ወዴት እየሄድን ነው! – አንዱ ዓለም ተፈራ

271667649 470140381306950 8693962778430973957 nአርብ፣ ታህሳስ ፳ ፱ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም. (1/17/2022)
አንዱ ዓለም ተፈራ፤

በምኖርበት አገር አሜሪካና፤ በትውልድ አገሬ ኢትዮጵያ አሁን በውስጣቸው የሚታየውን የፖለቲካ ሂደት፤ ትርጉሙን ማወቁ በጣም አስቸጋሪ ሆኖብኛል። የተለመደ የሚባለው ሩቅ ሆኗል። ነገን ቀርቶ ከትንሽ ሰዓታት በኋላ ሊከተል የሚችለውን መገመቱ ዋጋ ቢስ ሆኗል። የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ የኔ ቢጤዎች እጅና እግሩን መያዝ ያቃተን ኩነት ነግሷል። ወዴት እየሄድን ነው!

ኢትዮጵያ በሶስተኛው ዓለም ውስጥ የምትገኝ አገር ናት። አሜሪካ በአንደኛው ዓለም ከተቀመጡት ግንባር ቀደሟ ናት። ሁለቱም ያሉበት የፖለቲካ ቀውስ ተመሳሳይ ነው። በአሜሪካ፤ የቀድሞው ፕሬዘዳንት፤ በምርጫ ተሸንፎ ሥልጣኑን በመልቀቁ ተናዶና ተቆጭቶ፤ አገሪቱን በዘረኝነቱና በሥልጣን ናፋቂነቱ ጠምዝዞ እየዘወራት ነው። ሕግ አውጪዎቹ ሕግ-ማውጣቱን ትተው፤ ለነገ ምራጫቸው ብቻ በቦታው ተወዝፍውበታል። ጎራቸውን እያጠናከሩ በመካከላቸው ያለውን የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት፤ የሞትና የሽረት አድርገው፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የአስተዳደር ችግር ተጋርዶበታል። ባለፈው ዓመት፤ በዚህ በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ፤ በትክክል የተመረጠውን የዴሞክራቶች አስተዳደር፤ ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሥልጣን እንዳይዝ ለማድረግና የተቸነፈውን ሙሰኛና ዘረኛ የቀድሞ ፕሬዘዳንት በቦታው ለመመለስ ጥረው ነበር። በቀጭን ገመድም ትሁን፤ በአገሪቱ ያለው የዴሞክራሲ መሠረት፤ ይሄን መፈንቅለ መንግሥት ተንገዳግዶ አድኖታል። ከሕግ አንጻር፤ እንኳንስ ዋናዎቹን አቀናባሪዎች፤ ኮት አልባሾችንም መንካት አልተቻለም። በርግጥ እጅ ከፍንጅ የተያዙትን ሙጭጭሊዎች መቆንጠጥ ተችሏል። እናም ይህ ሂደት፤ አሜሪካን በምጥ ውስጥ ያለች አገር አድርጓታል። ስለ አሜሪካው ፖለቲካ ይሄን ያህል ካስቀመጥኩ ይበቃኛል።

በኢትዮጵያ ደግሞ፤ በሥልጣን ላይ ያለው መሪ፤ የሕዝቡን ቁጭትና ቆራጥነት ተጠቅሞና በርግጥም በግንባር ተገኝቶ ወራሪውን ኃይል ወደኋላ እንዲዞር ሠራዊቱን አበረታቷል። የትግሬዎቹን ነፃ አውጪ ግንባር ከፖለቲካ ግቡና የአመራር ሥርዓቱ ጋር ወደ መቃብሩ ሊገባ በመንደርደር ላይ ነው። መሪውና ብልፅግና ፓርቲ አሁን ተመልሰው የኋሊዮሽ በመሄድ፤ ድሉንና አገሪቱን በምጥ ውስጥ አስቀምጠዋታል። መሪውና ፓርቲው የራሳቸውን ዘለዓለማዊ የፖለቲካ ሥልጣን ለማደላደል የተዘጋጁ ይመስላል። በብዙዎቹ ሕይወት እየተገኘ ያለውን ድል፤ ወደ ጎን ገሸሽ እንዲል አድርገውታል። ከምርጫው በፊት ሁሉ የፖለቲካው ሂደት ተሳታፊዎች እንዲስማሙና ትክክለኛ ምርጫ እንዲሆን፤ ሕገ-መንግሥቱ እንዲስተካከልና ተወካዮቹ በትክክል የሚወክሉት እንዲታወቅ ከጣሩትና ከጎተጎቱት እንዱ ነበርኩ። ምርጫው ከተካሄደ በኋላም ምርጫውን ተቀብለው አሁን ዋናውን ጠላት የትግሬዎቹን ነፃ አውጪ ግንባር መከላከልና በዚያ ላይ ማተኮር እንጂ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ውርጅብኝ አይገባም! በማለት ከቆሙት አንዱ ነበርኩ። የሻጥር መግተልተሉን ካወገዙት አንዱ ነበርኩ። አሁን የተደረገው አንዴ በምህረትና በይቅርታ! ሌላ ጊዜ ደግሞ አገራዊ ምክክሩን አክካታች ለማድረግ በማሰብ! በሚል የቀረበው የፖለቲካ ስሌት ሂደት በጣም አሳዝኖኛል። አልፎ ተርፎ ደግሞ፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዘርፈው የወሰዱት ንብረት እንደሚመለስላቸውና፤ ይሄን የሚቃወም ካለ እርምጃ እንደሚወሰድበት ተዝቷል። ይህ አገሪቷን በምጥ ላይ ማስቀመጥ ነው!

እውነት ግፍና በደል የደረሰባቸው የአፋርና የአማራ ወገኖቻችን፤ በቁስላቸው ላይ ስንጥር መሰንቀር አይሆንም ወይ! ወይንስ እንጃባታችሁ! የፈለጋችሁትን በሉ፤ እኔ የፈለግሁትን አደርጋለሁ ባይ እብሪት ነው! ግራ ያጋባኝ፤ ስብሃት ነጋን ፈትቶ ደብረ ጽዮንን እፈልጋለሁ ማለት! ዋና ዋና የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎችን ፈትቶ ጌታቸው ረዳን ለማሰር መሯሯጥ! ትርጉሙ ምንድን ነው? እስኪ የተፈቱትን እና ወንጀላቸውን እናነፃጽር፤

ስብሐት ነጋ፣ ቅዱሳን ነጋ፣ አባይ ወልዱ፣ አባዲ ዘሙ፣ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ ኪሮስ ነጋ – እኒህ ሁሉ ጌታቸው ረዳ፣ ጻድቃንና ደብረ ጺዮን በተከሰሱበት ወንጀል ነው የተከሰሱት። በጉልበት በሕዝቡ ተመርጦ በኃላፊነት ቦታ የተቀመጠውን ፓርቲና አስተዳደር አሻፈረኝ ብለው፤ ያመጹ፣ እርምጃ የወሰዱ ናቸው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በመነሻው ካረዳቸው የሠራዊቱ አባላትና በትግራይ የሚኖሩ አማራዎች ባለፈ፤ ወረራ ገብቶ በአፋርና በአማራ ክልሎች ካደረሰው ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋና ወረራዉን ለመመከት ሠራዊቱ፣ የክልል ኃይሎችና የአማራ ፋኖ የገበሩት ሕይወትና የንብረት ውድመት ለምንድን ነው! መልሶ ይሄን አሸባሪ ቡድን በትግራይ ላይ ለመጫን! ከተከዜ ወዲህ አንደርስባችሁም ብሎ ለመቀመጥ! እነሱኮ፤ ከተከዜ ወዲህ አትድረሱብን! ብለው አይደለም የዘመቱት! ወሎን አልፈው ሸዋ ገብተው ነበር! ታዲያ ተከዜ ወሰን የሚሆነው ለምንድን ነው! ወዴት እየሄድን ነው!

