በዜማ የታጀበ የታሪክ ጉዞ ፣ የየመን ነጃሒድ ሥርወ መንግሥት፣ የሙሐመሺን የታሪክና የሕልውና መሠረቶች

ሚያዚያ 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ፣ ኢትዮጵያ
አጠቃሎ
ይህ ጽሑፍ የአርቲስት ቴዲ አፍሮ “መሬማ” የሚለው ሥራወን በጥልቀት በማየት መሬማ ማን እንደሆነች በሚገባ ለመግለፅ ሞክሯል። መሬማ አንዲት ግለሰብ ሳትሆን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አኽዳም ተብለው በኋላም መጠሪያቸው ተሻሽሎ ሙሐመሺን ስለተባሉት ማኅበረሰቦች ያሉበትን አሁናዊ አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ለማሳየት የተወከለች ገፀ-ባሕሪይ ናት። ሙሐመሺኖች ታሪካዊ ዳራቸው ሲታይ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ፣ በ6ኛው ክ/ዘ በአፄ ካሌበ ዘመነ መንግሥት ቀይ ባሕርን ተሻግረው የመንን ሲያሰተዳድሩ የነበሩ፣ ኋላም ከተሸነፉ በኋላ እዛው የቀሩ ኢትዮጵያዉያን ናቸው። በተጨማሪም ሙሐመሾኖች ከ1022-1158 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) የመንን ሲያሰተዳድሩ የነበሩ ሐበሾች ነበሩ። ነጃሒዶች በበመየን በዚያዲድ ሥርወ መንግሥት (819–1018 እ.ኤ.አ.) ወታደራዊ ባሮች (ማሙሉክ) የነበሩ በኋላም ሥልጣን በመጨበጥ ዘቢድ ከተማን ማዕከል በማድረግ ለ150 ዓመታት ሲያስተዳድሩ የነበሩ ሐበሾች በተለይም ከአማራ ነገድ ጋር ቀጥታ ተወላጅ የሆኑ ነበሩ። ሙሸመሺኖች አሁን ላይ አስከፊ በሆነ የኑሮ ሁኔታ ዉስጥ የሚገኙ ሲሆን ፖሊቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ መገለል ውስጥ ይገኛሉ። የአርቲስት ቴዲ አፍሮ መሬማ የተሰኘው ሥራውም ይህን እውነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
- መግቢያ
ኪነ-ጥበብ በተለይም ሙዚቃ፣ ጊዜንና ቦታን አቋርጦ የሰውን ልጅ ስሜት የመግዛት ረቂቅ ኃይል አለው። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ደግሞ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ይህንን ኃይል ተጠቅሞ ትውልድን ካለፈው የታሪክ ሰንሰለት ጋር ማገናኘት የቻለ ርእሰ አርቲስት ነው። ከፈጠራ ሥራዎቹ መካከል ሚያዚያ 8/8/2018 ዓ.ም የተለቀቀው ባለ 18 ዘፈኖች አልበም ሲሆን፤ 15ኛ ላይ የሚገኘው “መሬማ” የተሰኘው ድንቅ ሥራው፣ ዝም ብሎ የሚደመጥ ዜማ ሳይሆን የጠፋን፣ ሰሚ ያጣውን ተገፍቶ የተጣለውን የተጨቆነውን ፣ የተናቀውን ማንነት እና የደበዘዘን የታሪክ ገጽ የሚፈልግ ጥልቅ ጥሪ ነው። “መሬማን ፍለጋ” ስንል ሥጋ የለበሰች አንዲት ሴትን መፈለግ ብቻ አይደለም። መሬማ በቀይ ባሕር ማዶ የቀረውንና ከእናት ምድሩ ጋር የተቆራረጠውን ትውልድ ለማስታወስ (የማንነት ናፍቆት)፣ በመገለልና በጭቆና ተጥንቆ በመከራ ውስጥ ያለን ውበት (የጥቁርነትን ውበት፣ ሐበሻዊነት) ለዓለም ለማሳየት፣ ሀዘን፣ ትካዜ፣ መከራን ለመጋራት እና ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት የነበራትን የባሕር ማዶ ተፅዕኖ እና ያንን ታላቅነት በሴት ልጅ ስም ወክሎ አጉልቶ ለማሳየት ነው።
መሬማ ባጭሩ በየመን ምድር ‘አኽዳም’ (ሎሌዎች) ተብለው ስማቸው የጠፋው፣ ‘አሕባሽ’ ተብለው የተገፉ፣ ሥነ ኑባሬያዊ ግለ’ት እና ነገረ ህላዌ ተፋልሶ የደረሰባቸው፣ አሁን ላይ ‘ሙሐመሺን’ (የተገለሉ) ተብለው የሚጠሩ፣ ነገር ግን ሥሩ ከአክሱም ነገሥታትና ከነጃሒዶች የሚመዘዘው የኢትዮጵያዊነት የሩቅ ትውስታ ናት። ዘፈኑ ከአድዋ ተራራዎች ከአክሱም ራስ ጫፍ እስከ ሞያሌ ዳር፣ ከሐረር አውራ ጎዳናዎች እና በመላው ዓለም ዙሪያ አድማጭን ልብ ሰቅዞ ይዞ እየከነፈ ይገኛል።
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የምንዳስሳቸው ዋና ዋና ነጥቦች የቴዲ አፍሮ “መሬማ” የሚለው ዘፈን ጭብጡ ምን እንደሆነ፣ሙሐመሺኖች እነማን እንደሆኑ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የታሪክ አውታረ ተጋምዶ፣ መሬማ የአንድ ግለሰብ ፍቅረኛ ወይስ የሕዝብ የጋራ ትዝታ?፣ ሙሐመሺኖች የመነ ውስጥ እንዴት መገለል እንደደርሰባቸው እና አሁን ላይ በምን ደረጃ እንዳሉ እንዳስሳለን። መሬማን ፍለጋ መውጣት ማለት፣ በራስ ስሜት ውስጥ ተጉዞ ትላንትን ዛሬ ላይ መልሶ የመትከል ያህል ረቂቅ ጉዞ ነው። ይህ ዜማ በውስጡ የያዛቸውን ምስጢራዊ መልእክቶች እና የታሪክ ፍንጮች አንድ በአንድ እንፈትሻለን።
- ታሪካዊ ዳራ፡ አክሱም በየመን ላይ የነበራት የበላይነት
ማዶ ደቡባዊ የቀይ ባሕር አካባቢ የታሪክ ገጽታ በአፍሪካ ቀንድ እና በዓረብ ባሕረ ገብ መሬት መካከል ያለውን የፖለቲካ ሥልጣን፣ የሃይማኖት አስተሳሰቦችን እና የብሔር ማንነቶችን ልውውጥ ለረጅም ጊዜ ሲያስተናግድ የነበረ የታሪክ፣ ፖሊቲካ፣ እና ማኅበራዊ የሥነ ኑባሬ ንጣፍ ነው። ለዚህ ድንበር ተሻጋሪ ሁለንተናዊ አሻራ ማዕከል የሆነው የአክሱም መንግሥት (በ6ኛው ክፍለ ዘመን) እና የየመን ነጃሒድ ሥርወ መንግሥት (ከ1022–1158 እ.ኤ.አ.) ሲሆን፣ ይህም በቲሃማ ቆላማ አካባቢዎች የተመሠረተ የሐበሻ ተወላጆች የሱኒ ኤሚሬት ነበር። ስድስተኛው ክፍለ ዘመን፣ የአክሱም መንግሥት በጂኦፖለቲካዊ፣ ወሰን ተሻጋሪ ዓለም አቅፍ የባሕር ላይ ንግድ የጦፈበት እና በባሕል ረገድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅት ነበር። ይህ ዘመን በአፄ ካሌብ ብርቱ አመራር የአፍሪካ ኢምፓየር ኃይል እስከ ዓረብ ልሳነ ምድር ድረስ የተዘረጋበት የታሪክ ምዕራፍ ሆኖ ይታወቃል። በዛሬዋ ሰሜናዊ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ደጋማ ቦታዎች ላይ ተመስርቶ የነበረው የአክሱም መንግሥት፣ ከሜዲትራኒያን ዓለም እስከ ሕንድ ውቅያኖስ የሚዘረጋውን የንግድ መስመር በመቆጣጠር፣ ከቢዛንታይን እና ከሳሳኒድ ፋርስ ግዛቶች ጋር እኩል ተደማጭነት ያለው ኃይል ሆኖ ወጥቶ ነበር።
እለ አጽብሐ ወይም ሄለስቴዮስ በሚሉ ስሞች በታሪክ ድርሳናት የሚታወቀው የአፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት፣ ከ514 እስከ 542 ዓ.ም የዘለቀ ሲሆን፤ ይህም በመንግሥቱ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የግዛት መስፋፋት የታየበት ወቅት ነበር። ሙንሮ ሃይ እንዲህ ሲል በመጽሀፉ ጠቅሶታል፡
Another hero in Aksumite legend was king Kaleb, also called Ella Atsbeha. He was regarded as a great conqueror and Christian hero whose expedition to suppress the persecution of his co-religionists in the Yemen by the Jewish king there caused his name to be famous throughout the Christian world.
