April 4, 2024
12 mins read

፳ ፻ ፳ ዓ. ም. ሩቅ ነው – አንዱ ዓለም ተፈራ

ቀላሉ ነገር፤ እኔ የምፈልገውን ይሆናል ብሎ መተንበይ ነው።ሀቁ ግን በጣም የተወሳሰበና ጠለቅ ያለ ምልከታን የሚጠይቅ ነው።ከአራት ዓመታት በኋላ አገራችን ውስጥ ሊከተል የሚችለውን እውነታ ወዲህ ሆኖ ለመተንበይ፤ ብዙ በአገራችን የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ያሉ ተለዋዋጭ ጉዳዮችን ማገናዘብ ግድ ይላል።ከሰማይ ዝቀው የሚያቀርቡት ተዓማራዊ እወነታ የለም። አሁን አገራችን ያለችበት የፖለቲካ እውነታ፤ ዛሬ በቦታው ላለነው እንኳ ለመረዳትና እንዲህ ነው! ብሎ ለመግለጥ በጣም አስቸጋሪ ነው።በኢትዮጵያ ተጨባጭ የፖለቲካ እውነታ ደግሞ፤ ፳፻፳ ዓ. ም. በጣም ሩቅ ነው።በዚህ ጽሑፍ ያ ወቅት ሲመጣ፤ በአገራችን ሊከሰት ይችላል የምለውን ለማሳየት እሞክራለሁ።

ከላይ ተንጠልጥሎ ሁሉን የሚገዛው ጉዳይ፤ በመንግሥት ሥልጣን የተቀመጠው አካል እምነትና አካሄድ ነው።ይህን ሥልጣን የሚቆጣጠረው፤ በአገራችን ሕዝብ የቀን ተቀን የኑሮ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ሚና አለው።ይህ እንግዲህ፤በርሻው፣ በንግዱ፣ በትምህርቱ፣ በሕክምናው፣ በሰዎች እንቅስቃሴ፣ በአገር ውስጥ ጉዳይና በውጪ አገራት ጉዳይ ሂደቱ፣ ወደ ሥልጣኔ በሚደረገው ግስጋሴ ወይንም የኋሊይሾ ጉዞ፣በአገራችን ስላምና ልማት፣ በጥቅሉ፤ በነገው እውነታ ላይ ማዕከላዊ የሆነ ሁለተናዊ ሚና አለው። ያ እንዳለ ሆኖ፤ ይሄ አካል ብቻ አይደለም ሜዳውን ተቆጣጥሮ ጨዋታውን የሚመራው። አሁን ያለውን መንግሥት ለመተካትና የተሻለ መንግሥት ለማቋቋም የተሰለፉት፤ ተቀራራቢ ሚና አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ይሄን አካል በመደገፍ ወይንም በመፎካከር የተሰለፉት የማይናቅ ሚና አላቸው።ሕዝቡ በተደራጀ መንገድም ሆነ ባልተደራጀ መንገድ፤ ለዚህ ሂደት አስተዋፅዖ አለው። እስኪ አሁን ያለውን ሀቅ እንመለከት።

በሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ቡድን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ነው መባሉ ቀርቶ፤ መንግሥት ለመባል በቂ አይደለም። ይሄን ያልኩበትን ምክንያት ላብራራ።የአንድ አገርን መንግሥት፤ መንግሥት የሚያስብለው፤ አገሪቱን ወክሎ ሲገኝ፣ ለአገሪቱ አጠቃላይ ሰላምና ልማት፣ ለመላ ሕዝቡ የኑሮ አመቻች ሆኖ ሲገኝ ነው። እኒህ ብቻ መመዘኛዎች አይደሉም፤ ነገር ግን መሠረታዊ መነሻ ናቸው። እኒህ ካልተሟሉ ሌላው ገብስ ነው።

