–ዘውጋዊነትን መታገል የኢትዮጵዩያ ታላቅነት መሰረት–
አክሎግ ቢራራ (ዶር)
“የሕሳባችን ዋናው አላማ ፤ በዜጎቻችን መካከል፤ በዘርም ሆነ በሐይማኖት አንድም ልዩነት እንዳይኖር ማድረግ ነው። ማንኛቸውም ኢትዮጵያዊ ትክክለኛ መብት እንዲኖረውና የተወደደው ሕዝባችን ሁሉ የአንድ ትልቅ ቤተሰብ ተወላጆች ሆነው በወንድማማችነት እኩል በሠላም እንዲኖሩ ዘወትር የተከተልነው አላማ ነው።”
ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ
“ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ኢትዮጵያ”
ዶር ዐብይ አሕመድ
ክፍል ሶስት
አፄ ኃይለ ሥላሴን እኛ ኢትዮጵያዊያን “የአንድ ትልቅ ቤተሰብ ተወላጆች “ ሆነን በጋራ እንድንኖር ያሳሰቡትን የአንድ ታላቅ መሪ ምክር ብንሰማ ኖሮ አሁን ወደ አለንበት አዘቅት አንገባብ ነበር። ያደረግነው ተጻራሪውን ነው። በተመሳሳይ፤ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ኢትዮጵያ” አግባብ ያለው መፈክር፤ መርህና እሴት ነው። አቅጣጫ ወይንም ምኞት ወደ ተግባር ሲቀየር ተራራ ሊለውጥ ይችላል። የጋን መብራት ከሆነ ግን ፋይዳ ቢስ ነው። በምኖርበት በአሜሪካ ዜጎች ስለ ስኬት ሲተቹ “Walk the talk (የምትናገረውን ስራ ላይ አውል” ይላሉ።
በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ማንኛውም ዜጋ በሰብእነቱ፤ በሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብቱ ተከብሮ “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ አገሬ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት” ብሎ ራሱን ቀና አድርጎ፤ ሕገመንግሥቱ በደነገገው መሰረት በየትኛውም አካባቢ ሰርቶ፤ ኃብት ይዞ፤ ደህነነቱ በሕግ ተከብሮ፤ ያለ ምንም ስጋትና ጭንቀት የሚኖርባትን ኢትዮጵያን ገና አልመሰረትንም። “ስንኖር ኢትዮጵያዊ” ነን ለማለት የምንደፍረው የዜግነትና ዲሞክራሳዊ መብታችን ሲከበር ነው።
የኢህአዴግ ሕገመንግሥት ሲዋቀር ሰብሳቢና ወሳኝ መርህ ያደረገው “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮ፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” በሚል መለያ ነው። “እኛ ኢትዮጵያዊያን” ማለት የተከለከለው ለምንድን ነው? አንቀጽ 39 (1) “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፤ ብሔረሰብ፤ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማንኛውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” ይላል። ልክ ትህነግ/ ህወሓት እንዳደረገው፤ የዘውግ ልሂቃንና አለቃዎች ይህንን አንቀጽ የሚተረጉሙትና ተግባራዊ የሚያደርጉት ተራውን ነዋሪ እያማከሩ፤ የሁሉንም በመልካ ምድሩ የሚኖሩትን ግለሰቦች ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብቶች አክብረውና አስከብረው አለመሆኑን በተደጋጋሚ አይተናል። አንቀስ 39 (3) “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፤ ብሔረሰብና ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር መብት አለው” ይላል። ራስን ማስተዳደር የተከበረ ዲሞክራሳዊ መብት ነው። ራስን ማስተዳደር ግን ሌላውን ማፈን፤ መጨፍጨፍ፤ ማግለል ወዘተ ሊሆን አይችልም።
ክልላዊ መብት የክልሉ “ብሔር፤ ብሔረሰብና ሕዝብ” አባል አይደሉም ብሎ የበየነባቸውንና የለያቸውን ኢትዮጵያዊያን እንዴት ያስተናግዳቸዋል? ብሎ መጠየቅ አግባብ አለው። ተቃርኖውን በግልጽ ለማጤን አንድ ምሳሌ ላቅርብ። ኦሮሞ ወይንም ጉራጌ ወይንም ትግሬ ሆኖ ያለ ምንም ስጋት በጎንደር ከተማ ለመኖርና ኃብት ለመያዝ ይቻላል። ተከታታይ ጭፍጨፋው የሚያሳየው ግን፤ አማራ ሆኖ ከአማራው ክልል ውጭ ለመኖርና ኃብት ለመያዝ የሚቻልበት ሁኔታ እየጠበበ ሄዷል። ለምን?
