ግራጫ አተያይ – ዶ/ር መኮንን ብሩ

ደራሲ አደም ረታ ‘ግራጫ ቃጭሎች’ ሲል የሰየመዉ ልብ ወለድ  መፅሐፍ አለዉ። ጥሩ  መቸትና ግጭት ያለዉ መፅሐፍ ነዉና ጊዜ ሲኖራችሁ ታነቡት ዘንድ እጋብዛለሁ። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ 1993 ባሳተመዉ ኣማርኛ መዝገበ ቃላት ‘ግራጫ’ የሚለዉን ቃል ‘በነጭና በጥቁር መካከል ያለ ኣመዳም የቀለም ኣይነት’ ሲል ይተረጉመዋል።

ግራጫ ወይም በእንግሊዘኛዉ gray በሰዉ ልጅ የአስተሳሰብ አተያይ መተርጎም ካለበት ደግሞ መሐል ያለ፣ የሚያመዛዝን፣ ድርቅ ባለ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ያልተበተበ፣ ሚዛናዊ እና አቻቻይ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ፈረንጆች The elegance of the Gray thinking is boundless ይላሉ። ግራጫ አስተሳሰብ ወይም አተያይ ዉበቱ ማለቂያ የለዉም ብለዉ ያምናሉ። ብጭጭ ብሎ ያልነፃ ወይም ድቅድቅ ብሎ ያልተቆረ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት ሚዛናዊ ነዉ ብለዉ ይገምታሉ። በአንፃሩ ሁሉንም ነገር እንመጨረሻ እዉነት ወይም ሐሰት ደምደሞ መቀበል የሚፈልግ አልያም ሌሎች እንዲቀበሉ የሚነተርክ ጭንቅላት እንጭጭ ነዉ ይላሉ።

ለምሳሌ ለብዙ የዓለማችን ሰዎች ኢትዮጵያ የሚለዉ ቃል ትርጉም በጣም የተወሰነ ነዉ። ኢትዮጵያ ለብዙዎች በድርቅ ምክንያት የተራበ ሕዝብ የሚሰቃይባት ሀገር፤ አልያም ሁሉም ሯጭ የሆነባት ምድር፤ አልያም በዐፄ ኃይለስላሴ ዘመን ላይ ተቸክላ የቀረች የራስታዎች ምድር፤ አልያም ሶሻሊስት የሆነች ሀገር ነች። እዉነታዉ ግን ከጠቀስኳቸዉ በሙሉ የራቀ ቢሆንም አብዛኛዉ የሰዉ ልጅ ግን አስተሳሰቡን በተወሰኑ እወነት መሰል የአንድ ወቅት ክስተቶሎች ላይ ስለሚያሳርፍና እዛዉ ባለበት ተደላድሎ ስለሚቀመጥ የእርሱ እዉነት በተቀመጠበት ዙሪያ የሚመለከተዉ ክስተት ብቻ ይሆናል። ለዚህም ነዉ ፕሮፓጋንዳ ወይም ወገንተኛ ሚዲያ ከጦር መሳሪያ በላይ ኃይል ያለዉ።

ማመዛዘን አልያም ግራጫ አስተሳሰብ ተደላድለን ከተቀመጥንበት አስነስቶ ወዲህ ወዲያ በማለት ሌላ ዕውነቶች መኖር አለመኖራቸዉን እንድንፈልግ ስለሚያደርገን አድካሚ በመሆኑ ብዙዉ ሰዉ ግራጫን አተያይን ከመምረጥ ይልቅ ከአንድ ቡድን ወይም አካል ጋር እራሳን በመወገን መንጋነትን  ይመርጣል። ማሰብ ስለሚያደክም ሌላዉ አዉጥቶና አዉርዶ በወሰነወ የአሳብ ጎዳና ላይ ወይንም ተንኮለኛ በቀደደዉ  ቦይ ዝም ብሎ መፍሰስን ያቀበላል።

ፍፁም እወነት አልያም ፍፁም ሐሰት ተደርጎ በመንቆለጳጰፅ ተከሽኖ የሚቀርብ ነጭ ወይም ጥቁር ብቻ አስተያየት ለሰነፍ ሰዉ እተቀመጠበት ቦታ ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብ ምግብና መጠጥ ዓይነት ነዉ። ብልጣብልጦች ይህን ስተካኑበት ትዉልድን ከማስተማር ይልቅ ለእራሳቸዉ እኩይ ዓላማ ተደላድሎ የተቀመጠዉን ሰነፍ መንጋ በማድረግ እንደ ጋማ ከብት አልያም እርድ ከብት ሲገለገሉበት ዘመናት አልፈዋል። ሂትለር ሚሊዮኖችን ያስጨፈጨፈዉ በዚህ ምክንያት ነዉ። ስታሊን የእራሱን ዜጎች ለመቃብር የዳረገዉ በፕሮፓጋንዳ ነዉ። የሩዋንዳዉ ዕልቂት፣ የኒዮርኩ 9/11 ፣ የበርካታ ኢትዮጵያዊያን አንገት በየመን መቀላት፣ ወዘተ ወዘተ የዚህ ስንፍናና ብልጠት ዉጤት ነዉ።

ላለፉት ሰላሳ ሲደመር አስራ ሰባት ሲደመር የዐፄዉም ዘመን ኢትዮጵያዊያ ይብዛም ይነስም በሁለቱ ጎራ ሊመደቡ በሚችሉ ቀበሮና በጎች ስር በመሆኗ ለዘመናት መተራመሳችን ምክንያት ሲሆን ከራርሟል። አሁንም እየተተራመስን አለን።

ፊታዉራሪ መሸሻን የሚመስለዉ ፊዉዳሉ ኢትዮጵያ ለእሱና ለቤተ ዘመዱ ብቻ የተሰጠች ገፅ በረከት ይመስል የእራሱን ወገን ሲያሰቃይና ሲበዘብዝ መኖሩ ሳያንሰዉ ድኸነትና ጭሰኛነት ለሌላዉ ከፈጣሪ የተበረከተለት የመከራ ገፀ በረከት አስመስሎ በማስተማር በዕምነት ፕሮፓጋንዳ ጠርንፎ ጨለማ ዘመንን ያሳልፍ ዘንድ አድርጎል። ፍቅር እንኳ ላይበግረዉ የሰብለወንጌልንና በዛብዕን የመሰለ የአብሮነት ገፀ በረከት አምክኗል። ይህ ታዲያ ነጭ አልይያም ጥቁር፣ ጪሰኛ አልያም ባላባት፣ ባለጌ አልያም ጨዋ እንጂ ለግራጫ ቦታ ያልነበረዉ ዘመን በመሆኑ ነበር።

በተማሪዎች ትግል ታጅቦ ስልሳዎቹን መኳንንትና ሹማምንት እምሽክ አድሮጎ አለሁ ሲል ቀይ ኮኮብ እያዉለበለበ በትረ ስልጣኑን የተቆጣጠረዉም ደርግ ቀይ ሽብር አልያም ነጭ ሽብር፣ ወዛደሩ አልያም አድሃሪዉ፣ ጭሰኛዉ ወይም በዝባዡ፣ ሶሻሊስቱ አልያም ኢምፔሪያሊስቱ በማለት ትዉልድን በሁለት ጎራ አስቀምጦ ነበር አስራ ሰባት ዓመታት ሙሉ ትዉልድን ሲያቀጭጭና ሲቀጥፍ የከረመዉ።

ድንቁ ከያኒ ቴዲ አፍሮ እንዳለዉም በአስራ ሰባት መርፌ ተጠቅጥቆ የተሰቃየን ትዉልድ ነፃ አወጣለሁ ብሎ ከሰሜን ቁምጣ ታጥቆ ከተማ የገባዉም የትግራይ ነፃ አዉጪ ወንበዴ ሃያ ሰባቱንም ዓመታት የተገበረዉ ትዉልድን በሁለት ጎራ ከፋፍሎ ማምከን ነበር። ሲያሻዉ ነፍጠኛ አልያም ጠባብ፣ ሳይመቸዉ የደረርግ ርዝራዥ አልያም ሻቢያ፣ አልሆን ሲል ደግሞ አህዳዊና ጨፍላቂ በማለት ግራጫ አመለካከትን ከምድሪቱ አጥፍቶ ትዉልድን ወደ መንጋነት በመቀር ከድጡ ወደ ማጡ ዘፍቆናል።

