በአሜሪካ ወታደራዊ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከ1970ዎቹ ጀምሮ በወታደራዊው አለም ውስጥ ያሳለፉት ብ/ጄ/ል አሳምነው ፅጌ የመከላከያ ዩኒቨርስቲ ሀላፊም ለመሆን ችለው ነበር፡፡ ሆኖም ከ2001 አ.ም. ጀምሮ ከእነተፈራ ማሞ ጋር መፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርጋችኋል ተብለው ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ዘጠኝ አመታትን በእስር ቤት አሳልፈው በቅርቡ ለውጡን ተከትሎ ተለቀዋል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=pKU8igiCV3I&t=500s
ከእስር ከወጡ በኋላ የተገፈፈባቸው ማእረግ ተመልሶላቸው የአማራ ክልል ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ በመሆን ስራ የጀመሩት ብ/ጄል አሳምነው ዛሬ በአዲስ አበባ ለንባብ ከበቃው በረራ ጋዜጣ ጋር ቃለምልልስ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ቃለምልልስ በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ መሻሻሎች እየታዩበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሲናገሩም ‹‹ለአመታት የተሰራበት ስለሆነ፣ እንዲሁ በአጭር ቀናትና ሳምንታት አዲስና በጣም መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቅም አልነበረም፡፡ ቢሆንም አሁን አንፃራዊ መሻሻል እያየን እንገኛለን›› ብለዋል፡፡
በክልሉ ለተከሰቱት የፀጥታ ችግሮች ስምሪት የሚሰጠው ህወሃት ነው ስለሚባለው የተጠየቁት ጄኔራሉ ሲመልሱ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ህወሀት ነው ባንልም፣ ህወሀት ውስጥ ያሉ ሁኔታውን ለመቀልበስ የሚታገሉና ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ሀይሎች አሉ፡፡ ይሄ በጣም የአደባባይ ሚስጢር ነው›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹ግን ደግሞ በአደባባይ በአንድ የክልል ከተማ ፅ/ቤት ሲከፈት ህወሀት አለ ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የአካባቢው መንግስት ምን እያለ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል›› በማለት አስረድተዋል፡፡
የአማራ ክልል የፀጥታ ቢሮ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ጄኔራሉ ጦር መሳሪያ አንስተው ይታገሉ የነበሩና ወደአገራቸው የተመለሱ ታጣቂዎች የግል ትጥቃቸው ተከብሮላቸው በሰላም እየኖሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ይህንን ሲያብራሩም ‹‹መሳሪያቸው ተመዝግቦ፣ ተከብሮላቸው ወደ መደበኛ ህይወታቸው ተመልሰዋል›› ብለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት 498 ሽጉጦችን ደብቀው ስለተያዙት የክልሉ የፀጥታ ሀይል አባል ሲናገሩ ደግሞ ‹‹ማናችንም ቢሆን እንዲህ ያለ ነገር ይገጥማል ብለን አልጠበቅንም ነበር፡፡›› ካሉ በኋላ ግለሰቡን ‹‹ያለንበትን ሀገራዊና አካባቢያዊ ሁኔታ የዘነጋ፣ እኛ ደግሞ ለህዝቡ ያለንን ደጀንነትና ቅርበት ፍፁም የረሳ ብቻ ሳይሆን፣ የመክዳት ተግባር ነው የፈፀመው›› ሲሉ ገልፀውታል፡፡