ሶቪየት ኅብረት ከናዚ ጀርመን ጭፍጨፋ አስጥላቸው ኔቶ ሥር የተሸጎጡ የባልቲክ አገሮች *ከጎርባቾቭ ውሳኔ መዘዝ፤ – ከጌታቸው ወልዩ (ሜክሲኮ ባህረ-ሰላጤ)

ኔቶ የዩክሬንን ዳቦ ሊበላበት እስከ ተከተለው መንገድ

ጌታቸው ወልዩ

ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደ ምን ሰነበታችሁ? ይህ የዛሬው ጽሑፍ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ በጎርጎሮሳዊኑ ቀመር በ1940 ወደ ራሷ ግዛት የደባለቀቻቸውና ከተገነጣጠለች በኋላ የባልቲክ ሪፑብሊክ አገሮች የሆኑት ሉትዋኒያ፣ ላቲቪያና ኢስቶኒያ ወደ ኔቶ ያደረጉትን ጉዞ የሚየስቃኝ የዳቦ ወግ ነው። (The brade tale of the three Baltic countries)

እናም! በዛሬው ሰፋ ያለ የትንታኔ ጽሑፌ፤ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ስምንተኛውና የመጨረሻው ፕሬዚዳንት የሆኑትና ሚኻኤል ሰርጊዬቪች ጎርባቾቭ ሥልጣን መልቀቅን ተከትሎ በሶቪየት ኅብረት የተከሰቱ እርምጃዎች፤ ከሶቪየት ኅብረት ቅድሚያ የወጡ ሦስቱ የባልካን ሪፑብሊኮች የሶቪየት ኅብረት አደራን በመዘንጋት ወደ ኔቶ የተቀላቀሉባቸውን መንገዶችና ራሷ ሶቪየት ኅብረት በዋናነት ሩሲያ ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አፈንግጠው የወጡ አገሮችን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ጀርመን ወረራ ጊዜ እንዴት ከሒትለር ጨካኝ ሠራዊት መንጋጋ ፈልቅቃ እንዳወጣቻቸውና ኔቶ ዩክሬንን አባል ለማድረግ የፈለገበትን የብልጠት መንገድ “በዳቦ ወግ” አቀራረብ በዝርዝር አቀርብላችኋለሁና ሳትሰለቹ በጥሞና ትከታተሉ ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ። በመጨረሻም ምንም እንኳ ሩሲያ በጦርነቱ የሚያስጠይቋት ጎኖች ያሉ ቢሆንም ይህን ጽሑፍ ተከታትላችሁ ስታበቁ በዩክሬንና ሩሲያ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ትልቁን መንስኤ ልትረዱ ትችላላችሁ ።

ውድ ወገኖቼ:- እንዲህ ሆነላችሁ።በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር 1961 ጀምሮ፤ ምሥራቅ ጀርመንና ምዕራብ ጀርመንን እንደ አገር በአካልና በርዕዮተ-ዓለም ከፋፍሎ የጎሪጥ ያስተያያቸው፤ ትላልቆቹ ከተሞችን ምሥራቅ በርሊንንና ምዕራብ በርሊንን እንደ ባዳ የለያያቸው፤ ተሽከርካሪዎች

እንዳይተላለፉበት ተብሎ የተዘጋጁ ምሽጎችን ጨምሮ ዘመናዊ ካሜራዎች፣ እንደ አልጋ የተጋደሙ መርዘኛ ሽቦዎችና ምላጮችን በመያዙ “የሞት መስመር” (death strip) ለመሰኘት የበቃው የበርሊን ግንብ፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኖቬምበር 9 ቀን 1989 (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥቅምት 29 ቀን 1982 ዓመተ-ምህረት) ፈረሰ፤ ተገረሰሰ።

“በሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም ርዕዮተ-ዓለሞች ጎራ ለይተው የኀያላኖቹን ሶቪየት ኅብረትና ዩናይትድ ስቴትስን ዱካ ይከተሉ የነበሩ የርዕዮተ-ዓለም ወዳጆቻቸው የሆኑ አገሮችን ጨምሮ በርካታ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የጦር ሰዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የስለላና መረጃ ባለሙያዎችና የተለያዩ ወገኖች በበርሊን ግንብ መፍረስ የተነሳ እውነታውን ለማመን ተቸግረው ድንጋጤና ያለመረጋጋት በፈጠረው ሁኔታ ልባቸው ለሁለት አብሮ ተገመሰ።

በመቀጠል በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የዓለም ሕዝቦች፤ ዕይታቸውን የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ (Union of Soviet Socialist Republic) በምኅጻረ-ቃል “ዩ.ኤስ.ኤስ.አር” ስምንተኛውና የመጨረሻው ፕሬዚዳንት ወደ ሆኑትና የሶቪየት ኅብረት ግዛቶች ጥምር -ፕሬዚዲየም ሊቀመንበር ሆነው ወዳገለገሉት ሚኻኤል ሰርጊዬቪች ጎርባቾቭ ላይ አነጣጠሩ፤ አዲስ የታሪክ ክስተት ጅማሬ እንደሚኖር እየጠረጠሩ።

ገና እንደተወለዱ የቀይ ወይን ቀለም መልክ ያለው፤ በተለምዶ “ማርያም የሳመችው!” (St. Mary kiss) ወይም “መላእክ የሳመው!” (an Angel kiss) የሚሰኘው ምልክት አናታቸው ላይ የወጣባቸው፤ “የውልደት ጊዜ ምልክታቸው ከሶቪየት ኅብረት የአገር ካርታ ጋር ይመሳሰላል!” ተብሎ በድፍረት ብዙ ንግርት የተነገረላቸው፤ ፖለቲከኛው ሚኻኤል ሰርጊዬቪች ጎርባቾቭ ፤ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በአጭር ጊዜያት ዓለምን የሚለውጡ ተግባራትን እንደሚፈጽሙ አስታውቀው ነበርና ምዕራባውያኑ ከጎርባቾቭ አፍ ጠብ የምትለዋን ትንሿን ቃል ሁሉ እንደ ባቄላ ፍሬ እየለቀሙና የየዕለት የፖለቲካ ውሳኔዎቻቸውን ከስትራቴጂዎቻቸውና ፖሊሲዎቻቸው ጋር እያነጻጸሩና እያስማሙ ቀን ተቀን ይተነትኑ ገቡ።

“በሃይማኖታዊ መንገድ ትንቢት ተናጋሪ ነን!” ያሉ ነቢያት ነን ባዮች፣ “በልዩ ዕውቀት ነገን የመግለጽ አቅም አለን!” የሚሉት “ሱዝሴየርስ”(soothsayers)፣ ኮከብ ቆጣሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ሳይንስ፣ ዓለምአቀፍ ግንኙነት፣ የሕግ፣ የሥራ አመራር፣ የዲፕሎማሲ፣ የውትድርና፣ የፖሊስ፣ የስለላ፣ የውጊያ መረጃና የተለያዩ የሥራ ዘርፍ ባለሙያዎች በበኩላቸው ፤ “ጎርባቾቭ የተባሉት ፖለቲከኛ ያለ ምክንያት አልመጡምና! ወይ ሶቪየት ኅብረትን አስተካክለው ይመራሉ! አሊያ ሶቪየት ኅብረትን ከዶሮ ብለት በበዛ እንድትገነጣጠል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ!” እያሉ ግምታቸውን ያስቀምጡ ጀመር።

በሥልጣን ዘመናቸው “በሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ እጅግ አስገራሚ ለውጥ ይፈጥራሉ!” ተብሎ የተተነበየላቸው የገናናዋ ሶቪየት ኅብረት ፕሬዚዳንት የነበሩት ሚኻኤል ጎርባቾቭም፤ ቁልፍ የተሰኙ የለውጥ እርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ በጎርጎሮሳዊያኑ ስሌት ዲሴምበር 25 ቀን 1991 (ታኅሣሥ 16 ቀን 1984 ዓመተ-ምህረት) ሥልጣናቸውን ለቀቁና ዓለምን ከጫፍ ጫፍ አነቃነቁት።

“ብዙ ዋጋ ከፍየበታለሁ!” በሚሉት “ፔሬስትሮይካ” በተሰኘው መልሶ የመገንባትና የማዋቀር በአጭር ቃል “ተሃድሶ” መርሐ-ግብራቸውና “ግላስኖስት” ወይም “ግልጽነት” ማለትም “የመናገር የጻነት” በሚሰኙ የለውጥ እርምጃዎች የሚታወቁት ፕሬዚዳንት ሚኻኤል ጎርባቾቭ፤ ሥልጣናቸውን በለቀቁ በማግሥቱ ደግሞ የሶቪየት ኅብረት ግዛቶች ጥምር ምክር ቤት የሆነው “ሱፕሪም ሶቪየት” በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ጥላ ሥር የቆዩ 15 ግዛቶች ሁሉ ነጻነታቸውን አረጋግጠው ራሳቸውን የቻሉ አገሮች እንደሆኑ ይፋ ሲያደርግ፤ ዓለም “የጎርባቾቭ ሥልጣን መልቀቅ ያለምክንያት አልነበረም?!” አለና ከግራሞት አልፎ፤ አዳዲስ አገሮችን ለማየት አሰፈሰፈ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰንሹ የጦርነት ጥበብ ላማራ ሕዝባዊ ግንባር፤ ማጥቃት መከላከል ነው

እናም! ከቀሪዎቹ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ግዛትነት በፍጥነት ተፈናጥረው አገር ከሆኑት መካከል፦ “ሦስቱ የባልቲክ ሪፑብሊኮች” የሚሰኙትና በጎርጎሮሳውያኑ ቀመር ከማርች እስከ ሜይ 1990 ባሉት ወራት ከአሥራ አምስቱ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ግዛቶች ቅድሚያ ነጻነታቸውን ያወጁት ሊትዋኒያ፣ ላትቪያና ኢስቶኒያ፤ የሶቪየት ኅብረት ግዛቶች ጥምር ምክር ቤት የሆነውን “ሱፕሪም ሶቪየት” እያመሰገኑ በምዕራባውያን መም (ትራክ) ላይ ለመንደርደር ሲያቆበቁቡ አሜሪካንን ጨምሮ በአሜሪካ ጋሻ ጃግሬ ወዳጆቿ ምዕራባውያን ከፍተኛ ሙገሳ ቀረበላቸው።

በተለይ “ሊትዋኒያ”፤ ላቲቪያንና ኢስቶኒያን በመቅደም “አንድ ዋነኛ መንገድ ከአንድ መቶ ጠመዝማዛ መተላለፊያዎች ይሻላል!” በማለት አዲስ ዜማ እያቀነቀነችናእየተረተች

የኔቶን ወዳጅነት ትናፍቅ ገባች። አያሌ የምሥራቁ ዓለም ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችም የሉትዋኒያ እርምጃ ጅማሬ ገብቷቸው “ድመት ውስጥ ውስጡን አውሬ ነች!” እያሉ ሉትዋኒያን በነገር ይጎሽሟትና ይሸነቁጧት ጀመር።

በይበልጥም “ለአመታት በሶቪየት ኅብረት (በይበልጥ በሩሲያ) ስትደገፊ ኖረሽ፤ ዛሬ አፈንግጠሽ መውጣትሽ እንደ ምንስ ይበጅሻል? ወደ ምዕራባውያን ጎራ መቀላቀልስ አደራ በሊታ አያስብልሽም ወይ?” የሚሉ ጥያቄዎች ከተለያዩ ወገኖች ለሉትዋኒያ ይቀርቡላት ጀመር። ሉትዋኒያም በዳቦኛ የተረትና ምሳሌ ወጓ፦ “Good start is a half of work. God gave teeth, He will give bread” ስትል በአገሯ በታወቀው ተረትና ምሳሌ መልስ ሰጠች። ትርጉሙም፦ “ጥሩ ጅምር ከሥራ ዕቅድ ግማሹን እንዳከናወኑ ያመላክታል። ጥርስ የሰጠ እግዚአብሔርም፤ ዳቦ ይሰጣል! ” ማለት ነው።

