መግቢያ
ዛሬ በአገራችን እየተከሰተ ያለውን ቀውሳዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ እንደ አገር ተከስታ የታሪክ ዕድሜ ማስቆጠር ከጀመረችበት አንጻር ሲታይ መገኘት ከነበረባት ቦታ ላይ ለመገኘት አለመቻሏን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ሌላው ቢቀር ምንም እንኳ መልክዓ ምድር ቅርጿ የዛሬውን ባይመስልም እንደ አንድ አገር ከደርቡሾች፣ ከጣሊያንና በተዘዋዋሪ ደግሞ ከእንግሊዝና ከሌሎች ኃያላን አገራት ጋር ተዋግታ በማሸነፍ፣ የ”ሊግ ኦፍ ኔሽንስ” ብቸኛ የጥቁር አባል አገር፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ደግሞ በመሥራችነት መሳተፍ ብቻ ሳይሆን የድርጅቱ ሕገ መተዳደርያ ደንብ (ቻርተር) እንኳ ሲረቅቅ አንደኛውን የሥራ ቡድን በሊቀመንበርነት የመራች፣ የአፍሪካ አገራት ለነጻነት ያደርጉ የነበሩትን ትግል በመደገፍና ነጻ ከወጡም በኋላ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመሥረት ግንባር ቀደም ሚና በመጫወቷ ዝናን አትርፋ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ክብርን ተጎናጽፋ የኖረች አገር ናት።
አገሪቷ ጥንታዊ የመሆኗን ያህል፣ አገረ-ብሔር ሆና ሁሉም ሕዝቦቿ በእኩልነት የሚኖሩባት፣ የሚኮሩበትና የኛ የጋራችን ነው ብለው የሚያምኑበት የጋራ ማንነት ለመፍጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር አልቻለችም። ለዚህም ነው፣ በተለይም ካለፉት ሰላሳ ዓመታት ወዲህ ከጋራ ማንነት ይልቅ የየግል ማንነት ጎልቶ በመውጣት፣ በመሠረቱ የጋራ ማንነት ሆነው ሁሉም በእኩልነት ሊኮራባቸው በሚገባቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ አለመግባባት መጥፋት ብቻ ሳይሆን፣ የየግል ማንነቶች ከጋራ ማንነቶች ይበልጥ ጎልተው በመውጣት ለተለያየ ደረጃ ግጭት፣ መፈናቀል ወይም መገዳደል ምክንያት ሆነው እያስተዋልናቸው ያለነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የግል ወይም የቡድን ማንነቱን ይዞ በመገለጫቸውም እየኮራበት በዚያው ልክ ደግሞ የጋራ ማንነት ይዞ የበለጠ ሊኮራበት የመቻል ምሥጢሩ ከሁላችንም የተሠወረ ይመስላል። ይህ የየግል ማንነት ጎልቶ የጋራ ማንነቱ ጉዳይ እየኮሰሰ መታየቱ በአስቸኳይ ታርሞ፣ ግለሰቦች ሆኑ ቡድኖች የየግል ማንነታቸውን ይዘው እየኮሩበት፣ የጋራ ማንነትን ደግሞ ይዘው የበለጠ እንዲኩራሩበት ባላድርሻ አካላት ያላንዳች መዘግየት ዛሬውኑ የተቀነባበረ ርብርብ ካላደረጉ የነገዋ የጋራ አገራችን ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ አዎንታዊ ነው ብሎ ለመገመት ይዳግታል።
ላለፉት ዘመናት ስለተደረገው ስሕተት፣ ማለትም የጥንት አባቶቻችን የየግል ማንነታቸውን ወደ ጎን አድርገው ለጋራ ማንነት ቅድሚያ አለመስጠታቸው፣ ያለፈ ጉዳይ ነውና ሊያሳስበን አይገባም። ብናስብና ብንጨነቅም፣ የፈሠሰ ውኃ አይታፈስምና ምንም ለውጥ አናመጣም። ማድረግ የምንችለው ግን ያለፈው ትውልድ የሠራውን ስሕተትና የስሕተቱን መነሾ አውቀን፣ ዳግመኛ ያንን ስሕተት እንዳንሠራና፣ ብሎም ታሪክ የቸረንን አጋጣሚ ተጠቅመን፣ መላው ሕዝባችን የየግሉን ማንነት እንደ ያዘ አንድ የጋራ ማንነት እንዲኖረውና በጋራ ማንነቱ መገለጫዎችም ላይ የጋራ ስምምነት እንዲኖረው እያንዳንዱ ኢትዮጵያ ያላንዳች መድልዖ የሚሳተፍበት አንድ ሁሉን ዓቀፍ የሆነ የጋራ ብሔራዊ ምክክር መድረክ ያስፈልገዋል።
የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ፣ ይህን በአብዛኛው ፖሊቲከኞችና አክቲቪስቶች ዘንድ የተሳሳተ ትርጉም የተሠጠውን “ብሔራዊ ምክክር” ምንነትና ዓላማውን ለማስረዳትና ዛሬ እየተከሰተ ያለውን አገራዊ ቀውስ ከሥረ መሠረቱ ገርስሶ ለመጣል፣ ብሎም የጋራ ማንነትና በጋራ ማንነት መገለጫዎች የጋራ ስምምነት ላይ የምንደርስበትን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚሳተፍበተን የጋራ መድረክ የመፍጠርን አስፈላጊነትን ለማስረዳት የሚረዳ የውይይት መነሻ ሃሳብ ለማቅረብ ነው።
ብሔራዊ ምክክር ምንድነው?
