January 15, 2017
59 mins read

የኢትዮጵያ ፈተናዎችና መፍትሔ መንገዶች አስተያየት — በቀለ ገሠሠ (ዶ/ር)

መንደርደሪያ፤

በ20ኛዉና 21ኛዉ ክፍለ ዘመን ሌሎች አገሮች ከጊዜ ወደጊዘ በእድገት ጎዳና ወደፊት ሲራመዱ እኛ ሁልጊዜ ወደኋላ ነዉ የምንሄደዉ። ከራሷ ተርፋ ሌሎች አገራትን መመገብ የምትችል ኢትዮጵያ ተመጽዋች ሆና ስትቀጥል ሳይ እጅግ በጣም ያስገርመኛል፤ ያሳዝነኛል፤ ያበግነኛል።

የሕዝባችን መከራና ሰቆቃ እየከፋ ሄደ። የአገሪቷ ህልዉና ራሱ በጥያቄ ዉስጥ እየገባ መጥቷል። ለዚህም አላስፈላጊ ሰቆቃ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለዉ የወያኔ/ኢሕአደግ አስተዳደር በግልፅ ይጠየቅበታል። ሆኖም ግን በአገሪቷ ላይ የተሻለ የፖሊቲካ ለዉጥ ለማምጣት ከተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች፤ የሲቪክ ማህበራትና ግለሰቦች ጭምር ብዙ ነገሮች ይጠበቃሉ። እነዚህን ማሳሰቢያዎች እንደሚከተለዉ ሳቀርብላችሁ በጥሞና ተመልክታችሁ የሚቻላችሁን ሁሉ አስተዋጽኦ እንድታደርጉ በሕዝባችንና በኢትዮጵያ አምላክ ስም እጠይቃችኋለሁ።

  1. የ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ዋና ዋና አሳሳቢ ፈተናዎች

በተለይ ባለፉት 50 ዓመታት ዉስጥ ኢትዮጵያና መሰል አገሮች ከባድ ከባድ ፈተናዎች ሲደቀኑባቸዉ ቆይተዋል። ዛሬ ደግሞ እየባሰበት ይገኛል። ሌሎች አገሮች ችግሮቻቸዉን በተባበረ ክንድ እየቀረፉ ወደእድገት ጎዳና ሲያቀኑ እኛ መጨረሻዉ ላይ እንገኛለን። ከነዚህ ዉስጥ ቀጥለዉ የተመለከቱት ጥያቄዎች ከፍተኛና ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸዉ ይገባል ብዬ አምናለሁ፤ እስቲ እንመልከታቸዉ።

  • ከአምባገነን ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲ ስለመሸጋገር አስፈላጊነትና ተጋድሎ፤

በኢትዮጵያና በተመሳሳይ የአፍሪቃ አገሮች ዉስጥ የአምባ ገነን ሥርዓት የሚሊዮኖችን ሕይወት እንዳጠፋ፤ ንብረቶች እንዳወደመ፤ ህዝብ እንዳፈናቀለና እንዳሰደደ፤ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳቀጨጨና አላስፈላጊ ርሃብ እንደጋበዘ ማንም የማይስተዉ ሃቅ ነዉ። ዛሬ ብዙ የአፍሪቃ አገሮች በዲሞክራሲ ጎዳና መልካም መሻሻል ሲያሳዩ ኢትዮጵያ ዐይን ባወጣ አምባገነንነት ልዩ ሪኮርድ በጥሳ ከዓለም አገሮች ሁሉ በመጨረሻዉ ደረጃ ላይ ትገኛለች። እኔ እስከሰማሁትና እስከማዉቀዉ ድረስ በአገራዊ ምርጫ መቶ ከመቶ ድምፅ አግኝቻለሁ ብሎ የዓለም መሳቂያ ሆኖ የሚታየዉ የወያኔ/ ኢህአደግ አምባገነን መንግሥት ብቻ ነዉ። የዉጪ ታሪካዊ ጠላቶች እየሳቁብን ናቸዉ፤ ወዳጆች ደግሞ ክፉኛ አዘኑብን።

ዲሞክራሲ፤ ግልፅነትና ተጠያቂነት ሳይኖሩ ሰላም፤ አገራዊ እርጋታ፤ ዕድገትና የህዝብ ደህንነት ሊረጋገጡ አይችሉምና

1.2    የመሬት ባለቤትነትና፡አጠቃቀም ችግሮች

በአፍሪቃ፤ በእሲያ፤ በፓሲፊክና በአሜሪካ (ሰሜንና ደቡብ ጭምር) በዐለም ላይ ከነበሩት ችግሮች ዋነኛዉ የመሬት ንጥቂያ ነበር። ነዋሪ ባለቤቶች ሲነጠቁ፤ ሲፈናቀሉ፤ ሲራቡና ሲያልቁ የዉጪ ባለጉልበቶችና ወራሪዎች ይፈነድቁባቸዋል። ይሄ ችግር የደረሰባቸዉ ብዙ አገሮች መሻሻል ሲያሳዩ በኢትዮጵያ አገራችን ግን ዛሬ እጅግ ከባድ ችግሮች እንደተፈጠሩ ይሰማል። በተጨማሪም በአገራችንም  ካሁን በፊት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ተብለዉ የተቆጠሩት ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲታረሱ የቆዩ ከፊል የሰሜን ኢትዮጰያ ምድሮች ነበሩ። ዛሬ ግን በተለይ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ደኖች ተጨፈጨፉ፤ አፈር እየታጠበ ሄደ፤ መሬት ካለዕረፍት በተደጋጋሚ ታረሰ። በነዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች  የተቀሩትም የአገሪቷ መሬቶች ጠፍ እየሆኑ መጥተዋል። በዚህ ላይ የሰሀራ ምድረበዳ በረሃዉን ወደደቡብ እየገፋ ይገኛል። በተጨማሪም የአካባቢዉ አየር ብክለት ዓለምን በሙሉ እያሰጋ ይገኛል። የነዚህን ተጽፅኖዎች ለመቋቋም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች አሉ።

ዕዉቀቱና ልምዱ ያሏቸዉ ወገኖች በአምባገነን መንግሥታት ስለማይፈለጉ የተገደሉት ሄደዋል፤ በአገር ዉስጥ የቀሩት እንዳይሠሩ እጆቻቸዉን ታስረዋል፤ እንዳይናገሩ አፎቻቸዉን ተሸብበዋል፤ የተረፈዉ በስደት ላይ ይገኛል። ታዲያ አገሪቷን ማን ይንከባከባት?

