ምሕረት ሲሉ : ፍትሕ ስንል ለየቅል!!! – ከቴዎድሮስ ሃይሌ

የታማሚው የበሽታ ውጤት መክፉት ያስጨነቀው ዶክተር በደንበኛው ላይ ሊያስከትል የሚችለውን የአካልስቃይና የሞራል ስብራት አለሳልሶ በዘዴ ለመንገር መላ ይዘይዳል:: ታማሚውም ዶክተሩን ሲመለክት እንዴት ነውጤናዬ ሲል ይጠይቃል ? ዶክተሩም ለታማሚው ጥሩም መጥፎም ዜና አለ ይላል:: ታማሚም መጥፎው ምንድንነው? ጥሩውስ ዜና ብሎ ይጠይቃል? ዶክተሩም መጥፎው ዜና እግርህ የሚቆረጥ ሲሆን ጥሩው ዜና ደግሞጫማህን የሚገዛህ ማግኘትህ ነው:: አለው ይባላል::

መጥፎና ጥሩን በነገር አዋዝቶ ቢያቀርቡትም ውጤቱን ግን ፈጽሞ ቅንጣት ታህል አይለውጥም:: ጨለማና ብርሃን በምንም አይነት ውቡ ቋንቋ ቢገለጽ አንድ አይሆኑም:: ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ዛሬ በነስብሃትነጋና እስክንድር ነጋ ላይ የወሰዱት የምህረት ውሳኔ ከላይ ያነሳንው ሃኪም ሕመምተኛውን አጽናንቶ ለመንገርየሄደበትን እርቀት ያመሳስልባቸዋል ::

የሃገርን ብሄራዊ አደጋ የሚመለከቱበት አንግልና ቀውስን የሚፈቱበት አቅጣጫ ጥራትም ግልጽነትም ሁሌምአነጋጋሪ ከሆነ ቆይቷል:: ጠቅላይ ሚንትሩ በታሪክ አጋጣሚ ከሳቸው በፊት ከነበሩ መሪዎች በተሻለ ተቀባይነትናተወዳጅነት በአጭር ግዜ መቀዳጀት ቢችሉም በቀላሉ ተገማችና ሊታወቅ የሚችል ጠንካራና የነጠረ የፖለቲካስብዕና የሌላቸው ካለፉት በጣም የተለዩ አድርጏቸዋል::

አመራራቸው ግራ አጋቢ የውሳኔ አሰጣጣቸው አወዛጋቢ የፖለቲካ ርዕዮታቸው አጠራሪ እንደሆነም ቆይቷል:: የቅርብ ደጋፊዎቻቸውና የእርሳቸው አድናቂ የሆኑ ሊሂቃን ጭምር በቅጡ የማይረዷቸው መሪ ናቸው:: ሕዝባችን የመንግስቱን ሃገር ወዳድነት ; የመለስ ዜናዊን ዘረኝነት የሃይለማርያም ደሳለኝን ልፍስፍነት በቅጡ ተረድቶ ኖሯል:: ጠ.ሚ አብይን ግን ንግግርና ተግባራቸው አንዳንዴ የሚጣረስ : የሚወስዱት አቋም ብዙንው ግዜ የሚያምታታ ምን ለማድረግና ምን ለማለት እንደፈለጉ የማይገባ የሚሆንበት ግዜ የበዛ ሆኖ ቆይቷል::

ሴራ ተንታኞችና የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸው የአብይን ፍላጎት ለመረዳት የፓርቲያቸውን ወሳኝ ሰውና የእሳቸው የቅርብ ታማኝ እንደ ሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ሽመልስ አብዲሳን ማድመጥ ይገባል ይላሉ:: ገራገሩና የበታችነት ስነልቦና ዋግ እንደመታው አገዳ ሕሊናቸውን ያዳሸቃቸው ኦቦ ሽመልስ ብዙ አወዛጋቢ አመጽ የሚቀሰስና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ንግግር በአደባባይና በግላጭ በማቅረብ ይታወቃሉ:: በተለይም አቶ ሽመልስ በአንድ ወቅት የተናገሩ የምንችለውን convince አድርገን፣ ያልቻልነውን confuse አድርገን የድርጅታችንን ፍላጎት የማሳካት እቅድ ዘርግተና ሲሉ የተናገሩት ንግግር ያሳደረው ተጽዕኖ ከእሳቸው አልፎጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወስዷቸውን አቋሞች ጭምር በዚህ አውድ ስር እንዲታ አድርጎታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች “እንቅልፍን” በተመለከተ - አማኑኤል ዘሰላም