ብሔራዊ ምክክር እንደ አንድ፣ የማሕበረ ሰብን ፖሊቲካዊና ማሕበረሰባዊ ቀውሶችን መፍቻ ዘዴ ብዙም በማሕበረ ሰብ ሳይንስ ጠቢባን የተጠናበትና አንድ ወጥ ትርጉም የተሠጠው አይደለም። በመሆኑም የተለያዩ ጠቢባን በተለያየ መንገድ ይተረጉሙታል ወይም ይተነትኑታል። እንደ ጠቢባኑም ማንነትና ጥናቱንም ያነጣጠሩበት አገር ሁኔታ የምክክሩም ይዘትና ዓላማ የተለያየ ነው። ጥናቱና ሙከራው የተደረገባቸው አብዛኞቹ አገራትና ሊፈቱም የታሰቡት ቀውሶች የተከሰተቱት በየእርስ በርስ ጦርነት በታመሱ አገሮች፣ በወደቁ አገሮች ወይም በእርስ በርስ ጦርነት ሊበታተን ጫፍ ላይ በደረሱ አገሮች ስለሆነ፣ የምክክሮቹ ጭብጦች ከሞላ ጎደል ያተኮሩት በፖሊቲካ ሥልጣን ክፍፍል ላይ ነው። እነዚህ አገራት ከሞላ ጎደል በአገራቸው ታሪክና ባሕል ወይም የማንነት ጥያቄ ላይ ያን ያሕል የተለያየ ግምት ወይም እሴት ያላቸውና ባለፈው ታሪካቸው ውስጥ አንደኛው ባለ ድርሻ አካል ሌላውን ሲበድል ያልኖረና በማንነቶቹ መካከል ምናባዊም ሆነ ተግባራዊ የሆነ ያልተወራረደ ሂሳብ ያልነበራቸው ናቸው። ስለዚህም ነው ምክክሮቹ በተደረጉባቸው ደርዘን አገራት ውስጥ ምናልባት ከየመንና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ከሱዳን (ሁለቱም) በስተቀር በሁሉም አገራት በፖሊቲካ ሥልጣን ክፍፍሉ ተስማምተው አገራቸውን ከአደጋ ለመታደግ የቻሉት።
ከላይ እንዳልኩት በብዙ አገራት የተደረጉት ብሔራዊ ምክክሮች የተጠናቀቁት በፖሊቲካ ሥልጣን ክፍፍል ነው። በሌላ አነጋገር ለግጭቱና ለተከተለው አገራዊ ቀውስ ቁልፍ ጥያቄው የፖሊቲካ ሥልጣን ስለነበረ ባለ ድርሻ አካላቱ የፖሊቲካ ሥልጣኑን ከተከፋፈሉ በኋላ አንጻራዊ ሰላምን ተጎናጽፈዋል። ሆኖም ግን በሌላ አገራት የተከሱቱትን ማሕበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውሶችን ለመፍታት የተጠቀሙበትን የችግሮቹን መፍቻ ዘዴዎች እንዳለ ቀድቶ ለአገራችን ቀውሶች መፍቻ ለመጠቀም የሚቻል የሚመሰላቸው ብዙ ወገኖች አሉ። ለዚህም ነው ለምሳሌ ዛሬ በአገራችን ውስጥ እየተከሰተ ያለውን ማህበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውሶችን ለመፍታት ልክ በነዚህ አገራት የተካሂደውን የብሔራዊ ምክክር ይዘትና ቅርጽን እንዳለ ተውሶ በሥራ ላይ ማዋል ይቻላል ብለው የፖሊቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች አስተያየታቸውን ሲሠጡ የሚስተዋሉት። እነዚህ ወገኖች አንድ ያልተረዱት ቁልፍ ነገር ቢኖር፣ በነዚህ አገራት የተከሰተው ቀውስ ከሞላ ጎደል በፖሊቲካ ሥልጣን ዙርያ የሚሽከረከር ሲሆን፣ ባገራችን ግን ቀውሱ ለዘመናት ሥር የሰደደ ማሕበረ ሰባዊ ነቀርሳና ዛሬ ለምናስተናግደው የፖሊቲካ ቀውስም ዋነኛ ምክንያት የሆነው በጋራ ማንነትና በጋራ ማንነቱ መገለጫዎች ላይ የጋራ መግባባት አለመኖሩን ነው።
ከዚህ ተነስቼ ነው ብሔራዊ ምክክርን እንደሚከተለው ለመግለጽ የሞከርኩት፣ ብሔራዊ ምክክር ማለት ማህበረ ሰቡ በተለምዶ ይጠቀምበት ከነበረው የማሕበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውሶችን የመፍቻ ዘዴዎች ለየት ያለና፣ መንግሥትን፣ ፖሊቲካ ድርጅቶችን፣ የማሕበረ ሰብ ተቋማትና የማሕበረ ሰብ ተወካዮችን በአንድ የጋራ መድረክ ላይ በማምጣት ከተለመደው መንግሥታዊ ተቋማት አሠራር ውጪ፣ ግን ደግሞ በመንግሥት ድጋፍ የሚተገበር መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተወካዮቻቸው በኩል በአንድ የጋራ መድረክ ላይ መጥተው ለዘመናት ነቀርሳ ሆነው የጋራ ማንነትና በጋራ መገለጫዎቹም ላይ መግባባት እንዳይኖርና፣ ብሎም ማሕበረሰቡን በመለያየት ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቷም ሰላም፣ ፍትሕ፣ ዲሞክራሲና ኤኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይሰፍን ጠንቅ የሆኑትን ማኅበረሰባዊ ነቀርሳዎችን፣ ቅንነት በተሞላበት አገራዊ ውይይት አማኝነት መፍትሔ አግኝተውለት ስለ ወደፊት የጋራ ማንነትና ብሩህ የጋራ ሕይወት የሚመክሩበት ሁሉን አቀፍ የሆነ የጋራ ምክክር ማለት ነው።
ይህንን ትንሽ ውስብስብ ያለውን አገላለጽ ይዘቱን ስንመረምር የሚከተሉትን እናገኛለን፣
ሀ) መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት፣ ዘርፈ-ብዙ በሆኑ ማህበረ ሰባዊና ፖሊቲካዊ ቀውሶች ውስጥ ተዘፍቆ እንደሚገኝ፣
ለ) እነዚህን ተደራራቢ ማህበረ ሰባዊና ፖሊቲካዊ ቀውሶችን ለመቅረፍ በተለምዶ እንጠቀምበት የነበረውን በመንግሥታዊ ተቋማት ተቀይሰው ይተገበሩ የነበሩ ልማዳዊ የቀሶውች መፍቻ ዘዴዎች እስከ ዛሬ ድረስ አመርቂ ውጤት እንዳላስገኙ፣
ሐ) እነዚህን ለዘመናት ያጋጠሙንን ቀውሶች በአዲስ ዘዴ ለመፍታት፣ የማሕበረ ሰብ ተቋማትና የማሕበረ ሰብ ተወካዮችን፣ በሌላ አነጋገር፣ መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተወካዮቻቸው በኩል በአንድ መድረክ ላይ ተገኝተው ስለ ቀውሶቹና መፍትሔዎቻቸው መወያየቱ አስፈላጊ እንደሆነ፣
መ) የምክክሩ ዋና ዓላማ የነገዋ ኢትዮጵያ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ፍትሕ የሰፈነባት የጋራ አገራችን እንድትሆንና የጋራ መገለጫዎቹ እንዲኖሩን የሚረዳ ሁሉን አቀፍ የጋራ ምክክር ማድረግ እንዳለብን፣
ሠ) ብሔራዊ ምክክሩ ሁሉንም አሳታፊና ማለትም፣ ከምክክር ሂደቱ አንድም የሚገለል ድርጅት፣ ተቋም ወይም ግለሰብ እንደማይኖር ነው።
ምክክሩ ያልሆነው ደግሞ ምንድነው?
