የባቢሎን ኮሙኒኬሽን የሃገራዊ ህብረታችን ጸር ነው! – ገለታው ዘለቀ

ረቂቅ ነገሮችን በምሳሌ እያነሳሱ መወያየት እንዴት ጠቃሚ መሰላችሁ?።  ምሳሌ (analogy) በሰዎች ህይወት ውስጥ ትምህርትን ለረጅም ጊዜ ጠብቆ የሚያቆይና ረቂቅ የሆነ ሃሳብን ግዘፍ ነስቶ በአእምሯችን በቀላሉ  እንድናየው የማድረግ  ልዩ ሃይል ያለው ነገር ነው። ታዲያ  ዛሬ ከአንድ የጥንት ታሪክ በተለይ ስለ ተግባቦት ወይም ስለ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የምንማረው ነገር ትውስ ባለኝ ጊዜ ከወገኖቼ ጋር ለመወያየት ተነሳሁ…………።

መቼስ በታሪክ ስለሚነሳው የባቢሎን ግንብ ጉዳይ ሁላችን ሰምተናል። በጥንት ጊዜ የሰው ልጆች ኮሙኒኬሽን ጠንካራ ነበር። ተግባቦታቸው ሃያል ነበር። ይሁን እንጂ ከእለታት እንድ ቀን እንድ ሰው ድንገት ተነሳና ኢንዲህ ሲል መከረ

ጎበዝ አንድ ነገር ታየኝ አለ ለማህበሩ አባላት ሁሉ

ወንድማችን ሆይ! ምን ታይቶህ ነው እስቲ እባክህ አካፍለን? አሉት የማህበሩ አባላት  በጉጉት ……

የሸክላ ጡብ እንስራና አንድ አስከ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንገንባ፣ ከዚህ ከምናየው ደመና በላይ ከደረስን የመንግስተ ሰማያት በር ላይ ደረስን ማለት ነው። ይህ ስራችን ከኣምላክ ያጎራብተናል። ከዚህም በላይ ኣሻራችን ሁሉ ዘመን ተሻጋሪ ይሆንና ትውልድ ሁሉ ሲያደንቀን ይኖራል……………. አለ።

በዚህ ሃሳብ ብዙዎች ተገዙና ጭብጨባው ቀለጠ። ግጥም ተገጠመ፣ ዘፈን ተዘፈነ፣ ካርታ ተሰራ፣ ኣሰሪና ሰራተኛ ተለየ፣ የስራ ክፍፍል ተደረገ። ባቢሎን የድንጋይ እጥረት ስላለባት ጡብ ማምረት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነበርና በአንድ በኩል ጡብ የሚያመርት ሰራዊት በሌላ በኩል የተመረተውን ጡብ የሚገነባ ሰራዊት ተገነባና ይህ ሰራዊት ጎን ጎን ስራውን  አጦፈ፣  ግንቡ ተጀመረ……..።  በብዙ ድካም ግንቡ ከፍ እያለ መጣ…….። በዚህ ስራ ላይ የማይሳተፍ የለም ተባለ………። ህዝቡ በሚችለው ሁሉ ያለውን ይወረውራል…….። ግንበኞች ማታ ማታ አረፍ ሲሉ ፓርቲ እያደረጉ ይደንሳሉ…………። የባቢሎን ግንብ በእንዲህ ኣይነት ሁኔታ ትንሽ ከገፋ በኋላ የነዚህ ሰዎች ፍላጎት (motive) እግዚኣብሄርን ከሰማይ እጅግ አስከፋው። ታዲያ አምላክ ሲከፋው ጊዜ እርምጃ መውሰድ ፈለገ።  ይህ ርምጃ የሰራተኛውን ኮሙኒኬሽን መምታት ነበር። ስለሆነም  ግንበኞች  በስራ ላይ እያሉ ድንገት ቋንቋቸው ሁሉ ተደበላለቀባቸው። ግንቡን የሚሰሩ እልፍ ሰዎች አዲስ በመጣው የኮሙኒኬሽንና ተግባቦት ችግር ትርምስ ውስጥ ገቡ። ከላይ ከግንቡ ጫፍ ላይ ያለው ዋና ግንበኛ ከታች ያለውን ሰው  እስቲ እባክህ ጡብ አቀብለኝ ሲለው ይሄኛው ከታች ያለው ሰው ጭቃ ያቀብለው ጀመር። ኣንዱ ውሃ ሲጠይቅ ሌላው ጡብ ይወረውርለት ጀመር። አንዱ በዚህ በኩል ሳብ ሲል ሌላው በዚያ በኩል ይጎትታል። መደማመጥ፣ መግባባት የሚባል ነገር በድንገት ከባቢሎን መንደር ተነነ………….።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሤራና ግድያ ሀሤራና ግድያ ሀገርን ያፈርሳል እንጂ አይገነባም! - አሣምነው ጽጌ

