ከ1941-1945 ዓመተ ምህረት ድረስ ወደር በሌለው ጭካኔ አይሁዳውያን የተገደሉበት ጊዜ ነበር :: ዓለማችን ዛሬ መጋቢት 27ቀን ይህንን ክስተት ትዘክረዋለች ::
የሆልኮስት መሪ የነበረው ሂትለር ወደ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ አይሁዳውያንን በነዚያ ጥቂት አመታት ሲገድል በነዚህ አራትና አምስት አመታት ውስጥ በዚህ ጨካኝ ሰው አመራር በየቀኑ ወደ 3500 የሚሆኑ፣ በየሰዐቱ ወደ 291 የሚሆኑ አይሁዳውያን ይገደሉ ነበር ማለት ነው :: በጣም ዘግናኝ ነው በእውነት::
ለዚህ ሁሉ እልቂት በተለይ የሂትለር የጥላቻ ምንጭ (motive) ምንድን ነው? እያሉ ምሁራን ዛሬም ድረስ ይደመማሉ :: በጣም የሚያሳዝነውና ለዚህ ሁሉ እልቂት ምክንያት የሆነው ሂትለር አይሁዳውያንን በመጥላቱ ሳይሆን ሂትለር ይህንን ጥላቻውን በማንፌስቶ ላይ ቀርፆ ብዙ በጥላቻ የተሞሉ ካድሬዎችን በመግዛቱ ነው። በአለማችን ላይ ጥላቻ በቀላሉ የሚገዛቸው ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል። ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ የሚመስጣቸው፣ ለጥላቻ ክፍት የሆኑ ሰዎች በዚህ አለም ላይ ይኖራሉ። ነገር ግን ይህ ጥላቻ እየነዳቸው የሚያጠፉት ጥፋት ሁሌም ገደብ ይኖረዋል። ሂትለር በግል ጥላቻው ተገፋፍቶ ወንጀል ቢፈጽም የሚያደርሰው ጥቃት ኢምንት ይሆን ነበር። ነገር ግን ይህ ሰው አይሁዳውያንን መጥላቱን ለማሳመን መጽሃፍ ጽፎ ማኒፌስቶ ቀርጾ የናዚ ፓርቲን ተቀላቅሎ አሳምኖ መጣ። ቀጥሎም ብዙዎችን በጥላቻ ትምህርቱና ትንታኔው ማርኮ የዚህ ፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት ሊቀመንበር ሆኖ ቁጭ አለ። የአይሁዳውያን መከራ የበዛውና ግድያው እጅግ የከፋው ሂትለር ጥላቻውን በማኒፌስቶ ቀርጾ በማቅረቡና ተቀባይነት በማግኘቱ ወደ ፖሊሲ በመቀየሩ ከዚያም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የመንግስትን ማሺነሪ በመጠቀሙ ነው። በርግጥ ሂትለር የሚጠላውና የሚገድለው አይሁዳውያንን ብቻ አልነበረም። ስላቪኮችንም መግደል ያስደስተው ነበር። ሌሎች ብዙ ለዚህ ሰው የጥላቻ ማኒፌስቶ ልባቸውን ያልሰጡ ለዘብተኛ ጀርመኖችንም አስጨርሱዋል።
ከፍ ሲል እንደገለጽኩት ሂትለር ማይን ካምፕፍ (የእኔ ትግል) የሚለውን መጽሃፍ ሲጽፍ በዚህ መጽሃፉ ውስጥ የሚያቀርበው ትንታኔ የራሱን የጀርመን ዘር ኤርያን ወይም የላቀ ምርጥ ዘር መሆኑን በተለያየ መንገድ ያሳይና፣ ታዲያ ለዚህ ምርጥ ዘር ሁለንተናዊ እድገት የሁል ጊዜም ስጋት ናቸው ያላቸው ደግሞ በተለይ አይሁዳውያንን ነበር።