ምክክሩ፣ አንዳንድ የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ኤሊቶችና ተንታኞች እንደሚሉት፣ በፖሊቲካ ፓርቲዎች፣ ወይም በፖሊቲካ ፓርቲዎችና በመንግሥት መካከል የሚካሄድ ለፖሊቲካ ሥልጣን መያዣ ወይም ለሥልጣን ክፍፍል የሚያደርጉት ድርድር አይደለም። ከላይ እንዳልኩት፣ መድረኩ የማሕበረ ሰቡ አባላት በተለያየ ደረጃ፣ የጋራ ማንነትን በሚመለከቱ የተለያዩ አገራዊ ቀውሶች ላይ የሚወያዩበትና፣ ተወያይተውም ደግሞ የችግሮቹን ምንጭ አውቆ ፈልፍሎ በማውጣት በአገራችን ሰላም፣ ዲሞክራሲን ፍትሕ እንዲሰፍን የሚረዳ ዘላቂ መፍትሔን የሚያገኙበት ሁሉን ዓቀፍ የሆነ የምክክር መድረክ ማለት ነው።
የሌሎች አገራት ተሞክሮዎች፣
ብሔራዊ ምክክር በተካሄደባቸው አገራት በአንዳንዶቹ ስኬትን በሌሎች ደግሞ ውድቀትን አስመዝግቧል። የየአገራቱ፣ ባሕል፣ ማሕበረ ሰባዊ ቅንጅቱና ታሪካዊ አመሠራረቱ የተለያየ ስለሆነ፣ ለሁሉም አገራት አንድ ወጥ የሆነ ወይም ሳይንሳዊ ፎርሙላ ያለው የምክክር አጄንዳ ማዘጋጀት አይቻልም። ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ፣ በላይቤርያ፣ በቱኒዝያ፣ በሊባኖስ፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን የተደረጉት ምክክሮች አንጻራዊ ስኬትን ሲያስመዘግቡ፣ በየመን የተደረገው ግን ሳይሳካ ቀርቷል። እነዚህ ሁሉ ምክክሮች ዋናው ግባቸው በማሕበረሰቡ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ሲተገበር የነበረው በዘር መድልዖ ላይ የተመሠረተው ጨቋኝና አግላይ ፖሊቲኮ-አስተዳደራዊ ሥርዓትን ደምስሶ (ደቡብ አፍሪካ) በምትኩ እኩልነትና ፍትሕ የተሞላበት ሥርዓት እንዲፈጠር፣ እንዲሁም ተከታታይ ትውልድን ባካተተው የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ተበጣጥሶ የነበረውን ማሕበራዊ ትስስር እንደ ገና ለማገናኘትና አጠናክሮ ለመቀጠል (ሊባኖስ፣ ላይቤርያ፣ ሱዳን) ነበር። እነዚህን ሁሉ ምክክሮች ግን አንድ የሚያገናኛቸው መሠረታዊ ዓላማ ቢኖር በተፎክካሪ ወገኖች መካከል፣ የሚያስማማ መፍትሔን በማምጣት፣ ፉክክሩ የሚያገዳድልና የሚያጠፋፋ ሳይሆን ሰላማዊና መደማመጥ፣ ብሎም ልዩነትን አቻችሎ፣ ጉልበት ያለው የፖሊቲካ ሥልጣኑን ጨብጦ ሌላውን በጠላትነት ሳይኮንን ሁሉም የተስማማሙበት የፖሊቲካ መድረክ ለመፍጠር ነበር። በሌላ አነጋገር፣ በነዚህ አገራት የተደረጉት የብሔራዊ ምክክሮች ዓላማቸው የፖሊቲካ ሥልጣንን ፍትሓዊና ሰላማዊ በሆነ ዘዴ ተከፋፈሎ ሰላምና ለማስፈን ነበር።
በኢትዮጵያ ግን የብሔራዊ ምክክሩ ዓላማና ይዘት ከነዚህ ከላይ ከጠቀስኳቸው አገራት ለየት ያለ መሆን አለበት። ምክንያቱን በአጭሩ ለማስረዳት ልሞክር፣
ዘመናዊት ኢትዮጵያ “ከተመሠረተች” ቢያንስ አንድ መቶ አምሳ ዓመት ብታስቆጥርም፣ ከሷ በኋላ ተነስተው፣ ተበታትትነው የየራሳቸውን ውስን ግዛት ያስተዳድሩ የነበሩትንና በተለያዩ ማንነት ሥር ተደራጅተው የነበሩትን ጥቃቅን ግዛቶች አንድ ላይ አሰባስበው አገረ-ብሔርን ለመመሥረት ቁርጠኛ ውሳኔ አድርገው የታገሉት ለምሳሌ ጣሊያንና ፈረንሳይ ተሳክቶላቸው ዛሬ “የጣሊያን ሬፑብሊክ” “የጣሊያን ቋንቋ” “የፈረንሳይ ሬፑብሊክ” “የፈረንሳይ ቋንቋ” ደረጃ ላይ ሲደርሱ፣ ኢትዮጵያ ግን ዛሬም ልክ ከመቶ አምሳ ዓመት በፊት እንደ ነበረው ከሰማኒያ በላይ ብሔሮችንና ያንኑ ያሕል ቋንቋዎች እንደ ያዘች ቀርታለች። ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ የሚለውን ለታሪክ ተመራማሪዎችና ለፖሊቲካ ጠቢባን ብንተውና ዛሬ ባለንበት ማሕበረሰባዊ ቀውስ ላይ ብናተኩር፣ አገረ-ብሔር ለመመሥረት አለመቻላችን የዛሬው ችግራችን አልፋና ዖሜጋ ነው ቢባል የተጋነነ አይመስለኝም። ያለንበትን ሁኔታ በትክክል ለማስቀመጥ ካስፈለገ ደግሞ፣ ዛሬ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚስማሙበት የጋራ ታሪክ፣ ብሎም አንድ ኢትዮጵያ (የጋራ ማንነት) በሚለው ላይ አንዳችም መግባባት የለንም። (የማንግባባቸውን ጉዳዮች ከታች በዝርዝር እመለስበታለሁ)። እዚህ ላይ ለማንሳት የፈለግሁት ዋነኛው ጥያቄ ግን፣ አንድ ሁላችንም በጋራ አለን የምንላት አገርና ታሪክ የለንም የሚለውን ነው። በዚህ የጋራ ማንነት ላይ ስምምነት እስከሌለን ድረስ ደግሞ፣ የአገሪቷ ጠቅላላ ሁኔታ፣ ብሎም የፖሊቲካ ድርጅቶች በሥልጣን ክፍፍል ላይ መሻኮቱ፣ ማሕበረስቡ እርስ በርስ መፈነቃቀሉና መገዳደሉ ይቀጥላል፣ ሰላምና መረጋጋትም ሕልም ሆኖ ይቀራል።
በብሔራዊ ምክክሩ የሚሳተፉት አካላት እነማን ናቸው?
የብሔራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የፖሊቲካም ሆነ የማሕበረስቡ አጄንዳ ሆኖ ብቅ ካለ ወዲህ፣ በተናጠልም ሆነ በቡድን ባልተማከለ መልኩ ውይይቶች ሲካሄዱ ይስተዋላል። ሳያድለን ቀርቶ የኢትዮጵያን ችግር ሁሉ የምናየውና ለመፍታትም የምንሞክረው በፖሊቲካ ሥልጣን መነጽር ብቻ ስለሚመስለን፣ ስለ ብሔራዊ ምክክሩ ከሁሉም አስቀድመው መተቸትና መደገፍ የጀመሩት የፖሊቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች ናቸው። ትችቱና ድጋፉ ከሞላ ጎደል፤ በፖሊቲካ ፓርቲዎችና በመንግሥት መካከል ውይይት ተደርጎ የፖሊቲካ ሥልጣን እንዴት እንደሚከፋፈሉ (የሽግግር መንግሥት፣ የአደራ መንግሥት፣ ሌላ አዲስ ምርጫ ወዘተ) ነበር። ልክ ከላይ በጠቀስኳቸው አገራት የተካሄዱትን ምክክሮች ለአብነት እያቀረቡ፣ የፖሊቲካ ሥልጣንን እንዴት እንደሚከፋፈሉ ነበር የሚያነሱት። መንግሥቱም (ገዢው ፓርቲ) በታሪክ አጋጣሚ በእጁ የገባውን የፖሊቲካ ሥልጣን፣ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ሳይጋራ ለብቻው ይዞና፣ አንዳንዶች በሽብርተኝነት የተፈረጁትን ደግሞ ከምክክሩ መድረክ እንደሚያገልላቸው በአደባባይ መግለጫ ሲሠጥበት እየተስተዋለ ነው።
የብሔራዊ ምክክራችን ዋና ዓላማ ግን ስለ ፖሊቲካ ሥልጣን አከፋፈል ሳይሆን፣ ለምሳሌ፣ የፖሊቲካ ሥልጣንን በተመለከተ፣ በመቶ አምሳ ዓመት ታሪካችን ውስጥ አንድም ጊዜ የፖሊቲካ ሥልጣንን ዲሞክራሲያዊ በሆነና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ወይም የፖሊቲካ ድርጅት የየግሉን አስተሳሰብ እያስተናገደ በሰላማዊ መንገድ ወደ ሥልጣን መድረክ እንዳይወጣ ያደረገው ማሕበረሰባዊ ምክንያቱ ምንድነው የሚለው ለማወቅ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ዛሬ እያስተዋልን ያለው የፖሊቲካ ቀውስ የአንድ ማሕበረ ሰባዊ ቀውስ መገለጫ ሰበብ (symptom) እንጂ ምክንያት (root cause) አይደለም ማለት ነው። በመሆኑም ምክክሩ መሠረታዊ የሆኑና ለዛሬው ማሕበረ ሰባዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ የዳረጉንንና የጋራ ማንነት እንዳይኖረን ያደረጉንን ማሕበረ ሰባዊ ነቀርሳዎችን ጉልጉሎ በማውጣት በይዘታቸው ላይ ውይይት ተካሄዶ ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ ነው እንጂ፣ መንግሥትና ፖሊቲከኞቻችን እንደሚሉት ስለ ፖሊቲካ ሥልጣን ክፍፍል የሚደረግ ምክክር አይደለም። ያ ማለት ግን፣ ውይይቱ መልክ ይዞ እየጎለበተ ሲመጣ ዛሬ ስላለንበት የፖሊቲካ ቀውስና ተጓዳኝ የሆነውን የፖሊቲካ ሥልጣን ክፍፍል መፍትሔ ፍለጋን በአጄንዳው አያካትትም ማለት አይደለም።
የምክክሩን ባለ ድርሻ አካላት በተመለከተና ማን ሊካፈልበት ይችላል ለሚለው ቀጥተኛው መልስ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በግል፣ በቡድን፣ በድርጅት መልክ (ማሕበረሰባዊ፣ ፖሊቲካዊና ኃይማኖታዊ) በቀጥታ ወይንም ደግሞ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመረጣቸው ተወካዮቹ አማካይነት በምክክሩ ተካፋይ ይሆናል የሚለው ነው። በሌላ አነጋገር ከምምክሩ ሂደት የሚገለል አንድም ግለሰብ ወይም ማሕበረ ሰባዊም ሆነ ፖሊቲካዊ ድርጅት አይኖርም። ሁሉን ዓቀፍ ምክክር የተባለውም በዚህ ምክንያት ነው። ብሔራዊ ምክክር ማለት በሁለት ወገኖች መካከል የሚደረግ ድርድር ስላልሆነና እየተከሰተ ያለው አገራዊ ቀውስ የእያንዳንዱን ዜጋ ሕይወት በተለያየ ደረጃም ቢሆን የሚነካ ስለሆነ፣ ከዚህ ሂደት ውስጥ የሚገለል አንዳችም ግለሰብ ወይም ድርጅት ሊኖር አይችልም። ይህ ደግሞ በመንግሥት ወይም በሆነ አንድ ቡድን የሚወሰን ሳይሆን እንደ ማንኛውም የግለሰብ ወይም የቡድን መብት ልዩ ፈቃድ ሳያስፈልግ በቀጥታ የሚተገበር መብት ነው።
የኮሚሽኔሮቹ ሚና
ኮሚሽኔሮቹ በሙሉ በዚህ ሙያ ተፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ መቶ በመቶ ያሟሉ ግለሰቦች ላይሆኑ ይችላሉ። ዋናው መታወቅ ያለበት ቁም ነገር ግን፣ የኮሚሽኔሮቹ ዋነኛ ግዳጅ፣ ይህንን ለዘመናት ሥር ሰዶ ሕዝባችንን እያመሠ ያለውን ማሕበረ ሰባዊ ቀውስ በራሳቸው ጥረት ብቻ ለመፍታት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለቀውሱ ምክንያቶች ናቸው ብለው የሚያስቡትን አገራዊ ጉዳዮችን አሰባስቦ በጉዳይ ዕውቀትና ልምድ ላላቸው ጠቢባን ለማሰለፍ እና በአጠቃላይም የምክክሩን ሂደት ለማስተባባርና ለመምራት ነው።
የኮሚሽኔሮቹ አመራረጥ ሂደት በተፈለገውና መሆን ባለበት መንገድ ባይሄድም፣ በያዝነው ሳምንት አሥራ አንድ ኮሚሽኔሮች ተመርጠው ሥራቸውን ጀምረዋል። ይህንን ሂደት ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም። ካሁን በኋላ በሂደቱ ውስጥ ስለ ተስተዋሉ ስሕተቶችና ክፍተቶች ከማላዘን፣ ይህን በታሪካችን ለመጀመርያ ጊዜ በተግባር ለማዋል የምንሞክረውን ብሔራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን የምክክሩን ዓላማ በደንብ ተገንዝበን ኮሚሽኔሮቹ ግዳጃቸውን በተፈለገው ደረጃ እንዲፈጽሙ እያንዳንዳችን የየበኩላችንን አዎንታዊ አስተዋጽዎ ማበርከት አለብን።
