ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ጥር 19፣ 2017(January 27, 2025)
ሰሞኑን እስክንድር ነጋ “እመራዋለሁ የሚለውን የፋኖ ክንፍ” በመወከል ከአቢይ አህመድ አገዛዝ ጋር፣ እሱ እንደሚለው ውይይት፣ በመሰረቱ ድርድር እንዳደረገ በተለይም እነ ሀብታሙ አያሌው በሚቆጣጠሩት የኢትዮጵያ 360 ዲግሪ ሚዲያ ሰምተናል። ከመንግስት ጋር ለማደራደር የተገኙት ታዛቢዎች ደግሞ የውጭ አገራት ዓለም አቀፋዊ ስም የተከናነቡ ድርጅቶች ናቸው። የእነዚህ ታዛቢዎች ዋና ተግባር ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ አንድ መንግስት አስተዳድረዋለሁ በሚለው ህዝብ ላይ ስንትና ስንት ወንጀል ከፈጸመ፣ ወይም ደግሞ ስልጣን ላይ ለመውጣት ርስ በራሳቸው የሚዋጉ ኃይሎች ህዝባቸውን ካጫረሱና ህዝቡም ተስፋ ከቆረጠ በኋላ የመጨረሻ መጨረሻ ለዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው የሚስማማና በቀላሉም የሚጠመዘዝ አገዛዝ በመመስረት ድሮ የነበረውንና አሁንም ያለው የተመሰቃቀለ ሁኔታ እንዲቀጥል ማደረግ ነው። ከእነዚህ ዐይነት ድርጅቶች በስተጀርባም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ወይም ሲአይኤ እንዳለበት ይታወቃል። የእነዚህ ተዛቢዎችም ዋና ዓላማ ከላይ የተጠቀሰው ነገር ብቻ ሳይሆን፣ አንድ አገዛዝ በህዝቡ ላይ የፈጸመው ወንጀል እንዲረሳ ማድረግ፣ ወይም ትክክል ነው ተብሎ ሰፊው ህዝብ እንዲቀበለው ማድረግና ወንጀል ፈጻሚዎችም ከማንኛውም ወንጀል ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ ማድረግ ነው።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ እስክንድር ነጋ እመራዋለሁ የሚለው የፋኖ ክንፍ ከአቢይ አገዛዝ ጋር ለመደራደር መሻት በመሰረቱ የጠቅላላውን የአማራን ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጎዳና የነፃነትና የዲሞክራሲ ፍላጎቱን የሚያጨልምበት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት እንዳይወጣም የሚያደርገው የከፋፍለህ ግዛው አካሄድ ነው። እስክንድር ነጋ በስልጣን ጥም ያበደና በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነት መንፈስ የታነፀ ግለ-ሰብ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከወያኔ ጋር ባደረገው ግብግብ እስርቤት እንደገባ ይታወቃል፤ ብዙም ተሰቃይቷል። ይህንንም በመጠቀም በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች አግኝቷል። እነዚህ ደጋፊዎች ደግሞ እስክንድር ነጋን እንደ ጀግና ከመቁጠርና ከማመን በስተቀር እስክንድር ነጋ ምን ዐይነት ርዕይና ፍልስፍና እንዳለውና፣ የተወሳሰበውንም የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህል፣ የኢኮሎጂና የስነ-ልቦና ቀውስና፣ ሌሎች ልዩ ልዩ ችግሮች እንዴት እንደሚፈታ የሚያውቁት አንዳችም ነገር የለም። አብዛኛዎቹም ከመጮህና ግለሰብን ከማምለክ ውጭ በአጠቃላይ ሲታይ ሰለፖለቲካና፣ በተለይም ደግሞ ስለዓለም አቀፍ ፖለቲካ የሚያውቁት ምንም ነገር የለም። በተጨማሪም የወያኔና የአቢይ አህመድ አገዛዝ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በመደገፍ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ተግባራዊ ያደረጓቸውን አገር አፍራሽና ህዝብን በታታኝ ነገሮች በመመርመርና በማጥናት የራሳቸውን ፍርድ ለመስጠት ያልቻሉና የማይችሉ ናቸው። ስለሆነም ይህንን የተደናበረና የአላዋቂ የማህበረሰብ ክፍል አካል ድጋፍ በማድረግ ነው እስክንድር ነጋ በቀላሉ ዕውቅናን ለማግኘት የቻለው።