ምክንያቱም፤ በአብዛኛው ሲመረመርና ሲገመገም፤ የጭፍጨፋውና የሌላው ግፍ ኢላማ የሆነው የአማራው ዘውግ አባላትና የክርስትና ኃይማኖት አባላት ናቸው። ለምሳሌ፤ በምእራብ ወለጋ (ኦሮምያ) እና በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ በተከታታይ የሚካሄደው እልቂትና ግዙፍ ፍልሰት ከዚህ ከተሸራረፈና የተዛባ የሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብት ግድፈት ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህ የግፍ ግፍ የሚደርስባቸው ወገኖቻችን “ሲኖሩም ኢትዮጵያዊ” ናቸው ለማለት የሚያስችል መስፈርት ፈልጌ አላገኘሁም። በተጨማሪ፤ ቁጥራቸው ግዙፍ ወይንም ብዙ የሆኑት፤ ለምሳሌ በመተከል የሚኖሩት አማራዎች፤ አገዎች ወዘተ ሕገመንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ሊኖራቸው ይገባል። ግን የላቸውም። ምክንያቱም፤ “ይህ መብት ብሔሩ፤ ብሔረሰቡ፤ ሕዝቡ በሰፈረበት መልክአምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌደራሉ አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል” ይላል። “ሕገመንግሥቱ እኮ ይሰራል” ለሚሉት ግለሰቦችና ደጋፊዎች የማሳስበው በአፈጻጸም መስፈርትም ይገምገም ቢባል ሚዛናዊና ፍትሃዊ የሆነ ሁኔታ አይታይም። ግፍና በደል የሚደርስበት ሕዝብ መብት የለውም ማለት ነው?
“ስንኖር ኢትዮጵያዊ” ነን ብለን ራሳችንን ከለየን (የእኔ ምኞች ይኼው ነው)፤ ጉራጌ፤ ትግሬ፤ ሶማሌ፤ አኟክ፤ ወላይታ፤ አማራ፤ ኦሮሞ ወዘተ በማንኛው የኢትዮጵያ መልክአምድር፤ ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብቱ ተከብሮ ያለ ምንም ስጋት የሚኖርባትን ኢትዮጵያን እንደ ሉአላዊት አገር ተቀብለናል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ለድርድር አይቀርቡም የሚለውን መርህ ላስምርበትና ሌላው ለድርድር መቅረብ የሌለበት መርህ ደግሞ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብት መከበር ክፍተት ጉዳይ አለመፈታቱ ነው። ይህ መብት ደግሞ በማንነትና በእምነት የሚደረገውን ማንኛውንም ጥቃት፤ ግፍ፤ አድልዎ፤ በደል፤ ጭፍጨፋና ሌላ ወንጀል ሙሉ በሙሉ ህገወጥ እንዲሆን ያስገድዳል። በዚህ ላይ የጋራ ግንዛቤ የለም።
በአገር ውስጥ ሆነ ውጭ፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን “ስንኖር ኢትዮጵያዊ” ነን ብለን ኩራት የሚሰማን፤ መላው የዓለም ጥቁርና ሌላው የዓለም ሕዝብ የሚያከበረንና አገራችንም እንደ ቀድሞው የምትከበረው እርስ በእርሳችን ስንከባበር፤ ዘውግና እምነት ተኮር እልቂቶችን ለማቆም ስንችል፤ በጋራ ሆነን ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ስንቀርፍ ነው። ዋናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጋራ ጠላት ድህነት ነው። በእኔ ግምገማ፤ በዘውግና በቋንቋ ልዩነቶች የተደነገገው ሕገመንግሥትና የከፋፍለህ ግዛው አይነቱ የክልል አስተዳደር “ስንኖር ኢትዮጵያዊ “ ነን ለሚለው መሰናክል ሆኗል። በተጨማሪ፤ ተከታታይ ሁከት፤ ጥላቻና መከፋፈል ለዘላቂና ፍትሃዊ ልማት ማነቆ ሆኗል። በትግራይ የወደመውን መሰረተ ልማት ብቻ መገምገም በቂ ሊሆን ይችላል።