በነኚህ መመዘኛዎች በአገራችን ያለውን ገዢ ቡድን ስናቆመው፤ ይሽመደመዳል። አንድን ወገን፤ ለዚያውም አክራሪውን ክፍል ወክሎ የቆመ አካል ነው። ያ ብቻ ሳይሆን፤ ዐማሮችን ለማጥፋት መንግሥታዊ ተልዕኮው ያደረገ ነው።እናም አገራችንን ለማስተዳደር ሳይሆን ለመቀየር የተነሳ ነው። በዚህ ሂሳብ ኢትዮጵያዊ ወይንም የኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም። ይሄን ያልኩት፤ ገዢው ክፍል አገር አቀፍ የሆነ የተለየ ርዕዩተ ዓለም ስላራመደ ወይንም በተግባር ወደ ሥልጣኔ በፍጥነት ስለሄደ ወይንም ስላዘገመ አይደለም። በመሠረቱ አገር አቀፍ የሆነ ራዕይም ሆነ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ ስለሌለው ነው።

ከዚህ ተነስተን፤ ስላምን ባገር ስለማስፈን፣ ስለትምህርት ወይንም ስለሌሎች መንግሥታዊ ተግባራት ማተቱ ከንቱ ነው። እናም ሰላም ሳይሆን ጦርነትን መዝራቱ ከዚህ ማንነቱ ጋር የተያያዘ ነው። ይሄን መንግሥት ወደ ሥልጣን ለማምጣት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ “አትከፋፍሉን!” “አንድ ነን!” ብሎ ነበር የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር ከሥልጣን ያባረረው። ይሄ ገዢ ቡድን ተተክቶ ግን፤ በትግሮች ቦታ ኦሮሞዎችን ከመተካት ያለፈ የለወጠው ነገር የለም። ይልቁንም በበለጠ አረመኔነትና ልክ የሌሽነት፤ ያንኑ የትግሮች ነፃ አውጪ ግንባር የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር ዘይቤ አፋፋመው። ሕዝቡ ወዲህ፡ የተተካው መንግሥት ወዲያ! በረከትን እና ስብሃትን ፈቶ መስከረምን እና ታዲዮስ ታንቱን የሚያስር! ኦነግ ሸኔን በጉያው አስቀምጦ ዐማሮችን በድሮንና በታንክ የሚደበድብ! ይሄን ገዢ ቡድን፤ ኢትዮጵያዊም መንግሥትም ማለት አይቻልም።

ይሄን ጉዳይ ብቻ መነሻ አድርጎ፤ ፳፻፳ ዓ. ም.ን መተንበይ በጣም ቀላል ነው። የበለጠ ትርምስ፣ የበለጠ መተላለቅ፣ የከፋ ወደፊት ይሆናል። ጥሩነቱ ግን፤ ይሄ አካል ብቻ አይደለም በፖለቲካው ምህዳር ተጫዋች የሆነው። ሌሎች ተጫዋቾችም አሉ። ዐማራው ለህልውናው በሚያደርገው ትግል፤ የፋኖ ድርጅት ከፍተኛ ሚና አለው። ፋኖ፤ ለዐማራው ብቻ ሳይሆን፤ ለነገዋ የኢትዮጵያ መንግሥት እርሾ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፤ አሁን በዐማሮች ምድር ያለው፤ ገዢው ቡድን ወራሪ ሆኖ፤ ዐማሮች በፋኖ በኩል መከላከላቸውን ብቻ ሳይሆን፤ መንግሥታዊ ክንውናቸውን እያካሄዱ የለበት ሀቅ ነው። እናም በዐማራው ምድር፤ ፋኖ መንግሥት ነው። ታዲያ የፋኖ ዕድገትና ሂደት፣ የፋኖ ተግባርና እንቅስቃሴ፤ በአገራችን በ፳፻፳ ዓ. ም. ሊመጣ የሚችለውን ሀቅ ተናጋሪ ነው። ፋኖ አንድ ወጥ ሆኖ፤ ሌሎች ይሄንን አክራሪ ገዢ ቡድን “የኔ!” ያላሉ ኢትዮጵያዊያንን አስተባብሮ፤ ነገ የሽግግር መንግሥት ያቋቁማል።

