አወዛጋቢው የመንግስት ውሳኔ – ፋሲል የኔዓለም

ፖለቲካ ትርፍና ኪሳራን አስልቶ የሚከወን ስራ ነው። ከንግድ የሚለየው ነጋዴዎቹ ፖለቲከኞች መሆናቸው ብቻ ነው። ጠ/ሚኒስትሩም ይህን ውሳኔ ሲወስኑ፣ እንደ ነጋዴ፣ ትርፍና ኪሳራውን አስልተው ነው። ቢያንስ አምስት ነገሮችን ግምት ውስጥ አስገብተው የወሰኑት እንደሆነ አስባለሁ:-

አንደኛው፣ ከራሳቸው ጥቅምና ጉዳት አንጻር ነው። ማንኛውም ሰው ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት፣ በቅድሚያ የራሱን ጥቅም ታሳቢ ያደርጋል። ይህ አብዛኛው ፈላስፎች የሚስማሙበት “እውነታ” ነው። ጠ/ሚንስትሩም ሰው እንደመሆናቸው፣ ይህን ውሳኔ ሲወስኑ፣ ርዕዮታዊ ፍልስፍናቸው ን፣ እምነታቸውን፣ ህዝባዊ ድጋፋቸውን፣ የነገው ታሪካቸውን ወዘተ ግምት ውስጥ አስገብተው እንደሆነ ግልጽ ነው። ውስጣቸው ያሰበውን የሚያውቁት እሳቸውና ፈጣሪ ቢሆኑም፣ የኖቤል ሽልማት የተባለው ገመድ፣ መሪዎችን ከሪያሊስት ወደ ሞራሊስት፣ ከሞራሊስት ወደ ሪያሊስት ሲያመላልሳቸውና አንድ ወጥ ማንነትና አቋም እንዳይዙ ተጽኖ ሲፈጥርባቸው በኦባማና አሳንሱኪ ላይ አይተናል። የኖቤል ሽልማትና የተመድ የሰብዓዊ ኮሚሽን ቡቅርቡ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ በጠ/ ሚንስትሩ ውሳኔ ላይ ተጽኖ አሳድሮ ይሁን አይሁን፣ የሚያውቁት እሳቸውና ፈጣሪ ብቻ ነው ።

ሁለተኛው፣ ከፖርቲያቸውና ከመንግስታቸው ጥቅምና ጉዳት አንጻር ነው። ጠ/ ሚንስትሩ ይህን ውሳኔ ሲወስኑ የፖርቲያቸውንና የመንግስታቸውን አባሎች አማክረው፣ የአብዛኛውን ድጋፍ አግኝተው ከሆነ፣ በውስጣቸው የሚፈጠር ችግር አይኖርም። ችግሩ የሚመጣው ውሳኔውን የወሰኑት የፖርቲያቸውንና የመንግስታቸውን ሰዎች ሳያማክሩ ከሆነ ነው። ኦሮምያ ክልል ድጋፉን በይፋ ገልጿል ። በህወሃት- ኦነግ ቅንጅት ቅድሚያ ተጎጂ የሆኑት የአማራና አፋር ክልሎችስ? በጦርነቱ ፊት አውራሪ የነበሩት እነ ከንቲባ አዳነች፣ ፕ/ት ሙስጠፌ፣ አቶ ገዱ፣ ሬድዋን፣ ታዬ ደንደዓ፣ ዳንኤል ክብረትና ሌሎችስ ንቁ ባለስልጣኖቻቸው ምን ይላሉ? ውሳኔው አብዛኛው ባለስልጣን ሳይመክርበትና ድጋፉን ሳይገልጽ የተወሰነ ከሆነ፣ በመንግስት ውስጥ አለመተማመንና መሰነጣጠቅ ሊፈጠር ይችላል ።

ሶስተኛው ከህዝብና አገር ጥቅምና ጉዳት አንጻር ነው። የህዝብ ጥቅም በሁለት መልኩ ይገለጻል። አንደኛው ሰላምና መረጋጋትን ከማምጣት ፣ ሌላው ደግሞ ፍትህን ከማስፈን አንጻር ነው። የእነ አቶ ጃዋር ሙሃመድና የእነ እስክንድር ነጋ መፈታት ለአገራዊ ውይይቱ እንዲሁም ለሰላማችንና መረጋጋት እንደሚጠቅም ባያጠያይቅም፣ ሁሉም ነገር የሚወሰነው ግን ሁለቱ ፖለቲከኞች በሂደት በሚከተሉት የፖለቲካ አካሄድና ስልት ላይ መሆኑ ግልጽ ነው።