እስከማውቀው ድረስ የአማራው ሕዝብ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነቱ ተደራድሮ አያውቅም። ይህ የጸና እምነቱ ግን ለባሰ አደጋ አጋልጦታል። ኢላማም ሆኖ ግን አገሩን ይወዳል። አገር ወዳድነቱ፤ ኢትዮጵያዊነቱና በመላው ኢትዮጵያ መኖሩ እንዲጋለጥና ራሱን እንዳይከላከል አድርጎታል። በተጨማሪ፤ በክፍል ሁለት እንዳሳየሁት፤ ፕሮቻዝካ ሆነ ብሎ ወደ ጎን የተወው ሌላም ጉዳይ አለ። የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮችን ከግፍና ከጭቆና የታደገችውን ኢትዮጵያን የአንድ እምነት ተከታይ ብቻ አድርጎ ቀርጿት እንደ ነበረ መርሳት እንደ ነበረ ማስታወስ ተገቢ ነው። “The greater part of the non-Christian tribes in Abyssinia has no more burning desire than to be freed from the tyranny of the Amharas… If they would vote freely they would certainly prefer a European protectorate to universally hated extortionists and slave drivers. This country is cracking at all its joints and has only been kept together up to the present by methods of ruthless coercion.” አስቡብት፤ ኢትዮጵያ የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮችን መቀበሏን፤ የእስልምና ተከታይ አማራዎች መኖራቸውን፤ እንሱም አገር ወዳድ መሆናቸውን፤ ነጻነቷን አስከብራ የቆየችውን አገር፤ ሃበሻዎች ከሚገዟችሁ ይልቅ፤ ነጭዎች ገዢዎች ሆነው ቢገዟችሁና ቢያሰለጥኗችሁ ይመረጣል ብሎ “ባሩዱ” እንዲቀጣጠል አመቻችቶልን ከዚህ ዓለም ተለይቷል።
የአፓርታይዱን የአስተዳደር ቅርጽ (“ክልል የሚባለውን) ማን ጀመረው?
የጣልያን ፋሺስት መንግሥት ይህንን መርህ ተግባራዊ አደረገው። ኢትዮጵያን ዘውጋዊ ማንነትን መርህ አድርጎ ሙሉ በሙሉ የመበታተን እቅዱ መሰረት የተጸነሰውና ተግባራዊ የሆነው በፈረንጆቹ ነው። ዛሪ የምእራብ አገር ተቋማት፤ እንደ ዲዋል ያሉ ተመራማሪዎች የሚያስተጋቡት ትርክት ተመሳሳይ ነው።
ከፋፍለህ ግዛው የቅኝ ገዢዎች የበላይነት ዘዴ ነው። በአሁኑ ወቅት፤ መላውን አፍሪካን ተቀራምተው የተፈጥሮ ኃብቷን የሚመዘብሩት በዚህ መሰረት ነው። ህወሓት ለአርባ ዓመታት በተከታታይ በየቦታው ንጹሃን ኢትዮጵያዊያንን ሲጨፈጭፍ ምንም አይነት ጫና አልደረሰበትም ነበር፤ እቀባ የሚባል ነገር አልታሰበም ነበር። በአሁኑ ወቅት፤ በትግራይ ክልል እና በአካባቢው ለተከሰተው ህወሃት የቀሰቀሰው ሰብአዊ ሁከት ላይ ልዩ ትኩረት የተሰጠው በምን ምክንያት ነው?