በአክሱም አፈ ታሪክ ውስጥ ሌላኛው ጀግና ንጉሥ ካሌብ ሲሆን፣ እለ አጽብሐ ተብሎም ይጠራል። እርሱ ታላቅ ድል አድራጊ እና የክርስትና ጀግና ተደርጎ ይቆጠራል፤ በተለይም በየመን የነበረው አይሁዳዊ ንጉሥ በክርስቲያን ወገኖቹ ላይ ያደርስ የነበረውን ስደት ለማስቆም ያደረገው ዘመቻ፣ ስሙ በመላው የክርስትና ዓለም ዘንድ እንዲታወቅና ዝነኛ እንዲሆን አድርጎታል። ትርጉም የራሴ።
አፄ ካሌብ በየመን ጣልቃ እንዲገቡ ያደረጋቸውን ምክንያቶች ለመረዳት በወቅቱ የነበረውን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ መመርመር ያስፈልጋል። አክሱም የተገለለች አገር ሳትሆን በዓለም አቀፍ የንግድ እና የዲፕሎማሲ ሥርዓት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ነበረች። የፋርሱ የሃይማኖት መሪ ማኒ አክሱም በ3ኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩት አራት ታላላቅ መንግሥታት ማለትም ፋርስ፣ ሮም እና ቻይና ሲሆኑ ከነሱ ጋር ትቆጠር እንደነበር አስቀምጧል። ይህም ደረጃዋ በአዱሊስ ወደብ በኩል በነበራት ቁጥጥር የጸና ነበር። ይህ ወደብ እንደ ዝሆን ጥርስ፣ ወርቅ፣ ዕጣን እና መረግድ ያሉ የአፍሪካ ምርቶች ከሮም፣ ከሕንድ እና እስከ ሲሪላንካ ከሚመጡ የቅንጦት ዕቃዎች ጋር የሚለዋወጡበት ዋና ማዕከል ነበር።
አፄ ካሌብ በየመን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲያደርጉ የቀሰቀሳቸው ዋና ምክንያት በሕምያር መንግሥት ውስጥ የታየው ከፍተኛ የፖለቲካ ለውጥ ነው። በ5ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በሁለቱም የቀይ ባሕር ዳርቻዎች የአንድ አምላክ እምነት (Monotheism) እየተስፋፋ ነበር። አክሱም በ4ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ኢዛና ዘመን ክርስትናን ስትቀበል፣ በየመን የነበሩት የሕምያር መሪዎች ግን በንጉሥ ዩሱፍ አስአር ያታር (በታሪክ ዱ ኑዋስ) መሪነት የአይሁድን እምነት እንደ መንግሥት ሃይማኖት ተቀበሉ። ዱ ኑዋስ በየመን የነበረውን የአክሱም ተጽዕኖ ለማስወገድ ቆርጦ ተነሳ።
በ522 ዓ.ም አካባቢ፣ ዱ ኑዋስ በግዛታቸው ውስጥ ባሉ ክርስቲያኖች እና የአክሱም ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ ጥቃት ሰነዘረ። መጀመሪያ በሕምያር ዋና ከተማ በዛፋር የነበሩትን አክሱማውያን በማጥቃት ቤተ ክርስቲያናቸውን አቃጠሉ። ሆኖም እጅግ ዘግናኝ ድርጊት የተፈጸመው በ524 ዓ.ም በናግራን ከተማ ነበር። ናግራን የንግድ ማዕከል እና ከፍተኛ የክርስቲያን ማኅበረሰብ የነበረባት ከተማ ነበረች።
ናግራን ለስድስት ወራት በተከበበችበት ወቅት ነዋሪዎቿ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። ዱ ኑዋስ ከተማዋን በሰላም ከሰጡ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያደርስ ቃል ገብቶ ከገባ በኋላ ግን ሰቅጣጭ ጭፍጨፋ ፈጸሙ። እንደ “የሕምያራውያን መጽሐፍ” (Book of the Himyarites) ያሉ የታሪክ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በእሳት ጉድጓድ ውስጥ በሕይወት ተቃጥለዋል (ይህም በቁርኣን “የጉድጓዱ ሰዎች” ተብሎ ተጠቅሷል)። የሟቾች ቁጥር እስከ 70,000 ይደርሳል ቢባልም፣ ይበልጥ ትክክለኛ የሆኑ የሳባውያን የድንጋይ ላይ ጽሑፎች 12,000 ሰዎች መገደላቸውን እና 11,000 መማረካቸውን ይጠቅሳሉ።
ይህ ጭፍጨፋ በመላው የክርስቲያን ዓለም ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ። ከናግራን ያመለጡ ስደተኞች ቢዛንታይን ደርሰው እርዳታ ጠየቁ። የቢዛንታይኑ ንጉሥ ጀስቲን ቀዳማዊ በወቅቱ በቂ የባሕር ኃይል ስላልነበረው፣ ወደ እስክንድርያው ፓትርያርክ ጢሞቴዎስ አራተኛ ደብዳቤ በመላክ የአክሱም ንጉሥ ለዚህ ድርጊት አጸፋ እንዲመልስ ጥሪ አቀረበ። አፄ ካሌብም የክርስቲያን ወንድሞቻቸውን ደም ለመበቀል እና የአክሱምን የበላይነት ለመመለስ ዘመቻውን ጀመሩ።
ይህ ዘመቻ በ6ኛው ክፍለ ዘመን ከታዩት ታላላቅ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች አንዱ ነበር። አፄ ካሌብ ከአክሱም መደበኛ ሠራዊት እና ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጣ ከ70,000 እስከ 100,000 የሚደርስ ወታደር አሰባሰቡ። ዋናው ፈተና ይህን ግዙፍ ሠራዊት በባሕር ማሻገር ነበር። የቢዛንታይን ምንጮች እንደሚጠቁሙት፣ ሮማውያን ለአክሱም ሠራዊት መሻገሪያ የሚሆኑ 70 ያህል መርከቦች በአዱሊስ ወደብ እንዲገነቡ ወይም እንዲሰናዱ ረድተዋል።
ዘመቻው ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ቅዱስ ጦርነት ተደርጎ ነበር የተወሰደው። “ገድለ ካሌብ” እንደሚተርከው፣ ንጉሡ የአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመግባት ንጉሣዊ ልብሳቸውን አውልቀው ማቅ ለብሰው፣ እግዚአብሔር ድልን ከሰጣቸው መንግሥታቸውን ትተው መነኩሴ እንደሚሆኑ ተሳሉ። ድሉ የተገኘውም በተአምራዊ ሁኔታ እንደሆነ ይነገራል።