ሂትለር የወጣትነት ጊዜውን በቬይና ከተማ ያሳለፈ ሲሆን በዚያ ከተማ ውስጥ በዚያን ጊዜ የነበሩት የከተማይቱ ከንቲባ በዚሁ የአይሁዳውያን ጥላቻ የተለከፉ ሰው ስለነበር ከልጅነቱም ጥላቻ ሲሰበክ ይሰማ ስለነበር ይህንን ጥላቻ በልቡ ቁዋጥሮ የቆየ ሰው ነበር። ሂትለር ጥላቻውን ሳይንሳዊ አስመስሎና ማኒፌስቶ ቀርጾ የፖለቲካ ርዕዮት ሲያደርገው በአይሁዳውያን ላይ የጥፋቱን ጥግ እያሰፋ ነበር። በጥላቻ ብዙ ሰው ለመጨረስ የጥላቻ ፖለቲካ ትልቁ መሳሪያ ነውና። ሂትለር ያንን ዘግናኝ ፍጅት በመፈጸሙ ዘላለም በዚህ ታሪኩ ሲኮነን ይኖራል። ይህ ሰው ቢሞትም አለም አጽሙን አላሳርፍ ብሎ ዛሬም ይረግመዋል መንፈሱን ሁሉ ይታገለዋል።
በአይሁዳውያን ላይ የተፈጸመው ግድያ በቅርቡ በክፍለ አህጉራችን ላይ በሩዋንዳ ሃገር ከተፈጸመው በጣም ይበልጥ ነበር። ይሁን እንጂ በፍጥነቱ ማለትም በየቀኑ በነበረው ፍጅት የሩዋንዳውን እልቂት የሚደርስበት የለም። በሩዋንዳ ውስጥ ለመቶ ቀናት በቀን በአማካይ እስከ 8000 ሰው ይገደል ነበር። የዚህ ጥላቻ ምንጭ ምንድን ነው? ካልን አንድ ሁለት ሁቱዎች ቱትሲዎችን ስለጠሉ አልነበረም። በነዚህ አንድ መቶ ቀናት ነግሶ የነበረው የጥላቻ መንፈስ የተጠነሰሰው በኢንተር ሃሞይ መሪዎች ነበር። Théoneste Bagosora፣ Robert Kajuga እና ሌሎች የኢንተርሃሞይ አመራሮች ለዚህ ፍጅት ማኒፌስቶ ጽፈው የፖለቲካ ርዕዮት ቀርጸው በመነሳታቸው ነበር። እነዚህ መሪዎች ሩዋንዳን በምናብ ሲያዩ ቱትሲ የተባለውን ፍጡር ከሩዋንዳ መሬት በማጽዳት የበለጸገችና ለሁቱዎች ብቻ ምቹ የምትሆን ሩዋንዳን እንፈጥራለን ወይም ቱትሲን በሃይል በማዳከም የሁቱን የበላይነት እውን እናደርግና አለማችንን እናያለን በሚል ትምህርት ሰክረው ነበር። እነዚህ ሰዎች ይህንን የጥላቻ ማኒፌስቶ ቀርጸውና የጥላቻን መዝሙር ዘምረው ብዙ የኢንተርሃሞይ ሚሊሻ መግዛት ቻሉ።
የጥላቻ አስተማሪዎች ሲነሱ የሚጠሉትን አካል እስከ ሞት ጠልተነዋል ካሉ በሁዋላ “አፍቅረነዋል” የሚሉትን ህዝብ ደግሞ እስከ ሞት ወደነዋል የሚል ተቃርኖ መፍጠር የትርክታቸው ዋና መርህ ነው። ኢንተርሃሞይ ማለት አብረን እንታገል ማለት ነው። እኛ ሁቱዎች አብረን እንታገልና ሩዋንዳን የሁቱ እናድርጋት ነው ነገሩ።
በነገራችን ላይ ኢንተርሃሞይ ዛሬም ድረስ ተጠናክሮ በኮንጎና ኦጋንዳ ውስጥ ወታደራዊ ክንፉን ያንቀሳቅሳል። ብዙ ሃገሮች አሸባሪ ቢሉትም ዛሬም በሁቱ ፍቅር የተነደፍኩ የሁቱ ብሄር ውድ ልጅ ነኝ፣ ቱትሲን አጠፋለሁ እያለ ተደራጅቶ ይንቀሳቀሳል። ለዚህ ተግባሩ ቀለብ የሚሰፍሩ የኢንተርሃሞይ ተማሪዎች በየቦታው ዛሬም ድረስ አሉ።
ወደ መነሻዬ ልውሰዳችሁና ዛሬ ጥር 27 ቀን የሚዘከረውን የሆልኮስት ቀን ስናስብ አለማችን ከጸረሴማዊያን ድርጊት ነጻ መሆን እንዳለባት እያሰብን ነው። ከሆልኮስትና ከኢንተርሃሞይ አለም የምትማረው ነገር በጥላቻና ጠላትነትን በመፍጠር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ሁልጊዜም አደጋው ሰፊ መሆኑን ነው።
