የተከበራችሁ ወገኖች
ሴቶች የማህበረሰቡ ምሰሶና ያለ እነሱ እሴት አገር የሚባለው የማይኖር፤ እናቶቻችን ፣ ልጆቻችን ፣ እህቶቻችን፣ የትዳር አጋሮቻችን፣ የስራ ባልደረቦቻችን፣ m አለቆቻችን ሲሆኑ እንደ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የአገር ርዕሰ ብሔር ወይም እንደ ቀድሞዋ ጀርመን ቻንስለር አንጄላ ሜርክል ደግሞ የተዋጣላቸው „የምዕራቡ ዓለም“ መሪ ናቸው። በተለይም አሁን ባለንበት ዓለም ሴቶች ከፍተኛ የሆነው ኢኮኖሚ ተሸካሚ ሲሆኑ፤ ሸማቾችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው። 65% የሚሆነው የመኪና ሽያጭ አሜሪካ ውስጥ በሴቶች ተፅዕኖና ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚደረግ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ለምሳሌ ቤት ሲገዛም ሲሰራ የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ነው። በአለም አቀፍ የስራ ቢሮ (ILO –International Labor Office) ዘገባ መሰረት አንዲት ኢትዮጵያዊ የገጠር ሴት በቀን እስከ 16 ሰዓት ስትሰራ 3 ኪሎሜትር በአማካይ ለውሃ ፍለጋ ትጓዛለች። ቁጥራቸው የበዛ ልጆቿ ከራሷ በበለጠ እንዲኖር ለማድረግ የምትጥረውም ከፍተኛ ትዕግስት አዘል የሆነ አስተዳደራዊ ጥበብን በማከል ነው፡ ተሰፋዋ በአብዛኛው ከሷ የተሻሉና ስታረጅ የሚደጉሟትን ልጆችን ማፍራት ነው።
ሆኖም በአገራችን በአብዛኛው “ሴት” የሚለው ቃል እንደ ደረጃ ማሳነሻ፣ አልፎም አንደ ስድብ ሲቆጠር፤ “ወንድ” የሚለው ደግሞ ከፍ ለማድረጊያ፣ እንደ ጀግንነት የሚታይበት ባህል በብዛት የተስፋፋ ነው (ሴት ያሳደገው፣ ስራው እንደሴት፣ ወዘተ)። ሴቶች እንጨት በጀርባቸው ተሸክመው ጎብጠው ሲሄዱ፣ ወንዶች ደግሞ በአህያ ላይ ጭነው ቀና ብለው የሚራመዱበት፣ ነዋሪነትን ሳይሆን ትውልድነትን መሰረት ባደረገው የማንነት መግለጫ አንድ ብዛሄነት ባለው ቤተሰብ ውስጥ ያለእናት የተፈጠር ይመስል የአባት ብሄር ብቻ ለማንነት መግለጫም የሚሰየምበት ነው።
E ከዚህ መሰል አመለካከት መላቅቅ ቀዳሚ ተግባር ነው።
E የሴቶችን በአመራር ላይ ተሳትፎ ለማስተካከል በሌሎች አገሮች እንደሚታየው የኮታ ህግ ወይም ደንብ በመንግስት ወይም በፓርላማ እስካሁን ድረስ ካልወጣ መፅደቅ አለበት። ለምሳሌ ለሴቶች 25% የአመራር ቦታዎችን በማንኛውም የመንግሥት መስሪያ ቤትም ሆነ ትልቅ ካምፓኒ እስከ 2018 እንዲተግብሩ ማለት። እዚህ ላይ ለመድረስም በየዓመቱ የመድረሻ መፈተሻ ነጥቦችን ማውጣትን ማስተግበር። እዚህ ላይ እያንዳንዱ መስሪያ ቤት የራሱ ስትራቴጂ ሊያወጣ ይችላል።
E ለምሳሌ የእድገት ጣራዎችን ለሴቶች ዝቅ ማድረግ ፣ በጡረታም ሆነ መስሪያ ቤት በሚለቁት ምትክ ለሴቶች ቅድሚያ መሰጥት፣ ልዪ የአመራር ኮርሶችን መሰጠት፣ የሜንቶሪንግ ፕሮግራሞችን መቀየስ፣ ሴቶችን የስነ ልቦና በራስ መተማመን የሚያስችሉ የመረብ ትስስርን (network) መፍጠር ።
E ሴቶች የሚሰጣቸው የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ወይም የድርጅቶች ቦታዎች ወደ ቁልፍ ሪሶርች ማምጣት አስፈላጊ ነው። የመጀመሪያ የሴት ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር፣ ጠቅላይ አቃቢ ህግ፣ የመከላከያ ሚኒስተር፣ የሴት ብሔራዊ ባንክ ገዢ በጀርመን፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ እየተለመደ የመጣ ነው፡፡ እዚህ ላይ የብዛሂትነት ማኔጅመንት በጥሩ መልኩ በመተግበር ከሴት አብራሪ ቴክኔሺያኖች እስከ አስተናጋጆችን በማቀናጀት በረራዎችን ከሚያደርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጠቃሚ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፣ 50% በሴቶች ተይዞ የነበረው የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ ካቢኔም እስከ አውሮፓ ድረስ የተደነቀም ነበር።
E በማህበራት እና በስፖርት የፌዴሬሽን አመራር ላይ በቀዳሚነት እንደ ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ፕሬዝዳንቶች ይስፈልጋሉ።
በተለይም ለሴቶች መብት እና ክብር መጠበቅ ለይስሙላ (lip service) ሳይሆን ከልባቸው የሚከራከሩ ወንዶች ያስፈልጋል። ይህም ሴቶች ለራሳቸው ከሚናገሩት የበለጠ አሳማኝና የአስተሳሰብ ለውጥ አስራጭ ይሆናል።
E ለሴቶች የሚደረጉት ፕሮግራሞችና ዓላማ መድረሻዎች ያለ ወንዶች ተሳትፎ ሊሳኩ አይችሉም፡፡ በሴቶች የመረብ ትስስር ውስጥ ወንዶች መሳተፍ ይገባቸዋል፡፡
E በ2018 በአ/አ የተካሄደው የአፍሪካ መሪ ሴቶች ጉባኤ ከወሰድን ሴቶችን በልማቱና በአመራር ደረጃ ለማብቃት የሚቻለው መድረሻ ነጥቦችና ጊዜና አህዝ የሚይሰላ ከሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ በ 4 ዓመት ጊዜ ውስጥ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይህ ቁጥር ያላቸው ሴቶችን አሰልጥኖ ለማውጣት ብሎ ማቀድ፡፡
E የሴት ልጆች ቀን (girls day) በማዘጋጀት ለሴት ልጆች ትኩረት መስጠት፣ መስሪያ ቤቶችን ማሳተፍ፡፡ (ለምሳሌ የኔ ልጅ በጀርመን ፕሬዝዳንት ቤተ መንግስት እነዚህን ቀኖች በማሳለፍ ልምድና በራስ መተማመን ቀስማለች።)
በአገራችን ሴቶች በኢንፎርሜል ሴክተር በብዛት የሚገኙ በተለይም በተለያዩ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምክንያቶች ወደ ከተማ የሚፈልሱ ናቸው። አንዱ የኢንፎርሜል ሴክተርና በአብዛኛው በችግር በመነሳት የሚተዳደሩበት የሴተኛ አዳሪነት ሴክተር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሴቶች እህቶቻችን ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ የመተዳደሪያ ገቢ ለማግኘት ገላቸውን በመሸጥ በሴተኛ አዳሪነት ላይ ይገኛሉ። ይህንን በዓለም ረጅም ጊዜ ያለውን ‹‹የንግድ ሴክተር በመከልከል፣ በማገድ፣ ማስቆም አልተቻልም። በሐይማኖትም፣ በሞራልም ማህበረሰባዊ እይታዎችን የሚቃረነው ሴተኛ አዳሪነትን አንድ መስመር ማስያዝ ተገቢና ለሴቶች ትርጉም የሚሰጥ ዘዴ ያስፈልጋል። ሴተኛ አዳሪዎች የሚሰማሩባቸው መጠጥ ቤቶች (ሆቴሎች) ማስቀረት ባይቻልም ይህንንም በተለያዩ ደንቦች መገደብ ይችላል፡፡