የሉትዋኒያ አባባሎች ሸጋ ቢመስሉም ሉትዋኒያ የኋላ ኋላ “ብሔራዊ ደኅንነቴንና ዋስትናዬን ለማረጋገጥ!?” በሚል ሽፋን እየሄደችበትን ያለውን መንገድ የተመለከቱና በምዕራባውያን ተጠምዝዛ የበላችበትን የሶቪየት ኅብረት (በዋናነት የሩሲያ) ወጨት እንዳትሰብር የሰጉ የምሥራቁ ዓለምም ሆነ በምሥራቅ አውሮፓ የኔቶ መስፋፋትን የማይደግፉ የምዕራቡ ዓለም ፖለቲከኞች፤ ጥርጣሬ ባዘለ መልእክታቸው ለሉትዋኒያ አንድ ትልቅ ነገር በአደራ አሳሰቧት፤ አስታወሷት።

በአደራቸውም:-“በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የናዚ ጀርመን ጦር ሶቪየት ኅብረትን ሲወር በተለይ በጎርጎሮሳዊያኑ ስሌት 1941 ላይ ሊትዋኒያን ሲቆጣጠር ብዙ ሺ ሉትዋኒያውያን መገደላቸውን አስታውሰው፤ በርካታዎቹ ተይዘው በግዞት ወደለየለት ቀዝቃዛው የሳይቤሪያ አካባቢ መጋዛቸውንም ጠቅሰው፤ “ከዚያ የጭንቅ ዘመን ነጻ ያወጣችሽና ከናዚ ውድቀት በኋላ ግንባታሽን አፋጥና አሁን ላለሽበት ምጣኔ ሀብታዊ እድገት መነሻ ሶቪየት ኅብረት (ሩሲያ) ናትና በጭራሽ ውለታዋን እንዳትረሺ!?” የሚል ነበር።

ነገር ግን በባልቲክ ባህር በላቲቪያና ሩሲያ መካከል ያለችው ፤ በማርች 11 ቀን 1990 (መጋቢት 2 ቀን 1982 ዓመተ-ምህረት) ነጻነቷን አውጃ በሴፕቴምበር 1991 ተካሂዶ ከከሸፈው መፈንቅለ-መንግሥት በኋላ ዕውቅና ይገኘችው፤

ነጻ አገር ከሆነች በኋላ 25ሺ512 ካሬ ማይል (65 ሺ 300 ኪሎ ሜትር) የአገር ቆዳ ስፋት የያዘችውና ከፊል ፕሬዚዳንታዊ ሪፑብሊክ የሆነችው ምሥራቅ አውሮፓዊቷ የሉትዋኒያ ሪፑብሊክ፤ “ሁለመናዋን ሸክፋ ወደ ኔቶ ደጃፍ በፍጥነት ሄደች!” በማለት የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት-ሲአይኤ ወርልድ ፋክትቡክ ከጥቂት አመታት በኋላ ገለጸ።

ሉትዋኒያ ቀጠለችናም ይባስ ብላ በማርች 2004 የኔቶ፣ በሜይ 2004 የአውሮፓ ኅብረትና በጃንዋሪ 2015 የዩሮ ዞን ወይም የአውሮፓ ቀጣና አባል አገር ሆነች። እንደተሰጋውም “ሉትዋኒያ የኔቶ አባል አገር ሆና የበላችበትን ወጨት ሰበረች። በድርጊቷም ሩሲያን አስከፋች፤ እንዲሁም አስቆጣች!” አሉ ምሥራቃውያን ዲፕሎማቶች።

በተመሳሳይ ከሉትዋኒያ ቀጥላ በኦውገስት 21 ቀን 1991 (ነሐሴ 15 ቀን 1983 ዓመተ-ምህረት ቀድማ ነጻነቷን ያወጀችው ሚጢጢየዋ ሰሜን ምሥራቃዊቷ አውሮፓዊት አገር “ላቲቪያ” በምዕራባውያን የገመድ ጉተታ ተሸንፋ፤ በኔቶ ፎጣ ታቅፋ፤ በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር 2004 ላይ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን አባል አገር ሆነች። የዚያን ጊዜም የሩሲያ ፌዴሬሽን (ራሽያ)ና “ነጭ ራሽያ” የሚሰኙት ቤላሩሶች በንዴት እሳት ተንቀለቀሉ፤ “ቀንሽን ጠብቂ!” በሚል ዓይነት ስሜት “ለሁሉም ጊዜ አለው!” እያሉ፤ የታላቁን ጠቢብ ጥቅስ ከፍ አድርገው በላቲቪያና ሩሲያ አርያም (ሰማይ) ላይ እየሰቀሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ማነዉ ፈሪዉ ተቀዋሚ ወይስ ህወሃት/ ኢህአደግ?

አንዳንድ ፖለቲከኞችም “ላቲቪያ ቸኮለች። የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ግዛት በነበረችበት ዘመን የበላችውን ዳቦ በፍጥነት ረሳች! የበላችበትን ወጨት በፍጥነት ሰበረች!” እያሉ በነገር ይጎስሟትና ይሸነቁጧት ገቡ። ወዲያውም “ጌታዋን የተማመነች በግ…. ላቷን ውጭ ታሳድራለች!” እንዲሉ ላቲቪያ በማታውቀው ወዳጇ “በኔቶ” እጅጉን የመተማመኗን ነገር በተደጋጋሚ ይነቅፉት ተያያዙት።

ላቲቪያ ግን በዳቦ ተረትና ምሳሌዋ አስታካ እንዲህም አለች። “Once you’ve cut the bread you cannot put it together again.” (አንዴ ዳቦን ከቆረስከው በኋላ እንደገና ልታገናኘው አሊያ ድፍን ልታደርገው አይቻልህም! በቃ! ተመልሼ ከሶቪየት ኅብረት ጋ አብሬ አልቀጥልም! የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን አባል አገሮች ጥምረት ይሻለኛል!” ብላ ሩሲያን በስጋት እያየች፤ አዲስ ፍቅር አናውዟት በኔቶ ብብት ሥር ገብታ ተሸጎጠች።

በወቅቱም በላቲቪያና ሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል ወታደራዊና ፖለቲካዊ ውጥረት የተፈጠረ ቢሆንም ሩሲያ ላቲቪያን “ቀንሽን ጠብቂ!” ብላ ስለተወቻት ለጥቂት ከሩሲያ ጡጫ ተረፈች።

ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ግን አጋጣሚውን ተጠቀመችና በዴላዌር ግዛቷ ከላቲቪያውያን ስደተኞች የተወለዱትን የሥነ-ልሣን ዶክተር አርተርስ ክሪስጃኒስ ካሪንስ ወደ ላቲቪያ አስላከችና በምርጫ እንዲወዳደሩ በማድረግ በጎርጎሮሳዊኑ አመት በ2019 የላቲቪያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ አስደረገች። የሚገርመውና ሩሲያን ያስቆጨው የአሜሪካ ተወላጁ የላቲቪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ካሪንስ ለምርጫ ሲወዳደሩ፤ አምስት ወግ አጥባቂና ለዘብተኛ ፓርቲዎች ጥምረት እንዲፈጥሩ ተደረገ። በዚህ መኻል የአገሪቱ ፓርላማ፣ ምርጫ አስፈጻሚው አካልና የፓርላማ አባላት ጭምር ተባብረው “የአፍቃሪ-ራሽያ ኅብር ፓርቲ” የሚሠኘውን “pro-Russian Harmony Party” ከአምስቱ ፓርቲዎች ጥምረት አገለሉት። ይህን ዘገባም የእንግሊዝ ብሮድ ካስት ኮርፖሬሽን ዜና ወኪል “ቢቢሲ” ከአመታት በኋላ እንኳን ማርች 29 ቀን 2019 (መጋቢት 20 ቀን 2011 ዓመተ-ምህረት) ይፋ ሲያደርገው ሩሲያ እንደገና በላቲቪያ ላይ ጥርሷን ነከሰች።

ላቲቪያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ ጀርመን ገዳይ ጓዶችን (ቡድኖች) አዘጋጅቶ ሰባ (70) ሺ ላቲቪያውያን አይሁዶችን ሲፈጅባት ቀሪዎቹን ዜጎቿን ያተረፈችላት በዋናነት ሩሲያ መሆኗን ላቲቪያ በመዘንጋቷና የአሁኖቹ የእሥራኤል ባለሥልጣናት እንኳ የሩሲያ ውለታ ስለሚያውቁ ጦርነት ውስጥ የገቡትን ሩሲያና ዩክሬን እንሸምግል? እያሉ ይጠይቃሉ በማለት በርካታ ፖለቲከኞች በዘመናችን ሳይቀር ላቲቪያን ማውገዛቸውን ቀጠሉ፤ ከኔቶ ጋ ያላትን ዝምድና እያጣጣሉ።

ሌላው ከሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ግዛትነት ቅድሚያ አፈንግጠው ከወጡት “ሦስቱ የባልቲክ ሪፑብሊኮች” መካከል ከሉትዋኒያና ላቲቪያ የቀጠለችው ኢስቶኒያ በበኩሏ፤ ነጻ ከወጣች በኋላ እንደ ሉትዋኒያና ላቲቪያ ሁሉ በተመሳሳይ የኔቶ ናፋቂነት ጎዳና ላይ በመንደርደሯ፤ በወቀሳ ጅራፍ ትገረፍ ገባች።

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ኢስቶኒያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በናዚ ጀርመን የተፈጸሙባትን ስደትና ግዞት፣ ግፍና በደል፣ እልቂትና ፍጅት (holocaust) የሚያውቁ በርካታ የታሪክ ምሁራን፣ ወታደራዊ ጠቢባን፣ ዲፕሎማቶችና ፖለቲከኞች፣ የዓለምአቀፍ ደኅንነት፣ ጸጥታና ጦርነት ዘጋቢ ጋዜጠኞች “ኢስቶኒያ በጭራሽ የሶቪየት ኅብረትን ውለታ መርሳት የለባትም!” ብለው መናገር ከጀመሩ ረዥም አመታት ማስቆጠራቸው ነው።

አሁን አንድ ታሪክ ላስታውሳችሁ። ይህ ታሪክ የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን ታሪክ ጠንቅቆ የሚያውቅ ማናቸውም ወገን ሁሉ ያውቀዋል ተብሎ የሚገመተው “ኦፕሬሽን ባርባሮሳ” ወይም “ዘመቻ ባርባሮሳ” ሲሆን፤ ይህ ዘመቻ የሒትለር ናዚ ጀርመን ሠራዊት አባላት ከተባባሪዎቻቸው ፋሺስት ጣልያንና የጃፓን ሚሊተሪዝም ጋር ተባብረው እሑድ ጁን 22 ቀን 1941 ሶቪየት ኅብረት ላይ የፈጸሙት ወረራ መጠሪያ ስም ነው። “ዘመቻ ባርባሮሳ” በ12ኛው ክፍለ-ዘመን የሮማውያን ዐፄና የጀርመን ንጉሥ ከነበረው ባለ ቀይ ጺማሙ /ሪዛሙ (red beard) ፍሬደሪክ ባርባሮሳ መጠሪያ ስም በቀጥታ የተወሰደ ነበር።

እናም ናዚ ጀርመኖች በዘመቻ ባርባሮሳ ሶቪየት ኅብረትን ከወረሩ በኋላ በጁላይ 1941 (በሐምሌ 1933 ዓመተ-ምህረት) ኢስቶኒያን ተቆጣጠሩ። ቢቢሲ ጃንዋሪ 28 ቀን 2021 (ጥር 20 ቀን 2011 ዓመተ-ምህረት) ባሠራጨው ዘገባ “ናዚ ጀርመኖች ሶቪየት ኅብረት ላይ ወረራ ከፈጸሙ በኋላ፤ በጎርጎሮሳዊያኑ አመት 1944 በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢስቶኒያውያንን አግዘው ወደ ሳይቤሪያና ማዕከላዊ እስያ አጋዟቸው ወይም ለግዞት ወሰዷቸው!” በማለት ገልጿል።