እግረ መንገዴን የጀዋርንና በሱ መዝገብ የተከሰሱ ሁሉ መፈታታቸውን አብሬ አነበብኩ! ይገርማል! መልዕክቱ፤ በኢትዮጵያ፤ ወንጀል ሠርተህ ነፃ ትሆናለህ ከሆነ፤ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ተቀበሏት። በኔ እምነት፤ እኒህ ሰዎች ከሠሩት ጥፋት የከፋ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ወንጀል የለም! ታዲያ እነሱ ነፃ ከሆኑ፤ ማንን ወንጀለኛ ብሎ ማቅረብና መቅጣት ይቻላል! ለምን በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ያሉትና ከነዚህ አረመኔዎች የቀለለ ወንጀል የሠሩ በሙሉ በነፃ አይለቀቁም! ከነሱ የበለጠ ጤናቸው አስጊ የሆነባቸው እስረኞች የሉም! ከነሱ የበለተ የተሻሉ ክሳቸው ሊታጠፍላቸው የሚገባ እስረኞች የሉም! ማከያና ሚዛን ማስተካከያ እንዲሆን ደግሞ፤ “ኃይልን በመጠቀም መንግሥትን ለመቆጣጠር ሙከራ በማድረግ” የተከሰሱት እስክንድርና በእርሱ መዝገብ የተካተቱት በሙሉ መፈታታቸውንም አነበብኩ። ክስና ፍትኅ ማለት እንዲህ ከሆነ ማላገጥ ትርጉሙን ተነጥቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ያጠፋ እንዲቀጣ፣ የበደለ እንዲክስ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ ፍትሕ በሽግግር እና በተሃድሶ ፍትሕ ዕይታ፣ አገራዊ ባህሎቻችን እና እሴቶቻችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እናሰፍናለን።” ብለዋል። በርግጥ ይሄ የሚደረገው በዋናዎቹ ወንጀለኞች ነው? ወይንስ በአመለካከታቸው ከማንም የማይወግኑ ሀቀኛ ሰዎች ነው? በነገራችን ላይ ሰላም የሚመጣው፤ ያጠፋውን ሁሉ ምህረት በመሥጠት ሳይሆን፤ አጥፊ ተጠያቂ የሚሆንበት ሥርዓት ሲኖር ነው። ይሄን እያየሁ አይደለም! በዚሁ ሂሳብ፤ “ኢትዮጵያ ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፤ የትኛውንም መሥዋዕትነት ትከፍላለች” በማለት የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስፍረዋል። እኒህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች የትግራይን ወገናችን ይወክላሉ ብሎ መውሰድ፤ በትግራይ ወገናችን ላይ መቀለድ ነው። ካደረሱበት ግፍና በደል በላይ አሁንም በነሱ ላይ ለመጫን መጣሩ ይዘገንናል።

ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን በአንድነት አገራችንን በፖለቲካ ዲብሎማሲው ለመታደግ የተነሳነው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መቃብር እንዲገባ እንጂ፤ ተመልሶ የሚያንሰራራበትን መንገድ ለመክፈት አይደለም። በአገር ቤት፤ ትንሽና ትልቁ የተነሳውና የዘመተው፤ ደሙን፣ ንብረቱንና ጌዜውን ለአገሩ የሠጠው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከሥር መሠረቱ ተመንድጎ እንዲነቀል እንጂ፤ ተመልሶ እንዲያንሰራራ አይደለም። እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ! ብለዋል ቀደምቶቻችን፤ እንደ ትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ያለውን ትክክለኛ ስምና ተግባር ሲገልጡ! የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን ታሪክ እናውቃለን። ምህረት፣ ድርድር፣ ሽምግልና በዚህ ድርጅት ትርጉማቸው ግልጥ ነው። ለአሁን እውነታ የሚጥቅማቸው እስከሆነ ድረስ፤ ውሽትና ክህደት ይላበሳሉ። ይሄንን መሪያችን እና ድርጅታቸው አያውቁም ብሎ የሚከራከር የለም። ታዲያ ስሌቱ ምንድን ነው! ይህ ነው ወዴት እየሄድን ነው? ያሰኘኝ።