በእኔ ጥናትና ምርምር ኢትዮጱያን ለመከፋፈል ባለው ሴራ ምክንያት ነው። የጣሊያን ፋሽስቶች ምን አይነት ዘውግን መሰረት ያደረገ የአስተዳደር ጅኦግራፊ እቅድ ሰርተው ነበር?
የፋሽስቱ መንግሥት ኢትዮጵያን “Africa Orientale Italiana” በሚል ስያሜ ሸነሸናት፤ በጣልያንኛ “smembramento” (በመበታተን) ኢትዮያዊያን እርስ በእርሳቸው እንዲጋጩ መሰረት ጣለ።
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማውደምም ባለው እቅድ መሰረት የሚከተሉትን ህጋዊ ክፍፍሎች ዘረጋ፤
- አዲስ አበባ የራሷ አስተዳደር እንዲኖራት ተደረገ፤
- የአማርኛ ቋንቋ ተወግዶ ወጣቱ ትውልድ በአረብኛ፤ በከፋኛ፤ በኦሮሞኛ እንዲማር ተደረገ፤
- ኤርትርያ (ትግራይን ጨምሮ) አንድ ክልል ሆነች፤
- አማራ የሚባል ክልል ተመሰረተ፤
- ሃረር ራስ ገዝ ሆነ፤
- ሲዳሞ በኦሮሞ (“በጋላ”) አገር ገዢ እንዲተዳደር ተደረገ፤
- ባሌ፤ ሲዳሞ፤ ቦረና፤ ኦጋዴን፤ የጣልያን ሶማሌ መሬት ተጠቃለው በአንድ አገረ ገዢ እንዲተዳደሩ ተደረገ።
አሉታዊውና መዋቅራዊው ውጤት ምንድን ነው?
ዴል ቦካ የተባለ ተመራማሪ እንዲህ ወደሚል ድምዳሜ ደርሷል። “What immediately appears evident, from an analysis of the territorial division of these governments is the punitive concept which has inspired the legislator. The Ethiopian Empire has been dismembered, recomposed on prevalently tribal basis, and rendered unrecognizable.” ኢትዮጵያን እንደዚህ አድርገው በዘውግ ማንነት ስለበታተኗት የቀድሞዋን ኢትዮጵያን አስተዳደርና የሕዝቧን ስርጭት ይዘት ፈጽሞ ለማወቅ አይቻልም። ኢትዮጵያን እንዳልነበረች አደረጓት። አሁንም የምእራብ መንግሥታት የሚዶልቱት ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ለመበታተን ነው።
ለዚህ ምቹ ሁኒታዎችን የፈጠሩላችው ግን የአገር ውስጥ የዘውግ ልሂቃን፤ ምሁራንና ተጠቃሚዎች ናቸው።
የጣልያን ፋሽስት መንግሥት ኢትዮጵያን ለማዳከም ምን መስፈርት ተጠቀመ?