የኮሚሽኑ ተልዕኮ፣ እንቅስቃሴና የተልዕኮው ግብ ከሞላ ጎደል የሚከተሉትን ያጠቃልላል፣
ሀ) የጋራ ማንነት ስምምነት ያልተደረሰባቸውን እና ለዛሬው አገራዊ ቀውሶቻችን መነሾ ናቸው ተብለው የሚታመኑትን ማሕበረ ሰባዊ ቀውሶችን ጎልጉሎ ለማውጣት ሙያና ልምድ ያላቸውን ጠቢባንን አፈላልጎ ከኮሚሽኑ ጋር ተባባረው እንዲሠሩ መመልመል፣
ለ) የጋራ ማንነት ያልተደረሰባችው አገራዊ ጉዳዮች በመላው ሕዝብ ጥቆማና በባለሙያዎቹ ትብብር ከተገኙ በኋላ፣ ችግሮቹን በዘርፍ በዘርፍ መመደብና በያንዳንዱ ዘርፍ ላይ መሳተፍ የሚገባቸውን ባለ ድርሻ አካላትን መለየት፣ እንዳስፈላጊነቱ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ባለ ድርሻ አካላት ዕገዛ መጠየቅ፣
ሐ) በጠቢባን ፍለጋ የተገኙትን የማህበራዊ ጠንቆቻችንን ዓይነቶች፣ በአንድ ቅርጫት ውስጥ ማሰባሰብ፣
መ) እነዚህ ባለሙያዎች፣ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተገናኝተው በማሕበረ ሰባዊ ጠንቆቹ ላይ ተወያይተውበት መፍትሔዎችን እንዲጠቁሙ መድረኮችን ማመቻቸትና ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ተጓዳኝ የሎጂስቲክ እርዳታዎችን መስጠት፣
ሠ) ባለሙያዎቹ በባለድርሻ አካላት መካከል ከተካሄደው ምክክር የገመገሟቸውንና ያጠናቀሯቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አሰባስቦ በተፈጻሚነታቸው ላይ አቅጣጫዎችን መቀየስ።
ረ) በምክክሩ ሂደት የተደረሰባቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በተግባር እንዲተረጉሙ ለባለድርሻ አካላት ማከፋፈል የሚሉ ናቸው።
የመንግሥት ሚና፣
ብሐራዊ ምክክር እጅግ በጣም የተወሳሰበ ሂደት ያለበት ነው። እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ብሄሮች አገር ይቅርና አንድ ዓይነት ሕዝብና ኃይማኖት ባላቸው አገሮች እንኳ ሂደቱም ሆነ አፈጻጸሙ ከባድ እንደሆነ ጠቢባን ይናገራሉ። ሆኖም ግን፣ የፖሊቲካ ሥልጣን ዕርካብ ላይ በመቀመጡና መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ እወክላለሁ ስላለና አገራዊ ኃላፊነት ስላለበት፣ መንግሥት በምክክሩ ሂደት ውስጥ ከማንኛውም አካል በላይ የዕገዛ እጁን የመዘርጋት ኃላፊነት አለበት። ይህ ደግሞ መንግሥት ከማሕበረሰቡ ጋር ካለው የማህበረሰብ ውል (social contarct) የሚመነጭ ስለሆነ ግዴታ እንጂ መብት አይደለም። ሆኖም ግን፣ በዚህ የምክክር ሂደት ውስጥ የሚካፈሉትን ባለ ድርሻ አካላትን ፈልጎ በማግኘቱና (identification) ተካፋዮችን በመጋበዙ (invitation) እንዲሁም በጠቅላላው በምክክሩ ሂደት ውስጥ ኮሚሽኑ እንዳስፈላጊነቱ ሁኔታዎችን እንዲያመቻችለት አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርግለት ኮሚሽኑ ካልጠየቀው በስተቀር፣ መንግሥት በዚህ የምክክር ሂደት ከሌሎች ባላ ድርሻ አካላት የተለየ አንዳችም ሚና አይኖረውም። በሌላ አነጋገር፣ መንግሥት ድጋፍ እንዲሰጥ በኮሚሽኑ ካልተጠየቀ በስተቀር በምክክሩ ሂደት በምንም መልኩ ጣልቃ ሊገባ አይችልም።
የብሔራዊ ምክክሩ የአጄንዳ ቅርጫት ምን ምን ጉዳዮችን ሊያቅፍ ይችላል?
በብሔራዊ ምክክሩ አጄንዳ ውስጥ የሚካተቱና ባለ ድርሻ አካላት እንዲወያዩበት የሚጠበቀው፣ የጋራ አገር፣ የጋራ ማንነትና በጋራ ማንነቱ ላይ መግብባት እንዳይኖር መሰናክል የሆኑብንን የብሔራዊ ቀውሶቻችን ብዛት ወይም ዓይነት ዘርፈ-ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ገና ከወዲሁ ሙሉ ዝርዝሩን ማቅረብ አይቻልም። ዋናው መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር፣ ዝርዝሮቹን ለኮሚሽኔሮቹ የማቀበል ድርሻና ኃላፊነቱ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን ነው። ኮሚሽኔሮቹ ወይም ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ወዳጆችም ከያሉበት ሆነው ማሕበረሰባዊ ነቀርሳዎች ናቸው ብለው የሚገምቷቸውን የምክክር አጄንዳ ሊያቀርቡ አይችሉም ለማለት ሳይሆን፣ መሠረታዊው የቀውሶቻችን ዝርዝር “የማዋጣት” ተቀዳሚ ኃላፊነቱ የሕዝብ እንጂ የመንግሥት ወይም የኮሚሽኔሮቹ አለመሆኑን ለማስረዳት ያሕል ነው።
የየግል ማንነት ጫፍ ረግጦ የጋራ ማንነት እየኮሰሰ በመጣበት በዛሬው ያገራችን ሁኔታ ለጋራ ማንነት መሰናከል የሆኑትን አገራዊ ጉዳዮችን ጠቁሞና አሰባስቦ፣ ለውይይት አጄንዳ ማስያዙ ቀላል ላይሆን ይችላል። ዛሬ አንዱ ወገን ትክክለኛ ነው ብሎ ለግል ማንነት ተቀዳሚነት ማስረጃ በጽሁፍም ሆነ በአፈ ታሪክ የሚያቀርበውን ታሪክ፣ ሌላኛው ደግሞ፣ “ለዘመናት የነበረንን የጋራ ማንነት ለመካድ በኤሊቶች የቀረበ የውሸት ትርክት” አድርጎ ይመለከተዋል። ይህ እንግዲህ የሂደቱ አካል ስለሆነ ኮሚሽኑ ወደደም ጠላም መጋፈጥ ያለበት ዕዳ ነውና፣ በወቅታዊ አለ መግባባቶቹ ላይ አተኩሮ ከታላቁ የሩቅ ጊዜ አጄንዳ ላይ ዓይኖቹን ሳያነሳ፣ ለባላ ድርሻ አካላት ውይይት የሚቀርቡቱን የአጄንዳ ነጥቦቹን የሚያሰባስብበትን ዘዴ በጥልቅ ማሰብ አለበት። ተቀዳሚ ተልዕኮው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር፣ ለውይይቱ አስፈላጊ ናቸው ብለው የሚገምቷቸውን ጉዳዮች እንዴት ወደ ኮሚሽኔሩ ሊያደርሱ የሚችሉበትን ዘዴና ማዕከል መፍጠር ነው። ዘመኑ የቲክኖሎጂ በመሆኑም፣ ማሕበረሰቡ የሚጠቁሟቸውን ጉዳዮች የሚሰበስበት ማዕከል ለምሳሌ እንደ ዊኪፔዲያ (Wikipedia) ዓይነት የመረጃ ገበታ አቋቁሞ መድረኩን ለባለድርሻ አካላት በሙሉ ተደራሽ ማድረግ አለበት የሚለውን ለምሳሌ ያሕል ከወዲሁ መጠቆም ይቻላል።
