አገረቢሱ ባለአገር – በገዛ አገሩ የመኖር መብቱ ተገፎ (አገሬ አዲስ)

15-06-2014  (22-02-2022)    በ አገሬ አዲስ

ባለንበት ዘመንና በሰለጠነው ዓለም አገር እያለው አገረቢስ መሆን ግራ ከማጋባቱም በላይ ይሆናል ተብሎ የማይጠበቅ ነው።ባልተወለደበትም ሆነ ጭራሽ በማያውቀው፣ ለቤተሰቡም እንግዳና ባዳ በሆነ አገር በስደትም ሆነ በሥራ ወይም በትምህርትም ሆነ በጋብቻ መብቱ ተከብሮ መኖር በተለመደበት ዘመን የሰው ልጅ  በገዛ አገሩ የመኖር መብቱ ተገፎ፣ ማንነቱ ተረግጦ ከተወለደበትና ከኖረበት ቀዬ ሲፈናቀል፣ሲገደል፣ሲዘረፍ ማዬቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ ሆኗል።

በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከአንዱ ቦታ ወደሌላ ቦታ ሄዶ መኖር የተለመደና ከአፈጣጠሩ ጋር አብሮት የኖረው ልማዱ ነው።  የተፈጥሮ ጸባይ ሲዛነፍ፣ጎርፍና ድርቅ ሲከሰት ፣በእሳተገሞራ ሲወድም፣ በጦርነት ሰላም ሲያጣ፣ አለያም በሰላማዊ የእራስ ፍላጎትና ምርጫ፣ ለኑሮዬ ይስማማኛል፣ ወይም የተሻለ ኑሮ ልኖር እችላለሁ በማለት ወደመረጠው ቦታ የተወለደበትንና  የኖረበትን ቦታ ለቆ ወደሌላው ቦታ ለመሄድ ወይም ለመፍለስ ይገደዳል።

የሰው ልጅ ከአንዱ ወደሌላው ቦታ የሚሄደው ወዶ ወይም በላይ በተገለጹት ምክንያቶች ተገዶ ነው። በዓለም ላይ የከተማዎችን መስፋፋትና ማደግ ተከትሎ በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች የገጠሩን ነዋሪ ከተወለደበት ቦታ እንዲፈልስ አድርጎታል።የዓለም ግማሹ የሚሆነው የከተማ ነዋሪ ሕዝብ በአስገዳጅ ሁኔታ ወይም በፈቃደኝነትና በራስ ውሳኔ ከከተማ እድገትም አንጻር  ከገጠር ፈልሶ ወይም ፈልሰው ከመጡ ቤተሰቦች ተወልዶ ከተሜ የሆነ ነው።የተሻለ ሥራ መፈጠር በተለይም ለወጣቱ ከከባዱ የገጠር ኑሮ የማምለጫ አንዱና ዋናው ምክንያት ነው፤ሌላው ምክንያት ሰው ከተማ የሚገባው ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ብቻም ሳይሆን የሕግ ተቋማት በመኖራቸው አንጻራዊ ሰላም አገኛለሁ በማለት ነው።ገጠሩ ከሕግ ቁጥጥር የራቀ በመሆኑ የሽፍታዎችና የዘራፊዎች ሰለባ የመሆኑ ዕድል ከፍተኛ ስለሆነ ከዚያ ለመዳን የገጠሩ ነዋሪ ፊቱን ወደ ከተማ ያዞራል።ይህንን ተፈጥሮያዊ ውሳኔ እንስሳትና አእዋፎችም ይጋሩታል። ወቅት እያዩ ለሕይወታቸው አsf,ላጊውን ለማግኘት ሲሉ ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ቦታ መብረርና መጓዛቸው የሚታይና የተለመደ የዬወቅቱ ክስተት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ነበዴ(ሰላም) ሱማሌ ! (አስቻለው ከበደ አበበ-ሜትሮ ቫንኩቨር፣ ካናዳ)

ወደ አርእስቱ ስንመለስ የአንድ አገር ሕዝብ ከአንዱ ወደሌላው የአገሩ ክፍል ሄዶ የመኖር መብቱ የሚረጋገጥለት ሕግ መኖሩ ሲሆን ያንን ያላካተተና በተግባር ያልተረጎመ መንግሥት ያለው  አገር ደግሞ በአገር ደረጃ ለሕዝብ የቆመ ነው ተብሎ አይመደብም።አገር የሁሉም ዜጋ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ዜጋ ከፈለገበት ቦታ ሄዶ የመኖር፣የመሥራትና ሃብት የማፍራት መብት አለው።የዓለም አቀፉም ማህበረሰብ አንድ ሰው በሚኖርበት አገር ውስጥ መብትና ነጻነቱ እንዲከበርለት የሚያስገድድ ዓለም አቀፍ ሕግ አለው።የትም ቦታ ቢሆን የሰው ልጅ ሰብአዊ መብቱ በተለይም የመኖር መብቱ በማንም ሊጣስ እንደማይገባ አገራት ተቀብለው የፈረሙት ሕግ ያስገድዳቸዋል።በሕገወጥ መንገድም ድንበር ጥሶ የገባም ቢሆን በአግባቡ በሕጋዊ  ተይዞ ችግሩ ይታይለታል እንጂ በሃይል ሰብአዊ ክብሩን በሚያዋርድ መልኩ ማዋረድ አይፈቀድም፣ለዚያም የቆሙ የሕግ ባለሙያዎችና የሕግ አንቀጾች በዬአገራቱ ሕገመንግሥት ጉልህ ቦታና እውና ተሰጥቷቸው ለብዙዎቹ  መብት መታደግ ምክንያት ሆነዋል።ይህ ንግዲህ የአንድ አገር ተወላጅ ወይም ዜጋ ወደ ሌላ አገር ሄዶ ለመኖር የሚያስችለው የሕግ  አሠራር ሲሆን በተወለደበት አገር ደግሞ  በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት  በሚቆጣጠረው አገር ዜጋው  የትም ቦታ ቢሆን የመኖር መብቱን የሚያስከብርለትና የሚንከባከበው ሕግ ሊኖር ይገባል።ሌላው ቀርቶ በውጭ አገር ዜጋው መብቱን ሲገፈፍ ለማስከበር ሃላፊነት አለበት። ይህ ዓለም አቀፋዊ ሕግ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከምን ድረስ ይሠራል ብለን ብንመረምር የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን።

ከሃምሳ ዓመት ወዲህ የተከሰቱትን ብቻ ብንመለከት የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግርና የተፈጥሮ አደጋ ከቀዬው ሲያባርረው እግሩ እንደመራው መሰደዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በ1965 ዓም በድርቅ ምክንያት የትግራይና የወሎ ሕዝብ ሲራብ ብዙ ሕዝብ መሞቱ አይዘነጋም።ከሞት የተረፈው እግሩ እንደመራው በያቅጣጫው ተሰዷል።ችግሩን ለመቋቋም የተሳነው መንግሥት ለክብሩ ሲል  የርሃቡ ዜና ወደውጭ እንዳይወጣ፣በተለይም የአፍሪካ አንድነት ስብሰባ የሚካሄድበት ሰሞን ስለነበር ከእንግዶቹ እይታ ለማራቅ ብዙ ጥረት ቢያደርግም ሊሳካለት አልቻለም።በአዲስ አበባ ከተማ ለመግባት የቻሉትን በፖሊስ እያደነ በአንድ ከባቢ በማጎር ወደመጡበት ለመመለስ ብዙ ሞከረ፤ግን የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በማጋለጣቸው መንግሥት ባሰበው መንገድ ችግሩንና ችግረኞቹን ሊያፍን አልቻለም።በሕዝቡ እርብርቦሽ ሙሉ ለሙሉም ባይሆን ዕርዳታ ሊያገኙ ቻሉ።

ይህ የሕዝብ እልቂትና ፍልሰት ከሌሎቹ ችግሮች ጋር ተደማምሮ የስልሳ ስድስቱን ሕዝባዊ ተቃውሞ አስነስቶ ለዘውዳዊው ስርዓት መገርሰስና ለወታደራዊው አምባገነን መንግሥት መምጣት ምክንያት ሆነ።የአምባገነኑ መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ ያደረገው ለድርቅ የተጋለጡትን ዜጎች ድርቅ ወደሌለበት ሕዝብ ወዳልሰፈረበት ያገሪቱ ክፍሎች ወስዶ ማስፈር ነበር።ከከባቢው የአዬር ልዩነት፣የበሽታና የኑሮ ሸክም ክብደት የተነሳ ብዙዎቹ ሲሞቱ ያንን የተቋቋሙት ጫካ መንጥረው ከአውሬ ጋር ታግለው ጎጆ ቀልሰው ለመኖር ቻሉ።በሚያውቁት የእርሻ ሙያ የሚያመርቱት የእህል ምርት ከራሳቸው አልፎ ተርፎ ለከባቢያቸውም የሚጠቅም ሆነ።ከነባሩ ማህበረሰብ ጋር ግንኙነታቸውን በማጠናከርና በማሳደግ በጋብቻ ሰንሰለት ተሳስረው ከምርት ግንኙነት በላይ በቤተሰብነት አብረው ለመኖር ቻሉ።

ይህ በእንዲህ እያለ ከአሥር ዓመት በዃላ የድርቅ አደጋ ዳግም ተከሰተ።በዚህም ወቅት እንደ መጀመሪያው የሰሜኑ የትግራይና የወሎ የገጠር ሕዝብ  ለእርሃብ ተጋለጠ። ካለፈው በተሻለ ሁኔታ የእርዳታ አስተባባሪ ተቋም በመኖሩ እንደመጀመሪያ  ባይሆንም ግን ሕዝቡ ከሚኖርበት ቦታ መልቀቁና መሰደዱ አልቀረም።የቻሉ በአዲስ አበባ ከተማ  ገብተው በዬቤተክርስቲያኑና በዬመንገዱ ዳር ፈሰሱ።በወቅቱ ወታደራዊው አምባገነን መንግሥት የአሥረኛ ዓመቱን የሥልጣን ነጠቃ በዓሉን የሚያከብርበት ጊዜ በመሆኑ በሚሊዮን ዶላር ወጭ ከውጭ አገር ለድግሱ ውስኪና ኮኛክ በማግበስበስ ላይ ነበር። ለሚመጡት እንግዶች እይታና የበዓሉን ገጽ ያጠፋሉ ተብለው እነዚህ የድርቅ ሰላባዎች ባገራቸው ዋና ከተማ እንዳይታዩ እዬታፈሱ በማጎሪያ ጣቢያ ውስጥ ተጠቀጠቁ።ጥቂት የማይባሉም ወደየመጡበት እንዲመለሱ ሆነ። በስማቸው የሚነግደው ጁንታ የድርቅ ቀውስ የሚያስከትለውን ያውቃልና በራሱ ላይ እንዳይደገም ጥረት አደረገ።ችግረኞቹን  የሥልጣኑ አጋላጭ ጠላቶቹ አደረጋቸው።ለሁለተኛ ጊዜ በአገራቸው ዋና ከተማ በአዲስ አበባ መቀመጥ ወንጀል ሆኖ ተቆጠረባቸው።በጣም የሚገርመው ግን ለሥልጣኑ አደጋ የሆኑትን አማጽያንና የሶማሌን ተስፋፊ ጦር ለመመከት ግንባር ቀደም አድርጎ አስገድዶ በሚሊሽያ ስም  ያሰለፋቸው እንዚህኑ የገጠር ምስኪኖችን ነበር።

ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዲሉ በአገሪቱ ላይ ተደጋጋሚ የድርቅ ክስተት ተከስቶ ሰው ከስደት ባይተርፍም ከአርባ ምናምን አመት በዃላ ግን ባለፉት አራት ዓመታት የታዬው ዘግናኝ የሕዝብ መገደል፣ መፈናቀልና ስደት ግን ወደር የለውም።የአሁኑ በድርቅ ምክንያት ብቻ ሳይሆን እርሃብና ችግርን አሸንፈው በሰላም ካሉበት ማህበረሰብ ጋር ተስማምተውና ተዋልደው በሚኖሩ ዜጎች ላይ በሚከተሉት ሃይማኖት፣በሚናገሩት ቋንቋና በማህበረሰብ ማንነታቸው ተለይተው የሚደርስባቸው ጥቃት ነው።የነዚህ ንጹሃን ወንጀል የአንድ ማህበረሰብ ተወላጆች አማራ መሆናቸው ነው።በጎሳ ማንነት ላይ የተመሠረተ ስርዓት በመሆኑ የሚያጠቃቸው ሃይል መንግሥታዊ መዋቅሩን የያዘውና  የሚያሽከረክረው በዬተራ የሚለዋወጠው  ጎሰኛ ቡድን ነው።ለሃያ ሰባት ዓመታት በትግሬው ጎሳ ፣ላለፉት አራት ዓመታት ገደማ ደግሞ በወራሹ የኦሮሞ ጎሳ መከራውን እንዲያይ የተፈረደበት ዜጋ አማራ የተባለው ጎሳ ተወላጅ ነው።ይህ ማህበረሰብ  በሌሎቹ ጎሳ ተወላጆች ላይ ወንጀልና  ግፍ ፈጽሞ ሳይሆን ኢትዮጵያ ለተባለችው አገር ሽንጡን ገትሮ በመቆሙ ለትግሬውና ለኦሮሞው ጸረ ኢትዮጵያ አገር አፍራሽ  ቡድኖች የማይመች ስለሆነባቸው ብቻ ነው።በጦርነት የሚያጠፉትን እያጠፉ፣ከኖረበት ቦታ ዘርፈው አፈናቅለውታል፤እያፈናቀሉትም ነው።ከሰፈረበት ቦታ ብቻም ሳይሆን ከተወለደበት፣ካደገበት ቦታም ድረስ ወረው እዬገደሉትና እያፈናቀሉት ነው።በዚህ የመከራ ሞገድ የሚዋከበው ሕዝብ ሲጨንቀው መንግሥት አለ፣ሰላም አገኛለሁ በሚል ጉጉት ወደ ከተማዎች በተለይም ወደ መናገሻ ከተማዋ አዲስ አበባ ሲገባ በቦታው ያሉት የተረኛው ጎሳ ባለሥልጣኖች እንዳለፉት መንግሥታቶች ዓይንህን ላፈር ብለው እያዋከቡት ይገኛሉ።በሚፈጸመው ተከታታይ የማጽዳት እርምጃ ከኦሮሞ ክልል በተለይም ከምስራቅ ወለጋ ሆረጉድሩ ከተባለው ቦታ የተፈናቀሉ ወገኖቻቸውን እንዳለፉት ጊዜያቶች የአዲስ አበባ ወጣቶች ለመርዳት ቢንቀሳቀሱም የመንግሥት ተብዬው ቡድን በተለይም የከተማዋ አስተዳደር በታጠቀ የፖሊስና የጸጥታ ሃይሎች በማስገደድ እነዚህ የአገር ባለቤቶች ሆነው አገረቢስ የሆኑትን ዜጎች ከከተማው አስወጥተው እንደዕቃ በጭነት መኪና አጉረው ክልላችሁ ነው ወደሚሉት የአማራው መሬት ወደ ደብረብርሃን ወስደው ሜዳ ላይ አፍስሰዋቸዋል።ከነዚህ ምስኪኖች ጎን የቆመውና ለመብታቸው የተከራከረው የፖለቲካ ፓርቲ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የተባለው ብቻ ነው።ሌላውማ እንኳንስ ሌላው በስማቸው የሚነግደው የአማራ ፓርቲ ድርጊቱን ከመደገፍና  ከማጨብጨብ ባለፈ የተቃውሞ ድምጹን አላሰማም።

የከተማው አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ምክትል ሃላፊ የሆነችው ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ(ተፈራ)የተባለች  ባለጌ ” በናንተ ምክንያት የከተማችን ገጽታ እዬቆሸሸ ነው ከዚህ በዃላ አንድም ተፈናቃይ ወደ ከተማችን እንዳይገባ ጥብቅ ቁጥጥር እናደርጋለን” ስትል በትእቢት መናገሯ በማትክደው መልኩ ተረጋግጧል።መንግሥትን ያህል ነገር የራሱን ሕዝብ ቁሻሻ ነህ ብሎ ሲሰድበውና ሲያዋርደው፣እኔ ከተቀመጥኩበት ከተማ መግባት አይፈቀድልህም ብሎ በፖሊስ ሃይል ሲደበድበው ማዬቱ የጎሰኝነት ትእቢት ጥጉ የት እንደደረሰ ማሳያ ነው። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የደብረብርሃን አስተዳደር ወደሱ የተወረወሩትን ወገኖቹን ተቀብሎ መጠለያ መስጠት ሲገባው ባጀት የለኝም በሚል ሰበብ መልሶ ወደ አዲስ አበባ መላኩ ነው።በዚህ የጅዋጅዌ ጨዋታ ለሳምንታት መንገድ የጎዳቸው ፣የራባቸውና  የታመሙ ሕጻናት፣አዛውንት፣እርጉዝ ሴቶች ለተደጋጋሚ ብስቁልና ተጋልጠዋል።የከተማዋ አስተዳደር ወደ ሌላ የኦሮሙማው ጥቃት ቦታ ወደሆነው አርሲ ወስዶ ለማፍሰስ መወሰኑ ተሰምቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ በአብይ አህመድ በአንደበቱ አዲስ አበባን እንደስሟ እናደርጋታለን እንዳልነው እያደረግናት ነው ብሏል።ከእንጦጦ በአዲሱ መንገድ በመኪና ስወርድ ልክ አሜሪካን አገር ሆሊውድን ይዞ ወደከተማዋ በሚወስደው ቤቨርሊሂል በተባለው ውብ መንገድ የምጓዝ ይመስለኛል ሲል አሜሪካንን ላላዩት የፓርላማ አባላት እንዲያዩት ቅስቀሳ ከማካሄዱም በላይ አሜሪካንን ለመሆን ያለውን ፍላጎትና አድናቆቱንም አሳይቷል።ጥያቄው ኢትዮጵያዊ ሆኖ ኢትዮጵያን የሚመስል እድገት ማምጣቱ እንጂ የሌላ አገሮች ምስል ኮፒ መሆን አይደለም።ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት!

በጣም የሚያበሳጨው ሌላው ጉድ ይህ ሁሉ ግፍ በዜጎች ላይ ሲፈጸም ከቅርብ እርቀት ላይ የተሰበሰበው የፓርላማ አባላት ጉባኤ በጉዳዩ ላይ ትንፍሽ አለማለቱ ነው።አባላቱን ያስጨነቃቸው እነሱም የሚቦጫጨቁት የየክልላቸው የኤኮኖሚ የጥቅም ድርሻ ነው።ጠ/ሚንስተሩም አብይ አህመድ የጊዜውን ሦስት አራተኛ የጨረሰው በኤኮኖሚው ዙሪያ የተገኘውን ድልና ስኬት በማውሳት ነው።የተገኘው ስኬት ግን ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ከደረሰው ውድቀት በጣም ያነሰ መሆኑን ባቀረበው የገቢ ወጭ መጠን ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል።እዛው በዛው የሚቃረን ንግግር የማድረግ ልማድ ላለው ለአብይ አህመድም ሆነ የመዘንጋት ችግር አለበት ለተባለው የፓርላማ ስብስብ ግን ተቃርኖው አልታዬውም።ሕዝቡን ቀስፎ የያዘው የዋጋ ግሽበቱን በቸርቻሪው ነጋዴ ትከሻ ላይ በመጣል ምርት በማነሱ ሳይሆን ምርቱን በመደበቁ ነው ሲል ወንጀለኛ አድርጎታል።እርግጥ ነው በዚህ በኩል መጠነኛ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ባይካድም ዋናው ምክንያት ግን አይደለም።ዋናው ምክንያት ሰላም ባለመኖሩና ዜጎች የትም ሄደው እንዳያመርቱ የሚያግድ ስርዓት በመስፈኑ ነው።የኤኮኖሚው መስክ በአንድ ነጠላ ሥልጣኑን በተቆጣጠረ ጎሳ መዳፍ ስር በመግባቱና በዛም ፍላጎት በመቀዬሱ ነው።የጦርነት ኤኮኖሚ አለ ብሎ የልማት ኤኮኖሚ አድጓል ማለት እርስ በራሱ የሚቃረን ነው።በጦርነት ኤኮኖሚ የተማገደ አገር ጭራሽ ወደለዬለት ቀውስ ይገባል እንጂ እድገት አያስመዘግብም።በአገራችንም የሆነው ይኸው ነው። ሰላምና አንድነት የሌለው አገር በግጭትና  በጦርነት ላይ ስለሚማገድ አምርቶ ለማደር ይቸገራል፣ምርት ከሌለም ግሽበትና ችግር የኖራል።።ለዋጋ ግሽበቱም አንዱ ምክንያት የሕዝብ ብዛትና የወሊድ ቁጥር ነው ብሏል፤ሕዝብ ቁጥር መቀነስ እንዳለበትም አሳስቧል።ይህም አማራውን በዬቦታው መጨፍጨፍና ማስጨፍጨፍ በሥልጣን ላይ ያለው ኦነግ መራሹ መንግሥት  እንደ አንድ የችግር መፍትሄ ሆኖ ይዞታል ብሎ ለማሰብ ያስደፍራል።ሌላው ጉዳይ ለሙስሊሙ የኢድ አልፋጥር በዓል መንግሥት ትኩረት እንደሰጠውና ለመጀመሪያ ጊዜ በትልቅ ዝግጅት ለመካሄድ መታሰቡን ነው።በዚህም በዓል ላይ እውጭ ያለው ዲያስፖራ እንዲሳተf ጥሪ አድርጓል።የኢድ በዓል መከበሩ ተገቢ መሆኑ ባይካድም መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ገብቶ አድራጊ ፈጣሪ መሆኑ ትክክል አይደለም።የገንዘብ መሰብሰቢያም አድርጎ ሊጠቀምበት አይገባም። ዝግጅቱን የሃይማኖት ተቋሙ በባለቤትነት ሊይዘው ይገባል።የሚያስተዛዝበው ግን ለፋሲካና ለገናም ሆነ ለመስቀልና  ለጥምቀት በዓሉ መንግሥት ለምን ተመሳሳይ ጥሪና ቅስቀሳ  ሳያደርግ ቀረ?የሚለው ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አፈና ያላንበረከከው የአርባምንጭ ህዝባዊ ሰልፍ (Video)

በፓርላማ ውሎው ጠ/ሚኒስትሩ ብዙ ጉዳዮችን ያነሳ ሲሆን ጥያቄዎቹ ከአስር ቀናት በፊት የተላኩለትትና በካቢኔ አባላቱ ተጎራርደው መልስ የተሰጣቸው መሆኑን ጥያቄ የላኩት  የፓርላማው አባላት ከስብሰባው በዃላ ገልጸዋል።ስለ አገር አንድነት ሲያነሳ የማይደራደርበት አቋሙ መሆኑን እዬገለጸ የአገር አንድነትን አደጋ ውስጥ የሚከትን እንታገላለን፣ኢትዮጵያ አትፈርስም ብሎ ሲፎክር ለአንድነቱ ጸር የሆነውንና ሕዝቡን የሚያጋድለውን የጎሳ ፖለቲካና ሕገመንግሥት መሆኑን ግን አምኖ አልተቀበለም።ስለኦነግ ሸኔም አንስቶ ዓላማ ቢስና መዋቅር የሌለው ጨካኝ ቡድን ነው በማለት ከባድ የጦር  መሣሪያ ታጥቆ፣በከተማ ደግሶ እያስመረቀና ሰልፍ እያዘጋጀ ፣ሰፊ ቦታ መቆጣጠር የቻለ የመንግሥት ድጋፍ ያለው መሆኑን ግን ክዷል።ካደረሰው ጥቃት ሁሉ ያስቆጨው የስኳር ፋብሪካ ማቃጠሉ እንጂ  ሕጻን ሽማግሌ፣እርጉዝና እመጫት ማረዱና በእሳት ማቃጠሉ አይደለም።አዎ! ለብልጽግናው  መሪ ለሚከተለው ፍልስፍና  ሐብት እንጂ የሰው ሕይወት ዋጋና ቦታ የለውም።ደሃና ብስቁል ቢሞት ለሱ ደንታው አይደለም። ሌብነትንም አጥብቆ ኮንኗል ግን ሌቦቹ በራሱ መንግሥት ውስጥ  ከላይ እስከታች ድረስ የተሰገሰጉት ባለሥልጣኖች መሆናቸውን የሚያውቀው ሕዝብ በንግግሩ የሚመሰጥ አይሆንም።

ከወያኔ ጋር ስላለው ድርድርም አንስቶ አልተደረገም ብሏል፤በዚህም አባባሉ መደረጉን የገለጹትን የውጭ አገር ባለሥልጣኖች ጭምር ውሸታሞች አድርጓቸዋል።ቢደረግም ይበልጥ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም በማለት ብዙ ለማሳመን ሞክሯል።ወንጀለኛን መፍታትና ይቅርታ ማድረግም ከሰላም ድርድሩ ጋር የተያያዘ የታላቅነት ምልክት ነው ሲል የፈጸመውን ክህደት ተገቢና ትክክክለኛ እርምጃ ለማድረግ ሞክሯል። እስረኞችን በመልቀቅ ኢትዮጵያ ተጠቅማለች ሲል ያገኘችውን ጥቅም ግን አላብራራውም።

የፓርማውን ውሎ እዚህ ላይ አቁሜ ወደተነሳሁበት ርዕስ፣ በወገኖቻችን በተለይም በአማራው ማህበረሰብ ላይ በአዲስ አበባና በሌላው አካባቢ የሚፈጸመውን ግፍና በደል፣ የከተማው አስተዳደር የፈጸመውን ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ማጋለጥ ተገቢ ነው እላለሁ።የከተማውን አስተዳደር የወ/ሮ ሊድያን  ድፍረትና ብልግና የሰማ ሰብአዊነት የሚሰማው ሁሉ ድርጊቱን ሊቃወመውና  ሊያወግዘው ይገባል። አንድ ዜጋ በፈለገበት ቦታ የመኖር መብቱ በሌሎች የሚነጠቅና የሚቸር ሳይሆን የተፈጥሮ መብቱ ነው።እያንዳንዱ በራሱ ላይ ቢደርስ ምን ስሜት ሊሰማው እንደሚችል መገመቱ ከባድ አይደለም።ስለሆነም በሌላው ላይ የሚደርሰውን ሕገወጥና ኢሰብአዊ ድርጊት በራሱ ላይ እንደደረሰ አድርጎ ሊቆጥረው ይገባል።ዛሬ በአማራው ላይ የሚደርስ መከራና ግፍ ነገ የሁሉም እጣ ፈንታ ይሆናል።የኦሮሙማውና  የወያኔ የጥፋት እርምጃ ቦታና ጎሳ አይመርጥም፤የየራሳቸውንም ቢሆን ካልተመቻቸው ያጠፉታል፤እያጠፉትም ነው።ትግሉ ለአንድ ጎሳ ደህንነት ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላዩ ያገሪቱ ዜጋ ብሎም ለሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ነው።በጊዜው ካልተቀጨ ከኢትዮጵያም አልፎ ወደሌላው አገር እንደ ኮሮና ቫይረስ ይሰራጫል።ለመሰራጨቱም ምልክቶች በመታዬት ላይ ናቸው።የከበርቴ አገራቱም በዚህ ቀውስ ውስጥ የአፍሪካ ሕዝብ እንዲማገድ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው።ሰርጎ ለመግባት ትልቁ በር የእርስ በርስ ውጊያ ነው።ኤኮኖሚያቸውም ዋና የጀርባ አጥንት የያገራቱ ሰላም ማጣትና በጦርነት ውስጥ መማገድ ነው።የሰው መሞት ለመቃብር ሳጥን አምራቹ ደስታ እንደሆነው ሁሉ ለመሣሪያ አምራች አገሮችም እንዲሁ ጦርነት መፋፋሙና መስፋፋቱ የሚረኩበትና የሚቋምጡለት ትልቅ ገበያ  ነው። ለልማት ከሚሰጡት  ይልቅ ለጦር መሣሪያ የሚሰጡት ብድር ይበልጣል።ለምን ቢባል አትራፊና የማያከስር የንግድ መስክ ስለሆነ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ሁለቱ ታላላቅ ዕቅዶች” ክፍል 2 (ዮፍታሔ)