የእስክንድር ነጋን የትግል የህይወት ታሪኩን ለተከታተለ የጠራ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አመለካከት የለወም። 27 ዓመት ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜና፣ በአቢይ አህመድም ከተተካ በኋላ ሁለቱም አገዛዞች በጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሱትን መጠነ-ስፊ ጥቃት፤ በተለይም በጦርነት፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና በማህበራዊና በሌሎችም ነገሮች የሚገለጸውን አንዳችም ሀተታ በፍጹም አልሰጠም። እንደሚታወቀው የህወሃትም ሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረ-አበሮቹ ኢትዮጵያን ለማፈረካከስና ሰፊውም ህዝባችን ድንብርብሩ እንዲወጣ ለማድረግ ስልጣን ላይ የወጡ ናቸው። ባለፉት ሰላሳ ሶስት ዓመታት በአገራችን ምድር የተካሄደው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ጦርነቱም የኢትዮጵያ ህዝብ አጀንዳዎች ሳይሆኑ የአሜሪካን ኢምፔሪሊዝም አጀንዳዎች ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ የህወሃትም ሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ በራሳቸው አስተሳሰብ በመመራት አገራችንን በዕውቅ ለመግዛትና ህዝባችንን ከድህነት ለማላቀቅ ሳይሆን ለዝንተ-ዓለም ደሀና ለማኝ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ ነው። በተጨባጭ በምድር ላይም የሚታየው ሁኔታ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የግብረ-አበሮቹም ዋና ዓላማ በነፃ ገበያና በነፃ ንግድ ስም አሳበው አንድን ኃይል ስልጣን ላይ ካወጡ በኋላ የአንድን አገር የጥሬ-ሀብት በመቆጣጠርና በመዝረፍ ሰፊው ህዝብ ደሀ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ ነው። በዚያውም በስለላ ድርጅትና በከባድ መሳሪያ በታጠቀ ወታደር የሚታጀብ አገዛዝ በማድረግ ሰፊው ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይጎናፀፍ፣ ወይም በፍርሃት እንዲኖር ማድረግ ነው። በአብዛኛዎቹ የአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። በአንዳቸውም የአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ በራሱ ፍልስፍናና በነፃ አስተሳሰብ እየተመራ አገሩን የሚያስተዳድር አገዛዝ በፍጹም የለም። ለዚህም ነው በአብዛኛዎቹ የአፍሪካና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ስንትና ስንት የጥሬ-ሀብትና ልዩ ልዩ ሰብሎችንና ፍራፍሬዎችን ለማፍራት ወይም ለማብቀል የሚችል ፍሬያማ መሬት እያለ ሰፊው ህዝብ በጣም ጥቂት በሆኑ፣ ለምሳሌ እንደ ቡና፣ ካካኦ፣ ሙዝና ኦቾሎኒ …ወዘተ. ምርቶች ላይ ብቻ በማትኮር በድህነት ዓለም ውስጥ የሚኖረው። የተለያዩ አገዛዞችም ዋና ዓላማ ይህ ዐይነቱ የአስተራረስና የአኗኗር ስልት እንዲቀጥል በማድረግ ሰፊው ህዝብ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ነፃና ሁለ-ገብ የሆነ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ማድረግ ነው። ፍሪድሪሽ ሊስት የሚባለው የ19ኛው ክፍለ-ዘመን የኢኮኖሚና የፍልስፍና የጀርመን ምሁር የነበረውና የእንግሊዝን የነፃ ንግድ ፖሊሲ አጥብቆ የታገለው እንደሚያስተምረን አንድ አገር በማኑፋክቸሪንግ ላይ፣ እንዲያም ሲል በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የሆነ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚና ገበያ ከሌላት በውጭ ኃይሎች በቀላሉ ትጠቃለች፤ በባህልና አንድን አገር በሚያስተሳስሩ ልዩ ልዩ ነገሮችም ልትዳብር በፍጹም አትችልም እንደሚለን የህውሃትም ሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ይህ ዐይነቱ ነገር በአገራችን ምድር ተግባራዊ እንዳይሆን ነው የሰሩትና የሚሰሩትም። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነት አገዛዞች ዘራፊ አገዛዞች(Predatory States) በመባል ይታወቃሉ። በዓለም አቀፍ የፊናንስ ካፒታል ቁጥጥር ስር ያሉና በእነሱም የሚታዘዙ ናቸው።
