረው አረመኔውና አራጁ የኦሮሙማ “ምርጥ” ቡድንም እንደዚሁ በተራው ይጠፋል፡፡ ከአናቱ ጀምሮ ባለው መንግስት ውስጥ ተሰግስገው እንደዚሁም በከፍተኛ የመሪነት ቦታ ላይ ተቀምጠው በዘረኝነት ገምደው በሶረቡት ሴራ ይወድቃሉ፡፡ በዘረኝነትና በተረኝነት የበላይነትን መቀዳጀት አይቻልም፡፡ አገራችንን ለማፍረስ የሚጥሩ ሁሉ ለጊዜው ቢመስላቸውም መጨረሳሻ ላይ አይሳካላቸውም፡፤ ዉጤቱ እልቂት፣ ውርደትና የታሪክ አተላነት ብቻና ብቻ ነው የሚሆነው፡፤ የማንኛውም የእልቂትና የተንኮል ፖለቲካ ሄዶ ሄዶ ሲቸርስ ውጤቱ ጸጸት፣ ውድቀትና የህዝብ እልቂት እንጅ የሚቀየር እውነታ ፈጽሞ አይኖርም፡፡ ስለዚህ ይህንን መጥፎ ዘመን ጠንክረን እየታገልን እንድንወጣው እባክዎትን ከጠቃሚ ምክርዎ ጋር አይጥፉብን!!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.