የእናት አገር ጥሪ – ፀረ-ሸኔ – ዘመቻ ግብዓተ ኢትዮጵያ – ከአባዊርቱ

መንደርደርያ፣
 
ግልፅና ግልፅ ነው። ወያኔ ሽባ ሆኖ ቀሽምዶ ድንበር ላይ ሰፍሯል። ሸኔ መንደር ለመንደር እየተርመጠመጠ ህዝባችንን በነቂስ እየጨረሰ ነው። ስለሆነም በብልፅግና ተስፈኛ ፓርቲ አዲስ አመራር አዝማችነት፣ ከዳር እስከዳር በህዝባችን የተባበረ ክንድ ሸኔ የተባለን ሰው በላ የአራዊት ስብስብ ላንዴና መጨረሻ በዘመቻ መልክ ሁሉ ይሰማራ ዘንድ እንደሚከተለው በትህትና አሳስባለሁ።
 
፩) ይድረስ በስማችሁ እየተነገደ ታላቁን የዖሮሞን ስም እያዘቀጠ በዝምታችሁ ብቻ ዖሮሞን ያስዋረዳችሁ ያገሬ ልጆች – ተነስ፣ ዝመት፣ ከመንግስት መከላከያ ጎን ቆመህ ተፋለም – ቢያንስ ድምፅህን አሰማ። በተለየ ሁኔታ የሸዋው ወንድሞቼና እህቶቼ ክፉኛ ተኝታችሁዋል። እስከመቼ ? እንዴት አያቃጥላችሁም ” እነዚህ አውሬዎች ሲባል”? እውነት የተዋለድኳቸውና እንደማተቤ የማውቀው ዖሮሞ አውሬ ነው? ምንድነው ነገሩ? በርግጥ ሸኔዎቹ ዖሮሚፋ የሚናገሩ አውሬዎች ቢሆኑ እንጅ ላምን እየሳመ የሚያልብ ወገኔ የሰውን ልጅ እይበልትም፣ ህፃናትን ገድሎ አያቅራራም፣ ባህሉም አይደለም። እንዴት ዝም ይባላል? ዝምታው ያሳምማል፣ ክፉኛም ልብ ያደማል።
 
፪) የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሹማምንት
 
ከመሪው የብልፅግና ጎን በመሰለፍ በህብረት የበኩላችሁን ለማድረግ ” ምን እንርዳ” እያላችሁ ዳይሬክቲቭ ጠይቁ እንጅ ። ምርጫ ብቻ ሲመጣ ለሥልጣን ብቻ ያስተዛዝባል። ይህ የዝምታና ለስልጣን ብቻ ባህል መለወጥ አለበት። አገርን ካስቀደምን አይደለም መንደርተኛን ሸኔ ቀርቶ ታላቋን አሜሪካ በህብረታችን ማንበርከክ ይቻላል። ታሪካችንን ወደሁዋላ ሄደን ዋቢ አድርጎ ማየት ብቻ በቂ ነው። የአድዋ ዘመን ኢጣልያ እኮ ከዛሬዋ ዘመን አሜሪካ የማትተናነስን የአውሮፓ የስልጣኔ ማእከልን ነው እኮ ኩም አድርገን ፣ እንቁላል አሳቅፈን የሸኘነው። ታሪክህን እወቅ ምድረ ውሽልሽል በፍርፋሪ ተመፃዳቂ ሁላ!
 
፫) ይድረስ ለመከላከያው ፊልድ ማርሻል ጁላና ጄ/አበባው፣
 
አዲስ ስር ነቀል፣ በየቀበሌው የተደራጀ ልክ እንደ ሱማሌው ጦርነት ዘመን ፣ በዘመቻ መልክና በመከላከያ አዝማችነት በመላው ዖሮሚያ ህዝባዊ ሚሊሻ ከ ፫ ወር ያልበለጠ ዘመቻ ቢደረግ አንድ ሸኔ የተባለ የሰው አውሬ ለወሬ ነጋሪ አይተርፍም። ከነነፍሳቸው መልቀም ይቻላል አንዲት ጥይት ሳትባክን። እንደውም ዘመቻው” ሀ”  ብሎ ሲጀምር መሳርያ እያስቀመጡ እጅ ይሰጣሉ። ወቅቱ አሁን ነው። ዘመቻው ይጀመር። ምንም ፕላኒንግ አይፈልግም ። ለምን? በወያኔ የተደረገው ዘመቻ ልምድ አለና። ይህው ነው።
 
፬) ይድረስ የወገናችን ሰቆቃ የአቢይን ፆም እንኳ በቅጡ ሱባኤ እንዳትገቡ መንፈሳችሁ የተረበሸ ህዝበ ኦርቶዶክስ፣ መስሊም ወገኖቼና የሌሎችም ሃይማኖቶች ወገኖች
 
እነዚህ የፅልመት አገልጋዮች በሚሰሩት ሳትረበሹ በፅናት ከመንግስት ጎን በመቆም በማንኛውም መንገድ መርዳት። መረዳዳትና መደማመጥ። ከልብም መፀለይ በተለየ ሁኔታ ዘንድሮ በአሎቻችንም በተከታታይ ይውላሉናም።
 
 
እረፍት የነሳኝ ጉዳይ – በአቶ ታዬ ደንደአ በኩል ይድረስ ለዖሮሞ ልጆች ብዬ ከ፫ አመታት በፊት በፃፍኩት ላይ እንዲህ ብዬም ነበር፣
 
ቦሶኑን በቅፈቴ ራንዳ ጉባ ባቴ
ቁፍኒሺ ባያቴቱ ቢኔንቲ ቱፋቴ
“ጫማ ቃቃማና ”  ጄቴ ሌንጫን ያምቴ!!
 
ሌንጪስ ዱቢን dhiቤ ያማሺን ኮልፌቶ
አታም ናቱፋናን ቡኬdhaን ላሌቶ
ኢራጋሹ ዴሜ ባካሺን ጂርቱቲ
ዮሚዩ ቦሶኑን  ሲላስ ሌንጫ ሚቲ
ታዬ ያባቀልቢ  ቱን ዱቢን ሲጋልቲ?!!
 
እንዳልኩትም ሆነ በህይወት እያለሁም አየሁት። ለምን ይህን በዖሮሚፋ ልሣን በግእዙ ፊደል መልሼ አመጣሁት? መጀመርያ ያኔም እንደተረጎምኩት አሁንም ላምጣውና እንየው:
 
አሽቃባጭ ድኩላ አፋፍ ተስፈንጥራ
ደንደሱዋን ተማምና ትእቢት ተወጥራ
አንበሶን ጠራችው ልታቁዋደስ ጮራ።
 
አንበሶም ተገርሞ ባሽቃባጭዋ ጥሪ
እንዴት ብትንቀኝ ነው የሌላት መካሪ
እመር ብሎ ዘሎ ወጥቶ ባለችበት
አንበሶ ድኩላን አደረጋት ዱቄት
ታዬም  ይገባሃል የዚህ ስንኝ ትውፊት።!!!
 
1ኛ ድኩላዋ ወያኔ በአቢቹ ፊታውራሪነት ዱቄትም ባትሆን ጥጋብዋ ጋብ ብሎልናል። ጁዋርና ጓዶቹም ትምህርት አግኝተውበታል። የሸኔም እድል ከዚህ ያለፈ እንደማይሆን ለማሳየት ነው። ለምን? ዘመቻ ግብዓተ ኢትዮጵያ ሁሉንም አካታች ነውና፣ የሁሉንም ልብ ፈትሿልና፣ ሁሉም ሰላም ፈላጊ ነውና። ማ ቀረ? የጫካው ሸኔና የብልፅግናን ሸማ የተላበሱ ጥቂት አይዟችሁ ባዮች። ዘመቻው  እነዚህን ከአፈር ለመቀላቀል ነው – መቼስ የ ፬ አመታቱ የሰላምና እርቅ ጥሪ አልመለሳቸውምና።
 
ይድረስ ለአክራርያን – ወያኔን አይመለከትም
 
ቆም ብላችሁ አስተውሉ። እስቲ ታላላቆቹን የአማራና ዖሮሞን አክራርያን በጥቅሉ፣
 
የአማራ አክራርያን ሆይ!
በመጀመርያ ቤታችሁን አጥሩት። በዖሮሚያ ብዙ የተዛቡ ጉዳዮች አሉን፣ ህይወትን የሚያክል ክቡር ገላ አዎ እንዳልሆነ ሆኗል። ያማል፣ ያስተክዛልም። ለረጅም አመታት የተሰራ ደባ ውጤት መሆኑን ግን ታውቁታላችሁ። የተዋለድኩበትና ያደኩበት የዖሮሞ ህብረተሰብ አይደለም ሰውን ለከብቶቹ የሚራራ ህዝብ ነው። ይህንንም ታውቁታላችሁ በዘመነ ወያኔ በመወለድ ካልተረገማችሁ በቀር። እባካችሁ ይህ ቅን መሪ እንደሌሎች እንኳ ከወያኔ የተቃመሰው ባለመኖሩ ትንሽ ጊዜ ስጡት። አገራችንን አስተባብሮ ይቀይራታል።
የዖሮሞው አክራርያን፣ እናንተ እንኳ ለአክራሪነትም ብቁ ሳልልሆናችሁና ተራ ነፍሰገዳዮች በመሆናችሁ በዘመቻው መልሱን ታገኛላችሁ – ሸኔዎቹን ማለቴ ነው። ዖነግማ ተረድቷል።
 