እስክንድር ነጋ ዕውነተኛ ፖለቲከኛና የህዝብ ተቆርቋሪና፣ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲና ነፃነት የሚታገል ቢሆን ኑሮ ይህ ሁሉ የኢምፔሪያሊስቶች መሰሪህ ተግባር በገባው ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለህዝብና ለአገር ተቆርቋሪ፣ እንዲሁም ለዕውነተኛ ዲሞክራሲና ነፃነት እታገላለሁ የሚል ቢሆን ኖሮ በፍጹም አንድን ኃይል ወይም ህዝብን የሚከፋፍል ስራ ባልሰራ ነበር። የተከፋፈለ ኃይልና የጠላቶችን ሴራ በሚገባ የማያውቅ ደግሞ በምንም ዐይነት ዕውነተኛ ነፃነትን አያገኝም። ይህን ትተን አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በህዝባችን ላይ፣ በተለይም በአማራው ወገናችን ላይ የፈጸመውን ፋሺሽታዊ ድርጊት ስንመለከት ማንኛውም ኃይል ከእንደዚህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊ ኃይል ጋር እደራደራለሁ የሚል ከሆነ ራሱ ዲሞክራት አይደለም። ዋናው ፍላጎቱም በአቋራጭ ስልጣን ላይ ለመውጣትና የራሱን የስልጣን ጥም ለማርካት ብቻ ነው። እንደዚህ ዐይነት ኃይልም በመሰረቱ ዋናው ዓላማው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምንና የግብረ-አበሮችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚታገል ነው ማለት ነው። ስለሆነም የእስክንድር ነጋ አካሄድና የከፋፍለህ ግዛው ስትራቴጂ በጥብቅ መወገዝ ያለበት ነው። ማንኛውም አገር ቤትም ሆነ ውጭ ያለ በአማራው ህዝባችን ላይ የደረሰውንና የሚደርሰውን በደል የሚያወግዝ ሁሉ የእስክንድር ነጋንና የግብረ-አበሮቹን የውንብድና ሴራ ማውገዝ አለበት። በሜዳ ላይ የሚዋደቁት የተለያዩ የፋኖ ድርጅቶች በዚህ ሳትወናበዱና ኃይላችሁን ሰብሰብ በማድረግ በዕውነተኛ ፍልስፍናና የሳይንስ መሰረት ላይ በመሰባሰብ ትግላችሁን ማፋፋም አለባችሁ። ከፋሺሽታዊው አቢይ አህመድና በብልፅግና ስም ከሚያወናብዱት ተከታዮቹ ጋር በመደራደርና የጋራ መንግስት በመመስረት የአማራውም ሆነ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነታቸውን ሊጎናፀፉ በፍጹም አይችሉም። አማራውም ሆነ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተሟላ ነፃነታቸውን ሊጎናፀፉና የተከበረ አገር ሊመሰርቱ የሚችሉት እንደዚህ ዐይነት የኢምፔሪያሊስቶች፣ በመሰረቱ ፋሽዝምን በሚያስፋፉት የሚደገፍና የሚመከር የአቢይ አህመድ አገዛዝና መሰረቱ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ሲወገድ ብቻ ነው። የእስክንድር ነጋም አካሄድና ርዕይ በፍጹም ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። የእስክንድር ነጋ ርዕይ ቀኝ የሆነና ጠቅላላውን ህዝባችንን ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ሊያላቅቀው የሚችል አይደለም። ህዝባችን እየተሽመደመደና ማንም የውጭ ኃይል እየመጣ እንዲጨፍርበት የሚያደርግ ፋሽሽታዊ አካሄድ ነው። የእስክንድር ነጋ የትግል አካሄድም የኢትዮጵያ ህዝብ ዋና ጠላት ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው የጥቁር ህዝብም ጠንቅ ነው። ምክንያቱም ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች እንደዚህ ዐይነቱን የተሽመደመደና ምንም ዐይነት ርዕይ የሌለውን ኃይል በመጠቀም ነው አንድን አገርና ህዝብ ለዝንተ-ዓለም ጨለማ ውስጥ በመክተት ነፃና የተከበረ አገር እንዳይገነባ የሚያደርጉት። መልካም ግንዛቤ!!
