”የጥሞና ግዜ—” ፊልጶስ

በአንድ ወቅት በጦቢያን መጽሄት ላይ የተጻፈ  መጣጥፍ ፤  ” ወዴየት እየሄድን ነው?”  በሚል ርዕስ፤  በጸጋየ ገ/መድህን አረያ  ነበር።  መጣጥፋን ካነበብኩ በኋላ፤ ”እኒህ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ  አሁን በሕይወት ቢኖሩስ ምን ብለው ይጽፉ ይሆን?”’ ስል አሰብኩ።

በአቶ ጸጋየ መጣጥፍ ውስጥ አንዲት በግምት የሁለት ወይም ሶስት  ዓመት ዕድሜ ያላት የልጅ ምስል አለ። ልጅቱ ምን አልባትም የእናቷን ቀሚስና ጫማ ለብሳ ለመራመድ ትታገላለች።ጫማዋንም ሆነ ቀሚሱ መሸከም እንዳቃታት፤ ነገር ግን ወደፊት  ለመራመድ እየመከረች  መሆኗን መገመት ይቻላል። ከልጅቱ ምስል ጎን ደግሞ እንዲህ የሚል ጹሁፍ አለ፤  ”እየሄድኩ ነው፤ ግን ወዴት እንደምሄድ አላውቅም።”

በ’ርግጥም የተፈጥሮ ህግና ውህደት ነውና  እኛም ”እየሄድን ነው”  ግን ወዴት እየሄድን ነው?   ይህ ጥያቄ ምን አልባትም የሁላችንም የኢትዮጵያዊያን ጥያቄ ይመስለኛል። ”አሁን ካለንበት የባሰስ ወዴት ልንሄድ እንችላለን?” ሊባል ይችላል። በርግጥ ”የባሰ አታምጣ” ማለት አይከፋም እንጂ፤ ከወያኔ የባሰ አገዛዝ ይመጣል ብሎ ያሰበ አለ ወይ?

– ጠ/ሚ አብይ አህመድ በገዥው ፓርቲ፤  በእነሱ አጠራር በበልጽግና አንደኛ  መደበኛ ስብሰባ ራሳቸው አስመራጭና ተመራጭ ሆነው የተሰየሙበትንና  ፍጹም አምባገነናዊ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የኦሮሚያው ገዥ ከዓመታት በፊት ”ብልጽግናን ለእኛ ለኦሮሙማ እንዲያመቸን አድርገን ሰርተነዋል።” ያሉት በተግባር ስናይ፤ ብሎም የችግራችን መሰረቱ የሚመነጨው ከህግ- መንግሥቱ  መሆኑ ለዘመናት እንዳልተነገረና ለማሻሻል ወይም ለመቀየር ቃል እንዳልተገባ ሁሉ፤  ዛሬ  ”አፍንጫችሁን ላሱ” ስንባል፤  በርግጥ ወዴት እየሄድን ይሆን?

– የሃይማኖት አባት የተባሉት ጳጳስ  ለዓመታት በኢትዮጵያዊያን ላይ ሲፈጸም የነበረውና እየተፈጸመ ያለው ግድያና የዘር ማጽዳት ሳያሳስባቸው ፤ ህገ-ወጥ ጳጳስ መሆናቸው ሳይበቃ፤ ዛሬ ብድግ  ብለው ዘውጋቸውን መዘው ፤ የሿሚያቸው ”ቃለ-አቀባይ” ሆነው ፤ ሃይማኖቷ ያለችበትን ሃቅ ሲነግሩን፤ መንፈሳዊነት ወዴት እየሄደ ይሆን?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ባዶ ቤት በቁንጫ ይወረራል! - አገሬ አዲስ   

– የአስራ ሁለተኛ ብሔራዊ ፈተና ውጤት ”ራያና ቆቦ” ሆኖ ፤ ከተርኞች መንደር የተገኙትን  ወደ ከፍተኛ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ሲያደርግና፤  ሌላውን ተፈታኝ ዜጋ፤  ፈተናውን  በትክክል ማረምና ውጤቱን ማስተካከል ቀርቶ፤ ጾታየ ተሳስቷላ አስተካክሉልኝ ላለ ተማሪ እንኳን ” ወጤትሽን/ህን አጣርተናል። ነገር ገን ቀድም ሲል ከተገለጸው ውጤት ለውጥ የለውም።” ብሎ መልስ የሚሰጥ የትምህርት ሚኒስተር ስናይ፤ ይህ ትውልድ ወዴት እየሄደ ይሆን?

