the wider image: grim aftermath of ethiopian battle offers rare clues of brutal war
በመፍትሔዉ ፍለጋ ሁሉም ዜጋ ያስብበት (በዶ/ር በቀለ ገሠሠ)
1ኛ/ መንደርደሪያ፤
ከነዚያ ክልሎች አካባቢ የሚሰሙት ዜናዎች እጅግ በጣም የሚያሰቅቁና የሚያሳሳስቡ ናቸዉ። ግድያዉ፤ መፈናቀሉና ሰቆቃዉ እየበረከተና እየተባባሰ መሄዱን ማመን ያስቸግራል። ለምን? ለምን? ለምን? እነዚህ ጥያቄዎች ቶሎ እልባት ካላገኙ የበለጡ እጅግ አሳሳቢ ጉዳቶች ሊደርሱ ስለሚችሉ ችግሮቹ በሚከተሉት መንገዶች በአጣዳፊ መንገድ እንዲፈቱ ላሳስብ እወዳለሁ።
2ኛ/ የፌደራልና የህወሃት ጉዳይ
ህወሃትና ካድሬዎቹ ለ27 ዓመታት ብዙ ጉዳቶች እንዳደረሱ ይታወቃል። ፖሊቲካዉን እንደፈለጉት አሽከረከሩት። የዉሸት ትርክቶችን ነዙ። እስከዛሬ ድረስ በሥራ ላይ ያለዉን መርዘኛና ከፋፋይ ሕገ መንግሥት ዘረጉ። በከፋፍለዉ መግዛት ፖሊሲያቸዉ ህዝብን ከህዝብ አጋጩ። የብድር ገንዘብና የሀገር ንብረት መዝብረዉ በዉጪ ባንኮቻቸዉ አስቀመጡ።
ከ27 ዓመታት በኋላ ግን በተቀጣጠለዉ የህዝብ ትግል ከማዕከላዊ መንግሥት ተገፍተዉ ወደመቀሌ አፈገፈጉ። በመጨረሻም ሁለት ተጨማሪ ከባድ ወንጀሎች ፈጸሙ፤ 1ኛ/ በሰሜን ክንፍ የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር ላይ ጉዳት አደረሱ፤ 2ኛ/ በማይካድራ በሚኖሩት ወገኖች ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሱ ተሰማ። በዚህ ምክንያት ፌደራል መንግሥት ሕግና ሥርዓትን አስጠብቃለሁ ብሎ በህወሃት ላይ ጦርነት ከፈተ። ዳሩ ግን ዓላማዉን በደንብ ሳይመታና ህዝቡን ሳያረጋጋ ትግራይን ጥሎ ወጣ። ህወሃት ግን ያንን ክፍተት በመጠቀም ወዲያዉኑ ወደሥልጣኑ ተመልሶ ከባድ ጉዳቶች ለመሰንዘር ፉከራዉን ጀመረ።
ዛሬ ከትግራይ ክልል በመዉጣት በወልቃይት፤ በራያ፤ በአላማጣ፤ በአፋር፤ ወዘተ ላይ ጉዳቶች ለማድረስ እየሞከረ መሆኑ ይሰማል። ይሄ ጎዳይ የክልሎቹ ብቻ ሳይሆን የፌደራል መንግሥት ዋና ኃላፊነት መሆን አለበት። ችግሩ የአማራና የትግራይ፤ ወይም የትግራይና የአፋር መስሎ መታየት የለበትም፤ ሀገራዊ ጉዳይ ነዉና። ማንኛዉም ክልል ድንበሩን አቋርጦ ወጥቶ በህዝብ ላይ ጉዳት ሲያደርስ በዋናነት ክልሎች ደጀን ይሆናሉ እንጂ ብቻቸዉን የሀገር ፀጥታ አስከባሪዎች ሊሆኑ አይችሉም። ጥቃቶች በሚደርሱባቸዉ ቦታዎች በሙሉ በፌደራል መንግሥትና በመከላከያ ኃይል እርምጃዎች እንዲወሰዱ ይጠበቃል።