የግንበኞች ቁጣና ንዴት ተበራከተ። አንዳንዶች እርስ በርስ ተደባደቡ። ሌሎች ንግግር አቁመው ኩርፊያ ውስጥ ገቡ። ጭቃ አቀብለኝ ስልህ ጡብ እያቀበልክ ትቀልዳለህ ወይ? የምንሰራው ስራ የሁላችንም ኣይደለም ወይ? እያሉ ሁሉም ያጉረመርማሉ። ነገር ግን እንዱ ያንዱን ልሳን አልረዳው አለ። ግራ መጋባት በዚያ ግንብ ዙሪያ ሰፈረ።  ይሄኛው ሰው የሚለውን ያኛው ኣይሰማም። ትርምስና ጥል ክርክር ሲበዛ ኣንዳንዶች የሰሩትን ጡብ እየፈነቃቀሉ ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ ኣይነት ትርምስ ውስጥ ገቡ። የባቢሎን ግንብ በኮሙኒኬሽን ምክንያት ሳይሳካ ቀርቶ እነሆ የተረት የተረት ሆኖ ቀረ……….።

ከዚህ ምሳሌ የምንማረው ነገር ብዙ ነው። የሰው ልጅ በሚመሰርታቸው ትናንሽ ማህበሮች ብቻ ሳይሆን እስከ ትልቁ ማህበር ማለትም እስከ ሃገራዊ ማህበራችን ድረስ ኮሙኒኬሽን የኑሮዎቻችን ሁሉ የጀርባ አጥንት ነው። አንድ ማህበር የኮሙኒኬሽን ችግር ከገጠመውና ቋንቋው ከተደበላለቀ የሚሰራውን ስራ ሁሉ ከግብ ኣለማድረስ ብቻ ሳይሆን የሰራውን ሁሉ ሊያፈርሰው ይችላል።

እንደ ህዝብ ከእቁባዊ ማህበራችን ጀምሮ የግንኙነቶቻችን፣ የመረጃዎቻችን ጥራት የማህበራችንን ኣላማ ለመፈጸም የሚኖረንን የሃይል መጠን ይወስነዋል። በተለይ ደግም ትልቁና ወሳኙ ሃገራዊ ህብረታችን ከፍተኛ የኮሙኒኬሽን ጥራት ያስፈልገዋል። መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር የሚገናኝበት መስመር ላይ የቋንቋ መደበላለቅ ካለው፣ ኪሳራው ከባድ ነው። መሪዎች የቋንቋ መደበላለቅ ከገጠማቸው የሚገነቡት ነገር ኣይኖርም። መንግስት ለህዝቡ የሚሰጠው መረጃና በየጊዜው የሚተገብራቸው ተግባራት ተጠይቅን (logic) የማይጠብቅ ሲሆን ህዝቡ በሃይል ግራ ይጋባል። ከፍተኛ ግራ መጋባት ሲሰፍን ደግሞ ቁጣና እልህ ማህበራችንን ያምሳል። የባቢሎን ሰዎች ከፍ ካለው ጋር ስለተጋጩ ኮሙኒኬሽናቸው ተመታ።