– የአዲስ አበባ ወጣቶች ለምን የአድዋንና የካራ ማራን የድል ቀን አከበራችሁ ተብለው  እየታፈሱ ወደ ማጎሪያ መወርወራቸውን  ሳይበቃ በመጸዳጃ ክፍል ውስጥ  ሲታሰሩና፤  የኦሮሚያዊ መሪ  አዲስ አበባን የኦሮሙማ  የማድረጉ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑኑ ሲያረዱን፤

– ወያኔ ሁለተኛ ዙሩን የወረራ ጦርነት ለማካሄድ ዱብ- ዱብ እያለ እያማሟቀና በጎንደር፣ በወሎና በአፋር የያዘወን ግዛት እያጠናከረ መሆኑን ስንመለከትና፤ ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ”የተናጠል የተኩስ አቁም አድርገናል።” ተብሎ ሲነገረን፤ በ”ርግጥ የወያኔና የኦሮሙማ ግንኙነት ወዴት እየሄደ ይሆን?

– ኦነግ- ሸኔ  ከደፈጣ ተውጊነት ወደ መደበኛ ጦር ማደጉንና ወረዳዎችን ተቆጣጥሮ   የዘር ማጽዳቱን ሥራ ከአለፈው በበለጠ ለመፈጸም ጥንካሪውን ሲያሳይና  በቤተ-መንግሥት እየተዘወረ ከዚህ ደረጃ መድረሱን የራሳቸው ሰዎች ሲነግሩን፤ በርግጥስ  ወዴት እየሄድን ይሆን?

– የሰሜኑና የአፋር ህዝብ  ከቀየውና ከመኖሪያው መፈናቀሉ ሳያንሰው፡ የእለት ጉርስ  እጥቶ በርሃብ አለጋ እየተገረፈ ህጻናት መሞታቸውን እየሰማን፤ እንዲሁም  በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ያለው ወገናቸን በጠኔ እያለቀ፤ ገዥዎቻችን ደግሞ በድግስ ብዛት ዕረፍት አጥተው፤ ” ህዝብ ‘ራቡን ሲችለው ፤ ገዥዎቻችን ጥጋቡን አልችለው ሲሉ።” ወዴት እየሂድን ይሆን?

‘’ብሶት፡ ለቅሶና የየየ! ‘’ በሁሉም የጎሳ መንደር ይሰማል። ጨቋኙ ከተጨቋኙ የበለጠ የብሶትና አገር የማተራመስ ከበሮ ይደልቃል። ሁሉም በሚባል ደረጃ የጋራ አገርና የጋራ ማንነት፤ ወደደም ጠላም በጋራ እየኖረ መሆኑ ዘንግቷል። ከፊሉ አዲስ አገር ለመፍጠር በህዝብ ደም ይነግዳል። ከፊሉ  በመንደር ተቧድኖ ይቧቀሳል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ - ብታደርግ የተወገዘች፣ባታደርግም ውጉዝ ነችና ቀበቶዋን ታጥብቅ!

ሁሉም ተበዳይ ሆኗል። ሁሉም ተጨቅኝ ሆኗል። ሁሉም የጎሳው ተቆርቋሮ ሆኗል። ሁሉም ገዳይ ሆኗል። ሁሉም ተገዳይ ሁኗል። ሁሉም ተናጋሪ ነው። እደማጭ ግን የለም።  ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውሉ በጠፋ መንደርተኝነትና ትርምስ ውስጥ ህዝብ  በአገሩ፤ አገር አልባና  መንግስት አልባ ሆኖ የምድርን ፍዳ ሁሉ ይከፍላል።

===—- ተበደልኩኝ ባዩ፣ ሎሌ – አዳሪው በዝቶ
የችግራችንም፣ .ውል – ማሰሪያው ጠፍቶ፤

አሳሪው – ሲታሰር

ታሳሪው – ሲያስር፤
የሄደው – ሲመጣ፣ የመጣው – ሲሄድ
መውጫና  መውረጃው፣ ሆኖ የአገር መንገድ፤
ብዘራው አይበቅል፣ ቢበቅል አያፈራ
መጠላለፍ ሆኖ፣ ቀረ የ’ኛ ሥራ።——

ፓለቲከኛና ተቆርቋሪ ነኝ  የሚል፤  የጎሳውን ሆነ የኢትዮጵያን ስም እየጠራ፤ የሚታየውና የሚያልመው  ነገር ቢኖር፤ በኢትዮጵያ ህዝብ የሬሳ ከምር ላይ ተረማምዶ፤ ከቻለ ባለሥልጣን ካለያም  ከጦርነትና ከመከራ የተረፈውን ደሃ  ከእፋ ነጥቆ  ለመጉረስ ነው።

ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ፤  ከስሜን እስከ ደቡብ ፤ ከመሃል እስከ ዳር፤  የሰው ልጅ  በጦርነት እየተገረፈ፣ በድርቅ እየተመታና  በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ  ባለበት ሰዓት ፤   ባለፈው የሄድንበት ከዚህ አድርሶን፤ አሁንም  ሁሉም በየጎጡ መሽጎ፤ የጦርነት ነርጋሪት እየጎሰመ ፤   ህግና- ሥርዓት የሚፈጸመው በደካሞች ላይ ብቻ ሆኖ ስናይ፤” ወዴት እየሄድን ይሆን ?” ብሎ፤ ቆም ተብሎ የሚታስብበት  ከትላንት ወዲያ ነበር፤  አላደርግነውም። ትላንት ነበር፤ አላደረግነው። ዛሬስ??

ጊኒያዊያን ”ቅርጫት ሙሉ እንቁላል ተሸክመህ አትጨፍር ።” ይላሉ። ከአሁን በኋላ  በያዝነው መቀጠል ከማንችልበት ደረጃ  ድረሰናልና  ”ቅርጫት ሙሉ እንቁላል ተሸክመን እየጨፈርን’’  መሆናችን ለሁላችንም  ፤ ዛሬ እንኳን  በቃ ሊባል  ይገባል።

በእውነት በኛ ዘመን ያልተፈጸመ፣ የሴራ፣  የክፋትና የጭካኔ ዓይነት የለም።  ከዚህ በተቃራኒ ያለው  ሰላም፣ አንድነትና ሥልጣኔ ግን ”ርግማን እንበለው ኋላ ቀርነትና ድንቁርና ፤ እንደ ጥላ ስንቀርበው እየራቀን  በደምና በአጥንት የተግንባን አገርና ህዝብ  ለማፍረስ ከዚህ ደረጃ ደርሰናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ብሔራዊ ምርጫን የማካሄድ ሥልጣንና ሕገ መንግሥቱ (ለውይይት መነሻ) ባይሳ ዋቅ-ወያ

የሚሰማም ሆነ ወደ ልቦነው የሚመለስ ካለ፤  አሁን የቀረንና ያልሞከርነው ነገር ቢኖር፤ ነገር ግን በእጃችን ያለ፣ አሁኑኑ ቃል ገብተን ልናደርገ የሚገባን ነገር ቢኖር፤ ለሁላችንም ”የጥሞና ግዜ” መውሰድ ነው።

ለዚህ ምሳሌ የቢልጀሟ ከተማ በሆነችው ቪልቮርድ  የሚገኘው የፍርድ ቤት ውሳኔ ነው።  በአጭሩ   ቪልቮርድ ከተማ የፉላኒ ደችና የፈረሳይ ተናጋሪዎች የሚኖሩባት ከተማ ነች። ይሁን እንጅ  ከተማውን ለማስተዳደርና ለማዕከላዊ መንግሥት በሚደረገው  ውክልና የደችና የፈረንሳይ ቋንቋ ተናጋሪዎች ለዘመናት መግባባት አቅቷቸው፤ ሁሌ  ‘’በሰለጠነ’’ መንገድ እንደተናቆሩ  ይኖሩ ነበር። በዚህም ምክንያት  የአገሪቱ ማዕከላዊ መንግስትም  ችግሩን ሊፈተው ባለመቻሉ መጨራሻ ወደ ፍርድ ቤት ሂዱ። ፍርድ ቤቱ ለዘመናት የቆየውን የውክልና አለመግባባት፤  ዓመታት ዶሴ ክፍቶ ሲያከረከር ኖረ። በመጨረሻ ግን ፍርድ ቤቱ ያለፈውንም ታሪክና አሁን ያለውን ትውልድ  ከመጭው ትውልድ ጋር  ሊኖረው ስለሚችለው አንድምታ   ካጠናና ካገናዘበ በኋላ የሰጠው ብያኔ፤  ”  የቪልቮርድ የፍርድ ጉዳይ እንዲቆምና፤ ዶሴው ለአስር ዓመት እንዲዘጋ ወስኖ፣  ለሁለቱም ወገኖች የአሥር ዓመት የጥሞና ዘመን በመስጠት፤ ተሟጋቾቹን አሰናበታቸው።