በእውነታው ግን የአክሱም ሠራዊት ገባዛ በተባለ ቦታ ላይ በማረፍ ከሕምያር ሠራዊት ጋር ገጠመ። ዱ ኑዋስ የባሕር ዳርቻውን በሰንሰለት በመቆለፍ ለመከላከል ቢሞክሩም፣ የአክሱም ወታደሮች መከላከያውን ጥሰው ገቡ። ጦርነቱ አጭር እና ወሳኝ ነበር። የሕምያር ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ተሸነፈ። ዱ ኑዋስ ሠራዊታቱ ሲደመሰስ እና ንግሥቱ ስትማረክ ሲያዩ፣ በጠላት እጅ ከመውደቅ ይልቅ በፈረሳቸው ወደ ቀይ ባሕር በመግባት ሕይወታቸውን አጠፉ።
አክሱም ገደራ (ዘግዱር ሊሆንም ይችላል) በተባለው ነጋሲ ዘመን ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ደቡብ ዓረብን የያዘ ሲሆን ጢሃማ፣ ናግራን፣ አል ማዕፋሪ፣ ዛፋርን እና ደጋማውን ሰሜን ሐማሪን ጨምሮ በሕምያሪቶች እና ሳባውያን ጥምረት ተገፍቶ እስኪወጣ ድረስ፣ በስሩ ሲገዛ እንደ ነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። ይህ መስፋፋት በሃይማኖታዊ አስተሳሰብ፣ በንግድ ፍላጎት እና በስትራቴጂካዊ አስፈላጊነት ተገፋፍቶ፣ በ525 ዓ.ም በደቡብ ዓረቢያ የነበረው የሕምያር መንግሥት በአክሱም ግዛት ሥር እንዲጠቃለል አድርጓል።
የአክሱም ኢኮኖሚያዊ ልማት እነዚህን የንግድ መስመሮች የመጠበቅ አቅሟ ላይ የተመሠረተ ነበር። የፋርሱ ሳሳኒድ ግዛት የሐር እና የቅመማ ቅመም ንግድን ለመቆጣጠር በመሞከሩ ከአክሱም ጋር ተቀናቃኝ ነበር። በዚህም ምክንያት የቢዛንታይን ግዛት፣ በተለይም በንጉሥ ጀስቲን ቀዳማዊ እና በኋላም በጀስቲኒያን ቀዳማዊ ዘመን፣ ፋርስን ለመከላከል ከአክሱም ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመስረት ፈልገው ነበር። ይህ ግንኙነት በወታደራዊ ትብብር እና በሃይማኖታዊ አንድነት ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲያዊ መሠረት ነበረው።
በየመን የነበረው የአክሱም ተጽዕኖ ያበቃው በሳሳኒድ ፋርስ ጣልቃ ገብነት ነው። በ570 ዓ.ም አካባቢ የአብርሃ ልጆች (ያክሱም እና መስሩቅ) በየመን በነበሩት ሕምያራውያን ዘንድ ተቀባይነት አጡ። ሰይፍ ኢብን ዲ ያዛን የተባለ የሒምያር መኮንን አክሱማውያንን ለማባረር እርዳታ ፈልጎ ወደ ፋርሱ ንጉሥ ሖስሮ ቀዳማዊ ሄደ።
የየመን መጥፋት አክሱም ከዓለም አቀፍ ኃያልነቷ የምትወርድበት መጀመሪያ ነበር። በ541-542 ዓ.ም የተከሰተው የጀስቲኒያን ወረርሽኝ (Plague of Justinian) የሕዝቡን ቁጥር በመቀነስ የመንግሥቱን አቅም አዳክሞታል። በተጨማሪም የአፈር መሸርሸር እና የተፈጥሮ መመናመን ፖለቲካዊ ማዕከሉን ወደ ደቡብ እንዲሸጋገር አድርገውታል።
ንጉሥ ሖስሮ 800 ገደማ የፋርስ ፈረሰኞችን በጀነራል ዋህሬዝ መሪነት ላከ። ምንም እንኳን የፋርስ ጦር በቁጥር ጥቂት ቢሆንም፣ “ፓንጂጋን” የተባለውን ዘመናዊ የፍላጻ መተኮሻ መሣሪያ በመጠቀማቸው የአክሱምን ሠራዊት ድል አደረጉ። በሰንዓ በተደረገው ጦርነት መስሩቅ ኢብን አብርሃ ተገደለ፣ አክሱማውያንም ከየመን ተባረሩ። በ578 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) የመን የፋርስ ግዛት አካል ሆነች፤ ይህም ለ60 ዓመታት ያህል የዘለቀውን የክርስቲያን አገዛዝ አበቃ።
በ7ኛው ክፍለ ዘመን የእስልምና መነሳት እና የቀይ ባሕር የንግድ መስመሮች በሙስሊም አረቦች መያዝ አክሱምን ከዓለም አቀፍ ንግድ አገለላት። ሆኖም የአፄ ካሌብ ዝና ግን ጸንቶ ኖሯል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፣ በምሥራቅ ኦርቶዶክስ እና በሮማ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ቅዱስ ተቆጥረው ይከበራሉ።
የአፄ ካሌብ ዘመን አንዲት አፍሪካዊት አገር በወቅቱ የነበሩትን ታላላቅ ኃይሎች በመጋፈጥ የክርስትና መከታ የሆነችበት ታሪካዊ ወቅት ነው። በየመን የሚገኙት የግዕዝ ጽሑፎች እና በአክሱም የሚገኙት የነገሥታቱ መቃብሮች የዚያን ታላቅ ዘመን እና የቀይ ባሕር የበላይነት ምስክሮች ሆነው ዛሬም ይገኛሉ።
የነጃሒዶች ሥርወ መንግሥት (Najahid Dynasty) በታሪክ ሚዛን ሲፈተሽ “ከባርነት ወደ ንግሥና” የተደረገ አስገራሚ ሽግግርንና በየመን ምድር ላይ የታየን የሐበሻዎች (የአቢሲኒያውያን) ፖለቲካዊ የበላይነትን የሚወክል ጽንሰ-ሐሳብ ነው። ይህ ሥርወ መንግሥት በዋናነት የሚታወቀው በቀድሞው የዚያድ መንግሥት ውስጥ በታታሪ ወታደራዊ መሪነታቸውና በንጉሥ ጠባቂነታቸው ይታወቁ የነበሩ የሐበሻ ተወላጆች፣ የነበረውን የሥልጣን ክፍተት ተጠቅመው በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ራሳቸውን የቻለ ሉዓላዊ መንግሥት መመሥረት በመቻላቸው ነው። ነጃሒዶች የዘቢድን ከተማ ማእከል በማድረግ የቀይ ባሕርን የንግድ መስመርና የባሕር ዳርቻዎችን ለ150 ዓመታት ያህል የተቆጣጠሩ ሲሆን፣ ይህም በወቅቱ በነበረው ዓለም አቀፋዊ ግብይትና ጂኦ-ፖለቲካ ውስጥ የሐበሻ ተወላጆች የነበራቸውን ወሳኝ ሚና ያሳያል። በአጠቃላይ የሥርወ መንግሥቱ ምንነት የጥቁር ሕዝቦች ወይም የሐበሻዎች ወታደራዊ ስትራቴጂ፣ የከተማ ሥልጣኔ ግንባታ እና በባዕድ አገር ላይ የጸና የፖለቲካ ተጽዕኖ ማሳረፍ የቻሉበትን ብርቅዬ የታሪክ ምዕራፍ የሚያመለክት ነው።
