የካቲት 7 ቀን 2014 ዓም (01-03-2022)
መቼም አይጥን ያህል ደካማ ነገር ካላበደች በስተቀር የምትፈራውን የግዙፉን ድመት አፍንጫ ልማታ ብላ አትነሳም።ድመት እንኳንስ ባጠገቧ ቀርቦ ገና ከሩቅ ድምጹንና ኮቴውን የሰማች አቅሟን የምታውቅ አይጥ የምትገባበት ቀዳዳ እንደሚጠፋት የታወቀ ነው።ታዲያ የአይጥ ወኔና ለድመት ያላት ፍርሃት ይህ ሆኖ ሳለ ቀልቧን የሳተች አይጥ በኩራት የሚንጎባለለውን ትዕግስተኛ ድመት ልፈታተን ብላ ቀይ መስመሩን አልፋ አፍንጫውን መንካት ቀርቶ ባጠገቡ ሽርጉድ ልበል ካለች የመጨረሻ እጣፈንታዋ ጅራቷ ሳይቀር የድመቱ አስቤዛ መሆን ነው።ቁርጥምጥም አርጎ ይበላታል።
እንደዚች አቅሟን ያላወቀች ደቃቃ አይጥ የሚያደርጋቸው የሰው ልጆችም አሉ። አገሮችም አሉ። ትዕግስትና ይሉኝታ ብሎም ጨዋነት አስገድዶት ዝም ያለውን ሰው ወይም ማህበረሰብ እዬኮረኮሩ ግልፍተኛ ለማድረግ የሚሞክሩ በዓለማችን ብሎም በአገራችን በኢትዮጵያ እዬታዘብን ነው።
በዓለማችን የምናዬው የሰሞኑ የዩክሬንና የሩስያ ጦርነት በአይጧና በድመቱ ይመሰላል። መነሻ ሰበቡ የሳምንት ዕድሜ ብቻ ያለው ሳይሆን፣ ዓመታት ያስቆጠረ ነው።የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት ከሰላሳ ዓመት በፊት በገጠማት ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያት የነበራት ክብርና ግዙፍነት በምዕራባውያን በተለይም በአሜሪካ አሻጥር ተሸርሽሮ አቅሟ በተዳከመ ጊዜ የተወለደ ነው። ኡክሬን አንዷ የሶቪዬት ክፍለሃገር ሆና ሕዝቧም የሶቪዬት ሕብረት ዜጋ ሆኖ ለዘመናት የኖረች መሆኑ አይካድም።ከሰላሳ ዓመት በፊት የተፈጠረው አገር የማተራመስና የሶቪዬት ሕብረትን የማፈራረስ ሴራ ይህንን አንድነት በማናጋት የሶቪዬት ህብረት ሩስያ በሚለው የቀድሞ መጠሪያዋና ድንበሯ ስትመለስ፣ ኡክሬን እንደተቀሩት የሶቪዬት ግዛቶች ተገንጥላ የራሷን መንግሥት ለመመስረት ዕድል አገኘች።
የምዕራባውያን ሴራ በዚህ ብቻ አልቆመም ፤የተገነጠሉትን አገራት ኔቶና የአውሮፓ ሕብረት በሚባሉ አሜሪካ በምትነዳቸው ድርጅቶች ስር በማሰባሰብ ጸረ ሩስያ የሆነ ትግላቸውን አጧጧፉት።ከፖለቲካው ባሻገር በኤኮኖሚ የምትደቅበትን አሻጥር ተያያዙት።በዚህ ያልተንበረከከችው ሩስያ የተዳከመ ሃይሏን ሰብስባና በበለጠ አደራጅታ በኤኮኖሚውም ዘርፍ እድገት እያሳዬች የሌሎቹን አገራት እምነትና ከበሬታ መልሳ ለማግኘት ቻለች።ለዚህ ትንሳኤዋ ያበቃት አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የቪላድሚር ፑቲን አገር ወዳድነትና ያቋቋመው መንግሥት ነው። የሕዝቡ ኑሮም በመሻሻሉ ከ70% በላይ የሚሆነው የፑትንን አመራር የሚደግፍ ነው።በውስጥ በዴሞክራሲ ስም ውርውር የሚሉ የምዕራባውያኑ ደጋፊዎችና ተላላኪዎች ባይጠፉም የድመት አፍንጫ እንደምታሸተው አይጥ የሚገቡበት ጉድጓድ ጠቧቸው፤ግማሹ ለስደት ግማሹ ለእስራት ተዳርገዋል።የሩስያን መፈረካከስ ተከትሎ ያገሪቱን ሃብት ከምዕራባውያን ጋር ሲቦጫጨቁ የነበሩት የሌባ ሰንሰለት የዘረጋው ኦሊጋርኪ ቡድንም የሥራውን አግኝቷል።የእስራት ቅጣቱን የፈጸመው ሲቀር ሌላው የሰረቀውን ሃብት ተነጥቆ በዬአውሮፓ አገራትና አሜሪካ እግሬ አውጭኝ ብሎ ፈረጠጠ።
በፑቲን የምትመራው ሩስያ በዓለም አቀፍ መድረክ እንደገና ድምጿ ተሰሚ ሆነ።በመከላከያና በጦር መሣሪያ እራሷን ከመቻል አልፋ ለሌሎቹም የምትበቃ ሆነች።በሌላውም የቴክኒዎሎጂ መስክ ላይ ከምዕራባውያን እኩል በሚባል አለያም በበለጠ ደረጃ ላይ ደረሰች።ይህ ሁሉ እድገትና መሻሻል የምዕራቡን ተሰሚነትና ተቀባይነት እዬቦረቦረው ስለመጣ እንቅልፍ ነሳቸው። የሚያደርጉትን አሳጣቸው።ቀላል የማጥቃት ስልት አድርገው የወሰዱት የሩስያ አጎራባች የሆኑትን አገራት በጸረ ሩስያነት መቀስቀስና በግዛታቸው የኔቶን ጦር ማስፈር ነው።የኔቶና የአውሮፓ ህብረት አባል ያልሆነችው ኡክሬንን የአባልነት ካርድ እያሳዩ እንቁልጭልጭሽ እያሉ ከሳት ጫሪነት አልፋ የእሳቱ ሲሳይ አመድ ለመሆን የምትችልበትን ጦርነት እንድትቀሰቅስ ተመከረች፤የጅል መልእክተኛ ሆና ሩስያን ተፈታተነቻት። የበቀል ምላሹ ግን ከምትችለውና ሌሎቹም ከጠበቁት በላይ ሆነ።አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታለች ማለት ይህ ነው።
ትዕግስቱ ያለቀው ቭላድሚር ፑቲን የጦሩን 1/00 በማንቀሳቀስ ኡክሬንን ከያቅጣጫው መግረፍ ጀመረ።ንጹሃን የኡክሬን ዜጎች የጥቃቱ ሰለባ ሆነው ብዙዎች ሞቱ ፣በሚሊዮን የሚቆጠሩትም ህጻናት፣አዛውንትና ሴቶች ጎረምሳም ሳይቀር ከቤታቸው ወጥተው በማያቁት አቅጣጫ ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዱ። እንኳንስ ስደተኛ የራሳቸውንም ሕዝብ በቅጡ መያዝ ያልቻሉት አገራት ለተጨማሪ ችግርና ፈተና ተጋለጡ።የጦርነቱ ቆስቋሽ የሆኑት ምዕራባውያንና አሜሪካ የኡክሬን ሕዝብ ብቻውን እንዲጋፈጥ ፈረዱበት።በሩስያ ላይ ማዕቀብ ከማዥጎድጎድና የጦር መሳሪያ ከማቀበል ፣አሮጌ ልብስና ምግብ ከሕዝብ ሰብስቦ ከመስጠት ሌላ ሩስያን ሊዋጉ አልደፈሩም።ሆምጨው ፑቲን ያገሬን ድንበር ብታልፉ ወይም በጦር እናንበረክካለን ብትሉ አመድ ትሆናላችሁ ብሎ የኑክሌር ቁልፏን አሳያቸው።ብርክ ዋጣቸው።እንዲያ ነው ላመነበት የሚቆም ቆራጥ መሪ ማለት።የኡክሬኑ መሪ ዘሌንስኪ ድረሱልኝ እያለ ቢጮህም ብቻህን ተወጣው ከሚል የተለዬ አለንልህ! መጣንልህ! የሚል ጠፋ።ሳይወድ በግድም ለመደራደር ፈቃደኛ ሆነ።ውጤቱ ባይታወቅም በሩስያ ፍላጎት እንደሚጠናቀቅ ምልክት እዬታዩ ነው።
ፑቲን ከስህተት የጸዳ ነው ባይባልም፣ብዙ ድክመት ቢኖርበትም የአገርን ልዑልና በማስከበሩ በኩል የዘመናችን ወይም የሩስያ ምኒሊክ ቢባል አይበዛበትም።የዓለም ሕዝብ ከዚህ ሊቀስም የሚችለው ትምህርት የአሜሪካንንና የምዕራቡን መንግሥታት አምኖ ገደል ላለመግባት ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲያስብበት ነው።እነሱ የጫሩት እሳት አገራትን እንዳፈራረሰ ፣ከኢራቅ፣ከሊቢያ፣ከሶሪያ፣ከአፍጋኒስታን አሁንም ከኡክሬን የበለጠ ማስረጃ የለም።ለኡክሬንም ሆነ ለሌሎቹ አገራት የሚበጀው ከጎረቤት አገር ጋር በሰላም ተከባብሮ መኖሩ ነው።የሌሎች ተላላኪ መሆን መዘዙ ብዙ ነው።የምዕራቡ አገራት የተዘፈቁበትን የራሳቸውን ችግር እንኳን ሊወጡት አልቻሉም።የራሳቸው ሕዝብ በኑሮ ውድነት ተዘፍቆ፣በቤት እጦት ተማሮ በሚጮህበት ጊዜ ለሌላው ይተርፋሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።የሚያደርጉት ዘጥ ዘጥ ከትንሽ ጊዜ አያልፍም።ቋሚ ችግሩን ተሸክሞ የሚቀረው ገፋፍተው ለመከራ የሚማግዱት አገርና ሕዝብ ነው።የምዕራባውያን የጦር መሣሪያ ፋብሪካዎች ይህንን እንደ ትልቅ አጋጣሚ በመቁጠር ምርታቸውን የሚያስተዋውቁበትና የሚሸጡበት ዕድል ሆኖላቸዋል።የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካውም ጦrn,ቱን የዳቦ ቅርጫት አድርጎታል።ር የኡክሬንን ባንዲራ እዩሸጠ ለገበያ በማቅረብ ላይ ነው።ያንዱ ሞት ለሌላው ህይወት ይሏል ይህ ነው።የአውሮፓ ሕዝብ በሚነገረው ፕሮፓጋንዳ ተወናብዶ የዕዳው ተሸካሚ ሆኗል።የሁሉም ነገር ዋጋ ጨምሮበታል።ከዓመታት በፊት በርካሽ ዋጋ ተገዝቶ በማጠራቀሚያ(ዴፖ) የተቀመጠ ነዳጅ በአሁኑ ከፍተኛ ዋጋ ይሸጥለታል። ሌላውም ሸቀጣ ሸቀጥ እንዲሁ።ለችግሩ ተጠያቂ የሆነውን መንግሥቱን በመደገፍ ሩስያንና መሪውን ቪላድሚር ፑቲንን ተጠያቂ አድርጎ አደባባይ ወጥቶ ይወቅሳል።ነገ ሲገለጽለት ተቃውሞውን በመሪዎቹ ላይ ያዞራል።የቬትናም፣የደቡብ አፍሪካና የሌሎቹም አገሮች የጦርነት ታሪክ የሚነግረን ይህንኑ ነው።
ኡክሬን ሆይ አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታለች የሚለውን አባባል ከልብሽ ውሰጂውና ከዝሆኗ ሩስያ ጋር በሰላም ለመኖር ከገባሽበት የተላላኪ ጦርነት ውጭ።ሕዝብሽንም ከስደት ሰብስቢ።
ወደ አገራችን ፊታችንን ስንመልስ ያይጧንና የድመቷን ታሪክ የሚያሳዬን በእብደትና በትእቢት የተወጠረው ኦነግ መራሹ መንግሥት በትልቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚያደርገው ድፍረት ነው።ላለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ያገሪቱና የሕዝቡ እሴቶች፣ታሪኮችና ባሕሎች ላይ የማጥፋት ዘመቻ ሲደረግ ቆይቷል።ከነገ ዛሬ አደብ ይገዛል ብሎ በትእግስት የተቀመጠውን ሕዝብ በድንና ፈሪ አድርጎ በመቁጠር እዬተፈታተነው ነው፤ድፍረቱ ጣራ ነክቷል።አገር የማፍረስ ዓላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱት በትንሿ አይጥ የሚመሰሉት ቡድኖች ከቀን ወደ ቀን የሚፈጽሙት ጥፋት የሚያሳብድ መርዝ የላሰች አይጥ አድርጓቸዋል፣ከአቅማቸው በላይ እዬተወራጩ ነው።ሲወራጩ ደግሞ የሚያደርሱት ስብራት ቀላል አይሆንም። ለቃሙት ጸረ ኢትዮጵያ መርዝ ማርከሻ መድሃኒት በጊዜው ሊሰጣቸው ይገባል።
ያልተደራጀውን ሕዝብ አጭበርብረው ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ የፈጸሙት ክህደት ቁጥር ስፍር የለውም።አሁን ግን በቃችሁ ሊባሉ ይገባል።የድፍረታቸው ድፍረት ለኢትዮጵያኑ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ሕዝብ ነጻነት ፋና ወጊ የሆነው የአድዋ ድል መታሰቢያ የ126 ዓመት ክብረ በዓል ከድሉ ከሰባተኛው ዓመት ጀምሮ ላለፉት119 ዓመታት ሲከበርበት ከኖረው የዳግማዊ ምንሊክ አደባባይ ታግዶ አድዋ ድልድይ በተባለው ቦታ እንዲከበር ለማድረግ ጸረ አማራ፣ጸረ ምኒሊክና ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ባለው የኦነግ ባለሥልጣን በቀጀላ መርዳሳ ትዕዛዝ ተወስኗል።ይህ ሰው ከቅርብ ጊዜ በፊት “ኦሮሞን የጨፈጨፈው አማራና ምንሊክ ነው” በማለት በሚዲያ የተናገረ ጭፍን ኦነጋዊ ነው።ይህንን ያለ ሰው ለምንሊክና ለዓድዋ የድል በዓል ክብር ይኖረዋል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።ስለ ሰንደቅ አላማችንም ቢጫው ቀለም የኦርቶዶክስ ምልክት ነው ብሏል።በራሱ የኦነግ ባንዲራ ላይ ያለውን ቢጫ ቀለም ግን ሌላ ትርጉም የሰጠ ሃፍረተ ቢስ ነው።ስልጣን ከተሰጠው በዃላ የሚጠላውን የኢትዮጵያ ልሙጡን ሰንደቅ ዓላማ ፣አረንጓዴ ቢጫና ቀይ እያንገሸገሸውም ቢሆን ሲውለበለብ ለማዬት ተገዷል።እሱም ባላንባሻውንም ቢሆን ጨብጦ አውለብልቧል በቢሮውም ጠረጴዛ ላይ አስቀምጧል።