ይካሄዳል የሚባለው አገራዊ ምክክርን በተመለከተ፤ በመጀመሪያ ዙሪያውን እንቃኝ። ብልፅግና አቸንፎ የበላይነቱን ይዟል። ምርጫው ሕጋዊና ትክክለኛ ተብሎለታል። የሚያሰጋው ወይንም የሚያስፈራው ምንም ነገር የለም። ስለዚህ፤ አገራዊ ምክክሩ ሥልጣኑን የሚመለከት ሳይሆን፤ በምን መንገድ ትደግፉኛላችሁ? የሚል ጣይቄ ለማቅረብ ነው። እውነት አገራዊ ምክክሩ የሚያስፈልገው፤ አገሪቱን ወደፊት እንዴት እንውሰዳት? ይሄን በሚመለከት የሥልጣኑን ጉዳይ እንዴት እንጋራው? ሕገ-መንግሥቱን እንዴት ቀይረን አገራዊ ሕገ-መንግሥት እናዘጋጅ? አንድ አገር፣ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሰንደቅ ዓላማ ኖሮን፣ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን በመላ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነታችን የመኖር፣ ሀብት የማፍራትና በኅብረተሰቡ ማናቸውም መስተጋብር ሙሉ ተሳትፎ የምናደርግበት ሥርዓት እናብጅ? የሚል አይደለም። ይሄ ያሰጋዋል።

በዚህ አገራዊ ምክክር አቸናፊ የሆኑት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና አደራዳሪና አስፈራሪ የሆነው አሜሪካ ናቸው። የተደቆሱት ደግሞ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይም የአፋርና የአማራ ወገናችን ናቸው። ባንድ በኩል በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወረራ ተዘርዝሮ የማያልቅ በደልና ለመግለጥ የሚሰቀጥጥ አረመኔ ግፍ ተደርጎባቸዋል። ቀጥሎ ደግሞ ጠላታቸው ድል ሊሆን ሲቃረብ፤ መሪው አቁሙ አለበለዚያ እኔው እንደነሱው እወርድባችኋለሁ አላቸው። ወዴት እየሄድን ነው? ይሄ የማን መንግሥት ነው!

 

 

 

4 Comments

 1. የኦነግ መንግሥት ስለሆነ ወያኔ ጨርሶ ከሚጠፋ አማራን እያዳከመ busy እንዲያደርግ ይፈለጋል። ሕዝቢ ትግራይ ወያኔ የጋተውን የጥላቻ መርዝ ካላስወገደ፥ ሁለቱን ሕዝቦች አናክሰው ሥልጣናቸውንና አጀንዳቸውን ያደላድላሉ። ፕሮቴስታንት ነን ብለው የምዕራቡን፥ እስላም መስለው የዐረቡን የቱርኩን እርዳታ ይቀበላሉ ።
  ኦርቶዶክስ ሆይ ንቃ፣ ተጋሩ ሆይ የዘረኝነቱን መርዝ ትፋ፣ አማራ ሆይ ተደራጅ፥ የወገንህ እልቂት ይሰማህ። ስለ ድንግል ብሎ እግዚአብሔር ይቅር ይበለን።
  ለዐቢይ ብልግና የምታሽቃብጡ አማሮች ሁሉ፥ እባካችሁ የወገናችሁ ሕመም ይሰማችሁ፣ ሰው ሁኑ።
  ጊዜው የኛ ነው ብላችሁ ግፍ የምትሠሩ የምታሠሩ ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፍሩ። እናንተ እንኳ ከፍርድ ብታመልጡ፥ ለልጆቻችሁ ለዘራችሁ ግፍ አታኑሩ።