ዜጎች ከፍተኛ የዴሞክራሲና የፍትህ መርሆዎችን ማመሳከሪያ እያደረግን የመንግስትን ተግባራትና መረጃዎች መተንተን የዜጎች መብትና የሚጠበቅ ነው፣ በዚህ ጊዜ የመንግስት የቀን ተቀን ተግባር ጥያቄ ለማኝ ሲሆን ኮሙኒኬሽን አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው። ለዴሞክራሲያዊ መርሆዎች የማይገዙና የሚፋለሱ ድርጊቶችን ስናደርግ፣ ላጠፋነው ጥፋት የምንሰጣቸው ምላሾች ኣሳማኝ ያልሆኑ ምክንያቶችን ስናቀርብ፣ አንዱ መግለጫ ከሌላው ሲላተም ከህዝብ ጋር የሚኖረን ኮሙኒኬሽን ተበላሸ ቋንቋ ተደበላለቀ ማለት ነው። በመንግስትና በህዝ በመግስት ሰዎች መካከል ባቢሎን ፈጠርን ማለት ነው። መንግስት ተጠይቆችን የማይጠብቅ ነገር ሲያደርግ  ህዝብ ሁል ጊዜም መንግስት ይህን ፈቶ ይህን ለምን አሰረ…..፣ ይህን አስሮ ይህን ለምን ፈታ…… ይህን አንስቶ ያንን ለምን ጣለ፣ ያንን ጥሎ ይህንን ስለምን አነሳ…… ። እያለ መላ ይመታል።  የመንግስትን ስራዎች  በሚዛኑ ይለካቸዋል። ወደድንም ጠላንም የሪፐብሊክ ዘመን እንደዚህ ነውና። ስለዚህ መንግስት የተግባር ቋንቋውም ሆነ መግለጫዎቹ የሚጣረሱና የሚፋለሱ ሲሆኑ በህዝብና በመንግስት መካከል የባቢሎን ነገር ተፈጠረ ማለት ነው። ከተለያዩ ባለስልጣናት በአንድ ጉዳይ ላይ ተለያየ መግለጫ ከወጣ በዚያ መንደር ባቢሎን ተፈጠረ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ህዝብን ግራ ያጋባል። ማህበርን በመላምት ብዛት ያደናግራል። ለነገሩ መንግስት ብቻ ሳይሆን  የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከህዝብ ጋር የሚኖራቸው የኮሚኒኬሽን ጥራት በህዝብ ዘንድ የሚኖራቸውን የቅቡልነት (legitimacy) መጠን ይወስነዋል።  ከፍ ያለውን መርህ የጣሰና የተጣረሰ ስራ ስንሰራ ህዝቡ ከመርሆዎች ኣንጻር እያነጸረና ከተጠይቆች ኣንጻር አየመዘነ  ያቀለናል። ኮሙኒኬሽን እጅግ በጣም ወሳኝ የሆነ መስመር ነውና ስለሃገር ሲባል ሁሉም ማህበራት መጠንቀቅ ኣለባቸው። ከፍ ሲል እንዳልኩት በተለይ መንግስት በየእለቱ በሚያደርጋቸው ነገሮች ህዝቡን ግራ ማጋባት የለበትም። በቅርቡ አንዱ ሰው ግራ መጋባቱን እንዲህ ሲል ገለጸ። ጀነራል ባጫ ከጥቂት ቀናት በፊት የሙሉ ጀነራልነት ማእረግ አገኙ የሚለውን ዜና አጣጥሜ ሳልጨርስ አሁን በሳምንቱ አምባሳደር ተባሉ የሚል ዜና እያየሁ ነው ግራ አጋቢ ነው በውነት ይላል። ሌላው  ደግሞ የዛሬ ሳምንት እንዲህ ተብለን ነበር ዛሬ ደግሞ ይሄ ሆነ ምን እየሆነ ነው? አያለ ይደመማል ……..። የመንግስት ባለስልጣናት መግለጫዎች እርስ በርስ ይጋጫሉ፣ ምንድን ነው ነገሩ? የሚሉ ድምጾች ሲበዙ በጋራው ቤታችን ባቢሎናዊ ኮሙኒኬሽን እየተፈጠረ መሆኑን ያሳያል።   በተለይ መንግስት ለህዝብ የሚቀርቡ ነገሮችን በጥራት ማቅረብ ካልቻለ፣ ለሚፈጽማቸው ነገሮች ሁሉ ተጠይቁን የጠበቀና ጥራት ያለው  ምላሽ ካላቀረበ፣ ስራዎቹና መግለጫዎቹ ከመርህ ጋር የሚጋጩ ከሆነ፣ ኮሙኒኬሽን ፈረሰ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሃገርን ከምንም በላይ ይጎዳል። ስለዚህ ባቢሎናዊ ኮሚኒኬሽኖች መወገድ አለባቸው። ከባቢሎን ወንዞች ማዶ ያለውን በጎ የኮሙኒኬሽን መስመሮች መናፈቅ ለዚህም መስራት ያስፈልጋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  «የቅማንቶች ጥያቄ» ነበር. . . | አቻምየለህ ታምሩ