የነጃሒድ ሥርወ መንድሥት አስፈላጊነት ከቆየበት ጊዜ በላይ የሚዘልቅ ነው፤ “አማራ” የሚለውን ስያሜ እንደ ብሔር መገለጫ ከተጠቀሙ የታሪክ ማስረጃዎች ከመጀመሪያዎቹ የውጭ ምንጮች አንዱ ሲሆን፣ ለዛሬው የአል-ሙሐመሺን (ቀደም ሲል አል-አኽዳም ይባሉ የነበሩት) ማኅበረሰብ መገለል እንደ ታሪካዊ መሠረት ያገለግላል። ነጅም አደ-ዲን ዑማራህ አል-ሐከሚ “ታሪክ አል-የመን” (Tarikh al-Yaman) በሚባለው የታሪክ ድርሳኑ በየመን የነበሩ የሐበሻ ተወላጆች (ነጃሒዶች) አገዛዝ በዝርዝር መዝግቧል።ዑማራህ በመጽሐፉ ውስጥ የነጃሒዶችን ጥንካሬ፣ የዛቢድ (Zabid) ከተማን ውበት እና በወቅቱ የነበረውን የሐበሻውያን ሥልጣኔ ገልጿል። በተለይም፣ ነጃሒዶች ከኢትዮጵያ ነገሥታት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት፤ የነጃሒድ ሠራዊት የነበረውን የውጊያ ብቃት፤ በወቅቱ በየመን የነበረውን የንግድ ልውውጥ በሚገባ አስፍሯል።
የናጃሒድ ነገሥታት የዘመን ቅደም ተከተል (ዘቢድ የመን)፣
| ተ.ቁ |
የንጉሱ ስም |
የንግሥና ዘመን (እ.ኤ.አ በግምት) |
ማብራሪያ |
| 1 |
ነጃሕ |
ከ1022–1060 ዓ.ም. |
መስራች፤ በዛቢድ (Zabid) ስልጣን ላይ የወጣ አቢሲኒያዊ (ሐበሻ) ባሪያ ነበር። |
| 2 |
ሰዒድ አል-አሕዋል |
ከ1060–1063 ዓ.ም. |
የናጃህ ልጅ፤ አጭር እና ያልተረጋጋ የንግሥና ዘመን ነበረው። |
| 3 |
ጀያሽ ኢብን ናጃህ |
ከ1063–1086 ዓ.ም. |
ከሱለይሂዶች ጫና በኋላ የናጃሂዶችን ስልጣን መልሶ ያጠናከረ። |
| 4 |
አል-ፋቲክ ኢብን ጀያሽ |
ከ1086–1109 ዓ.ም. |
አንጻራዊ መረጋጋት እና መጠናከር የታየበት ወቅት። |
| 5 |
መንሱር ኢብን አል-ፋቲክ (Manṣūr ibn al-Fatik) |
በ12ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ |
የሽግግር ወቅት፤ የውስጥ መከፋፈል መታየት የጀመረበት ጊዜ። |
| 6 |
ቃይድ አቡ ሙሐመድ ሱሩር |
በ11ኛው ክ.ዘ አጋማሽ (አከራካሪ) |
አብሮ ገዥ ወይም ተቀናቃኝ ሳይሆን አይቀርም፤ ሁልጊዜ እንደ ብቸኛ ገዥ አይቆጠርም። |
| 7 |
አል-ፋቲክ ሳልሳዊ |
በ12ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ |
ከታላላቅ እና ውጤታማ ከነበሩት የመጨረሻ ነገሥታት አንዱ። |
| 8 |
መህዲ ኢብን አል-ፋቲክ |
እስከ 1158 ዓ.ም. |
የመጨረሻው ንጉሥ፤ በሞቱ ምክንያት ስርወ-መንግስቱ አብቅቷል። |
- የቲሃማ ጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ፡ የዚያዲድ ዘመን
የነጃሒድ ሥርወ መንግሥት መነሳት በዚያዲድ መንግሥት (819–1018 እ.ኤ.አ.) ውስጥ በነበረው የረጅም ጊዜ ወታደራዊ ባርነት (Mamlukism) ውጤት ነው። በዘቢድ ከተማ ይኖሩ የነበሩት ዚያዲዶች በየመን ውስጥ የሱኒ ሥልጣን ተወካዮች ነበሩ። በ10ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የዚያዲድ መንግሥት ሲዳከም፣ የመንግሥቱ አስተዳደር ከሐበሻ እና ከኑቢያ በመጡ ረሺድ እና ሁሰን ኢብን ሰላማ በተባሉ ወታደራዊ ባሪያዎች እጅ መውደቅ ጀመረ። ከእነዚህ ውስጥ ታዋቂው ሁሴን ኢብን ሰላማ የተባለ ኑቢያዊ ሲሆን፣ የመጨረሻዎቹ የዚያዲድ ነገሥታት ዋና ሚኒስትር (vizier) ሆኖ አገልግሏል። ሁሴን የዚያዲድ መንግሥት ከውድቀት እንዲድን በማድረግ እና በዘቢድ ውስጥ ታላላቅ መሠረተ ልማቶችን፣ መስጊዶችን እና የጉድጓድ ውኃዎችን በመገንባት ይታወቃል። ይህ የሐበሻ ተወላጆች በየመን ውስጥ የነበራቸው ሚና ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን የሥልጣኔ መሠረትም እንደነበረ ያሳያል።
ከሁሴን ኢብን ሰላማ ሞት በኋላ አስተዳደሩ መርጃን በተባለ የዚያዲድ ባሪያ-ተጠባባቂ እጅ የገባ ሲሆን፣ እሱም ሥልጣኑን በሁለት የሐበሻ አስተዳዳሪዎች፤ በነፊስ እና ነጃህ መካከል ከፈለ። ነፊስ የመጨረሻውን የዚያዲድ ሕፃን ንጉሥ በመግደል ሥልጣን ለመንጠቅ ቢሞክርም፣ ነጃህ ግን የአካባቢውን ዓረቦች እና የውጭ ወታደሮችን በማስተባበር በ1022 እ.ኤ.አ. ነፊስን አሸንፎ በዘቢድ የራሱን ሥርወ መንግሥት መሠረተ። ዑማራህ ነጃህ እንዴት ነፊስን እንደገደልው ሲገልፅ፤
Najah, on hearing of the treatment his master had undergone at the hands of Nafis, summoned his neighbours to his assistance, Arabs and non-Arabs. He marched upon Zabid, and repeated battles were fought between the two rivals-the battles of Rima’ and of Fashal, in both which Najah was worsted, that of al-‘Ukdah in which he was victorious, and that of al-‘Irk in which Nafis was killed near the Gate of Zabid, with the loss on the two sides of five thousand men.