ጠ/ሚንስትሩ በእነ አቦይ ስብሃት ፍች ላይ የሰጡት ውሳኔ ግን የህዝባችንንም ሆነ የአገራችንን ጥቅም የሚጎዳ ነው ብዬ አምናለሁ። ውሳኔው ምናልባት ህወሃቶችን ሊከፋፍል ይችላል የሚለውን ቀመር ታሳቢ አድርጎ የተላለፈ ከሆነ፣ ህወሃቶች በውሳኔው ይከፋፈላሉ ብዬ አላስብም። በተቃራኒው የኢትዮጽያ ህዝብ እርስ በርሱ መከፋፈል ብቻ ሳይሆን፣ በመንግስት ላይ የሚኖረው አመኔታ በከፍተኛ ደረጃ ስለሚሸረሸር፣ ህወሃት የልብ ልብ እንዲሰማው ያደርጋል ብዬ አስባለሁ ። ታዋቂው የፖለቲካና ታሪክ ሊቅ ቱስዲድስ፣ አቴናን የጣላት የአቴናውያን መከፋፈል ነው እንዳለው ፣ የመንግስትና የህዝብ መከፋፈል፣ ለውድቀታችን ምክንያት እንዳይሆን እሰጋለሁ።

ህወሃት ነፍስ ዘርታ በድጋሜ ጥቃት ብትፈጽም፣ ህዝቡ መንግስትን መሪዬ ነው ብሎ አምኖ ደጀንነቱን በመጀመሪያው ስሜት ይገልጻል ወይ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እቸገራለሁ። ምናልባት ህዝቡ ከህወሃት አብይ እስከነ ችግሩም ቢሆን ይሻለናል ብሎ፣ ምርጫ በማጣት ካልደገፈው በስተቀር፣ ያ በመሪው ዙሪያ ተፈጥሮ የነበረው አዲስ ኢትዮጵያዊ መነቃቃት፣ ተስፋና ወኔ፣ ከንፋሱ ጋር አብሮ ሄዷል። መንግስት በከንቱ የጣለውን የህዝብ አመኔታ የተባለውን ካርድ መልሶ ለማግኘት፣ ብዙ ስራዎችን መስራት ይጠበቅበታል ።

የህግ የበላይነትን ከማስፈን አንጻር ከታዬም፣ ውሳኔው ፖለቲካ ከህግ በላይ መሆኑን ያሳየን ነው። ይህም ይሁን ብለን ብንቀበለው እንኳን፣ በዚህ ውሳኔ የተጎዱ ዜጎቻችን በምን መልኩ ፍትህ ሊያገኙ እንደሚችሉ ባስብ ባስብ ሊታየኝ አልቻለም ። በፍትህ እደሳ ( restorative justice) ስም ወንጀለኞችን ከወንጀላቸው የማንጻት ስራ ተሰርቷል። በዚህም፣ ወንጀለኞችን በማንጻቱ እራሱ መንግስት ወንጀለኛ ሆኗል። መንግስት ቢያንስ የተጎዱ ዜጎችን ሳያማክርና አስፈላጊውን የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ሳያመቻች፣ በራሱ ፍላጎት የወሰደው እርምጃ ፣ በህወሃት ወንጀል ፍትህ ያላገኙት ዜጎቻችን፣ እንደገና በመንግስት ኢምክንያታዊ ውሳኔ፣ ሁለተኛ ፍትህ እንዲጠይቁ የሚያደርጋቸው ይሆናል ።

አራተኛው ከአህጉራዊ ፖለቲካ አንጻር ነው። ውሳኔው በአፍሪካ ህብረት ደረጃ በበጎ መልኩ እንደሚታይ ባያጠራጥርም፣ አብረውን የቆሙት ጎረቤቶቻችን አገሮች ውሳኔውን እንዴት እንደሚያዩት በሂደት እናየዋለን።

አምስተኛው፣ ከአለማቀፍ ፖለቲካ አንጻር ነው። ይህ ውሳኔ አሜሪካና አውሮፖን ያለዝባል ተብሎ ተስፋ እንደሚጣልበት አስባለሁ። እኔ የማየው ግን በተቃራኒው ነው። ፈረንጆቹ መንግስት ሸብረክ ማለቱን ካዩ፣ ተጨማሪ ጫና ለማድረግ ይበረታታሉ። ትንሽ ብንገፋው የጠየቅነውን መመለሱ አይቀርም በሚል እምነት፣ ከህወሃት ጋር ቁጭ ብሎ እንዲደራደርና መብራትና ባንክ የመሳሰሉትን በፍጥነት እንዲለቅ፣ ጫናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያደርጋቸዋል። በዚህ ሂደት ህወሃት በአቋሙ እንዲጸና ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲወጣ እድል ሊሰጠው ይችላል።

የሚያሳዝነው ግን ውሳኔው “በራስ መቆም፣ ፖን አፍሪካኒዝም፣ No More* የሚሉት አስተሳሰቦች፣ የሆነ ከፍታ ላይ ሳይደርሱ ዋጋቸው በአጭር ጊዜ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት መሆኑ ነው። በተለይ ትልቅ አጋር ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው ዲያስፖራ፣ ብዥታ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ በመሆኑ፣ መንግስት ትልቅ የማሳመን ስራ መስራት ይጠበቅበታል።

በአጠቃላይ ሲታይ በእነ አቶ ስብሃት ነጋ ላይ የተላለፈው ውሳኔ፣ የህዝብን ስሜት የሚጎዳ፣ “የሚታመንና ሊነበብ የሚችል መሪ አለን ወይ” የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ፣ የህዝብን የአጭርና የረጅም ጊዜ ጥቅም የሚጎዳ፣ በአገር ሰላምና ደህነት ላይ አደጋ የሚደቅን፣ ጊዜውን ያልጠበቀ ነው። የአቶ ስብሃት ጉዳይ መታየት የነበረበት ከእድሜያቸው ወይም ከነበራቸው ስልጣን አንጻር ሳይሆን፣ ከምልክትነታቸው አንጻር ነው። ስብሃት የአንድ ወንጀለኛ ድርጅት ምልክት ( figure) ናቸው። የእሳቸው መያዝ፣ የህወሃትን ሽንፈት ማሳያ ተደርጎ እንደተወሰደው ሁሉ፣ መለቀቃቸው ደግሞ የህወሃትን አሸናፊነት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ለማጠቃለል፣ መንግስት የህዝብ አመኔታን ለማግኘት፣ ከባድ ስራ ይጠይቀዋል ። ህዝቡ የቀረበለት አማራጭ ” መንግስትን በመደገፍ ህወሃት እንዳይጠናከር ማድረግ ወይም መንግስትን በመቃወም ህወሃት እንዲጠናከር ማድረግ” የሚሉት ሁለት አጣብቂኝ ውስጥ የሚሉት አማራጮች ብቻ በመሆናቸው፣ ሳይወድ በግድ የመጀመሪያውን ሊመርጥ ይችላል። ዶ/ር አብይ በፍጥነት ለህዝቡ ማብራሪያ በመስጠት ማሳመን ካልቻለ ፣ ከዚህ በሁዋላ የሚኖረው የስልጣን ጊዜ ተፈርቶ እንጅ ተወድዶ የሚያስተዳድርበት የሚሆን አይመስለኝም። ይህም ሁኔታ እንደ ማኪያቬሌው ልዑል ሊያደርገው ይችላል ብዬ እሰጋለሁ።

ህዝብ ምን ማድረግ አለበት? ይህን ውሳኔ በሰላማዊ ሰልፍ መቃወም ፣ ጦርነቱ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ፣ ህወሃት ሾልኮ እንዲገባ ሽንቁር ይከፍትለታል። በምርጫ ድምጻችን እንዳንነፍገው፣ ምርጫው ገና ነው። ያለን ብቸኛ አማራጭ፣ በመንግስት ውሳኔ አለመደሰታችንን በጽሁፍና በተለያዩ መንገዶች እየገለጽን፣ አገራችንን መደገፍ ነው። አገር ከአንድ መሪ ውሳኔ ወይም የስልጣን ጊዜ በላይ ናት። መሪዎች ያስደስቱናል፣ ያስከፉናል። ተጽኖአቸው ግን በጊዜ የተገደበ ነው። አገር ግን ቋሚ ናት። ሁሌም የነገው የተሻለ ይሆናል በሚል ተስፋ፣ አገራችንን መደገፍ ማቆም የለብንም።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.