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን  ይባርክ

5 Comments

  1. በቅድሚያ አቶ ገለታውን ለዚህ ጽሁፋቸው ሳላመሰግን አላልፍም።
    ጽሁፉ በአንድ ዓላማ ላይ በተሰለፉ መካከል እራሳቸውን ከፈጣሪ ጋር በማወዳደራቸው ወይም ለመወዳደር በመድፈራቸው ምክንያት በፈጣሪ ቁጣ ቋንቋቸውን ለያይቶ ካሰቡበት ሳይደርሱ እርስ በርስ ሳይግባቡ ጅምራቸው ከውጤት ላይ ሳይደርስ መለያዬታቸውን የሚያበስርና ከዚህ አይነቱ አለመግባባትና አቅምን አለማወቅ ብሎም ውድቀት ለመዳን አቅማችንን ማወቅ እንዳለብን ፣ከመጠራጠርና ከይሆናል ወጥተን ተባብረን እንድ ቆም የሚያሳስብ ነው።
    በግርፍፉ ትክክልና ተገቢ መልእክት የያዘ መሆኑ አይካድም፤ሆኖም ግን በእኔ እይታና እምነት በእኛ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለ ልዮነት በአንድ ተመሳሳይ ዓላማ ላይ ያረፈ አይደለም ።ሁላችንም እንደ ባቢሎን ግንብ አገራችንን ለመገንባት ሳይሆን የተነሳንበት አንዱ የተገነባችውን አገር አፈርሳለሁ፣የተገነባችበት ጡብ (ጎሳና ማህበረሰብ )እንዳለሁ ሲል ሌላው ደግሞ እንዴት ሲደረግ፣በጭራሽ አይደረግም በማለት የቆመ ነው።ባጭሩ የውዝግብ መነሻ በአፍራሽና በአለአፍራሽ መካከል ያለ ልዩነት ነው።
    ህዝብና መንግሥት የተባሉትም በነዚህ ክፍሎች የተመደቡ ናቸው።በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ኢትዮጵያ የጎሳ ስብስቦች የገነቧት አገር ነች፣አንዱ ጎሳ በሌላው ጎሳ ትእዛዝና ፍላጎት የተመሰረተች አገር ነች፣ስለሆነም እያንዳንዱ ጎሳ( ጡብ )ከግንባታው ወጥቶ እራሱን ችሎ ግንብ ሆኖ ይኑር የሚል ህዝብ የሚያራምድ ነው።
    ማጠቃለያ የተነሱበት ዓላማ የተለያዬ ስለሆነ
    አፍራሽና ገንቢ ሊግባባ የሚችልበት ምንም አይነት መንግድ ያለ አይመስለኝም።ለትልቅነትና ለተሻለ ቁመና የተመሰረተን ይዞ መቀጠል እንጂ አፍርሶ መሄዱ ልዩነቱን አያጠፋውም።አፍራሽን ገንቢ አድርጎ መቁጠር በርታ ቀጥልበት ብሎ ማፍረሻ መሳሪያ ማቀበልና ማበረታታት ነው።በሥልጣን ላይ ያለውንም ቡድን ለኢትዮጵያ ግንባታ የቆመ አድርጎ መማዬት እንዲሁ።

  2. አቶ ገለታው የትልቅ ሰው ልጅ ነው ባለፈው ቆጥቦ እንደነገረን የቤተሰቡም ማህተም ታሪካችን ላይ አርፏል የትልቅ ሰው ልጅ ሁልጊዚም ትልቅ ነው።