  • ችጋር፤ ርሃብ፤ በሺታና ቸነፈር

ብዙ የዓለም ህዝብ ችጋር፤ በሺታና ቸነፈር ለማስወገድ ብርቱ ጥረት ሲያደርግ በመቆየቱ ምክንያት መልካም ዕድገት በማሳየት ላይ ይገኛል። ቸሩ አምላካችን እጅግ ምስጋና ይግባዉና ያቺ የተቀደሰች አገራችን እጅግ በጣም ሃብታም ሆና የተፈጠረች ነበረች።በምድራችን ስፋት፤ በአፈሩ ለምነት፤ በወንዞቻችንና በሃይቆቻችን ብዛትና በተሟላ የተፈጥሮ ሀብት የተገጎነጸፈችና እጅግ የላቀች ቅድስት አገር ናት። እንኳን ለህዝባችንና ለሌሎችም የምትተርፉ አገር ነበረች። በዚህ ላይ በየዓመቱ ብዙ ቢሊዮን ፓዎንድ የዉጪ እርዳት እንደሚገባ ይነገራል፡፤

ሆኖም ግን ከሁሉም በታች ከሆኑት በጣም ጥቂት አገሮች መካከል ሆና ትገኛለች። ርሃብና ችጋር ቶሎ ቶሎ ይጎበኟታል፤ በቶሎም አይለቋትም፤ ሚሊዮኖች በየዓመቱ ይጠቃሉ፤ ሺህዎች እንደቅጠል ይረግፋሉ፤ ለምን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል።

  • ስደት

ዕጣ ፈንታችን ሆነና በተለይ ያለፉት 40 ዓመታት የስደትና የጥፋት ዘመናት ናቸዉ ማለት ጥያቄዉን ማጋነን አይሆንም፤ ሃቅ ነዉና። የተማረዉ ክፍል አምባገነኖቹን ካልደገፈ ቦታ የለዉም፤ ከተቃወመ ዒላማ ዉስጥ ይገባል፤ ይታሰራል፤ ይቀጠቀጣል፤ ይሰቃያል። ተርፎ ካመለጠ ምርጫዉ ስደት ብቻ ነዉ። ዉድ አገሩን ጥሎ ወጥቶ ሌሎች አገሮችን ያቀናል፤ አዉሮፓና አሜሪካን ጭምር።

ወጣቱ በአገሩ የመማር፤ የመሥራትና በሰላም የመኖር ዕድል ካላገኘ አገሩን ጥሉ ለመሰደድ ይገደዳል። በስደቱ ጉዞ ላይ ስንቶች ለጋ ወጣቶች በየበረሃዉና ባህሩ ላይ እንደቀሩ ቤት ይቁጠራቸዉ። ከተሻገሩም በኋላ የሚገጥሟቸዉን አሰቃቂ ችግሮች ሁላችንም የሰማናቸዉ ናቸዉ። ታዲያ ወጣቶች በዉድ አገራቸዉ ተምረዉ አድገዉ ተመንድገዉ በሰላም ካልተዘጋጁ  የሚቀጥለዉን  ኃላፊነት ማን ሊረከዉ ይችላል? ትልቅ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል።

1.5    የፈተናዎቹን ክብደት ለማጠቃለል፡

እንኳንስ አገራዊ ሁከት ተጨምሮበትና በሰላምም አየር እላይ ባጭሩ የተቀመጡትን ፈተናዎች መወጣት ቀላል ሥራ አይሆንም። የዉጪ መንግሥታት የየራሳቸዉን ጥቅም ብቻ ነዉ የሚያሳድዱት። ብዙዎቹም ከፋፍለዉ በመግዛት ነዉ የሚነግዱብን። ከሁላችንም ዜጎች ብዙ የተቀናጀ ጥረት ይጠበቅብናል። ሰላምና እርጋታ ከተገኘ ግን ለብዙዎቹ ፈተናዎቻችን መፍትሔ መንገዶች ይኖራሉ። የአገሪቷ መዉደቅ ለማንም ዜጋ አይበጅምና ሁሉም ዜጋ ሊያስብበት ይገባል።

  1. ወያኔ/ኢሕአደግ አስተዳደር ያለኝ መልእክት፤

2.1   ወደመንግሥት ሥልጣን አመጣጥ

በምን መንገድ ወደሥልጣን እንደመጣችሁ አትርሱ፤ ሁሉም ዜጋ የሚያዉቀዉ ነገር ነዉ። የአገራችን ታሪክ እታች ባጭሩ እንደተመለከተዉ እራሱን ይደጋግማል፤ አሁን ደግሞ እየባሰበት ይገኛል።

በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሥልጣን ወቅት ዘመናዊ ሕገ መንግሥት ወጣ፤ ብዙ ትምህርት ቤቶች፤ ኮሌጆች፤ ክልኒኮች፤ ሆስፒታሎች፤ ወዘተ ተገነቡ። ካገርም ዉጪ አፍሪቃ አገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ ታላቅ ዕርዳታ ተለገሰ። ሰሜንና ደቡብ ሱዳኖች እንዲስማሙ ታላቅ አስተዋጽኦ አደረጉ። ለአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ቁልፍ ሚና ተጫወቱ። ከዐለም መንግሥታት ምሥረታ በፊት በነበረዉ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ዉስጥም አገራችንን አባል በማድረግ ብዙ ጥረት አድርገዋል። ሆኖም ግን አገዛዙ የባላባታዊ ሥርዓት ስለነበረ በተለይ ጪሰኞች ክፉኛ ተጨቆኑ። ድህነትና ርሃብም ተደጋገሙ። የመሬት ይዞታንና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን መመለስ አቃታቸዉ። ያገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚፈለገዉን ያህል ሊንቀሳቀስ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የታሪክ ሂደት ሆነና የባላባታዊ ሥርዓት አክትሞ መሬት ላራሹ እንዲሆንና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን በተደረገዉ ረጅም ትግል የንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ሊወድቅ ቻለ።

በወቅቱ የተጠናከረ ተቃዋሚ የፖሊቲካ ፓርቲ ባለመኖሩ የሕዝቡ ትግልና ድል በወታደሮች ተቀማ። ነገር ግን ምንም እንኳን የፖሊቲካ አስተዳደር ብቃት ሳይኖረዉ በእጁ ባለዉ ጠብ መንጃ አማካኝነት ሥልጣን ላይ ቢቆናጠጥም በጦር ኢኮኖሚ ዉስጥ እንኳን ሆኖ ብዙ መልካም ለዉጦች አሳይቶ ነበር፤ የመሬት አዋጅ ሙከራ፤ መሠረተ ትምህርት ማስፋፋት፤ የመንገዶች፤ ድልድዮች፤ ክሊኒኮች፤ ሁስፒታሎችና ኮሌጆች ግንባታዎች። በዚህም ላይ እጅግ በጣም ብዙ ወጣቶች ለከፍተኛ ትምህርት ወደዉጪ ተልከዋል። ነገር ግን ዲሞክራሲ ታፈነ። ሕዝብ ለሚያሰማዉ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሹ ርሸና ሆነ። በዓለም ታይተዉ የማይታወቁ ፋሺስታዊ እርምጃዎች ተወሰዱ፤ ማሰር፤ መደብደብ፤ ማሰቃየት፤ መረሸን፤ ወዘተ። አብዮት ልጇን ትበላለች እየተባለ ፤ የፊዬል ወጠጠ  ተዘፈነብን። ከዚያም በኋላ ደርግ ልቡ አበጠበት፤ በሥልጣን ሰከረ። ብዙ ጄነራሎችንም ጭምር እንደጠላት ቆጥሮ በላቸዉ። ከዚያ በኋላ አዉራ ያጣዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሃሞቱ ፈሰሰ፤ ተስፋ ቆርጦ አፈገፈገ። በሂደቱም ደርግ በገዛ ኃጢአቱና በሕዝባችን የረጅም ጊዜ ቆራጥ ትግል ኃይሉ መነመነ። በመጨረሻ በለንደን ላይ በሄርማን ኮህን ሰብሳቢነት የዉሸት ‘የሰላም ኮንፌረንስ ተጠራ። በኮንፌረንሱ ላይ ህብረ ብሔራዊ የሆኑት ተቃዋሚ ድርጅቶች እንዲሳተፉ አልተፈቀደም። ለሦስት ቀናት የታሰበዉ ጉባኤ የእዉነት አልነበረም። ቀድመዉ የወሰኑትን ዉሳኔ በግልጽ አበሰሩ። የተፍረከረኩት የደርግ ልዑካን ወደ አሜሪካ አቀኑ። ካለብዙ እንቅፋት ሰተት ብላችሁ በምዕራቦቹ ቡራኬ ጭምር ለሥልጣን በቃችሁ።

