” ቤተ መንግሥት ስንገባ ምን ማድረግ እንዳለብን በቅጡ አላሰብንበትም፡፡ የነበረውን ስለ ማስወገድ እንጂ የተሻለ እንዴት እንደምናመጣ በደንብ አልሠራንም፡፡ ቤተ መንግሥቱን ከውጭ ስታየውና ውስጡ ሆነህ ስትኖርበት ይለያያል፡፡ ሥልጣኑን ለማግኘት ስትታገልና ስታገኘው ልዩነት አለው። መሬት ላይ ሆነህ ተራራውን ስታየውና ተራራው ላይ ሆነህ ተራራውን ስታየው እንደሚለያየው ዓይነት፡፡ ነባሮቹን ችግሮች አስወግደናል፤ ግን በአዳዲስ ችግሮች ነው የቀየርናቸው፤ ነባሮቹን ጦርነቶች አስቁመናል፤ ግን በአዳዲስ ጦርነቶች ነው የተካናቸው፣ ነባሮቹን ቅሬታዎች ፈትተናል፤ ግን በአዳዲስ ቅሬታዎች ነው ቦታቸውን ያስያዝነው”
አንድ የአፍሪካ የሽምቅ ውጊያ መሪ፤ ለብዙ ዓመታት በሽምቅ ውጊያ ታግሎ ነባሩን መንግሥት ካስወገደ በኋላ ለ12 ዓመታት ሀገሪቱን መራ፡፡ ሕዝቡ በሽምቅ ተዋጊነቱ ጊዜ የወደደውን ያህል በመንግሥትነቱ ጊዜ ሊወደው አልቻለም፡፡ ሲመጣ በጭብጨባና በሆታ ተቀበለው፣ ሲውል ሲያድር እያዘነበት ሄደ፣ ሲቆይ ተቀየመው፣ ሲሰነብት ተቃወመው፣ ሲከርምም ዐመፀበትና ከሥልጣኑ አባረረው፡፡ ‹ከሽምቅ ውጊያ በኋላ› (After ‹Gorilla fighting›) የተሰኘውን መጽሐፉን ሲጽፍ ከሀገሩ ተባርሮ በሰው ሀገር ያገኘው ናይጄርያዊው ደራሲ ቶማስ ኙዌንጌ ስሙን እንደማይጠቅስ ቃል ገብቶለት አነጋግሮት ነበር፡፡ የሽምቅ ውጊያ መሪው ‹ሆ› ብሎ በእልልታ የተቀበለው ሕዝብ ‹ሂድ› ብሎ በቁጣ ለምን እንዳባረረው ሲገልጥለት እንዲህ ነበር ያለው፡-
‹የነበረውን መንግሥት ጥለን ሥልጣን ለማግኘት ታግለናል፡፡ ሕዝብን ከጭቆና ነጻ ለማውጣት፣ ፍትሕና እኩልነትንም ለማስከበር ታግለናል፡፡ አሁን ሳስበው የተዘጋጀነው እስከ ቤተ መንግሥቱ ላለው ጉዞ ነበር፡፡ ቤተ መንግሥት ስንገባ ምን ማድረግ እንዳለብን በቅጡ አላሰብንበትም፡፡ የነበረውን ስለ ማስወገድ እንጂ የተሻለ እንዴት እንደምናመጣ በደንብ አልሠራንም፡፡ ቤተ መንግሥቱን ከውጭ ስታየውና ውስጡ ሆነህ ስትኖርበት ይለያያል፡፡ ሥልጣኑን ለማግኘት ስትታገልና ስታገኘው ልዩነት አለው። መሬት ላይ ሆነህ ተራራውን ስታየውና ተራራው ላይ ሆነህ ተራራውን ስታየው እንደሚለያየው ዓይነት፡፡ ነባሮቹን ችግሮች አስወግደናል፤ ግን በአዳዲስ ችግሮች ነው የቀየርናቸው፤ ነባሮቹን ጦርነቶች አስቁመናል፤ ግን በአዳዲስ ጦርነቶች ነው የተካናቸው፣ ነባሮቹን ቅሬታዎች ፈትተናል፤ ግን በአዳዲስ ቅሬታዎች ነው ቦታቸውን ያስያዝነው›