የበዓሉን አከባበር በተመለከተ የተላለፈው ትዕዛዝ የቀጀላ መርዳሳ ብቻ ሳይሆን የኦነጉ መሪ የአብይ አህመድና የጠቅላላው ኦሮሙማ ቡድን ውሳኔ ነው።ይህ ቡድን በሚመራው የብልጽግና ተብዬው የስራአስፈጻሚ ስብሰባ ውሳኔም የአዲስ አበባ ከተማ ስም ፊንፊኔ እንዲሆን ወስኗል።ሕገመንግሥቱና ባለ አምባሻው ባንዲራም እንደማይቀዬር አቋም ይዟል።
የአድዋ ድል መከበሪያ ቦታ መለወጥን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም የአዲስ አበባ ነዋሪ ከዳር እስከዳር ተቃውሞውን እዬገለጸ ይገኛል።የሕዝቡ ተቃውሞ ያስደነገጣቸው ኦነጋውያን የሚሉት ጠፍቷቸዋል።የስርዓቱ አካል የሆኑትም ባለሥልጣኖች ተቃውሞ እያሰሙ ነው።አንዳንዶቹም ብቅ እያሉ የተላለፈውን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ካለማቅረብ የተነሳ የመጣ ችግር ነው፤በዓሉ በተለመደው ቦታ ላይ ተጀምሮ በቀጣይ በአድዋ ድልድይ ይከበራል የሚል ማስተባበያ ሰጥተዋል።ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው ነውና ለተመረረ ሕዝብ ቁጣ መለሳለሱ አጥጋቢ መልስ ይሆናል ተብሎ አይገመትም፤ ሊሆንም አይችልም። ትግሉ ከአድዋ በዓል መከበር ቦታ በላይ ነው።ትግሉ በአንድ ጠባብ ቦታ፣በአድዋ አደባባይ ላይ ያተኮረና የተወሰነ ብቻ አይደለም። ትግሉ ኢትዮጵያን የማስቀጠልና አንድነቷን የማስከበር ትግል ነው።እስከድል ድረስ መቀጠል አለበት።
በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን የወልቃይትንና የራያና አዘቦንም መሬት ለወያኔ አሳልፎ ለመስጠት ካለው ፍላጎት እንቅፋት ይሆናሉ ያላቸውን የአማራውን ልዩ ሃይል ፋኖና፣የሚቃወሙትን ሁሉ ለማጥፋት እዬተንቀሳቀሰ ይገኛል።ይህ የጸረ ኢትዮጵያ የኦነጎች መራሹ እርምጃ በአጭሩ ካልተቀጨ ኢትዮጵያ የምትባል አገር መኖሯ ያጠራጥራል። ቀስ በቀስ እያለማመዱ የሚመዙት የነገር ገመድ ኢትዮጵያን ወደ መቃብሯ እዬጎተታት ነው።የኦነጎችና ተከታዮቻቸው ድፍረት ትንሿ አይጥ ትልቋን ድመት የመተናኮል ያህል ነው።የትልቋ ኢትዮጵያ ባለቤት የሆነው ዜጋ ተባብሮ የአይጧንና አጫፋሪዎቿን በጥባጭ ድርጊት እስከወዲያኛው ማምከን ይኖርበታል።ትእግስትም መጠንና መስመር አለው።እንደ ትናንቱ ዳግማዊ ምንሊክ፣እንደዛሬው እንደ ሩስያው መሪ ቪላድሚር ፑቲን ቆፍጠን ማለት ያስፈልጋል።ሃይልን አሰባስቦ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለሚፈታተኑ ሁሉ መቀጣጫ ማድረግ ተገቢ ነው።
ሕዝብ ያሸንፋል፣ የጎሰኞች ሴራ ይከሽፋል!
ኢትዮጵያ በነጻነትና በአንድነት ለዘላለም ትኑር!!
አገሬ አዲስ