ከላይ እንዳልኩት የብሔራዊ ምክከር አጄንዳዎችን በሙሉ ዘርዝሮ ማቅረቡ የሚቻል ባይሆንም፣ በግሌ እንደ አንድ ባለ ድርሻ አካል የሚከተሉት ጉዳዮች በአጄንዳው ቅርጫት ውስጥ መካተት አለባቸው ባይ ነኝ። ሌሎች ባለድርሻ አካላትም እንደዚሁ ለጋራ ማንነታችን አለመሳካት ምክንያቶች ናቸው የሚሏቸውን ተመሳሳይ ነጥቦችን ኮሚሽኑ በሚያቀርብልን መስመር በኩል ለማቅረብ መዘጋጀት አለባቸው። ዋናው ቁም ነገር፣ ይህንን የታሪክ አጋጣሚ ተጠቅመን፣ በየግላችን ወይም በየቡድናችን በኩል በአደባባይም ሆነ በስውር እያነሳን ለጋራ ማንነት መሰናክል ናቸው ብለን የምንወያይባቸውን አገራዊ ጉዳዮችን በግልም ሆነ በቡድን ለኮሚሽኑ እንዲደርስ ማድረግ ነው። የኔ አስተዋጽዎ የሚከተለው ነው።
ሀ) ታሪካችን፣ የአገራችንን ታሪክ በተመለከተ ብሔራዊ መግባባት አይታይም። ግማሹ የመቶ አምሳ ዓመት ዕድሜ አላት ሲል ሌላው ደግሞ የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ ያላት ጥንታዊት አገር ናት ይላል። አንዳንዶች “አገሪቷ የብሔሮች እስር ቤት ነበረች” “እንዲያውም አንዳንዶች ብሔሮች እንደ ባሪያ ሲሽጡ የነበሩና እንደ እኩል ዜጋ አይቆጠሩም ነበር” ሲል ሌላው ደግሞ በታቃራኒው ቆሞ “የለም በሕዝቦቿ መካከል እኩልነት ሰፍኖ ሕዝቦቿም ተጋብተውና ተዋልደው በሰላም ይኖሩ ነበር” ይላል። አንዳንዶች “የአድዋን ድል እውን ያደረገው የዚህና የዚህ ብሔረሰብ ፈረሰኞች ነበሩ እንጂ የዚያማ ብሔር ሕዝብ ፈርቶ ሲሸሽ ወይም ለጣሊያን ገብሮ ነበር ሲል” ሌላው ደግሞ በተቃራኒው ያወራል። ምኒልክ ለአንዱ ወገን “የኢትዮጵያ አባት፣ የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሊት” ለሌላው ወገን ደግሞ “የደቡብን ሕዝብ የጨፈጨፈ፣ በባርነት ያኖረ አንዳችም ዓይነት ስብዕና የሌለው አውሬ” ነበር ይላል። ለምንድነው ይህንስ ያሕል የተለያየ ትርክት ሊኖረን የቻለው? በሕዝቦቿስ መካከል በውነት እኩልነት ነበር ወይ? በውነትም ሕዝቡ ተጋብቶና ተዋልዶ፣ እኩል ዜጋ ሆኖ በሰላም ይኖር ከነበረ፣ ታዲያ ዛሬ ይህን ሁሉ መፈነቃቀልና መገዳደል ምን አመጣው?
ለ) ባንዲራችን፣ ለምንድነው ሕዝባችን ይህን ሁሉ ዘመን አንድም ጊዜ በታሪኩ ውስጥ የመከረበትና የተስማማበት የራሴ ነው የሚለው ባንዲራ ያልነበረውና የሌለው? በተለምዶ ባንዲራችን ነው የምንለው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ መደብ ያለው ሰንደቅ ዓላማችንስ ለምንድነው ለተለያዩ ያገራችን ሕዝቦች የተለያየ ትርጉም ሊሠጥ የቻለው? ባንዲራውስ የመንግሥት ነው ወይስ የሕዝብ? የፖሊቲካ ፓርቲ አርማ ወይስ የቤተ ክርስቲያን ነው? ለወደፊትስ ሁላችንም የምንስማማበት (በቀለሞቹ ብቻ ሳይሆን በአርማውም ጭምር) አንድ ብሔራዊ ባንዲራ ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?
ሐ) የዲሞክራሲ ባሕላችን፣ ከላይ እንዳልኩት፣ ከኛ በኋላ የተፈጠሩት አገራት ሳይቀሩ፣ ልዩነትን አቻችሎ ሃሳብን በሃሳብ የመዋጋት ልምድ አካብተው ማሕበራዊና ፖሊቲካዊ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲፈቱ እኛ ይህንን ባሕል እንዳናዳብር ያደረገን ምንድነው? እንኳን ያልተማረውና ለዘመኑ “ሥልጣኔ” ያልተጋለጠው ከዘጠና በመቶ ያሕል የሚሆነው ሕዝባችን ይቅርና፣ በሠለጠኑና ዲሞክራቲክ በሚባሉ አገሮች የተማርንና የሠራን ምሁራን፣ በነዚህ ዲሞክራቲክ አገሮች እየኖርንና እየሠራን፣ የዲሞክራሲ እምብርት የሆነውን ልዩነትን አቻችሎ ባልተስማሙበት ነገር እንኳ ላለመስማማት ተስማምቶ አብሮ በመኖርና ለጋራ ጉዳይ እንደመትጋት፣ ጠላት ተብሎ የተፈረጀን ተፎካካሪ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ማሸማቀቅ፣ ማዋረድና ብሎም የመደምሰስን ባሕል በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በመንግሥትም እየተጠቅምንበት ያለነው ለምንድነው?
መ) መንግሥትና ኃይማኖት፣ ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት (የመሃመድ ግራኝና የዮዲት ጉዲት የአገዛዝ ዘመንን ሳናካትት) ክርስትናን፣ በተለይም የኦርቶዶክስ ኃይማኖትን እንደ አገሪቷ ቀዳሚ ኃይማኖት፣ ብሎም “ኢትዮጵያ በሙስሊሞች የተከበበች የክርስቲያን ደሴት” እንደ ሆነች አድርገው ለሕዝቡ ሲያቀርቡ ነበር። ይህ ሁሉ በአገሪቷ ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ ወደ አርባ በመቶ የሚጠጋ የኢትዮጵያ ሕዝብ የእስልምና እምነት ተከታዮች መኖራቸውን በመካድ ነው። ይህ ለምን ሆነ? ይህንን የተሳሳተ ግምትን አስተካክሎ ኢትዮጵያዊ ማንኛውንም ኃይማኖት የሚከተሉትን ሕዝቦቿን በእኩል ዓይን የምታይበትንና የኃይማኖት እኩልነት በሕግም በተግባርም የተከበረባት የጋራ የሆነች አገር እንድትሆን ምን መደረግ አለበት?
ከዚሁ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳይ ነው። ተዋሕዶ ቤ/ክ በተመለከተ፣ ባገራችን የደቡብ ክፍል፣ ከሌሎች የፕሮቴስታንት ወይም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተቋማት በጣም በተለየ መልኩ ለየት ያለና ሥር የሰደደ ጥላቻና ብሎም መሰደድ የደረሰባት ተቋም ናት። ይቺ፣ አንዱ ወገን “የኢትዮጵያ መሠረት የሆነች፣ የኢትዮጵያን ግዛት ብቻ ሳይሆን ሕዝቧንም አንድ ላይ በማኖር የዘመናት ታሪክ ያላት የአገሪቷ ምሰሶ ናት” ሲሉ ሌላው ወገን ደግሞ “የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ በ1975 ዓ/ም የመሬት ዓዋጁ እስከ ታወጀበት ጊዜ ድረስ በደቡብ ኢትዮጵያ 33% ርስት የነበራትና የዚያን አካባቢ ሕዝቦች ያፈናቀለች ወይም በገባርነት ስትገዛ የነበረች የጨቋኙ ፊውዳል ሥርዓት ቀጥተኛ ተካፋይና በዝባዥ እንጂ የኃይማኖት ተቋም አይደለችም” ይላል። ታዲያ ይህን በተለያየ ጫፍ ላይ ያሉትን አስተሳሰቦችን በአንድ ላይ አምጥቶ ኃይማኖትን በተመለከተ አገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ምን መደረግ አለበት?
ሠ) የሃገረ ብሔር ምሥረታ ጉዳይ፣ ከላይ እንዳልኩት አገራችን ቢያንስ ቢያንስ የአንድ መቶ አምሳ ዕድሜ አላት። የሶሶት ሺህ ዓመት ታሪክ አላት የተባለውን ወደ ጎን እንተውና! ይህን ሁሉ ዓመት አስቆጥራ ግን፣ ዛሬም ሃገረ-ብሔር ለመሆን አልቻለችም። በአንጻሩ ግን፣ ለምሳሌ ጣሊያንና ፈረንሳይ ከኛ በኋላ ተነስተው አገረ ብሔር ሲሆኑ፣ ለምንድነው እኛ የዛሬ አንድ መቶ አምሳ ዓመት ከነበርንበት አገራዊ አስተዳደርና አወቃቀር አንዲት እርምጃ ወደ ፊት መራመድ ያልቻልነው? ለምንድነው የዛሬ አንድ መቶ አምሳ ዓመት የነበሩ 85 ብሔረሰቦች ዛሬም ከአንድ መቶ አምሳ ዓመት በኋላ ሁላቸውም ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውንና የብሔር ማንነታቸውን ይዘው አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ ሳይቀልጡ ውሃና ዘይት ሆነው ጎን ለጎን እየኖሩ ያሉት? እንደው የሶስት ሺህ ዓመቱን ብንተውና የመቶ አምሳ ዓመት ዕድሜ ብቻ ነው ያላት ነው ብንል እንኳ፣ ታዲያ ከሷ በኋላ የተፈጠሩና የሷን ዕድሜ ግማሽ እንኳ ያላስቆጠሩ አገራት እንዴት አገረ ብሔር መሥርተው፣ አንጻራዊ ሰላም፣ ዲሚክራቲክና ፍትሓዊ ሥርዓት የሰፈነበትን ሁሉም የሚስማማበውትና የጋራችን ነው የሚሉትን አገር እንዴት ለፈጥሩ ቻሉ?
ረ) ሕገ መንግሥታችን፣ ሌላው የኢትዮጵያን ሕዝብ የማያስማማን ጉዳይ ደግሞ የሕገ መንግሥታችን ሕጋዊነት ነው። በታሪካችን ውስጥ ሕዝባችን አንድም ጊዜ ተወያይቶበት፣ ተስማምቶበትና የኔ ነው ብሎ የተቀበለው ሕገ መንግሥት ባይኖርም፣ እንደ 1995ቱ ሕገ መንግሥት ሕዝቡን በተለያየ ጎራ የከፋፈለ ግን የለም። በዚያውኑ ልክ ደግሞ፣ ያለፉት አራቱ ሕገ መንግሥታት በተከታታይ ለውጥና አብዮት ሲፋቁ አንድም ኢትዮጵያዊ፣ በመፋቃቸው የተከፋ ባይኖርም፣ የ1995ቱ ሕገ መንግሥት ግን እንኳን መሻሻያ ሊደረግበት ይቅርና አንዲት አንቀጽ እንዳትቀየር ዘብ ቆመው የሚጠብቁ ብዙ ወገኖች አሉት። ሕገ መንግሥቱ፣ ምንም እንኳ ልክ እንደ ፊተኞቹ ሁሉ ያለ እኛ ፈቃድ ከላይ የተጫነብን ቢሆንም፣ ከሌሎቹ ሁሉ ሕገ መንግሥታት በተለየ መልኩ የሚንከባከቡትና ብሎም የኢትዮጵያን ብሔሮች መብት ለመጀመርያ ጊዜ በተግባር የገለጸ ነው ብሎ የሚያምንበት ወገን ያለውን ያሕል፣ አይ! አይደለም፣ ይህ ሕገ መንግሥት ለመጀመርያ ጊዜ ሕዝቦቻችንን የከፋፈለ፣ ብሎም ለመፈነቃቀልና ለመገዳደል ያደረሰ ሰነድ በመሆኑ ከነጭራሹ ተፍቆ በአዲስ መተካት አለበት የሚሉ ወገኖችም አሉ። ታዲያ በሁለቱ ጎራዎች መካከል ያለው ክፍተት በምን ሊሞላ ይቻላል? ሁላችንንም ባይሆን አብዛኞቻችንን የሚያስማማ፣ የጋራችን ነው የምንለው ሕገ መንግሥትስ እንዴት ልንፈጥር እንችላለን?