3ኛ/ በክልሎች መካከል የድንበር ግጭቶችን በተመለከተ
ተደጋግሞ እንደተገለፀዉ፤ ህወሃት ወደሥልጣን ሲመጣ የአማራ/ጎንደር አካላት የሆኑትን ምድሮች በጉልበት ቆርጦ ወደትግራይ ከለለ። እነዚህም ወልቃይትን፤ ጠገዴን፤ ጠለምትን፤ ወዘተ ሲያጠቃልሉ ከወሎ ደግሞ እነራያን ይመለከታል። ይሄ ችግር የአማራንና የትግራይን ህዝብ እርስ በርስ በማያናክስ መንገድ ሊፈታ ይችላል። 1ኛ/ ድንበሮችን በተመለከተ በቂ ታሪካዊ መዝገቦችና መረጃዎች አሉ። ዳሩ ግን ምድሮቹ ወደቀድሞዎቹ ክልሎች/ክፍሎች ይመለሱ ማለት የትግራይ ህዝብ አይኑርበት ማለት አይደለም። ህዝባችን ከጥንቱ ጀምሮ ወደፈለገበት ቦታ እየተዘዋወረ የመኖር፤ የመሥራትና የመነገድ መብት ነበረዉ። የህወሃት ከፋፋይ ሕገ መንግሥትና አምባገነንነት ያመጣብን አባዜ እንጂ በጭቁን ህዝብ መካከል ጠላትነት የለም።ህዝባችንም ይሄን ሃቅ በደንብ ማስታወስ ይኖርበታል።
ከዚያም ከዚህ ብዙ እልቂቶች ይሰማሉ። ስለዚህ ምን እንደምንጠብቅ ሊገባኝ አልቻለም። የትግራይ ህዝብ ለሺዎች ዓመታት በአብሮነትና በመልካል ጉርብትና ከአማራዉ፤ ከአፋሩ፤ ወዘተ ጋር በሰላም ኖሯል። ዛሬም በሰላም እንዳይኖር መከልከል የለበትም። ልጆቹን ለጦርነት መማገድ የለበትም። ልጆችን ወደትምህርት ቤቶች እንጂ ወደጦር ሜዳዎች መላክ እጅግ በጣም ከፍተኛ ኃጢያት ነዉ። ገበሬዉ በሰላም ካላረሰ፤ ነጋዴዉ በሰላም ካልተንቀሳቀሰ ምን ሊበላ ነዉ?
ይህ ጉዳይ በፓርላማና በድንበር ኮሚሺን አማካኝነት እልባት ሊያገኝ ይገባል። ሰላምና ዕድገት ይሰፍኑ ዘንድ ከፋፋዩም ሕገ መንግሥት ቶሎ መለወጥ ይኖርበታል።
ከነሩዋንዳ እንኳን መማር የማይችሉ ጽንፈኞች መበርከት እጅግ በጣም ያሳዝነኛል። እነዚህ ሰዎች ከስህተቶቻቸዉ እስኪማሩ ድረስ የሚሊዮኖች ሕይወት መጥፋት የለበትም።
ካለዚያ ጉዳቶች እየተባባሱ ይሄዳሉ፤ ወደሌሎችም ክልሎች ይቀጣጠላሉ። የተለመደዉ ርሃብ፤ ጥማት፤ እርዛት፤ ስደት፤ ልመናና እንግልት እየባሰበት ይሄዳል። ሰላም ሳይኖር ዕድገት ሊመጣ አይችልም። ተያይዞ መጥፋትን ያስከትላል።እግዚአብሔር ሁሉን አሟልቶ የፈጠራትና ለሁሉም የዳቦ ቅርጫት መሆን የሚትችል የተቀደሰች ሀገር እንደዚህ ስትወርድ በማየቴ ዘዝናለሁ፤ አለቅሳለሁ። የተማርነዉም፤ የታገልነዉም ለዲሞክራሲና ለዕድገት እንጂ እንደዚህ ዓይነት ዉርደትና ጥፋት ለማየት አልነበረም።