በትግል ላይ በነበራችሁበት ጊዜ ታራምዱት የነበረዉ የመገንጠል ጥያቄ ብዙ ኢትዮጵያዉያንን ሲያሳዝን የኖረ ቢሆንም ቅሉ ከደርግ የባሰ መንግሥት አይመጣም በማለት ብዙ ዜጋ በቀና ፊት ተቀብሏችሁ ነበር። ሥልጣን ላይ ከወጣችሁበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ግንባታዎች ተዘርግተዋል፤ ትልልቅ ፎቆችና ሰፋፊ መንገዶች ተሠርተዋል፤ በየክልሉ ብዙ ዩኒቬርሲቲዎች ተገንብተዋል። በጎኑ ግን ከፈጸማችኋችሁ ከባድ ከባድ ጥፋቶች መሃከል እታች ባጭሩ የተመለከቱትን ማቅረብ ማጋነን አይመስለኝም።

2.2   የተፈፀሙ ከባድ ጥፋቶች ባጭሩ፤

(ሀ)    የአገሪቷ ሕሊና እንዲናጋ እየተደረገ ነዉ ያለዉ

እኔ በመሠረቱ ዲሞከራሲያዊ ከሆነ ፈዴራላዊ ሥርዓት ጋር ችግር የለብኝም። እናንተ ግን ፈዴራላዊ ሥርዓትን እንደመሣሪያ በመጠቀም ሕዝቡን ከፋፍላችሁ በመግዛት ላይ ናችሁ።  ጎሣን ከጎሣ፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት፤ ወገንን ከወገን ጋር ታጋጫላችሁ። ትግል ከጀመራችሁበት ጊዜ እንስታችሁ አማራዉን በመነጠል ኢላማ ዉስጥ መግባት እንዳለበት አድርጋችሁ እንደ ዋና ጠላት ቆጠራችሁ። በማንነታቸዉም ምክንያት ብዙ አማሮች ተቀጠቀጡ፤ ታሰሩ፤ ተሰቃዩ፤ ተፈናቀሉ፤ ተገደሉ። ይሄ ትልቅ ኃጢአት ነዉ፤ ባለፉት በተፈራረቁ ጨቋኝ ሥርዓቶች ሥር በጎጃም፤ በጎንደር፤ በሰሜን ሸዋ፤ ወዘተ የሚኖሩት ጭቁን ዜጎች ከሌላዉ ወገን የተሻለ ምንም ጥቅም እንዳላገኙ የተሰወረ ሃቅ አይደለም። ለአገር አንድነትና ነፃነት መቆርቆር ደግሞ እንደጠላት የሚያስቆጥር መሆን አልነበረበትም። እግዚአብሔር የሰጠዉን ስብዕና ሆነ ንብረት (መሬት ጭምር) ሊነጠቅ ከቶ አይገባዉም። እንዲሁም የኦሮሞ ህዝባችን ክፉኛ እየተሰቃየ ይገኛል፤ ይታሰራል፤ መሬቱን ይቀማል። በሌሎቹም የአገሪቷ ክፍሎች ተመሳሳይ ጉዳቶች እየደርሱ እንዳሉ ይታወቃል።

(ለ)   ብዙ ሕዝብ መሬቱን እየተነጠቀ በመፈናቀል ላይ ይገኛል

እላይ እንደተጠቀሰዉ ዛሬ በአገራችን የመሬት ንጥቂያ ከዋና ችግሮች አንዱ ነዉ። በአማራ፤ በኦሮሞ፤ በጋምቤላ፤ በአፋር፤ ወዘተ ሕዝቡ መሬቱን እየተቀማና እየተፈናቀለ ይገኛል። ንጥቂያ የሚለዉ ቃል የተመረጠበት ምክንያት የዉጪዉ ስምምነት በአብዛኛዉ የሚፈፀመዉ ከአካባቢዉ የመሬቱ ባለቤቶች/ተጠቃሚዎች ፍላጎትና ይሁንታ ዉጪ በመፈጠራቸዉ ነዉ።  የአገሬዉ ነዋሪና ተጠቃሚ ሕዝብ በጉልበት ከመሬቱ ሲፈናቀል ብዙ መዘዞች ይፈጠራሉ፤ በጉልበት የተፈናቀለዉ ወገን ሰብዓዊ መብቱን ይነጠቃል። ርሃብ ላይ ይወድቃል። ገበሬ መሬቱን ከተነጠቀ ሕይወቱም ታሪኩም ጠፋ ማለት ነዉ። በዚህም ላይ ጥሩ ስምምነትና ከፍተኛ ቁጥጥር ካልተደረገ የዉጪ ኢንቬስተሮች የሚሮጡት ለትርፋቸዉ እንጂ ለአካባቢዉ ሕዝብ ሆነ ለአየሩ ጥራት አይደለም፤ ደኑ ሊጨፈጨፍ፤ አየሩና ወንዙ ሊበከል ይችላል። ይህ ብክለት አካባቢዉን ብቻ ሳይሆን ወንዙንና አየሩን ተከትሎ በሩቁ የሚኖሩትንም አያሌ ዜጎች፤ ከብቶችና አራዊት ጭምር ሊያጠቃና ሊያጠፋ ይችላል። ስለዚህ መሬቱን የተነጠቀዉ ዜጋ መብቱን ለማስጠበቅ ሲል ትግል ዉስጥ እንዲገባ ሲገደድ ሰላም፤ እርጋታና ዘለቄታ የሚኖረዉ ዕድገት ሊናጋ አይችልም ወይ?