የወንድሜ ፈቃድ ሃሳብ ሁለት ነገሮችን ይዟል። አንደኛው አማካሪ አስታራቂና ሰላም ፈላጊ መስለው በመሃላችን የሚገቡ የውጭ ሃይሎች ራስ ጠቀም ግብና አላማ ሲሆን ሁለተኛው የፋኖ አንድ ክንፍ ለሰላም እደራደራለሁ ማለቱ ለአማራ ህዝብ በጎነት የለውም የሚል ነው። የመጀመሪያው ሃሳብ እኔም የምጋራው በመሆኑ መፍትሄው መንቃትና ራስን ለውጭ ሃይሎች ተጠቃሚ ላለማድረግ ብልሃትን መፈለግና እሳትን በእሳት ሳይሆን በብልሃትና በዲፕሎማሲ መታገል ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው በምድሪቱ ሰላም ሲኖር ብቻ ነው። ያኔ ከውጭም ከውስጥም ሆነው እኛኑ ለማባላትና ለማዳከም ሥፍራ አይኖራቸውም።
በመሰረቱ የፋኖ ሁለት ዓመት የዘለቀ ፍልሚያ የአማራን ህዝብ ሰቆቃ ያባባሰና ህዝቡን ወደ ኋላ የመለሰ ለመሆኑ ሥፍራው ላይ ተገኝቶ መመልከት ይቻላል። የስማ በለው ወሬ ተከትፎና ታሽጎ ስለሚቀርብ እውነቱን ለመለየት ያስቸግራል። ዛሬ በአማራ ክልል ማረስ ያቆሙ፤ ንግድ ቤታቸው የተዘጋ፤ ከትምህርት የተፈናቀሉ፤ ህክምና በማጣት የሚያልቁ፤ የሚበላና የሚጠጣ ጠፍቶ በረሃብ የሚያልቁ እልፎች ናቸው። የዚህ እልቂት መንስኤው ደግሞ የፋኖና የብልጽግና ፍትጊያ ነው። በመሃል ላይ እንደ ገና ዳቦ እሳት የሚዘንብበት ነጻ እናወጣሃለን የምንለው ያ መከረኛና በስሙ የሚነገድበት ህዝብ ነው። በሃበሻ ፓለቲካ ዋናው ችግራችን ሰላም በጦር መሳሪያ ሃይል ብቻ ይመጣል ብሎ የማመን በሽታችን ነው። ዘፈኑ፤ ግጥሙ፤ መጣጥፍና ዲስኩሩ ሁሌ በለውና በይው ስለሚል ሰከን ብሎ ነገሮችን ለማየት ጊዜ አይገኝም። ዘፈኑ የቂጥሽ የባትሽ፤ ፉከራ መጣሁብህ ወዪልህ በመሆኑ ቆም ብሎ ጦርነት ለሰው ልጅ አይበጅም በማለት በየብሄራቸው እሳት የሚቆሰቁሱትን ሁሉ ተው ይህን መንገድ ሞክረነው የተረፈን የለም አማራጭ እንፈልግ እንደማለት ዛሬም ጦርነት፤ ትላንትም ጦርነት ለማንም ለምንም አይጠቅምም።
እስክንድር ነጋም ሆነ ሌሎች የፋኖ አመራሮች ማወቅ ያለባቸው በጋራ ከብልጽግና ጋር ሆነው የሚያፈናቅሉትንና የሚያወድሙትን ህዝብ ዞሮ ተመለሶ እንደነበረ ለማድረግ ጭራሽ የማይቻል መሆኑን ነው። የነቃ ብርሌ አይሆንም እቃ እንዲሉ። ጦርነት ጥሎ የሚያልፈው የሚታይና የማይታይ የስነ ልቦና ጠባሳ አይን ከሚያየው የስጋ ጉዳት የላቀ ነውና ጦርነትን ተደራድሮ ማቆም ብልህነት ነው እንጂ የሽንፈት ምልክት አይደለም። አዎን ይገባኛል የሃገራችን ነገር ” ቆርጥምን ሰድጄ ጎርድምን” እንዲሉ መሆኑን ለማወቅ ዋቢ ማቆም አያስፈልግም የምናየው ነውና። የ70 ዓመት አዛውንት ላይ የ6 ዓመት እስራት የሚፈርድ፤ የሚያጠቡ እናቶችን ጨለማ ቤት የሚዘጋ፤ በዚህም በዚያም የአማራን ህዝብ ቀን በሰጣቸው የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች መሰቃየት ከአንድ ሃገር እመራለሁ ከሚል መንግስት የሚጠበቅ እንዳይደለ ግልጽ ነው። ግን ሃበሻና ፓለቲካ እንዲያ ነው ሁሉ መፈነካከት። ይህን እልፈት የለሽ የብሄር ፓለቲካና የክልል ስርግብ ለማርገብ የሚቻለው በጦር መሳሪያ ሳይሆን በሰላም ሙግት ነው ባይ ነኝ። የብልጽግናው መንግስትና የታጣቂ ሃይሎች ከየትኛውም ወገን ይሁን በሰላም ለሰላም መደራደር ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል እንጂ ተሸናፊ አይኖርም። ግን አንደራደርም የሚሉትም ወገኖች ቢሆኑ ከጅም ቢያመልጡ ከተኩላው ይፋጠጡ ስለሆነባቸው እንጂ ሰላምን የሚጠላ የታመመ ሰው ብቻ ነው። ለዚህ ነው ፋኖዎች ዋስትና ሰተውና ተቀብለው በሰላም ለመኖር ትጥቅ ማውረድ ያለባቸው።
ባጭሩ የዓለም የፓለቲካ ኡደት ከሃገራችን የዘርና የክልል ፓለቲካ ጋር ተዳምሮ በህዋላ ሊጠፋ የማይችል እሳት ቦግ ብሎ ይነድና ምድሪቱን አመድ እንዳያደርጋት ማሰቢያ ጊዜው አሁን ነው። ወያኔን እናቶች እያለቀሱ ጦርነት እንዲቀር ሲለምኑት እንባቸውን ረግጦ የሆነውን አይተናል። አሁንም ገና አላረፈም። የፓለቲካ ንፋሱ አሁን ከመቀሌ ወደ አስመራ ነፍሶ የጠላቴ ጠላት በሚል ሂሳብ ሁለቱ ሃይሎች ጥምረት ፈጥረው ውጊያ አይጀምሩም ብሎ ማሰብ አርቆ አለማየት ነው። አምባገነኖች ለስልጣን ማቆያ ከሚጠቀሙበት ዋናው መሳሪያ ሰውን ለሃገርህ ለወገንህ ለድንበርህ ለነጻነትህ እያሉ ማፋለም ነው። ለዚህ ነው ሰላም ቀዳሚ አማራጭ የሚሆነው። በመሆኑም ሌሎችም የፋኖ እዞች የሰላም ድርድርን እንደ አንድ አማራጭ ማየቱ የተሻለ ነው ባይ ነኝ።