ነጃሕ ጌታው በናፊስ እጅ የደረሰበትን ግፍ በሰማ ጊዜ፣ አረብና አረብ ያልሆኑ ጎረቤቶቹን ለረዳትነት ጠራ። ወደ ዘቢድም ዘመተ፤ በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከልም ተደጋጋሚ ውጊያዎች ተካሄዱ። የሪማዕ እና የፋሻል ጦርነቶች ናጃህ የተሸነፈባቸው ሲሆኑ፣ አል-ዑቅዳ በተባለ ቦታ በተደረገው ውጊያ ግን ድል ተቀዳጀ። በመጨረሻም በአል-ዒርቅ ጦርነት ናፊስ በዘቢድ በር አቅራቢያ ተገደለ፤ በሁለቱም ወገኖች በኩልም የአምስት ሺህ ሰዎች ሕይወት አለፈ። ትርጉም የራሴ
- የነጃሒድ መነሳት፡ ሕጋዊነት እና የጃዛሊ ማንነት
ነጃሕ ከወታደራዊ ባርነት ወደ ሉዓላዊ ንጉሥነት ለመሸጋገር በኢስላማዊው ዓለም ውስጥ ሕጋዊ እውቅና ያስፈልገው ነበር። በመሆኑም በባግዳድ ከሚገኘው የአባሲድ ኸሊፋ አል-ቃዲር አል-ሙአያድ ናስር አል-ዲን (የሃይማኖት ረዳት እና አሸናፊ) የሚል የክብር ማዕረግ አገኘ። ይህ እውቅና ነጃሒዶችን በደጋማው የመን ከነበሩት የሺዓ እንቅስቃሴዎች ጋር ለሚደረገው ትግል የሱኒ ምሽግ እንዲሆኑ አደረጋቸው።
የነጃሒዶች የብሔር ማንነት በመካከለኛው ዘመን የታሪክ ጸሐፊዎች ዘንድ ትኩረት ተሰጥቶታል። ዑማራህ አል-ሐከሚ ነጃሕ መነሻ “ጃዛሊ” (Jazali) ከሚባል ጎሳ እንደሆነ ይገልጻል። ምንም እንኳን ይህ ስም በዘመናዊ ጥናቶች ውስጥ ብዙም ባይታወቅም፣ የ14ኛው ክፍለ ዘመን ሶርያዊ ጂኦግራፊ አዋቂ አል-ዲማሽቂ በሐበሻ ምድር “ዲጃዝል” (Djazl) የተባሉ በቁንጅናቸው የሚታወቁ ጎሳዎች እንዳሉ ጠቅሷል። ከአል-ዲማሽቂ መጽሐፍ ወደ ፈረንሳይኛ በኦገስት ፈርዲናንድ መህረን የተተረጎመው መጽሐፍ ላይ እንዲህ እጠቅሳለሁ፥
Habesh était fils de Koush b. Khâm b. Noé. Les ABYSSINIENS sont divisés en races : les AMH’ARAT, desquels sont sortis les Ne-djâsis, qui occupèrent le trône; les S A H ‘ A R T , les D J A Z L , qui se di-stinguent par leurs belles formes, les Khoûmid et Dâmaût; toutes ces tribus comprennent un très grand nombre de familles et de branches. — A u x Nègres appartiennent encore les Ndbiens, descen- dant, d’après la tradition, de Nouba b. Qofth b. Mior b. Nîçir b. Iihàm b. Noé et divisés, selon la relation des marchands d’Aswân, en diverses tribus, telles que : Andj, Azkersa, Tibân, Andâ et Kenka. Les Andj et les Anda habitent une grande île, nommée Andâ, for- mée par le Nil; ils ne portent point de vêtements; les Azkersa sont éloignés du Nil, les Tibân demeurent dans un district, richeen minerai de f e r , mais où aucun animal ne peut vivre, â causede la chaleur excessive.
ሐበሽ የኩሽ ልጅ፣ እርሱም የካም ልጅ፣ እርሱም የኖህ ልጅ ነው። ሐበሾች (አቢሲኒያውያን) በስድስት ዘሮች ይከፈላሉ፤ እነርሱም፦ ዙፋኑን የያዙት ነጋሲዎች የወጡባቸው አማራዎች፣ ሳሐርቶች፣ በቁንጅናቸው የሚታወቁት ጃዝሎች፣ ኩሚድ እና ዳሞቶች ናቸው። እነዚህ ሁሉ ነገዶች እጅግ ብዙ ቤተሰቦችንና ቅርንጫፎችን ያቀፉ ናቸው። እንደ ትውፊቱ ከሆነ ከኩሽ (ጥቁር) ዘሮች መካከል ኑባውያን ይገኛሉ፤ እነርሱም የኑባ ልጅ፣ የቆፍት ልጅ፣ የምስር ልጅ፣ የኒሲር ልጅ፣ የካም ልጅ፣ የኖህ ልጅ ዘሮች ናቸው። በአስዋን ነጋዴዎች ዘገባ መሠረትም በተለያዩ ነገዶች ይከፈላሉ፤ እነርሱም፦ አንጅ፣ አዝከርሳ፣ ቲባን፣ አንዳ እና ኬንካ ናቸው። አንጅ እና አንዳ በናይል ወንዝ በሚፈጠር ‘አንዳ’ በተባለ ትልቅ ደሴት ላይ ይኖራሉ፤ ምንም ዓይነት ልብስም አይለብሱም። አዝከርሳዎች ከናይል ወንዝ ርቀው የሚኖሩ ሲሆኑ፣ ቲባኖች ደግሞ በብረት ማዕድን የበለጸገ ቢሆንም በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ምንም ዓይነት እንስሳ ሊኖር በማይችልበት አካባቢ ይኖራሉ።
ይህ የሚያሳየው ነጃሒዶች ዝም ብለው የመጡ ባሪያዎች ሳይሆኑ የተለየ የሐበሻ ወታደራዊ ማኅበረሰብ አባላት እንደነበሩ ነው።
- የአማራ እና የየመን ግንኙነት፡ ሱሩር አል-ፋቲኪ የነጃሒዱ ፈርጥ
የነጃሒድ ዘመን ታሪክ ለአማራ ሕዝብ ጥንታዊ ታሪክ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። በ12ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የታሪክ ጸሐፊው ዑማራ አል-የመኒ እጅግ ታዋቂው የነጃሒድ ሚኒስትር እና የጦር አዛዥ የነበረው ካይድ አቡ ሙሐመድ ሱሩር አል-ፋቲኪ (1156 እ.ኤ.አ. ያረፈ) “ከአማራ ነገድ” (tribe of Amhara) እንደሆነ ገልጿል። እንደሚከተለው እጠቅሳለሁ፤
He of whom I speak was the noble Ka’id Abu Muhammad Surūr Amharah al-Fatiki. He belonged to the Abyssinian tribe of Amharah, and all I can relate of him is but as a drop in the sea of his great merits.