እኛስ —–መንግሥት ለወያኔ ብቻ  የሚሰጠውን የጥሞና ግዜ ለራሱም ሆነ  የሚመለከተው ሁሉ እንዲወስድ ያደርግ። ጥሞናው ለሁላችንም ያስፈልገናልና። ቅንነቱ ካለ የሚገድ ነገር የለምና፤  ለአገራችንም ሆነ ለወገናችን ” የጥሞና ግዜ” እንውሰድና” ፤ ለመወያየትም ሆነ ለመደማማጥ፤ ራስንም ለመጠይቅ ሆነ ለመጠየቅ፤ ለዛሬውም ሆነ ለመጭው ዘመን ተስፋ እናድርግ፤ ሰላምን እንዝራ። ቅድሱ መጸሃፍም ”–ሰላም ወዳድ ሰዎች፤ ሰላምን ዘርተው የጽድቅን ፍሬ ይሰበስባሉ።—” ይላልና።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!

—–//—-ፊልጶስ

መጋቢት-2014

E-mail: philiposmw@gmail.com

 

4 Comments

  1. ታላቋ ብርታኒያ የምትባለው ከተለያዪ አካባቢዎች ባሉ ሃገራት የተሰፋች ምድር ናት። ጣሊያን በመከራ ፍትጊያ አንድ የሆነች ሃገር ነች። ኸረ ስንቱ ይወራ የዓለማችን ታሪክ። ጉልበተኛና ጦር ሰባቂ ሌላውን አስገብሮ ያልኖረበት የምድር ጫፍ የለም። ዛሬ በአርጀንቲና ከአንደኛውና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተርፈው በተሻገሩ ጣሊያኖችና ጀርመኖች የተሞላች ሃገር ለመሆኗ አሊ አይባልም። በአሜሪካ የዚያውን ሃገር ነባር ህንዶች ገደል እየከተቱና እያሳደድ ከአውሮፓ እየተጠራሩ ቤት ሰርተው ትውልድ ያስቆጠሩ ሚሊዪኖች ናቸው። ፍትህ በምድር ላይ ኑሮ አያውቅም። ጀርመኖች ያላቸው ምድር አልበቃቸው ብሎ ከ 13 በላይ የአፍሪቃ ሃገሮችን በቅኝ ለማስተዳደር ሞክረው ያው በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሳቢያ ተቀምተው ለሌላው ነጭ ቅኝ ገዢ በጊዜው እንደሺያ ሃገሮች ታድለው ነበር። የጥቁር ህዝቦች መከራ መንስኤ ከሥር ጀምሮ ለተመለከተው ይበልጡ ራሳችን የምናፈልቀው እሳት ነው። ለዚህም ሩቅ ሳንሄድ በ 20 ውና አሁን ባለንበት ጊዜ የሆነውንና የሚሆነውን ማየት ያስፈልጋል። በአጭሩ የሃበሻ ሃገር መንግስታዊ ለውጥ ማለት የጠገበን አውርዶ የተራበንና ተረኛን በሥፍራው ማስቀመጥ ማለት ነው። ከላይ በጽሁፉ ላይ በዝርዝር የተገለጡት የከፍተኛ ትምህርት ውጤቱ መማታት፤ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ነን የሚሉ የመቶ ዓመት ሽማግሌ መግደል፤ በየስፍራው ሰውን ማፈናቀል፤ ዘረፋ ሁሉ ሆን ተብሎ የሚፈጸም የፓለቲካ ስልት እንጂ በነሲብ የሚሆን አይደለም። በዚህ ላይ ከሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎ ኦሮሚያ ክልል ሂደው እንዳይሰሩ፤ እንዳይማሩ የሚደረገውም ከዚሁ ሴራ ጋር በተገመደ ስብጥር ነው። የትግራዪ ግርግርና ጦርነት የጎዳው የትግራይንና የአማራን እንዲሁም የአፋር ወገኖቻችን በመሆኑ የኦሮሞ ጽንፈኞች ደስታቸው የትዬ ለሌ ነው። እኛ ስንቧቀስ እነርሱ ከፍታ ላይ እየወጡ፤ የሴራቸውን ስልት እያረቀቁ ኢትዪጵያን እያፈረሱ “ኢትዮጵያ አትፈርስም” እያሉ በአደባባይ ሲደነፉ ማየት ያሻጥራቸውን ጥልቀትና ዝቅጠት አጉልቶ ያሳያል።