በአንጻሩ ደግሞ፤ አሁን በመንግሥቱ ዙሪያ ያሉ ደጋፊም ሆነ ተፎካካሪ አካላት፤ የዚሁ ትንበያ ተጫዋቾች ናቸው። እነሱ የሚሠጡት የመንግሥት ድጋፍ ወይንም፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከገዢው ቡድን በላይ አድርገው በመመልከት የሚያከናውኑት ተግባር፤ የ፳፻፳ ዓ. ም.ን ሀቅ ሊነግረን ይችላል። ይህ ማለት፤ ገዢውን ቡድን ደግፈው ከቆሙ፤ ከስማጭ መርከብ ጋር ተቆራኝተው፤ ለጊዜው በጎውን መጪ ያዘገዩታል። የገዢውን ቡድን እውነተኛ ዓላማ ተረድተው፤ የራሳቸውን ቀዳዳ አበጅተው ከሕዝቡ ጋር ከቆሙ፤ ለውጡን በማገዝ አገራችን በትክክል ቀና መንገድ እንድትይዝ ይረዳሉ። እናም ፳፻፳ ዓ. ም.ን የተሻለ ቦታ ያስቀምጣሉ።

እንግዲህ ሶስቱን ክፍል ዳሰሰኩ። በዚህ ሂደት የሕዝቡ ተሳትፎ ምንድን ነው? ይሄን ለመመለስ ብዙ ጉዳዮችን ማገናዘብ ያስፈልጋል። በመሠረቱ ሕዝቡ በሰላም መኖር፣ ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ ማደር መሽከርከሪያ የኑሮ አምዱ ናቸው። ፳፻፳ ዓ. ም.ን በሚመለከት፤ በተናጠል ግለሰቦች ከሚያደርጉት አስተዋፅዖ ይልቅ፤ የተደራጁት ዋናውን ሚና ይወስዱታል። እናም የተደራጀው የኅብረተስ ክፍል ወሳኙን ሚና ይጫወታል። ሕዝቡ በግልጥም ይሁን በሕቡዕ የሚያደረው ተሳትፎ በተደራጀ መልክ እስካልሆነ ድረስ፤ አስተዋፅዖውን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስቸግራል። ስለዚህ፤ ሕዝቡ ቢበደልም፣ ኑሮ ቢከፋም፣ መብራት ቢጠፋበትም፣ የበርበሬ ዋጋ ቢንርበትም፣ ዳቦ ከሱቅ ባይገኝም፣ የሚያደርገው ሚና አነስተኛ ነው። የ፳፻፳ ዓ. ም. ሁኔታ፤ አሁን ባለው ገዢ ቡድን፣ ይሄን ገዢ ቡድን ተቃውመው በተነሱ አካላትና ገዢውን ቡድን በመደገፍም ሆነ በመፎካከር ተደራጅተው በቆሙ አካላት ይወሰናል።

አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሀቅ ደግሞ፤ ገዢው ቡድንና ፋኖ ናቸው የፖለቲካ መድረኩን ባብላጫው ይዘው የሚገኙት። በኔ ግንዛቤ፤ ገዢው ቡድን አጥፊ፣ ወደ ውድቀቱ እያሽቆለቆለ ያለ ኃይል፣ አገር አፍራሽና ኢትዮጵያዊያንን የሚጠላ አካል ነው። ፋኖ እያደገ ያለ፣ ወገኑን እና አገሩን ወዳድ፤ በስነ ስርዓት እየተመራ ያለና የወደፊቱ የበራ ኃይል ነው። በኔ እምነት በ፳፻፳ ዓ. ም.፤ ፋኖ አድጎ ከዚህ የፀረ ኢትዮጵያ ገዢ ቡድን የመንግሥቱን ሥልጣን በጉልበቱ ነጥቆ፤ ሰላምን በማስፈን፤ ዕድገትን አስገኝቶ፤ በውጪ አገራት የተበታተነው ወገኑን አፍቃሪው እና እምቅ ዕሴት ያዘለው ስደተኛ ወዳገሩ ተመልሶ፤ ባጭር ጊዜ ወስጥ አገራችን ታድጋለች። ለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋፅዖውን አሁን ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ። መልካሙን እመኛለሁ!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop