February 14, 2023
14 mins read

ከታሪክ ማህደር: ዋለልኝ መኮንን ማነው ? ያልተሳካው የአውሮፕላን ጠለፋ

ህዳር 29 ቀን 1965 ዓ.ም

ከ 50 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ረፋዱ ላይ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 707 ጄት አውሮፕላን ከአዲስ አበባ በአስመራ በኩል ወደ አቴንስ ሊያደርግ የታሰበው ጉዞ በቁጥር ሰባት የሚሆኑ ግለሰቦች አውሮፕላኑን በመጥለፍ ጉዞውን ወደ አልጄሪያ እንዲያደርግ ያሰቡት ዓላማ ሳይሳካ የከሸፈበት ዕለት ነበር።

በሃያዎቹ መጀመሪያ እድሜው ያደረጋቸው ንግግሮችና ክርክሮች ዛሬም ዘመናትን ተሻግረው እንደታሪክ ይጠቀሳሉ። የድፍረቱ ይባስ!! በ27 ዓመት እድሜው አውሮፕላን ለመጥለፍ መሞከሩ፣ እንኳን በእዉኑ በፊልሙም አለም ተዓምራችን ነው ዛሬም ለኢትዮጵያዊያን። ሌላ ድፍረቱን እናክልና ጥላሁን ግዛው በተገደለ እለት “የታጋያችንን አስክሬን የትግል ጓዶቹ እንጂ ገዳዮቹ አይቀብሩትም” ብሎ የጥላሁንን አስክሬን ከዛሬው የካቲት 12 ሆስፒታል የነጠቀውን የተማሪዎች ቡድን ሲያስተባብር የነበረው ሰው ዋለልኝ ነበር። በዚህ ዕለት ዋለልኝ ተማሪዎችን ሰብስቦ በቀ.ኃ.ሥ. ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከፎቅ ላይ ሆኖ ተማሪዎችን በማይክራፎን ቅስቀሳ አድርጓል።

 

➠ ዋለልኝ መኮንን ማነው ?

ዋለልኝ መኮንን ከአባቱ አቶ መኮንን ካሣና ከእናቱ ወ/ሮ ዘነበች ግዛው መጋቢት 11 ቀን 1938 ዓ.ም ደቡብ ወሎ አማራ ሳይንት ነው የተወለደው። ትምህርቱን በወቅቱ በደሴ ዝነኛ በነበሩት ንጉሥ ሚካኤልና ወ/ሮ ስህን ት/ት ቤት ተከታትሏል። በዋለልኝ የልጅነት ዘመን ውስጥ ሁለት ክስተቶች አይረሴ ናቸው። አንደኛው የአስር ሺህ ብር የሎተሪ እጣ አሸናፊ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአባቱን ላንድሮቨር መኪና አስነስቶ ሲያሽከረክር የደረሰበት የመኪና አደጋ ነው። በዚህ አደጋ ዋለልኝ ጉዳት ቢደርስበትም ሞትን አምልጦታል።

ከደሴ ወደ አዲስ አበባ በሚመጣበት በወቅቱ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ይተዳደር በነበረው ልዑል በዕደማርያም ትምህርት ቤት የ 12ኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀው ዋለልኝ፣ ቀጥሎ ያቀናው ወደ ቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርስቲ ነበር። በልዑል በዕደማሪያም ቆይታው በስነጽሁፍና በክርክር ችሎታው ስመጥር ነበር። በተለይም በክርክር ክበቡ ውስጥ በሚያደርጋቸው ክርክሮች የሥነ-አመክንዮ (logic) ችሎታው የሚደነቅ እንደነበር በወቀቱ የሚያውቁት ምስክር ናቸው።

ዋለልኝ ዛሬ በህይወት ኖሮ ስለማንነቱ እና ስለ ፍልስፍናው ከአንደበቱ ለመስማት ባንታደልም ትቶልን ካለፋቸው የብዕር ውጤቶቹ ውስጥ ዋለልኝን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለማየት ይቻለናል። ሕዳር 18 ቀን 1961 ዓ.ም በወጣው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ለብሔራዊ አገልግሎት ጅማ ይገኝ የነበረው ዋለልኝ መኮንን ጋዜጣው ያዘጋጅ የነበረውን “የምርጥ ጽሁፍ ዝግጅት” ማሸነፉን እንዲህ ሲል ይገልጻል።