    የትግራዪ ወስላታ ድርጅት ወያኔ ሃርነት (ባርነት) ትግራይ በዚህ ሁሉ ዘመኑ እንዴት ይህ እንደማይታየውና እንደ አበደ ውሻ አብይ ከስልጣን እስኪወርድ እንፋለማለን እያሉ ሲደነፉ መስማት ይዘገንናል። የሰው ልጅ እይታውንና የአስተሳሰብ ስልቱን ሳይሞርድ በደንበር ገተር የሚኖረው እስከ መቼ ነው? አሁን ማን ይሙት አቶ ጌታቸው ረዳ የወያኔ አፈ ቀላጤ ነው? አፉን ሲከፍት ሁልጊዜ የሚናገረው በፊት የተናገረውን ተጻራሪ፤ ተደጋጋሚ (አብይና ኢሳይያስ) ጀግኖች የትግራይ ተዋጊዎች ይህን ሰርተው ያን አርገው ይለናል። አያሳዝንም። ልብ ያለው እብደታችን ይብቃ መንገዳችን እንቀይር ብሎ አያስብም? ግን አልኮልና ሌላው እጽ ያደነዘዘው ጭንቅላት የዛሬን እንጂ የነገን አያይምና ይደነፋል። በቅርቡ ባወጣው ጽሁፍ የትግራይን ጉዳይ ከዪክሬኑ ፍልሚያ ጋር አነጻጽሮ እኛንም እርድን ሲል እጅግ ተገረምኩ። በቅድሚያ አንተ ጥቁር ነህ። እንድንጫረስ ይፈልጋሉ። በሁለተኛ ደረጃ የትግራይን ችግርና የዪክሬንን ፍትጊያ የሚያገናኘው ነገር የለም። በእርግጥ በፑተንና በወያኔ መሪዎች መካከል የጦር ስልትና ጭካኒያቸው ይመሳሰላል። ከዚህ ውጭ የተባበሩት መድረክ ላይ ወጥተህ ኡ ኡ ብትል ለጥቁር ህዝብ የሚገደው አንድም ነጭ የለም። የወሬ ማሟያ ግን ያደርጉናል። ተመራመርን በቦታው ሄደን አጠናን ብለውም መጽሃፍ ይጽፉብናል። ግን ይህ ሁሉ ከራሳቸው ጥቅም አንጻር እንጂ ለትግራይ ህዝብ አስበው አይደለም።
    ለትግራይ ተሰጠ የተባለው የጥሞና ጊዜ ጦሩ ጥሎ የፈረጠጠበት እንደነበር በጊዜው ጽፈናል። ግን የሚያሳዝነው ሽዋ ድረስ ወያኔ ገብቶ ያደረሰው በደልና ግፍ ተረስቶ አሁን የትግራይ ወራሪ ሃይል፤ ጅንታው እየተባሉ ሲጠሩ የነበሩት ወያኔዎች ግፋቸው ሁሉ ተዘንግቶ የመንግስትም ሆነ የግል ሚዲያዎች በድብስብስ ሌላ ሃሳብና ስም እየሰጡ ሲያልፉት አስተውለናል። ይህ ለባለወረፋው “የብልጽግና – የድህነት” ፓርቲ ይጠቅም እንደሆነ እንጂ የወያኔን ክፋት ህዝባችን ጠንቅቆ ያውቀዋል። ይህን ብልጽግና ነኝ የሚለውን ድርጅት አምስት አመት ጠብቆ በምርጫ ከወንበሩ ላይ ማሽቀንጠር አስፈላጊ ይመስለኛል። ግን ያ ይሆን ይሆን? በተማሪዎች የፈተና ውጤት ያልታመነ መንግስት በምርጫ ኮሮጆ ይታመናል? እናንተ ዛሬ ላይ በዘራችሁ ተሰልፋችሁ ጮቤ የምትረግጡ ተረኞችና ነፍሰ ገዳዪች ዳንኪራ ምቱ። ድሃውና በዘርና በቋንቋው ወይም በሃይማኖቱ የሚሞተው ይሙት። እንደ ጳጳሱ ያሉት መርጦ አልቃሾችም ዘር እየመረጡ ምሾ ያውርድ። ጊዜው ግን ሩቅ አይደለም። የምንሄድበት መንገድ ካልተስተካከለ ሁላችንም አይነ ስውሮችና መሪ አልባ እንደምንሆን ማወቅ አለብን። አንድ አሁን በህይወት የሌለ አሜሪካዊ ኮሜዲያን በዘመኑ ፍጻሜ ላይ ባስተላለፈው የጽሁፍ መልዕክት መደምደሚያ ያለውን ላካፍላችሁና እኔም ይብቃኝ። ” Life is not measured by the number of breathes we take, but by the moments that take our breath away.” What takes your breath away? Chasing your brother and sisters so you can hack them to death? Or is it the pursuit of money and fame that makes you short of breath? Remember, all this is all vanity, and your days are a fleeting shadow. Find your mission in life, and be a human to serve humankind. The rest of the your endeavor is a heap of refuse. በቃኝ!