 2. ዛሬ ከባይደን ጋር እንዳወራ የተነገረለት ጠ/ሚሩ በሾኬ እንደተጠለፈ አልተረዳውም። የመነጋገራቸውን ጉዳይ አስመልክቶ በአሜሪካ የተጻፈውን ልብ ብሎ ላነበበ ገና ይቀርሃል እኛ ያልንህን ሁሉ አላረክም እያሉት ነው። ስለ መፈታቱ ያሞግሳል፤ ስለ ጦርነት ድርድር ያነሳል ሌላም ዝባዝንኬ ጨምሮ አፍቃሪ ወያኔነቱን አመላክቶ ነገሩን ይዘጋል። አሜሪካ ወያኔ ስለ ፈጸመው ግፍ አንድም ቀን አንስታ አትውቅም። የቀድሞ የስደተኞች መጠለያን ማሰልጠኛ ያደረገው ወያኔ አሁን በዚህም በዚያም ባስቀመጣቸው የሚነገረው ግን 60 ሰው ሞተ፤ ሰው ተራበ ነው። በአማራና በአፋር ክልል ስለተፈጸመው ዘግናኝ በድል ግን አንድም ቀን የአሜሪካ መንግስት ተናግሮ አያውቅም። አልፎ ተርፎም ኤርትራ ይህን ሰራች ያን አረገች እያለ ከመኮነን በስተቀር ሲጀመር ሮኬት ወደ ኤርትራ የተኮሰና ኤርትራን ወደ ጦርነቱ ቀጠና ለማስገባትና ለዓለም ህዝብ ይኽው በሁለት በኩል ተወረርን ለማለት ያሴሩት ሴራ እንደሆነ አሜሪካ መረዳት አትፈልግም። የአሜሪካንን መንግስት ያመነ ውሃ የዘገነ ነው። ሰዎቹ በየአራት አመቱ ለይስሙላ ይለዋወጣሉ እንጂ በጥቁር ህዝብ ላይ ያላቸው እይታ ያው ነው። በየአራት አመቱ የሚደረገውም የስመ ዲሞክራሲ ምርጫ ቅይጥና ከእውነት የራቀ ነው። ባጭሩ በፈረንጆች ቋንቋ (Anocracy) እንደሚባለው ነው። የሊቢያውን ጋዳፊ ያለውን የጦር ዝግጅትና የምርምር ሂሳብ ትጥቁን ካስፈቱት በህዋላ ነው በደቦ ግባተ መሬቱን የፈጸሙት። ዛሬ ሊቢያ ወሮበሎችና የሃይማኖች አክራሪዎች የሚራወጡባት የፈራረሰች ሃገር ሆናለች።
  ወደ አንድ ዓለም ጥያቄ ስመለስ “ወዴት እየሄድን ነው ለሚለው” መልሱ ገደል ነው። ልክ ወያኔ ኦሮሞና አማራን እያማታና በክልል ፓለቲካ ጅሎችን የመንደር ባንዲራ አስይዞ እያስጨፈረ ለ 27 ዓመት እንደዘረፈው ሁሉ አሁን ወረፋው የኦሮሞ ነው ይሉናል። የፓለቲካ ስልቱ ደግሞ አማራን ማዳከም ነው። ለዚያም ነው ወሎ፤ ጎንደርና ሽዋ የወያኔ መፈንጫ ሆኖ እልፎች ተገለውና ተደፍረው፤ ሃብታቸው ወደ መቀሌ እንዲጫን የተደረገው። ሴራው ገና አላለቀም። አማራውም አልነቃም። የአሁኑ የኦሮሞ ስልት ወያኔና አማራን እያባሉ መኖር ነው። በዚያ ላይ አዲስ አበባ ተቀምጠው ለኦነግ ሸኔ ትጥቅና ስንቅ እያቀበሉ በየስፍራው ተሰባጥሮ የሚኖረውን አማራ ነክ ሁሉ መመንጠር ነው። ይህ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ግባቸው መስመር ዘርጊ ነው። አዲሲቷን “ኦሮሚያ” ለመመስረት።