አሁንም ውድድሩን የዩኒቨርስቲው ተማሪ አሸነፈ

<<የአዚናራ እስረኛ>> በሚል አርአስት ለተሰጠው የምርጥ ጽሑፍ

ውድድር ለ፪ኛ ጊዜ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ወጣት አሸንፏል። በዚሁ ውድድር በዳኞች ነጥብ የ፩ኝነት ያገኘው ዋለልኝ መኮንን፤ በብሔራዊ አገልግሎት በጂማ ከተማ እንደሚገኝ በአድራሻው ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዳኞቹ በሥነ ጽሑፍ ዝንባሌያቸው ከውጪ የተመረጡ ናቸው፡፡ ነጥብ ከመስጠታቸው በፊት የተወዳዳሪው ስም አይገለጥላቸውም፡፡ ሼልማት የሌለውን ነገር ግን የዛሬ ሳምንት የሚገለጠውን የ ፪ኛነት ማዕረግ ያገኘው እንደዚሁ ተማሪ ጌታቸው በቀለ ነው፡፡

ዋለልኝ መኮንን፤ የመጽሐፉ ሽልማት፡ጅማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በኩል ሰሞኑን ይላከለታል። ኛው ዙር ውድድር -የሲራራው ነጋዴ» በሚል አርእስት ነው፡፡ እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ልብ ወለድ ሆኖ ከ፩ ሺህ ቃላት መብለጥ የለበትም፡፡

(የምርጥ ጽሑፍ ዝግጅት)

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ኅዳር ፲፰ ፲፱፻፷፩

ዋለልኝ የሞቱን ጽዋ ከመጎንጨቱ ከ 18 ሰዓታት በፊት ተገናኝተን ነበር። ማታ ነው፣ አራት ኪሎ ከአንድ ሆቴል ደጃፍ ላይ። እኔና ጓደኛዬ ተስፋዬ ዮሐንስ ወደ ሆቴሉ ስንገባ፣ ዋለልኝ ከሆቴሉ ሲወጣ በር ላይ ተገጣጠምን። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ጓደኛዬ ተስፋዬ ለዋለልኝ ከዶ/ር ንጉሤ አየለ የተላከ መልዕክት አደረሰው። ዋለልኝ በወቅቱ በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ ስለነበር የጀመረውን ቴሲስ እንዲያጠናቅቅ ነበር የፕሮፌሰሩ መልዕክት….”ባክህ ዝጋ በለው” ነበር የዋለልኝ መልስ። በጊዜው ዋለልኝ ትምህርቱን አቋርጦ ከነ ገብሩ መርሻ ጋር አውራ ጎዳና ተቀጥሮ ይሰራ ነበር። ዋለልኝ ለመምህሩ መልዕክት ባክህ ዝጋ በለው የሚለውን መልስ ከመለሰ በኋላ የመስሪያ ቤቱን ቀይ ሬንውልት መኪና አስነስቶ ተፈተለከ። በኋላ እንደተረዳሁት እንደዛ ተፈትልኮ የሄደው የአውሮፕላን ጠላፊ ጓዶቹን ለማይቀረው ተልዕኮ ለማዘጋጀት ነበር። (ይህ ማስታወሻ ከዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጣጥፍ የተወሰደ ነው።)

➠ ጥቂት ዓመታት ወደኋላ

አጼ ኃይለሥላሴ የተማሪውን ንቅናቄ በተመለከተ አንድ ንግግር አድርገው ነበር። ንግግሩ አዋጅ የሚል አርዕስት ነበረው። ለኝህ ከሰማይ ለከበዱ ንጉሥ ንግግር መልስ ያልተጠበቀ አንድ ጽሁፍ ተበተነ። የአዋጁ አዋጅ ይላል ጽሁፉ፣ ጽሁፉ የንጉሡን ክብር የሚነካና እጅግ ድፍረት የተሞላበት ነበር። የጸሀፊውን ማንነት ለመለየት የንጉሡ ደህንነቶች አወጡ አወረዱ ግን ሊደርሱበት አልቻሉም። ጃንሆይ ግን ለዩት……ከጽሁፉ መካከል የሚከተለው አረፍተ ነገር ይገኝበታል።

“የታህሣሥ ደም ቢያቃዦት የለቀቁትን ቤተ-መንግሥት ስለሰጡ “ነደሞት” ወይ?”

በዚህ ዓረፍተነገር ውስጥ ያለችው “ነደሞት” የምትለው ቃል ጸሀፊው ወሎዬ ለመሆኑ የምትጠቁም ነበረች። በዚህም ምክንያት የዋለልኝ ስም ጥቁር መዝገብ ላይ ሰፍሮ በደህንነቱ ክትትል ስር ነበር።

➠ ያልተሳካው የአውሮፕላን ጠለፋ

ህዳር 29 ቀን 1965 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መስመር ቁጥር 730 ቦይንግ አውሮፕላን 94 መንገደኞችንና 9 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ከጥዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል በአስመራ በኩል ወደ አቴንስ፣ ሮም ከዛም ወደ ፓሪስ ለመብረር ዝግጅቱን አጠናቆ በካፒቴን ቀጸላ አማካኝነት ምድርን ለቀቀ። ከተሳፋሪዎቹ መካከል ሰባቱ እቅዳቸው አውሮፕላኑ ወደሚበርበት አቴንስ ፣ሮም፣ወይም ፓሪስ መጓዝ አልነበረም። ሰባቱ፦

1 .ዋለልኝ መኮንን

2. ማርታ መብራቱ

3. አማኑኤል ዮሐንስ

4. ጌታቸው ሀብቴ

5. ታደለች ኪዳነማሪያም

6. ዮሐንስ ፍቃዱ

7. ተስፋዬ ቢረጋ

የሰባቱ ዓላማ አውሮፕላኑን ጠልፈው ወደ አልጄሪያ በማቅናት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መንገድ አውሮፕላን ጠልፈው ከወጡት እነ ብረሀነመስቀል ረዳን ከመሳሰሉ ጓዶቻቸው ጋር በኢህአፓ መስራች ጉባኤ ላይ መገኘት ነበር።

መልከ-መልካሟ ማርታ መብራቱ ኮልት 38 ካሊበር ሽጉጥ በላስቲክ ጠቅልላ በጭኗ መካከል በገመድ አስራ ይዛ ገብታለች። አማኑኤል ዮሐንስ ቦምብ ይዟል። የተቀሩትም እንዲሁ በተለያየ መንገድ ሽጉጥ ታጥቀው ነበር አውሮፕላን ውስጥ የገቡት። አውሮፕላኑ ለ13 ደቂቃ ያክል ከበረረ በኋላ…

የሚቀጥለው ጽሁፍ በወቅቱ በአውሮፕላን ውስጥ ተሳፍረው ከነበሩት የአይን እማኝ አቶ አሰፋ አደፍርስ ለጋዜጠኛ ደረጄ ኃይሌ ከሰጡት ቃለ-ምልልስ የተወሰደ ነው።

አውሮፕላኑ ለ 13 ደቂቃ ያክል ከበረረ በኋላ ዋለልኝ ከተቀመጠበት ተነስቶ ወደፊት መጓዝ ጀመረ፣ በእጁ 38 ስፔሻል ሽጉጥ ይዟል። ከተሳፋሪዎቹ አንዱ የነበሩት አቶ አሰፋ አደፍርስ ላይ ዋለልኝ ሽጉጡን በመደቀን the aircraft is hijacked handsup! አላቸው። በወቅቱ ዋለልኝ አቶ አሰፋ anti-hijacker ነበር የመሰሉት። በሁለቱ መካከል በተፈጠረው ግብግብ የመጀመሪያዋ ጥይት ጮኸች። ግብግቡ ተጀመረ….ዋለልኝ በአንቲ-ሃይጃከር በካራቴ ተመቶ ወደቀ፣ ታደለችም ዋለልኝን ለማገዝ ስትሞክር ኃይሉ (anti-hijacker?) በቃሪያ ጥፊ መቶ ጣላት። በዚህ ጊዜ ነበር ማርታ መብራቱ ኮልት ሽጉጧን ይዛ ከኋላ ወንበር የተንቀሳቀሰችው፣ ዒላማዋ ደግሞ ከanti-hijacker አንዱ መቶ አለቃ ተስፋዬ አረሩ ነበር። ይህን የተመለከተው ኃይሉ ማርታን በመሳሪያ መቶ ጣላት፣ ማርታ ላትመለስ ለዘላለሙ አሸለበች። ትንቅንቁ ቀጥሏል……ዮሐንስ የቦንቡን ፒን ስቦታል፣ እጁ ግን ይንቀጠቀጥ ስለነበር የያዘው ቦንብ ከእጁ አመለጠውና ፈነዳ። በፍንዳታው ሰዎች ቆሰሉ። አሁን ከሰባቱ አውሮፕላን ጠላፊዎች ስድስቱ ሞተዋል፣ ታደለች ኪዳነማሪያም ብቻ ቆስላ ተርፋለች። ይህ ሁሉ በሁለትና ሶስት ደቂቃ እድሜ ውስጥ የተፈጸመ ነው። ይህን ሁሉ ያስተናገደው አውሮፕላን ተመልሶ 2:55 ሰዓት ላይ ተመልሶ አዲስ አበባ አረፏል።

#ታሪክን_ወደኋላ
# ዘ-ሐበሻ
Go toTop

Don't Miss

GXQtoP XcAA8RvI

ንጉሰ ነገስቱ ከስልጣናቸው እንዲወርዱ የተቋቋመው የደርግ አባላት በቀረበው ትዕዛዝ በሻለቃ ደበላ ዲንሳ የተነበበላቸው ደብዳቤ

መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ከ 48 ዓመት በፊት ልክ
ዋለልኝ መኮንን

ዋለልኝ መኮንን ዳግም ሞቷል! – ሙሉዓለም ገ/ መድህን

“ዋለልኝ መኮንን” የሚለው ሥም በኢትዮጵያ (የቅርቡ) የሃምሳ ዐመት ፖለቲካዊ ትርክት