ማግባት የሚመኙ፤ ግን ካገቡ በኋላ ምን እንደሚያደርጉ ያልተዘጋጁ፤ ገንዘብ የሚፈልጉ፤ ገንዘቡን ቢያገኙ ምን እንደሚሠሩበት በቅጡ ያላቀዱ፤ ውጭ ሀገር ለመሄድ የሚኳትኑ፤ ሄደው ምን እንደሚሆኑ ያላሰቡ፤ ተምሮ መጨረስ እንጂ ጨርሰው ምን እንደሚያደርጉ የተሰላ ዕቅድ የሌላቸው፤ ባለ ሀብት መሆን እንጂ ሀብቱን እንዴት እንደሚይዙት ዕውቀቱም ዝግጅቱም የሌላቸው፤ ሥልጣን ላይ መውጣትን እንጂ ሲወጡ ለሚሆነው ነገር የሠለጠ ሐሳብ ያልቋጠሩ፤ ፌስ ቡክ መክፈት እንጂ ከፍተው ምን እንደሚያደርጉ ባለማቀዳቸው ሺ ጊዜ ፕሮፋይል ፎቶ የሚቀያይሩ፤ የሚዲያ ዕድል ለማግኘት እንጂ ሲያገኙ እንዴት ዘልቀውና ልቀው መቆየት እንደሚችሉ ያላሰላሰሉ – ‹መኪና አሳዳጅ ውሾች› ተብለው ይጠራሉ፡፡
ማግባት አንድ ነገር ነው፡፡ በትዳር መዝለቅ ደግሞ ሌላ፡፡ ሀብት ማግኘት አንድ ነገር ነው፤ ትውልድ የሚሻገር ተቋም መመሥረት ደግሞ ሌላ፡፡ ታዋቂነትን ማግኘት አንድ ነገር ነው፡፡ እንደተወደዱና እንደተከበሩ መኖር ደግሞ ሌላ፡፡ ወደ ኪነ ጥበቡ አምባ መዝለቅ አንድ ነገር ነው፡፡ እንደተካኑና እንደተደነቁ መኖር ደግሞ ሌላ፡፡ የተሳለ፣ የበሰለ፤ የደቀቀ፣ የተሰለቀ ዕቅድ የሚያስፈልገው ከተራራው ጫፍ፣ ከሀብቱ ማማ ማዶ፣ ከሥልጣኑ እርከን ባሻገር፣ ከታዋቂነቱ ክብር ወዲያ፣ ከትዳሩ ጎጆ አልፎ፣ ከትምህርቱ ምረቃ በኋላ ያለውን መንገድ አስልቶ፤ ትርፍና ኪሣራውንም ገምቶ ለመነሣት እንዲቻል ነው፡፡
በአንድ ወቅት ‹መቶ ሺ ብር ብታገኝ ምን ታደርገዋለህ?› ተብሎ የተጠየቀ ሰው፤ ‹መጀመሪያ ስጠኝና ከዚያ በኋላ እነግርሃለሁ› አለ ተብሎ ተቀልዷል፡፡ ካሳቀም ሊያስቅ የሚገባው የሰውየው የዕቅድ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከበደ ሚካኤል በጻፉት ተረትና ምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የምናገኘው ዘፋኙ ጫማ ሰፊ የገጠመው’ኮ ይሄ ነው፡፡ ከጫማ ቤቱ በላይ እየኖረ የጫማ ሰፊውን ያህል ደስታን ያላገኘው ባለጠጋ፤ የዚህን ጫማ ሰፊ ዘፈን እየሰማ ይዝናና ነበር፡፡ በነጻ መዝናናቱ ቀማኛነት ስለመሰለው ጫማ ሰፊውን ጠራና አንድ ከረጢት ወርቅ ሰጠው፡፡