(ሐ)  የኢኮኖሚ ምዝበራ ይታያል

ከገዢዉ ቡድን ጋር ቁርኝት ያሏቸዉ ጥቂት ግለሰቦች ባንድ ሌሊት በቢሊዮኖች ሲቆጥሩ ሰፊዉ ሕዝብ ግን በችጋርና በረሃብ አለንጋ እየተጠበሰ ይገኛል። የኑሮ ዉድነት እጅግ አሰቃቂ ነዉ። የሚበላ ያጣ ሰፊዉ ወጣት ዕድሉ ስደት፤ እንግልትና ሞት ብቻ ሆኖ ይታያል። ዝሙት አዳሪነት እየጨመረ ነዉ። ለማኝነት፤ ህመም (የአዕምሮ ጭምር)፤ በቁምም ሆነ እስከመጨረሻዉ መሞት የተለመዱ ዕጣ ፈንታዎች ሆነዉ ይታያሉ።

መፍትሄዉ እጅግ በጣም ቀላል ነበር፤ እኩልነት ማምጣት፤ የአገር ንብረት የህዝብ መጠቀሚያ መሆኑን ማረጋገጥና ዘለቄታ የሚኖረዉ የኢኮኖሚ ዕድገት መዘርጋት ነበር።

(መ)  የዲሞክራሲ አቀንቃኞች እንደጠላት ይቆጠራሉ

ዲሞክራሲ ታፈነ፤  የተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች መሪዎችና ነጻ ጋዜጠኞች እንደጠላት እየተፈረጁ ይታሰራሉ፤ ይሰቃያሉ፤ ይሰደዳሉ። ይሄ ችግር ለወያኔ አዲስ ነገር አይደለም። ከሸአቢያ ጋር በመተባበር ደብዛቸዉን ያጠፋቸዉን የኢሕአፓ ሃቀኞችና ቆራጥ መሪዎች የነበሩትን (በአብነት ጸጋዬ ገ/መድህን (ደብተራዉ)፤ ስጦታዉ ሁሴን፤ አረጋሽ በርታና በለጠ ዓምሓን) ዬት እንደወደቁ እንኳን እስካሁን ድረስ የተናገሩት ነገር የለም። እነዚያ  የአገሪቷ አለኝታ የነበሩት ብሩህና ብርቅዬ ወጣቶች ለመሬት ላራሹ፤ ለዲሞክራሲና ለዜጎች እኩልነት  ቆርጠዉ ከመታገል በስተቀር የፈጸሙት ምንም ኃጢአት ባለመኖሩ በታሪክና በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ሳይሆን በሕግም ያስጠይቃል

ህዝብን በማሸበርና ዲሞክራሲን በማፈን ሰላም ከቶ ሊገኝ አይችልም። ሰላምና እርጋታ ሳይኖር ዘለቄታ ያለዉ ዕድገት ሊመጣ አይችልም። መጨረሻዉ ተያይዞ መጥፋት ብቻ ነዉ። ወርቃማ አማራጮች እያሉን ለምን እንደዚህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር እንደተመረጠ ከቶዉንም አይገባኝም።

(ሠ)  የተማረዉ ወገን እንደጠላት ይቆጠራል

ከገዢዉ ቡድን ጋር ያልወገነዉ የተማረዉ ክፍል ተገለለ፤ አገሪቷ እጅግ ለፍታ ያስተማረቻቸዉ ልጆችዋ ካላገለገሏት ማን ሊያሳድጋት ይችላል? ባለፉት አሥርት ዓመታት ደህና የተማሩና የሥራ ልምድ ያካበቱትን ባለሙያዎች የሲቪል ኮሌጅ ለብለብ ምሩቃን ሊተኳቸዉ አይችሉም። ባገሩ መኖርና መሥራት ያልቻለዉ ንፁሕ ዜጋ ተበትኖ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንና መዕራባዉያን አገሮችን ሲያገለግልና ሲያቀና ይገኛሉ።

(ረ)   በተለይ በወጣቶች ላይ የሚደርሰዉ ግፍ ቀላል አይደለም

የገዢዉ ቡድን አባላትና ደጋፊዎች ካልሆኑ በስተቀር የመማር፤ የመመረቅና የመሥራት ዕድል የማያገኙት ወጣቶች በከባድ ችግር ላይ እንደወደቁ ይሰማል። በርሃብና በችጋር የተጠበሰዉን ዜጋ ከባርነት በማይሻል ሁኔታ ለዐረብ አገሮች ማመቻቸት ያስጠይቃል?

ይባስ ብሎ በዐረብ አገሮች ሲቀጠቀጡ፤ ሲደፈሩ፤ ሲሰቃዩና ሲገደሉ እጎናቸዉ አለመቆምና አለመከላከል ከሁሉም የበለጠ ኃጢአት መሆኑ እንዴት ተሳናችዉ?

(ሰ)   ለማጠቃለል፡

ዉድ አገራችን ያለችበትን ጣጣና ወዴት እያመራች እንዳለች ሁሉም ዜጋ እኩል የሚረዳና የሚጨነቅ አይመስልም። የዉድ አገራችን መጎዳት፤ መከፋፈልና አያድርገዉ እንጂ መጥፋት ለማን ይበጃል? ባባቶቻችንና በአያቶቻችን ደምና አጥንት ተገንብታ ለብዙ ሺህ ዓመታት ተከብራ ኖራ በዓለም አቀፍም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋ እስካሁን የደረሰችዉን ያቺን ቅድስት አገር ዛሬ ጉልበትና ጠብ መንጃ አለን ባዮች ከፍተኛ መዘዙን ባለማስተዋል አጥፍተዋት ቢሄዱ በምድርም በሰማይ ሊያስጠይቃቸዉ እንደሚችል መገንዘብ ይኖርባቸዋል። አስተዉሉ ለተመለከተ ሁሉ ዜጋ እነዚህን ጥያቄዎች መረዳት ከባድ ሆኖ አይመስለኝም፡፡

  • የተቃዋሚ ድርጅቶች አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎች

(ሀ)    መግቢያ

በሰማዩ በስተቀር በምድር የመንግሥት ጥሩ የለዉም። ሁሉም የየራሱንና የደጋፊዎቹን ጥቅም ነዉ የሚያስቀድም። መንግሥት በአብዛኛዉ መልካም ነገር የሚሠራዉ በሕዝቡ ሲገደድ ነዉ። ሕዝቡን የሚያስተባብሩት ደግሞ ተቃዋሚ ድርጅቶች ናቸዉ። ‘አንድ ሕዝብ የሚገባዉን መንግሥት ያገኛል’ የሚልም አነጋገር አለ። የተጨቆነዉ ወገን ጭቆናዉን ተቀብሎ ቁጭ ካለ ሲሰቃይና ሲያልቅ ይኖራል።  ጭቆናዉ በቃኝ፤ አንገፈገፈኝ ብሎ ተባብሮ ለመብቱ የታገለዉ ህዝብ ግን የሚያስፈልገዉን ለዉጥ ያመጣል፤ የታወቀ ሃቅ ነዉ።

ተቃዋሚ ድርጅቶች ህብረት ካጡ፤ እርስ በርሳቸዉ ከተጠላለፉና ከተዳከሙ ሕዝቡን ማስተባበር አይቻላቸዉም። የአምባ ገነን መንግሥታትን ዕድሜ ብቻ ነዉ የሚያራዝሙት። ባለፉት 40 ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ የትግል ታሪክ ዉስጥ የታየዉ ይሄዉ እዉነታ ነበር። ጥሩ አእምሮ ያለዉ ዜጋ ይሄን ሃቅ ሊክድ አይችልም።

‘ኢትዮጵያ ሀገሬ፤ ሞኝ ነሽ ተላላ፤ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ’ ይላል የአገሬ ሰዉ።

ዐፄ ቴዎድሮስ ለዉድ ሀገራቸዉ ዕድገትና ሕልዉና ብለዉ ሲወድቁ ከጎናቸዉ የቀሩት ገብርዬና ጥቂት ወገኖች ብቻ ነበሩ። ካህኑ ጭምር ነበር ጠላት የሆነባቸዉ። በቀ/ኃ/ሥ ዘመን ላገሩ ነፃነት ከተዋደቀዉ አርበኛ ይልቅ የተንደላቀቀዉ የባንዳዉ ክፍል ነበር። በተፈራረቁት መንግሥታት ሥር ሃቀኞች ለዲሞክራሲና ለእኩልነት ደማቸዉን እንዳፈሱና አጥንታቸዉን እንደከሰከሱ ታሪክ ሲያስታዉሳቸዉ ይኖራል። በአንፃሩም ደግሞ ረጅም ራዕይ የሌላቸዉና የማይተባበሩ ተቃዋሚ ተብዬዎችና ሆድ አደር ተለጣፊዎችም ከባድ ጥፋቶች ሲደጋግሙ ይታያሉ። ህብረትና ዲሞክራሲ እያሉ ባፋቸዉ  ይሰብካሉ፤ በተግባር ግን አፍራሾች ሆነዉ ይታያሉ። አንዴ ተለጥፈዉ ገብተዉ በካድሬነት በማገልገል ህዝባችንን ይረግጣሉ፤ ፍትህ ያዛባሉ፤ ምርጫ ያጭበረብራሉ፤ ወደዉጪ ሲወጡ ደግሞ ለከባድ ጥፋቶቻቸዉ ገና ይቅርታ እንኳን ሳይጠይቁና ንስሐ ሳይገቡ የህዝብ አስተማሪዎችና መካሪዎች መሆን ይፈልጋሉ፤ መድረክም የሚሰጠዉ በአብዛኛዉ ለነዚህ ዓይነት አጭበርባሪዎች ነዉ። ለሚቀጥለዉም መንግሥት ደግሞ ዐይን አዉጥተዉ ፊት ለፊት ቆመዉ ይጠባበቃሉ። ሃቀኞችንና አርበኞችን ማን ይፈልጋቸዋል? የረባ ለዉጥ ለማምጣት እንደመተባበር እንቅፋቶች እየሆኑ የአምባገነን መንግሥታትን  የጭቆናና የህዝባችንን ሰቆቃ ዘመን ሲያራዝሙ የሚታዩ ሰዎች ናቸዉ። እኔ ብቻ ካልገዛሁ፤ እኔ ብቻ ካልመራሁ፤ እኔ ብቻ ካልበላሁ እያሉ ይስገበገባሉ።

ሰዎች ከሆንን ካለፉት ጥፋቶች መማር ይኖርብናል። ሁሉንም ባንድ ላይ መጨፍለቅና መፈረጅ ኃጢአት ነዉ።  እያንዳንዱ ዜጋ ትክክለኛዉን ግንዛቤ መጨበጥ ይኖርበታል። ሀቁን በመገንዘብና በመንተራስ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በጋራ መመስረት ይኖርብናል። ከዚህ በታች ከተመለከቱት ካለፉት ጥፋቶችና ዉድቀቶች ካልተማርን እንዴት ወደፊተ መራመድ ይቻለናል?

(ለ)    በርርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት

እላይ ባጭሩ እንደታየዉ፤ ሥርዓቱን ለመጣልና ዲሞክራሲን ለመገንባት በተለይ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ግልጽ ትግል ተጀመረ። እነ ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ፤ ገርማሜ ነዋይና ወርቅነህ ገበየሁን የመሳሰሉት ሃቀኛ ዜጎች ከፍተኛ ጥቅማቸዉን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸዉን ጭምር መስዋዕት በማድረግ በንጉሡ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ሙከራ አደረጉ። ዳሩ ግን በዘመኑ በቂ ተመክሮ ባለመኖሩና ባንዳንድ የዉስጥና የዉጪ ራስ ወዳዶች ሴራ ሊከሽፍ ቢበቃም ታላቅ ምሣሌ ጥሎ አለፈ። ከዚያም በመቀጠል በዓለም ገናናነትና ዝናን ያተረፈዉ ሀቀኛዉ የተማሪዎች እንቀስቃሴና ትግል እነዚህን ጭቆናዎች ለማስወገድ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል። በተቀናጀ የሕዝብ ትግል የታላቁ ንጉሠ ነገሥት የአገዛዝ ዘመን አከተመ።

(ሐ)   በወታደራዊ አገዛዝ ዘመነ መንግሥት

የንጉሠ ነገሥቱ አገዛዝ በሚያከትምበት ወቅት በደንብ የተደራጀ የፖሊቲካ ቡድን አልነበረም። በመሆኑም ለዉጡ በወታደሮች ሊጠለፍ በቃ። ዲሞክራሲ እንደገና ታፈነ፤ አምባገነንነት ነገሠ። በመሆኑም የተማሪዉ እንቅቃሴ እያየለ መጣ። በመቀጠልም ከዝነኞቹ የተማሪዎች፤ መምህራን፤ ሠራተኞች፤ ወዘተ እንቅስቃሴዎች የፈለቀዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ቅልጥ ያለ ትግሉን አቀጣጠለ። እንደነመኢሶን የመሳሰሉት ድርጅቶች ግን ከደርግ መንግሥት ጋር ወገኑ። ምናልባት የኢሕአፓ አባላት ተጠራርገዉ ካለቁ በኋላ ሥልጣኑን ከወታደሮች እጅ በቀላሉ ለመንጠቅ የሚችሉ መስሏቸዉ ይሆናል። በኋላ ግን ደርግም ነቃባቸዉና እነርሱንም ጠራርጉ ከኢሕአፓና ከሌሎች ጠላቶቹ ጋር ባንድ ጉድጓድ ቀበራቸዉ። ‘በቁማቸዉ ጎን ለጎን ቁመዉ በህብረት መታገል ያልቻሉት የኢትዮጵያ ልጆች ባንድ ጉድጓድ ተከተቱ’ ተብሎ በታሪክ ተመዘገበ።

