በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ስራ ላይ የተሰማራው il&FS አይኤል ኤንድ ኤፍኤስ የተሰኘው የህንድ ኩባንያ ሰራተኛ የሆኑት ህንዳዊያን እንደታገቱ ገለፁ፡፡ ከታጋቾቹ አንዱ እንደሆነ የገለፀው ኒራጅ ራጉዋንሺ በትዊተር ገፁ ዛሬ ይፋ እንዳደረገው እሱን ጨምሮ ሰባት ህንዳዊያን ከታገቱ አራት ቀን ሆኗቸዋል፡፡ኩባንያው ለሰራተኞቹ ደመወዝ ባለመክፈሉና ያለበትን እዳም ሊከፍል ባለመቻሉ ኢትዮጵያዊያኑ ሰራተኞችና አበዳሪዎች እገታውን እንደፈፀሙም አስረድቷል፡፡
ኩባንያው ከሁለት አመት በፊት በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አማካኝነት የወጣውን አለም አቀፍ ጨረታ አሸንፎ ወደስራ የገባ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት እንደከሰረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የሰራተኞቹ ደመወዝና ያለበት እዳ እንዲከፈል በተደጋጋሚ ለኩባንያው ጥያቄ ቢያቀርብም ከኩባንያው አጥጋቢ ምላሽ ሊያገኝ እንዳልቻለ የጠቆመው ራጉዋንሺ መልእክቱ ለጠ/ሚ/ር ናሬንድራ ሞዲ እና ለካቢኔያቸው እንዲደርስ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ታጋቹ ግለሰብ በተከታታይ ትዊት ያደረገ ሲሆን በእነዚህ ትዊቶቹም ‹‹አሁን ከታገትንበት ብንለቀቅም የአካባቢው ባለስልጣናት እስር ቤት ያስገቡናል፣ ወይንም ኩባንያው በፈጠረው ስህተት የአካባቢው ነዋሪ ይገድለናል›› ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡ በመልእክቱ እንዳስረዳው የታጋቾቹ ጥፋት ለኩባንያው ታማኝ በመሆን ፕሮጀክቱን ለመጨረስ መስራታቸው ነው፡፡ እነዚህ ህንዳዊያን ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር ተገናኝተው እንደነበር የተናገሩ ሲሆን የባለስልጣኑ ሰራተኞችም እርምጃ ከሚወስዱባችሁ በፊት የአካባቢውን ነዋሪ ወዝ አደር ደመወዝ መክፈል አለባችሁ የሚል ምክር እንደሰጧቸው አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘው የህንድ ኤምባሲም ተመሳሳይ ምላሽ እንደሰጣቸው ነው የተናገሩት፡፡
አሁን ከወደ ህንድ በሰማነው ዜና ደግሞ ኪሳራ ደርሶበት አክሲዮኑ በሀራጅ እየተሸጠ ያለውን ይህን ኩባንያ እያስተዳደረ ያለው ተቋም ስለጉዳዩ ሰምቶ ከኢትዮጵያ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ድርድር ጀምሯል፡፡ ለዚህ የመንገድ ስራ ፕሮጀክት ዋስትና የሚሰጥ የህንድ ድርጅት ካለ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ታጋቾቹ የሚለቀቁበትን መንገድ ሊፈልግ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ኩባንያው ከነቀምት እስከ ቡሬ ያለውን ከ160 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ በስምንት አመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ኮንትራቱን የወሰደው በ223 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህም ገንዘብ የተገኘው ከአለም ባንክ ከተገኘ ብድር እንደሆነ ለመረዳት ችለናል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=DKNGEfUvzgA