ጫማ ሰፊው አመስግኖ ወደ ቤቱ ተመልሶ ገባ፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ ‹የት ላስቀምጠው› የሚል ነበር። ጫማ ሰፊው አሮጌ ጫማ ለማስቀመጥ እንጂ ወርቅ ለማስቀመጥ የሚችል ነገር የለውም፡፡ ሲሠራ የዕለት ጉርሱን፣ የዓመት ልብሱን ለማግኘት እንጂ ሀብታም ለመሆንና ወርቅ ለመሰብሰብ አላሰበም፡፡ እዚያም እደርሳለሁ የሚል ምኞትም አልነበረውም፡፡ ለእርሱ ወርቁ ድንገቴ የሆነበትም ለዚህ ነው፡፡ ድንገቴ ሀብት የሚያገኙ ሰዎች የሚደርስባቸው የአእምሮ ድቀት ይህን የመሰለ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ የሆኑት ለዚያ ነው፡፡ ‹እንዴት እንደመጣ የማታውቀውን እንዴት እንደሚሄድ አታውቀውም› ይባላል፡፡
ጫማ ሰፊ፤ ዕንቅልፍ አጥቶ ነው ያደረው፡፡ ኮሽ ባለ ቁጥር ‹ሌባ ወርቅ ማግኘቴን ሰምቶ ሊወስድብኝ መጣ› እያለ፡፡ ለዕለት ጉርሱ ብቻ የሚሠራው ጫማ ሰፊ፤ ወርቅ የትና እንዴት እንደሚቀመጥ አያውቅም። እርሱ ወርቅ ለማግኘት አልተዘጋጀም፡፡ የሚሠራው ለማግኘት ነው፡፡ ሲያገኝ ምን እንደሚያደርግ ግን ያሰበው ነገር የለም፡፡ ‹ስጠኝና ምን እንደምሠራ እነግርሃለሁ› እንዳለው ሰውዬ፡፡
ወላጆቻቸውን ወይም ታላላቆቻቸውን አስቸግረው ሱቅ የሚከፍቱ፣ ታክሲ የሚያስገዙ፣ ሆቴል የሚጀምሩ ወጣቶች፤‹ብቻ አንድ ነገር ይከፈትልኝ፣ ውዬ የምገባበት ላግኝ፣ ይኼው እገሌ ተከፍቶለትና ተገዝቶለት ዛሬ ማን ይደርስበታል› በሚል ስሜት ይጀምሩታል እንጂ ያሰብኩትን ባገኘው ከዚያ እንዴት እቀጥለዋለሁ? ብለው ብዙም አይጨነቁም፡፡ የመጀመሪያው ቀን የሞላው ሱቅ እንዲሁ የሚኖር ይመስላቸዋል፡፡ መኪና በራሱ ባትሪና ሞተር መንቀሳቀስ ካልቻለ ስለገፉት ብቻ አይሄድም፡፡ የመገፋቱ ዓላማ መጀመሪያ ባትሪና ሞተሩ እንዲሠሩ፤ ሠርተውም ራሳቸውን ችለው እንዲሽከረከሩ ነው፡፡ እንግፋው – እንንዳው አይሆንም፡፡
የወላጆቻቸውን ሀብት ስለማግኘት ብቻ ሲያስቡ የኖሩ ልጆች ናቸው ወላጆቻቸው ዐርፈው ሀብታቸውን ሲወርሱ ማስተዳደሩ አቅቷቸው አንዴ በሐራጅ፣ አንዴ በዕዳ ያስሸጡት፡፡ ወላጆቻቸው የለፉበትን እንጂ ያለፉበትን አልወረሱም፡፡ ‹ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር፣ ሲይዙት ያደናግር› የሚለው ደርሶባቸዋል፡፡ እንደ ውሻው መኪናውን ለማግኘት ደከሙ እንጂ መኪናውን ቢያገኙት ምን እንደሚያደርጉት አስበውት አያውቁም፡፡