  የአሜሪካ መንግስት ሴረኛ መንግስት ነው። አሜሪካ ያሉ ታክሲ ነጂዎችን ሰብስቦ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ሲጥርና ጠ/ሚሩ ሃገር ለቆ እንዲወጣ ጫና ሲያደርግ ቆይቶ አሁን እንደገና ተገልብጦ መንግስት ለመንግስት ለስልክ ወሬ መብቃታቸው የመሰሪነታቸውን ጥልቀት ያሳያል። የሚራበው፤ የሚሞተው፤ የሚሰደደው የትግራይ ህዝብ ብቻ አይደለም። ግን ወያኔን መጠቀምና ማዳን ስለሚፈልጉ ሁሌ የሚናፈሰው ስለ ትግራይ ህዝብ ብቻ ነው። አሜሪካ ለትግራይ ህዝብ ግድ አይሰጣትም። ይህ የማይገባው ሃበሻ ካለ ደንቆሮ ነው። ለራሳቸው የፓለቲካ ጥቅም ግን የእኛ መገዳደልና መከፋፈል ወያኔን አይዞህ እያሉ የትግራይን ልጆች ማስጨረስ በፊተኛው ታሪካችንም ያየነው ስለሆነ የሚያስደንቅ አይሆንም። የአብይ ምላጭ ምላስ ከእውነት ጋር የተገናኘ አይደለም። ዲስኩሩ ከመብዛቱ የተነሳ የሰንበት ስብከት እንጂ የፓለቲካ ንግግርም አይመስልም። እንደ እስስት በየደረሰበት ሁሉ ራሱን እየቀያየረ የሚያወራውና የሚያደርገው ጭራሽ አይገናኙም። ብልጽግናው ድህነት፤ የሰላም ጥሪ ደም መፋሰስ ሆኖ እያየነው ነው። ለ 50 ዓመት ህዝብን ሲገል ሲዘርፍ ኑሮ የሰሜን እዝን ያጠቃውን የወያኔን ቁንጮ ለቆ ሌሎችን እስር ቤት ማቆየት በምድሪቱ ፍትህ እንደሌለ ያሳያል። ጠንጋራ የፕሮቴስታንት አማኞች ከአብይ ጋር እንዘጥ እንዘጥ ማለታችሁን አቁሙ። ፍትህ ላጡ ወገኖች ቁሙ። በወንጌል ስም የራሳችሁን መኖር ለእኛ አታሳዪን። ስለችቶናል። የሚታይ፤ የሚዳሰስ ተግባር ለተገፋው ህዝባችን አድርጉ። አሁን ማን ይሙት ምክር ቤቱ በድምጽ አብላጫ አሸባሪ ቡድን ብሎ ከፈረጃቸው ኦነጎችና ወያኔዎች ጋር ድርድር ይደረጋል? የስንት ሰው ህይወት ነው የጠፋው? ስንት አማራና አፋር መሞት አለበት ለኦሮሞ ብሄርተኞችና ለወያኔ ደም አፍሳሾች ደስታ? አይበቃም? ተው ይህ ግፍ እናንተ በር ይደርስና ያኔ ወዪ ትላላችሁ? እንኳን የሃበሻው አፋንኩሎ ስልጣን የሮም መንግስትም ተንኮታኩቷል። የወያኔ ደም አፍሳሾች መፈታት ፍትህ በምድሪቱ እንደሌለ ዋንኛ ማሳያ ነው። እኔ የፍርድ ሚኒስተሯን ወ/ሮ መዓዛን ቢያረገኝ ስልጣኔ በፍቃዴ እለቅ ነበር። የቀን ጅብ በንጋት ጅቦች እየተተካ ሰው መኖሪያ ባጣባት ምድር ላይ ከግፈኞች ጋር ከመተባበር መለየት የልብ ሰላም ይሰጣል። በቃኝ!

 3. እባክህን አዘጋጅ
  የልብህ ለቅሶና ጩኸት ገብቶኛል ተብሎ ይታረምልኝ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.