በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ እየተወሰ ያለው የጅምላ እስር ሊቆምና የታሰሩም ሊፈቱ ይገባል፤
ስድብ እንደ ፖለቲካ በሚቆጠርበት፣ ጎምቱ ፖለቲከኞች፣ የምክር ቤት አባላት እና ታዋቂ የሚባሉ ሰዎች ሳይቀሩ ማህበረሰብን፣ አንድን ሕዝብ በይፋ ከግራ ቀኝ በስድብ በሚያላጉበት አገር በመንግስት የተበሳጩ የአዲስ አበባ ወጣቶች ሹም አንጓጠጡ ብሎ በጅምላ እያደኑ ማሰር የፖለቲካ ትኩሳቱን ያንረው ይሆናል እንጂ መፍትሔ አይሆንም።
በተለይም በባዕላትና የአደባባይ ሰልፎች ላይ ሰዎች ብስጭቶቻቸውን ለመግለጽ መንግስትን ወይም አንድን ሹም ሙልጭ አርገው ሊሳደቡ ይችላሉ። ስድብ ከሞራል አንጻር ነውር፤ ከዛም ካለፈ ወደ ሹም ስም ማጥፋት ከተጠጋም ወንጀል ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በሞራልም ሆነ በሕግ የሚደገፍ ነገር አይደለም። ይሁንና ክፌት ሲበዛ፣ ግፍ ሲበረታ፣ ሰቆቃ የዕለት ተዕለት የኑሮ መገለጫ ሲሆን፣ የአስተዳደር በደል ሲበራከት፣ ሙስና ሲነግስ ዜጎቸ በመንግስታቸው ላይ ይቆጣሉ። ቁጣቸውንም በብዙ መልኩ ይገልጻሉ። በአደባባይ የሚደረጉ ተቃውሞዎች፣ ስድቦችና ቁጣን በጽሑፍ እና በምልክት መግለጽ ሰላማዊ የሆነ ተቃውሞ ነው። ሰላማዊ ተቃውሞ ማለት በቃላት ወይም በጽሁፍ ብቻ የተደገፈና አመጽ ያልተቀላቀለበት የሕዝብ ተቃውሞ ነው። አካላዊ ወይም ጉልበት ወይም መሳሪያ የተቀላቀለበት ሲሆን አመጽ ይሆናል።
ዜጎች ከበደልና ቀሬታ ብዛት መንግስትን ሲሳደቡ ያኔ ሹሞች ቆዳቸው ደንዳና፣ ሆደ ሰፊ እና ቻይ መሆን አለባቸው። ስድብና ነቀፌታ ተፈርቶ፤ ሥልጣን ተወዶ አይሆንም።
በአድዋ በዓል አከባበር ወቅት ሹምና መንግስትን ሙልጭ አድርገው ሰድበው ግን አንዲትም ቅጠል ሳይበጥሱ እቤታቸው የገቡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ነው የገለጹት። በሰላማዊ መንገድ በተደረገው ተቃውሞ ውስጥ ሴሜ ተጠቅሶ ተሰድቤያለው የሚል የሰደበውን ሰው ለይቶ መክሰይችላል።
ይሁንና የተከፋ ሕዝብ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊሰድባችውና ብስጭቱን በቁጣ ቃል ሊገልጽ ይችላል። የሰደባችሁን ሁሉ አስራችሁ ግን አትዘልቁትም። ይልቅስ ለመሰዳደብ ምክንያት በሆኑት አገራዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሕዝብ ጥያቄዎች በአግባቡና በወቅቱ ለመመለስ መስራት ይበጃል።
በሕዝባዊ ተቃውሞ ላይ የተነሱ የሕዝብ ቅሬታዎችን በጅምላ እስር መመለስ ቢቻል ኖሮ ወያኔ መቀሌ ባልገባች ነበር። ልምምዳችሁ ጠቅላዩ ደጋግመው እንደገለጹት ወደ አፈናዊ ቢሆንም ስለማያዋጣ አትሞክሩት። ያሰራችኋቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶች ፍቱና ችግሩን ወደ ውይይት ቀይሩት። የአዲስ አበባ ወጣት ትላንት ምስላችሁን በቲሸርት አሳትሞና ደረቱ ላይ ለጥፏችሁ እንዳልዞረ ሁሉ ዛሬ ለምን ዞረብን? ለምን ሰደበን? ብላችሁ ብጠይቁ ለከርሞም ከመንበራችሁ ትቆያላችሁ።
ባጭሩ ከሕዝብ ጋር አትላተሙ። እናንተ ስድብ እንደሚያስቆጣችሁ ሁሉ የአዲስ አበባም ነዋሪም ስድብ ይጎረብጠዋል። ምክር ቤት ቁጭ ብለው የከተማውን ሕዝብ ሙልጭ አድርገው የሚሳደቡ አባላቶቻችሁን ሳትቀጡ መቅረታችሁ ያመጣባችሁን ጣጣ እንደብልጡ ዳኛ ባላየ ብታልፉት ነው የሚበጃችሁ።
የዳኛውን ታሪክ ለማታውቁ፤ አንድ ተበዳይ ጎረቤቴ ሰደበኝ ብሎ ክስ ይዞ ዳኛ ፊት ይቀርባል። ዳኛውም ከሳሹን ምን ብሎ ሰደበህ? ብለው ይጠይቁታል። ከሳሽም እናትኸን ብሎ ሰደበኝ ይላቸዋል። ታዲያ ዳኛው እናትኸን ማለት ታዲያ ስድብ ነው ወይ? ይሄ ስድብ አይባልም ብለው ክሱን ውድቅ ያደርጉበታል። ያኔ ተከሳሽ በዳኛው ፍርደ ገምድልነት ተናዶ እናትኸን ማለት ስድብ ካልሆነ እርሶም ዳኛው እናትዎን፣ ፖሊሱም እናትኸን፣ ዐቃቤ ሕጉም እናትኸን ብሎ አረፈው።
እና ትላንት ሹሞቻችሁ ሕዝብን ሲሰድቡና ሲያንቋሽሹ ቀጥታችኋቸው ቢሆን ኖሮ ሕዝብ ትምህርት ወስዶ ከስድብ ይቆጠብ ነበር። ተሰደብን ብላችሁ ግን ሰዎችን ሰብስባችሁ ማሰር አግባብ አይደለም። መክሰስ ግን ይቻላል። በአደባባይ በተደረገ ስድብ የሚከሰስ ሰው ማስረጃው የተቀረጸው ምስል ወይም ድምጽ እና ምስክር ስለሆነ ሰዎችን አስሮ ረዥም ጊዜ የሚወስድ የምርመራ ስራ የለውም። በዚህ ሁኔታ ሰዎችን ከክስ በፊት አስሮ እና የዋስትና መብት ከልክሎ ማጉላላት ሀሳብን የመግለጽና መንግስትን በአደባባይ የመተቸትና የመቃወም መብትን የሚጋፋም ተግባር ነው።
–