ዛሬም የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት የወሰነው ውሳኔ አነጋጋሪ የሆነው ለዚህ ነው:: ወንጀለኛውን ደም መጣጩንና ሃገር ሻጩን በየዋኽ የፖለቲካ ታሳሪዎች ጀቡኖ በምህረት ስም ከፍርድ መንበር ማራቅ የሕግ ልዕልናን መናድ ተደርጎ የተወሰደው:: የጦር ወንጀል የፈጸመን በሰላም ከታገለውና በፖለቲካ አቋሙ ብቻ ለእስር የተዳረገውን ፖለቲከኛ በአንድ ሚዛን መለካት ተንበርካኪነት አልያም የconvince እና confuse ጭምብል ነው በሚል እያወያየ ያለው።

የደቡብ አሜሪካ ድራግ ነጋዴዎችና የማፍያ መሪዎች በፍትህ ስርዐቱና በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ባላቸው የግንኙነት ሰንሰለትና ሕገ ወጥ የጥቅም ተጋሪነት በአያሌ ንጹሃን ዜጎች ሕይወት መጠየቅ ሲገባቸው ፍርድ እየተገለበጠ በነጻ የሚወጡበት አሰራር እስከ ዛሬም ድረስ ይተገበራል:: በሃገራችንም በዘመነ ሕወሃት ሃገር የዘረፉና የንጹሃንን ሕይወት ያጠፉ ግለሰቦች ለነበረው የፖለቲካ ስርዐት ካላቸው ቀረቤታና ታማኝነት የተነሳ ሳይጠየቁ በነጻነት ይኖሩ እንደነበር አይዘነጋም::

የአብይ መንግስት እያስወገዘው ያለው መሰረታዊ ጉዳይም ይህው ነው:: የሕወሃት መሪዎችና አባላት የሃገር መከላከያ ሰራዊትን ከጀርባ እንዲወጋ አመራር የሰጠ በምክር የተካፈል ግልጽ የሆነ ወንጀል የፈጸመን አካል ከፍ ሲል በሞት ዝቅ ሲል በእድሜ ልክ እስር ሊጠየቅ የሚገባን ሽብርተኛ በምህረት ስም በነጻ መልቀቅ ሊገባን ያልቻለ እንቆቅልሽ የሆነው::

ለውጥ መጣ ከተባለበት ከባለፉት ሦስት አመታት ወዲህ : በተለይ በመንግስት አወቃቀር በፖለቲካና በጸጥታ አመራሩ ዳተኝነት አንዳንዴም ቀጥተኛ የሴራ ተባባሪነትና የአመራር ብቃት ማጣት ዜጎች ተወልደው ካደጉበት ሲባረሩ : በግፍ ሲገደሉና ያፈሩት ሃብትና ንብረት ሲወድም አንድም ተጠያቂ ለፍርድ ሊቀርብ ለተጎዱት ካሳ ለሞቱት ፍርድ ሲሰጥ አላየንም:: እንዲያውም በቁጥር ቅቀላ በሟቾች የብሄር ትንተና ሃቅ ሲታጠፍ እውነት ሲደፈቅና ፍትሕ ሲደፈጠጥ ማየት በተለይ የጠ.ሚ አብይ ዘመነ መንግስት ዋና ባህሪ ሆኖ ቆይቷል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአብይ አህመድ ቅጥፈቶች የሚነግሩን ሃቆች !! ( አሥራደው ከካናዳ )

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ለንግግራቸው ውበት ለተስፉ ቃላቸው ታማኝነት ሕዝባችን በሺዎች እየሞቱበት በቢሊዮን ዶላር ሃብቱ እየወደመበትና በሚሊዮን እየተፈናቀለም ላለፉት 3 አመታት በትግዕስትና በበስተዋይነት የመሪውን ቃል አምኖና ተቀብሎ ቆይቷል:: ሊነጋ ሲል ይጨልማል ለሠላሳ አመታት የተጨማለቀ ቢሮክራሲ እስኪጠራ የተሰገሰገው ባንዳና ጥቅመኛ ሲወገድ የመሪው ሕልም ይሳካል:: ሕዝብ ከቀውስ ፖለቲካውም ከንትርክ እርቆ እንደ መሪው ቃል ያማረና ዘመኑን የዋጀ የፖለቲካ ስርዐት ይኖረናል በሚል ተስፉ በታላቅ መ ስ ዕዋትነት በታግዘ ትግዕስት ጠብቀናል::

የትግራይ ወራሪ በተፈጠረበት ተንቤን በርሃ ሰጥሟል:: ሊያሰጋ የማይችል ዱቄት ሆኗል:: መቀሌ ከበሻሻ የማትሻል እስትራቴጂያዊም ፖለቲካዊም ተፈላጊነት የላትም ሲሉንም አምነናል:: መከላከያ ከትግራይ የወጣው ለትግራይ ገበሬ የእርሻ ግዜ ላለማውክና የሰላም አማራጭ ለመስጠት ነው ሲሉም ተቀበልን:: ዱቄት የተባለው ሕወሃት በሃገር ፍቅር የተሰለፈውን ሰራዊት በሴራና በፖለቲካ አመራሩ ድክመት እየደመሰሰ መሳሪያውን እየማረከና የሕዝብን ንብረት እየዘረፈ 800 ኪሎ ሜትር አቋርጦ ሰሜን ሸዋ ሲደርስ የመንግስትን ደካማነት እያወቀም ወቀሳና ቅሬታውን ውጦ ከመንግስት ጉን ሳይለይ ሕዝብችን ብዙ እጅግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል::

ብዙ ሸፍጥ እጅግ የከፉ ክህደት አሳፉሪ የአመራር ዝርክርክነት: አስነዋሪ የብቃት ማጣት አስገራሚ የመሪው ዝና ጥመኝነት የድል ሽሚያ ሁካታ አይተን እንዳለየ አልፈናል:; የእርቅ ጉባኤው ቱማታ የመልሶ ማጥቃቱ ዘመቻ ወደ ትግራይ አይሻገርም የተባለው መመሪያ የጦርነቱን በድል መጠናቀቅ ጮቤ እረገጣ ሁሉ ለሃገርና ለህዝብ ሲባል ባይጥምም ባያሳምንም መንግስ ትንና መሪን ለማክበር ሲባል ይሁን ተባለ:;

ብዙ ነገር መጣ ብዙ ነገርን አለፈ:: ሁሉንም ሕዝባችን በጨዋነት ቁጣውንም ተቃሞውን አምቆ ለሃገርሲል አድርግ የተባለውን አደረገ:: ዘመተ ተሰዋ በደጀንነት ያለውን አዋጣ ደሙን ሰጠ ሁሉን አደረገ:: ዲያስፖራውም በያለበት በቃ ሲል በምዕራባውያን አደባባይ ጮኽ የትግራይ ወራሪዎች ያወደሙትን ሊገንባየተፈናቀሉትን ሊያቋቁም የተራቡትን ሊያካፍል በታኝና ከፉፉዩን የስደት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተቋቁሞከመንግስት ጎን ቆመ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ደወል 3 ዘ ኢትዮጵያ ለሚድን በሽታ የሚገድል መድኃኒት መውሰድ ይብቃ! - ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

ኢትዮጵያን የቀውስ ቀጣና የጦርነትና የምስቅልቅል ዞን አድርገው ሃገሪቷን ለቀው የሌላ ሃገር ዜጎች እንዲወጡ ቀንና ሌሊት ሲቀሰቅሱ የቆዩትን የአሜሪካ መንግስትና የምዕራብውያ ሚድያ ሴራ አክሽፎ በመሪውየተላለፈውን ወደ ሃገር ኑ ጥሪ ብዙ ሺህ ዲያስፖራ አክብሮ በአሁኑ ሰዐት በሃገር ቤት ይገኛል:: ይህ ታላቅ ከፍታወገንን ያኮራና ኢትዮጵያዊነትን ያጠናከረ ሁኔታ ላይ የነዋሪውንም እንግዳውንም የደስታ ስሜት ያጠፉ ውሳኔባያደበዝዘው ምንኛ ባማር ነበር ::

ዛሬ ሃገራችን ላለችበት አደገኛ አጣብቂኝና ውድቀት የእራሱን ድርሻ ያለው የብልጽግና መንግስትናጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬም እንደ ለመዱት በሃገርና በሕዝብ ሕልውና ላይ ሃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ሰጥተዋል:: ጠቅላይ ሚንስትር አብይና ፓርቲያቸው ብልጽግና በፍትህ ሂደት በሕግ ልዕልና ላይ የፈጸመው ክህደት በወንጀልምበታሪክም የሚያስጠይቀው ይሆናል:: መሪውና ፖርቲው ፍትሕን የማያከብር ከህግ በላይ የሚራመዱ ፍጹምአንባገነን ስርዐት የለሽ ለመሆናቸው በዛሬው እለት የወሰዱት እርምጃ እንደ ማሳያ ቢቆጠር አይበዛብትም::

በሽብርተኝነት የተከሰሱ በሃገራችን መከላከያ ሰራዊት በሰሜን እዝ ላይ ክህደት ፈጽመው ለብዙ ሺየሰራዊት አባላት ሞት እስርና ለሃገር ውድቅት መንስዔ በሆኑ የሕወሃት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተሰጠው በነጻየመለቀቅ ብያኔ ሕዝብን ግራ አጋብቷል:: የመንግስትንም ቁርጠኝነትና ታማኝነት ጥያቄ ላይ ጥሏል:: ሊያስከትልየሚችለውም የሃይል አሰላለፍና የፖለቲካ አውድ ማወሳሰብ ሌላ የከፉ ቀውስ እንዳያዋልድም ተሰግቷል:: ግልጽነትም ተቀባይነትም ተነፍጎታል::

የሴራ ተንታኞች የሕወሃት ካድሬዎች የምዕራቡ ሚድያዎች ባንዶችና የዪቱብ ወሬ ሸቃጮችንፕሮፓጋንዳ ታግሶ የመንግስትን እንዝህላልነት እንዳላየ እልፎ እየከረፉውም ቢሆን አፍንጫውን ይዞ መንግስትንሲደግፍ የቆየው ኢትዮጵያንዊ ዛሬ በሰማው መርዶ ተሸማቋል:: የሽመልስ አብዲሳን የቁማር ጨዋት እንዲያስብየወሬ ነጋዴዎችንም ጩኽት መልሶ እንዲሰማ መንግስትን እንዲጠራጠር ተገዷል:: ለዚህ ነው የምንጠይቀውዶር አብይ ምህረት ሲሉ እኛ ኢትዮጵያውያን ፍትሕ ይሰጠን የምንለው::ምህረት በፍትሕ ተመዝና የምትከብር የበረከት ፍሬ እንጂ በጉልበት የምትገኝ ከሆነ የመርገም መንገድ የበቀልዛር የጥፉት አዙሪት ከመሆን አታልፍም::

ክብር ለመከላከያ ሰራዊታችንና ለመላው ሕዝባዊ ሃይል!!!

ኢትዮጵያዊነት ትላንትም ዛሬም ነገም ያሸንፉል!!

1 Comment

  1. ከብልግና ፓርቲ በጎ ነገር መጠበቅ ከበሬው ስር ስር ከአሁን አሁን ይወድቅልኝ ይሆን ብላ የምትከተል እንስሳን መምሰል ነው። ዋናው ችግር ለመብቱ፣ ለህልውናው ሲል ያልተደራጀ ሕዝብ መኖርና አደራጅ ልሂቃን አለመኖራቸው ነው። አምባገነኖች በልምምጥ ወይም በይሉኝታ ተሸንፈው አያውቁም። ወይ በፈጣሪ ቁጣ ተቀስፈው፣ ወይ አርጅተው በሞት፣ ወይ በሕዝባዊ እምቢኝ ባይነት ተገፍትረው ይታረማሉ።
    በእርሻህ ላይ አረም ሲፋፋ፥ አረሙን ከማማረር ማረም፣ መንቀል ይበጅሃል። መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ከቆረጠ፣ አንድ ከሆነ ተአምር ይሠራል። ይህን ስለሚያውቁ ነው አምባገነኖች በጎሣ የሚከፋፍሉን።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share