ከዚህ በፊት ለብዙ አመታት ሃገራችን ኢትዮጵያ ከብሄር ፖለቲካ በፍጥነት መውጣት አለባት እያልኩ ስጽፍ፣ ባገኘሁት አጋጣሚ እንዳቅሜ ስሰብክ የነበረው የብሄር ወይም የማንነት ፖለቲካ ትምህርት የሚፈጥረውን የጥላቻ ሃይል በሚገባ ስለገባኝና ስላጠናሁት ነው። በሃገራችን ውስጥ ብዙ ሰው ይህ መረዳት እንዳለውም አውቃለሁ። የብሄር ፖለቲካ አለምን ያባላ፣ ዩጎዝላቪያን ያወደመ፣ ማህበራዊ ካፒታላችንን ዶግ አመድ የሚያደርግ ከባድ ክፉ ሃይል ያለው ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያኮራን ታሪክ በዘርና በሃይማኖት ተቻችሎ በመኖር ረገድ ከቀረው አለም በጣም የተሻልን መነበራችንን ስናስብ ነው። ሂትለር አይሁዳውያንን በሚጨርስበት በዚያን ክፉ ጊዜ ሃገራችን ኢትዮጵያ ዘውዱዋን ሞአ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ እያለች ትጠራ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ አይሁዳውያን አውሮፓ የደረሰባቸው መከራ አልደረሰባቸውም። በዚህ ታሪካችን ልንኮራ ይገባል። ሙስሊሞች በስደት በነበሩበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ መጠጊያ የሆነች ሃገር ይህቺዋ የኛዋ ኢትዮጵያ ነበረች ። ይህ ታሪክ የሚያኮራን ነው ጎበዝ። እንዲህ ያለ ታሪክ ያለን ሰዎች ስለሆነን ታሪካችንን ጠብቀን ኢትዮጵያን የመቻቻልና የነጻነት ምድር አድርገን መቀጠል አለብን።
አሁን ኢትዮጵያችን ወደ መቻቻልና ዴሞክራሲ እንዳትራመድ የሚያደርገው ትልቅ ችግር የብሄር ፖለቲካ ነው ወገኖቼ። ከዚህ ትምህርት በፍጥነት መውጣት አለብን ጎበዝ። አብዮታዊ ዴሞክራሲና የብሄር ፖለቲካ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑት ጠላት የሚባል አካል ፈጥረው ነው። ይህ አይነት ፖለቲካ እታገለዋለሁ የሚለው ጠላት ከሌለ ፖለቲካው ፖለቲካ ስለማይመስለው የግድ አዳዲስ ትርክቶችን ጽፎ፣ ወይም ያሉትን አጋንኖም ቢሆን የሆነ ጠላት ይፈጥራል። ታዲያ ትልቁ ችግር ፖለቲከኞች ይህንን ሲያደርጉ እነዚህ ሰዎች ስልጣን በያዙ ቁጥር በስራቸው ተቁዋማትን ያዛሉና እነዚያን ተቁዋማቱ በሙሉ ለጥላቻ ቤት ያደርጉዋቸዋል። እኛ ኢትዮጵያውያን የብሄር ፍርድ ቤት፣ የብሄር ፖሊስ፣ የብሄር ባንክ፣ የብሄር አቃቤ ህግ፣ የብሄር ወታደር፣ የብሄር ዶክተር፣ የብሄር ፕሮፌሰር፣ የብሄር ድንበር፣ መስርተን ስንኖር ለዘር ፍጅት ዱብ ዱብ እያልን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ በጋራ ስምምነት የብሄርን ፖለቲካ እናፍርስ፣ የብሄር ተቁዋማትን የጋራ እናድርግ። ዛሬ የሆልከስትን ቀን ስናስብ ከዚያ ግድያ ለተረፉት ሁሉ እድሜንና ጤናን እመኛለሁ። ለመላው አይሁዳውያን ሁሉ መልካም መልካሙን እመኛለሁ።
እግዚአብሄር ሃገራችንን ይባርክ