
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ የፓርቲያችን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፓርቲያችን ሰብሳቢ የሆኑት ጓድ ዳንኤል ሽቱ በዛሬው ዕለት በክልሉ ፖሊስ ታስረው በወላይታ ሶዶ ከተማ ማዕከላዊ አስተዳደር ፖሊስ ጣቢያ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ ተረድተናል።
ኢሕአፓ ይህንን የፓርቲያችን አመራር እስር በከፍተኛ ስጋት የሚመለከት ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት በአስቸኳይ ስለ እስሩ ሕጋዊ መሠረት ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥና ጓድ ዳንኤል ሽቱን በአስቸኳይ እንዲፈታ ወይም በሕግ የተደነገገውን የፍርድ ሂደት እንዲያከብር ያሳስባል።
1. የፖለቲካ ልዩነት በእስር ሊፈታ አይችልም!
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግሥትን አፈጻጸም የመተቸት፣ የፖሊሲ አማራጮችን የማቅረብ፣ የሕዝብን ችግር የማሰማትና ለሰላማዊ የፖለቲካ ለውጥ የመታገል መብት አላቸው።
አንድ መንግሥት ትችትን እንደ ጠላትነት፣ የፖለቲካ ልዩነትን እንደ ወንጀልና ሰላማዊ ትግልን እንደ ስጋት መቁጠር ከጀመረ፣ የዴሞክራሲ መሠረቶች ተዳክመዋል ማለት ነው። ይህም ያለፉት አመታት ያሳዩን እውነት ሆኗል።
2. የሰላማዊ ትግል በሮች መዘጋት ለሀገር አደገኛ ነው!
ኢሕአፓ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል፣ በዴሞክራሲያዊ ለውጥና በሕዝብ ሉዓላዊነት የሚያምን ፓርቲ ነው። ሰላማዊ ትግል የሚሳካው ግን የፖለቲካ ነፃነት፣ የመደራጀት መብት፣ የመናገር ነፃነትና የሕግ ጥበቃ ሲኖሩ ብቻ ነው።
ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ሲታፈኑ፣ የፖለቲካ አመራሮች ያለ በቂ ሕጋዊ ምክንያት ሲታሰሩ፣ የሕዝብ ድምፅ ሲዘጋና የሰላማዊ ትግል መድረኮች ሲጠበቡ፣ በተደጋጋሚ እንዳስተዋልነው ሕዝብ አማራጭ የትግል መንገዶችን ለመጠቀም ይገደዳል።
3. አፈና የፖለቲካ ቀውስን ያባብሳል እንጂ አይፈታም!
የሀገራችን ዋና ችግር የፖለቲካ ልዩነት መኖሩ አይደለም፤ የፖለቲካ ልዩነቶችን በሕጋዊ፣ በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ መንገድ የሚፈታ የፖለቲካ ሥርዓት አለመጠናከሩ ነው።
ገዢው ፓርቲ በሕዝብ ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን በውይይትና በሕግ ከመመለስ ይልቅ በፖሊስ ኃይልና በእስር ለማስቆም በማለም ችግሩን ከሥሩ ከመፍታት ይልቅ የበለጠ እያወሳሰበው ይገኛል።
4. የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የፓርቲያችንን አመራር የእስር ምክንያትና ሕጋዊ ሁኔታ በግልጽ ለሕዝብ እንዲያሳውቅና የታሳሪውን ሰብዓዊ ክብር፣ ጠበቃ የማግኘት መብት፣ ከቤተሰብ ጋር የመገናኘት መብትና በሕግ የተጠበቁ መብቶች እንዲያከብር እናሳስባለን።
ኢሕአፓ የሕዝብን መብት ለማስጠበቅ፣ የፖለቲካ ነፃነትን ለማስፋትና በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ የጀመረውን ትግል ይቀጥላል።
ጓድ ዳንኤል ሽቱ በአስቸኳይ ይፈቱ!
የፖለቲካ አፈና ይቁም!
የዜጎች መብት ይከበር!
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ
ሕዳር 16 ቀን 2019 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