እዚህ ላይ አንድ እዉነታን ማስጨበጥ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ ያፈራቻቸዉ እጅግ በጣም ብሩህ የነበሩ ወጣቶች፤ መምህራን፤ መሃንዲሶች፤ ነርሶች፤ ዶክተሮች፤ ወዘተ ለዲሞክራሲና ለእኩልነት ሲሉ የከፈሉትን የሕኢወት መስዋዕትነት ታሪክ ሲያስታዉስ ይኖራል። ዛሬ ወደኋላ እየተመለከቱ እነዚያ ተማሪዎች ተሳስተዋል፤ እግዚአብሔርን ረሱ፤ ፀሐዩን ንጉሡ መንካት አልነበረባቸዉም፤ የባሰዉን አመጡብን፤ ወዘተ እያሉ ባለማወቅ የሚኮንኗቸዉ ወገኖች ሲያጋጥሙኝ እጅግ በጣም አድርጌ አዝናለሁኝ። እላይ እንደተጠቀሰዉ በትግሎቹ ረጅም ሂደቶች ዉስጥ አንዳንድ ስህተቶች አልተሠሩም አልተባለም። በሃይማኖት ላይ ግን ሁን ብሎ የዘመተ ትዉልድ አልነበረም። አብዛኞቹ በቤተክርስቲያን ወይም በመስጊድ ዉስጥ ተወልደዉ በመልካም ሥነ ምግባር ያደጉ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያልተለያቸዉ፤ ከራሳቸዉ በላይ ለአገራቸዉና ለህዝባቸዉ የሚያስቡና የሚቆረቆሩ ወርቅዬና ብርቅዬ ልጆች ነበሩ፤ ከወንዱም ከሴቱም። በቤተክርስቲያን አስተዳደር ላይ የነበረዉ ቅሬታ ቢኖር በጭፍን ነገሥታትን፤ መሪዎችንና መኳንንትን ብቻ እያወደሱ የተጨቆነዉን ወገን በመዘንጋታቸዉ ነበር፤ አሁንም ነዉ። ስለዚህ ታሪክ የሚገመገመዉ በወቅቱ በነበረዉ ንቃተ ሕሊና እና በተወሰደዉ የትግል እንቅስቃሴ እንጂ በዛሬ መነጽር መሆን የለበትም ብዬ አምናለሁ። ያለፈዉን እንደታሪክ እያየን፤ ከመልካም ጎኖቹ መልካም ትምህርቶች እየቀሰምን ዛሬ የተሻለዉን ወይንም ቢያንስ እኩል አስተዋጽኦ ከፍሎ አገርን ከጥፋት ማዳን እንጂ  ያለፈዉን ሁሉ እኩል እየኮነኑ ቁጭ ብሎ ማላዘንን እግዚአብሔር አይወደዉም፤ ለወገንም ለታሪክም አይበጅም። ትላንትን ለዚያዉም በተንሸዋረረ መነፅር እያዩ የትዉልዱን አባላት  እንዳሉ ለመኮነን መሞከር ከማህበረሰብ ሣይንስም አንፃር ትልቅ ስህተት ይሆናል። የዚያ ትዉልድ ተማሪዎች እኮ በኢትዮጵያ ምድር ተወልደዉ፤ ኢትዮጵያዉያን/ት ሆነዉ ኖረዉ፤ ኢትዮጵያ አለባት ብለዉ ላዩትና ላመኑበት ችግር፤ መፍትሄ ይሆናል ብለዉ ባመኑበትን አቋም ፀንተዉ ኢትዮጵያዊ/ት እንደሆኑ ነዉ የሕይወት ዋጋ የከፈሉት!

ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ሀቁን በይበልጥ ለማስጨበጥ ከነፃ ዜና አዉታሮች ብዙ ይጠበቅባቸዋል። ሰዉ ይሞታል፤ ይገደላል፤ ታሪክ ግን አይሞትም፤ መረሳትም የለበትም። ከዬት እንደመጣንና አሁን ያለንበትን ካላወቅን ወዴት እንደምናመራ በቅጡ ልንገነዘብ አይቻለንም። ከጥፋት ይሰዉረን።

(መ)  በወያኔ/ኢህአደግ አገዛዝ

እላይ እንደተገለጠዉ ከመግባታቸዉ በፊት በለንደን ላይ በተዘጋጀዉ የይስሙላ ‘የሰላም’ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት መገንጠልን የሚያራምዱ የፖሊቲካ ኃይሎች ብቻ ነበሩ። እነ ኦነግ ተከትለዉ ገብተዉ የሽግግሩን ቻርተር ፈርመዉ ተቀላቀሉ፤ ብዙም ሳይቆዩ በሥልጣን ድልድል ተጋጭተዉ በገቡበት አይሮፕላን ካገር ኮበለሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በግልም ሆነ በቡድን እየሆኑ ካሜሪካና ካዉሮፓ ሄደዉ አንዳንድ ቦታዎች ያዙ።

አዚህ ላይ በ2003 ዓ/ም ስለተፈጠረዉ ህብረት ትንሽ ልጠቅስ አወዳለሁ። የሕዝቡ ብሶት እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት ባገርም ሆነ በዉጪ ያሉት ወገኖች ተነቃንቀዉ አስፈሪ ትግል ጀመሩ። በ2003 ዓ/ም (በፈረንጆች አቆጣጠር) 15 የተቃዋሚ ፖሊቲካ ድርጅቶች ለ15 ቀናት በር ዘግተዉ ተወያይተዉ ተማምለዉ ህብረት ፈጠሩ። እነ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስና፤ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን የመሳሰሉ እጅግ በጣም የተከበሩ አባቶች ተሳትፈዉ ግሳጼ፤ ምክርና ቡራኬ ሰጧቸዉ። ይሄም ለሰላም ወዳድ ወገኖች በሙሉ ታላቅ ብሥራት ነበረ። የህብረቱም ሠነድ የሚከተሉትን ታላላቅ ስምምነቶች ያካተተ ነበር፤

  • ትግሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲሁን፤
  • በታቀደዉ የ2005 ዓ/ም አገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ የሚከተሉት አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎች መሟላታቸዉን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸዉ፤ የነፃ ምርጫ ቦርድ መመስረትና በያንዳንዱ ምርጫ ኬላ ላይ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ገለልተኞች ታዛቢዎች መገኘት እንደሚኖርባቸዉ፤
  • ሁሉም የፖሊቲካ ድርጅቶች እኩል እንዲሳተፉ ሁኔታዎች መመቻቸት እንደሚኖርባቸዉ፤
  • እነዚህ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ግን ከምርጫዉ መገለልና የሕዝብ ሰላማዊ አመፅ መቀስቀስና መምራት ግዳጅ መሆን እንዳለበት ተስማምተዉ ተፈራረሙ።

ዳሩ ግን ተደጋጋሚ ዕድላችን ሆነና ገና ዓመት ሳይሞላቸዉ አንዳነድ አባላት ህብረቱን ጥለዉ ወጡ። በህብረቱ ጎን ቅንጅትን ፈጠሩ። አሁንም ተስፋ ሳይቆረጥ ህብረትና ቅንጅት የጋራ ትግል ለማካሄድ ተስማሙ። እጅግ የሚያሳዝነዉ ግን በነዚህ ስምምነቶችና ቃልኪዳኖች ብዙም መግፋት አልተቻለም። ይባስ ብሎም ብዙ አባላት የነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ሥነ ሥርዓት ቅድመ ሁኔታዎች ገና ሳይሟሉ የሕዝባችንን ጥያቄ ንቀዉ ዘልለዉ በምርጫዉ ዉስጥ ተሳተፉ። ከዚያ በኋላ በግለሰቦቹና በፓርቲዎቻቸዉ ላይ የደረሰዉን ኣሳዛኝ ድርጊትና የሕዝባችንን ተደጋጋሚ ሰቆቃ ሁሉም ዜጋ የሚያዉቀዉ ሃቅ ስለሆነ መዘርዘሩ ጊዜ ማባከንና ሰዉ ማሰልቸት ይሆናል በማለት ዝርዝር ዉስጥ መግባት አልፈለግሁም።

