የሃገሬ ሰው እንዲያው በዘያዊው ቋንቋ እያዋዛና እያጣቀሰ ሲወያይ አንጀት ያርሳል። ከሰሞነኛው ከክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን የስልጣን መልቀቅ ዳርዳታ ጋር ተያይዞ “ሳይካካ ተቦካ”ና “ምን ተይዞ ጉዞ” እንዲሉ ምክራዊ ትንታኔያችን ከማዥጎድጎዳችን በፊት “ እረጋ ያለ ወተት እርጎ ይወጣዋል” እንዲሉ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ ይረጋጉ እንላለን። ሃገር መምራት እኮ እንደሰሞነኛው “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” እንዲሉ ዓይነት ትዳር አይደለም። ጨራርሶ፣ እንደዘመኑ አነጋገር “ሂሳብ አወራርዶ” እየሆነ መጥቷል። ይልቅስ “ሚስጥር የባቄላ ወፍጮ አይደለምና” ሚስጥር ለራስዎና አካባቢው ላለ ሚስጥረኛ እንጂ ለነውናፍ ነፊ አልነበረም። ሁሉን ዘርግፈው አውጥተውታል። ሁሉን ነግረውናል።
እኛ እምንለው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከዲያስፓራ ተብየውና ከጥቂት ተስፈኞች ፊት“ የአመራር ብቃቴ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ከሆነ ስልጣኔን እንኮችሁ” ሲሉ ያስተዳድሩታል ተብሎ የሚታሰበው መቶ ሃያ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዕቁብ አልገባም? ወይስ ምንም አያመጣም ብለው ይሆን?። ኢትዮጵያዊ ገበሬውን፣ ሰርቶ አደሩን ፣ አርብቶ አደሩን ፣ አባቶችና እናቶችን ወ.ዘ.ተ. የኔ ናችው ብለው ይሆን?
ሃገረ ኢትዮጵያ አልተመቸኝም ብሎ ሀለተኛ ቤቱን ካመቻቸና መንግስታት በተለዋወጡ ቁጥር ቆዳቸውን እንደ እስስት እየገፈፉ “አለን አለን” ከሚሉ ከዕድሜ ጠገብ፣ ያውም ያሸማግሉኝል ብለው ካስመረጧቸው “ወጭት ሰባሪዎች” ጋር ያውም “በሚስጥር ያዙት” ብሎ ቃል መገባባቱና ቀለበት ማሰሩ ያዋጣል ወይ ? ኧረ ያስቡበት፣ ያስተዛዝባል። ሆድ በአንቡላና በፍርፋሪ ሲነፋ በታችም በላይም ከሚስት ጋር “እከክልኝ፣ ልከክልህ” የሚሉት የቃል ኪዳን ውል የጤና ነውን?
ጓድ ሊቀመንበር መንግስት እኮ ግራ ሲገባቸው የመንግስት ስራ ዘግተው “ የሃገሬ ሕዝብ ሆይ ዛሬ ማታ በቴሌቭዥን ምስኮት ጠብቀኝ እማወያይህ አለኝ ብለው ጎራዴ መዘው “ኧረ ጎራው” የሚሉ ነበሩ።
በአንዳንድ ጉዳዮች ጓድ መንግስቱ ጨካኝና ቀለሙን ተቋም ውስጥ ገብተው ባይራቀቁበትም ፣ ለሕዝብ ያላቸው ፍቅር አንቱ ያስብላቸዋል።
የሃገሬ ሰው ምን ይላል “ ከተራበ ጅብ የጠገበ ጅብ ይብላኝ” ይላል። ይሄን ስል ስሙን ሳይሆን ወርቁን ማየት የግድ ይላል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ‘የፊቴ ቀለም ካላማራችሁ “ሥልጣኔን እለቃለሁ” ማለትዎ የዋሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማሸበርና ሆድ ለመብላት እንዳልሆነ ማረጋገጡ የግድ የሚል ሆኖ፣ በእርስዎ የአመራር ችግር ይሁን፣ ከችግሮቹ መደራረብ፣ ከጠላት ሰፊ ዝግጅት፣ መሰሬነትና የእኔ ነው በሚሉት ጓድወ መከዳትና መልፈስፈስ በመጣ መደናገጥ/Frustration/ የተነሳ ስልጣኔን እለቃለሁ ማለትዎ እንዳለ ሁኖ ‘ለተራበ ጅብ አሳልፈው እንዳይሰጡን፣ከገባንበት ወይም ካስገባችሁን አረቋ ሳትስወጡን እማ ወዴት ነው ሽሽት!!! “ የእናቴ መቀነት አጎላደፈኝ ማለት!!!፣ “ሸሽተውስ የት ሊገቡ!!”?። እያልን ጥያቄእችን አናቀርባለን፣ የውስጡን ቅኔያዊ ሚስጥር እርስዎ ነው የሚያውቁት።