፭) ይድረስ ለዳያስፖራ ምሁራንና ሊቃውንት!
አየር ላይ የምታውሉትን ምክርና ሃሳብ ሆን ብዬ ሳየው፣ ጥቂቶች ስም ባልጠራም ታውቁታላችሁና እባካችሁ ለጋራው ቤታችን የሚበጀውን ብቻ ምከሩልኝ። አቢይ አህመድ ሊሳሳት ይችላል ፣ ከፍፁምነት እጅግ የራቀ ነው። ሆኖም በሁላችንም ላይ ሊያርፍ የሚችለውን የቅንነት ፀጋ በሱ ላይ ያረፈ ያህል ይሰማኛል። ምን ቢማሩና ቢመራመሩ ቅንነት ካልታከለበት ምንም ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ አንድ በጣም የማደንቃቸው ዶር አቢይን ለማማከር አሳይመንት ይወስዳሉ፣ ሥራቸውንም በትጋት ይጀምሩና በደንብ እያካሄዱ የአገሪቱን አቅጣጫ የሚያስቀይስ ይበጃል ያሉትን ሪፖርት ያቀርባሉ። ደጋግመውም ይሞክራሉ፣ አቢይ ግን ሪፖርቱ ደርሶት መልስ አልሰጠም አሉ። በዚህ እኒህ ጎበዝ ያኮርፉና እራሳቸውን ከሃላፊነት ያገሉና የዚህን አለመግባባት መንፈስ – ያውም በእንግሊዝኛው – ለንባብ ያውሉታል። አርስቱ ደግሞ ለትችት እንኳ የማይመች የግል ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው “ሂስ ” አይነት ሆነብኝ። ውስጡ ሳይታይ በርእሱ ብቻ የሚያስበረግግ አተያይ ሆኖብኛል በበኩሌ። እኔ የሳቸውን ቅንጣት ክህሎት የሌለኝ ሰው አቢይን ለማስተማር ሆነ ህዝባችንን ለማንቃት በእንዲህ አይነት ከማቀርብ  አፃፃፉ ቅንነትን ቢላበስ አድማጭን ሆነ አንባቢን ብዙ ያማምራል። ደግሞስ ለኢትዮጵያ ከሆነ ለምንስ ሪዛይን አስፈለገ? እስከመጨረሻው መረዳዳት እያለ? በኔ እድሜ ይሁን በመሃል ያላችሁ ወገኖቼ ወጣቶቹን ለመመለስም ሆነ አቅጣጫን ለመጠቆም ካለንበት “ከፍታ” እጅግ መውረድን ይጠይቃል ሊያውም ከፍታውን ሁላችንም ከተማመንበት ነው።  በህብረታችንም አልሆነልን እንኳንስ ተኳርፈንና እባካችሁ ብዙ ትእግስትና መቻቻልን ትፈልጋለች አገራችን።
 
ማጠቃለያ!
ባለፈው ጦርነት አንድ ቆራጥ ወታደር እንዴት ጦር ሜዳ ወርዶ ፣ ጦርሰራዊቱን አስተባብሮ ፣ ህዝባችንን አቆራኝቶ ወያኔን ባሉበት ጣቢያ እንደገተረልን አይተናል። ዳያስፖራም ሆነ ያገርቤተኛው በአንድነት ተሞ አገርን እንደታደገ ሁሉ፣ ዛሬም ሸኔን ካለበት ጉረኖ ፈልፍሎ አውጥቶ ህዝብ ፊት ማስጣት ይቻላልና ሁሉም በነቂስ ለዚህ የመጨረሻው የኢትዮጵያ ትንሣዔ ግብዓተ ኢትዮጵያ ዘመቻ እንዲነሳ በትህትና አመለክታለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ጠላት ለማስደሰት ኢትዮጵያን ማስከፋት እና ትጥቅ ማስፈታት ለምን "

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share