የምክክሩ ድምዳሜው ምንድነው? (Outcome)
ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና አገራዊ ቀውሶች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ሊከሰቱ የሚችል ነገሮች ናቸው። በርግጥ አንዳንድ አገራት ማሕበራዊ ቀውሶቻቸውን በሰላም ፈትተው (አንዳንዶቹ በጉልበትም) አንጻራዊ የሆነ ሰላምና ፍትሕ የሰፈነበት ማሕበረሰብ ሊፈጥሩ ችለዋል። አንዳንዶቹ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ደግሞ፣ ችግሮቹ መኖራቸውን አምኖ፣ የችግሮቹን መሠረታዊ ምክንያቶችን ከሥሩ ጎልጉሎ በማውጣትና ዳግመኛ እንዳያንሰራራ አድርጎ አዲስ ማሕበረሰብ እንደ መፍጠር፣ ከመጀመርያውም ችግሮቹ መኖራቸውን በመካድ፣ ወይም ደግሞ ችግሮቹን ከሥሩ እንደ መንቀል ላይ ላዩን ብቻ እየቀባባን ውስጡ ግን በስብሶ ብሎም ለባሰ አገራዊ አደጋ እያሠጋን ይገኛል።
ወቅታዊው የአገራችን ፖሊቲካዊና ማሕበረሰባዊ ሁኔታ፣ ብሔራዊ ቀውሱን “እንደ ድሮው” (comme d’habitude) ብሎ ለማለፍ የማይቻል ደረጃ ላይ ነው። ምናልባትም በታሪካችን ውስጥ፣ ሕዝባችን እንደዚህ የተፈነቃቀለበትና የተገዳደለበት ዘመን አልነበረም ብል ማጋነን አይሆንም። ቁጭ ብለን በቅንነት ካልተወያየንና ካልተመካከርን፣ ብሎም ሰላምና ፍትትህ የሰፈነባትን ኢትዮጵያን ለመመሥረትና ለአንድ የጋራ ማነንት አንዳች ዓይነት የጋራ መግባባት ላይ ካልደረስን፣ የአገራችንና የሕዝባችን የወደፊት ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ወደድንም ጠላንም፣ ምክክሩ መሳካት አለበት። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በግልም ሆነ በቡድን የኮሚሽኑን ዓላማ ከግቡ የማድረስ ትልቅ ኃላፊነት አለብን። የምንተጋው ለዚህኛው ወይም ለዚያኛው ቡድን ጥቅም ሳይሆን፣ የሁላችንም ኅልውና ቀጣይነት እንዲኖረው ነው። ተባብሮ ከመጥፋት ደግሞ ተጋግዞ ክፉ ዘመንን አሸንፎ ተባብሮ ማደግ ይሻላል። ስለዚህ በምክክሩ ሂደት ውስጥ ሁላችንም በንቃት መካፈል ብቻ ሳይሆን፣ ለአገሪቷ ኅልውናና ለሕዝባቿ ሰላም፣ ብሎም አንድ የጋራ አገርና የጋራ ማንነት ለመፍጠር ሲባል፣ ጠቢባን የምክክሩን ውጤት አጠናቅረው ቀጣዩን የመፍትሔ አቅጣጫ ሲቀይሱልን፣ በቅንነት ተቀብለን፣ በተቻለን መጠን በተግባር ለመተርጎም ከወዲሁ ቃል መግባት አለብን ባይ ነኝ።
ምክክሩ እንዳይሳካ ሊያደርጉ የሚችሉ ክስተቶች፣ (Constraints)
የምክክሩ ሂደት ገና ሳይጀምር አንዳንድ ድርጅቶች ይኸኛው ወይም ያኛው ቅድመ ሁኔታ ካልተሟላ በምክክሩ አንካፈልም ሲሉ ይደመጣሉ። አብዛኛዎቻችን፣ (በተለይም የፖሊቲካ ድርጅቶች)፣ አውቀንም ይሁን ሳናውቅ፣ ምክክር፣ ብሔራዊ ዕርቅና ድርድርን እያማታን ነው። የምክክሩ ብቸኛ ዓላማ እስካሁን ያልነበረውንና የጋራ አገርና የጋራ ማንነትን ለመፍጠር የሚረዳ መፍትሔ መፈለግ ሲሆን፣ በፖሊቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ድርድር ደግሞ የየፓርቲያቸውን ዓላማ ለማሳካት እንዲረዳ የፖሊቲካ ሥልጣንን ለመከፋፈል ነው። ይህ ልዩነት ግልጽ ሆኖ ካልተቀመጠ የሂደቱን መሳካት ሊያደናቅፍ ይችላል። ከዚህ የሃሳብ ትርጓሜ በተጨማሪ፣ የመንግሥት አላስፈላጊ በሆነ መንገድ በኮሚሽኔሮቹ አመራረጥና አሿሿም ላይ ጣልቃ መግባት ደግሞ ብዙዎቻችን ስለ ኮሚሽኑ ነጻነትና ግልጽነት ጥርጣሬ እንዲያድርብን አድርጓል። ጥርጣሬው የተለመደና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተዋህዶን የኖረ ቢሆንም፣ ምክክሩ እስከነጉድለቱ፣ ስኬትን ያስመዘግባል የሚል ግምት አለኝ። ስለዚህ እኛ ባለ ድርሻ አካላት፣ የምክክር ኮሚሽኑን ዓላማ ብቻ ከግንዛቤ በመክተተ ለጋራ ስኬት ከማለት ብቻ በዚህ የመንግሥት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ በተቻለን መጠን መንግሥት በጭራሽ ጣልቃ እንዳይገባ በኮሚሽኑ በር ላይ ዘብ ከመቆም በተጨማሪ፣ የምክክሩን ውጤት በተግባር ለመተርጎም በተጠንቀቅ መቆም አለብን ባይ ነኝ።
በተጨማሪም ለዘመናት በአገሪቷ ሰፍኖ የባሕላችን አንዱ አካል የሆነው ያለመተማመን ባሕልና ዛሬ በጽንፈኞች ቅስቀሳ ምክንያት በሕዝቦች መካከል ተረጭቶ ያለው የርስ በርስ ጥላቻ መንፈስ፣ የኮሚሽኑ ተልዕኮ እንዳይሳካ ሊያደርግ ይችላል። ኮሚሽኑ እነዚህን እንቅፋቶች የማስወገድና ትክክለኛውን የብሔራዊ ምክክርን ይዘትና ዓላማ ለሕዝቡ የማስረዳት ከባድ ኃላፊነትን ወስዶ ለባለ ድርሻ አካላት እንደ አስፈላጊነቱ የማያቋርጥ የማንቂያ ትምሕርት ካልሠጠ በስተቀር፣ ምክክሩ በተፈለገው ልክ ውጤትን ላያስመዘግብ ይችላል።
ለማጠቃለል ያህል፣ ይህን ጽሁፍ ሳዘጋጅ፣ እንደ አንድ ባለ ድርሻ አካል የሚጠበቅብኝን ለማዋጣት እንጂ ሙያዊም ሆነ ተሞክሮ አለኝ ብዬ ከመገመት አይደለም። ዓላማዬ የብሔራዊ ምክክርን አስፈላጊነት በተቻለኝ መጠን አስረድቼ ለምክክሩ ስኬት ድጋፍን ለመሰብሰብ ነው። ስለዚህ ያስቀመጥኳቸውን ሃሳቦች በቅንነት ተረድታችሁና አላስፈላጊ ከሆነ ትችት ተቆጥባችሁ፣ ለብሩኅ ነገ ከማለት እንደዚሁ እንደኔ የበኩላችሁን እንድታዋጡ አደራ እላላሁ።
*****
ጄኔቫ የካቲት 2022 ዓ/ም