ይህ ብቻ አይደለም። በሒትለር የሚታዘዙት የጀርመን ወራሪ ጦር አባላት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢስቶኒያውያንን፣ የኢስቶኒያ አይሁዶችን፣ ኢስቶኒያውያን ጂፕሲዎችን፣ የኢስቶኒያ ሩሲያውያንን፣ የሶቪየት የጦር እስረኞችንና የሌላ አገር ዜጋ የሆኑ አይሁዶችን እጅግ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ገደሏቸው፤ ዘር ቆጥረው ፈጇቸው። የናዚ ጀርመን የጭካኔ ድርጊትም “በኢስቶኒያ የደረሰ ዕልቂት/ፍጅት” (The Holocaust in Estonia) ለመሰኘት በቃ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ መሬት ችብቸባ፤ በታሪክ እይታአጼ ዮሐንስና አጼ ካሌብ ቢኖሩ አንዴት ያዝኑ!

እናም! ኢስቶኒያን ከናዚ ጀርመን ጡጫና እርግጫ በዋናነት መንጥቃ ያወጣቻት ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት አሸናፊዎቹ አንዷ የሆነችው የሩሲያ ታላቅ ተጋድሎ የተደረገላት ሶቪየት ኅብረት ነበረች።

ይሁንና ከላቲቪያና ሩሲያ ጋር የምትዋሰነውና ከፊንላንድና ስዊዲን ጋር የባህር ንግድን የምትጋራው ኢስቶኒያ፤ በጥሩ ምጣኔ ሀብታዊ ቁመና ላይ ሆና ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ግዛቶች ነጻ ከወጣች በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መከራዋን ያሳዩዋት ጀርመንና ጣልያን ወደ ሚገኙበት ኔቶ አምርታ በጎርጎሮሳዊያኑ ቀመር 2004 የአባልነት መታወቂያ ተቀበለች።

ከሦስቱ ባልቲክ አገሮች ወደ ሰሜን ባልቲክ ከፍ ብላ የምትገኘው፤ ከፊንላንድ ጋ የሥነ-ልሳን ትስስር ያላት አገር የምትሰኘው፤ ቢቢሲ የዜና ምንጭ “ከአዲሶቹ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች እጅግ ስኬታማ የምጣኔ ሀብት ያስመዘገበች የአውሮፓ ኅብረት አባል አገር” (One of the most economically successful of the European Unions newer eastern European members.) እያለ የሚያንቆለጳጵሳት የኢስትኒያ ሪፑብሊክ፤ አያሌ የባልካን ፖለቲከኞች እንደጠረጠሩትና እንደገመቱት “ኢስቶኒያ ኔቶ ጉያ ሥር ገብታ በመሸጎጥ የሶቪየት ኅብረትን አደራ በላች! ሶቪየት ኅብረት ያበላቻትን ወጨት ሰበረች!” በማለት ተናገሩ፤ የምዕራባዊነት ናፋቂነቷን እየነቀፉ ኢስቶኒያን እያማረሩ።

እነዚሁ “ሦስቱ የባልቲክ ሪፑብሊኮች” የሚሰኙት ሉትዋኒያ፣ ላቲቪያና ኢስቶኒያ ይባስ ብለው ዩክሬንን “አንቺ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሶሻሊስት ሪፑብሊክ ዘመን ስንዴን ጨምሮ የብዙ እህል አምራች የነበርሽ የዳቦ ቅርጫት ስለነበርሽ! እነሆ የአውሮፓ የዳቦ ቅርጫት ስለሆንሽ ነይ ወደ ኔቶ?!” ሲሉ ክፉኛ መከሯት።

እነሆ! ሩሲያ ካመረረች “ሉትዋኒያ፣ ላቲቪያና ኢስቶኒያን ጦርነት ገጥማ በአጭር ጊዜ ጉርሻ መቀጣጫና ማስተማሪያ ልታደርጋቸው ትችላለች!” የሚባልበት አንዱ ምክንያትም አደራዋን በልተውና ወጨቷን ሰብረው በኔቶ እግር ሥር መውደቃቸው ብቻ ሳይሆን ዩክሬንና ጆርጂያን ጭምር የኔቶ አባል እንዲሆኑ በእጅ አዙር ይቀሰቅሳሉ ከሚል ስሜት በመነሳት ነው።