“ስለ እርሱ የምናገረው ክቡር ካዒድ አቡ ሙሐመድ ሱሩር አምሐራ አል-ፋቲኪ ነው። እርሱ ከአቢሲኒያ (ከሐበሻ) የአምሐራ ነገድ ወገን ሲሆን፣ እኔ ስለ እርሱ ልናገር የምችለው ነገር ሁሉ ከታላቅ ክብሩና ከመልካም ስብዕናው፣ ከባሕር ውስጥ እንደ አንዲት ጠብታ ብቻ የሚቆጠር ነው።” ትርጉም የራሴ።
ይህ መረጃ በሁለት ምክንያቶች እጅግ አስፈላጊ ነው፤ መጀመሪያ፣ ይህ መረጃ “አማራ” የሚለውን ስያሜ እንደ ብሔር የገለጸ ቀደምት የውጭ ምንጭ ነው። በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ ምንጮች (ለምሳሌ የቅዱስ ተክለሃይማኖት ገድል) “አማራ” የሚለውን ስም በብዛት ለቦታ ስም (ቤተ አማራ) ይጠቀሙበት ነበር። ነገር ግን ታደሰ ታምራት ስለ አማራ ነገድ “ከእነዚህ ማህበረሰቦች መካከል የአማራ ጎሳ በሰሜን በኩል የሚገኘው ሲሆን፣ ምናልባትም ቀድሞ የተመሠረተ ሳይሆን አይቀርም። ስለ አማራ (ማህበረሰብ) የሚገኙ ትውፊታዊ መረጃዎች አነስተኛ በመሆናቸው፣ ስለ አመጣጣቸው እዚህ ጋር የተወሰነ የዘመን ቀመር (ቀን) መስጠት የማይቻል ነው።” አንድ የመኒ የታሪክ ጸሐፊ ሱሩርን በዚህ ስም መጥቀሱ አማራዎች በሐበሻ ወታደራዊ ዳያስፖራ ውስጥ የሚታወቅ ማንነት እንደነበራቸው ያሳያል።
ሁለተኛ፣ የሱሩር አል-ፋቲኪ ከፍተኛ ሥልጣን በነጃሂድ መንግሥት ውስጥ የአማራ ተወላጆች የነበራቸውን ማኅበራዊ ዕድገት ያሳያል። ዑማራ ስለ ሱሩር መልካም ባሕሪያት ሲገልጽ “ከባሕር ጠብታ ያህል ብቻ ነው መናገር የምችለው” በማለት ታላቅነቱን መስክሯል። ይህ ግንኙነት አማራዎች በ1270 እ.ኤ.አ. የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ከመመሥረቱ በፊትም በቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንደነበሩ ያረጋግጣል። ከዚህ በተጨማሪ ዑማራህ ስለነሱ እንዲህ ሲል ይቋጫል᎓ “ከእነርሱ የተሻለ የግል ብቃት (ተሰጥኦ) ያለው የዓረብ ንጉሥ የለም፤ ቢበልጧቸውም በዘር ሐረግ ክብር ብቻ ነው። በልግስናቸው፣ በድንቅ የሕንጻ ጥበባቸው፣ እንዲሁም በጦርነት ወቅት በሚያተርፉት ዝናና በሰላም ጊዜ በሚያስመዘግቧቸው ደማቅ ስኬቶች የታወቁ ነበሩ።”
- የሕልውና ግጭት፦ ነጃሂዶች እና ሱለይሂዶችግጭት
የነጃሂድ ሥርወ መንግሥት ታሪክ ከሱለይሂድ ሥርወ መንግሥት (1047–1138 እ.ኤ.አ.) ጋር በነበረው የከረረ ግጭት የተሞላ ነው። ሱለይሂዶች ለግብጹ ፋቲሚድ ኸሊፋ ታማኝ የነበሩ የሺዓ እስማኢሊ ኃይሎች ነበሩ። የሱለይሂድ መሥራች ዓሊ አል-ሱለይሂ የሐበሻ ተወላጅ የሆኑትን የቲሃማ ገዥዎች እንደ ባዕድ ወራሪዎች ይመለከታቸው ነበር።
በ1060 እ.ኤ.አ. ዓሊ አል-ሱለይሂ ነጃሕን በመርዝ እንዳስገደለው ዑማራህ እንዲህ ሲል ጽፎታል፥
He lived in dread of Najah, the Prince of Tihamah, but sought to win his favour, assuming a humble demeanour, but never desisting in his efforts against him, until he succeeded in bringing about the death of Najah by poison, with the help of a beautiful female slave whom he sent as a present to his rival. Najah died at al-Kadra in the year 452.
…. እርሱ የቲሃማው መስፍን ነጃሕን እጅግ ይፈራው ነበር፤ ነገር ግን ትሑት በመምሰል የነጃሕን ሞገስ ለማግኘት ይጥራል፤ ሆኖም በነጃሕ ላይ የሚያደርገውን ተንኮል ከቶ አላቋረጠም ነበር። በመጨረሻም ለባላጋራው በስጦታ መልክ በላካት ቆንጆ ሴት ባሪያ አማካኝነት ነጃሕን በመርዝ በመግደል ተሳካለት። ነጃሕ በ452 (ዓመተ ሒጂራ) አል-ካድራ በተባለች ቦታ ሞተ። ትርጉም የራሴ
የነጃሕ ልጆች ሰኢድ አል-አህዋል እና ጀያሽ ወደ ዳህላክ ደሴቶች ለመሸሽ ተገደዱ ። ሆኖም በ1067 እ.ኤ.አ. ሰኢድ አል-አህዋል ዓሊ አል-ሱለይሂ ወደ መካ በመጓዝ ላይ እያለ ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር ገደለውና ንግሥቲቱን አስማ ቢንት ሺሃብን ማረከ። ንግሥት አስማ ለአንድ ዓመት በነጃሂዶች ምርኮ የቆየች ሲሆን፣ በመጨረሻም በዳቦ ውስጥ ደብቃ በላከችው ደብዳቤ ልጇ አል-ሙካራም መጥቶ እንዲያድናት ባደረገችው ጥረት ተለቃለች።
- የነጃሂዶች ውድቀት፡ ከሉዓላዊነት ወደ አኽዳምነት
በዚህ ንዑስ ረዕሰ ጉዳይ ላይ የምናነሳው ዐይነተኛ ነገር አኽዳሞች ወይም ሙሐመሺን የሚባሉት እነማን እንደሆኑና ለምን እንደተባሉ የምናይ ይሆናል። የነጃሂድ ሥርወ መንግሥት ውድቀት በ1158 እ.ኤ.አ. በዓሊ ኢብን መህዲ አል-ሒምያሪ በሚመራው የመህዲድ እንቅስቃሴ ተከሰተ። ዓሊ ኢብን መህዲ የሃይማኖት አክራሪነትን ከዘር ጥላቻ ጋር በመቀላቀል የአረብ ጎሳዎችን በሐበሻ ገዥዎች ላይ አነሳሳ።
ዘቢድን ከተቆጣጠረ በኋላ የመጨረሻውን የነጃሂድ ንጉሥ አል-ፋቲቅ ሣልሳዊን ገደለ። ነገር ግን ድሉ የሥልጣን ለውጥ ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም በሐበሻ ተወላጆች ላይ የሚፈጸም የማኅበራዊ መዋቅር ለውጥ ነበር። ዓሊ ኢብን መህዲ የቀሩትን የነጃሂድ ወታደሮች እና ዘሮቻቸውን የየመን ማኅበረሰብ አገልጋይ እንዲሆኑ እና በከተማ ዳርቻዎች ብቻ እንዲኖሩ የሚደነግግ አዋጅ አወጣ። ሙሐመድ አል መሕፈሊ እና ኢማን ሆማይዲ ካሳተሙት ጽሑፍ እጠቅሳለሁ፤
When the Najah dynasty took power in Zabid and the Tihama plains they brought in more people from Ethiopia. They persecuted the Yemenis, looted their property, took women as captives, and enslaved the indigenous Yemeni population. This led the people to form resistance groups against the Najahi state, led by the rebel Ali Bin Mahdi Al-Hymiari Al-Zabidi, who rallied Yemenis from the Tihama plains and the mountainous areas. After a four-year war, Ali was able to overthrow the Najah dynasty, and sentenced them to a life of slavery in which they would become servants of Yemeni society. He also issued a decree that forced them to build their homes on the outskirts of cities and villages, and was the first to call them Akhdam in recorded Yemeni history.