  3. ውድ ወንድሜ አቶ ገለታው ዘለቀ !
    በየጊዜው አንዳንድ ጽሁፎችን ትጽፋለህ። መጻፍህ መላክም ነው። አሁን ደግሞ በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር የኮሙኒኬሽን ችግር ነው ብለሃል። ይህ ችግር በራሱ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ብሎ ጥያቄ መጠይቅና መልስም ለማግኘት መጣር ያስፈልጋል። ያነሳሃቸው ጉዳዮች ትክክል ቢሆንም፣ ያነሳኸው አለመግባባት በእኛ አገር ብቻ ያለ ችግር አይደለም። ምናልባት የጎሳ ጉዳይና፣ አሁን ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ ያለው ግብግብ የአገራችንን ሁኔታ ልዩ ቢያደርገውም፣ በመሰረቱ በእኛና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተመሳሳይ ችግሮች አሉ። 1ኛ) ራሱ መንግስት ማለት ምን ማለት ነው? ተግባሩስ ምንድነው? የሚሉት ጥይቄዎች በደንብ በግልጽ የተቀመጡ አይደሉም። እንደምታውቀው በአገራችንም ሆነ በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተዋቀሩት መንግስታትና ስልጣንን የሚይዙት ከውስጥ ኦርጋኒካሊ ከታች ወደ ላይ ያደጉና የዳበሩ አይደሉም። ከውጭ በህዝብ ላይ የተጫኑ ናቸው ማለት ይቻላል። በዚህ መልክ የተዋቀሩት መንግስታት ምንም ዐይነት ፍልስፍናና ርዕይ ያላቸው አይደሉም። የመንግስትን ምንናትና ኃላፊነትን በሚመለከት ከፕሌቶ እስከ ሁምቦልድትና በሌሎችም ፈላስፋዎች በሚገባ ተተንትኖ ተቀምጧል። ይኸውም መንግስት ሲባል ጨቋኝ ሳይሆን የእየንዳንዱን ግለሰብ ነፃነት የሚጠብቅና፣ እያንዳንዱም ግለሰብ ራሱን የሚገልጽበትንና ምኞቱን ውይም ፍላጎቱን ተግባራዊ የሚያደርግበትን መድረክ ማዘጋጀት ነው። ስለሆነም ገዢዎች ወይም የመንግስትን መኪና የጨበጡትና ህዝብን የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጣቸው ከፍተኛ የሞራል ብቃትና ዕውቀትም እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ይህም ማለት ከፍተኛ ንቃተ-ህሊና ያላቸውና ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚችሉ መሆን አለባቸው። የሚያስተዳድሩትም ህዝብ ሰው እንደመሆኑ መጠን እንደማንኛችን ፍላጎትና ምኞት አለው። ሰላምን ይፈልጋል። ክብርን ይሻል። ሰርቶና ቤተሰብ መስርቶ መኖር ይሻል። ይህም ማለት በተቻለ መጠን ከስቃይ ይልቅ ደስታን ይሻል። ለዚህ ሁሉ ደግሞ መንግስት የሚባለው ፍጡር ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት። ሰለሆነም መንግስት የሚባለውና አገዛዙ አንድ ህብረተሰብ ከሁሉም አቅጣጫ የመመልከትና ህብረተሰቡ ሚዛኑን የሚያጣ ከመሰላቸው ወይም ደግሞ የሰፊውን ስነ-ልቦና የሚያበላሹ ነገሮች ሲስፋፉ እንዲቆሙ በአስቸኳይ እርምጃ ለመውሰድ የሚችሉ መሆን አለባቸው። ህዝቡም ራሱን ከማንኛውም አደጋ እንዲከላከል ይችል ዘንድ የግዴታ ንቃተ-ህሊናው የሚዳብርበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለባቸው። ሰፊው ህዝብ ሲማር፣ ሲያውቅና ሲደራጅ ራሱንም ከማንኛውም ከውስጥ የሚፈጠሩም ሆነ ከውጭ የሚመጡ አደጋዎችን ለመቋቋምና ለማረም ይችላል። እንደሚታወቀው ያልተማረና ያልነቃ፣ እንዲሁም የራሱ ድርጅት የሌለው ህዝብ በቀላሉ ለአደጋ ይጋላጠል። ለዚህ ነው የውጭ ኃይሎች እንደፈለጋቸው በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ እየገቡ እንደፈለጋቸው ለመፈትፈት የሚጥሩት። በእኛ ምሁራንና በፖለቲከኞች የአስተሳሰብ ድክመት የተነሳም ያለውን ክፍተት በመጠቀም እንደፈለጉት ያሽከረክሩናል።