የጣሊያን መንግሥት የተጠቀመው መሳሪያ ከፋፍሎ መግዛትን ነው። ይኼ ደግሞ የፖለቲካ ውሳኔ ነው። የጣልያኑ አፈቀላጤ ፕሮፌሰር ራፋኤል ዲ ላውሮ የጻፈው እንዲህ ይላል። “The choice of the capital of each tribal government and border demarcation of the five component territories have been decided following a clear political criteria , that is to say, consideration of political opportunity and verification of unfailing positive result. The legislator has made every thing possible to keep strictly to the principle uniting under one government, people of the same linguistic, and ethnic, and historical identity.” እያንዳንዱ “የዘውግ፤ የቋንቋና የባህል የጅዖፖለቲካ ርእሰ ከተማ፤ ምድርና የዚህ ምድር አባል” ኢትዮጵያን እንደ ሃገር፤ ኢትዮጵያዊነትን እንደ አንድ አገር የዜግነት መለያው እንዳይቀበል አደረገው። ዋናው መለያ የዘውግ ማንነት ሆኖ ተደነገገ። የፈረንጅዎች አምልኮ መሰረት ተጣለ።
መለስ ዜናዊ በህይወት በነበረበት ጊዜ የተናገረውንና ህወሓት በመመሪያው ላይ ያሰፈረውን መርህ ማስታወስ በቂ ነው። “የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ሕዝብ ምኑ ነው?—ሰንደቅ አላማው ጨርቅ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመታት ታሪክ ነው “ ወዘተ። መለስ የተናገረው የአስተሳሰብ ድህነትንና ድንቁርናነትን ያሳያል። የአክሱም ሃውልት ትግራይ ውስጥ ቢሆንም፤ የትግራይ ሕዝብ ገናና ታሪክና ቅርስ የጋራ ኃብት ነው ቢል ኖሮ አብሮነትን ያጠናክር ነበር። የኢትዮጵያን መለያ “ጨርቅ ነው ሲል” ደግሞ ብዙ የጥቁር አፍሪካ አገሮች የተቀበሉትን፤ የአድዋን ጀግንነትና ድል መለያችንን ናቀውና አፈረሰው ማለት ነው። እሱ የተናገረውና የህወሓት መርህ “የአማራው ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው” ያለው ትርክት ያስተላለፉት ቅርሶች ሁሉ ጸረ-ሰላም፤ ጸረ-ሕዝብ፤ ጸረ-ኢትዮጵያዊነትና ጸረ-ኢትዮጵያ ናቸው። የጥላቻ ባህልና ክህደት የሚጀምረው እንደዚህ እያለ መሆኑን መረዳት ለመፍትሄው ይረዳናል።
በዘውግና በቋንቋ የማይታረቁ ልዩነቶች ላይ የተደነገገው ሕገመንግሥትና የአፓርታይድን ሞዴል የተከተለው የክልል አስተዳደር በጽንሰሃሳቡና በአስተዳደር ውቅረቱ ከጣሊያን ፋሽስቱ የተወረሰ ነው። በአሁኑ ወቅት፤ የምእራብ አገሮች ትግራይን ልክ እንደ “ሉዐላዊ አገር” ማየታቸው ለእኔ ምንም አስደናቂ አይደለም። ኢትዮጵያ በዘውግና በቋንቋ ተሸንሽና የትግራይ መንግሥት እስከ ልዩ መለያዎቹ የራሱ መንግሥት አለው፤ ሌሎቹም ክልሎች ተመሳሳይ ቅርጾች አሏቸው በሚሉ ሰለባዎች ተበክለናል።
የትግራይ መንግሥት ልዩ ኃይል የወታደራዊ ኃይሉና የመሳሪያ አቅሙ ከፌደራሉ መንግሥት መከላከያ የላቀ ነበር። በተመሳሳይ የኦሮሞ ክልል መንግሥት በብዙ መቶ ሽህዎች የሚገመት ልዩ ኃይልና ከፍተኛ የመሳሪያ አቅም አለው። የኦሮሞውን ለየት የሚያደርገው ሁኔታ ግን አለ። ይኼውም፤ ሩብ ሚሊየን ወይንም ሶስት መቶ ሽህ የኦሮሞ ልዩ ኃይል ተሰማርቷል የሚለውን ብንቀበል መሰረታዊው ጥያቄ ማንን ለይቶ ለማገልገል? የሚለው ነው። ልይ ኃይል ለኢትዮጵያ አደገኛ ክስተት ፈጥሯል።
ይህ የኦሮሞ ልዩ ኃይል ለሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች የህይወት ዋስትና ለመስጠት አልቻለም። በምእራብ ወለጋ አማራው እየተለየ በተከታታይ ሲጨፈጨፍ የሞቱት “አማራዎች ተለይተው አይደለም፤ ኦሮሞውም ይሞታል” ወዘተ የሚል ትርክት በተደጋጋሚ ይለፈፋል። እኔ ትግሬ፤ አኟክ፤ ጉራጌ፤ አማራ፤ ኦሮሞ፤ ሶማሌ ወዘተ በሚል መለያ መጨፋጨፍ የሞት ሞት ነው የሚል እምነት አለኝ። ኦሮሞው አልሞተም የሚል ጤናማ ሰው የለም። ትላንት አኟኮችን የጨፈጨፈው አካል ህወሓት ነበር። ዛሬ አማራውን የሚጨፈጭፈው ማነው? ብሎ መጠየቅ የስብአዊ ፍጥረት ግዴታ ነው። በፖለቲካ ልዩነት፤ በጦርነት ፍልሚያዎች መግደልና በማንነት ለይቶ መግደል የተለያዩ ክስተቶች ናቸው። አማራው ሲጨፈጨፍ እያዩ የተለመደ ነው ማለት ከወንጀሉ የለንበትም ለማለት ወይንስ አቅም የለንም ለማለት ነው? ወይንስ ይህ መከረኛ የአማራ ሕዝብ ልክ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ፤ በሻሸመኒ፤ በባሌና ሌሎች አካባቢዎች በተደጋጋሚ እንደ ተነገረው ትርክት ሁሉ “መጤና ነፍጠኛ” ስለሆነ መጨፍጨፉ አግባብ አለው ለማለት ነው?
