መንግስት ከህወሀት ጋር ድርድር እያደረገ እንደሆነ እየሰማን ነው – መሳይ መኮነን

የህወሀቱ መሪ ደብረጺዮን ይህን የሚያረጋግጥ ነገር ትላንት ለአንድ የውጭ ሚዲያ ተናግሯል። ጠ/ሚር አብይም በአንዳንድ መድረኮች በገደምዳሜም ቢሆን ገልጸዋል። ለምን በይፋ ድርድሩን ማካሄድ እንዳልተፈለገ የሚታወቅ ነገር የለም። ግራ የገባ ነገር ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ምን ለማግኘት እዚህ ድርድር ውስጥ እንደገባ ለህዝብ መግልጽ ያልፈለገበት ምክንያት እንቆቅልሽ ነው።

ለአገራችሁና ለህዝባችሁ ህልውና ወደር በሌለው ፍቅር ነፍሳችሁንና ደማችሁን ሳትሳሱ የገበራችሁና ዛሬም ግንባራችሁን ያላጠፋችሁ የቁርጥ ቀን ልጆች ክብርና ምስጋና ይገባችሁዋል። ደማችሁና አጥንታችሁ የኢትዮጵያ መሰረትና ታዛ ነው። የእናንተን ጀግንነት ጊዜና ቦታ ፈጵሞ አይሽረውም!

ደብረጺዮን አሁንም የቀደመው የህወሀት አቋም እንዳልተቀየረ ይናገራል። ስለወልቃይትና ራያ ምንም የተለወጠ አቋም እንደሌላቸውና የአማራ ሃይሎች ከእነዚህ አከባቢዎች እንዲወጡ ትኩረት ሰጥቶ ይገልጻል። ሌሎቹም የህወሀት ጥያቄዎች አንዳሉ ናቸው። ታዲያ የኢትዮጵያ መንግስት ከህወሀት ጋር ንግግር የጀመረው ምን ሰጥቶ ምን ለመቀበል ነው?

ድርድር ወይም ንግግር ጨርሶ አያስፈልግም የሚል ግትር አቋም የለኝም። ግን በህወሀት ህልውና፣ በመሪዎቹ እጣ ፈንታ ላይ የሚደረግ ንግግር ቢያንስ መስዋዕትነታችንን የሚመጥን ነው። ያም ባይሆን እንኳን እነወሎ ሳይፈርሱ፣ አፋሮች መከራ ሳይበሉ በፊት መሆን ቢገባው ቢያቅረንና ቢጎረብጠንም ሞትና ውድመትን እናስቀራቸው ነበር። ተገድለን፣ ተዘርፈን፣ በቁም ተግጠን አልቀን፣ መከራ ከበላን በኋላ ድርድር ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ምንም ዓይነት የአቋም ለውጥ ካላሳየውና አሁንም ከእነእብሪቱ ከሚፎክረው ህወሀት ጋር ንግግር ማድረግ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጠው ትርጉም ምን ሊሆን ይችላል ተብሎ ታስቦ ይሆን?

የህወሀትን ሀይል ትጥቅ የሚያስፈታ፣ ወንጀለኞችን አሳልፎ ለፍርድ የሚያቀርብ አልያም ደግሞ የአሜሪካው ዲፕሎማት ኸርማን ኮህን እንደሚሉት ለህወሀት መሪዎች የወንድ በር ተሰጥቷቸው ከሀገር እንዲወጡና በስደት እንዲኖሩ የሚያደርግ ንግግር አልያም ድርድር ቢሆን ቢያንስ በጦርነቱ የተሰዉት ኢትዮጵያውያን ደም ከንቱ አልቀርም በሚል እንጽናናለን። የህወሀት የቀድሞ አቋሞች ባሉበት፣ እነዚያ የእብሪት ጥያቄዎች ላይ የሚደረግ ንግግርም ይበሉት ድርድር ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ውርደት ነው። በሚመራው መንግስት ክህደት ተፈጽሞበታል ብሎ ለመደምደም የሚያስችል በቂ ምክንያት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጸረ-ኦርቶዶሱ ብልጽግና ቁማርና ደጋፊ ሚዲያዎቹ - ሰርፀ ደስታ

የደብረጺዪን የትላንቱ መግለጪያ አላማረኝም። የኢትዮጵያ ህዝብ ዳግም አንገቱን የሚሰብር ዜና ከፊት ሊኖር እንደሚችል ጠቋሚ ነው። መንግስት በቅድሚያ ድርድር ወይም ንግግር እየተደረገ መሆኑን በይፋ መግለጽ አለበት። ከህዝብ ጀርባ የሚደረግ ማንኛውም ድርድር ኢትዮጵያ የምታሸንፍበትም ቢሆን አካሄዱ ከፍተኛ አመኔታን ያሳጣል። ድርድር መኖሩን መግለጽ ብቻ ሳይሆን ለምን ማድረግ እንዳስፈለገ፣ ምን ሰጥተን ምን ለማግኘት አልመን እንደገባንበትና ሌሎች ጉዳዮች ለህዝብ ግልጽ ተደርገው መነገር ይገባቸዋል።

እነስብሃት ነጋ ነጻ ሲደረጉ የኢትዮጵያ ህዝብ ስሜት ፈጽሞ ከግምት ውስጥ እንዳልገባ በቅርብ የምናስታውሰው ነው። ብዙ ውሳኔዎች የህዝብን የልብ ትርታ ወደ ጎን ተገፍቶ የሚወሰኑ መሆናቸው የፈጠሩትን ብሄራዊ ስብራት ልንዘነጋው አይገባም። አሁንም መንግስት በዚህ ‘ህዝብ ምንም አያመጣም’ አይነት በሆነው አደገኛ አካሄዱ መቀጠል የፈለገ ይመስላል። ጥሩ አይደለም። የሚመሩትን ህዝብ ያላከበሩ መንግስታት መጨረሻቸው አያምርምና ይታሰብበት።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

1 Comment

  1. መሳይ መኮንን ከሰማው ወሬ ውጭ መረጃ የለውም። ደብረጽዮን በቢቢሲ መግለጫ ሰጠ ማለት ይታመናል ማለት አይደለም። የደብረጽዮን እና የትህነግ ዓላማ ሰላም ፈላጊ እና ፈጣሪ መስሎ በውጭው ዓለም ፊት መታየት ነው። ይቺን ታክል እንዴት መጠርጠር እንዳልቻለ ይገርማል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share