ኛ/   የአማራጮች ግምገማ (Options Appraisal)

አሁን ባለንበት ቀዉጢ ዘመን ሊወሰዱ የሚችሉ አማራጮችንና የያንዳንዱን ጥቅምና ጉዳት እንደሚከተለዉ ማየትና መመርመር ይገባል ብዬ አምናለሁ።

(ሀ)   ሁኔታዎችን እንዳሉ መተዉ

የባሰዉ እንዳይመጣና አገሪቷም እንዳትበተን ያለዉ መንግሥት ቢቀጥል ይሻላል የሚሉ ጥቂት ሰዎች አሉ።  አብዛኞቹ ግን ወያኔ/ኢሕአደግ 25 ዓመታት ገዝቷል፤ በነዚህ ረዥም ዘመናት ብዙ ጉዳቶች ደርሰዋል፤ ዛሬ ደግሞ አገሪቷ በጊዜያዊ አዋጅ ስር እየማቀቀች ትገኛለች፤ በቃ፤ ለሁሉም ጊዜ አለው፤ ማንም ኃይል ለዘለዓለም ሊቀጥል አይችልም፤ የለዉጥ ሰዓት ደርሷል ይላሉ። ስለዚህ ባለዉ ሁናቴ ለረዥም ጊዜ የመቀጠል ዕድሉ በጣም የመነመነ ይመስላል። መንግሥትም ሆነ ህዝቡ ይሄንን ጠንቅቀዉ የሚገነዘቡ ይመስላል። ስለዚህ ይሄ እንደጥሩ አማራጭ ሊወሰድ የሚችልበት ሁናቴ ያለ አይመስልም።

(ለ)    ቅድስት አገር ማፍረስና ዘመነ መሣፍንትን መመለስ

የግንጠላ ዓላማን የሚያራምዱ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ኢትዮጵያ መፍረስ አንዳለባት ሲሰብኩ ይሰማሉ። በዚህም ላይ የአፍሪቃን ምድር መልሰዉ ሊቀራመቱ የሚሹና በተለይ ለአትዮጵያ ጥፋት የማይተኙ የዉጪ ታሪካዊ ጠላቶች  ይሄንን ዓላማ ከማራመድና ከመደገፍ የሚቆጠቡ አይመስሉም። ሆኖም ግን የኢትዮጵያን የቆዳ ስፋትና የህዝቧን ስብጥር ለተመለከተ አስተዋይ ይሄ የሚያዋጣ አማራጭ ሊሆን ከቶ እንደማይችል ያዉቃል። ቢፈልጉም እንኳን የእያንዳንዱን ጎሣ ድንበር ለመከለል በዓለም ላይ የሚገኙ የካርታ ልሂቃን ቢሰበሰቡ የሚቻላቸዉ ነገር አይሆንም። እያንዳንዱ ነገድ በሁሉም የአገሪቷ ክፍል ሰፍሮ ይገኛል፤ በደም፤ በጋብቻ፤ በወገንነት ተሳስሮ ለብዙ ዘመናት ኖሯል። አገሪቷን ብዙ ቦታ በጣጥሶ በድንበር ግጭት ጭቁኑ ህዝቡ እርስ በርሱ የሚጨራረስበት ምክንያት ይኖራል ብሉ መገመት በጣም ያዳግታል። የተገነባዉን ከማፍረስ ይልቅ ያለዉን በመጠገን በእኩልነት፤ በሰላም፤ በፍቅርና በብልፅግና አብሮ መራመዱ አማራጭ የለዉም የሚሉ  ዘጎች ቁጥር እጅግ በጣም ያመዝናል። ስለዚህ ይሄን ጥያቄ እንደአማራጭ መዉሰድ አይቻልም።

(ሐ)   የሚቀጥለዉን መንግሥት የዉጪ ኃይሎች እንዲያዘጋጁልን

ዛሬ ከዉጪ ታላላቅ ኃይሎች ተጽዕኖ ዉጪ የራሳችንን መንግሥት በራሳችን መመሥረት አንችልም ብለዉ የሚገምቱ ሰዎች ይኖራሉ። በሌላዉ ጎን ደግሞ እኛ ራሳችንን በራሳችን ማስተዳደር የምንችልና የብዙ ሺህ ዓመታት ልምድ ያለን ሰዎች የማንም አገር ጥገኛ መሆን አይገባንም። የዉጪ ኃይሎች ሁሌም የሚቆሙት ለራሳቸዉ ጥቅም እንጂ ለኛ እንዳልሆነ ታሪክ ምስክራችን ነዉ፤ ዛሪም እኛን እያፈናቀሉ መሬቶቻችንን ቀምተዉ ሲበለጽጉ እኛ በርሃብ አረንቋ እየተጠበስንና እያለቅን ነን፤ ወዘተ፤ ስለዚህ በምንም ዓይነት ወደ ቀጥታም ሆነ ተዘዋዋሪ ቅኝ ተገዥነት  ዉስጥ መግባት ከቶዉንም አይገባንም  የሚሉ ወገኖች ቁጥር እጅግ በጣም ስለሆነ ይሄም እንደአማራጭ ሊወሰድ የሚችል ጉዳይ አይደለም።

(መ)   የአገሩን ሠርዶ በአገሩ በሬ (ችግሮቻችንን እኛዉ በእኛዉ በህብረት መፍታት አለብን)

እላይ የተመለከቱት ሀሳቦች ጥሩ አማራጮች ሊሆኑ እንደማይችሉ ባጭሩ ለማሳየት ተሞክሯል። መፍትሔዉ በጎሣ ወይም በሃይማኖት ሳንከፋፈል ንጹሕ ዲሞክራሲን መገንባት ብቻ ነዉ። የዲሞክራሲ ግንባታ ደግሞ የወሬ ጋጋታ ሳይሆን በተግባር የሚታይ መሆን አለበት። ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ እያሉ ከህዝብ መሸሽ አይቻልም፤ የለዉጡ ባለቤት ህዝቡ ራሱ መሆን አለበትና። ህዝቡ ራሱ የፈለገዉን የመምረጥና የማስወገድ መብት ሳይኖረዉ የዲሞክራሲ እንቅስቃሴ አለ ብሎ መገመት ይቻላል? አይቻልም፤ ራስን ለማታለል ወይንም ህዝቡን ለማጭበረበር ካልሆነ በስተቀር። በአገር ዉስጥ ያለዉ ህዝባችን ሙሉ መብቱ መጠበቅ አለበት። በዓለም እንደአሸዋ የተበተነዉ ወገን ተመልሶ በኩራት እየኖረ ሕዝባችንን እንዲያገለግል ጥርጊያ መንገድ ማበጀት ይኖርብናል። እግዚአብሔር የሰጠንን ሰፊ የተፈጥሮ ኃብት ለወገኖቻችን ማብቃትና ርሃብን፤ ጥማትን፤ እርዛትን፤ ስደትንና እንግልትን ለማስወገድ ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል። ቁርጥ ያለዉ የዲሞክራሲና ራስን የመቻል አማራጭ ይሄን ይመስላል፤ በኔ ቅን እይታ።

፭ኛ/   መደምደሚያ

አሁንም ካለፉት ስህተቶችና ጥፋቶች መማር አንችልም ወይ?