“መጤ” የሚለው ብሂል “ስንኖር ኢትዮጵያዊ” ነን ከሚለው ጋር ይጋጫል።
የልዩ ልዩ ኃይሎች አመሰራረትና ጠንካራነት ለኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና ግዛታዊ አንድነት አደጋዎች ናቸው።
ሁኔታውን አሳፋሪና ሃላፊነት የጎደለው ያደረገውና በApril 6, 2021 በጀኔቫና በዋሽንግቶን ዲሲ የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች እንዳሳዩት፤ የፌደራሉ መንግሥት የአማራውን እልቂት ችላ ስላለው፤ አቅም ስለሌለው ፤ ሃላፊነት የጎደለው ሚና ስለሚጫዎት፤ ተባባሪ ወዘተ ስለሆነ ነው? መልሱን ለእናንተ ልተወው።
በምንም ሊካድ የማይቻለው ሃቅ አንድ ነው። በኦሮምያ ክልል የተሰማራው ግዙፍ ኃይል ከተሰማራበት ጊዜ ጀምሮ በተከታታይ ኦሮሞ ባልሆኑ ተራና ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚዘገንን እልቂት ተካሂዷል። ወደፊትም ቢሆን እልቂቱ ይቆማል የሚል እምነት የለኝም።
ለማጠቃለል፤ የኢህአዴግ መንግሥት ከተመሰረተበት ወዲህ፤ ኢትዮጵያ የብዙ አገሮችና የብዙ መንግሥታት አገር ሆናለች። የተለያዩ አገሮችና መንግሥታት አገር ከሆነች ደግሞ ይህ ሁኔታ የሚያስከትለው የዘውጎችን እየለያዩ ማጽዳትና መጨፍጨፍ ነው። ይህንን ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ለመፈጸም ደግሞ፤ ዜጎችን “መጤዎች፤ ነፍጠኞች፤ ቀለማችሁ ቀይ” ወዘተ እያሉ መለየትና ለጥቃት እንዲጋለጡ ማድረግ፤ ከቀያቸው ማስወጣት የተለመደ የሆነበት ምክንያት ራሱ ስርዓቱ የፈጠረው ስለ ሆነ ነው።
አንድ ሰው “መጤ” ከሆነ የሰብአዊ መብት የለውም። ማንም በፈለገው ቦታና አጋጣሚ፤ በመረጠው መሳሪያ ሊገድለው ይችላል። አማራው ብቻ ተጋልጧል፤ ሙቷል፤ ተሰቃይቷል፤ ተጨፍጭፏል ወዘተ የሚለውን ባልቀበልም ቅሉ፤ በማንነቱና በእምነቱ የህወሃታዊያን፤ የኦነጋዊያን፤ የጅሃዲስቶች፤ የሱዳኒሶች፤ የግብጾችና የምእራብ አገሮች ዋና ኢላማ የሆኑት ግን አማራውና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ናቸው። ይህንን ግፍና ጭካኔ የሚያጠናክሩት ደግሞ የአማራ አድር ባይ ልሂቃን፤ ምሁራንና አጋሮቻቸው ጭምር ሆነዋል።
የአማራው ምሁራን፤ ልሂቃን፤ ስብስቦችና ተቋማት በአካባቢ፤ በመንደር፤ በጎጥና በሌላ መለያየታቸው ለአማራው ተጠቂነት አስተዋፆ አድርጓል፤ እያደረገ ነው። የአማራው ሕዝብ ልክ እንደ አርመኖች፤ አይሁዶች፤ ፍልስጤማዊያንና ሌሎች ኢላማ የሆኑ ሕዝቦች ራሱን ከእልቂት ለመከላከል የሚችለው በመደራጀትና አቅሙን በመገንባት ነው። ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን አገር ወዳድ ወገኖቹ ጋር የጠነከረ ግንኙነት በመፍጠር ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ እርስ በእርስ የሚደረገውን ንትርክ ማቆም ግድ ያላል።