የጣዱትን ምጣድ አብስለውና ፈር ፈር ሳያሲይዙ እማ ወዴት ነው?። ይህማ ነውርና ክህደት ነው።
መቸም የኛ መንግስታትና መሪዎች አንዳንዴ የሥልጣኑን ዕርካብ ሲቆናጠጡና ችግር አፍጥጦ ሲመጣ እንመካከር፣ ተስፋም የመስጠትና ካልተመቸኋችሁ ሥልጣኑን እንኩአችሁ” ማለት ክስተታዊ ልምድና ስልታዊ ማፈግፈግ እየሆነ መጥቷል።
አቶ መለስ የአንድ ቡድን የሕውሃትን መሰሬ ዓላማ እንዳውለበለቡና በቆራጥና ጭቃኔ በተሞላበት አቋማቸው ንቅንቅ ሳይሉ እስከ ሩሃቸው ፍፃሜ ድረስ ከስልጣን የመውረድ ኑዛዜ አላደረጉም።
ዐፄ ኃይለሥላሴም ብልህ መሪና በተነፃፃሪነት ከኤርትራ ተገንጣዮችና ከትግራይ አስገንጣዮች ከሚቀርብባቸው ቅዋሜ በቀር በሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ቅቡልነት ስለነበራቸው ስልጣናቸውን ሙጭጭ አርገው በመያዝ አስከዕለተ መንፈንቀለ መንግስታቸው ድረስ ዘልቀዋል። አፄ ኃይለሥላሴ ወደመጨረሻው የንግሥናና የእርጅና ዘመናቸው ሥልጣናቸውን በሙሁራንና ህዝብ እንደተመከሩት ለልጆቻቸው ሥልጣናቸውን አስረክበው ቢሆን የተሻለች ሃገር፣ የደርግ መንግስት የማይፈነጭባትና መልካም ቁመና ያለት ኢትዮጵያ ትኖረን ነበር የሚለውን አመክንዮ ይህ ሂደት ገቢራዊ ስላልሆነ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ቢያዳግትም የሚበጀውን ህሳቢያቸውን ፈፅመው አሸልበዋል።
ጓድ መንግስቱ ኃይለማሪያምና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ የሚያመሳስላቸውና የሚጋሩት ነገር አለ። በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ፣ በእየመድረኩ እፍቅሮተ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚገልፁ፣ ኢትዮጵያን የሚደፍር፣ የሚአውክና የሚገዳደር ካለ መንግስቱ “አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር ድረስ ለእናት አገር እስከ ደም ጠብታ” የሚሉ። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ “ በኢትዮጵያ ለመጣ አንገቴን” የሚል ተምሣሏዊ አቋም ያላቸው ናቸው። በተለያዮ ጦርነቶች የመወጠር ተምሳሎት ስንዳስስ፣ፕሬዚዳንት መንግስቱ ያስተናገዱት ፈታኝ ጦርነቶች የሶማሊያው የዚአድባሬ ፣የኢሕአፓ፣ የኢዲዮ፣የሻቢያ ፣ የወያኔ፣የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወ.ዘ.ተ. ነበሩ። ይህ ሁሉ ሆኖ ልበ መሉው ፣ቆራጡና ትላንት እንደ ይሁዳ የኮነናቸው ጓድ መንግስቱ ምንም ጨቃኝ፣ ገዳይ ወ.ዘ.ተ. ቢሆኑ አሁን ቆራጥ ውሳኔ በሚያስፈልግበት ወቅት ልባቸውን “ለጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ቢያበዱሯቸው” እያልን ብምንሃብ እናፍቃቸዋልን። “ ቆፍጠን እንደመንጌ ለስለስ እንደ ኃይለማርያም “ እንዲሉ ነው ቅኝቱ።
ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም በ CIA ሽረባ ከስልጣን እስኪወገዱ ድረስ በአቋማቸው የረጉ ነበሩ። እንዲያውም አቡነ ገብርሔል ይመስለኛል ፣ ሕውሃትና ሻቢያ ሲያዋክቧቸው “ ቆራጡ ጀግና መንጌ ይህ ሁሉ ፈተናና የጦርነት ወላፈን ቢኖርም፣ ከዚች ወንበርዎ ቋንጣ ሁነው ይቀሯታል እንጂ ጥለውን አይሸሹም” ብለዋቸው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ባይበዛም እንደ ደርግ ስርዓት የጦርነት ፍልሚያ ከጅምሩ እንደ መንጌ በተመሳሳይ እያጋጠማቸው ነው።
