March 18, 2022
5 mins read

በመተሐራ ከተማ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 10 ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ

maxresdefault 6 1በዳግማዊት ዩሴፍ እና ኤደን ገብረእግዚአብሄር

በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ በመተሐራ ከተማ አልጌ ቀበሌ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች ትላንት መጋቢት 8 ምሽት በተፈጸመ ጥቃት 10 ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ። የፈንታሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፍሬዘር አበራ በበኩላቸው በጥቃቱ አምስት ሰዎች መሞታቸው እንዳረጋገጡ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው በአልጌ ቀበሌ ቀጠና አንድ፣ ቀጠና ሁለት እና ቀጠና ሶስት ተብለው በሚጠሩ ቦታዎች ላይ እንደሆነ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አምስት የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። ትላንት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት በአንድ ፑል ቤት ተሰብስበው ይጫወቱ የነበሩ ስምንት ወጣቶች መገደላቸውን ተናግረዋል። ቀሪዎቹ የጥቃቱ ሰለባዎች የተገደሉት በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ እንደሆነ አክለዋል።

በስፍራው የነበሩ አንድ የአይን እማኝ “በዚያ ሰዓት እዚያው ነበርኩ። ከፑል ቤት እንደሄድኩ ከሁለት ሶስት ደቂቃ በኋላ ተኩስ ሰማሁ። ሲተኩሱ ወደ ቤት ውስጥ ገባን። ከሄዱ በኋላ ተመልሰን ስንወጣ ሁሉም ሰው ወድቋል። ግማሹን ወደ አልጌ ጤና ጣቢያ ይዘን ሄድን” ሲሉ የነበረውን ሁኔታው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

በትላንቱ ጥቃት ከሞቱት ውስጥ አብዛኞቹ ከ18 እስከ 26 አመት በሚጠጋ የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች እንደነበሩ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል። በጥቃቱ ህይወታቸውን ካጡት ውስጥ ስድስቱ በዲግሪ እና ዲፕሎማ ተመርቀው ስራ በማፈላለግ ላይ የነበሩ ሲሆኑ ሶስቱ ደግሞ የቴክኒክ እና ሙያ ተማሪዎች እንደሆኑ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ገልጸዋል።

የዘጠኙም ሟቾች የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ አርብ መጋቢት 9 ከሰዓት በኪዳነምህረት ቤተክርስትያን በአንድ ስፍራ ላይ የተከናወነ ሲሆን የአንደኛው ሟች አስክሬን ደግሞ ወደ ወላይታ ተሸኝቷል። የአስር ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው የትላንቱን የፈጸሙት፤ “ለአካባቢው እንግዳ የሆኑ ሰዎች” እንደሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።

የፈንታሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፍሬዘር አበራ በበኩላቸው ጥቃቱን የፈጸሙት “ማንነታቸው ያልታወቀ ሽፍታዎች” እንደሆኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እስከ ዛሬ ከሰዓት ባላቸው መረጃ መሰረትም፤ በጥቃቱ አምስት ሰዎች መሞታቸውን እና በአምስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር እስከ አስር ይደርሳል ሲሉ የአስተዳዳሪውን ገለጻ ይቃረናሉ። የጥቃቱ ተጎጂዎች ዛሬ አርብ አዳማ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

ጥቃቱ የደረሰበት የመተሐራው አልጌ ቀበሌ ከተለያዩ አከባቢ የመጡ ተፈናቃዮች የሚገኙበት እንደሆነ የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ክስተቶች ሲያስተናግድ እንደቆየ ያስረዳሉ። የነዋሪዎቹን ገለጻ የሚጋሩት የፈንታሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፍሬዘር፤ ተደጋጋሚ ጥቃቶቹን በተመለከተ “ምን መስራት እንዳለባቸው፣ ምን አይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው እየተነጋገሩ” እንዳሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የትላንቱ ጥቃት መንስኤ “በህግ እየተጣራ ነው” ያሉት አስተዳዳሪው፤ ጥቃቱ ከብሔር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop