የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽኝ መፍረስ የለበትም! – ገለታው ዘለቀ

በሃገራት ህይወት ውስጥ ተራራም ሸለቆም አለ። መውጣት መውረድም፣ ከፍታም ዝቅታም አለ። ታዲያ በዚህ ምክንያት የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ሃገራት በተለይ የውስጥ ሰላም ማጣት ሲያናውጣቸው ወይም ያለፈ የታሪክ ግድፈት ሲንከባለል መጥቶ የዛሬውን ህይወት ሲበጠብጥባቸው፣ የሰላም፣ የዕርቅ ኮሚሽን እያቋቋሙ ችግሮቻቸውን እየፈቱ ለመሄድ ይሞክራሉ። ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ ሌሎች ሃገራት ሁሉ በዚህ ኮሚሽን እየታገዙ እርቅ ለማምጣት ሰርተዋል። በአለም ላይ ቢያንስ ሃምሳ የሚሆኑ ሃገራት የገጠማቸውን ቀውስ ለመፍታት የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን መስርተው ታግለዋል። አንዳንዶቹ ሃገራት የተሳካ ስራ ሲሰሩ ከዚህ ኮሚሽን ብዙም ያላተረፉም አሉ። ቀጥተኛም ባይሆን ተዘዋዋሪ ትርፎችን ብዙዎቹ ያስመዘግባሉ ተብሎ ይገመታል።

ወደ ሃገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ ዶክተር አብይ ስልጣን ሲይዙ የብዙዎች ተስፋ የነበረው ለውጡ በተለያዩ ኮሚሽኖች፣ በምሁራን፣ በፓርቲዎች፣ በህዝቡ ታግዞ የሽግግር ስራ እናያለን የሚል ነበር። ይሁን እንጂ ባለፉት አራት አመታት ግድም ሃገራችን አይታ በማታውቀው ግጭትና ጦርነት፣ የመፈናቀል ችግሮች ውስጥ አልፋለች፤ አሁንም መከራ እያየች ነው። ታዲያ እንዲህ ላለች ሃገር የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን በመርህ ደረጃ እጅግ አስፈላጊ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን መቋቋሙን በሚመለከት ቅሬታ የሚኖረው ሃይል ይኖራል ብየ አላምንም። ሁሉም ሃይል ሃገሪቱ ሰላምና እርቅ እንደሚያስፈልጋት ያምናል፣ የእርቅና ሰላም ኮሚሽን ሊኖራት ይገባል ብሎ ያምናል ብየ አስባለሁ። ችግሩ የተፈጠረው ይህ ኮሚሽን ሲቋቋም ጀምሮ ለፍሬ እንዳይሆን እንዳይሆን ተደርጎ መተከሉ ነበር።

የእርቅና ሽምግልና ማእከል ሲቋቋም መጀመሪያ በትኩረት ሊሰራበት ይገባ የነበረው ነገር ኮሚሽነሮቹና አባላቱ ገለልተኛ እንዲሆኑ ማድረጉ ላይ ነበር። የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ሲቋቋም እጅግ ብዙዎቹ አባላት የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ናቸው። ይህ ችግር  ኮሚሽኑ ፍሬ ሳያፈራ በአጭር እንዲቀጭ ካደረጉት ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ኮሚሽኑ ሶስት አመት ሙሉ በፓርላማውም ሆነ በሚመለከተው ክፍል ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ አልተደረገለትም ነበር። ስለሆነም ስንት የሚታረቅ ሃይል እያለ አንድም ሰው ሳያስታርቅ፣ ስንት ግፍ በሞላባት ምድር የአንድም አካል እምባ ሳያብስ እነሆ ፈረሰ እየተባለ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከሰማያዊ ፓርቲ የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ለሚዲያ ማህበረሰቡ የተላለፈ ጥሪ

መልካም። ኮሚሽኑ ከክትትልና ከአተካከል ችግር የተነሳ ፍሬ ሳያፈራ ቆየ። ነገር ግን ይህንን ኮሚሽን ማፍረስ ነው የሚሻለው ወይስ ማነጽ? የሚለው ላይ ትንሽ አስተያየት ለመስጠት ነው የዛሬው አነሳሴ።

እውነት ነው ይህ ኮሚሽን የረባ ስራ ሳይሰራ ዝም ብሎ የድሆችን ቀረጥ ሲያከስር መቆየቱ ያሳፍራል። ነገር ግን ይህ ችግር የራሱ የኮሚሽኑ ብቻ ሳይሆን የፓርላማውና የጠቅላይ ሚንስትሩ በአጠቃላይ የሚመለከተው ሁሉ ነው። ነገር ግን እንደ እኔ የገጠመንን ይህንን ችግር መፍታት ያለብን ኮሚሽኑን በማፍረስ ሳይሆን እንደገና አስተካክሎ በመትከል ነው።ማፍረስ አይገባም። የእርቅ ኮሚሽን ሰዎች ሃላፊነታቸውን አልተወጡም ማለት የእርቅ ኮሚሽንን ሁለተኛ ባይናችን አያሳየን ወደሚል ድምዳሜ ሊወስደን አይችልም። ኮሚሽነሮች ሃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል ኮሚሽን አይዘጋም። ገና ብዙ አመታት ሊቆይ የሚገባው ተቋም ነውና። ገለልተኛ የሆኑ ሰዎችንና ብቃት ያላቸውን ሰዎች በመምረጥ ይህንን ኮሚሽን እንዲቀጥል ማድረግ ነው እንጂ ኮሚሽኑን ማፍረስ በኢትዮጵያ ውስጥ እርቅ አይሰራም እንደማለት ነው። ወደፊትም ለትውልድ ጥሎት የሚያልፈው ትምህርትም የሚያኮራ አይሆንም።

ሌላው መሰረታዊ ጉዳይ የዚህን ኮሚሽን ስራ አሁን የተቋቋመው የምክክር ኮሚሽን ሊሰራው  አይችልም። ምክክሩ ተሳክቶ ቢራመድ እንኳን በተለይ የተበደሉን ለመካስ፣ እውነትን ለማፈላለግ፣ ከመግባባት ባሻገር ለሚኖረው የነፍስ ጽዳትና እርቅ፣ ሪስቶሬቲቭ ፍትህንና ሪትሪቢዩቲቭ የፍትህ እሰራሮችን እየተጠቀመ እንዲሰራ ይህ ተቋም የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። ይህ ኮሚሽን ለሃገራዊ መግባባት ትልቅ አጋዥ መሳሪያ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ከሚያስፈልጉዋት ዋና ዋና ተቋማት መካከል አንዱ የእርቅ ኮሚሽን ነውና ይህንን ተቋም እንደገና ነፍስ ዘርቶ ማቋቋም ይገባል። የእርቅ ኮሚሽን የሚፈርሰው ሃገር ስታምጥ ችግር ላይ ባለችበት ሰዐት ላይ ሳይሆን እረፍት ሲሰማት ዘና ስትል ነው። ኮሚሽኑን እንደገና በገለልተኛ ሰዎች ገንብቶ አዲስ ሃይል አስታጥቆ መቀጠል እንጂ ማፍረስ ተገቢ አይደለም። ፓርላማው ይህንን ማየት አለበት ። ተቃዋሚ ሃይሉም ይህንን ኮሚሽን በማቋቋሙ ረገድ ተሳታፊ ሆኖ ኮሚሽኑ እንዲቀጥል መደረግ አለበት ብሎ ሊታገል ይገባል ብየ አምናለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:   ከመሠረታዊው የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ የመንሸራተት አዙሪትና ውጤቱ - ጠገናው ጎሹ

ከፍ ሲል እንዳልኩት የምክክር ኮሚሽኑን ተፈጥሮ በሚገባ መረዳት አለብን። ከምክክር የሚመረቱ ሃሳቦች ተግባር ላይ ይውሉ ዘንድ ተቋማት መሳሪያ ናቸው። የብሄራዊ እርቅና ሰላም ኮሚሽን ዋና ደጋፊ ሃይል ነውና እንደገና እንዲመሰረት ያስፈልጋል። ዋናው ጉዳይ ግን ገለልተኛና ብቃት ባላቸው ሰዎች መመራቱ ላይ ነው መነጋገር ያለብን።

ይህ ኮሚሽን መፍረሱ የሚያመጣው የስነ ልቡና ችግር እንዳለም ማሰብ ያስፈልጋል። በእርቅና በሰላም ተስፋ የቆረጥን ህዝብ አይነት ስሜት ያመጣል። ስለዚህ ኮሚሽኑ እንደገና በሁሉም ሃይሎች ተሳትፎ ይጽና። ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ይዋቀር እንጂ አናፍርስ።  ኢትዮጵያውያን ሁል ጊዜም ለእርቅና ለሰላም ትልቅ ክብር እለን።

 

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ።

1 Comment

  1. ገለታው ብሄራዊ እርቁን ያመጣሉ የተባሉት የኮሚቴው አባላት ናቸው እነዚህ ሰዎች ማንና ለምን አላማ እንደተመረጡ የሚያውቁት አብይ መሀመድ፣ ሌንጮ ለታ ፣ሽመልስ አብዲሳና ደብረጽዮን ናቸው ።በዚህ ላይ ሆን ተብሎ ያልተወከለ የህብረተሰብ አካል አለ። ይህንና ያልተባሉትን ነገሮች ስናካትት የቃላት ገመድ ጉተታና የዘረኞችን የጥፋት ጥም ለማርካት ካልሆነ ለሀገር አንድነት ብዙም የሚፈይድ አይመስልም።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share