  2. ከአንድ የጎንደር ዲያቆን የሰማሁትን ላካፍል። ጊዜው ከወራት በፊት አብይ በታረክ ያልታየ “ያን ማዶ ተራራ ነገ እይዘዋለሁ” እያለ ለጠላትም ለወዳጅም በቀጥታ TV በሚያስተላልፍበት ያስወረረውን ነፃ እያወጣ የራሱን የጀግንነት ታሪክ ሊፅፈ የቋመጠበት ህዝቡ ደግሞ በመሪው ጀብዱ የተደመመበት ወቅት ነበረ። ዲያቆኑ ” ይህ ችግራችንን አይፈታም። ከፈታም 1%ቱን ነው። 99%ቱ ችግራችን ኢትዮጵያ ከአምላኳ ተጣልታለች። ጉልበት አግኝተን ወሻውን ብናባርር ጅብ ይመጣል: ጀቡን ስናባርር አንበሳ የመጣል: አንበሳውን ስናባርር ደግሞ ሰይጣን የመጣል። እና መፍትሔው ነስሀ መግባትና ወደ ልባችን መመለስ ነው።” አለ። ያለፈው ጀኔራል አሳምነው እንደተናገረው አሁን የገጠመን ከ500 አመት በፊት እንደነበረው ነው። ያኔ ግራኝን ሲያስወጡ ካቶሊክ አጨፋጨፈ: ካቶሊክን ሲያስወጡ ኦሮሞ መጣ። በኛ ትውልድ ደግሞ ደርግ አጥፍቶ ሄደ: ወያኔ አሁንም ዳር ይዞ እያጠፋን ነው። ብልፅግና ግን ጥፋቱን በጅምላ አድርጎታል። ብልፅግና ጅቡ ይሁን ሠይጣኑ ባላውቅም ጥፋቱ እንዲቆም ኢትዮጵያ ከአምሏኳ እንድትታረቅ ዲያቆኑ ያዘዘውን ለማድረግ እንሞክር። ሌላውም የትግል ስልት አንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።

    • 99% ኢትዮጵያ ከፈጣሪ ተጣልታለች የሚባለው የወስላቶች ወሬ ነው። ለእልፍ ዘመናት የሚበላ ሳይኖር ጽሞናል፤ እግዚኦ ብለናል፤ ሱባኤ ገብተናል፤ ማተብና መስቀላችን በአንገታችን ላይ አንጠልጥለናል። ታሪካችን ግን እንኳን ሊሻለው እየከፋ ይኸው እንሆ አሁን በክልል ተከፋፍለን በየሰበቡ እንገሻለጣለን። ለውጥ የማያመጣ ዋይታ ፍሬ ቢስ ነው። ትርፉ ራስ ምታት ብቻ! ችግሩ የሰው ልጅ ጭንቅላት ነው። ፈጣሪ የምናስብበት ህሊና ሰጥቶን እያለ እንስሳዎች የሆነው እኛው ነን። የሃበሻው ሃጢአት በዛ ለሚሉ ወስላቶች ደግሞ አሜሪካን፤ አውሮፓን፤ የአረቡን ሃገር፤ ህንድንና ሌሎችንም ሃገሮች አይቶ መፍረድ ነው። የእኛው ችግር ለማንኖርበት እምነት መስገድና መጾማችን ነው። ቤ/ክርስቲያን ገብቶ በደሌን ይቅር በለኝ ብሎ ከቤ/ክርስቲያን ቅጥር ውጭ ሲወጣ ደባ የሚሸርብ፤ ዘሩን የሚያሰላ፤ ቡጢ ይዞ ከስሩ ያሉትን ሊጨፈልቅ የሚሻ እቡይ እንዴት ባለ ሂሳብ ነው የእምነት ሰው የሚሆነው? ጭራሽ!
      የዲያቆኑ ሂሳብ በቀመር ያልተሰላ፤ በዘ ልማድ የሚለፈፍ የማያድን ጸበል እንደ መጠጣትና በዚያው ሰበብ የተቅማጥ በሽታን እንደመሸመት ያለ ጅልነት ነው። ሃይማኖት ሰዎች አይናቸውን ገልጠው ራሳቸውንና ጽንፈ ዓለሙን እንዳያዪ በምጽድቅና በልመና ብቻ እንዲኖሩ የሚያደርግ አሳሬ አስተሳሰብ ነው። የክርስቲያን ደሴት፤ የአፍሪቃ የዳቦ ቅርጫት፤ የሶስት ሺህ ዘመን ነጻነት ወዘተ እያሉ ራስን ከማመጻደቅ ይልቅ ቆም ብሎ የክፋትና የመገዳደል ታሪካችን ሳያሰልስ ደካሞችን፤ እናቶችና ህጻናትን፤ አዛውንትን በእሳት፤ በገጀራ፤ በጥይት፤ በቀስት በመግደል በየመንገድና በገደል እንድንወረውር የሚያደርገን ምን ነክቶን ነው ብለን ራሳችን መጠየቅ አለብን። ሰው መሆንህን የምታውቀው የሃይማኖት አሸንክታብ ስላበዛህ አይደለም። ሰው ሆነህ ሰውን በሰውነቱ መደገፍ ስትችል እንጂ። ስለሆነም የእስልምና፤ የክርስቲያኑ (ሁሉም አይነት ክርስቲያን ነኝ ባይን ይጨምራል) መድረክ ላይ ወጥቶ ቁና ቁና ከመለፍለፍ ረጋ ብሎ ለምን እዚህ ክፉ ጊዜ ላይ ደረስን? የወደፊቱስ ምን ብናረግ ይሻለዋል ብሎ በምድር ላይ ያለውን ተጨባጭ ነገር ከራስ ባህሪ ጋር በማገናዘብ በጎ ተግባር ለመፈጸም መታገል እንጂ መልስ በማይሰጥ የሰማይ አምላክ ላይ አንጋጦ የት አለህ ማለቱ ጅልነት ነው። በቃኝ!

  3. Tesfa: አንተ አንድ መንነቱን በደንብ የማታውቀውን አሜሪካዊ በአሜሪካ ቋንቋ ጠቅሰህ አዋቂነትህን አሳይተህ የኛን ችግርም ይፈታል በለህ ታስባለህ። ቢያንስ ከ90% በላይ የሚሆነው የሀገሬ ህዝብ የሚያምንበትን መንፈሳዊነትን: ሀገር በቀል ሊቅን መጥቀስ ግን አንደ ሞኝነት ትቆጥራለህ። ክፋት እንደ በዛ አምነሀል። ህግ የሚባልም አለ። ሰው ህግ ተላልፎ እውቀትን አገኘ። ክፋት ህግ መተላለፍ ነው። ህግ የተላለፈ ደግሞ ይቀጣል። ኢትዮጵያውያን ህጉን ተላልፈናል። ቅጣትም መጣ። ኢትዮጵያውንን ከእንግሊዞች ወይም ከሌላ ማመሳሰል ግን አይሰራም። እስራኤልና ባቢሎንን ማመሳሰል እንደማይቻል። እኔ በበኩሌ ጥፋቱ የእናንተን ትውልድ: አምላክን ትቶ ለኒንን ያመለከውን ትውልድ: ነጭ አምላኪውን ጥራዝ ነጠቅ ትውልድ: ከመንፈሳዊ ይልቅ ቁስ አምላኪውን ትውልድ ለማጥፋት የመጣ ይመስለኛል። ነገር ግን እናንተ በአብዛኛው አሜሪካና እንግሊዝ ነው የምትኖሩት። የግዜ ጉዳይ እንጅ እዜያም ይመጣል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share