ዛሬ በዉዲቷ አገራችን ላይ ቀኑ እጨለመባት ይገኛል።  ብዙም አማራጮች የሉንም።አሁን የደረስንበት ዉድቀት ህዝቡን ብቻ ሳይሆን ባለሥልጣናትንም እኩል ማሳሰብ አለበት። ሥልጣን ይመጣል፤ ይሄዳል። ገንዘብ አብሮ ጉድጓድ አይገገባም።  አገር ግን ለእኛ ብቻ ሳትሆን ለሚቀጥሉትም ትዉልዶች መትረፍ ይኖርባታል። አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን ደማቸዉን አፍስሰዉ አጥንታቸዉን ከስክሰዉ በነፃነት ያቆዩዋት ቅድስት አገር እንዴት በእኛ ዘመን እንዲህ እየተጎዳች ህልዉናዋ አጠራታሪነት ዉስጥ ይገባል? ምርጫዉም ሆነ ኃላፊነቱ የሁላችንም መሆን ይገባዋል።

ወያኔ/ኢሕአደግ ለዘለዓለም ሊገዛ አይችልም፤ ለሁሉም ጊዜ አለዉና። በዓለም ታላቅ ዝና ያተረፉት የቀ/ኃ/ሥና በአፍሪቃ አህጉር መሬትን ያንቀጠቀጠዉ የደርግ መንግሥት ቀናቸዉ ሲደርስ እንዴት እንደመነመኑና እንደከሰሙ መዘርዘር አይኖርብኝም፤ በታሪክ ፊት ተቀምጧልና። በሩቁም በእነ አሜሪካ ለረዥም ዓመታት ሲረዱና ሲደገፉ በነበሩት በእነ ሞቡቱ፤ የሻህ ንጉሥ፤ ሆስኒ ሙባረክ፤ ወዘተ ላይ በመጨረሻ የደረሰዉን ዉርደት መርሳት  የለብንም።

ተቃዋሚ የፖሊቲካ ድርጅቶች ነን የሚሉትና በተግባር ግን የጭቆናን ዘመን የሚያራዝሙ በሙሉ ካለፉት ስህተቶች ገና ሊማሩ አልቻሉም፤ ‘ድር ቢያብር አንበሳ ያስር’ የተባለዉን ቅዱስ አሳብ ደጋግመዉ መናቃቸዉ ያስተዛዝባል። ቁርጥ ያለ አቋም ያስፈልጋል፤ ከዛፍ ዛፍ መዝለል ዬትም አያደርስም። ለጊዜያዊ ጥቅማ ጥቅሞች በርካሽ መገዛትና አገርን መሸጥ በሰማይም በምድርም ያስጠይቃል። ቀኑ ሲደርስ ራቆታችንን ወደምድር እነደመጣን ሁሉ ራቆታችንን ወደዚያዉ እነደምንመለስ አንርሳ!!!

ምርጫዉ ለሁላችንም ክፍት ነዉ፤

  • ህብረት ማጠንከር የግድ ነዉ። እላይ ከተገለፀዉ የ2003 ዓ/ም የህብረት ምሥረታ፤ ከፍተኛ አስተዋጽኦና አለኝታነት ብዙ መማር ይኖርብናል። አሁንም የመንፈስ እጅግ በጣም ያስፈልገናል – ከሊቅ እስከዴቂቅ ድረስ። ካለዚያ አገራችንን ለማዳከም ወይ ለማጥፋት ለሚፈልጉት ጠላቶች መጋለቢያ ቦታ ሆነን እንቀራለን። በዚያ ደግሞ የሚደሰት ማንም ዜጋ ይኖራል ብዬ መገመት አልችልም። ወደ 2003 ዓ/ም ስምምነት ብንመለስ ይሻላል። ሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ተቀራርበዉ በዲሞክራሲ ግንባታ ላይ መተባበር ይኖርባቸዋል። እንዲያዉ ቁጭ ብለን ወያኔ/ኢሕአደግ፤ አሜሪካና ሌሎች የዉጪ መንግሥታት የሚቀጥለዉን መንግሥት ያመቻቹልናል ብሎ መጠበቅ ‘ዉሃ ቅዳ ዉሃ መልስ’ ብቻ ነዉ የሚሆነዉ። ካሁንም ወዲያ ቑጭ ብሉ በተደጋጋሚ የሚታለል ዜጋ አይኖርም።
  • የነፃ ዜና አገልግሎት ድርጅቶች/ሚዲያ ነን የሚሉት ሁሉ በቅንነት ሁሉንም ዜጎችና ድርጅቶች ማሳተፍ ይጠበቅባቸዋል። ከተሰቃዩ፤ ከታሰሩ፤ ከተሰወሩና ከተገደሉ ንፁሓን ዜጎች መካከል እየመረጡ ማቅረብና ሌሎቹን መርሳቱ የሙያ ጉድለት ስለሚሆንና ስለሚያስተዛዝብ የተሻለ ጥረት እንዲደረግ ጨምሬ ላሳስብ እወዳለሁ።
  • አገራዊ እርቀ ሰላም ማዉረድ የተባረከና ቀና ተግባር ነዉ። ከኒልሰን ‘ማዲባ’ ማንዴላ ጥረቶች ትንሽ ብንማር መልካም ነዉ። እርሳቸዉ ለአገራቸዉ ነፃነትና ሰላም ሲሉ ከአፓርታይድ ጠላቶቻቸዉ ጋር እንኳን ታርቀዋል። አሁን ያለፈዉ አለፈ። ይቅር መባባል አለብን። ለወደፊቱ መልካም ራዕይ ፈጥረን አገራችንን ከጥፋት ማዳን አለብን። በሕዝብ ተመርጠዉ በሕዝብ መሃል በነፃ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉና ሕዝባችንን ተንከባክበዉ አገራችንን ወደ ጥፋት ሳይሆን ወደ ዕድገት ጎዳና ሊመሩ የሚችሉትን መሪዎች መፍጠር አለብን። በተለይ ከኤርትራ ወገኖቻችን ጋር ሰላም መፍጠር አለብን፤ ተወደደም ተጠላ የብዙ ሺህ ዓመታት የጠበቀ ትሥሥር አለንና።
  • ለዚህም መፍትሔዉ ንጹሕ ዲሞክራሲን መገንባት ብቻ ነዉ።
  • በዓለም እንደአሸዋ የተበተነዉ ወገን ተመልሶ በኩራት እየኖረ ሕዝባችንን እንዲያገለግል ጥርጊያ መንገድ ማበጀት ይኖርብናል።
  • እግዚአብሔር የሰጠንን ሰፊ የተፈጥሮ ኃብት ለወገኖቻችን ማብቃትና ርሃብን፤ ጥማትን፤ እርዛትን፤ ስደትንና እንግልትን ለማስወገድ ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል።

ቸሩ አምላካችን ቅን ልቦና ይስጠን፤ ይታረቀን፤ ወገኖቻችንና ውድ አገራችንን ይጠብቅልን፤ አሜን

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop