የካቲት 03/06/2014 ዓ.ም የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 3ኛ ዙር፣ 1ኛ አመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አጠናቋል። ጉባኤው በዋነኛነት የትኩረት አቅጣጫውን አድርጎ የነበረው የስራ አስፈጻሚውን የ6 ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መርምሮ ማጽደቅ ላይ ቢሆንም ሌሎች መለስተኛ ጉዳዮችንም በጥሞና ተመልክቷል።
በዚህም መሰረት እኔን ጨምሮ በርካታ የም/ቤቱ አባላት ጠንከር ያሉ አስተያየቶችንና ማፈናፈኛ የማይሰጡና በተጨባጭ ምሳሌዎች የተደገፉ ጥያቄዎችን ከመፍትሄ ሀሳቦች ጋር ቀርበው የአስፈጻሚ አካላት የስራ ሀላፊዎች፣ የም/ቤቱ የመንግስት ተጠሪና ክብርት ከንቲባዋ ሠፊ ማብራሪያ ሠጥተዋል።
የስራ ሀላፊዎቹ ለአብዛኛዎቹ ጥያቄዎችና አስተያየቶች አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ ቢሆንም አንዳንዶቹ የስራ ሀላፊዎች በተወሰኑት ጉዳዮች ላይ የሠጡት ማብራሪያ ግን ከእውነታው ያፈነገጠ ብቻ ሳይሆን ለም/ቤቱም ሆነ ለአዲስ አበባ ሕዝብ ያላቸውን ንቀት በግልጽ ያሳዩበት ነበር ማለት ይቻላል።
በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ለተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የወጣው 1.9 ቢሊዮን ብር ለከተማዋ ተማሪዎች ብቻ ነው የወጣው ወይስ የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ተማሪዎችን ይጨምራል ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ የሰጡት መልስ “በኦሮሚያ ልዩ ዞን ስር የሚገኙ አካባቢዎች አዲስ አበባ ከርሷን ሞልታ ፈርሷን የምትጥልባቸው ናቸው” በሚል ጸያፍ ሀረግ ነበር የጀመረው።
ይህም አንድም ለጥያቄው ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ ምን ያለበት… እንደሚባለው ምክንያቱን ከእሳቸው በተሻለ መልኩ ለምናውቀው ሰዎች አሰልቺ በሆነ አቀራረብ ሊያብራሩልን ሞከሩ። ይህ ሀሳብ የእሳቸው ብቻ እንዳልሆነ መረዳት የሚቻለው ደግሞ ክብርት ከንቲባዋን ጨምሮ ከእሳቸው በኋላ መልስ የሰጡ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ይህንን ነውረኛ ሠው ሳያርሙት ማለፋቸው ነው።
በጣም የሚያስገርመው ደግሞ “በስንት ልመና የተገኘን ዕድልማ እጠቀምበታለሁ” ያሉትን የተከበሩ የም/ቤት አባል እንደዚህ አይባልም፣ መታረም አለበት በማለት ለመገሰጽ የፈጠኑት ክብርት አፈ ጉባኤ የአዲስ አበባ ሕዝብ ሲሰደብ ግን ዝምታን መምረጣቸው ነው። ይህንን ሁኔታ ለማረምና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የነበረኝን የተለየ ሀሳብ ለማቅረብ እንድል እንዲሰጠኝ ብጠይቅም ተከለከልሁ።
በዚህ አጋጣሚ አዲስ አበባ ከፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን አጎራባች አካባቢዎች ጋር ሊኖራት የሚገባውን ግንኙነት አስመልክቶ ሀሳቤን መግለጽ አፈልጋለሁ። በዚህ አጋጣሚ ማረጋገጥ የምችለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህር ቢሮ ሀላፊ እንዳሉት አዲስ አበባም ሆነች ነዋሪዎቿ ከሌላው ሕዝብ የተለየ ከርሳምም ፈርሳምም አይደሉም።
ይልቁንም ውሀና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ከፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን አካባቢዎች የምታገኘውን ያህል ለእነዚህ አካባቢ ነዋሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚደጎም የትራንስፖርት አገልግሎት ትሰጣለች። በዚህ ረገድ ለምሳሌ የአንበሳ አውቶብስ አገልግሎት እስከ ደብረ ዘይት፣ አለም ገና፣ ጫንጮ፣ ሰንዳፋ ወዘተ. ስምሪት እንዳለው ይታወቃል።
ሌላው የተሻለ የትምህርትና የጤና አገልግሎት የሚያገኙ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህም የእነዚህ አካባቢ ነዋሪዎች ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በመገኘታቸው የሚያገኙት እድል መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ይህን እድል ለማግኘት ረዥም ርቀት የሚጓዙና ተጨማሪ ወጭ የሚያወጡ ዜጎች ሚሊዮኖች መሆናቸውም ልብ ይባል።
እንዲሁም የእነዚህ አካባቢ ነዋሪዎች ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብም ሆነ የፋብሪካ ውጤቶችን ለመግዛት አዲስ አበባን የሚጠቀሙ መሆናቸው ግልጽ ነው። በዚህም ለምርቶቻቸው የተሻለ ዋጋ ከማግኘታቸውም በላይ የፋብሪካ ውጤቶችን ደግሞ በፋብሪካ ዋጋ የማግኘት ዕድ ያገኛሉ።
በመጨረሻም የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች ከሌላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተሻለ በአዲስ አበባ ከተማ የስራ ዕድል የሚያገኙ መሆኑም በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ማሳጠር ስለተፈለገ እንጂ እንዲህ እንዲህ እያልን አዲስ አበባ ለፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎች የምታስገኝላቸውን በርካታ ጠቀሜታዎች መዘርዘር ይቻላል።
እናም የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ለአዲስ አበባ ከሚያስገኘው ጥቅም በላይ አዲስ አበባ ለፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የምታስገኘው ጥቅም ሊበልጥ እንደሚችል አስበነው እናውቅ ይሆን? ይህንን እውነት በመገንዘብ ሚዛናዊ እይታ መያዝ ሀላፊነት ከሚሰማው ሰው ይጠበቃል።
ስለሆነም አንድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ሀላፊ ይህን እውነታ ሳያገናዝብ የሚሰጠው መልስ ይኸ ሰው በዋነኛነት ማንን ነው እያገለገለ ያለው የሚል ትዝብት ውስጥ እንደሚከተው ሊገነዘብ ይገባል። ከዛም አልፎ አዲስ አበባ ለፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የምትሰጠው የበጀትም ሆነ የቴክኒክ ድጋፍ ወሰኑ የት ድረስ ነው የሚለውም ጉዳይ ከፖለቲካ ውሳኔ ባለፈ በህግ ካልተደገፈ አስቸጋሪ ይሆናል።