E እድሜያቸው ከ 18 ወይም ቢቻል ከ21 ዓመት በላይ መሆናቸውን መቆጣጠር በየዓመቱ አንድ ጊዜ ሙሉ የጤና ምርመራና የጤና መታወቂያ ማቅረብ፣ ስራቸው እንደ ስራ ስለሚታይ የገቢ ቀረጥ ማስከፈል፣
E ወሲባዊ ግንኙነቶችን ከመከላከያ ውጭ ለሚፈፅሙት ሴቶችንም በተለይ ወንዶችን በህግ መጠየቅ፤ በቅርቡ ጀርመን የወጣው ህግ በቀይ መብራት የስራ ዘርፍ ያሉ ሴቶች በተለይ ደንበኛ ወንዶች ያለ መከላከያ ግንኙነት ማድረግ እስከ 10 ሺህ ዩሮ ያስቀጣል፡፡
የሴቶች ተሳትፎ እና ማንነትን በገንቢ መልኩ የበለጠ ማስተዋወቅ በተለይም በኪነጥበቡ
E በፖስተሮች እና በፊልም ትወና ላይ የሚታዩት ሴቶች የኢትዮጵያን መልክ እና ቁመና የሚያንፀባርቁ እንዲሁም የሁሉንም ማህበረሰብ ክፍል የሚወክሉ እንጂ፣ እንደ አብዛኛው የህንድ ፊልም አንድ ወጥ የሆነ መልክ ያላቸው መሆን የለበትም። ሴቶችም የሚሰጣቸው ገጸባህሪይ በፍቅር ታሪክ፣ በወንድ ጓደኛነት ብቻ የሚወስን እና የሚያሳይ ሳይሆን፣ ታሪክ የሚሰሩበት፣ ኃላፊነት እና አመራር የሚያሳዩበት እና የሚያስተምር መሆን አለበት።
E ይህም ከኛ አልፎ በመጨረሻም በአለም አቀፍ ብቁ የሆኑ ተዋናውያንና ፊልሞችን ማውጣት ያስችላል። ካስት የሚያደርጉትም በዝምድና ወይም በትውውቅ ሳይሆን በሌላ አካል በተለይም በፈቃድ ሰጪው ክፍል በሚፈተሽ መልኩ፣ ማስታወቂያ በማውጣትና በማወዳደር መሆኑ ይኖርበታል፡፡ በኪነጥበብ የተኮተኮተ፣ ትውልድ በስራው ውጤታማ ነው።
በኢትዮጵያ ስለ አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የወጣው አዋጅ ሴቶች በፆታቸው ምክንያት በማንኛውም ሁኔታ ልዩነት እንደማይደረግባቸው፣ የነፍሰጡር ሴቶች የምሽት ስራ እና እንዲሁም የትርፍ ሰዓት ማሰራት መከልከልን እና የ፴ የሥራ ቀናት የቅድመ-ወሊድ ፈቃድ እና ፺ የሥራ ቀናት የድህረ-ወሊድ ፈቃድን መፍቀዱ በእጅጉ የሚደገፍ ነው።
E ቢሆንም ተጨማሪ የተቀጣሪ እናቶችን መብት በሚጠብቅ መልኩ ሊሻሻል ወይም ህግ ሊወጣ ይገባል። ለምሳሌ በድህረ-ወሊድ እስከ አንድ ዓመት ቤት መቆየት እንዲችሉና ተመልሰው ወደ ስራ ገበታ ሲመጡም ስራቸውን ማግኝት እንዲችሉ ወይም የተቀነሰ የስራ ሰዓት መስራት እንዲችሉ መደንገግ። አንድ እናት መስራት ከፈለገች አባት „የድህረ-ወሊድ የአባትነት“ ፈቃድ በአንድ ዓመት ወስጥ በማግኝት እናት ስራ ከሄደች በፈርቃ ልጆችን የሚንከባከቡበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት።
ለመደምደም ዓለማቀፍ የሴቶች ቀን በጀርመን በርሊን ስራ ዝግ የሚሆንበት ዓመት በዓል ነው። ጀርመናዊቷን ክላራ ዜትኪን ማርች 8 የሴቶች ቀን እንዲሆን ስላደረገች በታሪክ ስትዘከር ትኖራለች፣ የአሷ እይነት ኢትዮጵያውያን ሴቶችን በዚህ ቀን እናስታውሳቸው።
መልካም ማርች 8
ነፃነት ስንል ሁል ጊዜ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎችን ነፃነት ነው።
– ሮዛ ሉክሰንቡርግ
ከመልካም የጤንነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)