በዘመነ ብልፅግናም በነጭ አልያም ጥቁር ሐሰትና እዉነት ላይ እየተቧጨቅን አለን። ሰከን ብለዉ ማመዛዘንን ሊያስተምሩን የሚዳክሩ አዋቂዎች የሉም ማለት ባይቻልም አብዛኛዉ ተናጋሪና ፀሐፊ ግን ወይ ክቦ ሰማይ ላይ የሚያስቀምጥ አልያም ቁልቁል እንጦሮጦስ የሚወረዉር ችኩልና ጮርቃ ነዉ። አምስትና ስድስት ሺህ ሰዎች በቀጥታ ስርጭት በየዕለቱ  ይከተታተሉናል ብሎ የሚኩራራ ተናጋሪ ከእርሱ አመለካከት የተለየ አቋም ያላቸዉን ሌሎች ሰዎች ‘ተደጋፊ ተደማሪ’ አልያም ‘ዉታፍ ነቃይ’ እያለ በአደባባይ ሲዘልፍ የሚጨበጨብለት ትዉልዱ ግራጫ አስተሳሰብን ያልተላመደ ጮርቃ ወይም መንጋ ስስለሚበዛዉ ነዉ።

ሌላን ስታማ አልያም ስትዘልፍ ጭብጨባዉ ከተበራከተ አብዛኛዉ ተመልካችህ ሐሜትን ወይም ዘለፋን ይወዳል ማለት ነዉ። ሐሜትና ዘለፋን የሚወድ አልያም የሚያሞካሽ ሰዉ ደግሞ  አዋቂ ሊባል አይችልም። ብዙ ስታዉቅ ብዙ ማዳመጥን ብቻ ሳይሆን ቁጥብ መሆንን ትላመዳለህ፤ ምክንያቱም ብዙ የሚያዉቅ ሌላዉም የራሱ እዉነት አለዉ ብሎ የሚቀበል ግራጫ አመለካከት ያዳብራልና።

ግራጫ አተያይ ያላቸዉ ሰዎች ሌላዉን ላለማስቀየም ከመጣር አልፈዉ የሚያምኑበትን እዉነት እንኳ ተጠንቅቀዉ ነዉ የሚያቀርቡት። ይህን ምናልባት በፕሬዘዳንት ኦባማና በፕሬዘዳንት ትራምፕ ምሳሌ ማስረዳት ይቀላል። ኦባማ አልፎ አልፎ ሲናገር ምን ያህል እንደሚጠነቀቅ ላስተዋለ የትራምፕ ግልብነትና ጮርቃነት  ይታወቀዋል። የእኛ ሀገር ተናጋሪ ተብዬዎች በየዕለቱ ኮምፒዉተራቸዉ ስክሪን ላይ አፍጥጠዉ  360 ዲግሪ እየተሽከረከሩ ስለ ሕግ ብርቱካን ሚደቅሳን … ስለ ኢኮኖሚ ብርሃኑ ነጋን ….፣ ስለቅስናና ቤተክርስትያን ጳጳሳትን….ስለዉትድርና ጄነራሎችን ከፍ ቁጭ ሲያደርጉና ሊያስተምሩ ሲቅበዘበዙ  ለሚመለከት አዋቂ የሚያሳፍር የዉድቀታችን መገለጫ ትዕይንት ቢሆንም መንጋዉ ግን ለማሰብና ለመጠየቅ ስለሚሰፍን እንደተቀመጠ ያጨበጭባል።

ምናልባት ብዙዎች መንጋ የሚለዉን ቃል በመጠቀሚ ይናደዱብኝ ይሆናል። እኔም ብሆን የሌሎችን ሐሳብ ሳላመዛዝን ተቀብዬ ሌላን የምጠላ አልያም የምዘልፍ ከሆነ መንጋ ነኝ። ሽመልስ አብዲሳ ነፍጠኛን ሰብረነዋል ብሎ ሲናገር ከማጨብጨብ ይልቅ ቁጣዬን የገለፅኩት መንጋ ለመሆን ባለመፍቀዴ ነዉ። ፍረጃን በጥቅሉ ተቀብሎ እንደ ገደል ማሚቱ የሚያስተጋባ ሰዉ የራሱ ጎዳና ስለሌለዉ መንጋ ነዉ። ግራጫ አተያይ ቢኖረን መልካም ነዉ። ኢትዮጵያንም ወደ መልካምነትና ወደ ነገ የምናሻግረዉ ድቅድቅ ጨለማ ወይም ብጭጭ ያለ ነጭ አመለካከት በመያዝ ሳይሆን ሁሉም ሊሆን ይችላል የሚል ግራጫ አተያይ ሲኖረን ነዉ።

ኢትዮጵያ ትቅደም።

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.