የአማራው ምሁራን፤ ልሂቃንና “አክቲቢስት” ተብየዎች መከፋፈል ለአማራው መጠቃት ግብዓት እያደረገ ነው። በተጨማሪ፤ የአማራውን ጭፍጨፋ በሚመለከት የፌደራሉን መንግሥት አትንኩ ባዮች ብቅ ብቅ ብለዋል። የሚዘገንን እልቂት እየተካሄደ “አትንኳቸው ባይነት” ከአድርባይነት ሊለይ አይችልም። “ኦሮሞ ደም ደማችን ነው” ካልን፤ “የአማራው ደም ደማችን ነው” ለማለት የማንችልበት ምክንያት ምንድን ነው?
አንዳዶቹ በሚዘገንን ደረጃ የኢትዮጵያን ችግሮች ያባባሱት የአማራ ዘውገኞች፤ ጽንፈኞች ናቸው የሚሉ መኖራቸው ያሳፍራል። አማራውን እና ለአማራው የሚሟገቱትን መልሶ ውንጀለኞች ናችሁ ብሎ መክሰስና መኮነን ከህወሓትና ከደጋፊዎቹ ትርክት በምን መስፈርት ይለያል? አይለይም። እነዚህን ከቤንዚን ላይ ክብሪት የሚነሰንሱ ግለሰቦችና ስብስቦች እባካችሁ ሁኔታውን አታባብሱት የሚሉ ምሁራን ወይንም ሽማግሌዎች አላየሁም፤ አልሰማሁም። ይህ የህሊና ቢስነት ሂደት ህላችንንም ወደ ታች ዝቅ ከማድረጉ በላይ፤ ኢትዮጵያን ወደ ባሰ ደረጃ ይመራታል የሚል ስጋት አለኝ።
ለወደፊቱ ምን ይደረግ?
- በዘውግና በክልል የተዋቀረው ሕገመንግሥትና ስርዓት መቀየር አለበት፤ ይህንን የሚሰራ ብሄራዊ/አገራዊ የባለሞያዎች ቡድን በአስቸኳይ እንዲመሰረት አሳስባለሁ።
- የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ የሆነ፤ ብሄራዊ የእርቅ፤ የሰላምና የብሄራዊ መግባባት ጉባኤ በአስቸኳይ እንዲካሄድ ይመኛልና ሁሉም ባለድርሻዎች ይህንን የተቀደሰ ጥሪ ተቀዳሚ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።
- ዘውግና እምነት ተኮር እልቂት በአስቸኳይ መቆም አለበት፤ አለያ፤ ኢትዮጵያን ይጎዳታል፤ ያዳክምታል።
- በአማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ የሚካሄደውን እልቂት በስሙ ለመጥራት እንድፈር፤ ጀኖሳይድ ወይንም ዘውግ ተኮር እልቂት ነው። ትላንት በአኟኩ ላይ፤ ዛሬ በአማራው ላይ የደረሰው እልቂት በሌላው ላይ ሊካሄድ እንደሚችል ማሰብ ለነገ የማይባል ነው።
- 5. የቤኒ-ሻንጉልና የኦሮምያ የበላይ ባለሥልጣናት ሃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለ ሆኖ፤ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትም ለእልቂቱ ተጠያቂ የሚሆንበት መረጃ አለ። ተከታታይ እልቂት እንዳይከሰት ቆራጥና የማያሻማ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስባለሁ። የፌደራሉ መንግሥት ለንጹሃን ዜጎች ተገን ለመሆን ካልቻለ ማን ሊሆን ይችላል? ፈረንጆቹ የሚፈልጉት እኛን መከፋፈል ነው።