የነጃሕ ሥርወ-መንግሥት በዘቢድ እና በቲሃማ ሜዳዎች ሥልጣን በያዙ ጊዜ ከኢትዮጵያ ተጨማሪ ሰዎችን አመጡ። የመመኑን ሕዝብም አሳደዱ፣ ንብረታቸውን ዘረፉ፣ ሴቶችን ማረኩ፣ እንዲሁም ነባሩን የየመን ሕዝብ በባርነት ገዙ። ይህም ሕዝቡ በነጃሂ መንግሥት ላይ የተቃውሞ ቡድኖችን እንዲያቋቁም አደረገው፤ አመፁን የመራው ደግሞ ከቲሃማ ሜዳዎች እና ከተራራማ አካባቢዎች የመናዉያንን ያስተባበረው ዓሊ ቢን ማህዲ አል-ሐይሚያሪ አል-ዛቢዲ ነበር።
ከአራት ዓመት ጦርነት በኋላ ዓሊ የነጃህን ሥርወ-መንግስሠሥት መገርሰስ የቻለ ሲሆን፣ በየመኑ ማኅበረሰብ ውስጥ አገልጋይ ሆነው እንዲኖሩ የዕድሜ ልክ የባርነት ፍርድ ፈረደባቸው። በተጨማሪም ቤቶቻቸውን ከከተሞች እና ከመንደሮች ዳርቻ ላይ እንዲገነቡ የሚያስገድድ አዋጅ አወጣ፤ በየመን ታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ “አኽዳም” (Akhdam) ብሎ የጠራቸው እርሱ ነበር። ትርጉም የራሴ
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ “አኽዳም” (አገልጋዮች) የሚለውን ስም የሰጣቸው እሱ ሲሆን፣ ይህ ወቅት የሐበሻ ተወላጆች ከገዥነት ወደ ተገለለ እና ዝቅተኛ ማኅበራዊ ደረጃ (subalternity) የተሸጋገሩበት የታሪክ ጠባሳ ሆኖ ይቆጠራል።
ሙሐመሺን (የተገለሉቱ) የሚለው መጠሪያ በማኅበረሰቡ አባላት የጸደቀው “አኽዳም” (አገልጋዮች) ከሚለውና በተደጋጋሚ ከሚጠሩበት አዋራጅ ስም ለማምለጥ ነው። ስለ ቡድኑ ብሔረሰባዊ አመጣጥ የተለያዩ አከራካሪ ሐሳቦች አሉ። አንዳንዶች እንደሚያምኑት ቡድኑ ከአፍሪካውያን ባሪያዎች ወይም እስከ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኋላ በሚሄድ ታሪክ ከነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች የተወለዱ ናቸው። በየመን ለዘመናት ቢኖሩም ባዕድነታቸው ዛሬም ድረስ በጉልህ ይንጸባረቃል።
- የሙሐመሺኖች መነሻ፡ የሕልውና ዕይታእና አሁናዊ ሁኔታዎች
በየመን ማኅበረሰብ ውስጥ የሙሐመሺን መገለል በ”አስል” (asl – ክቡር የዘር መነሻ) ጽንሰ-ሐሳብ የሚመራ ነው። የየመን ማኅበራዊ ደረጃ የሚመራው በዘር ሐረግ ላይ በተመሠረተ አስተሳሰብ ሲሆን፣ ሙሐመሺን ይህ የጎሳ “አስል” የላቸውም ተብሎ ስለሚታመን “ኑቃስ” (ጎደሎ ወይም ዝቅተኛ) ተደርገው ይታያሉ። የአኽዳሞችን መነሻ በተመለከተ ኔቮላ የሚባል ጸሐፊ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡
This social group (ṭabaqa ijtimaʿiyya) appeared in Yemen before Islam, in a peculiar period when the Ethiopians (Aḥbash) raided Yemen under the lead ership of Abraha al-Ashram. And that wasn’t, simply, a military campaign: it was also a religious one for [supporting] the Christian religion.
እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች (ṭabaqa ijtimaʿiyya) የመን ውስጥ የተገኙት ከእስልምና በፊት ኢትዮጵያውያን አብርሐ አል አሽራም በተባለው የንጉሡ እንደራሴ መሪነት ስር ነበር። ዘመቻውም ወታደራዊ ብቻ አልነበረም፡ ክርስቲያኖችን ለመርዳት የተደረገ ሃይማኖታዊ ዘመቻ ነበር። ትርጉም ያራሴ
ኔቮላ በመቀጠል ሦስት የየመን ደራስያንን በመጥቀስ ስለ አኽዳሞች ታሪካዊ መነሻ ያስቀመጡትን መላምት ተንትኗል። የመጀመሪያው በኔቮላ ጽሑፍ የተጠቀሰው ሻርጃብ የተባለው ጸሐፊ መነሻቸው ከአፍሪካ ነው በማለት የራሱን መላምት ያስቀመጠ ሲሆን መላምቶቹም (1) ከቅድመ ሽስልምና በፊት ሲጨቆኑ የነበሩ ነባር የየመን ዘሮች ናቸው፣ (2) መነሻቸው ባርያ የሆነ ሕዝብ ናቸው፣ (3) በቅድመ እስልምና ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ እና በኋላ ሐበሾች 522 እ.ኤ.አ ወደ የመን ሲዘምቱ አብረው የተመለሱ ናቸው፣ (4) ኢትዮጵያውያን የመንን በወረሩ ጊዜ የመን ውስጥ የነበሩና በዝቅተኛ የወትድርና እርከን ወስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ በኋላም ተመሳሳይ ተግባር የመን ውስጥ እያደረጉ ያሉ ናቸው የሚል ነው። ሽጃብ የተባለው ጸሐፊ ደግሞ የሻርጃንን መላምት በመንሻቸውና በሥራቸው መካከል ያለውን ግንኙነት በመርመር ሁለት መላምቶችን በሰንዘር አጠናክሮታል። እነሱም፣ (1) በሰይፍ ቢን ዲ ያዛን የተማረኩ የአብርሐ ወታደሮች ሲሆኑ ቆሻሻ ሥራዎችን እንዲያከናዉኑ የተደረጉ ናቸው፣ (2) ስይፍን የከዱ እና የገደሉ ሐበሾች ሲሆኑ፣ ነገር ግን ምሕረት ተደርጎላቸው በሕይወታቸው የየመንን ሕዝብ እንዲያገልግሉ የተደረጉ ናቸው የሚል ነው።
ሙሐመሺኖች አኽዳም ተብሎ ከመጠራትም ባሻገር በሌሎች ስሞችም ይጠራሉ። አል አሻድ ፋክረን (እጅግ የደኸዩ ጎስቋሎች)፣ አል አክተር ዱዓፈን (ኮስማኖች ወይም ተጠጋላጮች)፣ አል አቃሉ ሕዛን (እድለ ቢሶች/ገደ ቢሶች)፣ እና ከዚህ ለየት ባለ መልኩ ደግሞ አህፋድ ቢላል (የቢላል የልጅ ልጆች) ተብለውም ይጠራሉ።
ሙሐመሺኖች በየመን ውስጥ ዝቅተኛ የማኅበእርሰብ ቦታ ላይ የሚኖሩ ፣ ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እጅግ አሳኝ እና አስከፊ በሆነ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው። ሊቃዊም ሆነ ሕጋዊ ትኩረትም አልተሰታቸውም ወይም ደግሞ የተሰጣቸው ትኩረት እጅዱን አናሳ የሆነ ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሙሐመሺኖች ከ30,500,000 የሚሆነውን የየመን ሕዝብ ብዛት ከ1.4 እስከ 2.6 % (በመቶ) ይሸፍናሉ።
