በኢትዮጵያውያን ሕይዎት እንደሚቀልደው እንደ ከሀዲው ዐቢይ አሕመድ አይነት ፍጹም ስልጣን የነበረው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት፣ ፕሬዝደንትና ጠቅላይ ሚኒስትር አልነበረም። በነገሥታቱ ዘመን እያንዳንዱ መንግሥታዊ ውሳኔ ሲወሰን ሥርዓት ነበረው።የኢትዮጵያ ሥነ መንግሥት ፈላጭ ቆራጭ ንጉሠ ነገሥት የሚቀበል አልነበረም። ንጉሠ ነገሥቱ ስለፈለገ ብቻ የሚወስነው አንዳች አገራዊ ውሳኔ አልነበረም። ሁሉም ነገር ሥርዓት ነበረው።
–
በነገሥታቱ ዘመን አንድ መንግሥታዊ ውሳኔ ሲወሰን ማለፍ የነበረበትን አካሄድና የነበረን የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ከታች ጀምሮ እስከ ንጉሠ ነገሥቱ ድረስ ሥርዓቱ ምን እንደሚመስል ማወቅ የሚሻ ቢኖር ፕሮፈሰር ባይሩ ታፍላና ፕሮፈሰር ሄኔሪክ ሾለር አርመው ያሳተሙትን የኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥት ያንብብ። የመጽሐፉ ርዕስ “Ser’ata Mangest: An Early Ethiopian Constitution”ይሰኛል።
–
በመጨረሻው የኢትዮጵያ ነጉሠ ነገሥት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረውን መንግሥታዊ ውሳኔ አሰጣጥም ካየን አንድ ውሳኔ ሲወሰን የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የዘውድ ምክር ቤት፣ ፍርድ ቤት፣ አማካሪዎች፣ ወዘተ በሚባሉ መዋቅሮች አልፎ ነበር አንድ ውሳኔ የሚወሰነው።
ሌላው ቢቀር የሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና የሊቀመንበር መለስ ዜናዊ አገዛዞች እንኳን የሚፈልጉትን ውሳኔ ሕጋዊ የሚያደርጉበት ፓርቲ፣ ፓርላማ፣ የሚንስትሮች ምክር ቤት፣ ፍርድ ቤት፣ አማካሪዎች፣ ወዘተ ነበራቸው።
–
መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ሆነ መለስ ዜናዊ ስንት የኢትዮጵያ ልጆችን የፈጀ የጦር ወንጀለኛን በነጻ የመልቀቅን ያህል ውሳኔን ቀርቶ ማናቸውንም ተራ ጉዳዮችን እንኳን ቢሆን ከመወሰናቸው በፊት ቢያንስ በዲሞክራሲ ማዕከላዊነት በተጠረነፈው ፓርቲያቸው አስወስነው ነው ለሕዝብ ይፋ የሚያደርጉት። የሚያቀርቡትን ሀሳብም የሚቃወሙና የሚገዳደሩ የፓርቲያቸው ሰዎች ነበሩ። በደርግ ውስጥ እነ ሲሳይ ሀብቴ፣ እነ አጥናፉ አባተ፣ እነ ሞገስ ወልደ ሚካኤል፣ እነ ብርሀኑ ባይህ፣ ወዘተ የሚባሉ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሚያቀርባቸውን የውሳኔ ሀሳቦች የሚቃወሙ የፓርቲ ሰዎች ነበሩ። የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘመን የመጨረሻው ውሳኔዎች የሚወሰኑት የነዚህን ሰዎች ተቃውሞና ተጠይቃዊ ሙግቶች አልፈው ነበር።
–
ፋሽስቱ መለስ ዜናዊም ቢሆን የሚያቀርባቸውን የውሳኔ ሀሳቦች የሚጋፈጡ የፋሽስት ወያኔ አባላት የሆኑ ባልደረቦቹ ነበሩበት። ፋሽስት ወያኔ በ1993 ዓ.ም. የተከፈለው የመለስ ዜናዊን የውሳኔ ሀሰብ የሚገዳደሩ የማዕከላዊ ኮሚቴና የሥራ አስፈጻሚ አባላት በመኖራቸው ነው። ባጭሩ በፋሽስት ወያኔ ዘመን እንኳን አንድ ውሳኔ የድርጅታቸውን ሂደቶች አልፎ ነበር የሚወጣው።
–
በዐቢይ አሕመድ ዘመን ግን ፓርቲ፣ ፓርላማ፣ የሚንስትሮች ምክር ቤት፣ ፍርድ ቤት፣ አማካሪዎች፣ ወዘተ የሚባሉት መዋቅሮችን ለይስሙላ እንኳን አልፎ የሚወጣ ውሳኔ የለም። ገዱ አንዳርጋቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነት ተነስቶ የሆነ ቦታ መጣሉን የሰማው እንደ ማናቸውም ኢትዮጵያዊ ዜናው በቴሌቭዥን ሲነገር ነው። ኢታማጆር ሹሙ አደም መሐመድ ከኢታማጆር ሹምነቱ መሻሩን የሰማው በሜዲያ ነው። ደመቀ መኮንን ገዱ አንዳርጋቸው ተክቶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ መሾሙን የሰማው እንደ ሁላችንም በሜዲያ ነው። ብርሀኑ ጁላ አደም መሐመድን ተክቶ ኤታማጆር ሹም መሆኑን የሰማው ሹመቱ በቴሌቭዥን ከተነገረ በኋላ ነው። የጦር ወንጀለኞቹን የነ ስብሀት ነጋን በነጻ መለቀቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የደኅንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ ሌሎች የብል[ጽ]ግና አመራሮች የሰሙት የዐቢይ አሕመድ ውሳኔ በቴሌቭዥን ሲነበብ ነው። እንደዚህ አይነት ፍጹም አምባገነናዊ ውሳኔዎች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ኖረው አያውቅም።
–
ባጭሩ ዐቢይ አሕመድ የጦር ወንጀለኞቹን በነጻ ለመልቀቅ የወሰነው ውሳኔ በንጉሡ ዘመን በየትም በኩል አልፎ አይወጣም። ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ሊቀመንበር መለስ ዜናዊም ቢሆኑ እንዲህ ያለውን ነገር አይነኩትም ነበር። ኢትዮጵያን ያጋጠማት በታሪኳ አይታው የማታውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባይፈቅድ እንኳን የጦር ወንጀለኞችን ጭምር በነጻ የመልቀቅ ፍጹም ሥልጣን ያለውን እቡይና ፍጹም አምባገነን ነው።