ዩክሬን በበኩሏ፦ የኔቶ አባል ለመሆን ልቧ ቢፈልግም ወይ አልሄደች ወይ አልተወች መኻል ላይ እንደ ገበቴ ውሃ እየዋለለች፤ በዳቦ ተረትና ምሳሌዋ “Borrowed bread lies heavy on the stomach. “ተበድረው የበሉት ዳቦ በሆድ ውስጥ ከበድ ይላል!” ማለቷን ጀመረች፤ በእሳት ውስጥ ገብታ በመለብለብ ላይ ሳለች፤ ዕዳ ሆድ መክበድ ብቻ ሳይሆን እንቅልፍ እንደሚነሳ የኋላ ኋላ ስላወቀች።

የሩሲያ ፌዴሬሽንም “አላወቃችሁትም እንጂ ቁራሽ ዳቦን በእጅ የያዘ፤ ገነትን ከጥድ ዛፍ ሥር ያገኛታል!” (With a piece of bread in your hand you will find Paradise under a pine tree.) ስትል “ቀድማችሁ የሶቭየት ኅብረት አካል በነበራችሁበት ጊዜ ከሌሎች ግዛቶች ጋር በምቾት የገነት ያህል የኖራችሁበትን ጊዜ አትዘንጉ!” በማለት መናገሯን ቀጥላለች።

ሩሲያ መጨረሻ ላይ በሾርኔ እንዲህ ስትል ተናገረች ይባላል።

“A western priest blesses his own bread first.” አባባሉ፦ “ምዕራባዊ ካህን የሁሉንም ምዕራባውያን ዳቦ መባረክ ሲገባው የራሱን ዳቦ ቅድሚያ ይባርካል!” ማለት ነው። ይኸውም ጨዋታው ጀርመኖች እንደሚሉት “ዳቦህን ከበላሁ የአንተን ዘፈን መዝፈን እችላለሁ!” ከሚል የመነጨ ነውና።

እናም! “ምዕራባውያን ዩክሬን የኔቶ አባል እንድትሆን የሚገፋፏት ዳቦዋን ለመብላትና ከ3ሺ 5መቶ እስከ 5ሺ ኪሎ ሜትሮች የውጤት ርቀት ማውደም የሚችሉ ተምዘግዛጊ የአሜሪካ የመካከለኛ ርቀት አኅጉር አቋራጭ ሚሳኤሎች (U.S intermediate range missiles) በኪዬቭ በመትከል ሩሲያን የመጨረሻ አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት ነው!” የሚባለው ለዚህ ነው።

ውድ ወገኖቼ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት አንዱ መንስኤ ምስጢር ያለው ሦስቱ የባልቲክ አገሮች የሆኑት ሉትዋኒያ፣ ላቲቪያና ኢስቶኒያ በኔቶ በተቀደደላቸው ቦይ እንደ ፈሰሱ ሁሉ ዩክሬንም ከተቻለ ጆርጂያም እንደ ውሃ እንዲፈሱ በመፈለጉ ነው። “ኔቶም ሆነ ምዕራባውያን ዩክሬንን ገፋፍተው ጦርነት ውስጥ የከተቷት፤ ዳቦዋን እየበሉ፤ ሩሲያን እያሳቀሉ (እያሳጡ) ዘፈኗን ሊዘፍኑላት ነው!” እየተባለ ያለውም ለዚህ ነው።

በማጠቃለያ:- ኔቶ አባል የሚያደርጋቸው አገሮችን ዳቦ ቅድሚያ ይበላል። ቀጥሎ ዘፈናቸውን ይዘፍናል። ይኼው ነው። “When i eat your bread, i sing your sing.” አበቃሁ።

ለማንኛውም ቸሩ እግዚአብሔር አገራችንን ይጠበቅልን!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ አምላክ አገረ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share