ሌሎች ጥናቶች እንደሚያሳዩት ደግሞ ዛሬ በየመን ከ500,000 እስከ 3.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሙሐመሺን ይኖራሉ። ባርነት በሕግ ቢታገድም፣ ማኅበረሰቡ አሁንም በማኅበራዊ ደረጃ ዝቅተኛው ቦታ ላይ ይገኛል። በየመን ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት ሁኔታውን ይበልጥ አባብሶታል፤ የጎሳ ጥበቃ ስለሌላቸው ዕርዳታ የማግኘት ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው። ሙሐመሺኖች ከነሱ ዘር ውጪ ማንንም እንዲያገቡ አይፈቀድላቸውም፣ መሣሪይ መያዝ የተከለከሉ ናቸው፣ ኅክምና ቦታ ተገቢውን እንክብካቤ አይሰጣቸውም፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዘርፍ መንገድና ቆሻሻ በመጥረግ፣ መኪና በማጠብ፣ ሸክም በመሸከም፣ እና መሰል ዝቅተኛ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን ብቻ በመሥራት ይኖራሉ። ሙሐመሺኖች ለሠሩት የጉልበት ሥራ ተገቢውን ደሞዝ አይከፈላቸውም።
- የቴዲ አፍሮ መሬማ ግጥም እና የሙሐመሺኖች ነባራዊ ሁኔታ
እዚህ ላይ ነው የአርቲስት ቴዲ አፍሮ መሬማ የሚለው ሥራውን የሚናየው። ቴዲ በዘፈኑ እንዲህ ይለናል፣
ማዶ ባብል የመን በሰንዐ ከተማ፣
ውበትሽን እያየሁ ስወጣም ስገባ
እንደ አፋር አፍሌታ የጠየመው ፊቴ
ሌላው ቢቀር እንኳን እዪው ማንነቴን፣
ዞረሽ። ይላል
ሲወጣ ሲገባ የሚያያት መንገድ የምትጠርግ ጥቁር የመናዊት ናት መሬማ። አንገቷን ደፍታ መንገድ የምትጠርገው መሬማ ቀና ብላ እነኳ ሰው አታይም። እንደ አፋር አፍሌታ የጠየመው ፊቱን (ትቁር ሐበሻዊነቱ) ላፍታ እንኳ ዞራ እንድታየው ቢሻም በጭቆናና መገለል ሳቢያ የተደፋው አንገቷ ቀና ብሎ የመሄዱን ድፍረት ያገኘ አይመስልም።
ላ! ላ! አትበይኝ በቃ አይሆንም
ጠጋ ብለሽ አውጊኝ እስኪ ያለሽበት ሁኔታውን ፣
እያየሽው በትካዜ የምጠርጊው ጎዳናውን
አጎምብሰሽ ስተክዢ ተደግፈሽ መጥረጊያውን
አሳዘንሽኝ እኔንማ ስንታለ ሆድሽ መሬማ።
መሬማ በትካዜ አጎምበሳ መንገዱን ትጠርጋለች፣ መጥረጊያዉን ተደግፋ በትካዜ ያለችዉን መሬማን ጠጋ ብላ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታን አነድታዋየው የሻተ ይመስላል።
“ወዲህ አላቃት
አቃተኝ ደግሞ ላልፋት
ስሟን ጠይቄ በጠራት አትዞር ብከተላት
ባያት አምሳያዬን ብጠራት አትሰማ
መሬማ ….. ያ መሬማ”
ስሟን አያውቀውም ፥ ነገር ግን ሰዎችን ጠይቆ መሬማ ናት አሉት፣ እሱም በስሟ ጠራት አቤት አላለችውም፣ ዞራ ታየው ዘንድ ልቧ አለፈቀደም።
ቴዲ ሙሐመሺኖች ያሉበትን የኑሮ አስከፊነት እና መሪርነት አጉልቶ “አጎምብሰሽ ስተክዢ ተደግፈሽ መጥረጊያውን” ሲል አዚሞታል። ቴዲ በመቀጠል “መሬማ ኑሮሽ እንዴት ነው በሰነዓ ከተማ” በማለት የነገሩን አሳሳቢነትና አንገብጋቢነት ይበልጥ ትኩረት እንድሰጠው አድርጎናል። በሐሩሩ መንደር በሐጋይ በረሃ፣ ማዶ ባብል የመን በሰነዓ ከተማ፣ ባያት አምሳያየን ብጠራት አትሰማ፣ መሬማ ሲል ነገሩ ዝርያዋ ወይም አምሳሏ ከሱ (ሐበሻ) ጋር አንድ መሆኑን ይነግረናል።
ከ2007 ጀምሮ የሙሐመሺን ብሔራዊ ማኅበር መብቶቻቸውን ለማስከበር እየታገለ ይገኛል። በየመን የሚገኙት ሙሀመሺኖች ለዘመናት የቆየባቸውን ስር የሰደደ ማኅበራዊ መገለል እና የዘር መድልዎ ለመታገል የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በንቃት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ ኑዕማን አል-ሁዘይፊ የሚመሩት የተገለሉ ማኅበረሰቦች ብሔራዊ ኅብረት (National Union for the Marginalized) ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሲሆን፣ ድርጅቱ ሙሐመሺኖች በየመን የፖለቲካና ማኅበራዊ መድረኮች እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸውና የዜግነት መብታቸው እንዲከበር በጽኑ ይሟገታል። በተጨማሪም እንደ ምዋታና (Mwatana) ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በማኅበረሰቡ ላይ የሚፈጸሙ በደሎችንና በጦርነቱ ወቅት የደረሰባቸውን መፈናቀል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማጋለጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። እነዚህ አካላት በዋናነት የሚያተኩሩት እንደ “አል-አክዳም” ያሉ አዋራጅ ስሞችን በማስቀረት፣ የትምህርትና የጤና እድሎችን በማመቻቸት እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ በመለወጥ ላይ ሲሆን፣ በተለይም በቅርብ ዓመታት በዲጂታል ሚዲያ በመታገዝ የሙሀመሺኖችን ድምጽ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ ለማድረግ ችለዋል።
- ማጠቃለያ
የአርቲስት ቴዲ አፍሮ መሬማ የሚለው ዘፈኑ ጥልቅ ምሥጢርን ያዘለ ሥራ ነው። በታሪክ ውስጥ በታወቀ ዘመን ከፍታ ላይ የነበሩ ማኅበረሶበች አሁን ላይ ታሕታይ ወይም ታሕተ ታሕታይ ተብሎ ሊገለፅ በሚችል አኳዃን በአስከፊ ነባሪዊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሙሐመሺኖችን ሁኔታ የጋረደውን የታሪክ ጥቀርሻ ገላልጦ አሳየን። በአፄ ካሌብ ዘመነ መንግሠት ኢትዮጵያ የበላይነቷን በየመን ላይ ካሰፈነች እና አብርሃ አል አሸራም የሚባለውን እንደራሴ ሹማ ስታተደዳር ከቆየች በኋላ በሕምያሩ መኮንን ዓሊ ቢን ማህዲ አል-ሐይሚያሪ አል-ዛቢዲ ተሸንፈው አሁን ላሉበት የማኅበራዊ ኑሮ ሁኔታ ተዳርገዋል። በተጨማሪም፣ የነጃሒድ ሥርወ መንግሥት የታሪክ ጉዞ በየመን ታሪክ ውስጥ በአንድ የታሪክ አውድ ወታደራዊ ባሪያ የነበሩ፣ ሎዓላዊነታቸውን ያስከበሩ እና በአካባቢያዊ የጎሳ መዋቅር መካከል የነበረውን ግጭት ያሳያል። ነጃሒዶች የሐበሻ ተወላጆች ሆነው ሳለ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የሥልጣኔ ማዕከል መገንባት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል። ከአማራ ሕዝብ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እና በዘቢድ የነበረው የባሕል ልውውጥ የቀይ ባሕር አካባቢ የታሪክ ድምቀት ነው። ሆኖም የ1158 እ.ኤ.አ. ውድቀት ወታደራዊ ሽንፈት እንዴት ወደ ዘላቂ ማኅበራዊ መገለል እንደሚቀየር የሚያሳይ ትምህርት ነው። አክሱም 6ኛው ክፍለ ዘመን በየመን ላይ የነበራትን የበላይነትና የነጃሒድን ታሪክ መረዳት የታሪክ ምርምር ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም ድረስ መብታቸውን ለማስከበር ለሚታገሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመናውያን የክብር ማገገሚያ መሠረት ነው።