4ኛ/ የሀገራዊ እርቀ ሰላም አስፈላጊነት
አንዲት ጣት በሰበሰች ተብላ ተቆርጣ አትጣልም ይላሉ አበዉ ሲተርቱ። በርግጥ ህወሃት በትግራይ ከፍተኛ ተጽእኖ አላት። መፍትሔዉ ግን አማራጭ የተሻለ ሥርዓት ግንባት በማመቻቸት ህዝብን መሳብ እንጂ ማራቅ አያዋጣም።
የትግራይም ህዝብ የዓማራ ጭቁን ወገኑን እንደጠላት ማየት ትልቅ ኃጢያት ነዉ። ጠላቶች የተፈራረቁ በዝባዥ አምባገነን ሥርዓቶች ናቸዉ እንጂ ጭቁን ህዝብ አይደለም። እንንቃ ጎበዝ፤ ቅን ልቦና ይስጠን። አሁን ያለነዉ በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ዉስጥ መሆኑን አንርሳ።
አሁን የሚታየዉ እኮ ከፍተኛ እልቂት ነዉ። ይሄ እስከመቼ ድረስ ሊቀጥል ይችላል? በከፍተኛዉ እየተሰቃዩ ያሉት እኮ ሕፃናት፤ ሴቶችና አረጋዉያን ናቸዉ። ባለሥልጣናት እኮ ልጆቻቸዉና የዘረፉት ሀብትም ዉጭ ሀገራት ናቸዉ። እንደሀገር የምንቀጥል ከሆነ እርማት ማድረግ ይኖርብናል።
ይሄን ጥያቄ በተመለከተ የሚከተሉት አካላት ከእንቅልፋቸዉ ነቅተዉ የሚጠበቅባቸዉን ኃላፊነቶችና ግዳጆች እንዲወጡ በትህትና ላሳስብ እወዳለሁ፤
ሀ) የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ የመንግሥት ኃላፊነት፤
ለ) ወገን እንዳይጠቃ የመከላከያው ኃይል ኃላፊነት፤
ሐ) የኃይማኖት አባቶች የማስታረቅና የመገዘት ኃላፊነቶች፤ ታላቁ መጽሐፍ አትግደል፤ አትስረቅ፤ አታመንዝር፤ በባልንጀራህ ላይ በሀሰት አትመስክር፤ ባልንጀራህን እንደራስህ ዉደድ፤ የተራበዉን አብላ፤ የተጠማዉን አጠጣ፤ እንግዳ ተቀበል፤ የታረዘዉን አልብስ፤ የታመመዉን ጠይቅ፤ ወዘተ አለ እንጂ ግደል፤ አፈናቅል፤ ዝረፍ አላለም። የኦርቶዶክስ አከርካሪ ሰበርን ብለዉ በአደባባይ የሚፎክሩትን ሰይጣናዉያን እያያችሁ፤ እየሰማችሁ ዝም ማለት የለባችሁም፤ ማስተማርና መገዘት ግዳጃችሁ ነዉና፤
መ) የሀገር ሺማግሌዎች ኃላፊነት
ዉድ ወገኖች፤ የምታዉቁትን ላስታዉሳችሁ በማለት እንጂ ብዙ የጨመርኩት አዲስ ነገር የለም። ያለችኝን የማካፈልና የሚሰማኝን ስጋት የማጋራት ኃላፊነት ግን አለብኝ ብዬ ስለማምን ነዉ።
ቸሩ አምላካችን ጭቁን ህዝባችንና ዉድ ሀገራችንን ይጠብቅ