    እንደምታውቀው የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩ ወይም ገዢዎች ሰራተኛውና ገበሬው፣ እንዲሁም ሌላው በሰራውና በአፈራው፣ ቀረጥ በመክፈል ነው ራሳቸውን የሚመግቡና ሌሎችን መንግስታዊ ተግባራትን የሚፈጽሙት። ስለሆነም የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩ አስተዳዳሪዎች የህዝብ አገልጋዮች እንጂ በህዝብ ላይ የሚመጻደቁና የሚሆን የማይሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ህዝብን ወደ ድህነት ዓለም የሚገፈትሩ መሆን የለባቸውም። በሌላ ወገን ግን የመንግስትን መኪና የጨበጡ የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ግዴታቸውን የማይወጡ ከሆነ የግዴታ ኢ-ፍትሃዊነት ይፈጠራል። ኢ-ፍትሃዊነት በሰፈነበት አገር ውስጥ ደግሞ ማህበራዊ ግጭቶች ይፈጠራሉ። መንግስት የሚባለው ለህዝቡ የሚሆን የስራ መስክ ስለማይከፍትና፣ ህዝቡም እንዲማር አስፈላጊውን ነገሮች ስለማያደርግ የሰው አስተሳሰብ በማይረቡ ነገሮች ይጠመዳል ማለት ነው። ይህ በራሱ በሰው ዘንድ ወይም ደግሞ ፖለቲካ ያገባኛል በሚለው ዘንድ አለመግባባትን ይፈጥራል ማለት ነው። ነገሩን መስመር ለማሲያዝ በአገራችን ምድር ያለው ትልቁ ችግር የመንግስትን መኪና የጨበጡ ሰዎች አንድ አገርና ህዝብ እንደማህበረሰብ እንዲገነቡ፣ መግባባት እንዲኖርና ሰላም እንዲሰፍን ምን ምን ነገሮች ቀስ በቀስ መወሰድ እንዳለባቸው የማይገነዘቡ ከሆነ ወይም ደግሞ አንድ ችግር ሲፈጠር ለምን ተፈጠረ? ብለው ራሳቸውን የማይጠይቁ ከሆነ የግዴታ በመንግስትና በህዝብ መሀከል አለመግባባት ይፈጠራል ማለት ነው። ያም ተባለ ይህ በአንድ አገር ውስጥ አለመደማመጥና አለመግባባት የሚፈጠረው፣ ከዚህም በመነሳት ወደ ግጭት ውስጥ የሚገባው መንግስት የሚባለው ፍጡር የሚሰራውን የማያውቅ ከሆነ ብቻ ነው። የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከት ባለፉት አርባ ዓመታት ስልጣንን የጨበጡና የዛሬውም አገዛዝ ጠለቅ ያለ ዕውቀትና የሞራል ብቃት የሌላቸው ናቸው። ስለሆነም ዛሬ የተናገሩትን ነገ መልሰው አይደግሙትም። ወይም ደግሞ ሰው በደንብ የማያዳምጥ እየመሰላቸው በገሃድ ይዋሻሉ።
    የፋሺሽቱን የወያኔን አገዛዝ ድርጊት ትተን ወደ ዛሬው አገዛዝ ዘንድ ስንመጣ ባለፉት አራት ዓመታት በአገራችን ምድር ከለውጥ ይልቅ ከፍተኛ ነውጥ ነው የምናየው። ዶ/ር አቢይ አህመድ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ ህዝባችን አንዳችም ጊዜ እረፍት አግኝቶ አያውቅም። አማራው በማንነቱ ሲገደልና ሲፈናቀል፣ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች በገሃድ ሲገደሉ፣ ከተማዎችና መንደሮች በተደራጀ መልክ ሲፈርሱ፣ ይህንን ድርጊት ሁሉ የፈጸሙና የሚፈጽሙ ምንም ዐይነት ክትትል አይደረግባቸውም። አንዳንዶች ተጠርጥረውና በተጨባጭ ማስረጃ ከታሰሩ በኋላ በመንግስት ሽፋን እንዲፈቱ ይደረጋሉ። በሰሜኑ ክፍል በሰሜን ዕዝ ላይ እንደዚያ ያለ ዐይነት አሳዛኝ ድርጊት በወታደሩ ላይ ከተፈጸመና፣ ወታደሩም በአጭር ጊዜ ውስጥ አጻፋውን ሰጥቶ ድል ከተቀዳጀ በኋላ በአቢይ ትዕዛዝ ወታደሩ መቀሌንና ሌሎች አካባቢዎችን መሳሪያውን ጥሎ እንዲወጣ ነው የተደረገው። ወታደሩ ትግሬ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ከወያኔ ተዋጊዎች መሳሪያ እንዳይነጥቅ በአቢይ ትዕዛዝ ነው እንዲቆም የተደረገው። ወታደሩ ካፈገፈገም በኋላ ወሎ፣ አፋርና ጎንደር ድረስ ወያኔ ዘልቆ እንዲዋጋ የተደረገው ካለምክንያት አይደለም። አማራውን ለማዳከም ነው። በኮምቦልቻ፣ በደሴና በሌሎች የወሎ ከተማዎችና በአፋር ውስጥ የተፈጸመውን ዘግናኝ ድርጊት ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። በሀብትና በህዝብ ላይ ይህ ሁሉ አሰቃቂ ውርጅብኝ ሲወርድ ወታደሩ ዝም የሚመለከት ወይም ደግሞ እንዲያፈገፍግ ትዕዛዝ የሚሰጠው ነበር። በጦርነት ታሪክ ውስጥ ባልታየ መንገድ ወታደሩ ለማጥቃትም ሆነ ለማፈግፈግ ትዕዛዝ የሚሰጠው ከጠቅላይ ሚኒሰተሩ ቢሮ በጠቅላይ ሚኒስተሩ ነው። ይህም ማለት በዚያ አካባባቢ በህዝብ ላይ ለተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት በቀጥታ የሚጠየቀው ጠቅላይ ሚኒስተሩና አንዳንድ ዝም ብለው ትዕዛዝን የሚቀበሉ ጄኔራሎች ናቸው ማለት ነው። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ወያኔ ወደ አዲስ አበባ እየተቃረበ በመምጣት ላይ ነው ሲባል የዚያን ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ራሱን ለማዳን ሲል ሰፊው ህዝብ ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ አደረገ። ከእልክ አስቸጋሪ ጦርነትም በኋላ ወያኔ ከተቀጣና ከተሸነፈ በኋላ የያዛቸውን ቦታዎች ለቆ እንዲወጣ ተደረገ።
    ሰሞኑን ደግሞ የምንሰማው ከአሜሪካን በመጣ ቀጭን ትዕዛዝ መሰረት የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ከወያኔ ጋር ውስጥ ለውስጥ እንደሚደራደር ነው። ይህ ዐይነቱ ድርጊት ከፍተኛ ወንጀልና በህዝብ ላይ እንደመቀለድ ነው የሚቆጠረው። አንድ ፋሺሽታዊ ከሆነና ስንትና ስንት ወንጀል ከፈጸመ ሽፍታ ኃይል ጋር በምን መመዘኛ ነው 115 ሚሊዮንን እወክላለሁ የሚል መንግስት ለመደራደር የሚችለው? ይሁንና ግን እንደዚህ ዐይነት ድርድር አላደረግሁም በማለት መንግስት ለማስተባበል ሞክሯል። እነ ስብሃት ነጋ ስንትና ስንት ወንጀል ከሰሩ በኋላ ለምንድነው እንዲፈቱ የተደረገው? ለማንኛውም እንደዚህ ዐይነቱ እርምጃ መውሰድ የአገዛዙን፣ በተለይም የአቢይን መነፈሰ-አልባነት ነው የሚያረግጠው። ሰውየው ፖለቲካ ምን ማለት እንደሆእን ያልገባውና ተጨባጭ ሆኔታዎችንም ለማንበብ የማይችል መሆኑን ነው።
    ለማንኛውም ወደ አቶ ገለታው ዘለቀ አለመደማመጥና አለመግባባት ጉዳይ ጋር ስንመጣ፣ ሁኔታውን ከራሳችን የአዕምሮ አቀራረጽና ከቀሰምነው ዕውቀት ከሚባለው ውጭ ተነጥሎ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። ሳይንሳዊ ዕውቀት ባልተስፋፋበት፣ በተለይም ፖለቲከኛ ነን ባዮች ሎጂካዊና ራሽናል በሆነ መንገድ ማሰብ አይችሉም። ሎጂካዊና ራሽናል አስተሳሰብ ባልተስፋፋበት አገር ውስጥ ደግሞ በጥሞና ለመወያየት በፍጹም አይቻልም። ውይይት ቢካሄድ እንኳ ህብረተሰቡን በሚመለከቱ ጉዳዮችና እንዲመለሰለት በሚፈልጋቸው ነገሮች ላይ ሳይሆን፣ ሳይንሳዌ ግንዛቤ በማያስጨብጡና ለፈጠራ ስራ በማያመቹ እንደ ጎሳ በመሳሰሉት ወደ ምግብነት፣ ንጹህ ውሃ፣ መጠለያ፣ ትምህርትና ህክምናነት ወደ ማይለወጡ ትርጉም በሌላቸው ነገሮች ላይ የምንጨቃጨቀው። ከዚህ ዐይነቱ አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት ከተፈለገ ራሳችንን መመርመርና ችግርን በሚፈቱ ነገሮች ላይ ብቻ ማትኮሩ የጊዜው ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ እንደ አዲስ ሰው ሆኖ መፈጠር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ምክንያቱም ከሃያና ከሰላሳ ዓመታት በላይ በጭንቅላታችን ውስጥ ፕሮግራምድ ያደረግናቸው ነገሮች ስላሉ ከእነሱ በቀላሉ ለመላቀቅ ስለማንችል ነው።
    ለማንኛውም፣ በእኔ ዕምነት በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር ምን እንደምንፈልግና ለምንስ ዓላማ እንደምንታገል አለማወቃችን ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የአብዛኛዎቻችን ጭንቅላት በምድር ላይ የሚታዩ ችግሮችን በማያነብና፣ መፍትሄም ለመስጠት በማይችል የሚያጨቃጭቁ ነገሮች ፕሮግራምድ ሆኗል። በሌላ አነጋገርን፣ ከሳይንስ ርቀን የምንገኝና ከሳይንስ ጋር የተጣላን ነን ማለት ነው። ሳይንስና ፍልስፍና ሳይሆኑ የተሳሳተ ትረካ በተስፋፋበት አገር ደግሞ የግዴታ አለመግባባት አለ ማለት ነው። አብዛኛዎቻችን በፖለቲካ ዓለም ውስጥ የተሳተፍንም ሆነ የመንግስትን መኪና የጨበጡት ጭምር ጊዜ ወስደው ለጭንቅላት መዳበር የሚጠቅሙ መጽሃፎችን የማንበብ ጊዜ የላቸውም። ከዚህ ስንነሳ አንተ ለማብራራት የሞከርከው ነገር ይህን ያህልም የሚያስደንቅ አይደለም። ስለሆነም የኮሙኒኬሽንን ችግር ለመፍታት ራሳችን በቂ ዕውቀት አለን ወይ? የምንመራበትስ ፍልስፍና ወይም ርዕይ ትክክል ነው ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

    ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

    • ዶክተር እንደ ሁልጊዜው እናመሰግናለን ይህች ጽሁፍ የግርጌ ማስታወሻ ሁና ከምትወጣ እንዳልከው በእውቀትና አስተሳሰብ ለተጎዱ ለኢትዮጵያ ባለ ስልጣኖች( አገኘሁ ተሻገር፤ታየ ደንዳ፤ታከለ ኡማ፤አዳነች አቤቤ፤አረጋዊ በርሄ፤ብርሃኑ ነጋ፤ሺመልስ አብዲሳን ለመሳሰሉት ባድራሻቸው ብትልክላቸው ሰው ስለማያያቸው ተደብቀው ቢያነቡት ብዙ ይማሩበት ነበር።፡እኔ እንኳን ባለፈው አንተን ጨምሬ ለሀገሬ መፍትሄ ያመጣሉ ያልኳቸውን ስሞች ጠቅሼ ነበር።
      ሃገሩ መጫወቻ ሁኗል ዶ/ር አብይ “ተንትክትኮ ይሰክናል” ምን ታመጣላችሁ የሚል ዘይቤ አለው ይህ አላዋቂዎች የሚጫወቱበት የእኔም ሀብት ነው የእኔም ሀገር ነው ተወልደ ገ/ማርያም የተባለ ሰው በቁጥጥር ስር ይዋልልን ዘሩ እንጂ ችሎታው ተለክቶ በዚያ ቦታ የተቀመጠ አይደለም፤ ብዙ ወንጀሎች ሰርቷል ሲባል አብይ ጆሮ አይስጠውም። ሰሞኑን የተክለክለውን አዉሮፕላን በረራ ላይ እንዲዉል ያደረገ ሰው ነው ምክንያቱም ግልጽ ነው። ካሉን አምባሳደሮች ዉስጥ አብዛኛው እንኳን ኢትዮጵያን የምታህል አገር እራሱን መወከል አይችልም( ሱሌማን ደደፎ፤ሺፈራው ሺጉጤ….ይገኙበታል በእርግጥ ስዩም መስፍን ሌላውን ልሞክረው ብሎ ከቻይና አምባሳደርነቱ እራሱን አንስቷል። በዚህ አጋጣሚ የሱዳን፤የፈረንሳይ፤አምባሳደሮቻችንና ክቡር ታየ አስቀ ስላሴን ክብር ይገባቸዋል እላለሁ።፡ሌላው አምባሳደርም ሆኑ ሚኒስተሮች ከፍተኛ የሰራ ሃላፊዎች ልምድ እንዲወስዱ ስራ እንዲያበላሹ በዶ/ር አብይ የተሹሙ ናቸው። የአባይ ገቢ ማሰባሰቢያ አረጋዊ በርሄ ነው፤የማንነት አስመላሽ ኮሚቴም አረጋው በርሄ ነው ይህ ግለስብ ማንነትን ያጠፋ ሁኖ ሳለ ዛሬ ለዚህ ችግር ፈችነት አብይ መርጦታል። ታየ ደንዳ የጠብ ሚኒስቴር ከመሆን ይልቅ የሰላም ሚኒስትር ተብሎ ተሹሟል።አብርሀም በላይ በትግሬ ዉስጥ ክሙሉ ነጋ ጋር የህወአትን ሴል አጠናክሮ ዛሬ የመከላከያ ሚኒስቴር ሁኗል ነገሩ ሁሉ ለኦሮሙማና ለትግሬሙማ ግራ ባይገባም ለእኔ ግራ ገብቶኛል። ስለምታደርገው ሁሉ በግሌ ምስጋናዬ ይድረስህ። በዚህ አጋጣሚ የህዝብ እይታ ዉስጥ እንዳይገቡ የተደርጉ የእነ ሙስጠፌና የዶ/ር ስለሽ በቀለ ጉዳይም ያሳስባል።

  4. ሰላም ውድ ወንድሜ ለአቶ ሰመሰረ፣

    ለጤንነትህ እንደምን ሰንብተሃል? ለሰጠኸኝ መልካም አስተያየት በጣም አመስግንሃለሁ። ይህን ጽሁፍ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ ቢሮ አስተላልፌአለሁ። የሌሎች የኢ-ሜይል አድራሻ ስለሌለኝ ለመላክ አልቻልኩም። ጊዜ ሳገኝ አስፋፍቼ በድረ-ገጽ ላይ ለአንባቢያን አቀርበዋለሁ።

    ከመልካም ምስጋና ጋር

    ፈቃዱ በቀለ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share