አንድ የሚጮህ ውሻ ያለው ገበሬ ነበር አሉ። ውሻው መንገድ ዳር ይሆንና መኪና ባለፈ ቁጥር መኪናውን ለመያዝ እየጮኸ ይከተለዋል፡፡ የውሻውን የዘወትር ተግባር ያየ ጎረቤቱ፣ ገበሬውን ጠየቀው፡- ‹ይኼ ውሻህ ምን ሞኝ ቢሆን ነው የሚበርር መኪና ለመያዝ እንዲህ መከራውን የሚያየው? ለመሆኑ አንድ መኪና እንኳን መያዝ የሚችል ይመስልሃል?› ሲል ጠየቀው፡፡ የውሻው ባለቤትም ሳቅ አለና፤‹እኔ የሚገርመኝ እርሱ አይደለም፡፡ በዚሁ ከቀጠለ አንድ ቀን አንዱን መኪና ነክሶ ሊይዘው ይችል ይሆናል፡፡ እኔን የሚገርመኝ ሌላ ነው› አለው፡፡ ጎረቤቱም ‘ከዚህ የባሰ ምን ይገርምሃል?› ሲል ጠየቀው፡፡ የውሻው ባለቤትም፤ ‹እኔን የሚገርመኝ እንደምንም ብሎ መኪናውን አንድ ቀን ቢያገኘው ምን ሊያደርገው እንደሚችል አለማሰቡ ነው› አለው ይባላል፡፡
የመኪና አሳዳጅ ውሾች ዋናው ጠባይ ይኼ ነው፡፡ ቢያገኙት ምን እንደሚያደርጉት በቅጥ ያላሰቡበትን ዓላማ ይከተላሉ፡፡ ከዚያስ? ለሚለው መልስ የላቸውም፡፡ የሚያደርጉት ሌላው ስላደረገው፣ ብዙ ስለተወራለት፣ ሰው ሲያደርገው ስላዩት፣ ወይም ማስታወቂያዎቹ ስለጮኹለት ይሆናል፡፡ መኪና ስለመያዝ እንጂ ወዴት አቅጣጫ እንደሚነዱት አይዘጋጁም፡፡ ኮሌጅ ለመግባት እንጂ በኮሌጅ ለመዝለቅ፣ ዘልቀውም ኮሌጅ ለመበጠስ አይዘጋጁም፡፡ ውጭ ሀገር ለመሄድ እንጂ እዚያ ለሚገጥማቸው ውጣ ውረድ በውጭም በውስጥም አላቀዱበትም፡፡ ፓርቲ ለመመሥረት እንጂ፣ በፓርቲ ውስጥ ለመዝለቅ የወጠኑት ስልት የለም፤ ማኅበር ለማቋቋም እንጂ የማኅበርን ማዕበልና ንውጥውጥ (ዳይናሚክስ) ችለውና አሸንፈው ለመዝለቅ የተለሙት ትልም የለም፡፡ ዕቅድ ከምኞት የሚለየው በሦስት ነገር ነው፡፡ ወደምታስበው ዓላማ የሚወስድህን ትክክለኛ መንገድ አጥርተህ ካወቅከው፤ በመንገዱ ለሚገጥምህ ደስታና ኀዘን እኩል ከተዘጋጀህና ዓላማህ ላይ ስትደርስ በዓላማህ ለመዝለቅ የሚያስችል በቂ ስልት ካለህ፤ይሄ ዕቅድ እንጂ ምኞት አይደለም፡፡
እንሂድ ተብሎ ከቤት አይወጣም፡፡ የትና እንዴት እንደሚኬድ፤ ሲደረስም ምን አንደሚደረግ ሳይታወቅ፡፡ ሊቃውንት፤‹በሕይወት ውስጥ 10 በመቶው ከማግኘት፣ 90 በመቶው ግን ከአያያዝ ይሟላል› ይላሉ፡፡ ገንዘብ በሎተሪም ይገኛል፣ ወድቆም ይገኛል፣ በውርስም ይገኛል፣ በስጦታም ይገኛል፣ ተዘርፎም ይገኛል፡፡ አያያዝ ግን በስጦታም፣ በውርስም፣ በስርቆትም፣ በሎተሪም አይገኝም፡፡
ካገኘኸው በኋላ ምን እንደምታደርገው፣ እንዴት እንደምትይዘውና የት እንደምትወስደው የማታውቀውን ነገር፣ ለማጣት አግኝተኸዋል” ማለት ነው፡፡ ልክ እንደ መኪና አሳዳጁ ውሻ፡፡