በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
የሎዛን ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ ከሃገራቸው ተሰደው ወደ አውሮፓ በመርከብ በመምጣት ላይ እያሉ በጣሊያን ደሴት በላምፔዱዛ አቅራቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸዉን ያጡትን ነብስ ያላወቁ ሕጻናትን ጨምሮ ከ ሁለት መቶ በላይ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዉያን ወገኖቻችንን በጸሎት ለማሰብ እሁድ ኦክቶበር 20 ቀን 2013 ዓ/ም ጸሎተ ምህላ ስለምታደርስ በሎዛን ኦሎምፒክ ስታዲዮም አቅራቢያ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን እርሶም ተገኝተው የምህላው ተካፋይ ይሆኑ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ቦኑ ለከንቱ ዘሮጽኩ ወፃመውኩ እምሄሮድስ ነዓዊ
እምኢያምስጥኩ ወለምንት ዝይየ እምሀገርየ ወጻእኩ
ከአዳኝ ሄሮድስ ( ሞት) ላላመልጥ የሮጥኩት የደከምኩት በውኑ ለከንቱ ነውን ?
ለዚህስ ከሀገሬ ለምን ወጣሁ?
ሰቆቃወ ድንግል ወሰብአት ለእግዚአብሔር ወለ ወላዲቱ ድንግል ወለ መስቀሉ ክብር በዚህ መታሰቢያ ወቅት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተን በመንፈስ የራቁንን አቅርበን የእመቤታችንን ስደት በእምነት እያየን በማኅሌተ ጽጌ በዜማ « መልካሟ ርግብ ማርያም ሆይ ንጹሕ፣ ፀአዳ፣ ቀይህና ብሩህ የሚሆን ልጅሽን ታቅፈሽ ርኅሩኅ የሆነ ቅዱስ ሚካኤልና ፍሱሕ ቅዱስ ገብርኤልን አስከትለሽ ከሐዘናችንና ከችግራችን ታረጋጊን ዘንድ ፈጥነሽ ድረሽልን » ልንላት ያስፈልጋል፡፡
በቅዳሴያችንም« ድንግል ሆይ ርጉም በሆነ ሄሮድስ ዘመን ከልጅሽ ጋር ከሀገር ሀገር ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አስቢ፤ ድንግል ሆይ ከዓይንሸ የፈሰሰውንና በተወደደ ልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር እንባ አስቢ፡፡ ድንግል ሆይ ረአቡንና ጥሙን፣ ችግሩንና ሐዘኑን፣ ከእርሱ ጋር የደረሰብሽንም ጭንቅ ሁሉ አስቢ ልንላት ያስፈልጋል፡፡
አድራሻ፥ BOIS-GENTIL 9 LAUSANNE 1018 ከባብር ጣቢያው አንድ (1) ቁጥር ባስ BLECHERETE አቅጣጫ በመያዝ አስራ ሁለት ፌርማታ ተጉዘው BOIS-GENTIL የሚለው ማቆሚያ ላይ ወርደው ወደ ኋላ መለስ ብለው ጥቂት ሜትሮች ሄደው ወደ ግራ በሚያስገባው የመጀመሪያው መታጢፊያ እንደታጠፉ 100 ሜትር ገባ እንዳሉ ያገኙታል።
የሎዛን ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሰ/ ጉባኤ ጽ/ቤት