በጣና ሀይቅ የተከሰተው እንቦጭ አረም ከመቀነስ ይልቅ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተዘገበ፡፡ በረራ ጋዜጣ ዛሬ እንደዘገበው አረሙን ለማጥፋት የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ሙከራዎች ቢደረጉም እስካሁን ፍሬያማ ውጤት አልተገኘም፡፡ የጎንደርና የባህር ዳር ዩኒቨርስቲዎች ማጨጃ ማሽኖችን በመግዛት ለማስወገድ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ያመጡት ነገር የለም፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=pKU8igiCV3I&t=500s
እንደውም ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ለባዮሌጂካል ሙከራ ብሎ የወሰደው የእንቦጭ ናሙና አባይ ወንዝን ዕየወረረው እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በማክሰኝት ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ውብነህ ለበረራ ጋዜጣ ሲናገሩ ‹‹በእምቦጭ ጉዳይ የተያዘው ቀልድ ነው፡፡ የገንዘብ ምንጭ በማድረግ ችግሩ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡ በውጪ አገር ያሉ ገንዘብ ይለግሳሉ፡፡ ማሽኖች ተገዙ ይባላል፣ ያሉት ማሽኖች ተመረቁ ከተባለ ጀምሮ አንድም ቀን ስራ አልሰሩም›› ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ብርሃኑ ገለፃ አማራ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በርካታ ጣቢያዎች በእንቦጭ አረም ዙሪያ ዘጋቢ ፊልም ቢቀርፁም ሳይተላለፍ ቀርቷል፡፡
የኢትዮጵያ ደንና ምርምር ኢኒስቲትዩት ተመራማሪው አቶ አዱኛው አድማሱ ለጋዜጣው በሰጡት መግለጫ አረሙን ለማጥፋት በሜካኒካል፣ በባዮሎጂካልና በኬሚካል መንገዶች እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ጣና ሀይቅ ላይ ከተጋረጠው እምቦጭ በተጨማሪ በጎርጎራ በኩል አዲስ አረም መከሰቱንም ነው ያስታወቁት፡፡ የኢትዮጵያ ደንና ምርምር ኢኒስቲትዩት አንድ ባለሙያው እንደተናገሩት ይህ እሾሀማና ቁመቱ ዘጠኝ ሜትር የሚደርሰው አዲስ አረም የጣናን ሶስት ሄክታር ይዞታል፡፡ ለአረሙ እስካሁን የአማረኛ ስም እንዳልወጣለት ገልፀውም ሳይንሳዊ መጠሪያው aeschynomene elaphroxylon የሚባል እንደሆነና ከሴኔጋል የመጣ አደገኛ አረም መሆኑን አስረድተዋል፡፡