- 6. የአማራው ዘውግ ለችግሩ ዋና መንስኤ ራሱ አማራው–“ጽንፈኞች፤ ነፍጠኞች፤ ትምክህተኞች አማራዎች ናቸው” የሚሉ የአማራና ሌሎች ምሁራን፤ ልሂቃንና አክቲቪስቶች ከነዳጁ ላይ ክብሪት መጫራቸውን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ አሳስባለሁ። ሌሎቻችሁም በድፍረት ድምጽ አሰሙ፤ ምከሩ። የተበደለንና የተገፋን ሕዝብ መልሶ መውቀስ ከህወሓታዊያን፤ ከጽንፈኛ ኦነጋዊያን፤ ከግብጽ ቅጥረኞች የሚለይበት አንድም መስፈርት ፈልጌ ለማግኘት አልቻልኩም።
- የግብጽ መንግሥት የውክልና ጦርነት በስፋትና በግልጽ እየተካሄደ መሆኑ ይታያል። የአማራው ጭፍጨፋ ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት የለውም ሊባል አይችልም። ለምሳሌ፤ ሱዳን በጎንደር በኩል የሚገኘውን ደንበር አልፋ ሰፊ መሬቶችን መንጠቋ፤ ነዋሪዎችን መግደሏ፤ ንብረታቸውን ማውደሟና መዝረፏ። በአሁኑ ወቅት ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያን ለመውረር የጦር ልምምድና ዝግጅት ማድረጋቸው እና የአየር ኃይል ጥቃት ልምምድ በአባይ ወንዝ አካባቢ ማካሄዳቸው ኢትዮጵያን እንደናቋት ያሳያል።
- ግብጾች በቅርቡ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ሰልፍ እንደሚያደርጉ አገምታለሁ። እኛ ኢትዮጵያዊያን የህዳሴ ግድብ ሙሌት ስኬታማ እንዲሆን በመላው ዓለም ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ እንድናደርግ ጥሪ አቀርባለሁ።
- ከፍተኛ አድናቆትና ተስፋ ያለኝ በአዲሱ፤ በኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ላይ የማያሻማ አቋም በያዘው በኢትዮጵያ ፌደራል መከላከያ ኃይል ላይ ነው። ይህ በኢትዮጵያዊነትና በሃገር ወዳድነት የተመሰረተው መከላከያ ኃይል ህወሃትን ለመደምሰስ ያሳየው ጀግንነት፤ ቆራጥነትና ዘመናዊነት ኢትዮጵያን ለመታደግ የሚችል መሆኑን በማስመስከር ላይ ይታያል። ለዚህ ተቋም ያለኝን አክብሮትና ድጋፍ እገልጻለሁ።
- እኔን እጅግ የሚያሳዝነኝና የሚያሰጋኝ፤ የአማራው መጨፍጨፍ ብቻ አይደለም። ዘውግ ተኮር እልቂት የሁላችንም ጉዳይ መሆን አለበት። አሁን በግልጽ ለሚታየው አስጊና አደገኛ የጅኦፖለቲካ ሁኔታ፤ እስካሁን ድረስ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ስኬታማ አለመሆኑን ጨምሮ፤ ግብአት የሆነው ተግዳሮታችን በአገር ውስጥ በዘውግና በኃይማኖት መከፋፈላችን ነው። ይህ ተግዳሮት ለኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና ዘላቂ ጥቅም ማነቆ መሆኑን ከተረዳን መፍትሄውን ለመፈለግ የምንችልበት እድል ይኖረናል።
ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
April 14, 2021