የሌሎቹን እርዳታ ከመሻቱ በፊት የጥቃቱ ሰለባ የሆነው የአማራው ማህበረሰብ እራሱን ለማዳን እጅ ለእጅ ተያይዞና ተደራጅቶ አጥቂውን ሊመክት ይገባል።በለቅሶና በልመና ሊድን አይችልም፤አለመዳኑንም እየጮሁና እዬለመኑ ያለቁትን ወገኖቹን ማዬትና ማሰብ በቂ ነው።ትልቅ እንቅፋትና የጥቃት መሣሪያ የሆኑት ከራሱ መሃል የወጡት መሆናቸውን ሊያውቅና አደብ ሊያሲዛቸው ይገባል።እነዚህ እስካሉ ድረስ የሚደርስበት ስቃይና የዘር ማጥፋት ዘመቻ አይቆምም።ከውስጡ ሆነው አቅሙን የሚያዳክሙትና እንዳይደራጅም ምክንያት የሆኑት፣ለአደጋም የሚያጋልጡት እነዚህ ለሆዳቸው ያደሩ ጥቂት ባንዳዎች ናቸው። እነዚሁ ባንዳዎች ከአጥቂው ከተረኛው የኦነግ-ኦሮሙማ መንግሥት ጋር ተባብረው  ለአማራው መብትና ደህንነት የቆሙትንና የሕይወት ዋጋ የከፈሉትን የፋኖ ሕዝባዊ ጦር አባላት እንደ ጠላት በማሳደድ፣በማሰርና በመግደል ላይ ተሰማርተዋል።ከሕዝቡም ለመነጠል ያልሞከሩት የለም፤አሁንም በመሞከር ላይ ናቸው።በከባቢው ሕዝብ ስም ያደራጇቸውን ሆድ አዳሪዎች በማሰማራት የስነልቦና ጦርነት ከፍተዋል።ከዚያም በላይ በጉልበት ለማንበርከክ ባይሳካላቸውም ሙከራ ከማድረግ አልተቆጠቡም።በየስብሰባው ላይ የአማራ ስም እንዳይነሳ፣የደረሰበትም መከራና የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳይጋለጥ የሚከላከሉ በመሬትና በኮንደሚነም ብሎም በሥልጣን ቦታ በሚሸነገሉ አይሁዶች በኩል የሃይማኖትና የጎጥ ልዩነትም ውስጥ ገብቶ እርስ በራሱ እንዲጋጭና እንዲዳከም ብሎም የአማራው የማንነት ትግል እንዲከስም ጥረት እዬተደረገ ነው። በአንጻሩ የሌላ ጎሳ ተወላጅ ሆነው በኢትዮጵያዊነታቸው ስለአማራው የሚናገሩና የሚጮሁ ወገኖች መኖራቸው ለአገሪቱ እንዳገር መቀጠል ተስፋ የሚሰጥ ምልክት ነው።በስሙ የሚነግዱትን ወንጀለኞች ማጋለጥና መቅጣት የያንዳንዱ ሰላምና አንድነት ወዳጅ ኢትዮጵያዊ ድርሻ ነው። ስለአማራው መቆምና መጮህ የግዴታ የአማራ ተወላጅ መሆን አያስፈልግም፤ ለሰብአዊ መብት የቆመ ሰውነት የሚሰማው ሁሉ ተግባርና  ግዴታው ነው።በዚህ እረገድ ሳይታክቱና ሳይፈሩ ድምጻቸውን ለሚያሰሙት ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜጎች ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል።

አገረቢስ የሆነውን ሕዝብ የአገሩ ባለቤት ለማድረግ ተባብረን እንነሳ!

1 Comment

  1. Liked the photo

    በሀገሬ ጉዳይ እንዲህ ከምቃጠል
    ምናል ተመርጬ ገብቼ ፓርላማ
    በጭብጨባ መሐል እንቅልፌን ብተኛ።

    Bet yemaymetu sinignoch nachew innezih sewoch.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share