ሰሞኑን ወጣቱ ኮሎኔል ልባችን ሊሰልሉት ይሁን ያጋጠማቸው ውስጠ ሚስጥር ባናውቀውም “በቀላሉ ሸብረክ ማለታቸው”፣ “ወይ ባልጀመሩት ፣አነካክተው ወዴት ?” እንዲሉ “ቆፍጠን ማለት ነው” “ የተናገሩት ከሚቀር ምን ይበል” የሚባል ነገር አለና።
የሚገርመው ሁለቱም ሁለት ተቃርኗዊ የሆነ ስህተት ፈፅመዋል። ጓድ መንግስቱ በስሜት “ በግንቦት1982 መፈንቅለ መንግስት የሞከሩትን ምርጥ የአገራችን ጀኔራሎች
፣ጀኔራል አመሃ ደስታ፣ጀኔራል ፈንታ በላይን ወ.ዘ.ተ. መረሸናቸው። ይህ ኢሰባአዊ ድርጊታቸው ቅጥ ያጣ ሆኖ ስርዓቱ ጥርሱ ላልቶ፣ በሻጥር ተተብትቦ ኮበለሉ ወይም እንዲኮበልሉ ተደረጉ። እሱን ለአምላክ እንስጠው።
ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አገር ያጠፉ፣ ትውልድን አረንቋ ውስጥ የከተቱ፣ አሁን የሚታየውን
አሳርና ፈተና ሃገራችን እንዲገጥማት ፋና ወጊወችን ወ.ዘ.ተ. በጅልነት፣በድፍረትና በሕገ ተቃርኖ፣ ባልተለመደ መልኩና ከማይታየው ድብቅ ምዕናባዊ ኃይል ጋር ግንኙነት ፈጥረው በ(Thelephaty) ተገናኝተው ፈቱ። ይህ ስህተት እንደ ጓድ መንግስቱ ዓይነት ተመሳሳይ የማፈትለክ ክስተት ያጋጥም ይሆን የሚለውን፣ የቆየ ሰው ይየው።
ይህ አብዛኝውን ሕዝብ ያንጫጫ፣ አጃየብ ያሰኘ ክስተታዊ ስህተት፣ ደንዛዛውና ደነዙ ዲያስፓራ “ይህ ዕፅብ ድንቅ ተአምራዊ ተግባሮት ነው ብሎ” እንጨበጨበ፣ መላውን ዲያስፓራ የማይወክል ቢሆንም።
እንግዲህ ቀጣዮን ክዋኔ የምናየው ሆኖ ከአቋማቸው ሸብረክ ብለው “ ሥልጣኔን ከፈለጋችሁ ይሄው ጀባ” ማለታቸው የጓድ መንግሥቱ አይነት የሆነውን ኩነታዊ የፊልም ፕሮቫ እያሳዩን ይሆን? የሚል ህሳቦት በአዕምሯችን ተጭሯል ። ይቅር ይበሉኝ ፣ ይህስ እርምዎ ነው !!! አያደርጉትም!! የሰይጣን ጀሮ አይስማው።
ይህን ያነሳሁት ከዚህ ሁሉ አርማገዲዮን መሰል የገዘፈ ፈተና ገብተን፣ መንገዱን ሳያለሰልሱና ኮረኮቹን ሳያስወግድ የትም ወልፈት ማለት አይቻልም፣ ኮለኔልነትዎን ማውረድ፣ ወንጀልም ነው። ለአባይ ግድብ የወጣው መፈክር “እንደ ጀመሩት ይጨርሱት” ለበልሃሰብማ ትተውን እንዳይነጉዱ፣ ነውር ነው!!።
“አደራ በምድር አደራ በሰማይ” እንላለን። ክብር ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንደ ዐፄ ቴዎድሮስ ለሃገረ ኢትዮጵያ ራስዎን መስዋት ያደርጋሉ ብለን እንመክርዎም። አደናግሮ የሚያደናግር፣ የትውልድ ተስፋና አሻራዎችን የሚያሳጣ ስራ ይሰራሉ ብለን አናስብም።
ሌላ መርግ፣ያልጠበቅነው ውሳኔና ሃገርን ከአደጋ የሚጥል ውሳኔና መንሸራተት ሰሞኑን
እንዳስኮሞኮሙን ድንጋጤ የተሞላበት /Shocking surprises/ አያረጉንም ብለን እናስባለን። አደራ እንላለን።
የሃገር ኢትዮጵያን ግፅታ፣ ማንነትና የሕዝቧን ታላቅነት ወደ ጎን ትተው ለአሰፈሰፉ አራዊቶችና ኢትዮጵያን ሊቦጫጭቁ ለአኮበኮበ ቡድኖች፣ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ለሆኑት አሳልፈው እንዳይሰጡን”። አምላክ መርጦ የሚበጀንን መሪ ዱብ እስኪ ያድርግልን ድረስ እርስዎ እንደጀመሩ እርስዎ እስከዚያው ዳር ለማድረስ ይሞክሩ” እንላለን።
በተረፈ ቀና ቀናውን ፣ ደግደጉን እንዲያስቡ አምላክ እንዲረዳዎ ሙጥኝ ብለን እንፀልያለን።
ቸር ይክረሙ ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር።
ከተዘራ አሰጉ
ከምድረ እንግሊዝ።